onsdag 7. mai 2014

“ሰልፉ የተካሄደው በእኛ ትዕግስትና ጥንካሬ እንጂ በመንግሥት አልተፈለገም” ”

May 7/2014
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታዩ የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ላይ ያተኮረ “የእሪታ ቀን” በሚል ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል። ሰላማዊ ሰልፉ ከተከናወነ በኋላ የፓርቲውን ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራውን አነጋግረናቸዋል።
ሰንደቅ፡- ባለፈው እሁድ (ሚያዚያ 26 ቀን 2006 ዓ.ም) የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ምን ያህል የተሳካ ነበር?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ሰልፉ እንዳይካሄድ ከነበረው ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ አንፃር ከፍተኛና ስኬታማ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር።
ሰንደቅ፡- ሕብረተሰብ ውስጥ አለ ካላችሁት ችግር አንፃር እንደምትጠብቁት በቂ የሆነ ሕብረተሰብ በሰላማዊ ሰልፉ ወጥቷል የሚል እምነት አላችሁ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ካለው ሁኔታ አንፃር አዎ። አንደኛ ለመቀስቀስ ዕድል አልሰጡንም። የሰላማዊ ሰልፉን እውቅና ያገኘነው በእኛ ትዕግስት እንጂ እውቅናውን መስጠት አልፈለጉም። ከሕግ ውጪ በሆነ መልኩ ሰልፉን ለማካሄድ ማንም ሰው መፈረም ቢችልም አመራሩ ካልፈረመ እውቅና አልሰጥም አሉ። ሶስት የፓርቲ አመራሮች ሄደው ፈረሙ። እኔ በአጋጣሚ በማኅበራዊ ጉዳይ ሀዘን ላይ ስለነበርኩ እሱም ካልመጣ በመባሉ ከሶስቱ አመራሮች በተጨማሪ እኔ አራተኛ እንድፈርም ተደርጓል። በእርግጥ የእኔ መፈረም ችግር አይመስለኝም። ነገር ግን ህግ የማክበር ጉዳይ አይደለም። ጊዜ የማጣበብ ጉዳይ ነው። ከዚህ ጎንለጎን ለቅስቀሳ የወጡ አባሎቻችንን አሰሩብን። እውቅና ያለው ሰልፍ መሆኑን እያወቁ አባሎቻችንን አሰሩ። ለምሳሌ የፓርቲያችን የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን፣ የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነብዩ ኃይሉ ታስሯል። እንደዚሁም ዘላአለም የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ታስሯል። ከዚህ አንፃር ስታየው ሰላማዊ ሰልፉ ስኬታማ ነበር።
ሰንደቅ፡- የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አጋርነታችሁን በሰልፉ ላይ ለመግለፅ ሙከራ ቢያደርጉም መከልከላቸውን ገልፀዋልና ለምን ተከለከሉ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ማንም ሰው አልተከለከለም። በእርግጥ እኔን አላገኙም። ነገር ግን በኋላ ሳጣራ ማንም ኢትዮጵያዊ በዚያ ሰልፍ መሳተፍ የእኛ ፍላጎት ነው። ነገር ግን እንደሰማሁት የእነሱን (የሰማያዊ ፓርቲ ማለታቸው) ቲሸርት የራሳቸውን አርማ ይዘው ለመካፈል ሞክረዋል የሚል ነው። እነሱ ሰልፍ ባካሄዱ ጊዜ የእኛ አባሎች የእነርሱን አርማና መፈክር ይዘው ነው የተሳተፉት። እና እነሱ የሰማያዊ ፓርቲን በአንድነት ሰልፍ ለማስተዋወቅ ሙከራ ያደረጉ ይመስላል። በእኛ አባላት በኩል ሰልፉ የአንድነት ፓርቲ መሆኑን በመግለፅ መፈክሩም፣ አካሄዱም በአንድነት ፓርቲ የሚመራ መሆኑ ተነግሮአቸዋል። ይሄ ደግሞ ትክክል ነው። በእኛ በኩል ሁሉም መፈክር ላይ ማህተም አድርገናል። ከዚያ ውጪ ያለው መፈክር እኛን እንደማይወክል ቀደም ብለን ሰርተናል። ባጅም አድለናል። እና ሰልፉ የሌላ ፓርቲ ማስታወቂያ ወይም መፈክር ማቅረቢያ አይደለም። በተጠየቅ (logic) ብታየውም ሁሉም የሰልፉ አካሄድ የአንድነት መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።
ሰንደቅ፡- በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል እንደተቋምም ሆነ እንደ ግለሰብ ያለው ግንኙነት ጤናማ ነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- እኔ እንደማስበው ይሄ ለጥያቄ የሚቀርብ አይመስለኝም። በእኛ በኩል በራሳችን ትዕግስት ሁሉንም ፓርቲ የምናየው በእኩልነት ነው። ከሁሉም ፓርቲ ጋር በጋራ ለመስራት በራችንን ከፍተናል። ከዚያም አልፎ የእኛ አላማ ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር ነው። እንግዲህ እነሱ በዚህ ላይ ይስማሙ አይስማሙ እነሱን መጠየቁ ይሻላል። አንድነት ግን ከሁሉም ፓርቲ አብሮ ለመስራት እስከውህደት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። 
ሰንደቅ፡- ባለፈው እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል ቀጣይ አቅጣጫችሁ ምንድነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- እሁድ እለት የተካሄደው ሰልፍ እራሱን የቻለ የአዲስ አበባ የፓርቲው መዋቅር ያዘጋጀው ነው። ይህንን እንደ ትልቅ መዋቅር ነው የምናየው። ከአዲስ አበባ ውጪም በሲዳማ እና በምስራቅ ጎጃም እንዲሁም በአዳማ ይኖረናል። እነዚህ አካላት በራሳቸው አየጠነከሩ የአቅም ግንባታ እንዲያደርጉ በማድረግ እንዲቀጥሉ ነው። ለምሳሌ በደራሼ ጊዶሌ ከተማ በተመሳሳይ እሁድ እለት ሰልፍ ተካሂዷል። ወዲዚያው አንድ የስራ አስፈፃሚ አመራርና የቀጠና አስተባባሪ ልከናል። ወደፊትም ዞኖቹ የራሳቸውን አቅም ገንብተው የማዕከል የፖለቲካ አቅም ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ይካሄዳል። ከዚህ ጎንለጎን የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ አሁን ለመሬትና ለፍትህ እየተካሄደ ነው። በቀጣይ ደግሞ በሶስተኛው ፌዝ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነትና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ” መርሀግብር ይኖረናል። ከሰኔ 30 በኋላ የሚጀመር ይሆናል። ይህም ፖለቲካውን ከአንድነት ወደ ሕዝብ የማውረድ እንቅስቃሴ ነው። ከዚህ ጎንለጎን በስትራቴጂው ዘርፍ አማራጭ ፖሊሲዎች የማዘጋጀት፣ የምርጫ ማኒፌስቶ፣ የምርጫ ስትራቴጂ ማዘጋጀትና የአማራጭ ፖሊሲ ትውውቅ ውይይቶች ይካሄዳሉ። በዚህም በአዳራሽ ስብሰባ የተለያዩ ምሁራን በተገኙበት የሚደረግ ይሆናል።
ሰንደቅ፡- ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የመዋሃዱ ጉዳይ ያበቃለት ጉዳይ ሆኗል ማለት ይቻላል?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ያበቃለት ነገር የሚባል ነገር የለም። በእኛ በኩል ለውህደት ሙሉ በሙሉ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ አንድ ጠንካራ አብይ ብሔራዊ ፓርቲ መፈጠር አለበት ብለን እናምናለን። ውህደትን እንደ ጠንካራ ግብ ስለያዝነው ምንጊዜም ቢሆን የምንቀጥልበት ጉዳይ ነው።
ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ከመሆኑ አንፃር የፖለቲካ ምህዳሩ በምን ደረጃ ላይ ነው ትላላችሁ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- የፖለቲካ ምህዳሩ በእጅጉ እንደተዘጋ ነው። ሰልፍ ማካሄድ ወደማንችልበት ደረጃ ነው የደረስነው። የትናንትናውን ሰልፍ ለማካሄድ አንድ ወር ፈጅቶብናል። የሰልፍ እውቅና ማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ ለፖለቲካ ምህዳሩ አለመስፋት ዋነኛ ምሳሌ ነው። ሕዝባዊ ስብሰባ አዲስ አበባ ውስጥ ለማካሄድ አስበን አዳራሽ አጥተናል። የአዲስ አበባ አስተዳደር የሁላችንም አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት ካልቻለ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ለሰልፍ አንድ ወር መፍጀት የለበትም። እኛም ታግሰን ሁኔታውን አክብረን እውቅና ሲሰጠን ማየት የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን አያሳይም። አሁንም ከሁለት ወር በፊት የጀመርነው የአዳራሽ ስብሰባ በአዳራሽ እጦት ማካሄድ አልቻልንም።
ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ሰላማዊ ሰልፍ ስታደርጉ አይታይም፤ አሁን ግን ወደ አደባባይ የመውጣቱ ሁኔታ ከመታየቱ አንጻር በፖለቲካ ምህዳር መስፋት በኩል የተሻሻለ ነገር አለ ብለው የሚያምኑ አካላት አሉና እርስዎስ ምን ይላሉ?
     ኢንጂነር ግዛቸው፡- አንተ ማየት ያለብህ ሂደቱን ነው። ሰልፉን በነፃነት እያካሄድን አይደለም። እውቅና ለማግኘት አንድ ወር እየፈጀብህ ምህዳሩ ሰፍቷል ማለት አይቻልም። ሰልፉ በእኛ ትእግስትና ጥንካሬ እንጂ በመንግስት በኩል አልተፈለገም። ሰልፍ ስናካሂድ ብዙ ሰዎች ይታሰራሉ እና ሰልፉ መካሄዱ አይደለም ዋና አላማው፤ ሂደቱ ላይ አሁንም ነፃ አይደለንም። ሂደቱ ላይ አሁንም አፈና ይካሄድብናል። የማስፈራራት ዘመቻው ከፍተኛ ነው። ሚዲያው ሙሉበሙሉ የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ማስተላለፊያ ሆኗል። እኛን አያስተናግደንም። የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ሰልፉን እንደምናካሂድ ማስታወቂያ አዘጋጅተን ሄደን ተከልክለናል። የፍትህ አካላት አካባቢም ችግር አለ። የእኛ አባላት በመኪና ስለቀሰቀሱ ለአስር ቀናት ፖሊስ አሰራቸው። ሕግ አስከባሪውም በሕገ-መንግስቱ መሰረት እየሰራ አይደለም። ነፃ የሲቪል ማህበረሰብ የለም። ያሉትም የኢህአዴግን ቡራኬ ያገኙ ናቸው። እና ከድሮው በጣም ተዘግቷል። ሚዲያው ሚዛናዊ መሆን ሲገባው በእኛ ላይ ፕሮፓጋንዳ ያደርጋል እና ደምረው ስታየው በእጅጉ እየተዘጋ ነው።

mandag 5. mai 2014

አንድነት ፓርቲ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረገ! (ቪዲዮ እና ፎቶዎች ይዘናል)
ኢ.ኤም.ኤፍ) – ዛሬ ሜይ 4 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። የሰላማዊው ሰልፍ ጥሪ ለመጀመሪያ ግዜ በሸገር ሬድዮ የተላለፈ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ማስታወቂያውን “አላቀርብም” ብሎ የነበረው ኢቲቪ ከሰልፉ በኋላ፤ የተቃውሞውን ምስል ቆራርጦም ቢሆን በዜና እወጃው ላይ አቅርቦታል።
ሰልፉ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የተደረገ ነው። ከዚህ ቀደም በሰበብ አስባቡ ሲከለከል የነበረው “የእሪታ ቀን” ዛሬ እውን ሲሆን፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሰልፉን ተቀላቅለውታል።
"መንገድ ዘግታችኋል ቶሎ ቶሎ ሂዱ" ፖሊስ። "መንገዱ ለኛ የተፈቀደ ነው ሰዓታችንን እንዴት እንደምንጠቀም እናውቃለን" አመራሮች
አንድ ሁኔታውን የታዘቡ ግለሰብ እንዲህ ዘግበዋል። “የዛሬውን የአንድነት ፓርቲ ህዝባዊ ተቃውሞን በቦታው ተገኝቼ እንደታዘብኩት” ብለው ነው የጀመሩት… በዛሬው እለት ከጠዋቱ ሶስት ሰዐት ጀምሮ በርካታ የከተማይቱ እና የአካባቢው ነዋሪዎች የተገኙበት ታላቁ የእሪታ ቀን በድምቀት የተካሄደ ሲሆን በሠልፉ ላይ በርካታ መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡
በዛሬው የሰላማዊ ሰልፍ ያሬድ አማረ ወኔ የተሞላባቸውን መፈክሮች ሲያሠማ የነበረ ሲሆን ከእርሱ መፈክሮች በተደጋጋሚ ከጓደኞቼ ጋር ፈገግ ሲያደርገን የነበረው “እመነኝ” የሚላት ቃል ናት፡፡
በሰለማዊ ሰልፉ ከኢ/ር ግዛቸው እስከ ወጣቱ ሃብታሙ አያሌው  ድረስ ያሉ ፖለቲከኞች በብዛት ይታዩ ነበር፡፡ ዳዊት ሰለሞን የአንድነት መኪና ውስጥ ሆኖ መረጃዎችን በማህበራዊ ድህረ ገፆች ሲያከፋፍል…. ነበር፡፡
ሁሉም ነገር ባዶ!
ሰልፉ በአድዋ ድልድይ አድርጎ የመከላከያ ቤተሰቦች መኖሪያ ኢካባቢ በተለምዶ ሲግናል ተብሎ ከሚጠራው የመካላከያዎች ቤት ውስጥ የሚኖሩ የስርዐቱ ደጋፊዎች በተደጋጋሚ በመሀል ጣታቸው ሰልፈኛውን በመሳደብ ስሜታዊ ለማድረግ ሲሞክሩ ነበር፡፡
ሰልፉ በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ወረዳ 8 ፊት ለፊት በሚገኘው ሜዳ ላይ ኢ/ር ግዛቸው ባደረጉት ንግግር ተቋጭቷል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የአመራር አባል የሆነው ሃብታሙ አያሌው ሲያደርግ የነበረውን
ይመልከቱ።
እኛ ስለሰላማዊ ሰልፉ ተጨማሪ ዝርዝር ከምንሰጥበት የበለጠ እነዚህ ፎቶዎች እና መፈክሮች ብዙ ይናገራሉና… የአንድነትን ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ በፎቶ የተደገፈ እንቅስቃሴ፤ ከዚህ በታች  ይመልከቱ።

søndag 4. mai 2014

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አንድነት የጠራውን የሰላማዊ ሰልፍ እንደሚቀላቀሉ አስታወቁ

May 3, 2014
በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የሰነበቱትና ቀሪዎቹ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ዛሬ ባደረጉት ሳምንታዊ የወጣቶች የውይይት ፕሮግራም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) የ‹‹እሪታ ቀን›› በሚል የጠራውን ሰልፍ በግንባር ቀደምነት በመቀላቀል ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ አስታውቀዋል፡፡
ወጣቶቹ ሰልፉን እንደሚቀላቀሉ ያስታወቁት ‹‹ሰላማዊ ሰልፉ ውጤታማ እንዲሆን በምን መልኩ ልናግዝ እንችላለን?›› በሚል አጀንዳ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከውህደት በዘለለ በሰላማዊ ሰልፍም ሆነ በሌሎች የትግል ስልቶች መተባበርና አብሮ መስራት እደግፋለሁ የሚል አቋም እንደሚያራምድ በተለያዩ ሚዲያዎች መግለጹ የሚታወቅ ሲሆን ወጣቶቹ በሰላማዊ ሰልፉ የሚያደርጉት ተሳትፎ ፓርቲው ለትብብር ያለውን አቋም ያሳያል ብለዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለሰላማዊ ሰልፉ ድምቀት የሚያገለግሉ ሜጋ ፎኖች፣ ጥሩምባዎችና ሌሎችም ሰልፉን ለማድመቅ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ይዘው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
Addis Ababa Semayawi party rally April 27, 2014

fredag 2. mai 2014

ኢቴቪ በራሺያ ፍቅር ዩክሬንን ጠምዷታል፤ መዘዙ ለአገራችን ነው

 የአገራችን የመንግስት ቴሌቪዢንና ሬድዮ፣ ለበርካታ ሳምንታት በራሺያና በዩክሬን “ድራማ” ዙሪያ ያለማቋረጥ የሚያሰራጩት ነገር፣ ለአገራችን ምን አይነት መዘዝ እንደሚያስከትል የተገነዘቡት አይመስልም። “ድራማው”፣ የሚያሳዝንና የሚያሳስብ እንጂ፣ የሚያስቦርቅና የሚያስፈነድቅ ድራማ አይደለም። በጠበኛ እብሪት የተለከፈው የራሺያ መንግስት  ዋና አቀናባሪነትና ስፖንሰርነት በሚመራው በዚሁ ድራማ፤ ዩክሬን በጎሳና በሃይማኖት ስትሰነጣጠቅ እየታየ ነው። እና፣ ይሄን እያዩ በደስታ ጮቤ መርገጥ ተገቢ ነው?
የውጭ ጠበኞች የሚያሴሩባትና የውስጥ ጣጣዎች የሚያስቸግሯት አገርኮ ዩክሬን ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያም፣ ከሩቅና ከቅርብ፣ በጎሳም ሆነ በሃይማኖት ሰበብ “እንበጥብጣት” የሚሉ (የራሺያ አይነት)የውጭ አገር ጠበኞች አሉባት። አንዳንድ የግብፅ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ ሲዝቱ ሰምተናልኮ። ለብጥብጥ የሚሆን ሰበብ ደግሞ ሞልቷል። አገራችን፣ከጎሳና ከሃይማኖት ጋር የተቆራኙ ነባርና ኋላቀር የውስጥ ጣጣዎች የሉባትም እንዴ? እንደ ዩክሬን ለአደጋ የሚያጋልጡ የአገራችን ጣጣዎች ጥቂት አይደሉም። የራሺያ መንግስትና የኬጂቢ ኮለኔል የነበሩት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ በዩክሬን ላይ የሚያካሂዱት ዘመቻ ድብቅ ሚስጥር አይደለም። የግብፅ መንግስት፣ የሶማሌ ክልል ተወላጆች እንዲገነጠሉ በማሴር፣ “የራሳቸውን እድል በራሳቸው ይወስኑ” እያለ ዘመቻ ቢያካሂድ እንደማለት ነው። ከኢትዮጵያ ጎን የሚሰለፍ አለኝታ ይኖራል? ምናልባት፣ ዩክሬንንም ከጥቃት የሚያድን አለኝታ መንግስት አይኖር ይሆናል። ግን፣ አነሰም በዛ ከጎንሽ ነን ብለው የሚከራከሩላት የአሜሪካና የአውሮፓ ወዳጅ መንግስታትን አላጣችም። ኢቴቪ ይህንንም ሲያወግዝ ነው የምንሰማው። በራሺያ ሴራ ዩክሬን ስትሰነጣጠቅ እያየን ብንቦርቅ፣ በራሳችን ላይ መዘዝ መጋበዝ እንደሆነ እነኢቴቪ እንዴት አልተረዱትም?
በእርግጥ የራሺያና የዩክሬን ጉዳይ፣ እዚሁ ለአገራችን የራሱ አንደምታና ትርጉም እንደሚኖረው እነ ኢቴቪ አያውቁም ማለቴ አይደለም። ትርጉም እንዳለው ስለሚያምኑማ ነው፤ ነገሩን እንደራሳቸው ጉዳይ የእለት ተእለት ዘመቻ ያደረጉት። በእርግጥ፣ “ዜና ወይም ዘገባ አሰራጨን እንጂ ዘመቻ አላካሄድንም” ሊሉ ይችላሉ። ግን፤ዜና ወይም ዘገባ ማሰራጨት ሌላ! በራሺያ ፍቅር የታወረ እስኪመስል ድረስ፤ በዩክሬንና በምዕራብ አገራት ላይ ጭፍን የጥላቻ ዘመቻ ማራገብ ደግሞ ሌላ! የኢቴቪ ዜናዎችና ዘገባዎች፣ በስሜት የጦዘ “ቲፎዞ” ከሚሰነዘረው ጭፍን አስተያየት አይለዩም። ጭፍን አስተያየት፣ በዜና ወይም በዘገባ ስም ሲቀርብ ምን ይባላል? “ፕሮፓጋንዳ” ይባላል። ሌላ መጠሪያ ስም የለውም። ለዚያውም ማንንም የማይጠቅምና ሁሉንም የሚጎዳ ቀሽም ፕሮፓጋንዳ!
ፕሮፓጋንዳ በተፈጥሮው፣ እውነተኛ መረጃዎችን በማጥፋትና በማግለል፣ በማጣመምና በማድበስበስ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዳይፈጠር ስለሚያግድ ጎጂ ነው። ከረዥም ጊዜ አንፃርም፣ የእውነትን ክብር በመሸርሸር፣ በሁሉም ተቀናቃኝ ቡድኖች ዘንድ ጭፍንነት እየተስፋፋና ስር እየሰደደ እንዲሄድ ያደርጋል። የኢቴቪ ፕሮፓጋንዳ ቀሽምነት ግን፣ ከዚህም ይብሳል። ብዙ ሰዎች ወደ ፕሮፓጋንዳ የሚሮጡት፣ ውሎ አድሮ እንደሚጎዳ ስለማያውቁ፤ ወይም ደግሞ ጎጂነቱ ባይጠፋቸውም ለማያዛልቅ የአጭር ጊዜ ጥቅም እጅ ስለሚሰጡ ነው። የኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ ግን፤ቅንጣት ታህል የአጭር ጊዜ ጥቅም የለውም። ከንቱ ድካም ነው። “ከንቱ ድካም” ሲባል ግን፤ እርባና ቢስነቱን ለመግለፅ ያህል እንጂ፤ “ምንም ውጤት አያመጣም” ለማለት አይደለም። መጥፎ ውጤት ያስከትላላ – አገሪቱንና ነዋሪዎቿን ለአደጋ በሚያጋልጥ የተሳሳተ አስተሳሰብ የተቃኘ ፕሮፓጋንዳ ነዋ። “እርባና ቢስ ነው” የምለውም፤ ኢቴቪ ወደ ፕሮፓጋንዳ እንዲገባ የሚገፋፋ መነሻ ሰበብ የለም ማለቴ አይደለም።
ለግንዛቤ የሚያስቸግር ውስብስብ ጉዳይ አይደለም። በጭላንጭልም ቢሆን አይኑን በመክፈት ለአንድ አፍታ ከጭፍንነት ለመራቅ ፈቃደኛ የሆነ ሰው፣ በቀላሉ ሊገነዘበው ይችላል። የራሺያ መንግስት በዩክሬንና በሌሎች ጎረቤት አገራት ላይ የሚሸርበው ሴራና የሚያካሂደው ዘመቻ፤ የኤርትራ መንግስት በጎረቤቶቹ ላይ ከሚፈፅማቸው ጠበኛ ድርጊቶች ብዙም አይለይም። ይሄ አጥፊ ተመሳሳይነት ለኢቴቪ የማይታየው ለምን ይሆን? የፕሮፓጋንዳው መነሻ ሰበብስ ምንድነው? የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ አንድ ነው -“የቀለም አብዮት”!
መንግስት፣ ኢህአዴግ ወይም የመንግስት ሚዲያ፣ ለበርካታ አመታት በ“ቀለም አብዮት” ላይ ብቻ ክፉኛ ስላፈጠጡ፤ ዛሬ ዛሬ ሁሉም ነገር “የቀለም አብዮት” እየሆነ ይታያቸዋል። ሊያሳስባቸው አይገባም ማለቴ አይደለም። የስልጣን ጉዳይ ነውና ቢያሳስባቸው አይገርምም። እንዲያውም፤ እነሱን ብቻ ሳይሆን፤ ማንንም ሰው ሊያሳስበው ይገባል። “የመጣው ይምጣ” ወደሚል ተስፋ ቢስነት ለዘቀጠ ሰው ወይም “ሳይደፈርስ አይጠራም” ከሚል አላዋቂነት ላልተላቀቀ ሰው ካልሆነ በቀር፤  ነባሩን አስተዳደር የሚያናጋ እንቅስቃሴ ሲፈጠር ማንኛውም ጤናማ ሰው በጥሞና ማሰብ ማሰላሰል ይኖርበታል። “ለውጥ” በቁንፅል ለጤናማ ሰው በቂ አይደለም። የተሻለ ነገር ለማምጣት የሚያስችል መሆን አለበት – “ለውጥ”። “የመጣው ይምጣ” ብሎ በጭፍን መደናበር ግን ጤንነት አይደለም። “የባሰ ቢመጣስ?” የሚል ጥያቄ አለና ነው። ጤናማና ብልህ ሰው፤ ነገሮች ጥርት ብለው እንዲወጡ ለማድረግ ከመነሻው አስበው፣ መላ አበጅተውና መድረሻቸውን አቅደው ይጣጣራሉ እንጂ፤ “መጀመሪያ ይደፍርስ፤ ያኔ የደፈረሰውን ለማጥራት እናስብበታለን” ብለው በጭፍን አይገቡበትም። “ከደፈረሰ በኋላ ባይጠራስ?” የሚል ጥያቄ አለና ነው። 
በተጨባጭ ያለውን እውነታ ከመነሻው በአግባቡ መገንዘብ፤ ወደፊት የሚመኙትን የተሻለ ሕይወት በቅጡ ለይቶ መድረሻውን ማወቅ፤  ከመነሻ ወደ መድረሻ የሚጓዙበት ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ ያስፈልጋል። ተጨባጩን እውነት፣ የለውጡን መንገድ እና የታለመውን ሕይወት፣ … ሦስቱንም አስተሳስሮ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ከተገነዘብን፤በዘመናችን “የቀለም አብዮቶች” ተብለው የሚጠሩ “የለውጥ እንቅስቃሴዎችን” ሁሉ በጅምላ እየፈረጁ በደፈናው መደገፍም ሆነ መቃወም፤ ከአላዋቂነት ወይም ከጭፍንነት የዘለለ ትርጉም እንደማይኖረው ይገባናል። ለምን? “የቀለም አብዮቶች” ሁሉ እኩል አይደሉም። የብዙ ሰዎችን (የሕዝብን) ትኩረት በመማረክ የሚጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴ ከመሆናቸው በስተቀር፤ ብዙም ተመሳሳይነት የላቸውም። በተነሱበት እውነት፣ በመረጡት መንገድና ባለሙት የሕይወት ግብ ይለያያሉ።
ለምሳሌ የመጀመሪያው የቀለም አብዮት ነው ተብሎ በኢህአዴግ መፅሔት የተጠቀሰው፤ “velvet revolution”ን ተመልከቱ። በ1982 ዓ.ም ቼኮዝላቫኪያ ተብላ ትጠራ በነበረችው አገር የተካሄደ የለውጥ እንቅስቃሴ ነው። ያኔ የነበረው እውነታ ምን ነበር? አፈና በሰፈነበት የኮሙኒስት ስርዓት ውስጥ፤ በነፃነት ማሰብና ሃሳብን መግለፅ፣ ማንበብና ሃሳቦችን መቀበል ወንጀል ነበር። የሰዎች ስራ፣ ምርት፣ ንብረትና ኑሮ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ነው። ከኮሙኒስት ፓርቲው ውጭ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ መሰንዘርም ሆነ ፓርቲ ማቋቋም ወንጀል ነው። የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት የለም። በአጠቃላይ፤ በስለላ የታመቀ፣ በአፈና የደነዘዘ፤ በመንግስት ቁጥጥር የተራቆተና የደኸየ ኢኮኖሚ፤ በራሽን የታጠረና መላወሻ ያጣ ኑሮ፤ … በአጠቃላይ እያንዳንዱ ሰው ፓርቲንና መንግስትን በባርነት የሚያገለግል አቅም አልባ፣ ምስኪንና ክብረቢስ ፍጥረት ተደርጎ የሚቆጠርበት የውርደት ሕይወት ነበር። በአጭሩ በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ሕይወት ብዙም አይለይም። የነፃነትን ጭላንጭ የሚዘጋ፣ የብልፅግናን እድል የሚሰብር፣ የእኔነትን ክብር የሚያኮላሽ የኮሙኒዝም ስርዓት።
ደግነቱ፤ ሰው ብርቱ ነው። ከፍርሃትና ከአፈና የመላቀቅና የነፃነትን አየር የመተንፈስ ሰውኛ ፍላጎት ጠፍቶ አይጠፋም። መላወሻ ከሌለው የመንግስት ጭሰኝነትና ከንብረት አልባነት ተገላግሎ ንብረት የማፍራትና ብልፅግናን የመቋደስ ምኞት ተዳፍኖ አይቀርም። የካድሬና የቀበሌ ሊቀመንበር ሎሌ፤ የሚሊሻና የታጣቂ መጫወቻ ከመሆን ተገላግሎ፣ አንገትን ቀና አድርጎ ሕይወትንና ሰላምን የማጣጣም ህልም ብን ብሎ አይሰወርም።
በኮሙኒስት ስርዓት ውስጥ የነበረው እውነታ፤ በአፈናና በፍርሃት፣ በዝርፊያና በድህነት፣ በሸክምና በውርደት የተሞላ ኑሮ ነው። ወደፊት የተመኙት ሕይወትና ያለሙት መድረሻስ ምን ነበር? የነፃነት አየርን መተንፈስ፣ የብልፅግና እድልን መቋደስና የሕይወትን ጣዕም ማጣጣም ነው። በእርግጥም፤ ከአብዮቱ በኋላ፤ የግል ሚዲያና የፖለቲካ ምርጫ ተጀመረ። የግል ንብረትና የቢዝነስ ስራ ተፈቀደ። አንገትን ቀና አድርጎ የመራመድ የእፎይታና የሰላም መንፈስም ተገኘ። በእርግጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት እንዲሁም ሰው የመሆን ክብር በተሟላ ሁኔታ ሰፍኗል ማለት አይደለም። ግን ከድሮው በእጅጉ በእጅጉ ይሻላል። በከፊልም ቢሆን፤ ወዳለሙትና ወደተመኙት መድረሻ የሚያሸጋግር መልካም ለውጥ እውን ሆነ ማለት ነው። እንዴት?  በምን አይነት የለውጥ እንቅስቃሴ? አደባባዮችንና ጎዳናዎችን በሚያጥለቀልቁ የተቃውሞ ሰልፎች ነው፣ የቀድሞው አምባገነን የኮሙኒስት ስርዓት ፈርሶ ለውጥ የመጣው። 
እንግዲህ፤ የአገሬው ሰዎች ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ቃኝተናል – መነሻቸውን። የመጣውን ለውጥ ተመልክተናል – መድረሻቸውን። የተጓዙበትን አቅጣጫ አይተናል- መንገዳቸውን። ከዚህ ውስጥ ምን የሚያስወቅስ እንከን አገኛችሁበት? በተቃውሞ ሰልፍ ከአምባገነንነት መላቀቃቸውና ለውጥ ማምጣታቸው ያስወቅሳቸዋል? ደም ሳይፈስ በተቃውሞ ሰልፍ ብቻ መልካም ለውጥ መገኘቱ መታደል ነው። የሚያስሞግስ እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም። ሌላው ቀርቶ፤ የመቶ ሺዎችን ህይወት የቀጠፈና የሚሊዮኖችን ኑሮ ያናጋ ጦርነት ተካሂዶ በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣቱስ ያስወቅሳል እንዴ? ነውጠኛና አመፀኛ ብለን ኢህአዴግን ማውገዝ ተገቢ ነው? በጭራሽ። በእርግጥ፣ በጠባቡም ቢሆን ሃሳብን የመግለፅና በምርጫ የመሳተፍ እድል ባለበት አገር፤ “ለውጥ አመጣለሁ” ብሎ ወደ ጦርነት መግባት ተገቢ አይደለም። ሃሳብን የመግለፅና ምርጫ የማካሄድ እድል እየተዘጋ ካልሄደ በቀር፣ እንኳን በጦርነት ይቅርና በጎዳና ሰልፎች መንግስትን ለመለወጥ መነሳትም፤ ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ አለ። በተለይ ደግሞ፣ ከነባሩ ስርዓት በእጅጉ የተሻለ መልካም ለውጥ እንደሚመጣ በእርግጠኝነት የማናውቅ ከሆነ፤ ነገር ማደፍረስ ጥቅም የለውም። በስሜት ደረጃ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ከመመኘት ባሻገር፤ የምንመኛቸውን ነገሮች እውን ለማድረግ ምን አይነት ስርዓት እንደሚያስፈልግ በትክክል ካላወቅንና መድረሻችንን በቅጡ መለየት ካቃተን፤ “የለውጥ እንቅስቃሴ” ሁሉ ከንቱ ይሆናል። የእነ ግብፅ እና የእነ ሊቢያ አብዮቶች፤ እንዲሁም በጆርጂያና በዩክሬን የተካሄዱ ፀረ ራሺያ አብዮቶች በዚህ ጎራ የሚመደቡ ናቸው። በነባር ችግሮች እየተማረሩ የተሻለ ነገር ከመመኘት በስተቀር፤ መድረሻቸውን በግልፅ ለይተው ባለማወቃቸው፤ብዙም ሳይራመዱ ለቀውስ ተዳርገዋል። 
ግን ከእነዚህም የባሰ ሞልቷል። የተሻለ ነገር በመመኘት ሳይሆን ወደ ባሰ ክፉ ስርዓት ለመጓዝ የሚካሄዱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች አሉ። የሶሪያ እና የሴንትራል አፍሪካ ቀውሶችን መጥቀስ ይቻላል። በራሺያ አቀናባሪነት ዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ፀረ ምዕራብ አገራት እንቅስቃሴም፣ ከዚሁ የጥፋት ጎራ የሚመደብ ነው።
ፀረ ራሺያ አቋም የያዙ ዩክሬናዊያን አደባባዮች ማጥለቅለቅ “ለውጥ” ለማምጣት ተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱ፤ መንግስት በወሰደው እርምጃ ከመቶ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህ በኋላ ነው፤ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ተባርረው መንግስት የተለወጠው። ኢቴቪ ይህንን ምን ይለዋል? መፈንቅለ መንግስት ብሎ ይጠራዋል። በምርጫ ስልጣን የያዘ መንግስት የፈረሰው፣ “የቀለም አብዮተኞች” ባካሄዱት መፈንቅለ መንግስት ነው በማለት ኢቴቪ በየእለቱ ሳያወግዝ አያልፍም። በመንግስት ስለተገደሉት ሰዎች አንዳችም የትችት አስተያየት አይሰነዝርም። 
በራሺያ የሚደገፉ ዩክሬናዊያን፣ በክሬሚያ እና በሌሎች ምስራቃዊ ክልሎች ምን አይነት “የለውጥ እንቅስቃሴ” እንደሚያካሂዱ ተመልከቱ። በተቃውሞ ሰልፍ አልያም በታጣቂ ቡድኖች አማካኝነት፣ አደባባዮችን ብቻ ሳይሆን የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በሃይል ይቆጣጠራሉ። መንግስት መስሪያ ቤቶቹን ለማስለቀቅ ሲሞክር አምስት ሰዎች ተገድለዋል። ኢቴቪ ስለተገደሉት ሰዎች ሲናገር፤ 5 የነፃነት ታጋዮች ተገድለዋል በማለት ነው የገለፀው። ለማንኛውም “የነፃነት ታጋዮቹ” በሃይል የተቆጣጠሯቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች አልተለቀቁም። እናም በራሺያ የሚደገፉት “የቀለም አብዮተኞች” ፤ በምርጫ ስልጣን የያዙ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችን ለማፍረስ ችለዋል። በእርግጥ ኢቴቪ እነዚህን፣ የቀለም አብዮተኞች አይላቸውም። የራስን እድል በራስ የመወሰን መብታቸውን ለማስከበር የሚጠይቁ የነፃነት ታጋዮች እያለ ነው የሚጠራቸው።
ክሬሚያ የተሰኘው የዩክሬን ክልል እንዲገነጠልና ወደ ራሺያ እንዲጠቃለል የተደረገውም፤ እነዚሁ በራሺያ የሚደገፉ “የቀለም አብዮተኞች” (በኢቴቪ አጠራር “የነፃነት ታጋዮች”) ባካሄዱት የተቃውሞ ዘመቻ አማካኝነት ነው – በምርጫ ስልጣን የያዘውን አስተዳደር በሃይል በመቆጣጠርና በማፍረስ።
በአንድ በኩል፤በምርጫ ስልጣን የያዙ ፕሬዚዳንት በተቃውሞ አመፅ ከስልጣን ሲባረሩ፤ “በቀለም አብዮተኞች የተፈፀመ ትልቅ ወንጀል ነው” ተባለ። እሺ። በሌላ በኩል፤ በምርጫ ስልጣን የያዙ የክልል ፕሬዚዳንቶችና የከተማ አስተዳዳሪዎች፤ በተቃውሞ አመፅ ሲባረሩስ? “በነፃነት ታጋዮች የተገኘ ትልቅ ድል ነው” ተባለ። ታዲያ እንዲህ አይነቱ ፕሮፓጋንዳ እዚያው እርስ በርሱ የሚጣፋ ከንቱ ድካም አይደለምን? ለአጭር ጊዜ የሚያገለግል ጥቅም እንኳ የለውም። ይልቅ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ጉዳት አለው። እንዴት በሉ። በራሺያ አቀናባሪነትና ድጋፍ፣ የክሬሚያ ክልል ከዩክሬን ተገንጥሎ ወደ ራሺያ መጠቃለሉ፤ በኢቴቪ ቤት “የነፃነት ትግል” ነው። ይህንን ሁኔታ ወደ አገራችን አምጥተን እንየው።  ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ “በቀለም አብዮት” መንግስት ተለወጠ እንበል። ከዚያስ? ከዚያማ ልክ የራሺያ መንግስት እንዳደረገው፤ የሶማሊያ መንግስትም የኢትዮጵያ አካል የሆነው የሶማሌ ክልል እንዲገነጠል ድጋፍ ይሰጣል። የክልሉ መስተዳድር ስልጣን የያዘው በምርጫ ቢሆንም፤ በሶማሊያ መንግስት ስፖንሰር አድራጊነትና በተቃውሞ ሰልፈኞች አማካኝነት እንዲፈርስ ይደረጋል እንበል። ከዚያም በሶማሊያ መንግስት ወታደራዊ አለኝታነት ተማምነው፤ የኢትዮጵያን ህገመንግስት በሚጥስ መንገድ የሶማሌ ክልል እንዲገነጠል በምርጫ አስወስነናል ይላሉ፤ ወደ ሶማሊያ እንዲጠቃለልም ያደርጋሉ። ምናባዊ ታሪክ ነው። ነገር ግን ከእውነተኛው ታሪክ ጋር ያን ያህል አይራራቅም። እስከዛሬ አልተሳካም እንጂ፤በርካታ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ለረዥም አመታት ያቀነቀኑትን አቋም እንዲሁም በተደጋጋሚ ያካሂዱትን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሙከራ ስንመለከት፤ ምናባዊው ታሪክና እውነተኛው ታሪክ ተቀራራቢ መሆናቸውን ለመገንዘብ አይከብድም። 
ለነገሩ ከላይ እንደጠቆምኩት፤ የኤርትራ መንግስት ጠበኛ ባሕሪዎችንም መመልከት ይቻላል። ለወጉ ያህል እንኳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲንቀሳቀሱ የማይፈቅድ፣ ሌላው ቢቀር ለወጉ ያህል እንኳ ዜጎች በምርጫ እንዲሳተፉና ሶስት አራት ነፃ ጋዜጦች እንዲታተሙ እድል የማይሰጥ፣ ከጎረቤቶቹ ሁሉ የባሰ የለየለት አምባገነን መንግስት ነው። ነገር ግን፤ የተለያዩ ክልሎችን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚፈልጉ ቡድኖችን እያሰባሰበ ይደግፋል፤ እያስታጠቀ ያሰማራል – የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በሚል መፈክር እያሳበበ። እንዲህ አይነቱ ዘመቻ እንዴት እንደ ነፃነት ትግል ይቆጠራል?       
 አንድ የጥንት አባባል አለ – “ምን ያለበት ምን አያወራም” የሚል አይነት። አባባሉን ከዘመናዊ አኗኗር ጋር እንዲጣጣም ከፈለግን፤ “መስተዋት ውስጥ የተቀመጠ፣ ስለ ድንጋይ ውርወራ አያወራም” ልንለው እንችላለን። በመላው ዓለም ብዥታና ግርግር በበዛበት ዘመን ነው የምንኖረው። ከኋላቀርነትና ከግጭት ያልተላቀቀ አህጉር ውስጥ ነው ያለነው – ለዚያውም ለበርካታ አስርት አመታት ባልረገበ ጥላቻና ባልተቋረጠ ግጭት የሚታመሰው የአፍሪካ ቀንድ!  በዚያ ላይ፤ ከኋላቀር የጎሳና የሃይማኖት ጣጣዎች ጋር ስትዳክር ዘመናትን ያስቆጠረች ናት – አገራችን። እዚህ ውስጥ ሆነን፤ የድንጋይ ውርወራን እያዳነቅን ባናወራ ያሻላል።
Source-www.addisadmas.com

ሰበር ዜና- የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) ፕሬዝደንት ጋዜጠኛ በትረ ያቆብ ተሰደደ

May 2, 2014
Journalist Betre Yakobከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት በአፍሪካ ህብረት ጋባዥነት የኢትዮጵያን ችግርና አፈና በተለይ በሚዲያው ላይ ያለውን ጫና እና ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን አፈና ለመግለጽ ወደ አንጎላ አቅንተው ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለአፍካ ህብረትም የመፍትሄ ሀሳብ ማቅረቡና ለሰብአዊ መብት ኮሚሽነሩም መልስ መስጠቱ ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛ በትረ ያቆብ ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ አገሩ ለመመለስ በሚዘጋጅበት ወቅት የዓለም አቀፍ የጋዜጠኛ ማህበራትን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ እሱን ለማሰር የተደረገው ዝግጅት በተጨባጭ ማስረጃ ስላቀረቡለት መሰደዱን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች በታሰሩበት ወቅት ፖሊስ የበትረ ያቆብን ቤት በመፈተሸ ያገኘውን ወረቀት ሁሉ እንደወሰደም ምንጮቻችን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ጋዜጠኛ በትረ ያቆብ አንጎላ በተደረገው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ኮሚሽነሩን በግል እንዳገኛቸውና ኮሚሽነሩም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ በመግለጽ እንዲሚያገኙት ቃል ገብተውለት እንደነበር ተገልጿል፡፡ በተጨማም ከበርካታ የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና በሚዲያው ላይ ስለሚደረገው ጫና የተወያዩ ሲሆን አብዛኛዎቹ በተለያዩ መንገዶች እገዛ ለማድረግ ቃል ገብተውለት እንደነበር ከታማኝ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በስብሰባው ወቅት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገልጹ ጽሁፎች ለተሰብሰብሳቢዎቹ ተበትነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ መቋቋም ያስፈራቸው ሌሎች የጋዜጠኞች ማህበራት በትረ ያቆብን ለሂውማን ራይትስ ዎች፣ ለሲፒጄ፣ ለአርቲክል 19ና ሌሎች የጋዜጠኞች ማህበራት ይሰራል፣ ይሰልላል፣ የእነዚህ ድርጅቶች ተላላኪ ነው፣ ሪፖርት ይጽፋል በሚል በመግለጫቸውና ‹‹የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ›› በተባለው ፕሮግራም ይከሱት እንደነበር ጋዜጠኛ በትረ ያቆብ አገር ውስጥ በነበረበት ወቅት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻል፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia

torsdag 1. mai 2014

ሰበር ዜና፣ በጎንደር ተኩሱ ቀጥሏል፣ በግጭቱ 6 ሰው ሞቷል May 1, 2014

ነገረ-ኢትዮጵያ – ጎንደር ከተማ ውስጥ ቀበሌ 18 ልዩ ቦታ አርምጭሆ ሰፈር፣ ገንፎ ቁጭና ህዳሴ የተባሉ ሰፈሮች የከተማው አስተዳደር ‹‹ህገ ወጥ ሰፈራ ነው፡፡›› በሚል ቤቶችን ለማፍረስ መዘጋጀቱን ተከትሎ አፍራሾቹ ከህዝብ ጋር በፈጠሩት ግጭት ከ6 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸውንና መታሰራቸውን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ግጭቱ ከሶስት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ተኩል ድረስ ቀጥሎ የነበር ሲሆን ምንጫችን ደውሎ በሚነግረን ወቅት (ከቀኑ 6፡ 43) ተኩስ እንደነበር ለመረዳት ችለናል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎቹ ሚያዝያ 7/2006 ዓ.ም ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ትዕዛዝ በተላለፈበት ወቅት ህገ ወጥ አለመሆናቸውን፣ ካልሆነም መንግስት ቅያሬ ቦታና ጊዜ መስጠት እንዳለበት በመግለጽ አንለቅም ብለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዛሬው ቀን ግጭቱ የተነሳውም አፍራሾቹ እንዲፈርሱ የተወሰነባቸውን ቤቶች ቀለም በመቀባታቸውና ህዝቡም እንዳይቀቡ በመከልከሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
በግጭቱ ፖሊስ፣ ፌደራልና ልዩ ኃይል የተሳተፈበት ሲሆን ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ የአካባቢው ወጣቶች ላይ ድብደባና እስራት እየፈጸሙባቸው እንደሆነ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ‹‹ወጣቶችን እንደ እንሰሳ በአንድ ገመድ አስረው እየደበደቧቸው ነው፡፡ ህዝብ በጅምላ እየታሰረ ይገኛል፡፡ ግጭቱ ቢያቆምም በአሁኑ ወቅት በሶስቱም ሰፈሮች ጥይት እየተተኮሰ ነው›› ያሉት የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች የተወሰደው እርምጃ የጎንደርን ህዝብ በማስቆጣቱ ከዚህ የባሰ ግጭት እንዳይፈጠር ያሰጋል ሲሉም ገልጸውልናል፡፡ በግጭቱ ወቅት የመጀመሪያዋ የሞት ሰለባ የሆነችው ልዩ ኃይል ቤቷ እንዲፈርስ ቀለም ሲቀባ የተቃወመች የልጆች እናት እንደሆነችም ታውቋ፡፡