tirsdag 10. mars 2015

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተላለፈባቸው


Habitamu
  • በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
  • ᎐ተጨማሪ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል
• ‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው›› አብርሃ ደስታ
• ‹‹ችሎቱ ላይ ያጨበጨብነው በማፌዝ ሳይሆን በምሬት ነው›› የሺዋስ አሰፋ
• ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› ዳንኤል ሺበሽ
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከስምንት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እንዲሁም የዓረና ትግራይ ፓርቲዎች አመራሮች ‹ችሎት በመድፈር ወንጀል› ጥፋተኛ በመባላቸው ዛሬ መጋቢት 1/2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በሦስቱ አመራሮች ላይ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
የካቲት 26/2007 ዓ.ም ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና ንብረትም እንደተወሰደባቸው በመግለጽ አቅርበውት ለነበረው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨቡና 3ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ሳይፈቀድላቸው ‹‹ጥሩ ፍርድ፣ ጥሩ ብይን›› በማለት አቶ የሺዋስን በመደገፍ ችሎት ደፍረዋል ተብለው ጥፋተኛ መሰኘታቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተሰይሞ በአብርሃ ደስታ፣ በየሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ላይ የሰባት ወራት እስራት በእያንዳንዳቸው ላይ ወስኗል፡፡ ሦስቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ድጋሜ ችሎት ውስጥ አጨብጭበዋል፡፡ በዚህም ድጋሜ ጥፋተኛ ተብለዋል፤ ከሁለት ቀናት በኋላም የቅጣት ውሳኔ ይወሰንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሦስቱ ተከሳሾች ‹‹እድል ስጡን እንናገር፣ አቤቱታም አለን ተቀበሉን›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ሊሰማቸው አልፈለገም፡፡ በተለይ ዳንኤል ሺበሺ ‹‹ሌላ አቤቱታ አለኝ፣ ፍርድ ቤቱ ያዳምጠኝ›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ አሁንም ችሎቱ ላይ እያፌዛችሁ ነው በሚል ጥፋተኛ ሲላቸው ሦስቱም አመራሮች ፍርድ ቤቱን ማስፈቀድ ሳያስፈልጋቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው፡፡ ‹Already› የተደፈረ ችሎት ነው›› ሲል አብርሃ ደስታ ተናግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳኞቹ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል›› ሲሉ አብርሃ በበኩሉ ‹‹አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?›› ሲል መልሷል፡፡
አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ ‹‹ከስምንት ወር በላይ ታፍነናል፡፡ በህግ አይደለም የተያዝነው፡፡ ደግሞ ማጨብጨባችን በችሎቱ ከማፌዝ ሳይሆን ከምሬት በመነጨ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ መብታችን ተጥሷል፡፡ እኔ ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኔ ነው የታሰርኩት፡፡›› ብሏል፡፡
አቶ ዳንኤል ሺበሽ ድግሞ ‹‹አሁንም ችሎት ደፍራችኋል ካላችሁ ቅጣቱን ጨምሩብንና ሸኙን፡፡ በእርግጥ ዳኞች ላይ ያለውን ጫና እንረዳለን፡፡›› ሲል ችሎት ውስጥ ተናግሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ በተከሳሾችና በችሎቱ መካከል ያለው አለመግባባት ሲጨምር ዳኞቹ መጋቢት 3/2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ በመጥቀስ ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ከችሎት እየወጡ እያሉም አቶ ዳንኤል ሺበሽ ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፤ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› እያለ ችሎቱን ለቅቆ ወጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት መውጣታቸውን ተከትሎ፣ ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ ላይ በቀረበው አቤቱታ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ላይ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ አቤቱታው እንዲመዘገብለት የጠየቀው አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ‹‹በበኩሌ ያሉኝን መረጃዎች እያቀረብኩ ስነ-ስርዓቱን አክብሬ ክርክሩን አቀጥላለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡

tirsdag 24. februar 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ ቢኖር – ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

የጎረቤት ኬንያ ዳኛ ለኬንያ መንግሥት አስፈጻሚው ክፍል ልኩን ነገረው፤ ሕገ መንግሥቱን በመርፌ አስተኝተህ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ሕግ ለማውጣት አትችልም፤ ስለዚህም የሰነዘርኸውን የጉልበት ሕግ አንሣ፤ አለው፤ ዳኛ አይጥፋ! ሌላ ቢቀር ከጎረቤት ዳኝነትን እንስማ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ ቢኖር ስንት ጋዜጠኛ፣ ስንት የሃይማኖትና ስንት የፖሊቲካ መሪዎች ከየወህኒ ቤቱ ይወጡ ነበር! ሁላችንም እንደልባችን ሳንፈራ፣ ሳንፈራራ በሙሉ ነጻነት ችግሮቻችንን የወያኔን ጭቆና ጨምሮ ለመወያየትና መፍትሔዎችን ለመለዋወጥ የምንችልበት መድረክ፣ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ራድዮና ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖረን ነበር፤ ስንት ሰው ሥራ ያገኝ ነበር፡፡
ከሁሉም በላይ በየመንገዱ ጠመንጃ የያዘ ሊያስፈራራን የሚሞክር ሆድአደር እያየን፣ እንደዚሁም በየጫካው ያሉትን እያሰብን ሰላማችንን ከምናጣ አበባውን ትተን፣ ሩዙን ትተን፣ የተወደደልንን ጤፋችንን እያመረትን አዲስ ኑሮ ብንጀምር የተሻለ ነበር፡፡
ግን አንድ እንቅፋት አለብን፤ እነዚህ ከየኪዮስኩ እውቀት ገዝተን አዋቂዎች ሆነናል የሚሉት እንትኖች እንመጀመሪያ ችግሩ እንዲገባቸው፣ ሁለተኛ መፍትሔው እንዲገባቸው፣ ሦስተኛ ጉልበትና እውቀት አንድ አለመሆናቸውን ብቻ ሳይሆን በጉልበት እውቀት የማይገኝ መሆኑን ማሳመን በረዶ እየወረደ የስሜን ተራራን መውጣት ነው፤ በረዶ ሳይኖር ወጥቼዋለሁ!
እነዚህን የጉልበት አዋቂዎች — ስለሽማጌሌዎችና አሮጊቶች ሳያስቡ፣ ስለመብራት ኃይል ሳያስቡ፣ ስለውሀ ሳያስቡ ሁሉም በጉልበት ፎቅ ይውጣ የሚሉ! ይባስ ብለው ለእስረኛውም ፎቅ እየሠሩለት ውጣ! ሊሉት ነው!
እነዚህ የጉልበት አዋቂዎች የአበሻ ኑሮ፣ ቡናው፣ ሙቀጫው፣ ምጣዱ፣ በርበሬው፣ ቁሌቱ፣ ቄጤማው፣ ዶሮና በግ ማረዱ፣ ኧረ ስንቱ! ሳይገባቸው ቻይና በነገራቸው የሚያውቁትን የሚረሱ ማን ያስተምራቸው! እናውቃለን ስለሚሉ እንዴትስ ይማራለ? በእውነት ለመማር ቢፈልጉስ ስንት ዓመት ሊያስፈልጋቸው ነው! እግዚአብሔር እንሱንም እኛንም በምሕረቱ ይጎብኘን! የሚያስተምር ጎረቤት አያሳጣን!

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በጨለማ ቤት መታሰራቸውን አስታወቁ

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ የሚገኙት የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀጠና/ዞን አመራሮች ለ16 ተከታታይ ቀናት በጨለማ ክፍል መታሰራቸውን ለፍርድ ቤት አስታወቁ፡፡
ዛሬ የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡት የሰማያዊ (የፓርቲው የጎንደር አደራጅ አቶ አግባው ሰጠኝ)፣ የአንድነት እና መኢአድ የዞን አመራሮች ‹‹መረጃ አውጡ፣ የደበቃችሁትን ሁሉ ተናገሩ›› እያሉ እንደሚደበድቧቸውና በጨለማ ክፍል እንዳሰሯቸው ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ አሁንም መረጃየን ሰብስቤ አልጨረስኩም በሚል ተጨማሪ 8 ቀናት ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡
ተጠርጣዎቹ በማዕከላዊ እየደረሰባቸው የሚገኘውን ሰቆቃ አስመልክተው ለፍርድ ቤት አቤት ማለታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የቀረበበትን አቤቱታ እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የዛሬ አራት ወር ገደማ በፖሊስ ታስረው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ የተደረጉ ሲሆን፣ ጠበቃቸው በተደረገባቸው ክልከላ ምክንያት ተጠርጣሪዎቹን ካገኟቸው 2 ወር እንደሞላቸው ተናግረዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ አግባው ሰጠኝ እየተፈጸመበት ያለውን የመብት ጥሰት በመቃወም የርሃብ አድማ ላይ መሆኑ የታወቀ ሲሆን አድማውን ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት አመራሮቹ የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

fredag 20. februar 2015

አረና ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ምርጫ ያስመዘገባቸው እጩዎቹ ራሳቸውን ከምርጫው ለማግለል እየተገደዱ መሆኑን አስታወቀ።

አረና ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ከ100 በላይ እጩዎቹ ቢመዘገቡም በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰባቸው ጫና ምክንያት በርካቶች ከውድድር መውጣታቸውን ፓርቲው አመልክቷል። የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት ሳይቀሩ ካርድ የለም ተብለው እንዲመለሱ መደረጉን የፓርቲው የሕዝብ ግኑኙነት ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
አረና ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ምርጫ ያስመዘገባቸው እጩዎቹ ራሳቸውን ከምርጫው ለማግለል እየተገደዱ መሆኑን አስታወቀ። አረና ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ከ100 በላይ እጩዎቹ ቢመዘገቡም በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰባቸው ጫና ምክንያት በርካቶች ከውድድር መውጣታቸውን ፓርቲው አመልክቷል። የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት ሳይቀሩ ካርድ የለም ተብለው እንዲመለሱ መደረጉን የፓርቲው የሕዝብ ግኑኙነት ለዶቼቬለ ተናግረዋል። የክልሉ የምርጫ ቦርድ ሃላፊ ግን የአረናን አቤቱታ መሠረተ ቢስ ሲሉ አጣጥለዋል። ዝርዝሩን ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሄር አዘጋጅቶታል ።

søndag 1. februar 2015

ሬድዋን ሁሴንና የወደቀው ክሱ !


በኢትዮጵያችን ህግ ትርጉሟን አጥታ፤ፍትህም ተዋርዳ ከተጣለች የህወሃትን እድሜ ብታስቆጥርም እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ስለ ህግ የበላይነት ማውራታቸውን አላቆሙም። እነዚህ ቡድኖች የህግ የበላይነት ሲሉ እነርሱ ከፍ ብለው ከህግ በላይ፤ ከእነርሱ መንደር ያለሆነው ደግሞ ዝቅ ብሎ ከሥር ከጫማቸው ሥር ሁኖ እነርሱን ተሸክሞ የሚኖርበትን ሥርዓት ማስጠበቅ የሚችለውን ህግ ነው። እናንተን መሸከም ከበደኝ፤ ቀንበራችሁ ሰበረኝ የሚል ሰው ከተገኘ የሚጠብቀው ፍርድ “አሸባሪነት” ነው። ይህ የክፉዎችና የልበ ደንዳኖች ፍርድ ፍትህ ተብሎ በህወህቶች መንደር ይወደሳል። መፅሃፍ እንዲህ ይላል “ክፍዎች ሰዎች ፍርድን አያስተውሉም”። ህወሃቶች ባወጧቸው ህጎች የስንት ንፁሃን ዜጎች ቤት እንደፈረሰ፤ ስንት ህፃናት አሳዳጊ አልባ እንደሆኑ፤ ስንቶች አገራችውን ትተው ተሰደው እንደጠፉ ቆጥረን አንዘልቀውም። በህወሃት መንደር ህግ ዜጎችን ማጥቂያ እና ማስጨነቂያ መሣሪያ እንጂ የፍትህ ማስከበሪያ መሳሪያ አይደለም። በህወሃት ህግ ብዙ ዜጎች ጠፍተዋል፤ ብዙዎች ደግሞ በብዙ ጭንቀት እና መከራ ውስጥ ይገኛሉ።

በህወሃት መንደር የተሰባሰቡ ግለሰቦች እንደምን ያለ ብርቱ ጭለማ እና ድንቁርና ውስጥ እንደሚገኙ በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት እንችላለን። ለአሁን ግን ማሰብ ካቆሙ ቅጥረኞች መካከል ሬድዋን ሁሴን የተባለው ግለሰብ የሆነውን እንመልከት። ሬድዋን ሁሴን፤ ጌቶቹ እና ሌሎች መሰሎቹ ያሉበትን ዘመን ረስተው ወይም መረዳት ተስኗቸው፤ ከስልጣኔ መንገድም ወጥተው እንዲሁ በጭለማ ዓለም እየተደናበሩ ይገኛሉ። ሬድዋን ሁሴን ያለበትን ዘመንና የያዘው የህዝብ ስልጣን የሚያስከትልበትን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት መገንዘብ ስለተሳነው ቀና ብሎ ተናገረኝ ባላው ወጣት ላይ በአሜሪካን አገር ክስ መመሥረቱን ስንሰማ በብርቱ ተደንቀናል። አገራችንም በእንደነዚህ ዓይነት ማስተዋል በጎደላቸው ግለሰቦች የምትመራ መሆኑም በእጅጉ ያሳዝነናል።

ሬድዋን ሁሴንን በቨርጂኒያ አገረ ግዛት ያገኘው ወጣት ህወሃቶች በወገኖቹ ላይ የጫኑባቸው ሸክም ያሳመመው፤ በዚህም ህመም የተቆጣ ቁጣውንም በሰላም የመግለፅ መብቱ ያለ ገደብ የተከበረባት አገር ውስጥ ኗሪ ነው። ሬዲዋን ሁሴንን የመሰለ ራሱን ለምናምንቴ ነገር አሳልፎ የሸጠ ትንሽ ግለሰብ ይቅርና የሃያሏ አገር አሜሪካን ፕሬዝዳንትም ብዙ ወቀሳና ስድብ ይደርስበታል።ፕሬዝዳንቱም የህዝብ ተቀጣሪ መሆኑን ስለሚያውቅ ተወቀስኩ ወይም አንድ ዜጋ ተናገረኝ ብሎ የበቀል ሰይፉን አይመዝም። ፕሬዝዳንቱ ተሰደብኩ ብሎ ክፉ ቢናገር የሚከተለው መዘዝ ከስድቡ የበለጠ ጉዳት ስለሚያደርስበት ስድቡን መቻል እና መሸከም የሥራው አንዱ አካል ይሆናል።ህግ ባለበት አገር የአገሩ መሪ ህዝቡን ፈርቶ ይኖራል እንጂ፤ ህዝብ መሪውን ፈርቶ አይኖርም። ሬዲዋንና መሰሎቹ ግን እንዲህ አይደሉም። ህዝብን ረግጠውና አስፈራርተው መኖር የጎበዝ ተግባር ነው ብለው አምነው ተቀብለዋል።

ህወሃት ትንሹንም ትልቁንም ፈርቶ፤ ፍርሃቱ በወለደው ጭካኔ ዜጎችን ሁሉ አስሮ መኖር ልማዱ ሁኗል። በኢትዮጵያ ዜጎች ህወሃቶችን ፈርተው፤ ህወሃቶችም ዜጎችን አስፈራርተው የሚኖሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይሄ ሁኔታ ለማንም ወይም ለምንም እንደማይበጅ ለህወሃቶች ብንነግራቸውም ልቦናቸው በትዕቢት ታውሯልና አይሰሙንም። ሬድዋን ሁሴንም የዚህ መራራ ትዕቢት ትሩፋት ነው። እንደምን ሁኖ ቀና ብለው ያዩኛል፤ እንደምንስ ሁኖ ይናገሩኛል፤ እንደምንስ ሁኖ ስሜ በገበያ መሃል ይነሳል የሚል ትዕቢት ስለተፀናወተው ክስ መሠረተ፤ ክሱ ግን በህግ ፊት ሚዛን የማይደፋ በመሆኑ በአቃቤ ህጉ ውድቅ ተደረገ። ሬዲዋንም የፍትህን መራራ ፅዋ ተጎንጭቶ ሊውጣት ግድ ሆነበት። የህወሃት ቅጥረኞችና ህወሃቶች ውድቅ ከሆነው ከሬድዋን ህሴን ክስ ልትማሩ የሚገባችሁ የህግ የበላይነት በሰፈነበት አገር እናንተ ከተራው ዜጎች እኩል እንጂ የበላይ ልትሆኑ እንደማትችሉ፤ ከመጋረጃው ጀርባ ሁናችሁ ፍትህን የምትጠመዝዙበት እጃችሁ እንደሚታሰር እና ገና ወደፊት ደግሞ የእጃችሁን እንደምታገኙ ነው። እናንተን ከተራው ዜጋ እኩል የሚያደርግ ህግ ሲፈጠር የታጠቃችሁት ጠብመንጂያ የሸንበቆ ምርኩዝ፤ የመኖሪያ ድንኳን የሆናችሁ ማን አለብኝነታችሁ ደግሞ ፀሃይ እንዳየው ጤዛ እንደሚተን ልብ ልትሉ ይገባል። ሬዲዋንን የተናገረው ወጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁኖ ቢሆን ኑሮ ዛሬ እነሬዳዋን ፈተው በሚለቋቸው ውሾች ሊደርስበት የሚችለውን ስቃይ ስናስበው ይዘገንነናል። ከባህር ማዶ መሆኑ ከሥጋዊ ስቃይ አድኖታል።

እንግዲህ ህወሃቶች የምትፈፅሟቸው ግፎች በየደረሳችሁበት እየተከታተሉ እረፍት ማሳጣታቸውን የሚያቆሙ አይሆንም። የምትሠሯቸው ግፎች የሚያሳድዱት እናንተን ብቻ አይደለም። ከእናንተ አብራክ የሚፈጠሩ ልጆቻችሁንም ጭምር የክፉ ሥራዎቻችሁ ሰለባዎች ከመሆን አያመልጡም። ልጆቻችሁ ተሳቀው ከህዝብ ዓይንና ጆሮ ተደብቀው መኖር ዕድል ፈንታቸው ይሆናል። እናንተ የምትፈፅሙት ወንጀል ለልጆቻችሁ ኩራት ሳይሆን እፍረት፤ ክብር ሳይሆን ውረደት ሁኖ ይቆያቸዋል። ቢያንስ ለልጆቻችሁ ሠላም ስትሉ ከእኩይ ድርጊታችሁ መታቀብ ይሻላችሁ ነበር። እናንተ ግን ለትውልዱ ሠላም የሚሻለውን ትታችሁ የጥፋቱንና የደም መፋሰሱን መንገድ መርጣችኋልና ወዮታ አለባችሁ።

እናንተን መታገል ከስጋና ከደም ጋር የሚደረግ ትግል ብቻ አይደለም። የምትፈፅሟቸው ግፎች ከሰው ልጅ አዕምሮ የሚፈልቁ ብቻ አይመስልም።ከእናንተ ጋር የሚሰራ ሌላ የማይታይ የክፋት አባት ያለ እስከሚመስለን ድረስ ግፋችሁ አንገፍግፎናል። ይህን ግፍ ዝም ብለን የምናይ አይመሰላችሁ። ሊከፈል የሚገባውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል። ወጣቶችም ሳያቅማሙ አያቶቻቸው በተመላለሱባቸው ኮረብቶች ላይ ተሰማርተዋል። ክፉውን ለመቃወም፤ ደም አፍሳሹን ለማስቆም፤ ሌባውን ተው ለማለት፤ ትዕቢተኛውን አደብ ለማስያዝ፤ የነፃነት ቀበኛውን ለማስተማር ሰይፋቸው ከአፎቱ ተስማምቶ ተዘጋጅቷል።

የተከበራችሁ ያገራችን ዜጎች ሆይ !

ህወሃቶች በዜጎችቻን ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ ለእናንተ መንገር ለቀባሪው እንደ ማርዳት ይሆንብናል።የእነዚህ ቡድኖች ግፍ ፅዋውን ሞልቶ እየፈሰሰ ነው።የአገሪቷን ታሪክ አንድ በአንድ ለማጥፋት እየሠሩ ይገኛሉ-በየቦታው በእሳት የሚቃጠሉት ታሪካዊ አምባዎቻችን የአገሪቷን ታሪክ የማጥፋት ዘመቻ አካል ነው።ዜጎች አገር አልባ እንዲሆኑ ተደርገዋል፤ አብሮ በኖረው ህዝብ መካከል የሚዘራው የጥላቻ ዘር ለአገራችን አደጋ ሁኖ ተደንቅሯል። አገራችን ታሪኳ በሚመሰክርላት ሥፍራ ላይ እንዳትሆን፤ ለአፍሪካ ቀንድም ሆነ በአጠቃላይ ለዓለም ሠላም መጫወት የሚግባትን ሚና እንዳታከናውን ተደርጋለች። በተቃራኒው የግጭት አምባ፤ የችጋር ምሳሌ፤ የስደት ምልክት ሁና ከውዳቂ መንግስታት ተርታ ገብታለች። ይሄ ሁሉ እርግማን በህወሃት ምክንያት የመጣ ነው።

እኛ በአገራችን ላይ የተተከለውን ህወሃት የተባለውን እርግማን ነቅለን ለመጣል የምንችለውን ሁሉ እያደርገን ነው። ህወሃቶች የነፃነትን ዋጋ ተረድተው፤ ለፍትህ ክብር ሰጥተው፤ ዜጎችን አክብረው፤እኛም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር እኩል ነን። ከማንም አንበልጥም፤ ሌላውም ከእኛ አያንስም ብለው በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየት ፍርሃታቸው እና ድንቁርናቸው ቢፈቅድላቸው ለሁላችንም መልካም ነበር። ይህ መልካም ነገር ግን የእኛ ምኞት ብቻ ሁኖ ቀርቷል።ህወሃቶች የተፀናወታችው ትዕቢት የሰይጣን ትዕቢት ስለሆነ እንዲሁ በቀላሉ በጄ የሚሉ አይሆኑም። እኛ የቀረን አንድ መንገድ በማንኛውም መንገድ አገራችንን ከጥፋት ማዳን ብቻ ነው። ይህም ታሪካዊ ግዴታችን ሁኗል።

ይህን አገርን የማዳን ታሪካዊ ግዴታ የዚህ ቡድን ወይም ደግሞ የዚያ አካል ብቻ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ተግባር አይደለም። እያንዳንዱ ማሰብ የሚችል እና ለራሱ ትንሽ ክብር ያለው ዜጋ ሁሉ ኢትዮጵያን ለመታደግ የሚችለውን ጠጠር መወረወር ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያ ሬድዋን ሁሴንን በመሳሰሉ ምናምንቴዎች ስትዋረድ እጅን አጣምሮ ቁሞ መታዘብ ትክክለኛ ተግባር አይሆንም። የአገሪቷ ድሃ ዜጎች ስቃያቸው በዝቶ እና ጭንቀታቸው ልክ አጥቶ እያየን ዝም ብንል እርግማን ይሁንብን ካሉ ዜጎች ጋር መተባበሪያ ግዜው አሁን ነው።

እኛ አርበኞች-ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለፍትህ ንቅናቄ አገራችን ከገባችበት የውርደት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት የጀመርነውን ትግል እለት እለት እያደስነው፤ እለት እለት እያሰፋነው፤ እለት እለት እያሳደግነው ቀጥለናል። እኛ ዓይናችን እያየ ህዝባችን አይዋረድም፤ አገራችንም ከሥፍራዋ በታች ስትሆን ዝም አንልም።የሚከፈለውን ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፍለ አናቅማም። በአያት ቅደመ አያቶቻችን ደም ተከብራ የኖረች አገር ዳግም በእኛ ደም ተከብራ ትኖራለች። ቀጣዩ ትውልድም የተከበረች አገር ተርክቦ፤ እርሱም ተከብሮ ይኖር ዘንድ እኛ እንሰራለን እግዚአብሄርም ያከናውንልናል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

lørdag 31. januar 2015

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

ጥር 21/2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ የምርጫ ቦርድ የሚባል ተቋም ያለበትን ደረጃ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህ ደረጃ እንዲዋራድ ከጀርባ ሆኖ አመራር የሚሰጠው ገዢ ፓርቲም ሆነ መንግሰት በዚያው ልክ የሚገባቸውን የተዋረደ ደረጃ የያዙበት ዕለት ነው ብለን እናምናለን፡፡ አንድነት ፓርቲ አንድም የህግ ጥሰት ሳይፈፅም የሚያደርጋቸውን ሁሉ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና በሀገሪቱ ህግ እየፈፀመ ባለበት ሁኔታ በህግ ሽፋን የገዢው ፓርቲ ልሳን የሆነው ፋና ሬዲዮ፣ የመንግሰት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር የከፈቱት ዘመቻ የመጨረሻ የሆነውን አንድም ህጋዊ መሰረት የሌለውን ህገወጥ ውሳኔ በአንድነት ፓርቲ እና አባላት ላይ አሰተላልፈዋል፡፡UDJ/Andinet party logo
ገዢው ፓርቲና መንግሰት በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲነበብ ያደረጉት የፖለቲካ ውሳኔ በኢትዮጵያ ሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ከወረቀት አልፎ በተግባር እንዳይታይ ግብዓት መሬቱን ፈፅመዋል፡፡ በዚህ ፀያፍ ተግባር ከፊትም ሆነ ከጀርባ ሆነው የተሳተፉ ግለሰቦችም ሆኖ ተቋማት በታሪክ ተገቢው የውርደት ቦታ እንደሚይዙ እምነታችን ነው፡፡ ይህ ህገወጥ አካሄድ ህጋዊ መሰመር እንዲከተል የበኩላቸሁን ድርሻ የተወጣችሁ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች በሀገር ውሰጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ ሁሉ በተለይ በገዢው ፓርቲ እኩይ ሴራ በሀስት ተወንጅላችሁ በወህኒ ቤት ለምትማቅቁ ታጋዮች ታሪካችሁ በወርቅ ቀለም ተፅፎዋል፡፡ በቀጣይም ያለምንም መዘናጋት እና ተሰፋ መቁረጥ በምናደርገው ሰላማዊ ትግል በሀገራችን ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሰርዓት ትንሳኤ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለንም፡፡
የምርጫ ቦርድ ተብዬው ተቋም በህገወጥ መንገድ ለሆዳቸው ባደሩ ጥቂት አንድነት ፓርቲ አባላት እና በአንድነት አባልነት በማይታወቁ የገዢው ፓርቲ ጥርቅሞች ለተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ ዕውቅና ሰጥቻለሁ ማለቱን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ሲሆን፣ የአንድነት ፓርቲ አባላት ያነገብነው የነፃነት መንፈስ በምርጫ ቦርድ በሚሰጥ ሰርተፊኬትና ዕውቅና ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝ ስለአልሆነ ለነፃነት የምናደርገውን እልህ አስጨራሽ ትግል የምንቀጥል ሲሆን፤ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የአንድነት መዋቅሮች እና የአንድነት አባላት ለዚህ ህገወጥ ቡድን በግልፅ እውቅና እንዲነሱ እንጠይቃለን፡፡
ፓርቲያችን በመጨረሻ ሰዓት እንኳን ተፈትነው ለወደቁ ተቋማት እድል ለመስጠት ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ወሰኖ እንቅሰቃሴ በማድረግ ላይ ቢሆንም፤ በዛሬው ዕለት ጥር 22/ 2007 ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ የፓርቲያቸን ፅ/ቤት በፖሊስ ተወሮ የፓርቲው ንብረት ያለምን ህጋው ርክክብ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጎዋል፡፡ በአሰተዳደር የተሰጠን ውሳኔ በፍርድ ቤት የማሰለወጥ ህጋዊ ሰርዓት እንዳለ ቢታወቅም ህገወጥ አስተዳደራዊ ውሳኔን በፖሊስ ወረራ ለማሰፈፀም የተሄደበት መስመር ገዢው ፓርቲና መንግሰት አሁንም ከጫካ አሰተሳሰብ ያለመውጣቸውን እና የአውራ ፓርቲ ፍልስፍናቸውን በማናለብኝነት ለመተግበር መቁረጣቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ህገወጥ ድርጊት ተጠያቂው ትእዛዙን ያስተላለፈው ክፍል መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ሰለሆነም በሀገር ውስጥ እና በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅቶች፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሰርዓት እንዲጎለብት ፍላጎት ያለችሁ ሁሉ ይህን እኩይ ተግባር በማውገዝ ተጨባጭ እርምጃ እንድትወሰዱ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ድል የህዝብ ነው!!!

tirsdag 27. januar 2015

አቶ ትግስቱ አወሉ በአንድነት የክልል አመራሮች ላይ በስልክ ዛቻ እየፈፀሙ መሆኑ ተገለፀ፡፡


የአንድነት ፓርቲ ሰሞኑን በኢህአዲግና ምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ዘመቻ ተከፍቶበት እንደሚገኝ መላው ኢትዮጵያዊ እየተከታተለው ያለ እውነታ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን አንድነት ፓርቲን ለመፈረካከስ ከሚሰሩት ግለሰቦች መካከል አቶ ትግስቱ አወሉ የተባሉና የቀድሞ የአንድነት አባል በአሁኑ ሰዓት እራሳቸውን ፕሬዝደንት አድርገው ከምርጫ ቦርድ ጋር በጋራ በመስራት ላይ ያሉ ግለሰብ በ16/05/2007 ዓ.ም ላደረጉት ህገ-ወጥ ጉባኤ ተልእኳቸውን ለማስፈፀም በየክፍለሀገሩ የሚገኙ የአንድነት ፓርቲ የጉባኤ አባላትን በስልክና በአካል በመሄድ ለዚህ ህገ-ወጥ አንድነት ፓርቲ ነኝ ባይ ጉባኤ እንዲገኙ በማግባባት፤ከመንግስት ፈሰስ በተደረገላቸው ገንዘብ በመደለል እንዲሁም እንቢ ያሉ ግለሰቦችን ‹‹መንግስት ከኔ ጎን ነው እንቢ ካልክ/ሽ እርምጃ እንወስዳለን፤…..ወዘተ›› ማስፈራሪያ ሲጠቀሙ እንደነበር በየአካባቢው የሚገኙ የአንድነት አባላት ሰሞኑን ሲገልፁ የነበረ ሲሆን ዛሬ በደረሰን መረጃ መሰረት ግለሰቡ በደቡብ ወሎ የአንድነት መዋቅር በሚገኝባቸው ሐይቅ፤ወረባቦ፤ደሴ፤ኮምቦልቻ፤ኩታበር …….የመሳሰሉት ወረዳዎች የሚገኙ የአንድነት የወረዳ አመራሮች ጋር ስልክ በመደወል ከፍተኛ መስፈራራትና ዛቻ የተቀላቀለበት ድርጊት መፈፀማቸውን ከየወረዳዎቹ ያሉ የአንድነት አመራሮች ሪፖርት አድርደዋል፡፡ ግለሰቡ አንድነት ፓርቲ የኔ ነው፤እኔም ነኝ የምመራው፤ በኔ አስተዳደር ስር ሆናችሁ ላለመሳተፍ ከወሰናችሁ፤ በመንግስት በኩል ከፍተኛ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ተደርጓል›› ….ወዘተ የሚል ማስፈራሪያ እንደሚያሰሙ ገልፀዋል፡፡ አባላቶቹ አያይዘውም ‹‹እኛ አንድነት አንድ እንጂ ሁለት አይደለም፤ህጋዊ የሆነው አንድነት ፓርቲ በተገቢው ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ባለበት አግባብ መንግስትና ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ለመበታተን ለሚያደርጉት ዘመቻ ተገዢ አንሆንም፤ሰላማዊ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አቶ ትግስቱ አወሉ በህጋዊውና በትክክለኛው የአንድነት ፓርቲ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እራሳቸውን እጩ አድርገው አቅርበው በመሳተፍ የራሳቸውን አንድ ድምፅ ብቻ አግኝተው መውደቃቸው የሚታወስ ነው፡