onsdag 15. januar 2014

የአፍሪካው ልዑል የተሰኘውን መጽኃፍ በሬዲዩ ፋና መተረኩ ተቃውሞ ገጠመው

ኢሳት ዜና :- በፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት በመተረክ ላይ ባለው በታጋይ መዝሙር ፈንቴ ተርጓሚኒት  በአቶ ዳንኤል ግዛው ጸኃፊነት የቀረበው መጽሀፍ  በአማራ ህዝብ  ላይ  ጥላቻ እንዲፈጠር እያደረገ ነው በማለት የብአዴን አባላት ተቃውመውታል።
አባላቱ በብር ሸለቆ በመካሄድ ላይ ባለው ስልጠና ላይ  እንደተናገሩት ሬዲዩ ፋና ታሪካዊ ስህተት እየፈጸመ ነው ፡፡ “የህውሃት ድብቅ አላማ እውን እየሆነ ነው” ያሉት ፤ መካከለኛ እና ታዳጊ የብአዴን አመራሮች ፤ ከደቡብ ወንድሞቻችን ጋር ታሪክን በማሳሳት እና በማጥላላት የትውልድ ጠላትነትን አስፍቶ አሁንም የህውሃት የበላይነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው በማለት በጽኑ ተቃውመውታል።
ጥያቄው የቀረበላቸው  የኢህአዴግ የስልጠና ዋና ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ “መፅሃፉ እየተተረከ መሆኑን በፍጽም አላውቅም” ያሉ ሲሆን ፣ ምላሹን አጣርተው እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡ የመጽሃፉ ትረካ ባሰቸኳይ እንዲቆም የጠየቁት አመራሮች ፣ ፋና ራዲዮን መስማት ማቆማቸውንም ለአቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡ የመለያየት ፖለቲካው  መርዛማነት እያሰቃየን ነው ሲሉም አባላቱ አክለዋል፡፡
ከቀናት በሁዋላ ወደ ተለያዩ አካላት  በመደወል መረጃ ያሰባሰቡት አቶ አዲሱ ለገሰ፣ ” ሃይለማርያም እንደፈረመበት እና  ፍቅር እስከ መቃብር ሲል እንዳወደሰው”  በማሾፍ መልክ መናገራቸውንና  ከፋና ሃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ” የመጽሃፉ ትረካ ቢቋረጥ በሬዲዩ ጣቢያው ላይ የሚፈጥረው ችግር ታይቶ ቢያንስ ቢያንስ የአድማጭ አስተያየት ባለመቀበል ልናጠፋው እንሞክራለን” ሲሉ መልስ እንደሰጡዋቸውና ሰልጣኞችን ለማረጋገት እንደሞከሩ ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ “መጽኃፉን አንብቤ እከታተለዋለሁ” ያሉት አቶ አዲሱ፣ ስህተቱ መፈፀም የለበትም ሲሉ አክለዋል፡
“ስህተቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሁቱና ቱትሲ አይነት ግጭት የሚፈጥር ነው” ያሉት አባላቱ፣ ከደቡብ ወንድሞቻችን ጋር የሚፈፀም ቅራኔን አንፈልገውም” ሲሉ ለአቶ አዲሱ ገልጸውላቸዋል።
ሟቹ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊና አቶ በረከት ስምኦን መጽሀፉ እንዲታተም ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር ያሉት ምንጮች፣ ሬዲዮ ፋናም የሩዋንዳውን የራዲዮ ሚሊኮልን ስራ እየሰራ ነው ሲሉ” ተቃውመውታል።

onsdag 8. januar 2014

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት ወታደራዊ ጥቃት ፈፀመ


በሀገራችን ላይ የተንሠራፋውን አምባገነናዊ ሥርዓት ገርስሶ ለመጣል የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት በጠላት ላይ የሚወስዳቸውን ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃዎች አጠናክሮ በመቀጠል በታህሳስ 23 ቀን 2006 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር በላይ አርማጭሆ ወረዳ ልዩ ስሙ ገራርዋ ባምብላ ወንዝ በተባለው ቦታ መሽጎ የአካባቢውን ህብረተሰብ ሲያሰቃይና ሲያንገላታ ከነበረው የወያኔ 24ኛ ቴዎድሮስ ክ/ጦር እና ከፀረ-ሽምቅ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ባደረገው ውጊያ 24 የጠላት ወታደሮችን ገድሎ 11 በማቁሰል የግንባሩ ሠራዊት አንፀባራቂ ድል አስመዝግቧል፡፡ በዚሁ ዕለትም በተደረገው እልህ አስጨራሸ ውጊያ የወያኔ 24ኛ ቴዎድሮስ ክ/ጦር ከኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት የሚደርስበትን የተኩስ ናዳ መቋቋም ተስኖት ሙትና ቁስለኛውን እያዝረከረከ እግሬ አውጪኝ በማለት መፈርጠጡን ታውቋል::
ይህ በእንዲሀ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት በጠላት ላይ ባስመዘገበው ከፍተኛ ወታደራዊ ድል መደሰታቸውና ወደፊትም ሀገራዊና ሕዝባዊ አላማን አንግቦ የህብረተሰቡን እምባ በማበስ ግንባር ቀደም በመሆን ለሀገርና ለወገን ደራሽነቱን እያስመሰከረ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊትን በመደገፍ የቆመለትን አላማ ከግብ ለማድረስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው ግንባሩ በተከታታይ ጊዜያቶች የሚወስዳቸው ወታደራዊ ጥቃቶችና የሚያስመዘግባቸው አንፀባራዊ ድሎች የወገንን አንጀት በማራስ በአንፃሩ ደግሞ የጠላትን አንገት በማስደፋቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የአካባቢው ህብረተሰብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት የጀግና አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከግንባሩ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ቆርጠው መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡

mandag 6. januar 2014

የቴዲ አፍሮ ኮካኮላ ውል እንዲሰረዝ ዘመቻ ተጀመረ

January 6, 2014

ኢትዮጵያውያን ዝምታውን በመስበር የሶሻል ሚድያ ዘመቻ መክፈት ይገባቸዋል

በ2014 ብራዚል ለሚካሄደው የአለም ዋንጫ ላይ ቴዲ አፍሮ የክብር እንግዳ እንዳይሆን አዲስ ዘመቻ በእነ ጃዋር መሃመድ መጀመሩ ተሰማ።Coca-cola a global leader in the beverage industry
በዓለም ዙርያ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ ለተፈናቀሉ ወገኖች እየተረባረቡ ባሉበት በዚህ ፈታኝ ወቅት፤ ጃዋር እና ሜንጫዎቹ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ዘመቻቸውን በስፋት ተያይዘውታል። በዛሬው እለት ከአዲስ አበባ በደረሰን ዜና መሰረት ኮካኮላ የቴዲ አፍሮን የአለም ስፖርት ፌዴሬሽን (ፊፋ) ስፖንሰርነት እንዲያነሳ ጠይቀዋል። አዲስ አድማ ለመጀመርም ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
በ2014 ብራዚል ለሚካሄደው የአለም እግር ኳስ ዋንጫ አፍሪካን ወክሎ እንዲገኝ ኮካኮላ ቴዲን የመረጠው መሆኑ ይታወሳል። የአለም ስፖርት ፌዴሬሽን (ፊፋ) ወጣቱ ቴዲ አፍሮ አፍሪካን እንዲወክል መምረጡ ዘረኞቹን አስቆጥቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ቴዲ አፍሮ በአለም መድረክ ላይ የሚያቀርበው ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ቃና ሀገራችንን እና መላው አፍሪካን የሚያስጠራ ነው።
የሄነከኑ አድማ በኦህዴድ ብርቱ ጥረት የተሳካላቸው እነኚህ ባለ አድማዎች፣ ሰሞኑን የደስታ መግለጫቸውን በየድረ-ገጾቻቸው ላይ እየተለዋወጡ እንደሆነ ተገልጿል። ሄኒከን ኮንሰርቱን የሰረዘው ከኦህዴድ በተላለፈ ቀጭን ትእዛዝ ስለመሆኑ ማስረጃው አሉ።
እነ ጃዋር በዚህ አላበቁም። በዲሴምበር 8፤ 2013 በተላለፈ የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ እና ሌሎች ምሁራን ቃለ-ምልልስ ምክንያት የጀርመኑ (ዶቸ ቨለ) የአማርኛ ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ከስራ እንዲነሳም ከአቤቱታ ጋር ቀጭን ትእዛዝ ለቦርዱ አስተላልፎ ነበር። የዶቸ ቨለ ቦርድ ላይ ኦህዴድ ተጽእኖ ስለሌለው ይህ ዘማቻ ሊሳካ አልቻለም።
የኮካኮላው ዘመቻ የተነጣጠረው በቴዲ አፍሮ ላይ ሳይሆን በአኢትዮጵያዊነት ላይ ስለሆነ በአለም ዙርያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዝምታውን በመስበር በነዚህ ሰዎች ላይ የሶሻል ሚድያ ዘመቻ መክፈት ይገባቸዋል።

torsdag 2. januar 2014

በናታችሁ ከዚች አገር አውጡኝ!

January 2, 2014
Alex Abreham (Facebook)
በናታችሁ ከዚች አገር አውጡኝ ! በቃ ሱማሌም ኧረ ምናምን ሱዳንም ይሁን ብቻ ኢትዮጲያ የምትባል አገር የማልሰማበት አገር ውሰዱኝ !
አሁን ቤት አከራየ መጣና የቤት ኪራይ አምስት መቶ ብር ጨምር ሲለኝ ቤት አከራየ ሳይሆን ኢትዮጲያ አስጠላችኝ !! የቤት ኪራዩ ብቻ እንዳይመስላችሁ የግፍ አገር ናት ! ምንም ፍትሃዊ ነገር የላትም ! እንደድመት ወልዳ የምትበላ ጉድ !
እስካሁን የኖርኩበትን እድሜ ቢያንስ ሶስት አራተኛውን አንገቴን ደፍቸ በመማር አሳልፊያለሁ በተማርኩት ሙያም እችን ለዛዋ የተሟጠጠ አገር አገልግያለሁ ! በምሰራው ስራ በመስሪያ ቤቴ የተመሰገንኩ ባለሙያ ነኝ ! ግን አንድ ቀበሌ ለቀበሌ እያውደለደለ በአፉ የሚኖር መሃይም የቤት ባለቤት አፉን ሞልቶ ወይ ልቀቅ ወይ አምስት መቶ ብር ኪራይ ጨምር ይለኛል! የዛሬ አራት ወር ሁለት መቶ ብር አስጨምሮኛል እውነቴን ነው በአገሬ ላይ የማልጠቅም ዜጋ የመሆን ስሜት ነው የተሰማኝ ፡፡
እኔ ማንም ብር እንዲሰጠኝ አልፈልግም ሰርቸ ማግኘት የምችል ጤነኛ የተማርኩ ወጣት በመንግስት ችግር ምክንያት እንደለማኝ መመፅወት አለብኝ እንዴ እንደገና ለፍተው ያሳደጉ ቤተሰቦቸ ለእኔ ብር መደጎም አለባቸው እንዴ እንደህፃን ልጅ ለኔ ልብስ መግዛት አለባቸው እንዴ…. ውለታየን መክፈል ቢያቅተኝ እንኳን እንዳልችል እንዴት በማንም ሆዳም እገፋለሁ መብቴን እቀማለሁ
አንድ የሱማሌ ወይም የኤርትራ ስደተኛ ከእኔ የተሸለ እኔ አገር ላይ ይኖራል ! እንደዜጋ መብራት ውሃ በስርአት አላገኝም ያውም ከፍተኛ የሚባል የስራ ግብር እየከፈልኩ ! እንደዜጋ ትክክለኛ መረጃ አላገኝም ! እንደዜጋ ደፍሬ ስለችግሬ አላወራም ! ላቤን ጠብ አድርጌ የምኖር ዜጋ አባትና እናቴ እድሚያቸውን ሙሉ በፍፁም ታማኝነትና ትጋት ያገለገሏት ኢትዮጲያ ላይ እንደሁለተኛ ዜጋ መንከራተት እጣ ፋንታየ ሁኗል …… ኧረ የምን ሁለተኛ ምንም ደረጃ የሌለኝ ውዳቂ ዜጋ ነኝ እንጅ ! በእውነት ግን እኔ ትላንት ዩኒቨርስቲ ሁኘ ኢትዮጲያን የብርሃን ኩሬ አድርጌ ሳልም የነበርኩት ልጅ ነኝ …..ኦህህህ እውነቴን ነው እንደዛሬ መሮኝ አያውቅም !
ከአቅሜ በላይ እየሰራሁ የለፋሁበት ደመወዝ አምስት ሳንቲም ለመንግስት ግብር በማይከፍል ቤት አከራይ ሲቀማ መንግስት አድገሃል ልማት ምናምን እያለ ይቀባጥራል ! ወጣት ነኝ ጥሩ መልበስ ጥሩ መመገብ አለብኝ ለፍቸ ያገኘሁትን ብር በስርአት ልጠቀምበት መብት አለኝ …. በተዘዋዋሪ የመንግስት ስንፍና እና ሃላፊነቱን አለመወጣት ለማንም ስግብግብ መጫወቻ እያደረገን ነው !
የዛሬ አርባ አመት እች አገር እዛ ትድረስ እዚህ ስሜት አይሰጠኝም ወጣትነቴን እንደቀልድ በባዶ ተስፋ የምትበላ አገር ለኔ ምኔ ናት ጠልቻታለሁ አገሬን !! በውጭ አገር የሚኖሩ እንዴት የታደሉ ናቸው ! እየሸሹ ባህር የበላቸው ከፎቅ የተወረወሩ ምንኛ እድለኛ ናቸው !
ኢትዮጲያ ተስፋችንን የምታኮስስ ተስፋ ቢስ አገር ናት !! እንደዜጋ በደልን ድህነትን ፍርሃትና መሸማቀቅን ብቻ የምታሸክም አገር ናት አገሬ ! ሽ አመት በባርነት መኖር ይሻላል ኢትዮጲያ ውስጥ ከመኖር ! ስንት ጊዜ ችግሯን እንዳላየን በእናትነት ሸፋፍነን አለፍናት ስንት አመት ሙሉ ቻልን በባዶ ተስፋ ተምራችሁ ያልፍላችኋል እያሉን ዶክተር ብትሆን ኢንጅነር ምን በትሆን ምን ወፍ የለም ! ሙሰኛ አጭበርባሪ ውሸታም አስመሳይ ስትሆን ከሰውነት ክብርህ ዝቅ ስትል ብቻ እንደለማኝ ፍርፋሪ ትወረውርልሃለች !
አገሬን ጠልቻታለሁ ! ሰርቸ ለምኖር ለፍቸ ለምኖር ለእኔ ኢትዮጲያ ያደረገችልኝ ነገር ቢኖር የለፋሁበትን ገንዘብ በስግብግብነት መቀማት ብቻ ነው ! እግዚአብሄር እዚች አገር ላይ የፈጠረኝ ለምንድን ነው ? ማንም ሰው ከዚህ አስቀያሚና የግፍ የበደል የአድሎ አገር ቢያስወጣኝ እግሩ ላይ ወድቄ ከመሳም አልመለስም ! አገሬን ጠልቻታላሁ ! መልስ የሚሰጥ የሚጨነቅልኝ መንግስት የለኝም !! አገሬ ዛሬ በውስጤ ሙታለች !

fredag 27. desember 2013

በከፊቾ ዞን የጽላት ዝርፊያና ቀበኞቹ

"ባለሃብቶች በእድሳት ስም ቤተ መቅደስ ዘልቀው ጽላት ይቀይራሉ"

tabot


በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በከፊቾ ዞን በጥንታዊ አድባራት ጽላት መዘረፉን እናውቃለን ያሉ ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ገለጹ። የዜናው ምንጮች የዞኑ አገረ ስብከት በዞኑ በሚገኙ አድባራት ላይ ምርመራ እንዲያካሂድ ጠይቀዋል። ዝርፊያውን የሚያካሂዱት “ባለሃብቶች” መቀመጫቸውን አዲስ አበባና ጅማ ከተማ ያደረጉ የክልሉ ተወላጆች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ነዋሪነታቸው ቦንጋና ጊምቦ እንደሆነ የሚገልጹት የዜናው ምንጮች “ቀበኞች” በማለት የሚጠሯቸውን የጽላት ዘራፊዎች የዝርፊያ ስልት ተናግረዋል። በመጀመሪያ እድሜ ጠገብ የሆኑትን አድባራት ይለያሉ። በቃፊሮቻቸው አማካይነት መረባቸውን ዘርግተው ሰዎችን ያጠምዳሉ። ህዝበ ክርስቲያን በሚሰበሰብበት ወቅትና ዓመታዊ የበዓላትን ቀን መርጠው በርዳታና በእድሳት ስም ውዳሴ ይቀበላሉ።
በዞኑ የሚገኙት አቢያተ ክርስቲያናት እድሜ ጠገብ በመሆናቸው በርካታ ጥንታዊ ቅርስም እንዳላቸው የሚጠቁሙት ክፍሎች “ያረጁትን አድባራት እናድሳለን በማለት ጥቁር ለምዳቸውን ለብሰው መቅደስ ውስጥ ይዘልቃሉ” በማለት የዝርፊያው ድራማ እንዴት እንደሚከናወን ያስረዳሉ።
ለሃይማኖታቸው የቀኑና የታመኑ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችና አገልጋዮች ሲያጋጥሟቸው መቅደስ ውስጥ ተመላልሰው በሚሰበስቡት መረጃ መሰረት አብረቅራቂ ሃሰተኛ ጽላት በመተካት ዝርፊያ እንደሚካሂዱ፣ ለዝርፊያ የሚመችና ስብናው የወደቀ አገልጋይ ሲያገኙም በግልጽ ያሻቸውን አድርገው ስርቆቱን እንደሚፈጽሙ የዜናው ሰዎች ያስረዳሉ።
ድርጊቱ የቆየና ሰዎቹም የሚታወቁ እንደሆኑ የሚጠቁሙት እነዚሁ ክፍሎች፣ “ቀበኞቹ” ካላቸው የገንዘብ አቅም አንጻር እጃቸው ከወቅቱ ጉልበተኞችና የቤተ ክህነት ከፍተኛ አመራሮች ጋርም የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ከግምት በላይ አመላክተዋል። በዚህ ተነሳ “እንፈራለን፤ ፊት ለፊት ለመግጠምም እንቸገራለን” በማለት ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ምስጢራቸው እንዲጠበቅ አስጠንቅቀው መረጃውን ለመስጠት ችለዋል።
“ይህንን ዜና ጥቅማቸው የሚነካና ችግር ያለባቸው አካላት ዙሪያ ያሉ ጥቅመኞች ሊያስተባብሉት ይችሉ ይሆናል” ሲሉ ዜናው የሚያስደነግጣቸው ክፍሎች የሚወስዱትን የመጀመሪያ ርምጃ ያመላከቱት ተቆርቋሪዎች፣ “የእኛ ጥያቄ ግን ማጣራትና ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እውነታው እንዲረጋገጥ ነው” ብለዋል።
የዞኑ አገረ ስብከት ዛሬ ነገ ሳይል በተቀደሱ የማምለኪያ አድባራት ላይ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን ዝርፊያ የማጣራት ሃላፊነት እንዳለበት ያሳሰቡት ክፍሎች፣ ቀበኞቹ በርዳታ ስም እድሳት ባካሄዱባቸው አድባራት ላይ የሙከራ ምርመራ ቢደረግ ጥቆማው ምላሽ እንደሚያገኝም በርግጠኛነት ተናግረዋል።
በእድሳትና በርዳታ ስም መቅደስ በመዝለቅ ከሚከናወነው ዝርፊያ በተለየ በድርድር የሚካሄዱም ዝርፊያዎች ስለመኖራቸው ያመለከቱት ክፍሎች “ጉዳዩ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ስምና ቦታን ለይተን ለመጠቆም እንቸገራለን” ብለዋል። “መልዕክቱ ለቀበኞቹ፣ ለተባባሪዎቻቸውና የሚሰማ ተቆጣጣሪ አካል ካለ ለነሱ ነው” ሲሉም አክለዋል። በዞኑ ያሉ የህዝብ ወኪል እንደራሴዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥንቃቄ ወስደው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
“የቃል ኪዳን ጽላት ዘርፎ ከማነከስና ሰልሎ ከመሞት ውጪ ሌላ ዕድል የለም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉት ተቆርቋሪ አዛውንቶች በ2005 መገባደጃ ላይ ዋሻ ውስጥ ተገኘ የተባለ ጽላት የት እንደገባ እንደማይታወቅ አመልክተዋል። ዜናው የመገናኛ ሰዎች ዘንድ ሁሉ ደርሶ እንደነበር፣ ነገር ግን በማይታወቅ ሁኔታ ተዳፍኖ መቅረቱ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላትን እስካሁን እንደሚከነክናቸው አመልክተዋል።

tirsdag 24. desember 2013

በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቤት የፈረሰባቸው አባወራዎች ቅሬታ

በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ በመድሐኔዓለም ቤተክርስትያን ጀርባ ቤቶችና የመንገድ ሱቆች እየፈረሱ በመሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች በቂ ጊዜ ሳይሰጠን ተፈናቀልን ሲሉ ያማርራሉ።
bet
በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ በመድሐኔዓለም ቤተክርስትያን ጀርባ ቤቶችና የመንገድ ሱቆች እየፈረሱ በመሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች በቂ ጊዜ ሳይሰጠን ተፈናቀልን ሲሉ ያማርራሉ። ተፈናቃዮቹ በቁጥር ወደ 570 እንደሚጠጉም ተገልጿል። የነዋሪዎቹን ቅሬታ ተከትሎ የአዲስ አበባው ወኪላችን ጌታቸው ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት ለማነጋገር ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ገልጿል። ጌታቸው ተፈናቃዮቹንና አቤቱታ ያሰሙበትን የፖለቲካ ድርጅት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን በማነጋገር የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሮልናል።

lørdag 21. desember 2013

ከወያኔ ክፋትና እብሪት እንጂ ፍትህ አይጠበቅም

ወያኔ ባለፉት ሃያ ሁለት አመታት የአገራችንን የፍትህ ተቋሞች አንዴ አንደ ቂም መበቀያ ሌላ ግዜ ደግሞ እንደ ማጥቂያ መሳሪያ እየተጠቀመባቸዉ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹንና ጥርስ የነከሰባቸዉን የህብረተሰብ አባላት እያሰረ፤ እያሳደደና እየገደለ ከርሞ ዛሬ ላይ ደርሷል። በተለይ ከግንቦት 1997ቱ ምርጫ በኋላ ወያኔ ብዕርና ወረቀት ይዘዉ በሃሳብና በአመክኖ የታገሉትን ሰላማዊ ዜጎች “ሽብርተኞች”፤ ድምጻችን ይሰማ ብለዉ የመብትና የነጻነት ጥያቄ አንግበዉ በሰላማዊ መንገድ የታገሉትን ኢትዮጵያዉያን የእስልምና እምነት ተከታዮች ደግሞ “አክራሪዎች” እያለ ፍርድ ቤት በማቅረብ በፍትህ ተቋሞች በኩል የፖለቲካ ዉሳኔ በማሳለፍ ሠላማዊ ዜጎችን ለረጂም ግዜ እስርና እንግልት ዳርጓል።

ወያኔ ለኢትዮጵያና ለዜጎቿ ደንታ የሌለዉ እና ከስህተቱ የማይማር የግብዞችና የዘረኞች ስብስብ ስለሆነ አሁንም የአገሪቱን የፍትህ ተቋሞች እንደ ማጥቂያ መሳሪያ እየተጠቀመ የኢትዮጵያን ህዝብ በፍርሃት ጨለማ ዉስጥ ሸብቦ እየገዛ ለመኖር የቆረጠ ይመስላል። ባለፈዉ ሳምንት አጋማሽ ላይ የወያኔ አገዛዝ ከአንድ አመት ተኩል በላይ እስር ቤት ዉስጥ አጉሮ ያቆያቸዉን የድምጻችን ይሰማ መሪዎች ከፊሎቹን በነፃ ተለቅቀዋል የሚል ከፊሎቹን ደግሞ ተከላከሉ የሚል ትርጉም የለሽ ብይን ሰጥቷል። በህወሀት ታጋዮች የተሞላዉ ፍርደ ገምድሉ የወያኔ ፍርድ ቤት እንኳን ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ሽብር የመፈጸም ወንጀል ምንም አይነት ማስረጃ አልተገኘባቸዉም ሲል አገዛዙ ግን የፖለቲካ ክንዱን በመጠቀም ማስረጃ ያልተገኘባቸዉን ሠላማዊ ዜጎች የተከሰሱበትን መሰረተ ቢስ ክስ ተከላከሉ የሚል የፖለቲካ ዉሳኔ ሰጥቷል።

የወያኔ አገዛዝ የሙስሊሙን ህብረተሰብ የመፍትሄ አፈላላጊ ቡድን መሪዎች ፍርድ ቤት ያቀረባቸዉ ለምዕራባዉያን ለጋሾቹና ለአለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍትህ ያለ ለማስመሰል ነዉ እንጂ ወያኔ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን የፈረደባቸዉ ያሰራቸዉ ቀን ነዉ። የወያኔ የፍትህ ታሪክ በግልጽ እንደሚያሳየን ወያኔ ግለሰቦችን የሚያስረዉ ለክስ የሚያበቃ ማስረጃ አግኝቶባቸዉ አይደለም፤ ይልቁንም ወያኔ ማስረጃዎችን እየፈበረከ ለፍረድ ቤቶች የሚያቀርበዉ ግለሰቦችን ካሰረና ሰብዓዊ መብታቸዉን ከገፈፈ በኋላ ነዉ። ለምሳሌ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን አስሮ ብዙም ሳይቆይ የእነዚህን ሰላማዊ ዜጎች ተክለ ሰዉነት ጥላሸት የቀባና ግለሰቦቹን ያለ ማስረጃ ወንጀለኛ አድርጎ የፈረጀዉን “ጂሐዳዊ ሀረካት” የሚል የፈጠራ ድራማ ሰርቶ ለህዝብ አቅርቧል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሽብር በመፈጸም ወንጀል ተጠርጥረዉ የቀረቡለትን ግለሰቦች በተከሰሱበት ወንጀል ማስረጃ አላገኘሁባቸዉም ካለ በኋላ ሁሉንም በነጻ አለማሰናበቱ የሚያሳየን የወያኔ ፍርድ ቤቶች ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነጻ አለመሆናቸዉን ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍርድ ቤቶች የገዢዉ ፓርቲ የማጥቂያ መሳሪያዎች መሆናቸዉን ጭምር ነዉ። የወያኔን አገዛዝ ከሌሎች አምባገነኖች ለይቶ አደገኛ የሚያደርገዉና በምዕራባዉያን መንግስታትና በቀላጤዎቻቸዉ እንዲወደስ ያደረገዉም ይሄዉ አገዛዙ የሚቃወሙትን ኃይሎች የሚያጠፋቸዉ እንደሌሎቹ አምባገነኖች በግልጽ ሳይሆን በህግ ሽፋን ዉስጥ በስዉር መሆኑ ነዉ።

የወያኔዉ ፍርድ ቤት በተመሳሳይ ወንጀል ተከስሰዉ የቀረቡለትን ነገር ግን ምንም መረጃ ያላገኘባቸዉን የድምጻችን ይሰማ መሪዎች ገሚሶቹን በነፃ ለቅቆ የተቀሩትን ጥፋተኛ አለመሆናችሁን አረጋግጡ ብሎ መወሰኑ የወያኔን ሁለት እኩይ አላማዎች ያሳየናል። የመጀመሪያዉ የወያኔ አላማ በአላማቸዉ ጸንተዉ የቆሙትን የድምጻችን ይሰማ መሪዎች መከፋፈል ሲሆን፤ ሁለተኛ አላማዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የቀረቡላቸዉን የክስ መዝገቦች በሚገባ አጣርተዉ ዉሳኔ የሚሰጡ መሆናቸዉን ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ለማሳየት ነዉ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እንደዚህ አይነቶቹን የወያኔ እኩይ ተግባሮች ካወቀ ዉሎ አድሯል፤ ስለሆነም ከወያኔ ፍትህ ጠብቆ አያዉቅም፤ ወያኔ የክፋትና የበቀል ምንጭ ነዉና ለደፊትም አይጠብቅም። የድምጻችን ይሰማ መሪዎችም ሆኑ ከእነሱ በፊት በግፍ ታስረዉ መከራቸዉን የሚያዩት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤ ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማህበራት መሪዎች የታሰሩት ለቆሙለት የፍትህ፤ የነጻነትና የእኩልነት አላማ እንደ አለት ጸንተዉ በመቆማቸዉ ነዉ። እነዚህ ጀግኖች የታሰሩለት አላማ የሁላችንም አላማ ነዉና ፍትህ፤ እኩልነትና ነጻነት የጠማን ኢትዮጵያዉያን ክንዳችንን አስተባብረን የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ በሆነዉ በወያኔ ስርዐት ላይ ክንዳችንን በጋራ እናንሳ!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!