torsdag 1. mai 2014

ሰበር ዜና፣ በጎንደር ተኩሱ ቀጥሏል፣ በግጭቱ 6 ሰው ሞቷል May 1, 2014

ነገረ-ኢትዮጵያ – ጎንደር ከተማ ውስጥ ቀበሌ 18 ልዩ ቦታ አርምጭሆ ሰፈር፣ ገንፎ ቁጭና ህዳሴ የተባሉ ሰፈሮች የከተማው አስተዳደር ‹‹ህገ ወጥ ሰፈራ ነው፡፡›› በሚል ቤቶችን ለማፍረስ መዘጋጀቱን ተከትሎ አፍራሾቹ ከህዝብ ጋር በፈጠሩት ግጭት ከ6 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸውንና መታሰራቸውን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ግጭቱ ከሶስት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ተኩል ድረስ ቀጥሎ የነበር ሲሆን ምንጫችን ደውሎ በሚነግረን ወቅት (ከቀኑ 6፡ 43) ተኩስ እንደነበር ለመረዳት ችለናል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎቹ ሚያዝያ 7/2006 ዓ.ም ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ትዕዛዝ በተላለፈበት ወቅት ህገ ወጥ አለመሆናቸውን፣ ካልሆነም መንግስት ቅያሬ ቦታና ጊዜ መስጠት እንዳለበት በመግለጽ አንለቅም ብለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዛሬው ቀን ግጭቱ የተነሳውም አፍራሾቹ እንዲፈርሱ የተወሰነባቸውን ቤቶች ቀለም በመቀባታቸውና ህዝቡም እንዳይቀቡ በመከልከሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
በግጭቱ ፖሊስ፣ ፌደራልና ልዩ ኃይል የተሳተፈበት ሲሆን ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ የአካባቢው ወጣቶች ላይ ድብደባና እስራት እየፈጸሙባቸው እንደሆነ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ‹‹ወጣቶችን እንደ እንሰሳ በአንድ ገመድ አስረው እየደበደቧቸው ነው፡፡ ህዝብ በጅምላ እየታሰረ ይገኛል፡፡ ግጭቱ ቢያቆምም በአሁኑ ወቅት በሶስቱም ሰፈሮች ጥይት እየተተኮሰ ነው›› ያሉት የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች የተወሰደው እርምጃ የጎንደርን ህዝብ በማስቆጣቱ ከዚህ የባሰ ግጭት እንዳይፈጠር ያሰጋል ሲሉም ገልጸውልናል፡፡ በግጭቱ ወቅት የመጀመሪያዋ የሞት ሰለባ የሆነችው ልዩ ኃይል ቤቷ እንዲፈርስ ቀለም ሲቀባ የተቃወመች የልጆች እናት እንደሆነችም ታውቋ፡፡

fredag 18. april 2014

ወቅታዊ ሪፖርት በኖርዎይ:

የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዎይ የሚገኙ ኢትዮጵያን ስደቶኞች የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው የሚኖሩበት ሃገር እንደሚሰለሉ እና የወያኔ ሰላዮች በኖርዎያ እንደሚገኙ የኖርዎይ ደህንነት ፖሊስ ለሃገሩ ትልቅ መረጃ መስጠታቸውን በተመሳሳይ ሂውማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ያወጣውን መረጃ መሰረት በማድረግ የኖርዎይ መንግስታት ለወያኔ ሰላዮች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆም እና አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ለመጠየቅ እና ኖርዎይ በኢትዮጵያውያን ላይ ያላትን አሳይለም ፖሊሲ እንድታስተካክል በሚል የጠራውን ሰልፍ እጅግ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። ይህ ሰልፍ የኢትዮጵያን በኖርዎይ ምን ይህል የሃገራቸው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው እና እየታገሉ እንደሆነ የሚያሳይ ሰልፍ ነበረ። ከኖርዎይ ጂኦግራፊያዊ ይዘት አንጻር ለመሰባሰብ አስቸጋሪ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን ችግር ከምንም ሳይቆጥሩት ድምጻቸውን እንዳሰሙ ይገኛሉ በርቱ የሚያሰኝ ነው። በሌላውም ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንደ ኖርዎይ አንድ ሆነው ድምጹ የታፈነውን ህዝባችንን ድምጽ ሊሆኑለት ይገባል።











በኖርዎይ ዋና ከተማ ኦስሎ ከተለያዩ ቦታ በተሰባሰቡ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው
የሚደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ማስተናገዱን ተያይዘዋለች። በኖርዎይ የሚገኙ ጠንካራ
ተቃዋሚ ድርጅቶች በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት, የኢትዮጵያ
ስደተኞች ማህበር ትልቁን ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ የተለያዩ ድርጅቶች ለሚያዘጋጁት
ሰልፎች መሳካት ደግሞ በኖርዎይ ነዋሪ የሆኑ እና በተለያዩ ካንፕ ውስጥ የሚገኙ ሃገር ወዳድ
ኢትዮጵያውያን ተጠቃሽ ናቸው። ዓርብ አፕሪል 11 2014 ያየንው ይህንንው ነው። በዚህ
ዕለት የኢትዮጵያውያ ሰደተኞች ማህበር የጠራውን ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ነበር። ሠልፉ
የሚጀምረው ከቀኑ 12 ሰአት ይሁን እንጂ በሀገሩ ወቅታዊ ሁኔታ የሚንገበገበው ሀገር ወዳድ
ኢትዮጲያዊ ከተባለው ሰአት በፊት ጥሪ በተደረገበት ቦታ ተሰባስቦ የፕሮግራሙን መጀመር
ሲጠባበቅ ነበር። የተባለው ሠአት ሲጀምር የዝግጅቱ አስተባባሪዎች የእንኳን ደህና
መጣችሁና የዝግጅቱን አላማ በማስተዋወቅ ዝግጅቱ ጀምሯል። ልክ ንግግሩ እንዳለቀ
በፕሮግራሙ መሰረት ያለውን ችግር ወደ ሚያስረዳበት ፖርላማ ጉዞውን አድርጎዋል።
ህዝቡም ፖርላማ እስከሚደርስ ድረስ የተለያዩ መፈክሮችን እያሰማ ነበር። በሰልፉ ላይ
የተሳተፈው ህዝብም መፈክሩን የሚያሰማው እጅግ ከልቡ ተቆጥቶና በከፍተኛ ጩኸት ነበር።
በዚህ ወቅትም በጎዳና ላይ የነበሩ ኖርዊጅያኖች በመገረም መንገዳቸውን ትተው ቆመው
ሲያስተውሉ ነበር። አንዳንዶችም ካሜራቸውንና ሞባይላቸውን ወደ ሰልፈኛው ቀስረው
ለረጅም ሰአት ሲቀርጹ ነበር። በዚህ ሁኔታ ወደ ፓርላማው ከተደረሰ በኌላ የተለያዩ
ግለሰቦች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ስለ ወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ እና ስለሰልፉ አላማ
ንግግሮች አድርገዋል። ሠልፉን በተመለከተም መልዕክታቸውን ከፓርላማ ለተላኩት ግለሰብ
ሠጥተዋል።

            አፕሪል 12/2014 በኖርዌ ኦስሎ ከተማ በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ
የድጋፍ ድርጅት አዘጋጅነት የአትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንደዚሁም የዲያስፖራው
የትግል ተሳትፎን የዳሰሰ ታላቅ ስብሰባ ተካሂዷል። በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ በርካታ
አትዮጵያውያን ተገኝተዋል።













ለ6 ሠዓታት ያህል የተካሄደው ይህ ስብሰባ የጀመረው በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ አቢ አማረ ጋባዥነት በሀገራችን ባለው በዘረኛው አረመኒያዊ ስርአት በጭካኔ በግፍ ለተገደሉ እና በተለያዩ እስር ቤቶች በፓለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ያለጥፍታቸው ያሚሰቃዩትን ውድ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችንን በማሰብ በዚሁ ዘረኛ ቡድን ሰለባ ለሆኑ እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ ነበር። በመቀጠል አቶ ዩሀንስ አለሙ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ሊቀመንበር የመግቢያ ንግግር አድርገዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ የእለቱ ተጋባዥ እንግዳ የሆኑት የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ብዙነህ ጽጌ የተገኙ ሲሆን በሃገራችን ስላለው ጠቅላላ የፖለቲካ ሁኔታ እና የግንቦት 7ን አስተዋጽኦ ከህዝቡ የሚጠበቀውንም አጠቃሎ እጅግ ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል። በዝግጅቱ ላይ በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት አባሎች ‘’ላንቺ ነው ሃገሬ’’ የሚለውን መዝሙር አቅርበዋል።














ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!!!

lørdag 12. april 2014

ሒላሪ ክሊንተን ጫማ ተወረወረባቸው ( ቪዲዬ )



በመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ እየተባሉ የሚጠበቁት ሒላሪ ክሊንተን ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ጫማ ተወረወረባቸው፡፡ ጉዳት ባይደርስባቸውም ዜናው ግን የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ ስቧል፡፡
አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተን በላስ ቬጋስ በተጠራ የመልሶ መጠቀም ኢንዱስትሪዎች (Scrap Recycling Industries) ስብሰባ ላይ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ ከአዳራሹ ጫማ ተወርውሮባቸዋል፡፡
ጫማው ሳይመታቸው ቢቀርም ወርዋሪዋ ግለሰብ አስተካክላ ብትወረውር ግን ክፉኛ ጉዳት ልታደርስባቸው ትችል እንደነበር የቪዲዮው ምስል ያመለክታል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ አዳራሹ ጨለምለም ያለ በመሆኑ ክሊንተን ጫማው ከተወረወረ በኋላ ነው ያስተዋሉትና ደበቅ ለማለት የሞከሩት፡፡
ሒላሪ ክሊንተን በጉዳዩ ላይ ቀልድ በማከል አስተያየት የሰጡበት ቢሆንም የስብሰባው ኃላፊዎች ግን ታላቅ ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ጫማ ወርዋሪዋ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የዋለች ከመሆኗ በላይ ማንነቷ ገና አልተገለጸም፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ሚስት ሒላሪ ከፍተኛውን የፖለቲካ ሥልጣን ለመቆናጠጥ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በነበሩበት አራት ዓመታት ያከናወኗቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ደጋፊዎቻቸው ቢጠቀሱም የጋዳፊ ግድያ ከዚያም ጋር ተያይዞ የተከሰተው የቤንጋዚው ቀውስ እና የአሜሪካው አምባሳደር መገደል፣ በግብጽ የተካሄደው ለውጥና ከዚያም በአሜሪካና ምዕራባውያን ግፊት ለውጡ መቀልበሱ፣ በአፍጋኒስታንና ፓኪስታን ላይ የወሰዱት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በአፍሪካ እንደነ መለስ ካሉ አምባገነኖች ጋር በመሞዳሞድ ግብረሰዶማዊነት እንዲስፋፋ አሜሪካ የተከተለችው ፖሊሲ፣ ወዘተ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሒላሪ ኪሊንተን በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚ/ርነት ዘመናቸው ስላከናወኑት የሚያወሳ “የሚኒስትር ማስታወሻ” በገበያ ላይ ያውላሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
የዛሬ ስድስት ዓመት አካባቢ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በኢራቅ ከጠ/ሚ/ር ኑሪ አልማላቂ ጋር ንግግር ሲያደርጉ አገሩ በአሜሪካ ወራሪነት መፍረሷ ያናደደው ኢራቃዊ ጋዜጠኛ የጫማ ሚሳኤል ወርውሮባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
http://www.goolgule.com/shoe-thrown-at-hillary-clinton-at-vegas-speech/

mandag 7. april 2014

ህወሀት ኢሕአዴግን ለማገልገል ህዝባቸውን የሚጨፈጭፉ ሎሌዎች (በሁኔ አቢሲኒያዊ)


(ክፍል ሁለት)
በክፍል አንድ የወያኔውን ሎሌ ባጫ ደበሌን ብልሹ ስራዎች አይተናል ዛሬ 180 ዲግሪ ዞሮ የወያኔ አሽከር ስለሆነው ሬድዋን ሁሴን አንዳንድ ነገሮች እንላለን፡፡
መልካም ንባብ
አቶ ሬድዋን የ1987 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባዮሎጂ ምሩቅ ናቸው። ከምረቃ በኋላ ለማስተማር ጂንካ የተወሰነ ጊዜ አሳልፈዋል። ደቡብ ኢትዮጵያ ብዙም አልቆዩም። አዲስ አባባ መጥተው አወሊያ ትምህርት ቤት መምህር ኾኑ። የአወሊያ ትምህርት ቤት ቆይታቸው አስደሳች የኾነም፤ ያልኾነም ነበር። ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋራ በተደጋጋሚ ይጋጩ እንደነበር ይነገራል። በ1980ዎቹ መጨረሻ እና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የስልጤን የማንንት ጥያቄ በዋናነት በማቀንቀን ይታወቃሉ። “ስልጤ በደቡብ ክልል ውስጥ ውክልና ይገባዋል
ከሚለው አልፎ በዞን ደረጃ እንዲዋቀር ተሟግተዋል።” በወቅቱ በርካታ የስልጤ ተወላጆችን በቅርብ ማግኘት በመቻላቸው በጉዳዩ እንዲገፉበት ዕድል ሰጥቷቸዋል። በዚያውም የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ስሕዴፓ)ሲያቋቁም ከመሪ ተዋንያኑ አንዱ ሆነው ብቅ አሉ፡፡
ኢሕአዴግም እንደለመደው በአሁኑ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የቀድሞ የአለማያ ዩኒቨርስቲ የደን ልማት(ፎረስትሪ) ጥናት ተማሪ በነበሩት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የሚመራውን “የስልጤ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት” (ስሕዴድ) አቋቋመ። ሁለቱ የስልጤ ሕዝብ ድርጅቶች እርስ በርስ ይፎካከሩ ሲልም በግልጽ ይተቻቹ ነበር። ፀባቸው ሌላ አይደለም። እውነተኛ የስልጤ ሕዝብ ተወካይ ማን ነው?የሚለው ነው። ሬድዋን የእነ አቶ ሲራጅን ስሕዴድ፣ “አሻንጉሊት” እና “የኢሕአዴግ ተላላኪ” በማለት እስከ እስከ መወጀል ይደርሱ እንደነበር ይነገራል።
በ1992 ዓ.ም “የስልጤ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና ከጉራጌ ሕዝብ የተለየ ማንነት ያለው መኾኑ በሕዝብ ውሳኔ ሲረጋገጥ የአቶ ሬድዋንም ሚና እና የፖለቲካ አቅጣጫ ተቀየረ።” ይላሉ ለአዲስ ነገር ሐሳባቸውን ያካፈሉት ውስጥ አዋቂ። በ1992 በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ የሬድዋን ፓርቲ ከደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ተወዳድሮ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገቡ። ሬድዋን በፓርላማ በቆዩባት አጭር ወቅት በኢሕአዴግ ምን ያህል እንደ ተዋጡ ተገነዘቡ። ለፖለቲካ ግባቸው ስሕዴፓ ሳያንስባቸው አልቀረም።
ፓርላማ ከገቡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሬድዋን እና ጓዶቻቸው ስሕዴፓን አፍርሰው ድሮ ሲተቹት የነበረውን የአቶ ሲራጅን ስሕዴድ ተቀላቀሉ። የፓርላማ ውክልናቸውን ጥለው “የስልጤ ዞን የሕዝብ ጉዳዮች አደረጃጀት” ሐላፊ በመኾን እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ቆዩ። በ1997 ዓ.ም ከስልጤ ዞን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በመወዳደር የደቡብ ክልል ምክር ቤትን ተቀላቀሉ። ከዚያ በኋዋላ ነው የደቡብ ክልል ምክር ቤት የትምህርት ቢሮ ሐላፊ ብሎም የደኢሕዴን የሥራ አስፈጻሚነትን የተቀላቀሉት።
የስልጤ ዞን በምርጫ 97 ልክ እንደ ደሴት ነበረች። በዙሪያው የነበሩት አጎራባች ክልሎች በአብዛኛው የኢሕአዴግን ተቃዋሚዎች የመረጡ ሲኾን ስልጤ ግን ስህዴድን/ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን መርጣለች። በ97 ዓ.ም የነበረው የተቃዋሚዎች ማዕበል ጉዟቸውን አፋጥኖላቸዋል። በአምስት ዓመት ውስጥ ከወራቤ ከተማ ተነስተው የኢሕአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ “ወንጌል” ዋና አጥማቂ ኾነው ወጡ፤ በምድረ በዳ የሚጮሁ።
ኢሕአዴግ “ዱላ መቀባበል” በሚለው ጨዋታ “የፊት መሥመር ተሰላፊ የነበሩት ወደ ኋላ ኾነው፣ የድርጅት ሥራ የሚሠሩት ወደ ፊት የሚመጡበት ነው” በሚለው መሠረት “ትጉህ ባርያ” የነበሩት አቶ ሬድዋን የአቶ በረከት ስምዖን ቦታ ያዙ ተብሎ ። የሬድዋንም የተስፋ ምድር ይህች ነበረች። የአቶ በረከትን ቦታ ማግኘት
አቶ ሬድዋንን ኢሕአዴግ ግንባር ቀደም የምርጫ ተከራካሪ አድርጎ ለማምጣት በፓርቲው ውስጥ በዚሁ ታሪካቸው የተነሳ የሐሳብ ልዩነት እንደነበር ይነገራል። “ድሮ ይቃወመን በነበረ ሰው መወከል!” በሚል። ዋናው ነገር ሬድዋን ሥራቸውን አይዘነጉም። “የተለያዩ ማኅበራትን ታደራጃለህ”፤ “ከጀርባ ትቆጣጠራለህ”፤ የሚለው የፖለቲካ ቅኝት እየተሰጣቸው ለሚፈልገው ዓላማ ይሰናዳሉ። አቶ ሬድዋንም ይህችን አሠራር ከአዲስ አባባ የክፍለ ከተማ ስበሰባዎች፣ በፍቼ እና በአላጌ ተግብረዋታል። የአዲሱ በረከት ጠንካራ ጎኑም ይህ ነው።
እነ አቶ ሕላዌ መሠረቱን የጣሉለትን ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ የሚወስድ ግንባር ቀደም ካድሬ ይፈለግ ነበር። ኢሕአዴግ ዐይኑን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ጣለ። ደቡብ ኢትዮጵያ በፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት “የተካኑ” የሚባሉ ሰዎችን ማፍራት ይዟል። አቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ካሊድ አሕመድ፣ ሬድዋን ሁሴን፣ መኩሪያ ኀይሌ ከሌሎቹ አጋር የኢሕአዴግ ፓርቲዎች በላቀ ጎላ ብለው መታየት ጀምረዋል።
በወቅቱ የደቡብ ክልል የትምህርት ቢሮ ሐላፊ፣ የደኢሕዴን ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት አቶ ሬድዋን ሑሴን ደግሞ በተናጋሪነታቸው ይታወቃሉ። በዚያ ላይ የሕዝብ አደረጃጀት ልምድ አላቸው። የሁሉም ዐይን ሰውየው ላይ አረፈ። ሬድዋንም ወደ አዲስ አበባ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሐላፊነት ተመደቡ፡፡
ሥራው ቀላል እና ግልጽ ነው። “ፓርቲውን በሕዝብ ውስጥ ማሥረጽ።” “ከፍተኛ ቁጥር ያለው አባል መመልመል፤ የተመለመሉትንም ከእምነታቸው እንዳይናወጹ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ማስረጽ – ሁለተኛ ተፈጥሯቸው እስኪመስል። ” በከተማው አስተዳደር ውስጥ የፓርቲ ሥራ ከመንግሥት ሥራ ጋራ የጨው እና የውኃ ያህል እስኪወሃዱ ድረስ ሬድዋን እረፍት የላቸውም። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራጅተው የፓርቲውን ጥቅም በዘላቂነት እንዲያስከብሩ ይታትራሉ። ሬድዋን በሚመሩት የአዲስ አበባ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኙ አራት ወሳኝ የመመልመያ እና መከታተያ መዋቅሮችን ይመራሉ። የአባላት ሥልጠና፣ አነስተኛ እና ጥቃቅን እና ትምህርት፣ ግብር መልስ እና ሱፐርቪዥን እና የሕዝብ አደረጃጀት ናቸው።
ሁኔ አቢሲኒያዊ
ኦክስፎርድ ዩ.ኬ

የጠበቆች ማህበር በአርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ላይ የወንጀል ክስ መመስረታቸው ተሰማ


በአዲስ አበባ ታትሞ የሚወጣው ማራኪ መጽሔት እንደዘገበው በቅርቡ በሰይፉ ፋንታሁን የኢቢኤስ ሾው ላይ ቀርቦ በአዲስ ፊልሙ ላይ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቅሞ መስራቱን ለማህበረሰቡ ያሳየው አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ የጠበቆች ህብረት በጋራ የወንጀል ክስ አቅርበውበታል።
ጠበቃ ማቲያስ ግርማ ለማራኪ መፅሄት እንዳስረዱት በክሱ ላይ ሰይፉ ፋንታሁንና አለማየሁ ታደሰ ደጋፊ ሀሳብ በመስጠታቸው ክስ ይመሰረትባቸዋል ብለዋል። አርቲስቱ ምንም እንኳ ለፊልም ግብዓት “መስለው ሳይሆን ሆነው” ለመስራት ያደረጉት ተግባር ቢሆንም ህብረተሰቡን ከወንጀል ለመጠበቅ ሲባል ክስ እንደተመሰረተባቸው የጠበቆች ተወካዩ አስረድተዋል።

“ይህንን የበለጠ ማጣራት የነበረባቸው ፖሊስና አቃቤ ህግ ቢሆኑም ፣ በግልፅ በሀገሪቱ የአየር ክልል የተላለፈውን መረጃ ዝም ማለታቸው እንዳሳዘናቸውም ገልፀዋል። በሀገሪቱ የወንጀል ህግ ስርዓት በተለይ ግሩም በክሱ ጥፋተኛ ከተባለ እስከ ሰባት አመት እንዲሁም የ50ሺ ብር ቅጣት ይጠብቀዋል።

በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ 1996/97 አንቀፅ 525 ንዑስ አንቀፅ/ሀ መሰረት እስከ ” አደንዛዥ ዕፅን እራሱ ወይም ሌላ ሰው ሊጠቀምበት በማሰብ የገዛ፣የተጠቀመ፣ እንዲጠቀም ያደረገ፣,,,” ከ7 ዓመት እስከ 50ሺ ብር ቅጣት ይጠብቀዋል። እነ ሰይፉ ደግሞ “ወንጀልን ባለማወቅ” ክስ ተመስርቶባቸዋል።
መጽሔቱ ዘገባውን ሲያጠናቅቅ ለግሩም በቅርብ መጥሪያ ይደርሰዋል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።
Ze-Habesha 

mandag 31. mars 2014

የማሕበረ ቅዱሳን የመጨረሻዎቹ ቀናት – ከተመስገን ደሳለኝ


በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የሚመራው መንግስት ከናቅፋ እስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አይሮፕላን፣ ከምድር እሳት በሚያዘንቡ ቢ.ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥ ደበድብም፤ በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውን እያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምታት ሆነውበታል፡፡ የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጪ›› ቤዝ-አምባው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለጥቃት የመጋለጥ እድሉ አናሳ በሆነው የሳህል በረሃ በመሆኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያው አድርጎታል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመሆኑ፤ በርካታ ክፉ ቀናትን ያሳለፉት በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ገዳማት ውስጥ ተደብቀው እንደሆነና ከቦታ ቦታ መዘዋወር ሲፈልጉም የመነኮሳቱን አልባሳት ይጠቀሙ እንደነበረ በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በተለይም ታጋይ መለስ ዜናዊ፣ አባይ ፀሀዬ፣ ግደይ ዘርአፅዮን፣ ስዩም መስፍን፣ ስብሐት ነጋን…. የመሳሰሉ የአመራር አባላት የገዳማቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡ ከዚሁ ጋ ተያይዞ የሚነገርም አንድ ታሪክ አለ፤ የመንግስት ፀጥታ ሰራተኞች ሁለት የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች በትግራይ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ ከመነኮሳቱ ጋር ተመሳስለው መሸሸጋቸው መረጃ ይደርሳቸውና በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮችን በመላክ ዙሪያ ከበባ ያደርጋሉ፡፡ ይሁንና መደበቂያ በመስጠት የረዷቸው መነኮሳት ሁለቱን ታጋዮች ‹‹ወይባ›› በመባል የሚታወቀውን ረጅሙን ቀሚሳቸውን አልብሰው እና ቆብ አስደፍተው ከአካባቢው በማሸሽ ይታደጉዋቸዋል፡፡ የታሪኩ ባለቤት መለስ ዜናዊ እና አባይ ፀሀዬ ነበሩ፡፡ በርግጥ እነዚህ የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች ‹በእንዲህ አይነቱ ከመርፌ አይን እጅግ በጠበበ ዕድል ህይወታችን ከሞት መንጋጋ ተርፎ ኮለኔል መንግሥቱን በጓሮ በር ወደ ዜምባብዌ ሸኝተን በትረ-መንግሥቱን ለመጨበጥና ለሃያ ምናምን ዓመታት ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር አንቀጥቅጠን ለመግዛት እንበቃለን› የሚል ጠንካራ እምነትና የእርግጠኝነት ስሜት በወቅቱ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ለእነርሱም ቢሆን እጅግ አዳጋች ይመስለኛል፤ የሆነው ግን ይህ ነበር፡፡

‹‹ማሕበረ-ቅዱሳን››


መለስ ዜናዊና ጓዶቹ በለስ ቀንቷቸው ባልጠበቁት ፍጥነት የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግስጋሴ ሲያፋጥኑ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ሰብሳቢበት፣ በደህንነት ሠራተኞች እና የኢሠፓ ካድሬዎች ገፋፊነት ትምህርታቸውን አቋርጠው ለወታደራዊ ስልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴና የጦር ማሰልጠኛ ከተቱ፤ ዩኒቨርሲቲውም ተዘጋ፡፡

…ከመላው ዘማቾቹ አስራ ሁለት የሚሆኑ ተማሪዎች ተሰባስበው ሲያበቁ፣ በየቀኑ ካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኘው ‹ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን› በመሄድ፣ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በፀሎት መማፀን የህይወታቸው አካል አደረጉት፤ ከቀናት በኋላም በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ሁለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል ዕሳቤ ‹ማህበረ ሚካኤል› ብለው የሰየሙትን የፅዋ ማህበር መሠረቱ፡፡ …ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1977 ዓ.ም በ‹ፓዊ መተከል› ዞን የተደረገውን ‹የመልሶ ማቋቋም› ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ከተለያዩ የፅዋ ማህበራት ጋር በመዋሀድ የዛሬውን ‹ማህበረ-ቅዱሳን› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነብይነት ፀጋ አልነበራቸውም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነበር፡፡

ኃይማኖትን ጠቅልሎ የመያዝ ዕቅድ

በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሓት አመራር ገዳማትን ለመሸሸጊያነት ብቻ ሳይሆን ለእርካብ መወጣጫነትም ጭምር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ከድርጅቱ መስራቾች አንዱ የነበረው አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ‹‹A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopi›› በሚል ርዕስ ጽፎት፤ ኋላም ወደ መጽሐፍ በቀየረው የጥናት ጽሁፉ ላይ፣ ‹‹የቤተ-ክርስቲያኗን ሥልጣን (በትግራይ የነበረውን) ለማድቀቅ ሲባል በስብሀት ነጋ የሚመራ የስለላ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ይህ ቡድንም ደብረ-ዳሞን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ባሉ ገዳማት አባላቱን መነኮሳት በማስመሰል፣ የገዳማቱን እንቅስቃሴ በህወሓት ፍላጎት ስር የማስገዛት ስራ ሰርቷል›› ሲል በገፅ 317 ላይ ገልጿል፡፡ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ሐይማኖትን ጠቅልሎ ለመያዝ የተነሳበትን ገፊ-ምክንያትም እንዲህ በማለት አብራርቶታል፡-

‹‹ቤተ-ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግስት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊ ንቃት (ማንነት) ማስተማሪያም ነበረች፡፡ …ለህወሓት እንቅስቃሴ እንቅፋት እንደነበረች ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ-ክርስቲያኒቱን በህወሓት ዓላማ ስር ለማሳደር ፍላጎት ነበር፤ በዚህ የተነሳም የእርሷን ተፅእኖ ለማግለል ጥልቅ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡›› (ገፅ 315-316) ዶ/ር አረጋዊ ‹‹ጥልቅ እርምጃዎች›› ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አንደኛው ‹‹ለአጥቢያ ቀሳውስቱ ኮንፍረንስ በማዘጋጀት፣ በትግራይ ውስጥ ያሉትን ቤተ-ክርስቲያናት ለብቻ ነጥሎ ህወሓት በሚያራምደው የትግራይ ብሔርተኝነት ስር ማካተት›› እንደነበረ በዚሁ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ይሁንና አስገምጋሚ መብረቅ የወረደብን ያህል የምንደነግጠው፣ ዶ/ሩ ከዚሁ ጋ አያይዞ ‹‹የተጨቆነው የትግራይ ብሔርተኝነት የተነሳሳውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን ተፅእኖ ለመገዳደር ነው›› በማለት መመስከሩን ስናነብ ነው፡፡ የአረጋዊ መረጃ የሰሚ-ሰሚ ወይም በቢሆን ሃሳብ የተቀኘ አይደለም፤ ይልቁንም ራሱም በመሪነትና ሃሳብ በማዋጣት ከተሳተፈበት ከድርጅቱ የፖለቲካ ፕሮግራም የተቀዳ እንጂ፡፡

የሆነው ሆኖ ህወሓት ከ1970-72 ዓ.ም ድረስ ባሰለጠናቸው ካድሬ ‹‹ካህናት›› አማካኝነት ‹‹ነፃ በወጡ›› መሬቶች ላይ ራሱን የቻለ የቤተ-ክህነት አስተዳደር (ከሲኖዶሱ የተገነጠለ) መመስረቱ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ ለእነዚህ ቤተ-ክርስቲያናት መተዳደሪያ ደንብ ከመቅረፅ አልፎ ዓላማውንም እንደ አስርቱ ትዕዛዛት በፍፁም ልባቸው የተቀበሉ ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› አድርጓቸው እንደነበረ፣ አረጋዊ በርሄ ተንትኖ አስረድቷል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰርጎ ገብነት በእስልምናም ላይ መተግበሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች በሚበዙበት አካባቢዎች ወላጆቻቸው ሙስሊም የሆኑ ታጋዮችን እየመረጠ እና ከክርስቲያን ቤተሰብ የወጡ ካድሬዎችንም ሀሰተኛ የሙስሊም ስም እየሰጠ ‹የትግሉ ዓላማ እስልምናን ማስፋፋት› እንደሆነ በመግለፅ የፕሮፓጋንዳ ስራ ይሰራ ነበር፡፡ በዚህ ስልቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአንዳንድ ዓረብ ሀገራትን ቀልብ ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ ከዓረቦች በገፍ ዕርዳታ ያጎረፈለት ሲሆን፣ ወደ መሀል ሀገር የሚያደርገውን ጉዞም አፋጥኖለታል፡፡

ከመንግስት ለውጥ በኋላም ሁለቱን ሐይማኖቶች የተቆጣጠረው በታጋይ ‹‹ካህናት›› እና ‹‹ሼሆች›› ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ዛሬም በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት የበላይ በሆነው ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ውስጥ ከሚገኙት አስራ ስምንት መምሪያዎች፣ አስራ ስድስቱ በህወሓት ሰዎች የመያዛቸው ኩነት ስልቱ በተሳካ ሁኔታ መተግበሩን ያስረግጣል፡፡ በተለይ ዋነኛው ሰው አቡነ ማቲያስ ሲኖዶሱን ብቻ በሚመለከት ጉዳይ ላይ ጭምር ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ‹‹የመንግስት ባለሥልጣናትን ላማክር›› ሲሉ በተደጋጋሚ መደመጣቸው እና አንዳንድ ጳጳሳት ተቃውሞ በሰነዘሩባቸው ቁጥር በአፃፋው ‹‹መንግስት ያግዘኛል ብዬ ነው እዚህ መንበር ላይ የተቀመጥኩት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር›› በማለት በግላጭ ሲመልሱ መስተዋላቸው ለስርዓቱ ጣልቃ-ገብነት እንደማሳያ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም ለሶስት ወር የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ሆነው የሰሩ አንድ ጳጳስም ‹‹ሁልጊዜም ቋሚ ሲኖዶሱ ሲሰበሰብ እርሳቸው (ፓትርያርኩ) ‹መንግስት እንዲህ አለ›፣ ‹መንግስት ሳይፈቅድ›… የሚል ንግግር ይጠቀማሉ›› በማለት ለፋክት አስተያየት ሰጥተዋል (በነገራችን ላይ ፓትርያርኩ የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ እንቅልፍ የማብዛትና መሰል ችግሮች ስራቸውን እያስተጓጎሉባቸው እንደሆነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝ እተኛለሁ፤ ስተኛ ደግሞ እረሰዋለሁ›› በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል)

በእስልምና እምነት ውስጥም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ከቀድሞውም መጅሊስ የባሰ እንደሆነ በርካታ መዕምናን የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡ ይህ መጅሊስ የሚዘወረው እንደተለመደው በምክትል ፕሬዚዳንቶች ሲሆን፤ ይች አይነቷ ጨዋታ ደግሞ ህወሓት ጥርሱን የነቀለበት ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሼህ ከድር ለ17 ዓመታት የትግራይ ክልል መጅሊስና የሸሪአ ፍ/ቤቱን ደርበው በመያዝ መእምናኑን ቀጥቅጠው ሲገዙ ከመቆየታቸውም በላይ ታጋይ እንደነበሩ በኩራት ለመናገር የሚደፍሩ እንደሆነ የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ በአናቱም ከታማኝ የመረጃ ምንጭ ባይረጋገጥም የመጅሊሱ ፕሬዚዳንት ሼህ ኪያር መሀመድ ከእኚሁ ‹‹ታጋይ›› ምክትላቸው ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ባለመቻላቸው እና ‹‹መንግስት የሚያዘውን ሁሉ ለመስራት ለምን እንገደዳለን?›› የሚል ተቃውሞ እስከማሰማት በመድረሳቸው በቅርቡ ከኃላፊነታቸው ሊነሱ እንደሚችሉ ተወርቷል፡፡

ኢህአዴግ እና ‹‹መንፈሳዊ›› ገበያው


ግንባሩ የእምነት ተቋማትን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጠርንፎ መያዝን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የመንቀሳቀሱ መግፍኤን ከሶስት ጉዳዮች አንፃር በአዲስ መስመር ለመተንተን እሞክራለሁ፡-
የመጀመሪያው ቤተ-ክህነት በነገስታቶቹ ዘመን የነበራትን ፖለቲካዊ ተሰሚነት (ምንም እንኳን ራሱ ኢህአዴግም በአፋዊነት ከማውገዝ ቸል ባይልም) ለቅቡልነት መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎቱ ነው፡፡ በገቢር እንደታየውም በኃይል በተቆጣጠራቸውም ሆነ ካድሬዎቹ ሊደርሱባቸው በማይችሉ የገጠር ቀበሌዎች ተቀባይነት ለማግኘት ማህበራዊ አክብሮት ባላቸው ሼሆች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት… ሲቀሰቅስ ተደጋጋሚ ጊዜ ተስተውሏል፡፡ እንዲሁም የእስልምና እምነት በታሪክ ያሳለፈውን አገዛዛዊ ጭቆናንም ሆነ የደርጉን ሁሉንም ሐይማኖት ማግለልን በማጎን ለፕሮፓጋንዳ ተጠቅሞበታል (በወቅቱ የድርጅቱ አመራር አባል የነበረው አቶ ገብሩ አስራት፣ እንደ ሼሆች በመልበስና በመጠምጠም ከፍተኛ አስተዋፆ ማበርከቱን ብዙሀኑ ታጋዮች አይዘነጉትም) በዚህ ዘመንም በቤተ-እምነቶች ካድሬ-ጳጳሳትንና ካድሬ-n ሼሆችን አሰርጎ የማስገባቱ ምስጢር ይኸው ነው፡፡

በሁለተኛነት እንደምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው የታገለለትን ዘውግ ተኮር ፖለቲካ ያለአንዳች ተግዳሮት ማሳለጥን ታሳቢ ማድረጉ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ሐይማኖቶች ‹‹የሰው ልጅ በሙሉ የአንድ አምላክ ፍጡሮች ናቸው›› በሚል አስተምህሮ የሚመሩ ከመሆናቸው አኳያ፣ በዘውግ ከፋፍሎ ማስተዳደርን ቀላል አያደርገውምና ነው፡፡ ስለዚህም መፍትሔው አክራሪ ብሔርተኛ ‹‹መንፈሳውያን›› በየእምነት ተቋማቱ እንዲፈለፈሉ እና ከፍተኛውን የሥልጣን እርከን መቆጣጠር እንዲችሉ በማብቃት ላይ የተመሰረተ ብቻ መሆኑን የህወሓት መሪዎች ያውቃሉ፡፡ ይህ ‹‹እውቀታቸው››ም ይመስለኛል ሀገራዊ ስሜት የሌላቸው፣ በችሎታ ማነስ እና በስነ-ምግባር ጉድለት የሚታወቁ፤ እንዲሁም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቅቡል ያልሆኑ ሰዎች ቦታውን እንዲይዙ እስከማድረግ ያደረሳቸው፡፡

የራሳቸው የስለላ መዋቅርም በጥቅምት 2 ቀን 1995 ዓ.ም ‹‹ለዋናው መ/ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ከ-ል.ዮ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ጉዳይ ይመለከታል›› በሚል ርዕስ ለደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት በላከው ጥናታዊ ዘገባ ላይ እውነታውን እንዲህ ሲል ገልፆታል፡- ‹‹…ለፓትርያርኩ ወዳጅነት አላቸው የሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ከሦስትና አራት ብዙም ያልበለጡ ናቸው፡፡ ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ተቀባይነትና ከበሬታ ያጡ በመሆናቸው ህልውናቸውን የአንዳንድ መሪዎችን ስም በመጥራትና እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ላይ የተንጠላጠለ ሆኗል››፡፡ ከዚህ ሪፖርት በኋላም እንኳ ለማስተካከል አለመሞከሩ መከራከሪያውን አምነን እንድንቀበል ያስገድደናል፡፡

አገዛዙ መንፈሳዊ ተቋማትን ጠቅልሎ ለመያዝ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሶስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት፣ ምንም እንኳ ‹‹ተሳክቷል›› ሊባል ባይቻልም፤ በስነ-ምግባር መታነፅ፣ በሀገር አንድነት ማመን፣ ለሕዝብ ጥቅም መቆም፣ የትኛውንም ህገ-ወጥነት ‹ለምን› ብሎ መጠየቅና መሰል መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን መርሁ አድርጎ የሚነሳ ትውልድ እንዳይፈጠር መከላከልን ታሳቢ በማድረግ እየሰራ ያለውን ሴራ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ ሰዎች በዚህ መልኩ የሚቀረፅ ትውልድን ዛሬ ባነበሩት አይነት የጭቆና ቀንበር ለተራዘሙ ዓመታት መግዛት ከባድ እንደሆነ ለመረዳት አይሳናቸውምና ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አንስተን ማለፍ ያለብን ጭብጥ፤ መቃብር ከሚቆፈርለት የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጋር የሚያያዝ ነው፤ የሐይማኖቱና የማዕከላዊ መንግስቱ የቅድመ-አብዮቱ ጋብቻ (በምንም አይነት መከራከሪያ ትክክለኛነቱን ልንሟገትለት ባንችልም)፣ ቤተ-ክርስቲያኗ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱ የታሪክ ብያኔ ከፍተኛ አስተዋፆ ማድረጓን አያስክደንም፡፡ ይህም ‹የሐይማኖቱን ተቋም የብሔርተኝነቱ ወካይ ሆኖ እንዲታሰብ ይገፋዋል› ብሎ ለሚያምነው ህወሓት፣ ሐይማኖቱ ተቋማዊ ነፃነት እንዳይኖረው የሚቻለውን ሁሉ ሲያደርግ፤ ሐይማኖቱን በማዳከም የብሔርተኝነት መንፈሱንም ማላላት ይቻላል ከሚል መነሾ ነው ብሎ መደምደም ተምኔታዊ አያስብልም፡፡

ገደል አፋፍ የቆመው ማሕበረ ቅዱሳን…


ስርዓቱ የሐይማኖት ተቋማትንና መንፈሳዊ መሪዎቹን ለመቆጣጠር ገፊ-ምክንያቶች ሆነውታል ብዬ ከላይ ለማብራራት የሞከርኳቸውን ሶስት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ መተግበርን አስቸጋሪ ያደረገበት፣ ቀጥታ በምዕምናኑ የተመሰረቱ ማሕበራት መሆናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ለማስረጃም ያህል ከኦርቶዶክስ ክርስትና-ማሕበረ ቅዱሳን፤ ከእስልምና ያለፉትን ሁለት ዓመታት የእምነቱ ተከታዮች ወካይ ሆኖ የተመረጠው ኮሚቴ አባላት መንግስትንም ሆነ መጅሊሱን በመገዳደር ያደረጉትን አበርክቶ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁንና የሙስሊሙን ተወካዮች በገፍ ሰብስቦ እስር ቤት ካጎረ በኋላ፣ ከሲኖዶሱም ሆነ መሰል ማሕበራት ጠንካራ እንደሆነ የሚነገርለትን ማሕበረ ቅዱሳንን ዋነኛ ኢላማው አድርጎ ለመደፍጠጥ የቆረጠ ይመስላል፡፡ የማሕበሩ አባላት በዓለማዊ እውቀት የተራቀቁ፣ በሀገር አንድነት በፍፁም የማይደራደሩ፣ በጥቅመኝነት የማይደለሉ… የመሆናቸው ጉዳይ አገዛዙ ከኃይል አማራጭ የቀለለ መፍትሔ የለም ብሎ እንዲያምን አድርጎታል ብዬ እገምታለሁ፡፡

በርግጥ በአቶ መለስ ዜናዊ ይዘጋጅ እንደነበረ ከህልፈቱ በኋላ በተነገረለት የኢህአዴግ የንድፈ ሃሳብ መጽሔት ‹‹አዲስ ራዕይ›› ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አብዛኛውን ጊዜ ‹‹የከሰሩ ፖለቲከኞች ‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት፣ አንድ ሐይማኖት አንድ ሀገር› እና ‹ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ቀደም ሲል ሲደርስበት የነበረውን በደል በማራገብና በመቀስቀስ፤ ከዚህም አልፎ ተገቢነት የሌላቸው አዳዲስ ጥያቄዎችን በማቅረብ ለማነሳሳትና ለማተረማመስ ሲሰሩ ማየት የተለመደ ሆኗል›› በማለት ከሚያቀርበው የሾላ-በድፍን ፍረጃ ዘልሎ ብዙም መንፈሳዊ ማሕበራትን በስም ጠቅሶ ሲያወግዝ አይሰማም ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ማንኛውንም ሐይማኖታዊ የመብት ጥያቄን ‹‹ወሃቢያም ይሁን ማሕበረ ቅዱሳን…›› በማለት ማውገዙ የተለመደ ሆኗል፡፡ ከውግዘትም ተሻግሮ ጥያቄያቸውን በሕጋዊ መንገድ ወደ አደባባይ ያወጡትን የሙስሊሙን ተወካዮች ሰብስቦ አስሯል፤ በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ሰላማዊ ተቃውሞዎችንም በማስታከክ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ግድያና ስቀየትን ጨምሮ ብዙ ግፍ በመፈፀም ጉዳዩን በጠብ-መንጃ ብቻ የሚፈታ አድርጎ ካወሳሰበው ሰነባብቷል፡፡

‹‹ቀጣዩ የኢህአዴግ ኢላማ ማሕበረ ቅዱሳን ይሆን?›› በሚል ርዕስ ከስድስት ወር በፊት በዚሁ መጽሔት ላይ ለማተት እንደሞከርኩት ሁሉ፤ ከላይ በተዘረዘሩ የፖለቲካ አጀንዳዎች እና በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ በለመደው የማጭበርበር መንገድ አሸንፎ ያለኮሽታ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም ዓለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ነፃ ተቋማት እንዳይኖሩ በይፋ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ድርጊቶችን እየፈፀመ ያለው የእነ አባይ-በረከት መንግስት፣ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ትኩረቱን ማሕበረ ቅዱሳን ላይ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ይህንን አፈና ለማሳካትም ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በፍፁም ልባቸው ከመተባበር ለአፍታም እንደማያመነቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡
ለምሳሌ ያህልም አንዱን በአዲስ መስመር ላቅርብ፡-

ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት አስተዳደርን ወደ ዘመናዊነት ለማሻገር ሲኖዶሱ ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ እናም ጥናቱ ተጠናቆ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ብርቱ ተቃውሞ ስለገጠመው፣ በሀገረ-ስብከቱ ሥራ-አስኪያጅ አቡነ እስጢፋኖስ አማካኝነት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት አዳራሽ ከሁሉም አድባራትና ገዳማት የተወጣጡ 2700 ሰዎች የሚሳተፉበትና አስራ አራት ቀን የሚፈጅ የውይይት ፕሮግራም ይዘጋጃል፡፡ ይሁንና ውይይቱ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ጠዋት ፓትርያርኩ፣ ከአቡነ እስጢፋኖስ ጋር በስልክ ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው መወዛገባቸውን ሰምቻለሁ፡-

‹‹ጥናቱን የሚሰሩት ባለሙያዎች ናቸው ብለውኝ አልነበረም ወይ?››
‹‹አዎ! ታዲያስ ባለሙያዎች ናቸው የሰሩት፡፡››
‹‹አይደለም! የማሕበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፤ እርስዎ አታለውኛል!››
‹‹የጥናት ኮሚቴው አባላት በቤተ-ክርስቲያን ልጅነታቸውና በየአጥቢያው ባላቸው ተሳትፎ ተጠርተው የመጡ ሙያቸውን ‹አስራት› ያደረጉ ናቸው፡፡››
‹‹በፍፁም! ጥናቱ የማሕበረ ቅዱሳን ነው!››
‹‹ቅዱስ አባታችን ቢሆንስ? ከጠቀመን ችግሩ ምንድን ነው?››
‹‹በቃ! ውይይቱ ከመንግስት ይቋረጥ ተብሏል፡፡››
‹‹ለምን ይቋረጣል?››
‹‹የጥናቱ ተቃዋሚዎች ረብሻ ያስነሳሉና የፀጥታ ስጋት አለ፡፡››
‹‹ለምንድን ነው ረብሻ የሚያስነሱት? ከፈለጉ መጥተው መሳተፍ ይችላሉ፤ እኛ እየተወያየን አይደለም እንዴ! ተቃውሞ ያለው መጥቶ ሃሳቡን ይግለፅ እንጂ ማቋረጥ እንዴት መፍትሄ ይሆናል? ደግሞስ ሲኖዶሱ አይደለም ወይ ‹ሰነዱ ወደታች ወርዶ ይተችበት› ብሎ የወሰነው?››
‹‹የለም! ይቁም ተብሏል፤ ይቁም!››
‹‹እንግዲያውስ የከለከለው አካል ራሱ መጥቶ ይንገረን፡፡››

…የስልክ ምልልሱ ከተጠናቀቀ ከሰዓታት በኋላ አንድ ባለሥልጣን አቡነ እስጢፋኖስ ቢሮ ድረስ መጥቶ ትእዛዙን ያስተላለፈው እርሱ እንደሆነ ገልፆ ውይይቱ እንዲቋረጥ አሳሰባቸው፤ እርሳቸውም ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግን እናንተ ‹የፀጥታ ስጋት አለ› ብላችሁ በደብዳቤ ኃላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛም ለካህናቱም ሆነ ለመዕምናኑ ሁኔታውን ዘርዝረን እንገልፃለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ይሸኙታል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ለጊዜው ግልፅ ባልሆነ አንድ ምክንያት መንግስት ‹‹ይቋረጥ›› የሚለውን ማስፈራሪያ ሊያነሳ የቻለው፡፡ ኩነቱ ግን ፓትርያርኩ ማሕበሩን በጥርጣሬ ማየታቸውንና አገዛዙ ለሚወስድበት ማንኛውም አይነት እርምጃ ተባባሪ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

ሌላው መንግስትና ፓትርያርኩ፣ ማሕበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ በሰምና ወርቅነት እየሰሩ መሆናቸውን የሚያመላክተው የዛሬ ሳምንት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት የማሕበሩ ተቃዋሚዎች ያደረጉትን ውይይትና የአቋም መግለጫ ስናስተውል ነው፡፡ ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉ ክፍል እንደሚያስረዳው፣ ተሰብሳቢዎቹ ማሕበሩን በተመለከተ ባወጡት የአቋም መግለጫ የሚከተሉትን ነጥቦች ዘርዝረዋል፡- ‹‹የዋነኛ አመራሮቹ የባንክ አካውንት ይመርመር፣ የማሕበሩ ሒሳብ መንግስት በሚመድበው የውጪ ኦዲተር ይመርመር፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹ (ከቀረጥ ነፃ ያስገባቸው ቀላልና ከባድ መኪናዎቹ ሳይቀሩ) ወደ ቤተ-ክህነት ይግቡ፣ የንግድ ተቋማቱ (ትምህርት ቤት፣ ሬስቶራንቶቹን፣ ንዋየ ቅድሳት ማምረቻና ማከፋፈያውን) ያስረክብ፣ ከምዕምናን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው አስራት እየፈረጠመበት ስለሆነ እንዳይቀበል ይከልከል፣ የግቢ ጉባኤ (በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርፀው እንዳይወሰዱ መስራት፣ ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ-አስኪያጁ ተነስቶ፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ስር አንዱ ንዑስ ክፍል ይሁን…›› የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ከዚህ ሴራ ጀርባ ፓትርያርኩና መንግስት በትብብር መቆማቸውን የሚያሳየው በተቀረፀው ድምፅ ላይ፣ የውይይቱ መሪ አዳራሹን መጠቀም የቻሉት በአቡኑ መልካም ፍቃድ እንደሆነና እርሳቸው በዛሬው ውይይት ያልተገኙት የሕዳሴው ግድብ ምክር ቤት አባል በመሆናቸው ግዮን ሆቴል ስብሰባ ስላለባቸው መሆኑን ከመግለፅም በዘለለ፤ ‹‹ቅዱስ አባታችን በዚህ የተቃውሞ ምክንያት ከሥራ የሚባረር የለም አይዟችሁ አትፍሩ ብለውናል›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከዚህ ግቢ አቅም ኖሮት የሚያስወጣን የለም፤ ካስወጡን ግን መንግስታችን ስለሚተባበረን (ቸር ስለሆነ) ከእርሱ ሌላ መሬት ተቀብለን የራሳችንን ቤተ-ክርስቲያን እናቋቁማለን›› እና ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት አገልጋዮች የሚል ማሕበር እንመሰርታለን›› እስከማለት መድረሳቸው ከአገዛዙ ጋር ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ያመላክታል፡፡ በነገራችን ላይ በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተጠሩት ከመቶ ስልሳ ዘጠኙ አድባራትና ገዳማት፣ እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞቻቸው መካከል የተገኙት የስምንት አድባራት አስተዳዳሪዎችና 150 ሠራተኞች ብቻ እንደነበሩ ከመረጃ ምንጮቼ አረጋግጫለሁ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ምኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም አዝማችነት ማሕበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በተከታታይ በ‹‹ጥናት›› ስም የሚወጡ ወረቀቶች ማሕበሩን ከአክራሪነትም አሻግረው ‹‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ›› ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡ በጥቅሉ የእነዚህ ‹‹ጥናት›› ተብዬዎች መደምደሚያ ‹‹ማሕበሩ የትምክተኞች ምሽግ ነው፣ አክራሪነት አለበት፣ አመራሩና የሕትመት ውጤቶቹ የፖለቲካ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፣ በቤተ-ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ ይገባል፣ ሕዝቡ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ይሰራል፣ በውጭ ፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ይዘወራል›› የሚሉ ናቸው፡፡ የማሕበሩ የአመራር አባላት እንዲህ አይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከአቶ በረከት ስምኦን እስከ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም፤ ከአዲስ አበባ የፀጥታ ኃላፊዎች እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ ፀጋዬ በርሄ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሮአቸው ተገኝተው ውንጀላው ማስረጃ የማይቀርበበት የሀሰት እንደሆነ ቢያስረዱም መፍትሄ እንዳላገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በግልባጩ በመንግስት ተቋማት ያሉ የፋክት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወር ከሚካሄደው የሲኖዶሱ መደበኛ ጉባኤ በፊት፣ ከሃያ የሚበልጡ የማህበሩ አመራርን ከሽብርተኝነት ጋር በማያያዝ ለመክሰስ እና ማሕበሩንም እንደተለመደው በዶክመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት በአቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የሚመራው የሐይማኖቶች ምክር ቤት ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ ዶ/ር ሽፈራው አቡኑን ቃል-በቃል የጠየቃቸው ጥያቄም ይህንን መረጃ የሚያጠናክር ነው፡-

‹‹በማሕበረ ቅዱሳን አመራር ውስጥ ከሃያ በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አሉ››
‹‹ለዚህ ምንድን ነው ማስረጃህ? አቅርበውና እስቲ እንየው?››
‹‹ሀገር ውስጥ ካሉ ፅንፈኛ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በስደት የሚገኙና በሽብር ተግባር የተሰማሩ ጋዜጠኞች በአመራርነት አሉበት (የሁለት ሰዎችን ስም ጠቅሷል)››
‹‹እኛ እስከምናውቀው ማሕበሩ ከእንዲህ አይነት ተግባር የራቀ ነው፤ እናንተ ማስረጃ አለን ካላችሁ ደግሞ አቅርቡልንና እንየው፤ ከዚህ ውጪ ይህንን አይነት ክስ አንቀበልም፡፡››

በአናቱም ከወራት በፊት የስርዓቱ የንድፈ ሃሳብ መጽሔት የማሕበሩን ስም ሳይጠቅስ በደፈናው የወነጀለበትን እና ‹‹ለምን?›› ብለው የሚጠይቁ ጳጳሳትን በሚከተለው አገላለፅ ማሸማቀቁን ስናስታውስ የማሕበሩ ዕጣ-ፈንታ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ መቆሙን ያስረግጥልናል፡፡

‹‹በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ትርምስና ብጥብጥ ለመፍጠር፤ በኦርቶዶክሶችና ሌሎች ሐይማኖቶች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩት የደርግና የተለያዩ ትምክህተኛ ኃይሎች ቅሪቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የትምክህት ኃይሎችና አንዳንድ የእምነቱ አባቶች በጋራ ሐይማኖትን በፖለቲካ ዓላማ ዙሪያ መጠቀሚያ አድርገው እየሰሩ ለመሆናቸው ከ97 ምርጫ በኋላ እንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳት ቅንጅት በጠራው ሰልፍ ላይ የሐይማኖት አባትነት ካባቸውን እንደለበሱ ከመሰለፍ አልፈው አስተባባሪ ሆነው መታየታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡›› (አዲስ ራዕይ ሐምሌ-ነሐሴ 2005)

የሆነው ሆኖ ከፍረጃውና ከእስራቱ በተጨማሪ ማሕበሩን ለማዳከም በዋናነት በአገዛዙ የተነደፉት እቅዶች ማሕበሩ መሰረቱን የጣለበት የግቢ ጉባኤን ከመከልከልና ንብረቶቹን ከመውረስ ጋር የሚያያዙ ናቸው (ከላይ የተጠቀሰው የአቋም መግለጫም ለማሕበሩ የደም-ስር የሆኑትን እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ትኩረት እንደሰጣቸው ልብ ይሏል)

ስቅለትን-ለተቃውሞ


ኢህአዴግ ወደ ስልጣነ-መንበሩ ከመጣ ሦስተኛ ዓመት ላይ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግቦችና ቀጣይ እርምጃዎች›› በሚል ርዕስ ለካድሬዎቹ በበተነው ድርሳን (በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ የተዘጋጀ ነው ተብሎ ይገመታል)፤ ይህን አሁን የተነጋገርንበትን ሐይማኖታዊ ተቋማትን በሚያቅዳቸው የስልጣን ማራዘሚያ አማራጮች ስለመጠቀም ካወሳ በኋላ ተቋማቱን ለስርዓቱ ፖሊሲዎች እንዲታመኑ ማድረጉ ዋነኛ እንደሆነ ያሰምርበታል፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ፣ እስከ ከፍተኞቹ መንፈሳዊያን መምህራን ድረስ ዘልቆ በመግባት ሐይማኖቶቹን መምራት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብ መሆን እንዳለበት ያው ሰነድ በግልፅ ቋንቋ ይናገራል፡፡ እንግዲህ ከመጅሊሱ እስከ ማሕበረ ቅዱሳን ያየነው መንግስታዊ አፈና የዚህን ሃያ ዓመት የሞላው የተፃፈ ሀሳብ መተግበርን ነው፡፡

ግና፣ ከዚህ ቀደም በተፃፈ ነውረኛ ሀሳብ ትግበራ ፊት ከሁለት አስርት በላይ ህልውናውን ለማቆየት የተጋው ማሕበረ ቅዱሳን፣ ከላይ በሚገባ በጠቀስኳቸው አሳማኝ መረጃዎች እና ተጨባጭ ሁነቶች በተከታታይ መከሰት መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ተመልክተናል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ፤ መነሳት የሚኖርበት መሰረታዊ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማሕበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲሆን፤ ምላሾቹም ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የማሕበሩ አመራሮችና አባላት እስከዚህች ቀን እያደረጉ ያለው የውስጥ ለውስጥ የእርምት እንቅስቃሴን ይመለከታል፡፡ በሐይማኖቱ ተቋማት በኩል ለዓመታት ሲሞከር የቆየው ይኸኛው አማራጭ፣ እንደ አስተዋልነው ማሕበሩን ሞት አፋፍ ላይ ከመድረስ ሊታደገው አልቻለም፡፡ ስለዚህም፣ ወደ ሁለተኛውና ዋነኛ የመፍትሔ አማራጭ መሻገር ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ስፅፍ ለማስረዳት እንደሞከርኩት፤ የማሕበሩ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት፤ ማሕበራቸውን ብቻ ሳይሆን ህልውናቸውንና ህያውነታቸውን የመሰረቱበትን ሐይማኖት ለማውደም የሚተጋውን ስርዓት በሰላማዊ አመፅ መናድ ብቸኛው የዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መሻገሪያ መንገድ ነው፡፡ በዋናነት የተማሩ ከተሜ ወጣቶችን፣ በአለማዊም ሆነ በትምህርተ-ሐይማኖቱ የማይታሙ ዜጎችን የያዘው ይህ ማሕበር፤ ከህዝበ ሙስሊሙ ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› የአደባባይ ተቃውሞ ስኬቶችና ሂደቶች በመማር፤ ፊቱ በተገተረው ኢህአዴግ ላይ በሕጋዊና ሰላማዊ እምቢተኝነት ከማመጽ የተሻለ አማራጭ እንደማይኖረው የሚረዳ ይመስለኛል፡፡

‹‹ችግሮች ሁሉ የየራሳቸው በጎ ገፆች አሏቸው›› እንዲሉ፤ ማሕበሩ የደረሰበት ይህ ፈታኝ ጊዜን ተከትለው የሚመጡ ሁለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚካሄደው የስቅለት በዓል ነው፡፡ የሐይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተ-ክርስቲያናቱ የሚውሉበት ይህ በዓል፣ አገዛዙ እጁን ከማህበሩ ላይ እንዲያነሳ ለመጠየቅ የተመቸ ቀን ስለመሆኑ ማስታወስ አባላቱን አሳንሶ መገመት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሁለተኛውና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩ የ2007 ምርጫን ነው፡፡ ለየትኞቹም የህገ-መንግስቱ ሀሳቦች አልያም የሞራል ዕሴቶች የማይገዛው ኢህአዴግ፣ በሐይማኖቱ ላይም ሆነ በማሕበሩ ላይ የዘረጋውን የረከሰ እጅ እንዲያነሳ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሕዝባዊ አመፅ መሆኑ ላይ እስከተማመንን ድረስ፣ ከዓመታዊ የንግስ በዓላት ጀምሮ ያሉ መድረኮችን በዕቅድ ለመጠቀም የዝግጅቱ ጊዜ ዛሬ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴም፣ ካነሳነው ርዕሰ-ጉዳይ አኳያ የማሕበሩን መኖር የሚሹ ሁሉ ቀጣዩን የምርጫ ወቅት ለማስገደጃነት የመጠቀም ተሞክሮዎቻቸውን ተፈላጊው ብቃት ላይ እንደሚያደርሰው አምናለሁ፡፡ ጥቂት ሊባሉ የማይችሉ አባላቱ፣ የምርጫውን ተጨባጭ ዕድል መንግስታዊ ተቋማት በማሽመድመድ ጭምር እንዴት ስርዓቱን ወደመቃብሩ ማሻገር እንደሚያውቁ ስንገነዘብ፤ ቀሪው ጉዳይ ‹‹ሐይማኖታችሁን ተከላከሉ›› ብለው ላስተማሩት ቅዱሳን መጻሕፍትና ለሰማያዊው መንግስት የመታመን ብቻ እንደሚሆን እንረዳለን፡፡

torsdag 27. mars 2014

ዓባይና የአሜሪካ ጨዋታ (ፕ/መስፍን ወልደ ማርያም)

አሥራ ዘጠነኛው ምዕተ-ዓመት አስተሳሰብ ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሰው ዓላማ ለአውሮፓ ቄሣራውያን ዋና ግባቸው ሆኖ እስከሃያኛው ምዕተ-ዓመት ዘልቆአል፤ አሀን ፈጽሞ በተለየ ዘመን አሜሪካ ይህንን አስተሳሰብ ይዞ የተነሣ ይመስላል።
ኢትዮጵያን የተቆጣጠረ ዓባይን ይቆጣጠራል፤ ዓባይን የተቆጣጠረ ግብጽን ይቆጣጠራል፤ ግብጽን የተቆጣጠረ ኃይልቀይ ባሕርን ከመግቢያና መውጫው 
ጋር ይቆጣጠራል፤ቀይ ባሕርን ከመግቢያና መውጫው ጋር የተቆጣጠረ ኃይልዓለምን ይቆጣጠራል።
አሜሪካ በግብጽ ላይ የተከለው ጥፍሩ ሲነቃነቅ መነቀሉ አለመቅረቱን ስላወቀው ሌላ የሚተክልበት አገር ይፈልጋል፤ በአካባቢው የግብጽን ነፍስ የሚነካ ከኢትዮጵያ የተሻለ አገር የለም፤ ለአሜሪካ ዓለም-አቀፍ ዓላማ ኢትዮጵያ ስትመረጥ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም፤ በመሀከለኛው ምሥራቅ የአረቦችን የተባበረ ኃይል ለመቋቋም የተመረጡ ሦስት አረብ ያልሆኑ አገሮች — ቱርክ፣ ኢትዮጵያና ፋርስ (ኢራን) — ነበሩ፤ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካ ዓለም-አቀፍ ኃይል መሰማት በጀመረበት ጊዜ ኢትዮጵያን ከከበቡአት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ጋር የነበርዋትን የቆዩ ውዝግቦች ለመቋቋም የአሜሪካ ድጋፍ በጣም አስፈላጊ ነበር፤ አሜሪካን ከአውሮፓ አገሮች ጋር እየመዘኑና እያመዛዘኑ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የተደረገው ዲፕሎማሲ (ዓለም-አቀፍ የሰላም ትግል) የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት በእውነት ከሚያኮሩት ተግባሮች አንዱ ነው፤ ይህንን ትግል አምባሳደር ዘውዴ ረታ ምስጋና ይድረሰውና የኤርትራ ጉዳይ በሚለው መጽሐፉ ግሩም አድርጎ አሳይቶናል።
ምናልባት ገና ያልተጠና ጉዳይ በዘመኑ ኢትዮጵያ የነበራት ታሪካዊ ክብር ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታሪክና ዝና ጋር ተዳምሮ በአፍሪካ ተደማጭነት ነበራት፤ ይህንን ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገሮች ላይ የነበራትን ጫና (የዛሬውን አያርገውና) በመጠቀም አሜሪካ አፍሪካን በሙሉ ለዓላማዋ ለማሰለፍ ኢትዮጵያን መሣሪያዋ ለማድረግ ትሞክር ነበር።
እየቆየ የኢትዮጵያ መንግሥት የነጻነት መንፈስን በማሳየት ለአሽከርነት አልመች በማለቱና ለአሜሪካም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች (የእውቀት ጥበቦች) በመፈጠራቸው ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ዓለም-አቀፍ ዓላማ አስፈላጊነትዋ በመቀነሱ አሜሪካ ኢትዮጵያን ችላ ማለት ጀመረ፤ የ1966 ግርግር ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን ጠለቅ ብሎ ማጥናት ያስፈልጋል፤ በዚህ መሀልም የሶቭየት ኅብረት ዓለም-አቀፋዊ ጉልበት እየተሰማ በመሄዱ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ዓላማ ቀስ በቀስ እየለወጠ ሄደ፤ ከዚህም ጋር የሶቭየት ኅብረት ተጽእኖ እያደገ ሄደ፤ የአሜሪካ አያያዝ እየላላ ሲሄድ የሶቭየት ኅብረት አያያዝ እየጠበቀ ሄደ፤ 1966 የአሜሪካ መውጫና የሶቭየት መግቢያ ሆነ ለማለት ይቻል ይሆናል፤ ከዚሁ ጋር አብሮ የሚታየው በኢትዮጵያ የባህላዊው ሥርዓት መሰነጣጠቅና የቆየው ትውልድ መዳከም ነው፤ የአሜሪካ መዳከም ሶቭየት ኅብረትን ሲያጠነክር፣ የአሮጌው ትውልድ መዳከም አዲሱን ትውልድ አጠነከረ፤ ይህ ማለት አሮጌው ትውልድ ከአሜሪካ ጋር የተያያዘውን ያህል አዲሱ ትውልድ ከሶቭየት ኅብረት ጋር ተያያዘ፤ የኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታ ብቻውን ለውጥ እንዳላመጣና ዓለም-አቀፍ ሁኔታዎችና የልዕለ ኃያላኑ ተጽእኖም ምን ያህል እንደነበረ አመላካች ነው።
የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት መውደቅና የአሜሪካ ተጽእኖ መዳከም በአንድ በኩል፣ የደርግ መፈጠርና የእነኢሕአፓና መኢሶን በአጋፋሪነት መውጣት ከሶቭየት ኅብረት ተጽእኖ መጠናከር ጋር በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ሁኔታን ፈጠሩ፤ የአዲሱን ሁኔታ አዲስነት በግልጽና በትክክል መገንዘብ ያስፈልጋል፤ በኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ተከብሮና ታፍሮ የቆየው የዘውድ ሥርዓት ተናደ፤ ተዋረደ፤ በኢትዮጵያ ስር እየሰደዱ የነበሩ መሳፍንትና መኳንንት ከስራቸው ተመነገሉ፤ አዲስ የመሬት አዋጅ ወጣና የመሬት ከበርቴዎችን ሙልጭ አውጥቶ ገበሬውን በሙሉ እኩል ባለመሬት አደረገው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻ ወጣ ባይባልም የኢትዮጵያ መሬት ነጻ ወጣ፤ ወታደር፣ ገዢ ሰላማዊው ሕዝብ ተገዢ ሆነ፤ ትርፍ መሬትና ትርፍ ቤት ሁሉ ተወረሰ፤ ቤትን የሚያከራዩ የኪራይ ቤቶችና ቀበሌዎች ብቻ ሆኑ፤ ደሀዎችንና መሀከለኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ኑሮ ለማቃለል ከሦስት መቶ ብር በታች የነበረው የቤት ኪራይ ሁሉ ተቀነሰ፤ ደርግ በሁለት ዓመታት ውስጥ የአብዛኛውን ገበሬ ኑሮና የአብዛኛውን የከተማ ነዋሪ ኑሮ የሚነኩ መሠረታዊ ለውጦችን አወጀ፤ እያደር ደርግ አስከፊ እየሆነና እየተጠላ ቢሄድም እነዚህ ሁለት አዋጆች ብዙ ኢትዮጵያውያንን እስከዛሬ ድረስ ለደርግ ባለውለታ አድርገዋል፤ እነዚህ አዋጆች ወያኔ ገና አፍርሶ ያልጨረሳቸው የደርግ ሐውልቶች ናቸው።
በውጭ አመራር ደግሞ የአሜሪካ ተጽእኖ ክፉኛ ተበጠሰ፤ አሜሪካ ማለት ስድብና ውርደት ሆነ፤ አሜሪካ ማለት በዝባዥነትና የቄሣራዊ ተልእኮ አራማጅ ማለት ሆነ፤ የአሜሪካ ማስታወቂያ ቢሮ ተዘጋ፤ ብዙ የአሜሪካ እንደወባ መከላከያ ያሉ የተራድኦ ድርጅቶች ተዘጉ፤ አሜሪካ ለዩኒቨርሲቲዎች ሲያደርግ የነበረውን እርዳታ አቋረጠ፤ በዚህ በተለይም የዓለማያ ዩኒቨርሲቲ በጣም ተጎዳ፤ የወባ ቢምቢም ከ‹‹ኢምፒሪያሊዝም›› ጭቆና ነጻ ወጣችና  አዲስ አበባ ደረሰች! ይባስ ብሎም አለማያ ዩኒቨርሲቲ ያፈራቸው አሉ የተባሉት በተለያዩ የእርሻ ሙያዎች የተካኑት አብዛኞች ሙልጭ ብለው ከአገር ወጡ።
አሜሪካ ከደርግ ጋር እየተጋገዘ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ክፉኛ አዳከመው፤ አያይዞም በኢትዮጵያ ዳር ዳር የሚነደውን እሳት አቀጣጠለው፤ በአንድ በኩል የውስጥ ተገንጣይ ቡድኖችን — የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት፣ የኤርትራ ነጻ አውጪ ድርጅት፤ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ድርጅት — በሌላ በኩል በድንበርም ሆነ በሌላ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር የሚፋለሙትን አገሮች ሶማልያንና ሱዳንን በግልጽ መርዳት ጀመረ፤ እንዲያውም ከግብጹ ፕሬዚደንት ሳዳት ጋር እየተመካከረ ኢትዮጵያን ለማዳከም ሞከረ፤ ከመሞከርም አልፎ ኤርትራን አስገነጠለ፤ የኢትዮጵያን ዙፋን ለወያኔ አመቻቸ፤ አሜሪካ ኮሚዩኒስት ነኝ የሚለውን ወያኔን በጎሣ ፖሊቲካ አስታጥቆ ቀለቡን እየሰፈረ በኢትዮጵያ ላይ ሠራው፤ ደርግ በሰይፍ ብቻ አንድነትን ለማምጣት መሞከሩና ሕዝቡን ለጦርነት ማነሣሣቱ አሜሪካንን አስደንግጦታል፤ ለአሜሪካ ደርግ የቀሰቀሰው የአንድነት ብሔራዊ ስሜት የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ የሚፈስስ መስሎ ታየው፤ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያን የአንድነት ብሔራዊ ስሜት የማፈራረስ እቅዱን አወጣ፤ የሚያሳካለትንም ቡድን አገኘ።

ጣህሪር አደባባይና ዓባይ
ስንት ሰዎች በካይሮ ያለው አደባባይ ከዓባይ ጋር ግንኙነት አለው ብለው ያምናሉ? እስቲ ጠጋ ብለን እንመርምረው፤ ጣህሪር አደባባይ የግብጽ ሕዝብ የነጻነት ጥሪ ነበር፤ በአሜሪካ አጋዥነት ተጭኖት የነበረውን አገዛዝ ለማውረድ ቆርጦ መነሣቱን የገለጸበት አደባባይ ነው፤ የጣህሪር አደባባይን ማእከል ባደረገ ቆራጥ ትግል አገዛዙን አንኮታኩቶ አወረደው፤ በሰላማዊና ሕጋዊ ምርጫ የግብጽ ሕዝብ አዲስ መንግሥትን መሠረተ፤  የእስልምና ወንድማማቾች የሚባለው ቡድን አሸናፊ ሆኖ መውጣቱን አሜሪካም ሆነ እሥራኤል በጸጋ የተቀበሉት አይመስልም፤ ስጋት አላቸው፤ ለግብጻውያን ከአገዛዙ ጋር የሚወርድ ሌላ ጭነት አለባቸው፤ አሜሪካ ለራስዋም ዓላማ ሆነ ለእሥራኤል ዓላማ በግብጽ ላይ የምታደርገውን ከባድ ጫና ማንሣት ከትግሉ ዓላማዎች አንዱ ነበር፤ አሜሪካንና እሥራኤልን ያሰጋው የለውጡ ዓላማ አገዛዙን መጣሉ ሳይሆን በእነሱ ጥቅም ላይ ያነጣጠረውን ክፍል ነበር፤ በጦር መሣሪያ በኩል ግብጽ የአሜሪካ ጥገኛ ነች፤ ቀደም ሲል የሶቭየት ኅብረት ጥገኛ ነበረች፤ በአሁን በአለው የጊዜው ትርምስ አሜሪካ ግብጽ አንዳታመልጠው ይፈልጋል፤ ስለዚህም ስጋት አለው።
ግብጽን ሰንጎ ለመያዝና ለማስጨነቅ ከዓባይ የበለጠ ኃይል የለም፤ ዓባይን ሰንጎ  ግብጽን ለማስጨነቅ ከኢትዮጵያ  የበለጠ  ምቹ  አገር  የለም፤ በተጨማሪም ኡጋንዳን፣  ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን ከአሰለፈ ለአሜሪካ ሁኔታው ይበልጥ ይመቻቻል፤ ጫናው በግብጽ ላይ የጠነከረ ሊመስል ይችላል፤ አሜሪካ የግብጽን ወዳጅነት ለዘለቄታው ለማጣት ይፈልጋል? ለእኔ አይመስለኝም፤ አሜሪካ የአረቦችን ሁሉ ጠላትነት ይፈልጋል? ለእኔ አይመስለኝም፤ ታዲያ እስከምን ድረስ ነው አሜሪካ ግብጽን ለማስጨነቅ የሚፈልገው? ዋናው ጥያቄ ይህ ነው
ትልቁ የአስዋን ግድብ ሲሠራ የነበረውን ውዝግብና መካካድ ለማንሣት ይዳዳኛል፤ ግን ሰፊ በመሆኑ አልገባበትም፤ አንዳንድ ሁነቶችን ብቻ ልጥቀስ፡– የምዕራብ ኃይሎች በተለይም አሜሪካና ብሪታንያ ለግድቡ ሥራ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ሀሳባቸውን ለወጡ፤ የሶቭየት ኅብረት አንድ ቢልዮን ተሩብ ያህል ዶላር ለማበደር ዝግጁ ሆነ፤ ግብጽም ብድሩን ለመክፈል እንድትችል በዓለም-አቀፍ ኩባንያ ይተዳደር የነበረውን የስዌዝ ቦይ ብሔራዊ ሀብትዋ አድርጋ አወጀች፤ ይህንን በመቃወም ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና እሥራኤል ግብጽን ወረሩ፤ በተባበሩት መንግሥታት ግፊት (አሜሪካና የሶቭየት ኅብረት በተባበሩት መንግሥታት መድረክ ላይ በአንድ ላይ የቆሙበት ብርቅ ሁኔታ ነበር፤) ወረራቸውን አቁመው ከግብጽ ወጡ፤ በኋላ ነገሩ ሁሉ ተገለባብጦ ግብጽ ሶቭየት ኅብረትን ትታ የአሜሪካ ወዳጅ ሆነች!
አሜሪካ የሶርያን ሳይጨርስ፣ የኢራንን ሳይጀምር ከግብጽ ጋር ውዝግብ ቢጀምር ምን ጥቅም ያገኛል? ደግሞስ በዓባይ ጉዳይ በኢትዮጵያና በግብጽ ውዝግብ የሚያሸንፈው አሜሪካ መሆኑ ያጠራራል ወይ? አሜሪካ ሲያሸንፍ ግን ከኢትዮጵያና ከግብጽ አንዳቸው ይወድቃሉ፤ ወይም ይቆስላሉ፤ ሁለቱንም እኩል አያቅፋቸውም፤ ደርግ አሜሪካንን በማስቀየሙ በአለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ መሬትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያስከተለው መዘዝ እያሰቃየን መሆኑን ልንረሳው አይገባንም
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና በግብጽ መሀከል ያለው ጉዳይ አህያ ላህያ ቢራገጥ ዓይነት አይመስለኝም።