lørdag 10. mai 2014

ነፍሰጥሩዋ ቦይንግ


ከምስሉ የምትመለከቱት ከኣዲስ ኣበባ ቦሌ ኣለም ኣቀፍ ኤርፓርት ተነስቶ ኣሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የሚበረው ቦይንግ 777 መንገደኞች ኣውሮፕላን ነው። ከኣዲስ ዋሽንግተን የደርሶ መልስ ቲኬት ዋጋ 1600 (ኣንድ ሺ ስድስት መቶ ዩሮ) ነው። ይህ ማለት 2200 (ሁለት ሺ ሁለት መቶ በዶላር) ይሆናል በኛ ደግሞ 44,000 (ኣርባ ኣራት ሺ ብር) ማለት ነው። ገንዘቡ ኪስ የሚፈታተን ቢሆንም ለኢሃዴጋውያን ቀላልና እንደ ለገጣፎ መንገድ ቀን በቀን የሚመላለሱበት መንገድ ነው። ነፍሰጥሩ ተብላ የተሰየመችው ይቺ ኣውሮፕላን በየጊዜው ይዛ የምትሔደው የኢሃዴጋውያን ባለስልጣናት ሚስቶች ለመውለድ የደረሱ ሲሆን ይህ የሚያደርጉበት ምክንያት የማዋለጃ ሆስፒታል ፍለጋ ሳይሆን የሚወለደው ጨቅላ የኣሜሪካ ዜግነት እንዲኖረው ለማድረግ ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊነት ክብር የማይሰጡት ኢሃዴጋውያን ባሁኑ ወቅት በኢኮኖሚና የውስጥ ችግር ቀን በቀን ቁል ቁል በመሄድ ላይ ያለችውን ኣገርና የህዝብን ጥያቄ መመለስ ኣቅሙና ብቃቱን ያጣ የሚመስለው የራሳቸውን ቤት በማሳመርና ከኣብራካቸው የወጣውን ደግሞ የወጪ ዜግነት እንዲኖረው በማድረግ ላይ እየተረባረቡ ይገኛል። በሃሰት ዲስኩርና ፕሮፓጋንዳ ተወጥሮ የሚሰራው ኢሃዴግ ወያኔ ብሩን ወደ ዶላር እየቀየረ ከኣገር በማስወጣት ላይ ይገኛል። ሁለት ልብ ሆኖ መኖር ያቀደ የሚመስለው ዛሬ በኣገር ውስጥ ሰውን እየገደለ በሌላ በኩል ደግሞ ወጪ ኑሮውን በማመቻቸት ጊዜው በልማት ወሬዎች ሸፋፍኖ ገመናውን ለመደበቅ እየጣረ ይገኛል። ይቺ ጃርት የበላው ዱባ የመሰለችው ኢትይጵያ በወያኔ ኣንገቱዋ ተሰብሮ እንዳትነሳና ኣንድ የብሄር ጎሳ ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል እየተሰራም ይገኛሉ። ነገ ለምትፈርሰው ኣገራችንን ዛሬ ላይ ሆነን ካላመመን ነገ የምንቀበለው በልተው የተፉትን መሆኑን ኣንጠራጠር::

torsdag 8. mai 2014

“የኢትዮጵያ የብሔሮች ጥያቄና መፍትሔዉ” እስክንድር ነጋ(ከቃሊቲ እስር ቤት)


የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጋር ተያይዞ፣ የብሔረሰቦች የእኩልነት መብት በቃልና በፕሮግራም ብቻ ሳይሆን፣ በግብር መታወቅ አለበት፡፡ የእያንዳንዱም ብሔረሰብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ሌሎችም መለያዎች በእኩልነት መታወቅና መከበር አለባቸዉ፡፡ ብሔሮች ሁሉ ትልቅም ሆነ ትንሽ የራሳቸዉን የወደፊት ዕድል የመወሰን መብት መታወቅና በትክክል ከስራ ላይ መዋል አለበት፡፡ ብሔሮች ቋንቋቸዉንና ጠቃሚ የሆኑትን ባህሎቻቸዉን በነፃ እንዲያዳብሩ መደረግ አለበት፡፡ ማንም ሰዉ በዉስጥ አስተዳደራቸዉ ላይ ጨቋኝ ተፅዕኖ እንዳያደርግ መከላከል አለበት፡፡ ኢትዮጵያን ከብሔሮች እስር ቤትነት ወደ ብሔሮች ማበቢያ ሥፍራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይቻላልም፡፡ የሕዝቦች አንድነት፣ በሳንጃና በመድፍ በተቋቋመዉ አንድነት ፋንታ፣ በመግባባትና በመፈቃቀድ ላይ ሊመሠረትና እንደአለት ጸንቶ ሊኖር የሚችለዉ በዚህ መንገድ ብቻ ነዉ፡፡ በንጉሱ እና በደርግ ጊዜ የብሔርን ጥያቄ አንግበዉ የተነሱ አካላት ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ(ሻቢያ)፣ ሕወሓት እና ኦነግ ነበሩ፡፡ በአሁን ግዜ ግን ነፃ አዉጭ ብሔር የሌለዉ የደቡብ ክልል ብቻ ነዉ ይህም ሊሆን የቻለዉ እንደሚመስለኝ የጎሳዎች ብዛት እና የመልክአምድራዊ አቀማመጥ ብሎ ነግሮኛል፡፡ አምባገነን ባለበት አገር ላይ የብሔር ጥያቄ የሚያነሱ አካላት እየበዙ እንጅ እያነሱ አይሄዱም፡፡ እንደ ምሳሌ ታላቋን ሩስያ ማንሳት በቂ ነዉ፡፡ በእስታሊን አምባገነንነት ምክንያት አብዛኞቹ አገሮች ለመገንጠል ምክንያት ሆናቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የዩጎዝላቪያ፣ የራሽያ እና የሶማሊያ እጣ ፋንታ ሳያጋጥማት እኛ ቀድመን ልናድናት ይገባል፡፡ ይሄም ሊሆን የሚችለዉ በአንድ እና አንድ መንገድ ብቻ ነዉ፡፡ እሱም በሰላማዊ ትግል ወያኔን ስናስወግድ ብቻ፡፡ከዛም ስራዉ የኛ የጋዜጠኞች እና የፖለቲከኞች ይሆናል፡፡ የብሔር ፖለቲካ የበሰበሰ እና ያለፈበት መሆኑን ምርጫ 1997 አስተምሮን አልፏል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ኤርትራ እንዳትገነጠል የበኩልን ድርሻ ቢወጣም በወያኔ እንቢተኝነት በ1984 ዓ.ም ምህረት ህዝቡን አሰሩ፣ ገደሉ አቆሰሉ፡፡ ይህም አልበቃ ብሏቸዉ የኤርትራ ህዝብን በምርጫ በማወናበድ ምርጫቸዉን አሳኩ፡፡ በየት አገር ነዉ ባርነት ወይስ ነፃነት የሚል ምርጫ የተካሄደባት አገር አለች፡፡የኤርትራ ህዝብ ግን የጣሊያን እና የእንግሊዝ አስተዳደር አሻፈረኝ ብሎ ወደ እናት አገራቸዉ ለመመለስ የበኩላቸዉን ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናቶች ይናገራሉ፡፡ ሁለት ኤርትራዊያን ግለሰቦችን ማንሳት ያዉም በቂ ነዉ ዘርዐይ ደረስ ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ ሲቀልዱ በመበሳጨት ጣሊያኖች ላይ ጉዳት አድርሷል፤ አብርሃም ደቦጭ በግራዚያኒ ላይ ቦምብ በመወርወር የመግደል ሙከራ ያደረገ እና ያቆሰለ፡፡ህዝቡም ሲጠይቅ የነበረዉ ኢትዮጵያዊነት ነዉ፡፡ይህንንም አሳክተዉ ከ60 ዓመታት በኋላ ተመልሰዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ መሳካትም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስተር የነበሩት የአክሊሉ ሀብተወልድ ድርሻ ላቅ ያለ ነበር፡፡
“ኢትዮጵያ ወይም ሞት” በማለት በሀገር ፍቅር ማህበር ስር የተሰለፉ ሀገር ወዳድ ኋይሎች ህዝቡን በማስተባበር በነቂስ ወጥቶ የኤርትራን ግዛቶች ሲያጥለቀልቅ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር አብረዉ ለመኖር የሚፈልጉ ህዝቦች ነበሩ፡፡ ሁሉም የኤርትራ ህዝብ ለመገንጠል ከሻቢያና ከወያኔ ጋር አብረዉ ቁመዋል ማለት ከእዉነት የራቀ ነዉ፡፡ የኤርትራ መገንጠል ለአስገንጣኞች አካላት ብቻ ነዉ የጠቀመዉ፡፡ ኤርትራ በመገንጠሏ የኤርትራ ህዝብ ምን አገኘ? የኢትዮጵያ ህዝብስ ምን አገኘ? አሁንም የኤርትራ ህዝብ በጭቆና፣ በርሀብ፣ በስደት እና በበሽታ እያለቀ ነዉ፡፡ መገንጠል እንደማያዋጣ የኛዉ ኤርትራ አስተምራናለች፡፡
እስክንድር ነጋ የሚፈልገዉ እኩልነትና ነፃነት የሠፈነበት፣ የህዝቦቿ አንድነት ከብረት የጠነከረባትና ብሔረሰቦች ሁሉ ያበቡባት፣ የማንም ተመፅዋች ያልሆነ በራሱ የሚተማመን በማንም ፊት የባታችነት ስሜት ሊኖረዉ የሚችል ህዝብ እንዲይፈጠር ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል የፈጀዉን ጊዜ ቢፈጅምና የፈለገዉን ያህል መሥዋዕትነት ቢጠይቅም፣ ብዙ ችግሮችና መሰናክሎችን ከፊታችን ቢደቀኑም፤ የዚች ዓይነት ኢትዮጵያ እንድትመሰረት እስከ መጨረሻዉ ለመታገል ቆርጨ ተነስቻለዉ፡፡ የእናት አገራችን ህልዉና ላያስጠብቅ የሚችለዉ ለ22 ዓመታት ፈላጭ ቆራጭ ጫማ ስር የተረገጠችበት ብሔራዊ ነፃነቿን ክብሯ ተገፍፎ የቆየችበት ዓመታት ነዉ፡፡ በሁሉም ወገን የሚደረገዉ መሯሯጥና መሰናዶ ሲታይ አበረታታች ነዉ፡፡ ወሳኝ የሆነዉ ፍልሚያ ገና ከፊታችን እንደሚጠብቀን ምንም ጥርጥር ሊኖረዉ አይችልም፡፡
የግንቦት 7 መስራች እና መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በሚመለከት ከግብፅ መንግስት እርዳታ ተቀብሏል ተብሎ ወሬ እየተናፈሰ መሆን ስጠይቀዉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ብርሃኑ የሚያደርገዉ አይመስለኝም ካደረገዉ ግን በጣም አዝኘበታለዉ፡፡ ለምንድን ነዉ አባቶቻችን የሰሩትን ስህተት የምንደግመዉ፡፡ መኢሶን፣ ኢህአፓ፣ ጀብዐ እና ወያኔ በአንድ ይሁን በሌላ መልኩ የዉጭ እርዳታን እየተቀበለዉ፡፡ አገራችን እና ህዝቧን ጎርቷል፡፡ ኤርትራን እንድናጣ ሁነናል፡፡ አሁንም መናገር የምፈልገዉ ኢህአዴግን እና ኢትዮጵያን ለይተን ማዬት አለብን፡፡ ኢህአዴግን የጎዱ እየመሰላቸዉ አገራችንን እያደሟት ነዉ፡፡
ለተቃወሚ ፓርቲዎች እችን መልዕክት አስተላልፏል፡፡
1.የዉጭ ኋይሎች ድጋፍ የዚችን ኩሩና ታሪካዊ አገራችንን ብሔራዊ ክብርና ነፃነት የማይነካ፣ ራስን ለመቻል የምታደርገዉን ጥረት የሚያግዝ እንጅ የማያደናቅፍ እርዳታ መሆን አለበት፡፡
2. ማንኛዉም ህዝብ በዉጭ እርዳታ ላይ በመተማመን አብዮቱን ከግብ ለማደረስ እችላለሁ ብሎ ካሰበ ራሱን ማታለሉ ብቻ ሳይሆን አብዮቱንም ብሔራዊ ነፃነቱን ያጣል፡፡ ማንም ህዝብ በተለይም ደግሞ እንደኢትዮጵያ ሕዝቡ ኩሩና ባለታሪክ ሕዝብ ከሆነ ለገዛ ነፃነቱ፣ ለገዛ ለዉጡ ለገዛ ክብሩ ከሁሉም በፊት መተማመን ያለበት በራሱ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ስለሆነም የዉጭ እርዳታን በሚመለከት በኩል ብሔራዊ ክብርና ነፃነት እንደዚሁም ከሁሉ በፊት በራስ መተማመን የሚለዉ ዋናዉ መመሪያችን ይሆኑ፡፡
እስክንድር ነጋ
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ጊዜያቸዉን ማባከን የለባቸዉም የሰማያዊ ፓርቲ እና አንድነት ፓርቲ የሰላማዊ ትግል መንገድ መቀላቀል አለባቸዉ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ “ሰላማዊ ትግሉን(አብዮቱን) እኛ ካልመራነዉ አብዮት አይሆንም” ከሚል አመለካከት መጀመሪያ መላቀቅ አለባቸዉ፡፡ትግሉን ማንም ይምራዉ ማን ሕዝቡ ለትክክለኛዉ የስልጣን ባለቤት መሆን አለበት፡፡ ዛሬ የሚወነጃጀሉት ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ማሌሪድ፣ ሰደድ፣ ወዝ ሊግ፣ ሻዕቢያ፣ ህወሓት ይህን የህዝብ መብት ረግጠዉ እና አፍነዉ በህዝቡ ቦታና ጥያቄ እራሳቸዉን መተካታቸዉ ሲሆን ዋና የህዝቡን የበመደል መነሻ ምክንያት ይህ ነዉ፡፡ በመሆኑም በአንዳንድ ታዳጊ አገሮች ዉስጥ ሕዝቡን በዙሪያቸዉ አጠቃለዉ ለማሰለፍ አይነት ተግባራዊነት ታላላቅ ሰዎችን የመሰሉ እንኳን ለማፍራት አልቻለችም፡፡ ከዚህ አኳያ ጋንዲን ያፈራች ህንድ፣ ማኦን ያፈራች ቻይና፣ ማንዴላን ያፈራች ደቡብ አፍሪካ እና ፓትርስ ሉሙባን ያፈራች ኮንጎ ጋር ሀገራችን በአቻ አትታይም፡፡ እነዚህ ታላላቅ ሰዎች ከሀገራቸዉ አልፈዉ የአለም ሰዎች ሁነዉ ኑረዋል፡፡እየኖሩም ነዉ፡፡ እንዲያዉም ኢትዮጵያ ዛሬ የጎደላት ነገር ቢኖር እኒህን የመሰሉ ቅን ሰዎችን ማግኘት ነዉ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንኳን የብሔረሰቦችን የአመለካከት ድንበር አቋርጦ በማለፍ የህዝቦቷን አመኔታ ሊያገኝ የቻለ የፖለቲካ ሰዉ መፍጠር ቀርቶ ለተወለደበት ብሔረሰብ ለመቆም የቻለ ሀቀኛ የህዝብ ሰዉ መፍጠር አልተቻለም፡፡
በመጨረሻም እስክንድር ልብን በሚማርክ ሁኔታ ስለ ኢትዮጵያ እናት እና አባቶቻችን ለብዙ ዓመታት ታግለዉና ተዋግተዉ ነፃነታቸዉን ያወጁት፡፡ ስለዚህ ይህ ትዉልድ ጭቆናና ግፍ በቃኝ ብሎ የራሱን መሪዎች ገርስሶ መጣል አለበት፡፡
“እኔ ለዲሞክራሲ ስል ታሰርኩ እንጅ ሌላ ምን ሆንኩኝ ለነፃነት የምከፍለዉ መስዋዕትነት እስከ ሞት ድረስ ነዉ”
እስክንድር ነጋ
“እኔ ከኢትዮጵያ የተሻለ አገር የለኝም የምታሰርባት፣ የምገረፍላት፣ የማለቅስላት፣………. በቃ በአጭሩ እኔ የምሞተዉ በአገሬ በኢትዮጵያ መሬት ነዉ፡፡ ነፍሴም የምታልፈዉ ሥጋዬም የሚፈርሰዉ በምወዳት አገሬ ኢትዮጵያ ነዉ”
እስክንድር ነጋ
“ብሔሮች በጋራና በሰላም ለመኖር ዘላለማዊ ዋስትናቸዉ ደግሞ ዲሞክራሲያ መንግስት ነዉ”
እስክንድር ነጋ
ጠያቂዎቹ እየበረከቱ ሲመጣ ቻዉ ተባብለን ተለያየን በሌላ ቀን እነዚህን አይጠገቤ ወሬዎችህን እንደምትደግምልኝ ተስፋ አረጋለዉ፡፡
አምላክ ከአንተ ጋር ይሁን ብዬ ወጣዉ፡፡
ከእስክንድር ዐይን ርቄ በሄድኩኝ ቁጥር ሆድ ባሰኝ አቅም አነሰኝ ይህን ንፁህ ሰዉ ማሰር ምን ይሉታል፡፡
በረከት ስምዖን፣ አባይ ፀሐዬ፣ ሳሞራ የኑስ…………… ተዉ ፍቱ ይህን ጀግና፡፡
ተዉ ተዉ ተዉ………… ከሆስኑ ሙባረክ፣ ከጋዳፊ ተማሩ፡፡
ቅዳሜ ጧት 3፡00-3፡30(ከቃሊቲ እስር ቤት)
አብዲሳ አጋ(ገሞራዉ)

onsdag 7. mai 2014

“ሰልፉ የተካሄደው በእኛ ትዕግስትና ጥንካሬ እንጂ በመንግሥት አልተፈለገም” ”

May 7/2014
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታዩ የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ላይ ያተኮረ “የእሪታ ቀን” በሚል ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል። ሰላማዊ ሰልፉ ከተከናወነ በኋላ የፓርቲውን ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራውን አነጋግረናቸዋል።
ሰንደቅ፡- ባለፈው እሁድ (ሚያዚያ 26 ቀን 2006 ዓ.ም) የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ምን ያህል የተሳካ ነበር?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ሰልፉ እንዳይካሄድ ከነበረው ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ አንፃር ከፍተኛና ስኬታማ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር።
ሰንደቅ፡- ሕብረተሰብ ውስጥ አለ ካላችሁት ችግር አንፃር እንደምትጠብቁት በቂ የሆነ ሕብረተሰብ በሰላማዊ ሰልፉ ወጥቷል የሚል እምነት አላችሁ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ካለው ሁኔታ አንፃር አዎ። አንደኛ ለመቀስቀስ ዕድል አልሰጡንም። የሰላማዊ ሰልፉን እውቅና ያገኘነው በእኛ ትዕግስት እንጂ እውቅናውን መስጠት አልፈለጉም። ከሕግ ውጪ በሆነ መልኩ ሰልፉን ለማካሄድ ማንም ሰው መፈረም ቢችልም አመራሩ ካልፈረመ እውቅና አልሰጥም አሉ። ሶስት የፓርቲ አመራሮች ሄደው ፈረሙ። እኔ በአጋጣሚ በማኅበራዊ ጉዳይ ሀዘን ላይ ስለነበርኩ እሱም ካልመጣ በመባሉ ከሶስቱ አመራሮች በተጨማሪ እኔ አራተኛ እንድፈርም ተደርጓል። በእርግጥ የእኔ መፈረም ችግር አይመስለኝም። ነገር ግን ህግ የማክበር ጉዳይ አይደለም። ጊዜ የማጣበብ ጉዳይ ነው። ከዚህ ጎንለጎን ለቅስቀሳ የወጡ አባሎቻችንን አሰሩብን። እውቅና ያለው ሰልፍ መሆኑን እያወቁ አባሎቻችንን አሰሩ። ለምሳሌ የፓርቲያችን የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን፣ የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነብዩ ኃይሉ ታስሯል። እንደዚሁም ዘላአለም የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ታስሯል። ከዚህ አንፃር ስታየው ሰላማዊ ሰልፉ ስኬታማ ነበር።
ሰንደቅ፡- የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አጋርነታችሁን በሰልፉ ላይ ለመግለፅ ሙከራ ቢያደርጉም መከልከላቸውን ገልፀዋልና ለምን ተከለከሉ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ማንም ሰው አልተከለከለም። በእርግጥ እኔን አላገኙም። ነገር ግን በኋላ ሳጣራ ማንም ኢትዮጵያዊ በዚያ ሰልፍ መሳተፍ የእኛ ፍላጎት ነው። ነገር ግን እንደሰማሁት የእነሱን (የሰማያዊ ፓርቲ ማለታቸው) ቲሸርት የራሳቸውን አርማ ይዘው ለመካፈል ሞክረዋል የሚል ነው። እነሱ ሰልፍ ባካሄዱ ጊዜ የእኛ አባሎች የእነርሱን አርማና መፈክር ይዘው ነው የተሳተፉት። እና እነሱ የሰማያዊ ፓርቲን በአንድነት ሰልፍ ለማስተዋወቅ ሙከራ ያደረጉ ይመስላል። በእኛ አባላት በኩል ሰልፉ የአንድነት ፓርቲ መሆኑን በመግለፅ መፈክሩም፣ አካሄዱም በአንድነት ፓርቲ የሚመራ መሆኑ ተነግሮአቸዋል። ይሄ ደግሞ ትክክል ነው። በእኛ በኩል ሁሉም መፈክር ላይ ማህተም አድርገናል። ከዚያ ውጪ ያለው መፈክር እኛን እንደማይወክል ቀደም ብለን ሰርተናል። ባጅም አድለናል። እና ሰልፉ የሌላ ፓርቲ ማስታወቂያ ወይም መፈክር ማቅረቢያ አይደለም። በተጠየቅ (logic) ብታየውም ሁሉም የሰልፉ አካሄድ የአንድነት መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።
ሰንደቅ፡- በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል እንደተቋምም ሆነ እንደ ግለሰብ ያለው ግንኙነት ጤናማ ነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- እኔ እንደማስበው ይሄ ለጥያቄ የሚቀርብ አይመስለኝም። በእኛ በኩል በራሳችን ትዕግስት ሁሉንም ፓርቲ የምናየው በእኩልነት ነው። ከሁሉም ፓርቲ ጋር በጋራ ለመስራት በራችንን ከፍተናል። ከዚያም አልፎ የእኛ አላማ ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር ነው። እንግዲህ እነሱ በዚህ ላይ ይስማሙ አይስማሙ እነሱን መጠየቁ ይሻላል። አንድነት ግን ከሁሉም ፓርቲ አብሮ ለመስራት እስከውህደት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። 
ሰንደቅ፡- ባለፈው እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል ቀጣይ አቅጣጫችሁ ምንድነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- እሁድ እለት የተካሄደው ሰልፍ እራሱን የቻለ የአዲስ አበባ የፓርቲው መዋቅር ያዘጋጀው ነው። ይህንን እንደ ትልቅ መዋቅር ነው የምናየው። ከአዲስ አበባ ውጪም በሲዳማ እና በምስራቅ ጎጃም እንዲሁም በአዳማ ይኖረናል። እነዚህ አካላት በራሳቸው አየጠነከሩ የአቅም ግንባታ እንዲያደርጉ በማድረግ እንዲቀጥሉ ነው። ለምሳሌ በደራሼ ጊዶሌ ከተማ በተመሳሳይ እሁድ እለት ሰልፍ ተካሂዷል። ወዲዚያው አንድ የስራ አስፈፃሚ አመራርና የቀጠና አስተባባሪ ልከናል። ወደፊትም ዞኖቹ የራሳቸውን አቅም ገንብተው የማዕከል የፖለቲካ አቅም ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ይካሄዳል። ከዚህ ጎንለጎን የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ አሁን ለመሬትና ለፍትህ እየተካሄደ ነው። በቀጣይ ደግሞ በሶስተኛው ፌዝ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነትና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ” መርሀግብር ይኖረናል። ከሰኔ 30 በኋላ የሚጀመር ይሆናል። ይህም ፖለቲካውን ከአንድነት ወደ ሕዝብ የማውረድ እንቅስቃሴ ነው። ከዚህ ጎንለጎን በስትራቴጂው ዘርፍ አማራጭ ፖሊሲዎች የማዘጋጀት፣ የምርጫ ማኒፌስቶ፣ የምርጫ ስትራቴጂ ማዘጋጀትና የአማራጭ ፖሊሲ ትውውቅ ውይይቶች ይካሄዳሉ። በዚህም በአዳራሽ ስብሰባ የተለያዩ ምሁራን በተገኙበት የሚደረግ ይሆናል።
ሰንደቅ፡- ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የመዋሃዱ ጉዳይ ያበቃለት ጉዳይ ሆኗል ማለት ይቻላል?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ያበቃለት ነገር የሚባል ነገር የለም። በእኛ በኩል ለውህደት ሙሉ በሙሉ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ አንድ ጠንካራ አብይ ብሔራዊ ፓርቲ መፈጠር አለበት ብለን እናምናለን። ውህደትን እንደ ጠንካራ ግብ ስለያዝነው ምንጊዜም ቢሆን የምንቀጥልበት ጉዳይ ነው።
ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ከመሆኑ አንፃር የፖለቲካ ምህዳሩ በምን ደረጃ ላይ ነው ትላላችሁ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- የፖለቲካ ምህዳሩ በእጅጉ እንደተዘጋ ነው። ሰልፍ ማካሄድ ወደማንችልበት ደረጃ ነው የደረስነው። የትናንትናውን ሰልፍ ለማካሄድ አንድ ወር ፈጅቶብናል። የሰልፍ እውቅና ማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ ለፖለቲካ ምህዳሩ አለመስፋት ዋነኛ ምሳሌ ነው። ሕዝባዊ ስብሰባ አዲስ አበባ ውስጥ ለማካሄድ አስበን አዳራሽ አጥተናል። የአዲስ አበባ አስተዳደር የሁላችንም አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት ካልቻለ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ለሰልፍ አንድ ወር መፍጀት የለበትም። እኛም ታግሰን ሁኔታውን አክብረን እውቅና ሲሰጠን ማየት የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን አያሳይም። አሁንም ከሁለት ወር በፊት የጀመርነው የአዳራሽ ስብሰባ በአዳራሽ እጦት ማካሄድ አልቻልንም።
ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ሰላማዊ ሰልፍ ስታደርጉ አይታይም፤ አሁን ግን ወደ አደባባይ የመውጣቱ ሁኔታ ከመታየቱ አንጻር በፖለቲካ ምህዳር መስፋት በኩል የተሻሻለ ነገር አለ ብለው የሚያምኑ አካላት አሉና እርስዎስ ምን ይላሉ?
     ኢንጂነር ግዛቸው፡- አንተ ማየት ያለብህ ሂደቱን ነው። ሰልፉን በነፃነት እያካሄድን አይደለም። እውቅና ለማግኘት አንድ ወር እየፈጀብህ ምህዳሩ ሰፍቷል ማለት አይቻልም። ሰልፉ በእኛ ትእግስትና ጥንካሬ እንጂ በመንግስት በኩል አልተፈለገም። ሰልፍ ስናካሂድ ብዙ ሰዎች ይታሰራሉ እና ሰልፉ መካሄዱ አይደለም ዋና አላማው፤ ሂደቱ ላይ አሁንም ነፃ አይደለንም። ሂደቱ ላይ አሁንም አፈና ይካሄድብናል። የማስፈራራት ዘመቻው ከፍተኛ ነው። ሚዲያው ሙሉበሙሉ የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ማስተላለፊያ ሆኗል። እኛን አያስተናግደንም። የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ሰልፉን እንደምናካሂድ ማስታወቂያ አዘጋጅተን ሄደን ተከልክለናል። የፍትህ አካላት አካባቢም ችግር አለ። የእኛ አባላት በመኪና ስለቀሰቀሱ ለአስር ቀናት ፖሊስ አሰራቸው። ሕግ አስከባሪውም በሕገ-መንግስቱ መሰረት እየሰራ አይደለም። ነፃ የሲቪል ማህበረሰብ የለም። ያሉትም የኢህአዴግን ቡራኬ ያገኙ ናቸው። እና ከድሮው በጣም ተዘግቷል። ሚዲያው ሚዛናዊ መሆን ሲገባው በእኛ ላይ ፕሮፓጋንዳ ያደርጋል እና ደምረው ስታየው በእጅጉ እየተዘጋ ነው።

mandag 5. mai 2014

አንድነት ፓርቲ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረገ! (ቪዲዮ እና ፎቶዎች ይዘናል)
ኢ.ኤም.ኤፍ) – ዛሬ ሜይ 4 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። የሰላማዊው ሰልፍ ጥሪ ለመጀመሪያ ግዜ በሸገር ሬድዮ የተላለፈ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ማስታወቂያውን “አላቀርብም” ብሎ የነበረው ኢቲቪ ከሰልፉ በኋላ፤ የተቃውሞውን ምስል ቆራርጦም ቢሆን በዜና እወጃው ላይ አቅርቦታል።
ሰልፉ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የተደረገ ነው። ከዚህ ቀደም በሰበብ አስባቡ ሲከለከል የነበረው “የእሪታ ቀን” ዛሬ እውን ሲሆን፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሰልፉን ተቀላቅለውታል።
"መንገድ ዘግታችኋል ቶሎ ቶሎ ሂዱ" ፖሊስ። "መንገዱ ለኛ የተፈቀደ ነው ሰዓታችንን እንዴት እንደምንጠቀም እናውቃለን" አመራሮች
አንድ ሁኔታውን የታዘቡ ግለሰብ እንዲህ ዘግበዋል። “የዛሬውን የአንድነት ፓርቲ ህዝባዊ ተቃውሞን በቦታው ተገኝቼ እንደታዘብኩት” ብለው ነው የጀመሩት… በዛሬው እለት ከጠዋቱ ሶስት ሰዐት ጀምሮ በርካታ የከተማይቱ እና የአካባቢው ነዋሪዎች የተገኙበት ታላቁ የእሪታ ቀን በድምቀት የተካሄደ ሲሆን በሠልፉ ላይ በርካታ መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡
በዛሬው የሰላማዊ ሰልፍ ያሬድ አማረ ወኔ የተሞላባቸውን መፈክሮች ሲያሠማ የነበረ ሲሆን ከእርሱ መፈክሮች በተደጋጋሚ ከጓደኞቼ ጋር ፈገግ ሲያደርገን የነበረው “እመነኝ” የሚላት ቃል ናት፡፡
በሰለማዊ ሰልፉ ከኢ/ር ግዛቸው እስከ ወጣቱ ሃብታሙ አያሌው  ድረስ ያሉ ፖለቲከኞች በብዛት ይታዩ ነበር፡፡ ዳዊት ሰለሞን የአንድነት መኪና ውስጥ ሆኖ መረጃዎችን በማህበራዊ ድህረ ገፆች ሲያከፋፍል…. ነበር፡፡
ሁሉም ነገር ባዶ!
ሰልፉ በአድዋ ድልድይ አድርጎ የመከላከያ ቤተሰቦች መኖሪያ ኢካባቢ በተለምዶ ሲግናል ተብሎ ከሚጠራው የመካላከያዎች ቤት ውስጥ የሚኖሩ የስርዐቱ ደጋፊዎች በተደጋጋሚ በመሀል ጣታቸው ሰልፈኛውን በመሳደብ ስሜታዊ ለማድረግ ሲሞክሩ ነበር፡፡
ሰልፉ በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ወረዳ 8 ፊት ለፊት በሚገኘው ሜዳ ላይ ኢ/ር ግዛቸው ባደረጉት ንግግር ተቋጭቷል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የአመራር አባል የሆነው ሃብታሙ አያሌው ሲያደርግ የነበረውን
ይመልከቱ።
እኛ ስለሰላማዊ ሰልፉ ተጨማሪ ዝርዝር ከምንሰጥበት የበለጠ እነዚህ ፎቶዎች እና መፈክሮች ብዙ ይናገራሉና… የአንድነትን ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ በፎቶ የተደገፈ እንቅስቃሴ፤ ከዚህ በታች  ይመልከቱ።

søndag 4. mai 2014

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አንድነት የጠራውን የሰላማዊ ሰልፍ እንደሚቀላቀሉ አስታወቁ

May 3, 2014
በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የሰነበቱትና ቀሪዎቹ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ዛሬ ባደረጉት ሳምንታዊ የወጣቶች የውይይት ፕሮግራም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) የ‹‹እሪታ ቀን›› በሚል የጠራውን ሰልፍ በግንባር ቀደምነት በመቀላቀል ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ አስታውቀዋል፡፡
ወጣቶቹ ሰልፉን እንደሚቀላቀሉ ያስታወቁት ‹‹ሰላማዊ ሰልፉ ውጤታማ እንዲሆን በምን መልኩ ልናግዝ እንችላለን?›› በሚል አጀንዳ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከውህደት በዘለለ በሰላማዊ ሰልፍም ሆነ በሌሎች የትግል ስልቶች መተባበርና አብሮ መስራት እደግፋለሁ የሚል አቋም እንደሚያራምድ በተለያዩ ሚዲያዎች መግለጹ የሚታወቅ ሲሆን ወጣቶቹ በሰላማዊ ሰልፉ የሚያደርጉት ተሳትፎ ፓርቲው ለትብብር ያለውን አቋም ያሳያል ብለዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለሰላማዊ ሰልፉ ድምቀት የሚያገለግሉ ሜጋ ፎኖች፣ ጥሩምባዎችና ሌሎችም ሰልፉን ለማድመቅ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ይዘው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
Addis Ababa Semayawi party rally April 27, 2014