tirsdag 4. mars 2014

ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል! (ግንቦት7)

March 4, 2014
Ginbot 7 weekly editorialየባህርዳር እና አካባቢው ሕዝብ ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ሺህ ጊዜ እንደሚሻል አካሉን ብቻ ሳይሆን ህሊናውንም ለትግራዩ ነፃ አውጪ ህወሓት ባርነት ላስገዛው “የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)” እያለ እራሱን ለሚጠራው ድርጅት መሪዎች ተናገረ።
ባርነት ክፉ ነው። በባርነት ላይ የጭንቅላት ባዶነት ሲታከልበት ደግሞ አለምነው መኮንንን የመሰሉ የብአዴን መሪዎችን ይፈጥራል። የብአዴን መሪዎች ለጌታቸው ህወሓት ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ራሳቸውን ማዋረዳቸው ሳያንስ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ በጅምላ መስደባቸው ብአዴን እንደ ድርጅት የሚገኝበት የተዋረደ ደረጃ ያሳያል።
ህሊና ያለው ባርያ ዛሬ ነፃ ባይሆንም ወደፊት ነፃ የመውጣት ህልም አለው። ዛሬ በጉልበተኛ የባርያ አሳዳሪ ነፃነቱን ቢያጣም የህሊና ነፃነቱን ያላስደፈረ ባርያ ለነፃነት መታገሉ የማይቀር ነው። እንደ ብአዴን መሪዎች በታማኝ ባርያነቱ እየፈነጠዘ ያለ ባርያ ግን ነፃ ሰው የመሆን ህልሙንም ጭምር አጥቷል። እንዲህ ዓይነቱ ባርያ በአካልም፤ በመንፈስም ባሪያ ነው። ነፃ ሰው የመሆን እድል የለውም።
የአማራ ሕዝብ ብአዴንን የመሰለ አሳፋሪ ድርጅት በታሪኩ ገጥሞት አያውቅም። በፋሽስት ጣልያን ወረራ ጊዜ ለጠላት ያደሩ ባንዶች እንኳን ከዛሬዎቹ ብአዴኖች የተሻለ ክብር ነበራቸው። እነሱም ከዛሬዎቹም በተሻለ በጌቶቻቸው ጣሊያኖች ይሰሙ ነበር። በገዢዎቹ ለመወደድ የራሱን ሕዝብ የሚዘልፍ፣ የሚሰድብና የሚያዋርድ እንደ ብአዴን ያለ አዋራጅ ድርጅት በአማራ ምድር አልታየም።
ለዚህም ነው የባህርዳር እና አካባቢው ሕዝብ የብአዴንና የወያኔን አፈናዎችን በጣጥሶ የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ቁጣውን በባዶ እግሩ አደባባይ በመውጣት የገለፀው። እግር ባዶ መሆኑ ጭንቅላት ባዶ የመሆኑ ያህል የሚያሳፍር አይደለም። ድህነት ወንጀል አይደለም። ነፃ አዕምሮና የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ አስተዳደር ካለ ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የየካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ምን ሕዝባዊ ተቃውሞ ላደራጁና በተቃውሞውም ለተካፈሉ ሁሉ ያለውን አክብሮት ይገልፃል። ሕዝብ ብሶቱን የሚገልጽበት ሕዝባዊ ተቃውሞ ማደራጀትና መምራት መቻል ትልቅ ነገር ነው። ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የማደግ እድል አላቸው። ስለሆነም ግንቦት 7 ለባህርዳሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ አደራጆችና ተሳታፉዎች “እንኳን ደስ ያላችሁ” በማለት የትግል አጋርነቱን መግለጽ ይሻል።
ግንቦት 7፣ ብአዴንን ከአባላቱ ለይቶ ማየት ይሻል። ከዚህም በተጨማሪ የብአዴንን ከፍተኛ አመራር ከሌላው ለይቶ ይመለከታል። ብአዴን ነፍሳቸውን ሳይቀር ለወያኔ በሸጡ ሰዎች የሚመራ፤ ነፃ የመውጣት ተስፋ የሌለው ራሱ ባርያ የሆነ ድርጅት ነው። አባላቱ ግን ከዚህ የተለዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግንቦት 7 ያውቃል።
ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከዚህም በፊትም ደጋግሞ እንደገለጸው፤ በተለያዩ ጊዜያት ራሳቸውን ከወያኔ ባርነት ነፃ ለማውጣት በወሰዱት እርምጃ መስዋእትነት የከፈሉ የብአዴን አባላት መኖራቸውን ያውቃል። ግንቦት 7 ለእነዚህ ቆራጦች ትልቅ አክብሮት አለው። ዛሬም ህሊናቸውን ሙሉ በሙሉ ያልሸጡ የብአዴን አባላት አሉ ብሎ ያምናል። እነዚህ ወገኖቻችን ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የግል፣ የወገንና የአገር ግዴታ አለባቸው ብሎ ያምናል።
ስለሆነም ዛሬም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመን ጥሪዓችንን እናድሳለን።
የብአዴን አባላት ሆይ!!! የገዛ ራሳችሁን፣ የአማራን ሕዝብ እና ኢትዮጵያን እያዋረደ ካለው ብአዴን ተላቀቁ፤ አሊያም እውስጡ ሆናችሁ ድርጅቱን ግደሉት። የብአዴን መኖር ለወያኔ ካልሆነ በስተቀር ለማንም አይበጅም። ነፃነት ካለ ድህነትን በሥራ ማሸነፍ ይቻላል። ሰው ባርያ ሆኖ በሀብት ቢንበሸበሽ ምን ይፈይድለታል?
የብአዴን አባላት ሆይ!!! ወደ ህሊችሁ ተመለሱ። ራሳችሁንም የበደላችሁትን ሕዝብ የመካስ እድል አድል አላችሁ ተጠቀሙበት። ይህንን ባታደርጉ ግን ለገዛ ራሳችሁ ፀፀት፤ ለልጆቻችሁ ሀፍረትን የምታወርሱ መሆኑን አትዘንጉ። ወያኔ መሸነፉ በጭራሽ የማይቀር መሆኑን እያወቃቸው በድህረ ጣልያን ወረራ ባንዶች ያገኙትን ምህረት እናገኛለን ብላችሁ አታስቡ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

mandag 3. mars 2014

አህመድ በማያውቃቸው ሰዎች ኩላሊቱ የተዘረፈበት ኢትዮጵያዊ

ከሳውዲ አረቢያ ተመላሾች አስከፊ የህይወት ገጽታ አህመድ በማያውቃቸው ሰዎች ኩላሊቱ የተዘረፈበት ኢትዮጵያዊ
የሃያ አመቱ አህመድ ከሳውዲ አረቢያ የተመለሰው ከአንድ ወር የእስራት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ከስደት ተመላሾች ማገገሚያ ውስጥ ይገኛል፡፡
አህመድ በሆዱ አካባቢ የሚታዩት ጠባሳዎች የቅርብ ግዜ ጠባሳዎች እንደሆኑ ያስታውቃሉ፡፡ በህክምና ባለሞያዎች በተደረገለት የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራም አህመድ የግራ ኩላሊቱን እንዳጣ ይጠቁማል፡፡
አህመድ ከማእከላዊ የአማራ ክልል አካባቢ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ነው በጅቡቲ እና በየመን አቆራርጦ ሳውዲ አረቢያ የገባው፡፡ ለዚህም ጥቂት የማይባሉ ሺህ ብሮችን ከፍሏል፡፡
አህመድ ለአንድ አመት ከስድስት ወር በረያድ በእንጨት ሰራተኝነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከሚያገኘውም ገቢ ለቤተሰቦቹ አቅሙ የፈቀደውን ይልክ ነበር፡፡ ከሶስት ወር በፊት ነበር በሰው ልጅ ላይ ሊፈጽሙት የሚከብደው አሰቃቂ ድርጊት የተፈጸመበት በወቅቱ አህመድ የነቃው በሪያድ ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡
ራሱን በፋሻ ተጠቅልሎ ነበር ያገኘው፡፡ ነገር ግን ወደ ሆስፒታሉ እንዴት እና በማን እነደመጣ የሚያውቀው ነገር ጨርሶ አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር አህመድ ‹‹ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የለውም›› በሚል ምክንያት ወደ እስር ቤት የተወረወረው፡፡
በመጨረሻ አህመድ ወደ ሃገሩ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ መንግስት አማካኝነት በአውሮፕላን የሃገሩን መሬት ለመርገጥ የቻለው፡፡
በአሁኑ ሰዓትም ወዳደገበት የትውልድ መንደሩ ለመመለስ የዶክተሮቹን መጨረሻ ውሳኔ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

søndag 2. mars 2014

አይተ ስብሐት ነጋ ‹‹ሕወሃት ውስጥ በነጻነት መናገርና መጻፍ ይቻላል››

ለዛሬው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ቃለ ምልልስ የሰጡት አይተ ስብሃት ነጋ ሕወሃት ዴሞክራሲያዊ መሆኑን በማስመር ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት በድርጅቱ የተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡‹‹ሕወሃት ውስጥ በነጻነት መናገርና መጻፍ ይቻላል››ብለውናል፡፡መቼም አቦይ ላለፉት 22 ዓመታት ስልጣን ላይ ስለቆየው ሕወሃት የተናገሩ ከሆነ አስገራሚ ነው፡፡ምናልባት አንድ እኔ ስላላወቅኩት በሌላ አገር ስለሚገኝ ሕወሃት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የእኛ አገሩ ሕወሃት ስብሃት የሚሉት ቁመና እንደሌለው ለማወቅ የድርጅቱ የፖሊት ቢሮ አባል መሆንን አይጠይቅም፡፡ሕወሃት ለተለየ ሐሳብ ቦታ የሌለው አባላቱን እንደ አንድ የፋብሪካ ሳሙና አንድ አይነት መልክ እንዲላበሱ የሚያደርግ አዲስ ሐሳብ ይዘው የሚመጡበትን እነ እከሌ ‹‹የድርጅቱ ጋንግሪን ሆነዋል››እያለ ከመቁረጥ የማይመለስ፡፡አመራሮቹንና አባላቱን እንደ ገደል ማሚቶ በሊቀመንበሩ የተባለውን ብቻ እየተቀባበሉ እንዲያስተጋቡ የሚያዝ ውስጣዊ ዲሞክራሲን የማያውቅ ለመሆኑ ድርጅቱን የተሰናበቱ ሰዎችን በመጠየቅ መረዳት ይቻላል፡፡
የአረና ሰዎች በትግራይ ክልል ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንቅፋት እየፈጠረ አረናዎችን በድንጋይ ማስደብደቡና ለእስር መዳረጉ የሚያሳየው ድርጅቱ የተለየ ሐሳብ ለህዝቡ መቅረቡን ምን ያህል እንደሚፈራ ነው፡፡
ስዬ አብርሃ፣አስገደ ገብረስላሴ፣አረጋሽ፣ገብሩ አስራትና ሌሎችም የሕወሃት የቀድሞ አመራሮች ከድርጅቱ የወጡት ከሊቀመንበሩ የተለየ አቋም በማራመዳቸው ነበር፡፡በሀሳብ የተለዩትን ሰዎች ሕወሃት የሚሸከምበት አቅም በማጣቱም አመራር ሲሰጡለት የከረሙትን ለእስር በመዳረግ የሐሳብን መንገድ ፈጽሞ እንደማያውቃት አሳይቷል፡፡ዛሬ ደርሶ አቦይ ሕወሃትን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ መሞከራቸው አስቂኝ ይሆናል፡፡

118 ኛዉ የአድዋ ድል በዓል አከባበር

118 ኛዉ የአድዋ ድል በዓል መታሰብያ በኢትዮጵያና በተለያዩ የዓለም ሃገራት በሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ በከፍተኛ ድምቀት ተከበረ።
Feier 118. Schlacht von Adua
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፤ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘዉ የአፄ ሚኒሊክ አደባባይ የጥንታዊ ኢትዮጵያ የአርበኞች አባላት፣ የመንግሥት ተወካዮች እና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ዶክትር ታቦር ገመድህን፤ በአፄ ሚኒሊክ ሃዉልት ስር የአበባ ጉንጉን አኑረዋል። ኢትዮጵያዉያን የጣልያን ወራሪ ጦርን ድል ያደረጉበት ይህ በዓል፤ ለአፍሪቃዉያን እና ለመላዉ ጥቁር ሕዝብ ደግሞ ኩራትን ማቀዳጀቱ ይታወቃል። በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የአፍሪቃ አገሮች ላደረጉት ከፍተኛ የነፃንት ተጋድሎ የኢትዮጵያዉያኑን፤ የአድዋ ድል በቀደምትነት የሚጠቅሱበት እና የህሊና ጥንካሬን የሚያገኙበትም ነበር።
የ118 ኛዉ የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ በተለይ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘዉ የአፄ ሚኒሊክ አደባባይ እንዴት ተከብሮ እንደዋለ ወኪላችን ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ ተከታትሎ የድምፅ ዘገባ ልኮልናል።
ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ

torsdag 27. februar 2014

አብርሃ ደስታ… ታስሮ ተፈታ!!


EMF – በትግራይ ውስጥ የሚደረጉ ግፍ እና በደሎችን ያለመሰለስ በማጋለጡ ይታወቃል:: ለሰብአዊ መብቶች መከበር በመቆሙ ከህወሃት ሰዎች ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ እና ዛቻዎች ሲደርሱበት ነበር:: ባለፈው ሳምንት ቃሊቲን ለመጎብኘት የፖለቲካ እስረኞችንም ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በነበረበት ወቅት “እንዴት የፖለቲካ እስረኛ ለመጠየቅ ከትግራይ ድረስ መጣህ?” በሚልም ለእስር ዳርገውታል:: ሁኔታውን እራሱ አብርሃ ደስታ እንዲህ በማለት ገልጾታል::
አዲስ አበባ ነበርኩ። ሰኞ ጧት ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌና ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ለመጠየቅ ቃሊቲ ማረምያቤት ሄድኩኝ። ጥበቃዎቹ ወደ ማረምያቤቱ አስተዳዳሪ ወሰዱኝ። አስተዳዳሪው ምርመራ ይሁን ዛቻ በማይታወቅ መልኩ ካስፈራራኝና ከሰደበኝ በኋላ ከማረምያ ቤቱ ተባረርኩ። አስተዳዳሪው “አንተ ከትግራይ አክራሪ አማራዎችን ለመጠየቅ ስትመጣ አታፍርም?!” አለኝ። ከፈለኩ ብሄር ብመጣም የፈለኩትን ሰው የመጠየቅ መብት አለኝ። የታሰረ ሰው መጠየቅ አያሳፍርም” መለስኩለት። ካሁን በኋላ “ወደ ቃሊቲ የምትገባው ታስረህ ካልሆነ በቀር እነ አንዱኣለምን ለማየት ድርስ አትላትም!” ብሎ ፖሊሶችን እንዲያስወጡኝ አዘዘ።
ወደ ቂሊንጦ ማረምያ ቤት ተጓዝኩ፤ ኡስታዝ አቡበክር አህመድን ለመጠየቅ። “አሸባሪ ለመጠየቅ መጣ” ተብዬ ለሦስት ሰዓታት ታሰርኩ። የቂሊንጦ ማረምያቤት ዋና አስተዳዳሪ እምባዬ ህቡዕ “አሸባሪዎችን ለማበረታታት መጣህ፣ ማረምያቤቱን ለመበጥበጥ ነው የመጣኸው። እንዳውም አሁን በማረምያቤቱ ረብሻ ተነስቷል። ስለዚህ ይታሰር” ብሎ በማዘዙ ወህኒቤት ዉስጥ ቆየሁ።
 ዝርዝር ጉዳዩን ለመፃፍ እሞክራለሁ። አንዱኣለም አራጌና ርእዮት አለሙን አላየኋቸውም። አቡበክር አህመድ (ና ሌሎች ጉደኞቹ) ግን አግኝቻቸዋለሁኝ። እነ አቡበክር አህመድን በማግኘቴ ደስ ብሎኛል።

onsdag 26. februar 2014

ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ የጀመረችውን ዘመቻ ዓለም አቀፍ ገጽታ ልታላብሰው ነው

February 26/2014


-



















-ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነካቢኔያቸው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ

የግብፅ መንግሥት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የጀመረውን ዘመቻ ዓለም አቀፍ ገጽታ ለማላበስ አዲስ እንቅስቃሴ ሊጀምር ነው፡፡

ከወደ ግብፅ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የግብፅ የውኃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ይህንን አዲስ እንቅስቃሴ ያስተባብራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ግድቡን በተመለከተ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ለማቅረብ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተገትቶ፣ አዲሱ ዘመቻ ፊቱን ወደ ጣሊያንና ኖርዌይ አዙሯል፡፡ ከዚያም ወደተለያዩ አገሮች ይቀጥላል፡፡

ባለፈው ሳምንት የውኃ ሚኒስትሩ መሐመድ አብዱል ሙታሊብና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነቢል ፋህሚ ወደ ጣሊያን ጉዞ አድርገዋል፡፡ የግብፅ መንግሥት ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ዋነኛ ሸሪክና የግድቡ ግንባታ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ ባሉዋት ጣሊያን የተደረገው ጉብኝት ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡

የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የግድቡን ጥናትና ግንባታ የሚያካሂድ በመሆኑ፣ ጣሊያን የግብፆች የአዲሱ ዘመቻ ዓላማ መሆኗ እየተነገረ ነው፡፡ የውኃ ሚኒስትሩ ሙታሊብ ለግብፅ ሚዲያዎች እንደገለጹት፣ የጣሊያን ጉብኝት ግቡን በመምታቱ ወደ ሌሎች አገሮችም ጉዞው ይቀጥላል፡፡ ምንም እንኳ የተገኘው ስኬት ምን እንደሆነ ባይብራራም፣ ሙታሊብ ለጣሊያን መንግሥት ባለሥልጣናት በግድቡ ምክንያት ግብፅ ሊደርስባት የሚችለውን የውኃ ችግር ማስረዳታቸውን፣ የጣሊያን ባሥልጣናትም ችግሩን አሁን ገና መስማታቸውን መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡ የሚቀጥለው ጉዞም ለህዳሴው ግድብ የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች ባሉዋት ኖርዌይ እንደሚሆን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ኖርዌይ ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ መቼና የት እንደሰጠች ግን አላብራሩም፡፡ ግብፆች ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ አገሮች መካከል አንዷ ኖርዌይ ናት በማለት ሌሎችም አገሮች ዕርዳታ ይሰጣሉ የሚል አንድምታ ያለው አስተያየት መሰንዘራቸው ተሰምቷል፡፡ 

የግብፅ መንግሥት የሚቀጥለው ዕርምጃ በተለያዩ አገሮች የሚደረግ ጉዞ ሲሆን፣ በየአገሮቹም የግብፅን አቋም በሰፊው ማስተዋወቅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የዚህ ጉዞ ዓላማ ለግብፅ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ማስገኘት መሆኑ ተወስቷል፡፡ ከእነዚህ ጉዞዎች ለግብፅ ድጋፍ ማስገኘት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ማሳጣትም ነው ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡ ግብፅን አይጐዳም እያለች ባለችበት ወቅት፣ ግብፆች ግን ይህ ግድብ በግብፅ ህልውና ላይ አደጋ የጋረጠ ነው በማለት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ መዘጋጀታው ተሰምቷል፡፡

ለተመድና ለአፍሪካ ኅብረት የሚቀርበው አቤቱታ ከፕሬዚዳንታዊው ምርጫ በኋላ የሚመሠረተው መንግሥት ተግባር እንዲሆን ወደጐን ተገፍቶ፣ አሁን የተያዘው በተለይ በአውሮፓ አገሮች ውስጥ ሰፊ ዘመቻ መጀመር እንደሆነ ሾልከው የወጡ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ በግድቡ ላይ ጥያቄ ለማስነሳት ሌላ ዘመቻ መታቀዱም ይሰማል፡፡ ሰሞኑን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋህሚ ነቢል በታንዛኒያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ጉብኝቱንም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪክዊቴ ማንም አገር ግድብ ሲገነባ የተፋሰስ አገሮችን ማማከር አለበት ማለታቸው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡     

የግብፅ የውኃ ሚኒስትር ሙታሊብ መንግሥታቸው በርካታ አማራጮችን በመያዝ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ስምምነት መድረሱን በይፋ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት በበርካታ አገሮች ግድቡ ግብፅን እንዴት እንደሚጐዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል፡፡ የግብፅን ተለዋዋጭ አቋምና ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ወገኖች ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአፀፋው ተዘጋጅቷል ወይ በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡ ከራሷ አልፎ ለአካባቢው አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጐት መሟላት ወሳኝ መሆኑንና የግድቡን የጥራት ደረጃ በሚገባ ማሳየት አለባት ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ እውነታውን ይዛ በግብፅ ፕሮፓጋንዳ መበለጥ የለባትም በማለት ያስረዳሉ፡፡ 

ይህ በዚህ እንዳለ የግብፅ ጊዜያዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐዚም አል ቤብላዊና የሚመሩት ካቢኔ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በአገሪቱ ሊካሄድ የሁለት ወራት ዕድሜ ሲቀረው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ እስኪከናወን ድረስ አገሪቱን እንዲያስተዳድር የተመረጠው የግብፅ ጊዜያዊ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትርና የሚመሩት ካቢኔ ባለፈው ሰኞ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ማስገባታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ያስገቡበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ፣ እሳቸውና ካቢኔያቸው የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሊ መንሱር እንዳስገቡ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን መልቀቂያውን ለምን እንዳስገቡ ባይገልጹም፣ ከካቢኔያቸው ጋር የ15 ደቂቃ ውይይት አድርገው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹በግብፅ መንግሥት ውስጥ ብቻ ለውጥ ማምጣት ትርጉም የለውም፡፡ የግብፅ ሕዝብ የሚፈልገውንና የሚመኘውን ለመሆን በራሱ መጣር አለበት፤›› ሲሉ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አል ቤብላዊ፣ ‹‹ግብፅ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆነች ሁሉ ሊጨበጡ የሚገባቸው ትልልቅ ዕድሎች እየተበላሹባት ነው፡፡ ስለዚህ ጊዜው ለአገራችን ስንል መስዋዕትነት የምንከፍልበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሙያቸው ኢኮኖሚስት የሆኑት ቤብላዊ የግብፅ ሕዝብ አገሬ ምን አደረገችልኝ ከማለት ባለፈ፣ ለአገሬ ምን አደረግኩ ብሎ መጠየቅ እንዳለበት ገልጸው፣ የአጭር ደቂቃ መግለጫቸውን አጠናቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚመሩት ካቢኔ በአጠቃላይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ትችት ሲጐርፍባቸው ነበር በማለት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ይገልጻሉ፡፡ በበርካታ መገናኛ ብዙኃን ትችቶችም ሲወርዱባቸው ነበር፡፡ 

የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲን አሸባሪ ብሎ ለመፈረጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረጅም ጊዜ አጥፍተዋል፡፡ በቅርቡ በፀደቀው የደመወዝ ስኬል የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች እንዳይካተቱ ማድረጋቸው፣ በአገሪቱ ውጥረትና የሽብር ጥቃቶች እንዲንሰራፉ አድርገዋል በማለት ይተቿቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪና የጨርቃ ጨርቅ ሠራተኞች፣ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው የፖሊስ አባላት፣ የፖስታ ቤት ሠራተኞች፣ እንዲሁም የሕክምና ዶክተሮች በተቃውሞ ውስጥ እየተሳተፉ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው ያቀረቡትን መልቀቂያ የአገሪቱ ጊዜያዊ መንግሥት ተቀብሎት፣ በአል ቤብላዊ መንግሥት የቤቶች ሚኒስትር ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ኢብራሂም መህሊብ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመሾም ካቢኔያቸውን እንዲመሠርቱ ማክሰኞ ዕለት ተነግሯቸዋል፡፡

የአገሪቱን ትልቁን የኮንስትራክሽን ኩባንያ ከአሥር ዓመታት በላይ ሲመሩ የነበሩት መህሊብ፣ የአዲሱ ካቢኔያቸው አባላት ‹‹የቅዱስ ጦርነት ተዋጊዎች›› ይሆናሉ ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፀጥታ በማስከበር ሽብርተኝነትን እንዋጋለን፤›› ያሉት መህሊብ፣ ካቢኔያቸውን በሦስት ቀን ውስጥ እንደሚያዋቅሩ ገልጸዋል፡፡ 

በሆስኒ ሙባረክ ዘመን የገዥው ፓርቲ (ናሽናል ዲሞክራቲክ ፓርቲ) አባል የነበሩት መህሊብ ካቢኔውን ሲመሠርቱ፣ አብዛኞቹን ሚኒስትሮች በነበሩበት ቦታ ላይ ይመድባሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚታወቁት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት በግብፅ እንደገና አመፅ ሊቀሰቀስ ይችላል እየተባለ ነው፡

ዜና በጨዋታ፤ ከረዳት አብራሪው እስከ ዋና ጥበቃ ሰራተኛው


ዜና በጨዋታ፤ ከረዳት አብራሪው እስከ ዋና ጥበቃ ሰራተኛው (Abe Tokchaw)
በዋሽንግተን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአበራሪ ሃይለ መድን አበራ ያላቸውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፈ መገልፃቸው ተሰምቷል። ሰለፈኞቹ ትላንት በስዊዝ ኤምባሲ ፊት ለፊት ተሰለፈው፤ ሃይለመድን አበራ እንደ ወንጀለኛ እንዳይታይ የስዊዝን መንግስት ተማጽነዋል።
ሰለፈኞቹ፤ አብራሪው የዘጠና ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን  ፍትህ እጦት በአለም አደባባይ ይበልጥ ያስገነዘበ ጀግና ነው ሲሉም አሞካሽተውታል።
ባልተያያዘ ዜና
ትላንት በአዲስ አባባ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ… (በቅንፍም፤ ይህ ሚሊኒየም አዳራሽ ሲገነባ ለሚሊኒየሙ ክብረ በዓል አከባበር ለስድስት ወራት ብቻ ተብሎ ነበር። ነገር ግን ከማን አይቶ ቦታውን ይለቃል… ይሄው ስድስት አመቱ መጣ… ሀገሪቷን ኤክስፓየርድ ዴት የማይታወቅበት ሀገር አደረጓት እኮ…ይሄው እነ እንትና ኤክስፓየርድ ካደረጉ ስንት ጊዜያቸው ገና ከአርባ እስክ ሃምሳ አመት እንፈልጋለን ይሉናል። (በሌላ ቅንፍም ሰዉ አርባቸውን ለመብላት ቋምጧል… )) ቅንፋችንን ቀናንፈን ስንወጣ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ የሚገኘው ህብረት ባንክ አጠገብ የሚስራ አንድ የጥበቃ ሰራተኛ ሶሰት ጥይቶችን ወደ ሰማይ ከተኮስ በኋላ አራተኛውን በራሱ ላይ በመተኮስ ራሱን አጥፍቷል።
ሰውየው ራሱን ከማጥፋቱ በፊት ኑሮ መረረኝ እያለ ሲጮህ እንደነበር አዲሳባ የምትገኘው ጋዜጠኛ ፂዮን ግረማ ኮረጄያለሁ።
እንግዲህ ይህንንም እብድ ነው እስኪሉን ድረስ የሃገራችን ሁኔታ የገዛ አውሮፕላን የሚያስጠልፍ የገዛ ክላሻችንን የሚያስጠጣ ሆኖ ቀጥሏል። ማለት እንችላለን።
ዜናው በዚህ አለቀ!
መከራችንም በዚሁ ባለቀ!