tirsdag 11. mars 2014

“በዴሞክራሲ” ስም የሚደረግ የመሬት ነጠቃና የዘር ማጥፋት ወንጀል በኢትዮጵያ

“በዚሁ ከቀጠለ አገሪቷ ወደ እርስበርስ ግጭት ማምራቷ አይቀሬ ነው”
panelist
በአይነቱ የመጀመርያ የሆነ የውይይት መድረክ የካቲት 27 2006ዓም/March 6, 2014/ በኦስሎ፣ ኖርዌይ ከተማ ተደረገ። Frontline Club Oslo በተባለ ድርጅት አማካኝነት በኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ስም እየተካሄደ ያለውን የመሬት ነጠቃ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን አካላት በመጥራት ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል። በስብሰባውም ላይም ከውጭ ጉዳይና  ከሌሎች መስሪያ ቤቶች፣ ከዩኒቨርሲቲ፣ ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በኦስሎ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለጉዳዩ ቅርበት ያላችው አካላት ተገኝተዋል።
ስብሰባውን የጠራው ድርጅት በመወከል ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት ማርየስ ቮንዳርፈር እንደተናገሩት Fronline Club የተባለ ድርጅት በኦስሎ የተቋቋመው በያዝነው ዓመት ሲሆን አላማውም በዓለምአቀፍ ታዋቂ የፊልም እና የፎቶግራፍ ባለሙያዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ እና ምሁራንን በመጋበዝ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቶች እና ዶክመንተሪ ፊልሞችን ማቅረብ መሆኑን ገልጸዋል።  የዓመቱ  ስራውንም የጀመረው በዚሁ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንደሆነ ተመልክቷል።
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ጠንካራ ነቀፋና ተቃውሞ ያልተለየው መሆኑ ይታወቃል። የዚህም ውይይት ዋና አላማ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ የሚደርሰውን ችግር ትኩረት ለመስጠትና ተጽዕኖ ለማድረግ የሚያስችሉ አካላትን ጠርቶ ማወያየት ነው። በመሆኑም በውይይቱ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍንና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የምዕራባውያን መንግስታት በተለይም የኖርዌይ መንግስት ሚና ምን መሆን እንዳለበት በስፋት ትኩረት ተሰቶበታል። በውይይቱ ላይ አራት የተለያዩ አካላት ንግግር አድርገዋል።Abdulahi
የውይይቱ የመጀመሪያ ተናጋሪም አቶ አብዱላሂ ሁሴን ሲሆኑ እርሳቸውም የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪና የኦጋዴን ቲቪ ቻናል ሃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት ያሰባሰቡትን መረጃ በቪድዮ የተደገፈ ዶክመንተሪ በዚህ ስብሰባ አቅርበዋል። የቀረበው ቪድዮ በክልሉ ፕሬዝዳንት እና በክልሉ ባለስልጣናት፣ ፖሊሶችና የጸጥታ አካላት መካከል የተደረጉ ምስጢራዊ ስብሰባዎችን አካቷል። በክልሉ እየተደረገ ያለውን ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ማሰርን፣ ማሰቃየትን፣ ግድያን እና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና ስቃይ ራሳቸው የጸጥታ ኃይሎች የሰጡትን ምስክርነት ዶክመንተሪው አካቷል። በመንግሥት ወታደሮችና ፖሊሶች አማካኝነት በክልሉ እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ወንጀሎች ዶክመንተሪው በማስረጃነት የሚያሳይ በመሆኑ በቀጣይነት ሄግ ለሚገኘው አለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ አቶ አብዱላሂ አመልክተዋል።
በሶማሌ ክልል በሚሰሩበት ወቅት በተለያዩ ቦታዎች በህዝቡ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ችግር የተመለከቱ መሆኑን ከመጥቀሳቸው በተጨማሪ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል ትኩረት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል። ዓለምአቀፉ ማህበረሰብም ሆነ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን በመንግስት ባለስልጣናት እና የጸጥታ ኃይሎች እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ በቂ መረጃ እንደሌላቸው አቶ አብዱላሂ አመልክተዋል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማስረዳት ተናጋሪው ሁለት ነጥቦች አንስተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ኢህአዴግ ጋዜጠኞችንና ዓለምአቀፍ ገለልተኛ ድርጅቶች ወደ ክልሉ እንዳይንቀሳቀሱ በመከልከሉ ሲሆን ይህም ድርጊት በተጨባጭ በክልሉ እየደረሰ ያለው እውነታ እንዳይሰማ፣ እንዳይታይ አድርጎታል። በሁለተኛ ደረጃ ኢህአዴግ ምዕራባዊያንን በውሸት የማሳመኑን ስልት የተካነበት በመሆኑ እስካሁን በክልሉ የሚደርሰውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሸፈኑ ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል ብለዋል። የሳቸውም አላማ ይህንን የሰበሰቡትን የቪዲዮ መረጃ ለዓለምአቀፉ ህብረተሰብ በማቅረብና በክልሉ የሚደርሰውን የዝር ማጥፋት ወንጀል በማስቆም ለዚህ ተጠያቂ የሚባሉ ባለስልጣናትና የጸጥታ ኃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በመቀጠል ንግግራቸውን ያደረጉት እውቁ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር የሆኑት የተከበሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ ሲሆኑ የኖርዌይ ህዝብና መንግስት ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለአጠቃላይ ሰብዓዊነት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽዖ በማድነቅ ንግግራቸውን ጀምረዋል። በግጭትና በተለያዩ የፖለቲካ ቀውሶች ምክንያት በዓለማችን ተጠቂ ህዝቦች ካንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመሰደዱ ሁኔታ የተለመደ መሆኑን በማመልከት ብዙ ስደተኞች ወደ ኖርዌይ የሚመጡበት ምክንያት አገሪቷ ሃብታም እና የበለጸገች ስለሆነች ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና ለሰብዓዊነት ክብር ቅድሚያ በመስጠቷ መሆኑን አቶ ኦባንግ አመልክተዋል።
Panelist2በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የመሬት ነጠቃ ሁኔታ በመጥቀስ የኖርዌይ መንግስትና እርዳታ ሰጪዎች ሊወስዱ የሚገባቸውን እርምጃ በንግግራቸው ጠቁመዋል። በመቀጠልም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት የሚያሳይ ምስል በማቅረብ ምን ያህል አገሪቱ በተፈጥሮ የታደለች መሆኑንና ያገሪቱ ዋና ችግር የመልካም አስተዳደር እጦት እንደሆን አስረድተዋል። በስልጣን ያለው አገዛዝ በህዝቡ ላይ የሚያደርሰው ጭቆና አላንስ ብሎ የአገሪቱን መሬት ለህንድ፣ ለቻይና እና ለሳውዲ ኢንቨስተሮች በርካሽ እየሸጠ ይገኛል። በዚህም ምክንያት ከሚሸጠው መሬት የሚፈናቀሉ ዜጎች በአስከፊ የድህነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በመጥቀስ የሚያፈናቀሉት ዜጎች ህይወት በመሬቱ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ኢህአዴግ በኢንቨስትመንት ስም የሚደርገው ድርጊት የዜጎችን ኑሮ አናግቷል። ምዕራባዊያን አገሮችም በተለይም የኖርዌይ መንግስት ይህንን አስከፊ የህዝቡን ስቃይ እና ችግር እያዩ እንዳላዩ በመሆን ለአምባገነናዊ መንግስት የሚያደርጉትን ድጋፍ እና ድጎማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ይገኛሉ። ይህም የምዕራባዊ መንግስታት ዕርዳታ ህዝቡ እራሱን በራሱ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ነጻ እንዳያወጣና ለማውጣት የሚያደርገውን ጥረት ላይ ትልቅ እንቅፋት እንደሆኑበት አቶ ኦባንግ ተናግረዋል።
ይህ ሁኔታም በዚሁ ከቀጠለም አገሪቷ ወደ እርስ በርስ ግጭት የማምራት ሁኔታ አይቀሬ መሆኑን በማመልከት ምዕራባዊ አገሮች በተለይ የኖርዌይ መንግስት ይህ ከመሆኑ በፊት የህዝቡ ስቃይ እና እንግልት የሚቆምበትን መንገድ በማፈላለግ እና በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ትልቅ ሚና መጫወት እንዳልባቸው አቶ ኦባንግ አሳስበዋል።
በሶስተኛ ደረጃ ንግግራቸውን ያደረጉት ዮሃን ሂላን የተባሉ የማህበራዊ ምሁር ሲሆኑ በሰሜን እና በምስራቅ አፍሪቃ በልማት ዘረፍ የማማከር እና የምርምር ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ከመድረኩ ተጠቅሷል። ባሁን ወቅትም በርገን በሚገኘው በክርስትያን ኤይድ ኢንስቲትዩት ውስጥ እየሰሩ ሲሆን ይህም ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ታውቋል። እኝህ ምሁር ከኢህአዴግ ጋር ያላቸውን ቀረቤታ እና ለአምባገነናዊው መንግስት ያላቸውን አወንታዊ አስተያየት በሚያመለክት መልኩ ንግግር አድርገዋል። በስልጣን ላይ ያለው “መንግሥት” ከጎረቤት አገሮች አንጻር የተሻለ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚታይበትን መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን እኝህ ምሁር ባቀረቡት አስተያየት ላይ ከመድረኩም ሆነ ከተሳታፊዎች ትችት ተሰንዝሮባቸዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች እንደተገለጸው እንደ ዮሃን ሂላን የመሰሉ ምሁር ነን ባይ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ህዝብ በምን ሁኔታ እንዳለ የማያውቁና በተጨባጭ እውነታውን የማያሳይና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመጠቀም የምርምር ውጤቶችን የሚያቀርቡ ምሁራን እንዳሉ የተጠቆመ ሲሆን በዚህም የተሳሳተ የምርምር ድምዳሜ ምክንያት ምዕራባውያን መንግስታት የተወላገደ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዲከተሉ አድርጓል።
በመጨረሻም በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ጥገኝነት ጠያቂወች ዙሪያ የሚያጠነጥን ዶክመንተሪ ቪድዮ ያቀረቡት አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተማጋች የሆኑት ሶልቬይ ስይቨርሰን ናቸው። ይህንን ዓይነቱን ጥናት ለማድረግ ያነሳሳቸው ዋናው ምክንያት የኖርዌይ መንግስት እና የኢትዮጵያ “መንግስት” ስደተኞችን ለመመለስ ያደረጉትን ስምምነት አሳስቧቸው መሆኑን ተናግረዋል። በኖርዌይ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ በመጥቀስ የኖርዌይ መንግስትም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የጉዳዩን ውስብስብነት እንዳልተመለከተው ጠቁመዋል። ያቀረቡትን ዶክመንተሪ ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያቀርቡና የተሻለ የጥገኝነት ፖሊሲ እንዲቀረጽ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ አጭር ውይይት የተደረገ ሲሆን የተለያዩ አካላት ጥያቄና አሰተያየቶች ሰንዝረዋል። የስብሰባው አዘጋጆችም በጉዳዩ ዙሪያ ተከታታይ ውይይት እንደሚደረግ በመጠቆም የዕለቱን መረሃ ግብር አጠቃለዋል።
ከስብሰባው ጋር በተያያዘ የተቀናበረ ቪዲዮ ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ

tirsdag 4. mars 2014

የአላሙዲ የሃብት ደረጃ ከዓለም ቢሊየነሮች እድገት አሳየ፤ የዓለማችን 61ኛው ቢሊየነር ሆኑ


ታዋቂው የዓለማችን የቢዝነስ መጽሔት ፎርብስ በየዓመቱ የዓለማችንን ቢሊየነሮች ደረጃ የሚያሳውቅበትን መረጃ ይፋ አደረገ። ባለፈው ዓመት የዓለማችን ሁለተኛው ሃብታም የነበሩት የማይክሮሶፍት ባለቤት ቢል ጌትስ የዓለማችን አንደኛ ቢሊየነር ሲሆኑ የፌስቡክ ባለቤት ማርክ ዙከምበርግ 21ኛው የዓለማችን ቢሊየነር ሆኗል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በመሬት ነጠቃ የሚከሰሱት ሼህ መሀመድ አላሙዲ የዓለማችን የሃብታምነት ደረጃቸው ከዓመት ዓመት እድገት እያሳየ አምና ከነበሩበት የ65ኛ ደረጃ 4 ደረጃዎችን በማሻሻል የዓለማችን 61ኛው ሃብታም ሆነው በመጽሔቱ ተቀምጠዋል። እንደ ፎርብስ ገለጻ የ8 ልጆች አባት የሆኑት በአባታቸው የሳዑዲ፤ በእናታቸው ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆኑት አላሙዲ $15.3 ቢሊዮን አላቸው።
ከሳዑዲ አረቢያ ሃብታሞች መካከል ሁለተኛው የሆኑት አላሙዲ የወያኔ/ኢሕአዴግ ደጋፊ ከመሆናቸውም በላይ፤ ከስር ዓቱ ጋር በፈጠሩት ስር የሰደደ ወዳጅነት በአድልዎ አብዛኛው የኢትዮጵያ ወሳኝ የንግድ ተቋማት በርሳቸው ስር እንዲያዙ ትልቅ ውለታ እንደተዋለላቸው በተደጋጋሚ እንደሚተቹ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ምንም እንኳ ሼኩ በነዳጅ ዘይት ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ቢሆኑም በተለይም የኢትዮጵያን ወርቅ በእርሳቸው ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ የሰውዬው ሃብት ከእለት ወደ ዕለት እንዲጨምር አስችሎታል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።
የፕላኔታችን 10ሩ ቢሊነሮች የሚከተሉት ናቸው።
1ኛ. ቢል ጌትስ 76 ቢሊዮን ዶላር
2ኛ. ቻርሎስ ሳሊም ሄሉ 72 ቢሊዮን ዶላር
3ኛ. አማሪኮ ኦርቴጋ 64 ቢሊዮን ዶላር
4ኛ. ዋረን ብፌት 58.2 ቢሊዮን ዶላር
5ኛ. ላሪ ኤልሰን 48 ቢሊዮን ዶላር
6ኛ. ቻርለስ ኮች 40 ቢሊዮን ዶላር
7ኛ. ዳቪድ ኮች 40 ቢሊዮን ዶላር
8ኛ. ሼልደን አንደርሰን 38 ቢሊዮን ዶላር
9ኛ. ክርስቲ ዋልተን እና ቤተሰቦቿ 36.7 ቢሊዮን ዶላር
10ኛ. ጂም ዋልተን 34. 7 ቢሊዮን ዶላር
የፌስቡክ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ በ28.5 ቢሊዮን ዶላር 21ኛ፣ አላሙዲ በ15.3 ቢሊዮን ዶላር 61ኛ፣ ቸልሲ ስፖርት ክለብ ባለቤት ኢብራሞቪች በ9.2 ቢሊዮን ዶላር 137ኛ ሆነዋል።
zehabesha

ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል! (ግንቦት7)

March 4, 2014
Ginbot 7 weekly editorialየባህርዳር እና አካባቢው ሕዝብ ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ሺህ ጊዜ እንደሚሻል አካሉን ብቻ ሳይሆን ህሊናውንም ለትግራዩ ነፃ አውጪ ህወሓት ባርነት ላስገዛው “የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)” እያለ እራሱን ለሚጠራው ድርጅት መሪዎች ተናገረ።
ባርነት ክፉ ነው። በባርነት ላይ የጭንቅላት ባዶነት ሲታከልበት ደግሞ አለምነው መኮንንን የመሰሉ የብአዴን መሪዎችን ይፈጥራል። የብአዴን መሪዎች ለጌታቸው ህወሓት ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ራሳቸውን ማዋረዳቸው ሳያንስ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ በጅምላ መስደባቸው ብአዴን እንደ ድርጅት የሚገኝበት የተዋረደ ደረጃ ያሳያል።
ህሊና ያለው ባርያ ዛሬ ነፃ ባይሆንም ወደፊት ነፃ የመውጣት ህልም አለው። ዛሬ በጉልበተኛ የባርያ አሳዳሪ ነፃነቱን ቢያጣም የህሊና ነፃነቱን ያላስደፈረ ባርያ ለነፃነት መታገሉ የማይቀር ነው። እንደ ብአዴን መሪዎች በታማኝ ባርያነቱ እየፈነጠዘ ያለ ባርያ ግን ነፃ ሰው የመሆን ህልሙንም ጭምር አጥቷል። እንዲህ ዓይነቱ ባርያ በአካልም፤ በመንፈስም ባሪያ ነው። ነፃ ሰው የመሆን እድል የለውም።
የአማራ ሕዝብ ብአዴንን የመሰለ አሳፋሪ ድርጅት በታሪኩ ገጥሞት አያውቅም። በፋሽስት ጣልያን ወረራ ጊዜ ለጠላት ያደሩ ባንዶች እንኳን ከዛሬዎቹ ብአዴኖች የተሻለ ክብር ነበራቸው። እነሱም ከዛሬዎቹም በተሻለ በጌቶቻቸው ጣሊያኖች ይሰሙ ነበር። በገዢዎቹ ለመወደድ የራሱን ሕዝብ የሚዘልፍ፣ የሚሰድብና የሚያዋርድ እንደ ብአዴን ያለ አዋራጅ ድርጅት በአማራ ምድር አልታየም።
ለዚህም ነው የባህርዳር እና አካባቢው ሕዝብ የብአዴንና የወያኔን አፈናዎችን በጣጥሶ የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ቁጣውን በባዶ እግሩ አደባባይ በመውጣት የገለፀው። እግር ባዶ መሆኑ ጭንቅላት ባዶ የመሆኑ ያህል የሚያሳፍር አይደለም። ድህነት ወንጀል አይደለም። ነፃ አዕምሮና የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ አስተዳደር ካለ ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የየካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ምን ሕዝባዊ ተቃውሞ ላደራጁና በተቃውሞውም ለተካፈሉ ሁሉ ያለውን አክብሮት ይገልፃል። ሕዝብ ብሶቱን የሚገልጽበት ሕዝባዊ ተቃውሞ ማደራጀትና መምራት መቻል ትልቅ ነገር ነው። ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የማደግ እድል አላቸው። ስለሆነም ግንቦት 7 ለባህርዳሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ አደራጆችና ተሳታፉዎች “እንኳን ደስ ያላችሁ” በማለት የትግል አጋርነቱን መግለጽ ይሻል።
ግንቦት 7፣ ብአዴንን ከአባላቱ ለይቶ ማየት ይሻል። ከዚህም በተጨማሪ የብአዴንን ከፍተኛ አመራር ከሌላው ለይቶ ይመለከታል። ብአዴን ነፍሳቸውን ሳይቀር ለወያኔ በሸጡ ሰዎች የሚመራ፤ ነፃ የመውጣት ተስፋ የሌለው ራሱ ባርያ የሆነ ድርጅት ነው። አባላቱ ግን ከዚህ የተለዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግንቦት 7 ያውቃል።
ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከዚህም በፊትም ደጋግሞ እንደገለጸው፤ በተለያዩ ጊዜያት ራሳቸውን ከወያኔ ባርነት ነፃ ለማውጣት በወሰዱት እርምጃ መስዋእትነት የከፈሉ የብአዴን አባላት መኖራቸውን ያውቃል። ግንቦት 7 ለእነዚህ ቆራጦች ትልቅ አክብሮት አለው። ዛሬም ህሊናቸውን ሙሉ በሙሉ ያልሸጡ የብአዴን አባላት አሉ ብሎ ያምናል። እነዚህ ወገኖቻችን ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የግል፣ የወገንና የአገር ግዴታ አለባቸው ብሎ ያምናል።
ስለሆነም ዛሬም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመን ጥሪዓችንን እናድሳለን።
የብአዴን አባላት ሆይ!!! የገዛ ራሳችሁን፣ የአማራን ሕዝብ እና ኢትዮጵያን እያዋረደ ካለው ብአዴን ተላቀቁ፤ አሊያም እውስጡ ሆናችሁ ድርጅቱን ግደሉት። የብአዴን መኖር ለወያኔ ካልሆነ በስተቀር ለማንም አይበጅም። ነፃነት ካለ ድህነትን በሥራ ማሸነፍ ይቻላል። ሰው ባርያ ሆኖ በሀብት ቢንበሸበሽ ምን ይፈይድለታል?
የብአዴን አባላት ሆይ!!! ወደ ህሊችሁ ተመለሱ። ራሳችሁንም የበደላችሁትን ሕዝብ የመካስ እድል አድል አላችሁ ተጠቀሙበት። ይህንን ባታደርጉ ግን ለገዛ ራሳችሁ ፀፀት፤ ለልጆቻችሁ ሀፍረትን የምታወርሱ መሆኑን አትዘንጉ። ወያኔ መሸነፉ በጭራሽ የማይቀር መሆኑን እያወቃቸው በድህረ ጣልያን ወረራ ባንዶች ያገኙትን ምህረት እናገኛለን ብላችሁ አታስቡ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

mandag 3. mars 2014

አህመድ በማያውቃቸው ሰዎች ኩላሊቱ የተዘረፈበት ኢትዮጵያዊ

ከሳውዲ አረቢያ ተመላሾች አስከፊ የህይወት ገጽታ አህመድ በማያውቃቸው ሰዎች ኩላሊቱ የተዘረፈበት ኢትዮጵያዊ
የሃያ አመቱ አህመድ ከሳውዲ አረቢያ የተመለሰው ከአንድ ወር የእስራት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ከስደት ተመላሾች ማገገሚያ ውስጥ ይገኛል፡፡
አህመድ በሆዱ አካባቢ የሚታዩት ጠባሳዎች የቅርብ ግዜ ጠባሳዎች እንደሆኑ ያስታውቃሉ፡፡ በህክምና ባለሞያዎች በተደረገለት የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራም አህመድ የግራ ኩላሊቱን እንዳጣ ይጠቁማል፡፡
አህመድ ከማእከላዊ የአማራ ክልል አካባቢ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ነው በጅቡቲ እና በየመን አቆራርጦ ሳውዲ አረቢያ የገባው፡፡ ለዚህም ጥቂት የማይባሉ ሺህ ብሮችን ከፍሏል፡፡
አህመድ ለአንድ አመት ከስድስት ወር በረያድ በእንጨት ሰራተኝነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከሚያገኘውም ገቢ ለቤተሰቦቹ አቅሙ የፈቀደውን ይልክ ነበር፡፡ ከሶስት ወር በፊት ነበር በሰው ልጅ ላይ ሊፈጽሙት የሚከብደው አሰቃቂ ድርጊት የተፈጸመበት በወቅቱ አህመድ የነቃው በሪያድ ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡
ራሱን በፋሻ ተጠቅልሎ ነበር ያገኘው፡፡ ነገር ግን ወደ ሆስፒታሉ እንዴት እና በማን እነደመጣ የሚያውቀው ነገር ጨርሶ አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር አህመድ ‹‹ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የለውም›› በሚል ምክንያት ወደ እስር ቤት የተወረወረው፡፡
በመጨረሻ አህመድ ወደ ሃገሩ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ መንግስት አማካኝነት በአውሮፕላን የሃገሩን መሬት ለመርገጥ የቻለው፡፡
በአሁኑ ሰዓትም ወዳደገበት የትውልድ መንደሩ ለመመለስ የዶክተሮቹን መጨረሻ ውሳኔ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

søndag 2. mars 2014

አይተ ስብሐት ነጋ ‹‹ሕወሃት ውስጥ በነጻነት መናገርና መጻፍ ይቻላል››

ለዛሬው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ቃለ ምልልስ የሰጡት አይተ ስብሃት ነጋ ሕወሃት ዴሞክራሲያዊ መሆኑን በማስመር ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት በድርጅቱ የተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡‹‹ሕወሃት ውስጥ በነጻነት መናገርና መጻፍ ይቻላል››ብለውናል፡፡መቼም አቦይ ላለፉት 22 ዓመታት ስልጣን ላይ ስለቆየው ሕወሃት የተናገሩ ከሆነ አስገራሚ ነው፡፡ምናልባት አንድ እኔ ስላላወቅኩት በሌላ አገር ስለሚገኝ ሕወሃት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የእኛ አገሩ ሕወሃት ስብሃት የሚሉት ቁመና እንደሌለው ለማወቅ የድርጅቱ የፖሊት ቢሮ አባል መሆንን አይጠይቅም፡፡ሕወሃት ለተለየ ሐሳብ ቦታ የሌለው አባላቱን እንደ አንድ የፋብሪካ ሳሙና አንድ አይነት መልክ እንዲላበሱ የሚያደርግ አዲስ ሐሳብ ይዘው የሚመጡበትን እነ እከሌ ‹‹የድርጅቱ ጋንግሪን ሆነዋል››እያለ ከመቁረጥ የማይመለስ፡፡አመራሮቹንና አባላቱን እንደ ገደል ማሚቶ በሊቀመንበሩ የተባለውን ብቻ እየተቀባበሉ እንዲያስተጋቡ የሚያዝ ውስጣዊ ዲሞክራሲን የማያውቅ ለመሆኑ ድርጅቱን የተሰናበቱ ሰዎችን በመጠየቅ መረዳት ይቻላል፡፡
የአረና ሰዎች በትግራይ ክልል ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንቅፋት እየፈጠረ አረናዎችን በድንጋይ ማስደብደቡና ለእስር መዳረጉ የሚያሳየው ድርጅቱ የተለየ ሐሳብ ለህዝቡ መቅረቡን ምን ያህል እንደሚፈራ ነው፡፡
ስዬ አብርሃ፣አስገደ ገብረስላሴ፣አረጋሽ፣ገብሩ አስራትና ሌሎችም የሕወሃት የቀድሞ አመራሮች ከድርጅቱ የወጡት ከሊቀመንበሩ የተለየ አቋም በማራመዳቸው ነበር፡፡በሀሳብ የተለዩትን ሰዎች ሕወሃት የሚሸከምበት አቅም በማጣቱም አመራር ሲሰጡለት የከረሙትን ለእስር በመዳረግ የሐሳብን መንገድ ፈጽሞ እንደማያውቃት አሳይቷል፡፡ዛሬ ደርሶ አቦይ ሕወሃትን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ መሞከራቸው አስቂኝ ይሆናል፡፡

118 ኛዉ የአድዋ ድል በዓል አከባበር

118 ኛዉ የአድዋ ድል በዓል መታሰብያ በኢትዮጵያና በተለያዩ የዓለም ሃገራት በሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ በከፍተኛ ድምቀት ተከበረ።
Feier 118. Schlacht von Adua
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፤ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘዉ የአፄ ሚኒሊክ አደባባይ የጥንታዊ ኢትዮጵያ የአርበኞች አባላት፣ የመንግሥት ተወካዮች እና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ዶክትር ታቦር ገመድህን፤ በአፄ ሚኒሊክ ሃዉልት ስር የአበባ ጉንጉን አኑረዋል። ኢትዮጵያዉያን የጣልያን ወራሪ ጦርን ድል ያደረጉበት ይህ በዓል፤ ለአፍሪቃዉያን እና ለመላዉ ጥቁር ሕዝብ ደግሞ ኩራትን ማቀዳጀቱ ይታወቃል። በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የአፍሪቃ አገሮች ላደረጉት ከፍተኛ የነፃንት ተጋድሎ የኢትዮጵያዉያኑን፤ የአድዋ ድል በቀደምትነት የሚጠቅሱበት እና የህሊና ጥንካሬን የሚያገኙበትም ነበር።
የ118 ኛዉ የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ በተለይ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘዉ የአፄ ሚኒሊክ አደባባይ እንዴት ተከብሮ እንደዋለ ወኪላችን ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ ተከታትሎ የድምፅ ዘገባ ልኮልናል።
ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ

torsdag 27. februar 2014

አብርሃ ደስታ… ታስሮ ተፈታ!!


EMF – በትግራይ ውስጥ የሚደረጉ ግፍ እና በደሎችን ያለመሰለስ በማጋለጡ ይታወቃል:: ለሰብአዊ መብቶች መከበር በመቆሙ ከህወሃት ሰዎች ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ እና ዛቻዎች ሲደርሱበት ነበር:: ባለፈው ሳምንት ቃሊቲን ለመጎብኘት የፖለቲካ እስረኞችንም ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በነበረበት ወቅት “እንዴት የፖለቲካ እስረኛ ለመጠየቅ ከትግራይ ድረስ መጣህ?” በሚልም ለእስር ዳርገውታል:: ሁኔታውን እራሱ አብርሃ ደስታ እንዲህ በማለት ገልጾታል::
አዲስ አበባ ነበርኩ። ሰኞ ጧት ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌና ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ለመጠየቅ ቃሊቲ ማረምያቤት ሄድኩኝ። ጥበቃዎቹ ወደ ማረምያቤቱ አስተዳዳሪ ወሰዱኝ። አስተዳዳሪው ምርመራ ይሁን ዛቻ በማይታወቅ መልኩ ካስፈራራኝና ከሰደበኝ በኋላ ከማረምያ ቤቱ ተባረርኩ። አስተዳዳሪው “አንተ ከትግራይ አክራሪ አማራዎችን ለመጠየቅ ስትመጣ አታፍርም?!” አለኝ። ከፈለኩ ብሄር ብመጣም የፈለኩትን ሰው የመጠየቅ መብት አለኝ። የታሰረ ሰው መጠየቅ አያሳፍርም” መለስኩለት። ካሁን በኋላ “ወደ ቃሊቲ የምትገባው ታስረህ ካልሆነ በቀር እነ አንዱኣለምን ለማየት ድርስ አትላትም!” ብሎ ፖሊሶችን እንዲያስወጡኝ አዘዘ።
ወደ ቂሊንጦ ማረምያ ቤት ተጓዝኩ፤ ኡስታዝ አቡበክር አህመድን ለመጠየቅ። “አሸባሪ ለመጠየቅ መጣ” ተብዬ ለሦስት ሰዓታት ታሰርኩ። የቂሊንጦ ማረምያቤት ዋና አስተዳዳሪ እምባዬ ህቡዕ “አሸባሪዎችን ለማበረታታት መጣህ፣ ማረምያቤቱን ለመበጥበጥ ነው የመጣኸው። እንዳውም አሁን በማረምያቤቱ ረብሻ ተነስቷል። ስለዚህ ይታሰር” ብሎ በማዘዙ ወህኒቤት ዉስጥ ቆየሁ።
 ዝርዝር ጉዳዩን ለመፃፍ እሞክራለሁ። አንዱኣለም አራጌና ርእዮት አለሙን አላየኋቸውም። አቡበክር አህመድ (ና ሌሎች ጉደኞቹ) ግን አግኝቻቸዋለሁኝ። እነ አቡበክር አህመድን በማግኘቴ ደስ ብሎኛል።