fredag 2. mai 2014

ኢቴቪ በራሺያ ፍቅር ዩክሬንን ጠምዷታል፤ መዘዙ ለአገራችን ነው

 የአገራችን የመንግስት ቴሌቪዢንና ሬድዮ፣ ለበርካታ ሳምንታት በራሺያና በዩክሬን “ድራማ” ዙሪያ ያለማቋረጥ የሚያሰራጩት ነገር፣ ለአገራችን ምን አይነት መዘዝ እንደሚያስከትል የተገነዘቡት አይመስልም። “ድራማው”፣ የሚያሳዝንና የሚያሳስብ እንጂ፣ የሚያስቦርቅና የሚያስፈነድቅ ድራማ አይደለም። በጠበኛ እብሪት የተለከፈው የራሺያ መንግስት  ዋና አቀናባሪነትና ስፖንሰርነት በሚመራው በዚሁ ድራማ፤ ዩክሬን በጎሳና በሃይማኖት ስትሰነጣጠቅ እየታየ ነው። እና፣ ይሄን እያዩ በደስታ ጮቤ መርገጥ ተገቢ ነው?
የውጭ ጠበኞች የሚያሴሩባትና የውስጥ ጣጣዎች የሚያስቸግሯት አገርኮ ዩክሬን ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያም፣ ከሩቅና ከቅርብ፣ በጎሳም ሆነ በሃይማኖት ሰበብ “እንበጥብጣት” የሚሉ (የራሺያ አይነት)የውጭ አገር ጠበኞች አሉባት። አንዳንድ የግብፅ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ ሲዝቱ ሰምተናልኮ። ለብጥብጥ የሚሆን ሰበብ ደግሞ ሞልቷል። አገራችን፣ከጎሳና ከሃይማኖት ጋር የተቆራኙ ነባርና ኋላቀር የውስጥ ጣጣዎች የሉባትም እንዴ? እንደ ዩክሬን ለአደጋ የሚያጋልጡ የአገራችን ጣጣዎች ጥቂት አይደሉም። የራሺያ መንግስትና የኬጂቢ ኮለኔል የነበሩት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ በዩክሬን ላይ የሚያካሂዱት ዘመቻ ድብቅ ሚስጥር አይደለም። የግብፅ መንግስት፣ የሶማሌ ክልል ተወላጆች እንዲገነጠሉ በማሴር፣ “የራሳቸውን እድል በራሳቸው ይወስኑ” እያለ ዘመቻ ቢያካሂድ እንደማለት ነው። ከኢትዮጵያ ጎን የሚሰለፍ አለኝታ ይኖራል? ምናልባት፣ ዩክሬንንም ከጥቃት የሚያድን አለኝታ መንግስት አይኖር ይሆናል። ግን፣ አነሰም በዛ ከጎንሽ ነን ብለው የሚከራከሩላት የአሜሪካና የአውሮፓ ወዳጅ መንግስታትን አላጣችም። ኢቴቪ ይህንንም ሲያወግዝ ነው የምንሰማው። በራሺያ ሴራ ዩክሬን ስትሰነጣጠቅ እያየን ብንቦርቅ፣ በራሳችን ላይ መዘዝ መጋበዝ እንደሆነ እነኢቴቪ እንዴት አልተረዱትም?
በእርግጥ የራሺያና የዩክሬን ጉዳይ፣ እዚሁ ለአገራችን የራሱ አንደምታና ትርጉም እንደሚኖረው እነ ኢቴቪ አያውቁም ማለቴ አይደለም። ትርጉም እንዳለው ስለሚያምኑማ ነው፤ ነገሩን እንደራሳቸው ጉዳይ የእለት ተእለት ዘመቻ ያደረጉት። በእርግጥ፣ “ዜና ወይም ዘገባ አሰራጨን እንጂ ዘመቻ አላካሄድንም” ሊሉ ይችላሉ። ግን፤ዜና ወይም ዘገባ ማሰራጨት ሌላ! በራሺያ ፍቅር የታወረ እስኪመስል ድረስ፤ በዩክሬንና በምዕራብ አገራት ላይ ጭፍን የጥላቻ ዘመቻ ማራገብ ደግሞ ሌላ! የኢቴቪ ዜናዎችና ዘገባዎች፣ በስሜት የጦዘ “ቲፎዞ” ከሚሰነዘረው ጭፍን አስተያየት አይለዩም። ጭፍን አስተያየት፣ በዜና ወይም በዘገባ ስም ሲቀርብ ምን ይባላል? “ፕሮፓጋንዳ” ይባላል። ሌላ መጠሪያ ስም የለውም። ለዚያውም ማንንም የማይጠቅምና ሁሉንም የሚጎዳ ቀሽም ፕሮፓጋንዳ!
ፕሮፓጋንዳ በተፈጥሮው፣ እውነተኛ መረጃዎችን በማጥፋትና በማግለል፣ በማጣመምና በማድበስበስ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዳይፈጠር ስለሚያግድ ጎጂ ነው። ከረዥም ጊዜ አንፃርም፣ የእውነትን ክብር በመሸርሸር፣ በሁሉም ተቀናቃኝ ቡድኖች ዘንድ ጭፍንነት እየተስፋፋና ስር እየሰደደ እንዲሄድ ያደርጋል። የኢቴቪ ፕሮፓጋንዳ ቀሽምነት ግን፣ ከዚህም ይብሳል። ብዙ ሰዎች ወደ ፕሮፓጋንዳ የሚሮጡት፣ ውሎ አድሮ እንደሚጎዳ ስለማያውቁ፤ ወይም ደግሞ ጎጂነቱ ባይጠፋቸውም ለማያዛልቅ የአጭር ጊዜ ጥቅም እጅ ስለሚሰጡ ነው። የኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ ግን፤ቅንጣት ታህል የአጭር ጊዜ ጥቅም የለውም። ከንቱ ድካም ነው። “ከንቱ ድካም” ሲባል ግን፤ እርባና ቢስነቱን ለመግለፅ ያህል እንጂ፤ “ምንም ውጤት አያመጣም” ለማለት አይደለም። መጥፎ ውጤት ያስከትላላ – አገሪቱንና ነዋሪዎቿን ለአደጋ በሚያጋልጥ የተሳሳተ አስተሳሰብ የተቃኘ ፕሮፓጋንዳ ነዋ። “እርባና ቢስ ነው” የምለውም፤ ኢቴቪ ወደ ፕሮፓጋንዳ እንዲገባ የሚገፋፋ መነሻ ሰበብ የለም ማለቴ አይደለም።
ለግንዛቤ የሚያስቸግር ውስብስብ ጉዳይ አይደለም። በጭላንጭልም ቢሆን አይኑን በመክፈት ለአንድ አፍታ ከጭፍንነት ለመራቅ ፈቃደኛ የሆነ ሰው፣ በቀላሉ ሊገነዘበው ይችላል። የራሺያ መንግስት በዩክሬንና በሌሎች ጎረቤት አገራት ላይ የሚሸርበው ሴራና የሚያካሂደው ዘመቻ፤ የኤርትራ መንግስት በጎረቤቶቹ ላይ ከሚፈፅማቸው ጠበኛ ድርጊቶች ብዙም አይለይም። ይሄ አጥፊ ተመሳሳይነት ለኢቴቪ የማይታየው ለምን ይሆን? የፕሮፓጋንዳው መነሻ ሰበብስ ምንድነው? የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ አንድ ነው -“የቀለም አብዮት”!
መንግስት፣ ኢህአዴግ ወይም የመንግስት ሚዲያ፣ ለበርካታ አመታት በ“ቀለም አብዮት” ላይ ብቻ ክፉኛ ስላፈጠጡ፤ ዛሬ ዛሬ ሁሉም ነገር “የቀለም አብዮት” እየሆነ ይታያቸዋል። ሊያሳስባቸው አይገባም ማለቴ አይደለም። የስልጣን ጉዳይ ነውና ቢያሳስባቸው አይገርምም። እንዲያውም፤ እነሱን ብቻ ሳይሆን፤ ማንንም ሰው ሊያሳስበው ይገባል። “የመጣው ይምጣ” ወደሚል ተስፋ ቢስነት ለዘቀጠ ሰው ወይም “ሳይደፈርስ አይጠራም” ከሚል አላዋቂነት ላልተላቀቀ ሰው ካልሆነ በቀር፤  ነባሩን አስተዳደር የሚያናጋ እንቅስቃሴ ሲፈጠር ማንኛውም ጤናማ ሰው በጥሞና ማሰብ ማሰላሰል ይኖርበታል። “ለውጥ” በቁንፅል ለጤናማ ሰው በቂ አይደለም። የተሻለ ነገር ለማምጣት የሚያስችል መሆን አለበት – “ለውጥ”። “የመጣው ይምጣ” ብሎ በጭፍን መደናበር ግን ጤንነት አይደለም። “የባሰ ቢመጣስ?” የሚል ጥያቄ አለና ነው። ጤናማና ብልህ ሰው፤ ነገሮች ጥርት ብለው እንዲወጡ ለማድረግ ከመነሻው አስበው፣ መላ አበጅተውና መድረሻቸውን አቅደው ይጣጣራሉ እንጂ፤ “መጀመሪያ ይደፍርስ፤ ያኔ የደፈረሰውን ለማጥራት እናስብበታለን” ብለው በጭፍን አይገቡበትም። “ከደፈረሰ በኋላ ባይጠራስ?” የሚል ጥያቄ አለና ነው። 
በተጨባጭ ያለውን እውነታ ከመነሻው በአግባቡ መገንዘብ፤ ወደፊት የሚመኙትን የተሻለ ሕይወት በቅጡ ለይቶ መድረሻውን ማወቅ፤  ከመነሻ ወደ መድረሻ የሚጓዙበት ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ ያስፈልጋል። ተጨባጩን እውነት፣ የለውጡን መንገድ እና የታለመውን ሕይወት፣ … ሦስቱንም አስተሳስሮ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ከተገነዘብን፤በዘመናችን “የቀለም አብዮቶች” ተብለው የሚጠሩ “የለውጥ እንቅስቃሴዎችን” ሁሉ በጅምላ እየፈረጁ በደፈናው መደገፍም ሆነ መቃወም፤ ከአላዋቂነት ወይም ከጭፍንነት የዘለለ ትርጉም እንደማይኖረው ይገባናል። ለምን? “የቀለም አብዮቶች” ሁሉ እኩል አይደሉም። የብዙ ሰዎችን (የሕዝብን) ትኩረት በመማረክ የሚጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴ ከመሆናቸው በስተቀር፤ ብዙም ተመሳሳይነት የላቸውም። በተነሱበት እውነት፣ በመረጡት መንገድና ባለሙት የሕይወት ግብ ይለያያሉ።
ለምሳሌ የመጀመሪያው የቀለም አብዮት ነው ተብሎ በኢህአዴግ መፅሔት የተጠቀሰው፤ “velvet revolution”ን ተመልከቱ። በ1982 ዓ.ም ቼኮዝላቫኪያ ተብላ ትጠራ በነበረችው አገር የተካሄደ የለውጥ እንቅስቃሴ ነው። ያኔ የነበረው እውነታ ምን ነበር? አፈና በሰፈነበት የኮሙኒስት ስርዓት ውስጥ፤ በነፃነት ማሰብና ሃሳብን መግለፅ፣ ማንበብና ሃሳቦችን መቀበል ወንጀል ነበር። የሰዎች ስራ፣ ምርት፣ ንብረትና ኑሮ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ነው። ከኮሙኒስት ፓርቲው ውጭ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ መሰንዘርም ሆነ ፓርቲ ማቋቋም ወንጀል ነው። የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት የለም። በአጠቃላይ፤ በስለላ የታመቀ፣ በአፈና የደነዘዘ፤ በመንግስት ቁጥጥር የተራቆተና የደኸየ ኢኮኖሚ፤ በራሽን የታጠረና መላወሻ ያጣ ኑሮ፤ … በአጠቃላይ እያንዳንዱ ሰው ፓርቲንና መንግስትን በባርነት የሚያገለግል አቅም አልባ፣ ምስኪንና ክብረቢስ ፍጥረት ተደርጎ የሚቆጠርበት የውርደት ሕይወት ነበር። በአጭሩ በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ሕይወት ብዙም አይለይም። የነፃነትን ጭላንጭ የሚዘጋ፣ የብልፅግናን እድል የሚሰብር፣ የእኔነትን ክብር የሚያኮላሽ የኮሙኒዝም ስርዓት።
ደግነቱ፤ ሰው ብርቱ ነው። ከፍርሃትና ከአፈና የመላቀቅና የነፃነትን አየር የመተንፈስ ሰውኛ ፍላጎት ጠፍቶ አይጠፋም። መላወሻ ከሌለው የመንግስት ጭሰኝነትና ከንብረት አልባነት ተገላግሎ ንብረት የማፍራትና ብልፅግናን የመቋደስ ምኞት ተዳፍኖ አይቀርም። የካድሬና የቀበሌ ሊቀመንበር ሎሌ፤ የሚሊሻና የታጣቂ መጫወቻ ከመሆን ተገላግሎ፣ አንገትን ቀና አድርጎ ሕይወትንና ሰላምን የማጣጣም ህልም ብን ብሎ አይሰወርም።
በኮሙኒስት ስርዓት ውስጥ የነበረው እውነታ፤ በአፈናና በፍርሃት፣ በዝርፊያና በድህነት፣ በሸክምና በውርደት የተሞላ ኑሮ ነው። ወደፊት የተመኙት ሕይወትና ያለሙት መድረሻስ ምን ነበር? የነፃነት አየርን መተንፈስ፣ የብልፅግና እድልን መቋደስና የሕይወትን ጣዕም ማጣጣም ነው። በእርግጥም፤ ከአብዮቱ በኋላ፤ የግል ሚዲያና የፖለቲካ ምርጫ ተጀመረ። የግል ንብረትና የቢዝነስ ስራ ተፈቀደ። አንገትን ቀና አድርጎ የመራመድ የእፎይታና የሰላም መንፈስም ተገኘ። በእርግጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት እንዲሁም ሰው የመሆን ክብር በተሟላ ሁኔታ ሰፍኗል ማለት አይደለም። ግን ከድሮው በእጅጉ በእጅጉ ይሻላል። በከፊልም ቢሆን፤ ወዳለሙትና ወደተመኙት መድረሻ የሚያሸጋግር መልካም ለውጥ እውን ሆነ ማለት ነው። እንዴት?  በምን አይነት የለውጥ እንቅስቃሴ? አደባባዮችንና ጎዳናዎችን በሚያጥለቀልቁ የተቃውሞ ሰልፎች ነው፣ የቀድሞው አምባገነን የኮሙኒስት ስርዓት ፈርሶ ለውጥ የመጣው። 
እንግዲህ፤ የአገሬው ሰዎች ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ቃኝተናል – መነሻቸውን። የመጣውን ለውጥ ተመልክተናል – መድረሻቸውን። የተጓዙበትን አቅጣጫ አይተናል- መንገዳቸውን። ከዚህ ውስጥ ምን የሚያስወቅስ እንከን አገኛችሁበት? በተቃውሞ ሰልፍ ከአምባገነንነት መላቀቃቸውና ለውጥ ማምጣታቸው ያስወቅሳቸዋል? ደም ሳይፈስ በተቃውሞ ሰልፍ ብቻ መልካም ለውጥ መገኘቱ መታደል ነው። የሚያስሞግስ እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም። ሌላው ቀርቶ፤ የመቶ ሺዎችን ህይወት የቀጠፈና የሚሊዮኖችን ኑሮ ያናጋ ጦርነት ተካሂዶ በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣቱስ ያስወቅሳል እንዴ? ነውጠኛና አመፀኛ ብለን ኢህአዴግን ማውገዝ ተገቢ ነው? በጭራሽ። በእርግጥ፣ በጠባቡም ቢሆን ሃሳብን የመግለፅና በምርጫ የመሳተፍ እድል ባለበት አገር፤ “ለውጥ አመጣለሁ” ብሎ ወደ ጦርነት መግባት ተገቢ አይደለም። ሃሳብን የመግለፅና ምርጫ የማካሄድ እድል እየተዘጋ ካልሄደ በቀር፣ እንኳን በጦርነት ይቅርና በጎዳና ሰልፎች መንግስትን ለመለወጥ መነሳትም፤ ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ አለ። በተለይ ደግሞ፣ ከነባሩ ስርዓት በእጅጉ የተሻለ መልካም ለውጥ እንደሚመጣ በእርግጠኝነት የማናውቅ ከሆነ፤ ነገር ማደፍረስ ጥቅም የለውም። በስሜት ደረጃ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ከመመኘት ባሻገር፤ የምንመኛቸውን ነገሮች እውን ለማድረግ ምን አይነት ስርዓት እንደሚያስፈልግ በትክክል ካላወቅንና መድረሻችንን በቅጡ መለየት ካቃተን፤ “የለውጥ እንቅስቃሴ” ሁሉ ከንቱ ይሆናል። የእነ ግብፅ እና የእነ ሊቢያ አብዮቶች፤ እንዲሁም በጆርጂያና በዩክሬን የተካሄዱ ፀረ ራሺያ አብዮቶች በዚህ ጎራ የሚመደቡ ናቸው። በነባር ችግሮች እየተማረሩ የተሻለ ነገር ከመመኘት በስተቀር፤ መድረሻቸውን በግልፅ ለይተው ባለማወቃቸው፤ብዙም ሳይራመዱ ለቀውስ ተዳርገዋል። 
ግን ከእነዚህም የባሰ ሞልቷል። የተሻለ ነገር በመመኘት ሳይሆን ወደ ባሰ ክፉ ስርዓት ለመጓዝ የሚካሄዱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች አሉ። የሶሪያ እና የሴንትራል አፍሪካ ቀውሶችን መጥቀስ ይቻላል። በራሺያ አቀናባሪነት ዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ፀረ ምዕራብ አገራት እንቅስቃሴም፣ ከዚሁ የጥፋት ጎራ የሚመደብ ነው።
ፀረ ራሺያ አቋም የያዙ ዩክሬናዊያን አደባባዮች ማጥለቅለቅ “ለውጥ” ለማምጣት ተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱ፤ መንግስት በወሰደው እርምጃ ከመቶ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህ በኋላ ነው፤ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ተባርረው መንግስት የተለወጠው። ኢቴቪ ይህንን ምን ይለዋል? መፈንቅለ መንግስት ብሎ ይጠራዋል። በምርጫ ስልጣን የያዘ መንግስት የፈረሰው፣ “የቀለም አብዮተኞች” ባካሄዱት መፈንቅለ መንግስት ነው በማለት ኢቴቪ በየእለቱ ሳያወግዝ አያልፍም። በመንግስት ስለተገደሉት ሰዎች አንዳችም የትችት አስተያየት አይሰነዝርም። 
በራሺያ የሚደገፉ ዩክሬናዊያን፣ በክሬሚያ እና በሌሎች ምስራቃዊ ክልሎች ምን አይነት “የለውጥ እንቅስቃሴ” እንደሚያካሂዱ ተመልከቱ። በተቃውሞ ሰልፍ አልያም በታጣቂ ቡድኖች አማካኝነት፣ አደባባዮችን ብቻ ሳይሆን የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በሃይል ይቆጣጠራሉ። መንግስት መስሪያ ቤቶቹን ለማስለቀቅ ሲሞክር አምስት ሰዎች ተገድለዋል። ኢቴቪ ስለተገደሉት ሰዎች ሲናገር፤ 5 የነፃነት ታጋዮች ተገድለዋል በማለት ነው የገለፀው። ለማንኛውም “የነፃነት ታጋዮቹ” በሃይል የተቆጣጠሯቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች አልተለቀቁም። እናም በራሺያ የሚደገፉት “የቀለም አብዮተኞች” ፤ በምርጫ ስልጣን የያዙ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችን ለማፍረስ ችለዋል። በእርግጥ ኢቴቪ እነዚህን፣ የቀለም አብዮተኞች አይላቸውም። የራስን እድል በራስ የመወሰን መብታቸውን ለማስከበር የሚጠይቁ የነፃነት ታጋዮች እያለ ነው የሚጠራቸው።
ክሬሚያ የተሰኘው የዩክሬን ክልል እንዲገነጠልና ወደ ራሺያ እንዲጠቃለል የተደረገውም፤ እነዚሁ በራሺያ የሚደገፉ “የቀለም አብዮተኞች” (በኢቴቪ አጠራር “የነፃነት ታጋዮች”) ባካሄዱት የተቃውሞ ዘመቻ አማካኝነት ነው – በምርጫ ስልጣን የያዘውን አስተዳደር በሃይል በመቆጣጠርና በማፍረስ።
በአንድ በኩል፤በምርጫ ስልጣን የያዙ ፕሬዚዳንት በተቃውሞ አመፅ ከስልጣን ሲባረሩ፤ “በቀለም አብዮተኞች የተፈፀመ ትልቅ ወንጀል ነው” ተባለ። እሺ። በሌላ በኩል፤ በምርጫ ስልጣን የያዙ የክልል ፕሬዚዳንቶችና የከተማ አስተዳዳሪዎች፤ በተቃውሞ አመፅ ሲባረሩስ? “በነፃነት ታጋዮች የተገኘ ትልቅ ድል ነው” ተባለ። ታዲያ እንዲህ አይነቱ ፕሮፓጋንዳ እዚያው እርስ በርሱ የሚጣፋ ከንቱ ድካም አይደለምን? ለአጭር ጊዜ የሚያገለግል ጥቅም እንኳ የለውም። ይልቅ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ጉዳት አለው። እንዴት በሉ። በራሺያ አቀናባሪነትና ድጋፍ፣ የክሬሚያ ክልል ከዩክሬን ተገንጥሎ ወደ ራሺያ መጠቃለሉ፤ በኢቴቪ ቤት “የነፃነት ትግል” ነው። ይህንን ሁኔታ ወደ አገራችን አምጥተን እንየው።  ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ “በቀለም አብዮት” መንግስት ተለወጠ እንበል። ከዚያስ? ከዚያማ ልክ የራሺያ መንግስት እንዳደረገው፤ የሶማሊያ መንግስትም የኢትዮጵያ አካል የሆነው የሶማሌ ክልል እንዲገነጠል ድጋፍ ይሰጣል። የክልሉ መስተዳድር ስልጣን የያዘው በምርጫ ቢሆንም፤ በሶማሊያ መንግስት ስፖንሰር አድራጊነትና በተቃውሞ ሰልፈኞች አማካኝነት እንዲፈርስ ይደረጋል እንበል። ከዚያም በሶማሊያ መንግስት ወታደራዊ አለኝታነት ተማምነው፤ የኢትዮጵያን ህገመንግስት በሚጥስ መንገድ የሶማሌ ክልል እንዲገነጠል በምርጫ አስወስነናል ይላሉ፤ ወደ ሶማሊያ እንዲጠቃለልም ያደርጋሉ። ምናባዊ ታሪክ ነው። ነገር ግን ከእውነተኛው ታሪክ ጋር ያን ያህል አይራራቅም። እስከዛሬ አልተሳካም እንጂ፤በርካታ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ለረዥም አመታት ያቀነቀኑትን አቋም እንዲሁም በተደጋጋሚ ያካሂዱትን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሙከራ ስንመለከት፤ ምናባዊው ታሪክና እውነተኛው ታሪክ ተቀራራቢ መሆናቸውን ለመገንዘብ አይከብድም። 
ለነገሩ ከላይ እንደጠቆምኩት፤ የኤርትራ መንግስት ጠበኛ ባሕሪዎችንም መመልከት ይቻላል። ለወጉ ያህል እንኳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲንቀሳቀሱ የማይፈቅድ፣ ሌላው ቢቀር ለወጉ ያህል እንኳ ዜጎች በምርጫ እንዲሳተፉና ሶስት አራት ነፃ ጋዜጦች እንዲታተሙ እድል የማይሰጥ፣ ከጎረቤቶቹ ሁሉ የባሰ የለየለት አምባገነን መንግስት ነው። ነገር ግን፤ የተለያዩ ክልሎችን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚፈልጉ ቡድኖችን እያሰባሰበ ይደግፋል፤ እያስታጠቀ ያሰማራል – የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በሚል መፈክር እያሳበበ። እንዲህ አይነቱ ዘመቻ እንዴት እንደ ነፃነት ትግል ይቆጠራል?       
 አንድ የጥንት አባባል አለ – “ምን ያለበት ምን አያወራም” የሚል አይነት። አባባሉን ከዘመናዊ አኗኗር ጋር እንዲጣጣም ከፈለግን፤ “መስተዋት ውስጥ የተቀመጠ፣ ስለ ድንጋይ ውርወራ አያወራም” ልንለው እንችላለን። በመላው ዓለም ብዥታና ግርግር በበዛበት ዘመን ነው የምንኖረው። ከኋላቀርነትና ከግጭት ያልተላቀቀ አህጉር ውስጥ ነው ያለነው – ለዚያውም ለበርካታ አስርት አመታት ባልረገበ ጥላቻና ባልተቋረጠ ግጭት የሚታመሰው የአፍሪካ ቀንድ!  በዚያ ላይ፤ ከኋላቀር የጎሳና የሃይማኖት ጣጣዎች ጋር ስትዳክር ዘመናትን ያስቆጠረች ናት – አገራችን። እዚህ ውስጥ ሆነን፤ የድንጋይ ውርወራን እያዳነቅን ባናወራ ያሻላል።
Source-www.addisadmas.com

ሰበር ዜና- የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) ፕሬዝደንት ጋዜጠኛ በትረ ያቆብ ተሰደደ

May 2, 2014
Journalist Betre Yakobከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት በአፍሪካ ህብረት ጋባዥነት የኢትዮጵያን ችግርና አፈና በተለይ በሚዲያው ላይ ያለውን ጫና እና ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን አፈና ለመግለጽ ወደ አንጎላ አቅንተው ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለአፍካ ህብረትም የመፍትሄ ሀሳብ ማቅረቡና ለሰብአዊ መብት ኮሚሽነሩም መልስ መስጠቱ ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛ በትረ ያቆብ ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ አገሩ ለመመለስ በሚዘጋጅበት ወቅት የዓለም አቀፍ የጋዜጠኛ ማህበራትን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ እሱን ለማሰር የተደረገው ዝግጅት በተጨባጭ ማስረጃ ስላቀረቡለት መሰደዱን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች በታሰሩበት ወቅት ፖሊስ የበትረ ያቆብን ቤት በመፈተሸ ያገኘውን ወረቀት ሁሉ እንደወሰደም ምንጮቻችን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ጋዜጠኛ በትረ ያቆብ አንጎላ በተደረገው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ኮሚሽነሩን በግል እንዳገኛቸውና ኮሚሽነሩም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ በመግለጽ እንዲሚያገኙት ቃል ገብተውለት እንደነበር ተገልጿል፡፡ በተጨማም ከበርካታ የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና በሚዲያው ላይ ስለሚደረገው ጫና የተወያዩ ሲሆን አብዛኛዎቹ በተለያዩ መንገዶች እገዛ ለማድረግ ቃል ገብተውለት እንደነበር ከታማኝ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በስብሰባው ወቅት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገልጹ ጽሁፎች ለተሰብሰብሳቢዎቹ ተበትነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ መቋቋም ያስፈራቸው ሌሎች የጋዜጠኞች ማህበራት በትረ ያቆብን ለሂውማን ራይትስ ዎች፣ ለሲፒጄ፣ ለአርቲክል 19ና ሌሎች የጋዜጠኞች ማህበራት ይሰራል፣ ይሰልላል፣ የእነዚህ ድርጅቶች ተላላኪ ነው፣ ሪፖርት ይጽፋል በሚል በመግለጫቸውና ‹‹የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ›› በተባለው ፕሮግራም ይከሱት እንደነበር ጋዜጠኛ በትረ ያቆብ አገር ውስጥ በነበረበት ወቅት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻል፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia

torsdag 1. mai 2014

ሰበር ዜና፣ በጎንደር ተኩሱ ቀጥሏል፣ በግጭቱ 6 ሰው ሞቷል May 1, 2014

ነገረ-ኢትዮጵያ – ጎንደር ከተማ ውስጥ ቀበሌ 18 ልዩ ቦታ አርምጭሆ ሰፈር፣ ገንፎ ቁጭና ህዳሴ የተባሉ ሰፈሮች የከተማው አስተዳደር ‹‹ህገ ወጥ ሰፈራ ነው፡፡›› በሚል ቤቶችን ለማፍረስ መዘጋጀቱን ተከትሎ አፍራሾቹ ከህዝብ ጋር በፈጠሩት ግጭት ከ6 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸውንና መታሰራቸውን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ግጭቱ ከሶስት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ተኩል ድረስ ቀጥሎ የነበር ሲሆን ምንጫችን ደውሎ በሚነግረን ወቅት (ከቀኑ 6፡ 43) ተኩስ እንደነበር ለመረዳት ችለናል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎቹ ሚያዝያ 7/2006 ዓ.ም ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ትዕዛዝ በተላለፈበት ወቅት ህገ ወጥ አለመሆናቸውን፣ ካልሆነም መንግስት ቅያሬ ቦታና ጊዜ መስጠት እንዳለበት በመግለጽ አንለቅም ብለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዛሬው ቀን ግጭቱ የተነሳውም አፍራሾቹ እንዲፈርሱ የተወሰነባቸውን ቤቶች ቀለም በመቀባታቸውና ህዝቡም እንዳይቀቡ በመከልከሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
በግጭቱ ፖሊስ፣ ፌደራልና ልዩ ኃይል የተሳተፈበት ሲሆን ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ የአካባቢው ወጣቶች ላይ ድብደባና እስራት እየፈጸሙባቸው እንደሆነ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ‹‹ወጣቶችን እንደ እንሰሳ በአንድ ገመድ አስረው እየደበደቧቸው ነው፡፡ ህዝብ በጅምላ እየታሰረ ይገኛል፡፡ ግጭቱ ቢያቆምም በአሁኑ ወቅት በሶስቱም ሰፈሮች ጥይት እየተተኮሰ ነው›› ያሉት የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች የተወሰደው እርምጃ የጎንደርን ህዝብ በማስቆጣቱ ከዚህ የባሰ ግጭት እንዳይፈጠር ያሰጋል ሲሉም ገልጸውልናል፡፡ በግጭቱ ወቅት የመጀመሪያዋ የሞት ሰለባ የሆነችው ልዩ ኃይል ቤቷ እንዲፈርስ ቀለም ሲቀባ የተቃወመች የልጆች እናት እንደሆነችም ታውቋ፡፡

fredag 18. april 2014

ወቅታዊ ሪፖርት በኖርዎይ:

የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዎይ የሚገኙ ኢትዮጵያን ስደቶኞች የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው የሚኖሩበት ሃገር እንደሚሰለሉ እና የወያኔ ሰላዮች በኖርዎያ እንደሚገኙ የኖርዎይ ደህንነት ፖሊስ ለሃገሩ ትልቅ መረጃ መስጠታቸውን በተመሳሳይ ሂውማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ያወጣውን መረጃ መሰረት በማድረግ የኖርዎይ መንግስታት ለወያኔ ሰላዮች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆም እና አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ለመጠየቅ እና ኖርዎይ በኢትዮጵያውያን ላይ ያላትን አሳይለም ፖሊሲ እንድታስተካክል በሚል የጠራውን ሰልፍ እጅግ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። ይህ ሰልፍ የኢትዮጵያን በኖርዎይ ምን ይህል የሃገራቸው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው እና እየታገሉ እንደሆነ የሚያሳይ ሰልፍ ነበረ። ከኖርዎይ ጂኦግራፊያዊ ይዘት አንጻር ለመሰባሰብ አስቸጋሪ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን ችግር ከምንም ሳይቆጥሩት ድምጻቸውን እንዳሰሙ ይገኛሉ በርቱ የሚያሰኝ ነው። በሌላውም ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንደ ኖርዎይ አንድ ሆነው ድምጹ የታፈነውን ህዝባችንን ድምጽ ሊሆኑለት ይገባል።











በኖርዎይ ዋና ከተማ ኦስሎ ከተለያዩ ቦታ በተሰባሰቡ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው
የሚደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ማስተናገዱን ተያይዘዋለች። በኖርዎይ የሚገኙ ጠንካራ
ተቃዋሚ ድርጅቶች በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት, የኢትዮጵያ
ስደተኞች ማህበር ትልቁን ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ የተለያዩ ድርጅቶች ለሚያዘጋጁት
ሰልፎች መሳካት ደግሞ በኖርዎይ ነዋሪ የሆኑ እና በተለያዩ ካንፕ ውስጥ የሚገኙ ሃገር ወዳድ
ኢትዮጵያውያን ተጠቃሽ ናቸው። ዓርብ አፕሪል 11 2014 ያየንው ይህንንው ነው። በዚህ
ዕለት የኢትዮጵያውያ ሰደተኞች ማህበር የጠራውን ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ነበር። ሠልፉ
የሚጀምረው ከቀኑ 12 ሰአት ይሁን እንጂ በሀገሩ ወቅታዊ ሁኔታ የሚንገበገበው ሀገር ወዳድ
ኢትዮጲያዊ ከተባለው ሰአት በፊት ጥሪ በተደረገበት ቦታ ተሰባስቦ የፕሮግራሙን መጀመር
ሲጠባበቅ ነበር። የተባለው ሠአት ሲጀምር የዝግጅቱ አስተባባሪዎች የእንኳን ደህና
መጣችሁና የዝግጅቱን አላማ በማስተዋወቅ ዝግጅቱ ጀምሯል። ልክ ንግግሩ እንዳለቀ
በፕሮግራሙ መሰረት ያለውን ችግር ወደ ሚያስረዳበት ፖርላማ ጉዞውን አድርጎዋል።
ህዝቡም ፖርላማ እስከሚደርስ ድረስ የተለያዩ መፈክሮችን እያሰማ ነበር። በሰልፉ ላይ
የተሳተፈው ህዝብም መፈክሩን የሚያሰማው እጅግ ከልቡ ተቆጥቶና በከፍተኛ ጩኸት ነበር።
በዚህ ወቅትም በጎዳና ላይ የነበሩ ኖርዊጅያኖች በመገረም መንገዳቸውን ትተው ቆመው
ሲያስተውሉ ነበር። አንዳንዶችም ካሜራቸውንና ሞባይላቸውን ወደ ሰልፈኛው ቀስረው
ለረጅም ሰአት ሲቀርጹ ነበር። በዚህ ሁኔታ ወደ ፓርላማው ከተደረሰ በኌላ የተለያዩ
ግለሰቦች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ስለ ወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ እና ስለሰልፉ አላማ
ንግግሮች አድርገዋል። ሠልፉን በተመለከተም መልዕክታቸውን ከፓርላማ ለተላኩት ግለሰብ
ሠጥተዋል።

            አፕሪል 12/2014 በኖርዌ ኦስሎ ከተማ በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ
የድጋፍ ድርጅት አዘጋጅነት የአትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንደዚሁም የዲያስፖራው
የትግል ተሳትፎን የዳሰሰ ታላቅ ስብሰባ ተካሂዷል። በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ በርካታ
አትዮጵያውያን ተገኝተዋል።













ለ6 ሠዓታት ያህል የተካሄደው ይህ ስብሰባ የጀመረው በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ አቢ አማረ ጋባዥነት በሀገራችን ባለው በዘረኛው አረመኒያዊ ስርአት በጭካኔ በግፍ ለተገደሉ እና በተለያዩ እስር ቤቶች በፓለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ያለጥፍታቸው ያሚሰቃዩትን ውድ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችንን በማሰብ በዚሁ ዘረኛ ቡድን ሰለባ ለሆኑ እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ ነበር። በመቀጠል አቶ ዩሀንስ አለሙ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ሊቀመንበር የመግቢያ ንግግር አድርገዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ የእለቱ ተጋባዥ እንግዳ የሆኑት የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ብዙነህ ጽጌ የተገኙ ሲሆን በሃገራችን ስላለው ጠቅላላ የፖለቲካ ሁኔታ እና የግንቦት 7ን አስተዋጽኦ ከህዝቡ የሚጠበቀውንም አጠቃሎ እጅግ ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል። በዝግጅቱ ላይ በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት አባሎች ‘’ላንቺ ነው ሃገሬ’’ የሚለውን መዝሙር አቅርበዋል።














ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!!!

lørdag 12. april 2014

ሒላሪ ክሊንተን ጫማ ተወረወረባቸው ( ቪዲዬ )



በመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ እየተባሉ የሚጠበቁት ሒላሪ ክሊንተን ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ጫማ ተወረወረባቸው፡፡ ጉዳት ባይደርስባቸውም ዜናው ግን የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ ስቧል፡፡
አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተን በላስ ቬጋስ በተጠራ የመልሶ መጠቀም ኢንዱስትሪዎች (Scrap Recycling Industries) ስብሰባ ላይ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ ከአዳራሹ ጫማ ተወርውሮባቸዋል፡፡
ጫማው ሳይመታቸው ቢቀርም ወርዋሪዋ ግለሰብ አስተካክላ ብትወረውር ግን ክፉኛ ጉዳት ልታደርስባቸው ትችል እንደነበር የቪዲዮው ምስል ያመለክታል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ አዳራሹ ጨለምለም ያለ በመሆኑ ክሊንተን ጫማው ከተወረወረ በኋላ ነው ያስተዋሉትና ደበቅ ለማለት የሞከሩት፡፡
ሒላሪ ክሊንተን በጉዳዩ ላይ ቀልድ በማከል አስተያየት የሰጡበት ቢሆንም የስብሰባው ኃላፊዎች ግን ታላቅ ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ጫማ ወርዋሪዋ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የዋለች ከመሆኗ በላይ ማንነቷ ገና አልተገለጸም፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ሚስት ሒላሪ ከፍተኛውን የፖለቲካ ሥልጣን ለመቆናጠጥ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በነበሩበት አራት ዓመታት ያከናወኗቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ደጋፊዎቻቸው ቢጠቀሱም የጋዳፊ ግድያ ከዚያም ጋር ተያይዞ የተከሰተው የቤንጋዚው ቀውስ እና የአሜሪካው አምባሳደር መገደል፣ በግብጽ የተካሄደው ለውጥና ከዚያም በአሜሪካና ምዕራባውያን ግፊት ለውጡ መቀልበሱ፣ በአፍጋኒስታንና ፓኪስታን ላይ የወሰዱት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በአፍሪካ እንደነ መለስ ካሉ አምባገነኖች ጋር በመሞዳሞድ ግብረሰዶማዊነት እንዲስፋፋ አሜሪካ የተከተለችው ፖሊሲ፣ ወዘተ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሒላሪ ኪሊንተን በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚ/ርነት ዘመናቸው ስላከናወኑት የሚያወሳ “የሚኒስትር ማስታወሻ” በገበያ ላይ ያውላሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
የዛሬ ስድስት ዓመት አካባቢ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በኢራቅ ከጠ/ሚ/ር ኑሪ አልማላቂ ጋር ንግግር ሲያደርጉ አገሩ በአሜሪካ ወራሪነት መፍረሷ ያናደደው ኢራቃዊ ጋዜጠኛ የጫማ ሚሳኤል ወርውሮባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
http://www.goolgule.com/shoe-thrown-at-hillary-clinton-at-vegas-speech/

mandag 7. april 2014

ህወሀት ኢሕአዴግን ለማገልገል ህዝባቸውን የሚጨፈጭፉ ሎሌዎች (በሁኔ አቢሲኒያዊ)


(ክፍል ሁለት)
በክፍል አንድ የወያኔውን ሎሌ ባጫ ደበሌን ብልሹ ስራዎች አይተናል ዛሬ 180 ዲግሪ ዞሮ የወያኔ አሽከር ስለሆነው ሬድዋን ሁሴን አንዳንድ ነገሮች እንላለን፡፡
መልካም ንባብ
አቶ ሬድዋን የ1987 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባዮሎጂ ምሩቅ ናቸው። ከምረቃ በኋላ ለማስተማር ጂንካ የተወሰነ ጊዜ አሳልፈዋል። ደቡብ ኢትዮጵያ ብዙም አልቆዩም። አዲስ አባባ መጥተው አወሊያ ትምህርት ቤት መምህር ኾኑ። የአወሊያ ትምህርት ቤት ቆይታቸው አስደሳች የኾነም፤ ያልኾነም ነበር። ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋራ በተደጋጋሚ ይጋጩ እንደነበር ይነገራል። በ1980ዎቹ መጨረሻ እና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የስልጤን የማንንት ጥያቄ በዋናነት በማቀንቀን ይታወቃሉ። “ስልጤ በደቡብ ክልል ውስጥ ውክልና ይገባዋል
ከሚለው አልፎ በዞን ደረጃ እንዲዋቀር ተሟግተዋል።” በወቅቱ በርካታ የስልጤ ተወላጆችን በቅርብ ማግኘት በመቻላቸው በጉዳዩ እንዲገፉበት ዕድል ሰጥቷቸዋል። በዚያውም የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ስሕዴፓ)ሲያቋቁም ከመሪ ተዋንያኑ አንዱ ሆነው ብቅ አሉ፡፡
ኢሕአዴግም እንደለመደው በአሁኑ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የቀድሞ የአለማያ ዩኒቨርስቲ የደን ልማት(ፎረስትሪ) ጥናት ተማሪ በነበሩት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የሚመራውን “የስልጤ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት” (ስሕዴድ) አቋቋመ። ሁለቱ የስልጤ ሕዝብ ድርጅቶች እርስ በርስ ይፎካከሩ ሲልም በግልጽ ይተቻቹ ነበር። ፀባቸው ሌላ አይደለም። እውነተኛ የስልጤ ሕዝብ ተወካይ ማን ነው?የሚለው ነው። ሬድዋን የእነ አቶ ሲራጅን ስሕዴድ፣ “አሻንጉሊት” እና “የኢሕአዴግ ተላላኪ” በማለት እስከ እስከ መወጀል ይደርሱ እንደነበር ይነገራል።
በ1992 ዓ.ም “የስልጤ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና ከጉራጌ ሕዝብ የተለየ ማንነት ያለው መኾኑ በሕዝብ ውሳኔ ሲረጋገጥ የአቶ ሬድዋንም ሚና እና የፖለቲካ አቅጣጫ ተቀየረ።” ይላሉ ለአዲስ ነገር ሐሳባቸውን ያካፈሉት ውስጥ አዋቂ። በ1992 በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ የሬድዋን ፓርቲ ከደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ተወዳድሮ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገቡ። ሬድዋን በፓርላማ በቆዩባት አጭር ወቅት በኢሕአዴግ ምን ያህል እንደ ተዋጡ ተገነዘቡ። ለፖለቲካ ግባቸው ስሕዴፓ ሳያንስባቸው አልቀረም።
ፓርላማ ከገቡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሬድዋን እና ጓዶቻቸው ስሕዴፓን አፍርሰው ድሮ ሲተቹት የነበረውን የአቶ ሲራጅን ስሕዴድ ተቀላቀሉ። የፓርላማ ውክልናቸውን ጥለው “የስልጤ ዞን የሕዝብ ጉዳዮች አደረጃጀት” ሐላፊ በመኾን እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ቆዩ። በ1997 ዓ.ም ከስልጤ ዞን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በመወዳደር የደቡብ ክልል ምክር ቤትን ተቀላቀሉ። ከዚያ በኋዋላ ነው የደቡብ ክልል ምክር ቤት የትምህርት ቢሮ ሐላፊ ብሎም የደኢሕዴን የሥራ አስፈጻሚነትን የተቀላቀሉት።
የስልጤ ዞን በምርጫ 97 ልክ እንደ ደሴት ነበረች። በዙሪያው የነበሩት አጎራባች ክልሎች በአብዛኛው የኢሕአዴግን ተቃዋሚዎች የመረጡ ሲኾን ስልጤ ግን ስህዴድን/ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን መርጣለች። በ97 ዓ.ም የነበረው የተቃዋሚዎች ማዕበል ጉዟቸውን አፋጥኖላቸዋል። በአምስት ዓመት ውስጥ ከወራቤ ከተማ ተነስተው የኢሕአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ “ወንጌል” ዋና አጥማቂ ኾነው ወጡ፤ በምድረ በዳ የሚጮሁ።
ኢሕአዴግ “ዱላ መቀባበል” በሚለው ጨዋታ “የፊት መሥመር ተሰላፊ የነበሩት ወደ ኋላ ኾነው፣ የድርጅት ሥራ የሚሠሩት ወደ ፊት የሚመጡበት ነው” በሚለው መሠረት “ትጉህ ባርያ” የነበሩት አቶ ሬድዋን የአቶ በረከት ስምዖን ቦታ ያዙ ተብሎ ። የሬድዋንም የተስፋ ምድር ይህች ነበረች። የአቶ በረከትን ቦታ ማግኘት
አቶ ሬድዋንን ኢሕአዴግ ግንባር ቀደም የምርጫ ተከራካሪ አድርጎ ለማምጣት በፓርቲው ውስጥ በዚሁ ታሪካቸው የተነሳ የሐሳብ ልዩነት እንደነበር ይነገራል። “ድሮ ይቃወመን በነበረ ሰው መወከል!” በሚል። ዋናው ነገር ሬድዋን ሥራቸውን አይዘነጉም። “የተለያዩ ማኅበራትን ታደራጃለህ”፤ “ከጀርባ ትቆጣጠራለህ”፤ የሚለው የፖለቲካ ቅኝት እየተሰጣቸው ለሚፈልገው ዓላማ ይሰናዳሉ። አቶ ሬድዋንም ይህችን አሠራር ከአዲስ አባባ የክፍለ ከተማ ስበሰባዎች፣ በፍቼ እና በአላጌ ተግብረዋታል። የአዲሱ በረከት ጠንካራ ጎኑም ይህ ነው።
እነ አቶ ሕላዌ መሠረቱን የጣሉለትን ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ የሚወስድ ግንባር ቀደም ካድሬ ይፈለግ ነበር። ኢሕአዴግ ዐይኑን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ጣለ። ደቡብ ኢትዮጵያ በፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት “የተካኑ” የሚባሉ ሰዎችን ማፍራት ይዟል። አቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ካሊድ አሕመድ፣ ሬድዋን ሁሴን፣ መኩሪያ ኀይሌ ከሌሎቹ አጋር የኢሕአዴግ ፓርቲዎች በላቀ ጎላ ብለው መታየት ጀምረዋል።
በወቅቱ የደቡብ ክልል የትምህርት ቢሮ ሐላፊ፣ የደኢሕዴን ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት አቶ ሬድዋን ሑሴን ደግሞ በተናጋሪነታቸው ይታወቃሉ። በዚያ ላይ የሕዝብ አደረጃጀት ልምድ አላቸው። የሁሉም ዐይን ሰውየው ላይ አረፈ። ሬድዋንም ወደ አዲስ አበባ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሐላፊነት ተመደቡ፡፡
ሥራው ቀላል እና ግልጽ ነው። “ፓርቲውን በሕዝብ ውስጥ ማሥረጽ።” “ከፍተኛ ቁጥር ያለው አባል መመልመል፤ የተመለመሉትንም ከእምነታቸው እንዳይናወጹ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ማስረጽ – ሁለተኛ ተፈጥሯቸው እስኪመስል። ” በከተማው አስተዳደር ውስጥ የፓርቲ ሥራ ከመንግሥት ሥራ ጋራ የጨው እና የውኃ ያህል እስኪወሃዱ ድረስ ሬድዋን እረፍት የላቸውም። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራጅተው የፓርቲውን ጥቅም በዘላቂነት እንዲያስከብሩ ይታትራሉ። ሬድዋን በሚመሩት የአዲስ አበባ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኙ አራት ወሳኝ የመመልመያ እና መከታተያ መዋቅሮችን ይመራሉ። የአባላት ሥልጠና፣ አነስተኛ እና ጥቃቅን እና ትምህርት፣ ግብር መልስ እና ሱፐርቪዥን እና የሕዝብ አደረጃጀት ናቸው።
ሁኔ አቢሲኒያዊ
ኦክስፎርድ ዩ.ኬ

የጠበቆች ማህበር በአርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ላይ የወንጀል ክስ መመስረታቸው ተሰማ


በአዲስ አበባ ታትሞ የሚወጣው ማራኪ መጽሔት እንደዘገበው በቅርቡ በሰይፉ ፋንታሁን የኢቢኤስ ሾው ላይ ቀርቦ በአዲስ ፊልሙ ላይ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቅሞ መስራቱን ለማህበረሰቡ ያሳየው አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ የጠበቆች ህብረት በጋራ የወንጀል ክስ አቅርበውበታል።
ጠበቃ ማቲያስ ግርማ ለማራኪ መፅሄት እንዳስረዱት በክሱ ላይ ሰይፉ ፋንታሁንና አለማየሁ ታደሰ ደጋፊ ሀሳብ በመስጠታቸው ክስ ይመሰረትባቸዋል ብለዋል። አርቲስቱ ምንም እንኳ ለፊልም ግብዓት “መስለው ሳይሆን ሆነው” ለመስራት ያደረጉት ተግባር ቢሆንም ህብረተሰቡን ከወንጀል ለመጠበቅ ሲባል ክስ እንደተመሰረተባቸው የጠበቆች ተወካዩ አስረድተዋል።

“ይህንን የበለጠ ማጣራት የነበረባቸው ፖሊስና አቃቤ ህግ ቢሆኑም ፣ በግልፅ በሀገሪቱ የአየር ክልል የተላለፈውን መረጃ ዝም ማለታቸው እንዳሳዘናቸውም ገልፀዋል። በሀገሪቱ የወንጀል ህግ ስርዓት በተለይ ግሩም በክሱ ጥፋተኛ ከተባለ እስከ ሰባት አመት እንዲሁም የ50ሺ ብር ቅጣት ይጠብቀዋል።

በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ 1996/97 አንቀፅ 525 ንዑስ አንቀፅ/ሀ መሰረት እስከ ” አደንዛዥ ዕፅን እራሱ ወይም ሌላ ሰው ሊጠቀምበት በማሰብ የገዛ፣የተጠቀመ፣ እንዲጠቀም ያደረገ፣,,,” ከ7 ዓመት እስከ 50ሺ ብር ቅጣት ይጠብቀዋል። እነ ሰይፉ ደግሞ “ወንጀልን ባለማወቅ” ክስ ተመስርቶባቸዋል።
መጽሔቱ ዘገባውን ሲያጠናቅቅ ለግሩም በቅርብ መጥሪያ ይደርሰዋል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።
Ze-Habesha