tirsdag 19. august 2014

ጠብ-መንጃ አናነሳም! (ተመስገን ደሳለኝ)

“ብሶት የወለደው” ኢህአዴግ ከሁለት አስርታት በፊት በሰሜን ተራሮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ጋር ያደረገውን የጎሬላ ውጊያ “አጃኢብ” በሚያሰኝ ቆራጥነት በድል መወጣቱ የማይታበል እውነትነው፤ ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላም ለሚሰነዘርበት ማንኛውም አይነት የኃይል ጥቃት፣ ያውም ማቸነፍ አለማሸነፉን ሳያሰላ በፍጥነት ዘሎ ለመዘፈቅ ሲያንገራግር የተስተዋለበት ጊዜም አልነበረም፤ አሀዱ ብሎ የአመፅ ትግል ከጀመረበት ዕለት አንስቶ ላለፉት አርባ ዓመታት ከጀብሃ እስከ ኢህአፓ፤ ከኦነግ እስከ ኦብነግ፤ ከትህዴን እስከ አርበኞች ግንባር፤ ከሻዕቢያ እስከ አልሸባብ… በስም ተዘርዝረው ከማያልቁ ብረት-ነካሽ ድርጅቶች ጋር ወደ ፍልሚያ ለመግባት ከመወሰኑ በፊት ሰላማዊ መፍትሄዎችን ግራና ቀኝ የመፈተሽ ትዕግስትም ሆነ ልባዊ ፍላጎት እንዳልነበረው የራሱ የታሪክ ድርሳናት ሳይቀሩ በግላጭ ይናገራሉ፡፡ በተለይም ሀገር በቀሎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች በእንዲህ አይነቱ አስገዳጅ ሁኔታ ነፍጥ አንግበው የመገኘታቸው ምስጢር በቀጥታም ሆነ በዘወርዋራው የሥርዓቱ እጅ ስላለበት መሆኑን የሚያስረዱ ማሳያዎች የበዙ ናቸው፡፡ ከነዚህ መሀል አንዱና ዋነኛው በርሱ አጋፋሪነት የፀደቀውን ሕገ-መንግስት፤ በፕሮፍ መስፍን ወልደማርያም አገላለፅ “በሕገ-አራዊት”ነት ቀይሮ በአደባባይ መብቶቻቸውን መጨፍለቁ ነው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በነፃ ምርጫ ማሸነፍም ሆነ ሥልጣን መጋራትን ‹ግመል በመርፌ ቀዳዳ…›ን ያህል ማጥበቡ እና “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” የምትለዋ የከረምች እብሪት ድርጅቶቹ “ዱር ቤቴ” እንዲሉ ያስገደዷቸው ገፊ-ምክንያቶች ስለመሆናቸው ቅንጣት ያህል አያጠራጥርም፡፡
በግልባጩ በበርካታ ድርሳናት ስለጀብዱውና ተጋድሎው የተተረከለት አብዮታዊ-ግንባሩ፣ ለሕዝባዊ እምቢተኝነት ፈሪ እና ድንጉጥ የመሆኑ ነገር ተደጋግሞ መወሳቱ ሌላ እውነት ነው፡፡ ብረት ያነሱ ተቀናቃኞቹን በብረት ለመጋፈጥ ካለው ወኔ  ይልቅ፣ ሰላማዊ ትግልን በተመሳሳይ ቋንቋ የማስተናገድ ፍርሃቱ እጥፍ ድርብ እንደሚልቅ በተጨባጭ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ በድንጋጤ ሲርበተበት፣ እንቅልፍ ሲያጣ፣ ግብታዊ እርምጃ ሲወስድ… የተስተዋለውም በሕግ የደነገገውን መብት ተንተርሰው የተቀሰቀሱየተቃውሞ ትግሎች የተጠናከሩበት ጊዜያት ላይ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የሰሞኑም ዘመቻ ነፃ-ፕሬስ ግባት ከዚሁ የሚመደብ ነው፡፡
በሰላማዊ የትግል ስልቶች ማዕቀፍ ስር የሚገኙ መብቶታቸውን የተጠቀሙ ቆራጦች ለተቃውሞ በወጡ ቁጥር፣ ቅጥ-ባጣ መልኩ መፍረክረኩን እና የእውር-ድንብር እርምጃ የመውሰዱን እውነታ ለማስረገጥ በተለያየ ጊዜ የተመለከትናቸው ማሳያዎችን እየጠቀሱ መሟገቱ አስቸጋሪ አይደለምና ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር ላስታውስ፡-
በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተነሳውንና የአካዳሚያዊ ነፃነትን የጠየቀውን ሰላማዊ ተቃውሞ ተከትሎ በመዲናይቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ንቅናቄ ምን ያህል የሚይዝ የሚጨብጠውን አሳጥቶት እንደነበረ ለመረዳት፣ በሃያና ሰላሳ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማይቱን ኗሪዎች (አብዛኛዎቹ በተቃውሞ ያልተሳተፉ) ከየቤታቸው እንዴት አፋፍሶ ለግፍ እስር እንደዳረጋቸው ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በወቅቱ ክስተቱ አገሪቱን ለሁለት ቀናት መንግስት-አልባ አስመስሏት እንደነበረ በተሳታፊነትም በታዛቢነትም ሁኔታውን የተከታተልን ዜጎች ሁሉ አንዘነጋውም፡፡

በ1995 ዓ.ም የሲዳማ ተወላጆች፣ ክልላዊነትን እና የሀዋሳ ከተማ ዕጣ-ፈንታን በሚመለከት ጥያቄ አንስተው በደቡብ ክልል ርዕሰ- መዲና ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ጊዜም፣ አብዮታዊ-ግንባሩ ምን ያህል ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ እንደነበረ ማስታወሱ ለዛሬው ጠ/ሚንስትርም ሆነ ለብዙዎቻችን የሚከብድ አይሆንም፤ ሥርዓቱ ያዘመታቸው የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት አባላት ሕጋዊውን የሲዳማ ተወላጆች ጥያቄ ለመቀልበስ፣ ጎዳናዎቹን በደም-አባላ በማጥለቅለቅ የፈፀሙት አሳዛኝ ጅምላ ጭፍጨፋ (ዘር ማጥፋት) በታሪክ መዝገብ ጥቁር ገፅ ላይ በማይፋቅ መልኩ ተከትቦ አልፏል፡፡ ይህም ሆኖ የዚህ ሰላማዊ ተቃውሞ ውጤት፣ ለፌደራል መንግስቱ፣ ክልሉን በኃላፊነት ሲመራ የነበረውን ኃይለማርያም ደሳለኝን፣ በሽፈራው ሽጉጤ እንዲተካ ያስገደደ የሽንፈት ፅዋ ማስጎንጨቱ ይታወሳል፡፡

በምርጫ 97 ዋዜማ ሚያዝያ 30 ‹‹ዴሞክራሲን እናወድስ›› በሚል መሪሕ-ቃል ‹‹ቅንጅት›› በጠራው ስብሰባ ላይ ተገኝቶ መስቀል አደባባይን ያጥለቀለቀው የሕዝብ ‹‹ሱናሜ››፣ ሥርዓቱን ለከባድ ድንጋጤ አጋልጦ፣ በሀፍረት አኮራምቶ፣ ለከፋ ስቃይ ዳርጎት እንደነበረስ ከቶ ማን ሊዘነጋው ይቻለዋል? ያኔ የተመለከትነው ገዥው-ፓርቲን ከፍተኛ ፍርሃት ላይ የጣለ አስደንጋጭ ትዕይንት፣ ዛሬም ድረስ ለሚተገብረው የቅድመ-ምርጫ አደን መስዋዕት እየዳረገን እንደሆነ ሁላችንንም የሚያስማማ እውነታ ነው (በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹ምን አልባት ሕዝቡ በቁጣ የቤተ-መንግስቱን አጥር ገርስሶ ሊገባ ይችል ይሆናል› በሚል ፍርሃት ከእነ ቤተሰቡ ደብረዘይት አየር ኃይል ግቢ ተሸሽጎ አሳልፏል የሚለው ወሬ ከሹክሹክታም በዘለለ በከተማዋ በስፋት ተናፍሶ ነበር)፡፡

ሕዝበ-ሙስሊሙ ያቀጣጠለው ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የተቃውሞ ትግልም፣ አገዛዙን እንዴት በፍርሃት እንዳራደው ለመረዳት በጉዳዩ ዙሪያ በየጊዜው የሚወጡ እርስ-በርስ የተምታቱ መግለጫዎችን እና ረብ-የለሽ ‹‹ዘጋቢ›› ፊልሞቹን መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ይህንን ፍፁም ሰላማዊና ስልጡን የተቃውሞ ንቅናቄን ለማፈን የተወሰዱት የኃይል እርምጃዎችም፣ የእነ አባይ ፀሀዬን የይስሙላ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከማጋለጡ ባለፈ፣ ድርጅታቸው-ኢህአዴግን ለሳልሳዊ የውስጥ ክፍፍል መዳረጉን የመረጃ ምንጮች ያወሳሉ፡፡
በአናቱም ግንባሩ፣ በተቃውሞ ጎራ በተሰለፉ ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ነውረኝነቱን በግላጭ በሚያሳይ መልኩ የራሱን ሰዎች አስርጎ በማስገባት ለመከፋፈል ከሚሞክርበት ማኪያቬሊያዊ ሴራ በተጨማሪ፣ አመራሩን እና የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉ አባሎቻቸውን በጥቅማ ጥቅም በመደለል፣ ከሀገር በማሳደድ፣ ከፖለቲካ ተሳትፎ ራሳቸውን አግልለው በፍርሃት ‹‹ጎመን በጤና››ን እያጉረመረሙ የበይ-ተመልካች ሆነው አርፈው እንዲቀመጡ የብረት መዳፉን ለመጫን እና ለመሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶቹ ማስፈፀሚያነት በቢሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት አፍስሶ ጠንክሮ የመስራቱ (እየሰራም የመሆኑ) ጉዳይ አከራካሪ አይደለም፡፡ ይህንን ኩነት በምኩንያዊነት ለማስረገጥ በኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የአቶ በረከት ስምዖን ምክትል የነበረውና ሀገር ጥሎ የተሰደደውን የቀድሞ ሚኒስቴር ዲኤታን የአቶ ኤርምያስ ለገሰን ምስክርነት መጥቀስ ተገቢ በመሆኑ፣ በቅርቡ ‹‹የመለስ ትሩፋቶች›› በሚል ርዕስ ለንባብ ካበቃው መጽሐፉ አንድ ማሳያ ላቅርብ፡-
‹‹በምርጫ 92 ኢህአዴግ መሸነፉን አስቀድሞ ካረጋገጠ በኋላ የተከተለው ስትራቴጂ የሕዝቡን ውሳኔ ባይቀይረውም ለማጭበርበር ጠቅሞታል፡፡ …የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት የሚያጠፉ ሶስት እርስ በእርስ የሚመጋገቡ ስትራቴጂዎችን ነደፈ፡፡ ስትራቴጂዎቹ እንደሚከተለው ነበሩ፤ በእጩ ምዝገባ ወቅት በተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ውስጥ ለኢህአዴግ የሚሰራ አስርጎ ማስገባት፤ በየወረዳው ምርጫ ቦርድ በሚፈቅደው መሰረት የተፎካካሪ እጩዎችን ከተቻለ በማሳመን ካልተቻለ በመደለልና በማስገደድ ራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረግ የሚሉ ነበሩ፡፡›› (ገጽ 58-59)
በነገራችን ላይ ኤርሚያስ ለገሰ በዚህ መጽሐፉ ለእንዲህ አይነቱ እኩይ ሴራ ስላልተበገረ አንድ ያልተዘመረለት ጀግና በዝርዝር አስፍሮልናል፡፡ ሰውየው በቅፅል ስሙ ‹‹አበበ ቀስቶ›› ተብሎ የሚታወቀው እና በምርጫ 92 በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 24 ኢዴፓን ወክሎ ለውድድር የቀረበው ክንፈ ሚካኤል ደበበ ነው፡፡ የአገዛዙ ካድሬዎች ክንፈ በአካባቢው ጠንካራ ድጋፍ እንዳለው ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበረ ብርቱ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፤ በዚህም ‹‹ምርጥ›› የሆነ አደናቃፊ ስልት ተነድፎ ለመተግበር መሞከሩን አቶ ኤርሚያስ እንደሚከተለው ይነግረናል፡-
‹‹(ክንፈ) ከምርጫው ፉክክር ገለል የሚልበት አማራጮች ታሰቡ፡፡ እሱን ማስፈራራቱ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ምድር ቢንቀጠቀጥም የሚፈራ ሰው አይደለም፡፡ በቁጥጥር ስር ለማዋል ደግሞ ወንጀል ሲሰራ እጅ ከፈንጅ መያዝ አለበት፡፡ ስለዚህ የቀረው የመጨረሻ አማራጭ በገንዘብ መደለል ሆነ፡፡›› (ገጽ 65)
ተራኪው ይቀጥላል፤ ለድለላው 50 ሺ ብር ወጪ ይደረጋል፤ በደላይነት ደግሞ ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም (ይህ ሰው የወቅቱ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ መሆኑን ልብ ይሏል) እና ኪሮስ የተባሉ የህወሓት አባላት ይመደባሉ፤ አቤም ሊያግባቡት ቤቱ ድረስ በመጡ ግለሰቦች ሃሳብ በመስማማቱ፣ ልዑልና ግብረ-አበሩ 35 ሺውን ለራሳቸው አስቀርተው 15ሺ ብር ይሰጡታል፤ የወረዳው የኢህአዴግ አመራርም በተከተለው ‹‹እፁብ-ድንቅ›› መፍትሔ ለጊዜው ከስጋት ነፃ ይሆናል፤ ግና፣ ይህ ሁኔታ ብዙ አልቆየም፡፡
ከሳምንታት በኋላ፣ ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ሸገር ተወልዶ፣ ሸገር ያደገው የአራዳ ልጅ አበበ ቀስቶም በታሪክ ሲዘከር የሚኖርበት ውሳኔውን እንዲህ ሲል አረዳቸው፡‹‹የተጋበዝኩትና ብራችሁን የተጠቀምኩት እናንተ ጋር የማይነጥፍ የብር ማምረቻ ስላለ ነው፡፡ ምርጫ የምወዳደረው ግን ለገንዘብ ሳይሆን ይህን አስከፊ ሥርዓት ለመጣልና ለነፃነቴ ነው፡፡ በዚህ ላይ ለመደራደር ህሊናዬ አይፈቅድም፡፡›› (ገጽ 65-66)
ዛሬ ‹‹አሸባሪ›› በሚል ክስ ተወንጅሎ፣ የሃያ አመት የእስር ቅጣት ተላልፎበት፣ በአሰቃቂው የቃሊቲ ወህኒ ተጥሎ የሚገኘው አበበ ቀስቶ እንዲህ ያለ ድፍረትና ቁርጠኝነት የነበረው ጀግና ስለመሆኑ አብዮታዊ ግንባሩን አደግድገው ያገለገሉት ካድሬዎች ጭምር እየመሰከሩለት ይገኛሉ፡፡
ከግል ገጠመኜ ደግሞ አንድ ልመርቅ፤
የ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኜ በምሰራበት ወቅት፣ አቤ በ‹‹አሸባሪ››ነት ተከሶ ፍርድ ቤት ይመላለስ ነበር፤ ከዕለታት በአንዱ ቀንም እጅግ የሚያሳዝንና የግፉአን እናቶችን የሀዘን እንባ የሚወክል ጽሑፍ ከወህኒ ቤት ይልክና በጋዜጣችን ላይ ይታተማል፡፡ ቀደም ብሎ እስክንድር ነጋ፣ አንዱአለም አራጌ እና ናትናኤል መኮንንም በተመሳሳይ መልኩ የላኳቸው ጽሑፎች ተስተናግደዋል፤ ይህ ከሆነ ሁለት ሳምንት በኋላ ‹‹የተከበረው›› ፍርድ ቤት እነዚህን ጽሑፎች እንዲታተሙ በመፍቀዴ ‹‹ችሎት መድፈር›› የሚል ክስ መስርቶብኝ ዳኞች ፊት ቀረብኩ፤ ከአራቱ ታሳሪዎች መካከልም አቤ ተለይቶ ተጠርቷል፤ የመሀል ዳኛውም አንድ ጥያቄ ጠየቀው፡-
‹‹ይህንን ጽሑፍ አንተ ነህ የጻፍከው?››
አበበ ቀስቶ መልስ ለመስጠት አልተቻኮለም፤ ዳኞቹ፣ ዓቃቢ-ሕግጋን እና የችሎቱ ታዳሚዎች በሙሉ ምን ሊል ይችላ ይሆናል? በሚል ጉጉት እየጠበቁት ነው፤ የእኔ አይደለም ቢልስ? ማን ያውቃል? …ጥቂት ሰከንዶች በአስጨናቂ ዝምታ ካለፉ በኋላም፣ ልበ-ሙሉ ፖለቲከኛ ፈገግ ብሎ መናገር ጀመረ፡-
‹‹አዎ፣ እኔነኝ የጻፍኩት! ፍላጎቴም እዚህ እናንተ ፊት ላነብላችሁ ነበር፤ ሆኖም ሰዓት የለንም ብላችሁ ስትከለክሉኝ ጊዜ ነው፣ ለተመስገን የላኩለት!››
(በቀጣዩ ሳምንት ስለመጽሐፉ በስፋት ለመወያየት ቀጠሮ ይዘን፣ ወደጀመርነው ርዕሰ-ጉዳይ እንመለስ)
ስለምን ነፍጥ አናነሳም?
በኢሕአዴግ ዘመነ-አገዛዝ ብረት የማንሳትን ተገቢነት የሚያቀነቅኑ ልሂቃን፣ ለትግሉ ስልት አግባብነት የሚያነሷቸውን መከራከሪያዎች በሁለት መልኩ ልናያቸው እንችላለን፡-
በቀዳሚነት ከገዥው-ፓርቲ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር አያይዘው፣ ለአቻቻይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያስፈልጉ ባህሪያት በፍፁም የማይስተዋሉበት፣ ይልቁንም ‹ሕገ-መንግስታዊነትን፣ የሕግ የበላይነትን፣ የተቋማት ነፃነት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን፣ የመሰሉ ዕሴቶችን በመጨፍለቅ የሚታወቅ ነው› የሚል ጥቅል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ እውነታው እነርሱ እንደሚሉት ቢሆንም እንኳ፣ ብረት የሚቀላቀልበት ትግል የሚያፈራርሳቸውን ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን እንደገና ከፍርስራሹ ዓመድ ላይ ለመጀመር የሚያስገድድ መሆኑን ግን የዘነጉት ይመስለኛል፡፡
ሁለተኛው ጭብጥ፣ የማሕበረሰቡን የፖለቲካ ባህል እና የአንድ ወቅት የሰላማዊ ትግልን ሙከራ ክሽፈት በማውሳት የሚቀነቀነው ነው፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ለጦረኛነት፣ ተዋስኦን ለሚጨፈለቅ የመጠፋፋት መንገድ የቀረበ የመሆኑን መሞገቻ ለክርክር በመግፋት የሃሳባቸው ማጠንጠኛ ያደርጉታል፡፡ ይሁንና የመድበለ-ፓርቲ ሥርዓትን እና ነፃ የአደባባይ ክርክርን ያልተላመደ ማሕበረሰብን አሁንም ለትጥቅ ትግል መጥራት ይህንኑ አሉታዊ ሕዝባዊ ባህርይ ከማጠናከር የዘለለ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው ለመሟገት የሚያስችሉ በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ ‹ማሕበረሰቡ ለተራዘመ ሰላማዊ ትግል አይሆንም› ብለው የሚከራከሩ ጸሐፍት የሚጠቅሱት፣ 97 ላይ የተጨናገፈውን እንቅስቃሴና መሰል ሕዝባዊ ተቃውሞን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በተለይም የቅንጅት ጉምቱ ፖለቲከኞች እስኪበቃን እንደነገሩን፣ ስህተቱን ሁላችንም የምንጋራው ይሆናል (የኢሕአዴግ ቢልቅም ቅሉ!)፡፡ ግና፣ የወቅቱ ክስተት ከሰላማዊ ትግል አማራጮች አነስተኛ ሚና የሚሰጠውን የምርጫ ፖለቲካን ብቻ ግብ ያደረገ መሆኑ ‹ትግሉን ሞክረነዋል› የሚለውን መከራከሪያ ያጎደለው ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ይልቅ፣ ሰላማዊ ሕዝባዊ አብዮትን አንድም ጊዜ በቅጡ ሳንሞክር (በቀቢፀ-ተስፋ ተሞልተው የሥልጣን ጥማት ካሰከራቸው ቀልባሾች ሳንታደገው) ጠብ-መንጃ ወደማንገብ መመለስ ቢያንስ በቂ መከራከሪያዎችን ያሳጣል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከላይ በጥቅሉ ከጠቀስኳቸው ጭብጦች ባለፈ፣ እነዚህ ኢህአዴግ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ማግስት አንስቶ ነፍጥ የነከሱ ቡድኖች፣ንፁሃን ዜጎችን እንዳሻው እንዲያስር እና እንዲያሰድድ ፖለቲካዊ ሰበባ-ሰበቦች ከመስጠት ባሻገር ያዋጡት በጎ አበርክቶ (ተጨባጭውጤት) አለመኖሩን ልብ ማለት ያሻል፡፡
የሆነው ሆኖ የዚህ ጽሑፍ ተጠየቅ ከተለመዱት ሁለቱ የትግል ስልቶች አንዱን መባረክ እና ሌላኛውን ማውገዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም በህወሓት ጠቅላይነት የሚመራው ገዥው-ግንባር፣ ከብረት ትግል ይልቅ፣ በሕገ-መንግስቱ ማዕቀፍ ስር ለሚጠቃለሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ብርክ የሚይዘው መሆኑን በማውሳት፤ ባለፉት እትሞች በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› የጠቀስኳቸውን አተገባበሮች በበቂ ሕዝባዊ ጉልበት መግፋት እንደሚያዋጣ ዳግም አፅንኦት ለመስጠት ነው፡፡ ርግጥ ነው ሁላችንንም ግራ-ገቡ ኢህአዴግ ፍርሃት በናጠው ቁጥር ሲያሻው በገፍ ወህኒ እያጎረ፤ ሲፈልግ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንኳን ያልጨረሱ ብላቴኖችን ግንባር በጥይት እያፈረሰ፣ በል ሲለው ደግሞ ይህንን መከራ እና ስቃያችንን የምንተነፍስበት ሚዲያ እያሳጣን በምሬት እንደሞላን አንክድም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም ግን ድርጅቱ የተካነበትንና ለፍልሚያ የሚመርጠውን ጠብ-መንጃ አናነሳም፡፡ ጠብ-መንጃ የማናነሳው ልበ-ሙሉነታችን ከህወሓት-ኢህዴን መስራቾች የጉብዝና ዘመን ያነሰ ሆኖ በመገኘቱ አይደለም፤ ሚሊዮናት ዘመን ተጋሪዎቼ ለሀገር ጉዳይ፣ ለሕዝብ ጥቅም ግንባራቸውን እንደማያጥፉ አውቃለሁና፡፡ የደኑ መመንጠር ምሽግ ስላሳጣን ወይም የምናፈገፍግበት መሬት ስለጠፋንም አይደለም፡፡ ብረት-ጠል የሆንነው፣ በሰላማዊ ሕዝባዊ ዓመፅ ይህን ሥርዓት አስቁሞ፣ ኢትዮጵያን ማደስ እንደሚቻል ካለን የፀና እምነት ባሻገር፣ ነባራዊውም ሁነት ጮኾ የሚያስረግጥልን ይሄንን በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ የመጨረሻ ሙከራ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ዳግም ነፍጥ እንዳይነሳ አስተማማኝ ዋስትናን ሰጥቶ እንደሚጠናቀቅም አልጠራጠርም፡፡ በረዥሙ የጭቆና አገዛዝ በተለይም በእርስ በርስ ጦርነት ለተጎዳና ለደኸየ ሕዝብ፣ የወጣቶቹን ደም ለሚያስገብር ትግል አሳልፎ መስጠት፣ የነገይቱን ኢትዮጵያ ባድማነት ማወጅ ነውም ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ‹ብረት ያዋጣል› የሚሉ ኃይሎች በመረጡት መንገድ ሥርዓቱን አስገድደው ወደ ብሔራዊ እርቅና አገራዊ ሕዳሴ ሊያመጡልን ከቻሉ፣ የትግላቸው ታላቅ አበርክቶ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ ወደምናልመው ሁለንተናዊ ሕዳሴ ለመድረስም የሚኖራቸውን ሚና በምንም አይነት መነሾ ላሳንሰው አይቻለኝም፡፡
ከዚህ በላቀ በተከታታይ የተወያየንበት የ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ማዕቀፍ፣ በሕዝባዊ የአደባባይ ዓመፅ ሥርዓቱን ከማውረዱ በዘለለ፣ በደም-እልባት ያጣነውን አንድ ዋነኛ እሴት አውሶን የሚያልፍ ይመስለኛል፡፡ በሰላማዊ አብዮት የሚሳተፍ ዜጋ አገራዊ ሕዳሴን በማምጣት፤ ሁላችንንም በእኩልነትና በነጻነት የሚያኖር ፖለቲካዊ ሥርዓት ማዋለዱ አይቀሬ ነው፡፡ በመጪው አስተዳደር የሚከወኑትን ሀገራዊ ጉዳዮች በያገባኛል የሚከታተል፣ እያንዳንዱን የዜግነት መብቱን አጠንክሮ የሚጠይቅ እና በውይይት (በሃሳብ ብዙሃነት) የሚያምን ትውልድ በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ሂደት እንደሚፈጠር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የንቅናቄው አድማስ ሁሉን አቀፍ መሆኑ ከተሳካለት ደግሞ በድህረ-ለውጡ የሚነብረውን የፖለቲካ ባህል በእጅጉ የዘመነ ያደርገዋል፡፡ ‹የአብዮተኞች አባት› ተብሎ የሚወደሰው ካርል ማርክስ ከጓዱ ፍሬዴሬክ ኤንግለስ ጋር በጻፈው መድብል ላይ ይህን እውነት አስረግጦ አልፏል፡፡ ‹‹German Ideology›› በሚለው ያሰላሳዮቹ የጋራ ስራ ላይ የአብዮት ሂደት ዋና ፋይዳ ከለውጡ በኋላ የሚፈጠር ማሕበረሰብ የነቃ እንደመሆኑ፣
መጪዎቹ የሥልጣን ተረካቢዎች በቁመቱ ልክ ካልሆኑ (ካልመጠኑት) ለእነርሱም አስቸጋሪ እንደሚሆን የማስረገጡ እውነታ ነው፡፡
ለዚህም የቅርቡን የአረቡ መነቃቃት ማየት ያዋጣል፡፡ የግብፅ ሕዝብ ከአብዮቱ በፊትና በኋላ ያለውን የንቃት ልዩነት ማንም የሚያስተውለው ነው፤ ዛሬ ላይ የምናየው ማሕበረሰብ የሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ ከነበረበት አንፃር ሲታይ ፍፁም ፖለቲካዊ ስለመሆኑ በብዙዎች ተወስቷል፡፡ ለእያንዳንዱ አገራዊ ጉዳይ ያገባኛል በማለት መሟገትን የዕለት ተዕለት ስራው አድርጎታል፡፡ ከዚህ አብዮታዊ ሃሳብ ትይዩ በብረት የሚመጣ ለውጥ፣ ተመልሶ ማሕበረሰባዊ ፍዝነት ውስጥ እንደሚጥለን መረዳታችንም፣ መጪውን የአብዮት አማራጭ ብቸኛው ትውልዳዊ ዕዳ ወደማድረጉ ገፍቶታል፡፡ ከሞት ይልቅ ህይወት፣ ከድቀት ይልቅ ጥንካሬ፣ ከመበታተን ይልቅ አንድነት የሚሰጠንን ሰላማዊ የለውጥ ንቅናቄ በቀጣዩ ዓመት ስለመከወን ደግመን ደጋግመን ማሰላሰል ደግሞ የዘመኑ አስገዳጅ ኃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የሕዳሴ አብዮት ለፖለቲካው ( አስራት አብርሃም)

ወዳጄ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የህዳሴው አብዮት አይቀሬ እርግጠኛ ሆኗል፤ እኔም ያለኝ ግምት ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም የዛሬው ፅሁፌ የሚያተኩረው የህዳሴው አብዮት እንዴትና የት ይጀምር? በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይሆናል። በእኔ እምነት የህዳሴው አብዮት መጀመር ያለበት ከራሱ ከተቃውሞ ጎራ ነው የሚል ነው። ምክንያቱም የለውጡን ሀይል የሚመራው ይሄ የተቃውሞ ጎራ ስለሚሆን በመጀመርያ ውስጡን ማጥራትና ማጠናከር ስላለበት ነው። ስለዚህ፣ ከሁሉም ነገር በፊት የተቃውሞ ጎራው በትክክልና በተገቢው ሁኔታ እንዲታደስና እንዲለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው። ስለፖለቲካው መታደስና መለወጥ ሲታሰብ ደግሞ እንዴት ነው የሚታደሰው? እንዴት ነው የሚለወጠው? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ይሆናል። የመጀመርያው ነገር፣ እስካሁን ከተጓዝንበት ኋላቀርና ውጤት አልባ የትግል ስልት የሚያወጣን፣ የተለየ ያካሄድ ለውጥና የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ለማደረግ የሚያስችለን ብቁ የሆነ ፖለቲካዊ አመራር ወደፊት እንዲመጣ ማድረግ ነው። በተለይ ደግሞ ፖለቲካዊ ትግሉ በአስራር፣ በአደረጃጀት፣ በዴሞክራሲያዊ ባህልና በበሳል አመራር ማጠናከርና ማነፅ ቀዳሚው ተግባር ነው የሚሆነው።
በቅርቡ ሊካሄድ ታስቦ የነበረውና በኋላ በምርጫ ቦርድ ምክንያት ለጊዜው የተቋረጠው የአንድነትና የመኢአድ ውህድ ፓርቲ ፕሬዝደንት የሚሆን ሰው ለመምረጥ በአንድነት ውስጥ የታየው እጅግ ማራኪና አስተማሪ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ውድድር፣ የሰለጠነ የእጩዎቹ ደጋፊዎች ቅስቃሳ የዚሁ የህዳሴው አብዮት ጅማሮ አድርጌ ነው የምወስደው። ይሄ ዴሞክራሲዊ የሆነ ውድድር በማህበራዊ ሚዲያዎች፣ በጋዜጦችና በመፅሔቶች በጉልህ ይታይ ስለነበር የተቃውሞ ጎራ አባላት፤ ህዝቡ፣ የገዥው ፓርቲ ሰዎችም ጭምር በአንክሮ እንዲከታተሉት ምክንያት ሆኗል። ይህ እንቅስቃሴ አንድነትን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚወስደው ከሆኑም ባሻገር ልክ እንደ ዐረቡ አብዮት ወደ ሁሉም የተቃውሞ ጎራ የሚዛመት አዲስ መንፈስ ነው ብዬ ነው የማስበው። ምንም እንኳ በተወሰነ መልኩ በዴሞክራሲያዊ ውድድርና በውስጣዊ መከፋፋል መካከል ያለውን ልዩነቱ በትክክል ያልገባቸው ወይም እንዲገባቸው ያልፈለጉ አንዳንድ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር የነበረ ቢሆንም በአጠቃላዩ እንቅስቃሴ ሲታይ ግን በኢትዮጵያ የፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ በአዲስነቱ፣ በፈር ቀዳጅነቱና በአንፀባራቂነቱ ሊታወስ የሚችል ነው። ከዚህ ልምድ በመውሰድ የአንድነት አባላት ዴሞክራሲያዊ በሆነና በሰለጠነ መንገድ መሪዎቻቸውን መምረጥ የሚችሉበት ሁኔታ ከፈጠሩ፤ የሌሎች ፓርቲ አመራር አባላትም በተመሳሳይ መንገድ መሄድ የማይችሉበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ስለዚህ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የተሳካ የተሀድሶ አብዮት ማካሄድ ከቻልን ቀጥሎ በመኢአድ፣ በመድረክ፣ በአረና፣ በኦፌኮ፣ በደቡብ ህብረት፣ በኢዴፓና በአጠቃላይ በተቃውሞ ጎራ ባሉ ኃይሎች ሁሉ ይሄ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲቀጣጠል እድል የሚፈጥር ነው የሚሆነው። በመሆኑም ውህደቱ ለጊዜው ቢጨናገፍም በአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ የተጀመረውን የትግል መነሳሳት መቀዝቀዝ የለበትም። ይሄ መነሳሳት ፓርቲውን በአዲስ መንፈስና በአዲስ ፖለቲካዊ አካሄድ ለማስኬድ በሚያስችል መልኩ ልንጠቀምበት እንችላለን። ባለበንት እንድንረግጥ ከሚያደርገን ያረጀና ያፈጀ ፖለቲካዊ አሰራር ፖለቲካው ይላቀቅ ዘንድ የለውጥ ኃይሉ በአንድነት ውስጥ የፓርቲው ህግና ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት የተሀድሶ እና የለውጥ እንቅስቃሴ ማካሄድ መቻል አለበት። ይሄ የለውጥ እንቅስቃሴ የፓርቲውን አንድነትና ጥንካሬ አስጠብቆ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣ ከሆነ በሁሉም የተቃውሞ ጎራ ውስጥ የሚቀጣጠል፤ በእንቅልፍና በድንዛዜ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ሁሉ የለውጥና የፀደይ አብዮት ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆን ነው።
ይሄ ብቻ አይደለም፤ እውነተኛ የተቃውሞ ኃይሉ ወደ አንድ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አውራ ፓርቲነት የሚለወጥበት ሁኔታ እንዲፈጠርም ምክንያት ይሆናል። በሁሉም ፓርቲዎች ያለው የየራስ ፓርቲ ጥግ አስይዞ ፖለቲካውን ባለበት እንዲረግጥ እያረገ ያለው ፖለቲካዊ አሰራርና ኋላቀር አካሄድ መለወጥና ከስሩ መንቀል ከተቻለ፤ የአንድ አውራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ውልደት እውን የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ከዚያ በኋላ አንድነት፣ መኢአድ፣ ሰማያዊ፣ ኦፌኮ፣ አረና ወዘተ የሚል ሳይሆን አንድ የተጠናከረ የተቃውሞ ጎራ መንፈስ ብቻ ነው የሚኖረው። ትግሉም በአምባገነኑ ገዥው ፓርቲ እና በዴሞክራሲያዊው አውራ ፓርቲ መካከል ብቻ ስለሚሆን በሰላማዊ ትግል ህዝባዊ ማዕበልና ንቅናቄ ለመፍጠር የተመቻቸ ነው የሚሆነው። የህዳሴው አብዮት በተቃውሞ ጎራ መካሄድ አለበት ሲባል፤ የተቃውሞ ጎራው በውህደትም ይሁን በሌላ መንገድ (ከየፓርቲው እየፈረሰ የተሻለ ወደ ሚለው ፓርቲ በመግባት) ወደ አንድ የለውጥ ኃይልነት ይሰባሰባል፤ ይደራጃል። ከዚያ ኋላ በጠቅላላ በሀገሪቱ የህዳሴ አብዮት እንዲካሄድና እውን እንዲሆን ማደርግ የሚከብድ አይሆንም። እንዲህ በተበታተነ ሁኔታ ከተገባ ግን መጨረሻው ያው እንደተለመደው ውድቀት ነው የሚሆነው ነው።
የተቃውሞ ፖለቲካ የለውጥ እና የመነሳሳት ሰፈር፣ የአዲስ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ መንፈስ ጎራ መሆን አለበት እንጂ በተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች የከሰሩና የከሸፉ ፖለቲከኞች ማጠራቀሚያና መደበቂያ ዋሻ መሆን የለበትም። በራስ ውስጥ የህዳሴ አብዮት ማካሄድ ወሳኝ ቅድመ ሁነት የሚሆነው፣ በፖለቲካው ጎራ እየተስተዋለ ያለው አባታዊነት፣ ቡድናዊነትና ራዕይ አልባነት ይቀየር ዘንድ ነው። ለዚህ ደግሞ በመጀመርያ የፓርቲ አባላት በፓርቲያቸው ውስጥ ያላቸው መብት እኩል መሆኑ፤ ከየትኛውም የፓርቲያቸው አባልና አመራር ጋር የሚኖራቸው ማንኛውም ዓይነት ግንኙነትም በእኩልነትና በነፃነት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ታውቆና ተረጋግጦ ኋላቀርና ፊውዳላዊ ከሆነው የጌታና የሎሌ ዓይነት ግንኙነት ነፃ መውጣት አለባቸው። ከዚህም ባሻገር ፖለቲካ ማለት የአንድን ግለሰብ ወይም የተወሰነ ቡድን ምንዝር ሆኖ መኖር አድርገው የሚያስቡ አባላት ካሉ በተገቢው ሁኔታ ማሰልጠንና ማስተማር ያስፈልጋል። በተቋውሞ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር የዴሞክራሲ እና የሌበራሊዝም ባህል ጠንቅቆ ያለማወቅ፤ በአጠቃላይ ደግሞ የፖለቲካ እውቀት ማነስ ነው። ስለዚህ ይሄ ሁኔታ መቀየር አለበት፤ ይሄ የሚቀየረው ደግሞ ለአባላትና ለደጋፊዎች ተደጋጋሚ የሆነ ስልጠና መስጠት፤ የክርክርና የውይይት መድረኮች በማዘጋጀች ተመሳሳይና ተቀራራቢ የሆነ ፖለቲካዊ አቅምና ራዕይ መፍጠር ሲቻል ነው። ከዚህም በተጨማሪ በተቻለ አቅም የጥናትና የንባብ ማዕከላት በማቋቋም በፅንሰ ሀሳብ እና በፖለቲካዊ እውቀት የታነፁ ጠንካራ አባላትና ደጋፊዎች እንዲኖሩ በማድረግ ፖለቲካዊ ትግሉ በብቃትና በጥበብ ለመምራት የሚያስችል አቅምና ሁኔታ መፍጠር ይቻላል።
አሁን ባለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የፓርቲ ፖለቲካ ብቻውን ብዙም አዋጪ አይደለም፤ ትግሉ ወደ ህዝባዊ ማዕበልና ንቅናቄ መቀየር ካለበት ሰፋ ያለ መዋቅር መፍጠር ያስፈልጋል። ይሄ ህዝባዊ ማዕበልና ንቅናቄ ደግሞ አሁን ባሉት ድኩማን ፓርቲዎች ሊመራ የሚችል ነገር አይደለም። ሲጀመር በየፓርቲዎቹ ያሉት መሪዎች ከፍተኛ የግል የስልጣን ጥም ያለባቸውና በደመነ ነፍስ ፖለቲካውን መምራት የሚፈልጉ፤ ራዕይ አልባ መሪዎች ናቸው። በመሆኑም አሁን ልናካሄደው እያሰብነው ያለውን ፍፁም ሰላማዊ የሆነ፣ ዘመናዊ የለውጥና የህዳሴ እንቅስቃሴ ለመምራት አቅም አላቸው ተብሎ የሚታሰብ አይደለም። እኔ በበኩሌ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ በዶ/ር መራራ ጉዲና፣ በኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው እና በመሳሰሉት የስልሳው ትውልድ ቅሪቶች ትግሉ ተመርቶ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም። ሰላማዊ ትግሉ ለውጥ እንዲያመጣ ከፈለግን ፖለቲካው ላለንበት ዘመን በሚመጥኑ ጠንካራና ቆራጥ ሰዎች መመራት አለበት። የአንዷለም አራጌ፣ የናትናኤል መኮነን፣ የሀብታሙ አያሌው፤ የዳንኤል ሽበሺ ፓርቲ ከፖለቲካዊ እስር ይቅርታ ጠይቆ በተፈታ ሰው ሊመራ የሚችለው እንዴት ነው! አንዷለም አራጌ ከስርዓቱ ጋር ተደራድሮ፣ ይቅርታ ጠይቆ መውጣት፣ ከዚያም ሊቀመንበር መሆን አቅቶት እኮ አይደለም! ዳገቱ ላይ የሚቆም ሰው በመጥፋቱ እኔ እስኪ መስዋዕት ሆኜ ምሳሌ ልሆን ብሎ ነው፤ በእስር ቤት መከራና ግፍ እየተቀበለ ያለው። ለእነዚህ ጀግኖች እያስተላለፍነው ያለው መልዕክት እኮ ትክክል አይደለም። በግፍ ያሰራቸውን ሰርዓት ይቅርታ ጠይቀው እንዲወጡ የሚያደርግ ነው። ለዚህ ነው ለመታሰርና ለመሞት የተዘጋጁ አባላት በተመሳሳይ ሁኔታ ለመታሰርና ለመሞት በተዘጋጀ መሪ መመራት አለባቸው የምለው።
እኔ ለኢንጂነር ግዛቸው እንደመሪዬም፣ እንደ አንድ የሀገሬ አንጋፋ ፖለቲከኛም ትልቅ አክብሮት ነው ያለኝ፤ ለፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና ለዶ/ር መራራ ጉዲናም እንዲሁ ተመሳሳይ የሆነ አክብሮት አለኝ። በጊዚያቸው ያደረጉት ተጋድሎም ቢሆን እጅግ የሚመሰገን ነው። በተለይ ዶ/ር መራራ ጉዲና በኦሮሞ ህዝብ ፖለቲካዊ ትግል ላይ የራሳቸው አሻራ ያኖሩና በዓይነቱ የተለየ የትግል መንገድ ያሳዩ ትልቅ ሰው ናቸው። ለዚህ አበርክቷቸው ትልቅ ምስጋና ሊሰጣቸው የሚገባ ነው። ነገር ግን እነዚህ አንጋፋ የፖለቲካ መሪዎች ባለፉት ሀያ አመታት ትግሉን መርተው የሚፈለገው ያህል አመርቂ ለውጥ አላመጡም በሚለው መሰረታዊ ነገር ላይ ማትኮር ያሻል።
ስለዚህ ከእኛ ወዲያ ላሰር ከሚል የግል ስሜትና ፍላጎት ወጥተው እስኪ ደግሞ ከታች ያሉት አዳዲስ ትውልዶች ይምሩትና እንየው፤ እኛ ደግሞ አጠገባቸው ሆነን ምክርና ድጋፍ እንስጥ ወደሚል በጎ ሀሳብ መምጣት መቻለ አለባቸው። በእውነቱ እንነጋገር ከተባለ፣ ኢንጂነር ግዛቸው በጣም ትልቅ ሥራ ሰሩ የሚባለው ተመልሰው ወደ መሪነት ሲመጡ ካቢኒያቸው ብቃት ባላቸው ታጋዮችና ምሁራን እንዲዋቀር ማድረጋቸው ነው። ተክሌ በቀለ፣ በላይ ፍቃዱ፣ ስዩም መንገሻ፣ ዳንኤል ተፈራ፣ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ፣ ሰሎሞን ስዩም፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳዊት አስራደ፣ ዘካርያስ የማነ ብርሃን፣ አለነ ማህፀንቱንና ሌሎችም ያየን እንደሆነ ሥራቸውን ለማመስገን እንገደዳለን። በእድሜም ቢሆን በወጣትነት እድሜ ላይ ካሉት ጀምሮ እስከ ጎልማሳ እድሜ ድረስ ያሉ ናቸው። ይሄ በራሱ ፈር ቀዳች የሚባል ዓይነት ነው። ችግሩ ግን እንዲህ ዓይነቱ ጠንካራ ስብስብ የያዘ ካቢኔ ለራሳቸው ለኢንጂነሩም ቢሆን ፈታኝ የመሆኑ ነገር ነው። እንዲህ ያለ በልምድ፣ በትምህርትና በእውቀት የተጠናከረ ካቤኔ መሪ መሆን ባንድ በእኩል መታደል ሲሆን፣ በሌላ በእኩል የግል ስሜትና የክብር ጉዳይ የሚቀድም ከሆነ ደግሞ የዚያው ያህል ስራዎች እንዲበላሹ፣ አብሮ የመስራትና የመተጋገዙ መንፈስ እንዲዳከም ምክንያት ይሆናል።
በመሰረቱ ለውጥ የምንፈልገው በፖለቲካው ዘገምተኝነት እጅግ በጣም ስለተሰላቸን ነው። ለውጥ እንፈልጋለን፤ ፖለቲካው ከገባበት የአዙሪት ሽንፈት የሚላቀቅበት መንገድ እንፈልጋለን፤ ስለዚህ እነዚህ አንጋፋ ፖለቲከኞች እንቅፋት መሆን የለባቸውም፤ ወይም ራሳቸውን ለመለወጥና በተገቢው ሁኔታ ትግሉን ለመምራት ቆርጠው መነሳት አለባቸው፤ ወይም አቅሙ ላላቸው ማስተላለፍ መቻል አለባቸው። ካሁን በፊት እንዳልኩት የፖለቲካ ብቃት በእድሜ ማነስም ሆነ መብዛት የሚገናኝ አይደለም። ችግሩ ያለው የቀደመው ትውልድ ትንታጉና ብቃት የነበረው ሁሉ በልዩ ልዩ መንገድ ማለቁ ነው። አሁን የዚያ ትውልድ አመዱ ብቻ ነው የቀረው ማለት ይቻላል፤ ያሉትም ቢሆኑ በእድሜ መግፋት፣ በኑሮ ጫና እንዲሁም በዴሞክራሲያዊ ባህል እጥረት ምክንያት አሁን ያለውን ትግል ለመምራት ይቸገራሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ። ስለዚህ ፖለቲካዊ ፍላጎትና መሪ የመሆን ምኞት ካላቸው፤ ቢያንስ በዴሞክራሲያዊና በሰለጠነ መንገድ የምናደርገውን የለውጥ ትግል እነርሱም በተመሳሳይ ሁኔታ በሰለጠነ መንገድ መታገልና መወዳደር ይችላሉ፤ በፖለቲካው መስክ እስካሉ ድረስ መብታቸውም ነው። ነገር ግን ኋላ ቀር ከሆነው የጠልፎ መጣል ሴራ እና የፍረጃ ፖለቲካ መውጣት መቻል አለባቸው።
ከሁሉም ነገር በፊት ለሀገርና ለህዝብ ነው መታሰብ ያለበት። በፖለቲካው ትግል መስክ ያገናኘንም ዋነኛው ምክንያት ይሄ የሀገር እና ህዝብ ጉዳይ ነው። የህዳሴው አብዮት ማካሄድ አስፈላጊ የሚሆነው የተወሰነ ቡድን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማርካት ሳይሆን በጠቅላላ ሀገርና ህዝብ ለመለወጥ፤ የህግ የበላይነት የሰፈነበት የተደላደለ ህገመንግስታዊ ስርዓት ለማምጣት ነው።
በሌላ መልኩ ካየነው ደግሞ፣ የተቃውሞ ጎራው የተሳካ ተሀድሶ ማካሄድ ከቻለ፣ በገዥው ፓርቲ ቤት ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን የሚችል ነው። ከዚህም ባሻገር ትልቅ የሆነ የአስተሳሰብና የአተያይ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርግ ነው። ከድል በኋላ ግንባሩን የተቀላቃሉ ወጣቶችና ምሁራን “እኛስ ከማን እናንሳለን? ለምን እውነተኛ የሆነ የተሀድሶና ለውጥ እንቅስቃሴ አናደርግም?” ብለው እንዲያስቡና እንዲነሳሱ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይሄ ከሆነ ደግሞ ብዙ ነገር ተቃለለ ማለት ነው። ታንክና መድፍ እያንጋጋ ከመጣው አሮጌ አመራር ይልቅ በብዙ መልኩ እኛ የሚመስሉትን አዲሶቹ የኢህአዴግ ትውልዶች ጋር መነጋገርና መግባባት የሚቻል ነው የሚመስለኝ። ሲጀመር እነርሱ ስልጣን ቢያጡም እንዲህ እንሆናለን፣ እንታሰራለን፣ ይበቀሉናል የሚሉበት ሁኔታ የለም። ስልጣን ቢያጡ እንኳ ሰርተው ወይም ነግደው የሚኖሩበት ሁኔታ ነው የሚኖረው። እንዲያውም በስርዓቱ አማካይነት የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅምና የትምህርት እድል እንዲኖራቸው የተደረገ በመሆኑ እውነተኛና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የነፃ ገበያ ስርዓት ሲሰፍን በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ ለመሆን ከሌላው የተሻለና የተደራጀ አቅም ያላቸው ይሆናሉ።
ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ ገለልተኛ የሆኑ ተቅዋማትና የህግ የበላይነት የሰፈነበት የተደላደለ ስርዓት እስካለ ድረስ ሰዎች በነበራቸው ፖለቲካዊ አመለካከት የሚጠቁበት ሁኔታ ፈፅሞ አይኖርም። ለዚህ ነው፤ እኔ የተሻለ አስተሳሰብና ፖለቲካዊ ባሀል በማምጣት በገዥው ፓርቲ ጥላ ስር ያሉትን ዜጎች ሳይቀር አዎንታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር የዚህ የህዳሴው አብዮት አካል እንዲሆኑ ማድረግ እንችላለን የምለው። በመሆኑም ይሄ የለውጥ ፕሮጀክትና የተሀድሶ እንቅስቃሴ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይና የሚታለፍ መሆን የለበትም። በዚህች ሀገር ያለው ፖለቲካዊ ባህል እንዲለውጥ የምንፈልግ ሁሉ ሀሳቡ ማስፋት ማጠናከር ብሎም ወደ መሬት በማውረድ ለተግባራዊነቱ ቆርጠን መነሳት፣ በተገቢው ሁኔታም መንቀሳቀስ መቻል አለብን። በዚህ መንገድ ከታገልን ለሁላችንም የምትበቃ፤ የተሻለችና ሁሉም ዜጎቿ ያለልዩነት የሚኮሩባት ሀገር እንድትኖረን ማድረግ እንችላለን። ስለዚህ የህዳሴው አብዮት በዚህ ሁኔታና እይታ ነው መቃኘት ያለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ።

lørdag 16. august 2014

ከግብረሰዶማውያኑ ጀርባ (አርአያ ተስፋማሪያም)


ከጥቂት አመት በፊት በኢትዮጵያ በተለይ አዲስ አበባ የሚገኙ ግብረሰዶማውያን ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ በሸራተን ሆቴል የሃይማኖት አባቶች ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት በስፍራው ተገኝተዋል። ፕሮግራሙ ሊጀመር 15 ደቂቃ ሲቀረው በድንገት የደህንነት ሰዎች ይገቡና ጋዜጠኞች እንዲወጡ ያደርጋሉ። ቀጥሎ ለሃይማኖት መሪዎቹ « ይህን መግለጫ መስጠት አትችሉም» ተባሉ። « ማነው ከልካዩ?..» ሲሉ ጠየቁ፤ ጭራሽ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው። የተቃውሞ መግለጫው በዚህ መልኩ ተደናቀፈ። በመቀጠል ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ተጠየቀ። የሸራተኑን መግለጫ ያደናቀፈው ባለስልጣን ጣልቃ ገብቶ ሰልፉን አስከለከለ። ይህን ሁሉ ያደረጉት የወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚ/ር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም መሆናቸውን የቅርብ ምንጮች ያረጋግጣሉ። በቅርቡ አሜሪካ መጥተው የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ በአፍሪካ ከጤና ጋር በተያያዘ አንድ ተቋም በሃላፊነት እንዲመሩ ተፈልገዋል። ከያዙት ስልጣን ፓርቲያቸው እንዲለቃቸውና አሜሪካኖቹ ወደሚፈለጉት ቦታ ዶክተሩን ለመውሰድ እቅድ መኖሩን አንዲት ከፍተኛ ሃላፊን በመጥቀስ ምንጮች ገልፀዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ስለዚህ ጉዳይ ይነጋገሩ አይነጋገሩ የታወቀ ነገር የለም። ዶክተሩ የተመረጡት « በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚ/ር ሆነው ብዙ ነገር ሰርተዋል፤ ለምሳሌ ኤ.ች.አይ.ቪ/ ኤድስ፣ የወሊድ ቁጥጥር፣ የጤና ተቋማት ግንባታ..» ወዘተ በሚል ይጠቅሳሉ። ነገሩ ወዲህ ነው..የሚሉ ወገኖች ባለስልጣኑ የተፈለጉት « ለግብረሰዶማውያን መብት ዘብ በመቆም አሜሪካ በዚህ ዙሪያ ለምታራምደው አቋም ዶ/ር ቴዎድሮስ በተደጋጋሚ አጋርነታቸውን በማሳየታቸውና በተጨማሪ ስለግብረሰዶማውያን መብት ደግፈው ስለሚፅፉ ነው» ይላሉ። የሚያሳዝነው ዶ/ር ቴዎድሮስ « የማሰር ሱስ የለብንም..» ከማለት አልፈው የታሰሩትን ሙስሊሞች ከጓንታናሞ ጋር ለማያያዝ መሞከራቸውና ቀጥሎ ለማስተባበል መሯሯጣቸው ነው። እውነት ለመብት የቆሙ ቢሆን ኖሮ ከአምላክ ድንጋጌና ተፈጥሮ ላፈነገጡ ሳይሆን ካለሃጢያታቸው በእስር እየተሰቃዩ ለሚገኙ ወገኖች መሆን ነበረበት።

torsdag 14. august 2014

ነጻነትን ለመጎናጸፍ ባሩዷን ማሽተት የግድ ነው !!! ሪያድ ኢብራሂም

ነጻነትን ለመጎናጸፍ ባሩዷን ማሽተት የግድ ነው !!! ሪያድ ኢብራሂም
የወያኔ የግፍ ስርዓት በህዝብ ትከሻ ላይ ድሩን አድርቶ ፤ የማይጠረግ እስኪመስለን ድረስ ሁለት አስርት አመታቶችን በላያችን ላይ ዘልቋል ።በሰላማዊ መንገድ የግፉ ስርዓት ተቋጭቶ ፍትህና እኩልነት በሀገራችን ይሰፍን ዘንድ ብዙ ተሞክሯል ። ነገር ግን በወያኔ ስልጣን አልጠግብ ባይነት እና የሰላማዊው መንገድ ክርችም ብሎ በመዘጋቱ ባሩዷን ማሽተት ግድ የሆነበት ጊዜ ላይ ከደረስን ከራርመናል ።ትግሉ ከኛ ምን ያህል የአላማ ጽናትን ይፈልጋል ? ምን ያህልስ መስዋእትነትን ያስከፍለናል ? እንዴትስ ብንታገል ካሰብነው የነጻነት ደጃፍ ባጭሩ ያደርሰናል ብለን ብንጠያየቅ ትክክለኛ ጊዜው አሁን ይመስለኛል።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊም በተለይም በወጣትነት የእድሜ ክልል ያለው የህብረተሰብ ክፍል ስልጣንን ከህወሃት መዳፍ ውጭ አይቶት ስለማያውቅ ፤ ሀገሪቱን እነሱ ብቻ እንዲመሩ መለኮታዊ የሆነ ፈቃድ ያላቸው እስኪመስለው ድረስ ውስጡ አምኖ ተቀብሎት ነበር ለማለት ይቻላል ።ዳሩ ቢያምንም አይፈረድበትም ፤ ምክንያቱም እድሜ ሙሉውን በገዢነት የሚያውቀው ወያኔን ብቻ ነውና ።ነገር ግን ከጥቂት አመታት ወዲህ ስንመለከት በሀገር ውስጥም ሆነ በባእድ ሀገራት በሚያስደንቅ ሁኔታ የወጣቱን አዲስ የሆነ የትግል መንፈስ በተለያዩ መድረኮች እየታየ ነው።እንደ እኔ ግምት ፤ የትግል መንፈሱን እንዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ካጦዙት አንዱ ስርዐቱ እጅግ ከፋ የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱና ሌላው የገዥው አምባገነን ቡድን በአፈሙዝ ወደ ስልጣን የመጣ ቡድን በመሆኑ ለሰላማዊ መንገድ ባይተዋርና በር የማይከፍት በመሆኑ ነው ።
የወያኔ ስርዓት በርካታ የሆኑ ሰላማዊ ፣ ቡድኑን ከህዝብ የሚያስታርቁ እድሎችን በት እቢትና በተአብዮ በመወጠር ሳይጠቀምበት ቀርቷል።ሳይጠቀምበት ካመለጡት እድሎች መሃከል የግንቦት 1997 ምርጫ በዋናነት ይጠቀሳል ። በዚያ ወቅት ህዝቡ ሙሉ በሙሉ በህወሃት መሪዎች ያለገደብ የተያዘው ስልጣን ህዝብ እጅ ይገባል ብሎ በጉጉት እየጠበቀ ያለበት ጊዜ ነበር ።በጊዜው ገዥው ፓርቲ በምርጫው ሙሉ በሙሉ የተሸነፈ ቢሆንም ሽንፈቱን መቀበል ተስኖት አፈሙዙን ወደ ህዝብ ሰድሮ ንጹሃንን በግፍ መጨፍጨፉ መቼም ከህሊናችን የሚፋቅ አይደለም ።በዚያ ወቅት በሰላም ስልጣናቸውን ለህዝብ ቢያወርዱት ኖሮ ላሳዩት ቀናኢነትና ህዝቡን በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የስልጣን ባለቤት በማድረጋቸው ፤ ምናልባትም በ2002 ምርጫ ህዝቡ በድጋሚ እድሉን ሊሰጣቸው ይችል ነበር ብዬ እገምታለው ።
በወቅቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹና ህዝቡ እውን ወያኔ ስልጣኑን ወደ ህዝብ ያወርደው ይሆን ? የሚለው ጥያቄ በአብዛኞቻችን አይምሮ ውስጥ የምርጫውን ውጤት እስክናውቅ ድረስ ልብ ያንጠለጠለ ጉዳይ ነበር ።እንደው ግን ድምጻችን ብቻ ሳይሆን ልባቸውም አሸንፏቸው በጉልበት ከያዙት የሃላፊነት ቦታ በሰላም ገለል ቢሉ ኖሮ፤ ህዝቡም ያሁኑን ያህል የከፋ ቂም በቀል በወያኔ ላይ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም ።ምክንያቱም የህዝቡ ሙሉ ትኩረት የስልጣን ባለቤትነቱ መረጋገጡ ላይ ስለነበረ ፤ በስልጣን ላይ በቆዩበት ጊዜያት ላጠፉት ጥፋትም የመጠየቅ አዝማሚያ አይስተዋልም ነበርና።
አሁን ግን ወያኔ መሽቶበታል ። ይቅር ከመባባያው ክልል በጣም እርቆ ተጉዟል ።በአሁኑ ሰዓት በየትኛውም አቅጣጫ የአስከፊውን ስርዓት ገፈት ቀማሽ ያልሆነ ዜጋ ፈልጎ ማግኘት ከክምር ጭድ መሃል የወደቀን መርፌ እንደመፈለግ ይቆጠራል ።
ችግር ብልሃትን እንደሚፈጥር ሁሉ አብዝቶ መበደልም የነጻነት ትግልን እውን ያደርገዋል ።የወያኔ ቡድን እንዴት ሊወገድ እንደሚችል በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የፖለቲካ ምሁሮች ያስኬዳል ያሉትን ስልቶች ጠቁመዋል ።ከዚህም መካከል የትጥቅ ትግል አንዱ ነው ።በትጥቅ ትግል መንግስታቸውን ካወረዱ ሀገራት ልምድ በመነሳት ፤ የእርስ በእርስ ጦርነት ለአንድ ሀገር መጠነ ሰፊ ጉዳቶችን የሚያስከትልና የማይረሳ የታሪክ ጠባሳ አሳርፎ የሚሄድ ስለሆነ በሃገራችን ባይከሰት መልካም ቢሆንም ፤ ነገር ግን እንደ ወያኔ ያለ አስከፊና ጨቋኝ ስርዓት ለረጅም ጊዜያት ስልጣኑን የሙጥኝ ብሎ ህዝብን እየጨቆነ ፣ እያፈነ፣ እያሰረና እየገደለ መዝለቁም ፤ ይበል የሚያሰኝ ስላልሆነ የትጥቅ ትግሉን አስፈላጊነት እርግጥ ያደርገዋል ።
እርግጥ ነው ባሩድ ሳናሸት የሚገኝ ነጻነት ቢኖር ማንም አይጠላም ። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በገዥው መደብ በኩል በገሃድ የምናየው እብሪትና ትእቢት ፣ ህዝብን የመናቅና ያለማድመጥ ሁኔታ ትግሉን የግድ ያደርገዋል ። ምናልባት አንድ ቀን የባሩድ ሳይሆን የሽቶ መዐዛ ያሸትቱናል ብለን ለ23 ዓመታት በተስፋ ጠብቀን ነበር ። ግን አልሆነም ከዚህ በኋላም እንደማይሆን የአሁኑ አካሄዳቸው በራሱ እማኝ ነው ። ይህን አስከፊ እና በጥቂት አጉራ ዘለል የስርዓቱ ዋና አንቀሳቃሽ የሚከወነው እልህ ውስጥ የሚያስገባ ሀገራዊ በደል ማስቆም የእኛ ሃላፊነት ነው ።
የህወሃት መንግስት ስልጣን ከያዘበት ጀምሮ በጦር መሳሪያ ግዢ ስራ የተጠመደ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም ።ቢሆንም የሚያስፈራንና አላማችንን አንዲት ጋትም ብትሆን ወደኋላ የሚያፈገፍግ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ለነጻነት ትግል ለመነሳት ብዙ ሃይል ወይም ብዙ የጦር መሳሪያ አይደለም የሚያስፈልገው የቆረጠ ልብ እንጂ ይሄንን ደግሞ ካሁኖቹ ጨቋኝ ገዥዎቻችን መማር እንችላላን ። የወያኔ ቡድን ለትግል ሲነሳ 11 ሆነው መነሳታቸውን ሁላችንም የምናውቀው ነው ።ቀጥሎ የነሱን ቆርጦ መነሳት የተመለከተው ወገናቸው የመሪዎቹን ፈለግ ተከትሎ ለድል በቃና በተራው ጨቋኝ ሆኖ ቁጭ አለ ። ወገኖቼ ! ታድያ ታግሎ ያታገላቸው የቁጥራቸው መበራከት አሊያም የጦር መሳሪያ ብዛት አልነበረም ትግራይን ነጻ የማውጣት የአላማ ጽናት እንጂ ፤ እኛም ከዚህ ምሳሌ በመነሳት ኢትዮጵያን ካለችበት የጭቆና ቀንበር ለማውጣት ቁርጠኛ ልብ ያስፈልገናል ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ስርዓቱ ሞቷል ከኛ የሚጠበቀው ተገቢውን የቀብር ስነስርዓት ማስፈጸም ብቻ ነው !!!!
እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ !!

እነ ወይንሸት ሞላ በዋስ እንዲፈቱ በድጋሚ ታዘዘ

ያለአግባብ ታስረው የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲዋ ወይንሸት ሞላና ፎቶ አንሺ ጋዜጠኛዋ አዚዛ መሃመድ ከሁለት ሳምንታት በፊት በአንዋር መስጊድ ይካሄድ በነበረው የጁምአ በአል ላይ ተገኝተው ነበር። የፖሊስ እና ደህንነት ሃይሎች ሰላማዊውን ሰው ሲደበድቡ እና ሲያስሩ፤ እነ ወይንሸት ሞላም በስፍራው በመገኘታቸው ብቻ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባቸው ታስረዋል። በተለይም ወይንሸት ሞላ እጇ እስኪሰበር ድረስ ነበር የተደበደበችው። ባለፈው ሳምንት የዋለው የልደታ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለቱም እንዲፈቱ ቢያዝም፤ ፖሊስ ወዲያው ጉዳዩን ሰበር ችሎት ወስዶ ዋሳቸውን አሳግዶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
ወይንሸት ሞላ
ወይንሸት ሞላ (የሰማያዊ ፓርቲ ሴት ወጣቶች ሃላፊ)

አዚዛ መሃመድ - የአዲስ ጉዳይ መጽሄት ፎቶ አንሺ።
አዚዛ መሃመድ – የአዲስ ጉዳይ መጽሄት ፎቶ አንሺ።
በዛሬው ቀን የዋለው ችሎት ወይንሸት ሞላ፣ አዚዛ እና ኢብራሂም አብዱልሰላም በ5ሺህ ብር የመታወቂያ ዋስ እንዲፈቱ ውሳኔ ሰጥቷል። እንደከዚህ ቀደሙ መልሰው ካላሰሯቸው በቀር ሶስቱም በቅርቡ ከ እስር ይወጣሉ ተብሎ ይታወቃል።

onsdag 13. august 2014

በምእራብ ኢትዮጵያ ለኩምሩክ ድንበር አቅራቢያ ጦርነት ተካሄደ።

Augest 13/2013

ከወያኔያዊ ምርጫ በፊት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሊያሰጋ ይችላል ሲሉ ዲፕሎማቶች ተናግረዋል።

ምንሊክ ሳልሳዊ
ወያኔ ራሱን ለማንገስ ከሚጠራው ምርጫ በፊት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበር አከባቢዎች ጦርነት ሊካሄድ ይችላል ሲሉ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ዲፕሎማቶች ተናግረዋል።በተለያዩ አጋጣሚዎች የተነሱ የሳተላይት ፍቶዎች በማስረጃነት በመጥቀስ ይህን ሰሞን በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከአፍሪካ ህብረት ሰዎች እና ከአከባቢው የፖለቲካ አዋቂዎች ጋር የተለያዩ ስብሰባዎችን የሚያካሂዱት ዋናው የዚሁ ጦርነት ስጋትና አከባቢው ላይ ብሄራዊ ጥቅማቸው ላይ ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን በመገምገም ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ዲፕሎማቶቹ የአሜሪካ መንግስት የሲአይኤን ሪፖርት ተከትሎ በትራንስፖርት ቢሮአቸው አማካኝነት በሰሜን ኢትዮጵያ የአየር በረራ የሚከለክል ደንብ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፤ የዚህ ጉዳይ ዋነኛ ምክንያት ደሞ አከባቢው ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መሆኑና በጦርነት ቀጠና የተመዘግበ ድንገት ጦርነት ይነሳል የሚል ግምት የተወሰደበት መሆኑ በአከባቢው ከፍተኛ የሆነ ከባድ መሳሪያዎች ታንኮች እና ብረት ለበስ አውዳሚ የጦር መሳሪያዎች የተከማቹ በመሆኑ ጦርነት አይቀሬ ስለሆነ በቋፍ ላይ ባለ የጦርነት ቀጠና ላይ አየር ማብረሩ ስጋት እንደሆነ ይናገራሉ፡፤ስለዚህ እንደ ዲፕሎማቶቹ እምነት ከወያኔያዊው ምርጫ በፊት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ያስጋል።

በምእራብ ኢትዮጵያ በቤንሻንጉል ጉምዝ ወደ ድንበር ከተማው ኩምሩክ አክባቢ በግምት 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የወያኔው መከላከያ ሰራዊት ካምፕ አቅራቢያ በሰራዊቱ እና ከደቡብ ሱዳን ሰርገው ገብተዋል በሚባሉ ሃይሎች መካከል የ3 ሰአታት ጦርነት መካሄዱን አንድ የምእራብ እዝ መኮንን በላኩልኝ መረጃ ገልጸዋል።

ወታደሮቹ በክምፑ አከባቢ ቅኝት በሚያደርጉበት ጊዜ ድንገት የመጡ ሰርጎቦች የተባሉ ሃይሎች አከባቢውን በመውረር ከባድ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን 26 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሲግደሉ በርካቶች ቆስለዋል። በዚህ የሰአታት ጦርነት እንደ መኮንኑ አባባል ከተዋጊዎቹ ወገን ጥልው የሸሹት ሁለት ሬሳ ብቻ ነው ብለዋል።

tirsdag 12. august 2014

ፕሬስ የሌለው መንግስት ከሚኖረን መንግስት የሌለው ፕሬስ ቢኖረን እንመርጣለን

ዳዊት ሰሎሞን

እርግጥ ነው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች ለስደት ሲዳረጉ ‹‹አዲስ ዘመንንም አዲስ ነገርንም አላነብም››በማለት ነግረውን ነበር፡፡ሌጋሲያቸውን ለማስቀጠል ቤተ መንስግስት የገቡት ሃይለማርያም በበኩላቸው በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ የፎርቹንን ኮሪደር እንደሚያነቡ ሲናገሩ አድምጫለሁ፡፡

የቅንጅት አመራሮች በድርድሩ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እንደገቡ ብዛት ያለው የኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ተጠርዞ መመልከታቸውን መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡ገዢዎቻችን ከቀድሞዎቹ ነገስታት ባነሰ መልኩ ‹‹አዝማሪ ምን አለ?››በማለት ለመጠየቅ አለመፍቀዳቸው ትርጉሙ ንቀት ብቻ ነው፡፡ህዝቡን የሚፈልጉት እነርሱ ሲናገሩ እንዲያደምጥ ብቻ እንጂ ሲናገር ሊሰሙት አይደለም፡፡ስለዚህ ጋዜጦችን አያነቡም፡፡የማያነቧቸውን ጋዜጦች አዘጋጆች ለስደት ሲዳረጉ ደግሞ ቅንጣት ታህል አትሰማቸውም፡፡

በጥቂት ወራት ውስጥ የተደረጉ ፕሬስን ከአገሪቱ ገጽ ለማጥፋት የተወሰዱና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ተመልከቱ፡፡ጋዜጠኞች ተሰባስበው ለመመስረት ቀና ደፋ ያሉለት አዲስ ማህበር እውቅና ተነፈገው፣የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ሶስት ጋዜጠኞች ለእስር ተዳረጉ፣ትግራይን ህዝብ ፍዳ በሶሻል ሚዲያ ሲያጋልጥ የቆየው አብርሃ ደስታ ጨለማ ቤት ተወረወረ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስጠናሁ ያለውን ወረቀት አቅርቦ ጋዜጦችን በኒዮ ሊበራሊስትነት ከሰሰ፣ከጫካ ጀምራ የህወሃት አፍ የነበረችው ፋና የጋዜጣ አከፋፋዮች ላይ ዘመቻ ከፈተች፣ዘመቻውን ተከትሎ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ አከፋፋዮችና ጋዜጣ አዟሪዎች ስቅይት ደረሰባቸው፣ፍትህ ሚኒስትር የህትመት ውጤቶች አሳታሚዎች ላይ ከፍተኛ የወንጀል ክስ መመስረቱን ነገረን፣ክሱ መነገሩን ተከትሎ ማተሚያ ቤቶች ጋዜጦችን የማስተናገድ ፍርሃት ወረራቸው አንዳንዶቹም በግልጽ ይህን ጋዜጣ እንዳናትም ቀጭን ትዕዛዝ ደርሶናል አሉ፣ካፌዎች በግድግዳቸው ላይ ‹‹ጋዜጣ ባለማንበብዎ እናመስግናለን እና ጋዜጣ ማንበብ አይቻልም››የሚሉ ማስታወቂያዎችን መለጠፍን ስራቸው አደረጉት ፡፡

ስደት ብርቃችን አይደለምና ይህው የተወዳጇን አዲስ ጉዳይ መጽሔት ባለቤትና አዘጋጆች ስደት ሰማን ፡፡ይህ ለኢህአዴግ ምኑ ነው?ፕሬስ የሌለው መንግስት እንዲኖረን የሚፈልግ በመሆኑ ደስታውን የሚችለውም አይመስለኝም፡፡ኮካዎች ምን ትላላችሁ?

mandag 11. august 2014

የከዱ የግንቦት 7 አባላት አቶ አንዳርጋቸውን እያሰቃዩ ነው ተባለ፤ 2 መምህራንና 1 ዳኛ በአንዳርጋቸው ጉዳይ ታፍነዋል

የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን መያዝ ተከትሎ ለወያኔዎች ከአዲስ አበባ እስከ ደብረዘይት ትልቁን የምርመራ ስራ እየሸፈኑ ያሉት ከግንቦት ሰባት ሕዝባዊ ሃይል ጋር በኤርትራ የነበሩ እና ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር የፖለቲካ ስራ ሲሰሩ የነበሩ በኋላም ከድተው የገቡ ቅጥረኞች መሆናቸው ታውቋል። እነዚህ ቅጥረኞች ከመጀመሪያው ሰርጎ ገቦች እንደሆኑ ሳይጠረጠር ወደ ግንቦት ሰባት ከገቡ በኋላ ከአቶ አንዳርጋቸው መያዝ ቀደም ብሎ በመክዳት ወደ ወያኔ የተቀላቀሉ ናቸው ሲል ጦማሪ ምኒልክ ሳልሳዊ ዘገበ።

እንደ ምኒልክ ዘገባ ከሆነ በአዲስ አበባ እና በደብረዘይት ትልልቅ ሆቴሎች ተይዞላቸው በምርጥ መኪኖች እየተንሸራሸሩ አቶ አንዳርጋቸውን በማሰቃያ ክፍል ውስጥ በማምጣት እውነቱን አውጣ አንተ እንደዚህ ብለኸን አልነበረም በማለት በተለያየ ጊዜ በስብሰባ እና በውይይት ወቅት የተነጋገሩትን የፖለቲካ ኦፕሬሽኖችን እና የትግል ስትራቴጂዎችን በመጥቀስ ከፍተኛ ስቃይ እና ድብደባ እያደረሱብት ነው።


ከሕወሃት ከአንድ ብሄር ከተመለመሉ መርማሪዎች ጋር በጋራ በምርመራ ላይ የተሰማሩት ሶስቱ የግንቦት ሰባት ከሃዲ አባላት አንዳርጋቸውን በማሰቃየት ላይ ያሉት -

1) ሽታው ሽፈራው ኤርትራ የነበረ የጎጃም ሰው
2) ቴዎድሮስ ስዩም ኤርትራ የነበረ ከአዲስ አበባ የሄደ
3) ኢልያስ ጥረት ጎንደር ውስጥ የነበረ እና ከአንዳርጋቸው ጋር ሲሰራ የነበረ ናቸው ሲል በዝርዝር የጠቆመው ጦማሪ ምኒልክ ሳልሳዊ በወያኔ ተንኮል ተተብትበው ግንቦት ሰባትን በመክዳት ለምቾታቸው የሕዝብን ትግል በጥቅም በመለወጥ በዘመናዊ መኪና እየተንፈላሰሱ በአዲስ አበባ እና ደብረዘይት ምርጥ ሆቴሎች ውስጥ እየተዝናኑ የነጻነት ታጋይ የሆነውን አንዳርጋቸውን በቶርች በማሰቃየት ላይ መሆናቸውን ዘግቧል።


ምርመርውን በመሪነት የሚያንቀሳቅሱት የሕወሓት ደህንነቶች የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ በአከባቤው አንዳርጋቸውን በተመለከተ ለብአዴን ይሁን ለ ኦሕዴድ ሰዎች ምንም አይነት መረጃ እንዳይሰጣቸውና ወደ ማሰቃያ ክፍሉ ምንም እንዳይቀርቡ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገ እንደሆነ ለማረጋገጥ መቻሉን የገለጸው ጦማሪው ከአንዳርጋቸው ጋር የተያያዘውን የሃገር ውስጥ ኔትወርክ በማፈራረስ ረገድ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው ከሃዲዎች እስከ ክፍለሃገር ድረስ በስፋት እየሰሩ ሲሆን እስካሁን በማፈራረስ ሙከራው ምንም አይነት ውጤት እንዳልገኙ ታውቋል ብሏል።


ጦማሪው ዘገባውን ሲቋጭም “ከአንዳርጋቸው ጋር በተያያዘ ከየክልሉ የግንቦት ሰባት መዋቅር ውስጥ አሉ የተባሉ እየተለቀሙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከጎንደር ክፍለሃገር መምህር ተስፋዬ ተፈሪ እና መምህር ጌታቸው የተባሉ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን እንዲሁም የጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደሆነ የሚነግረው አቶ አበራ በከሃዲዎች ጥቆማ ከሃምሌ አጋማሽ ጀምሮ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ የት እንደታሰሩ እንኳን እንደማይታወቅ ተገልጿል።” ብሏል።

torsdag 7. august 2014

በአምስት ነጻ ጋዜጦች ላይ ጥቁር ሽብር እየተፋፋባቸው ነው!!

Augest 7/2014
(ኢ.ኤም.ኤፍ) ከትላንት በስትያ የፍትህ ሚንስትር መስሪያ ቤት በህዝብ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ሬድዮ አምስት ጋዜጦችና መጽሄቶች ህገ መንግስቱን ለመናድ መሞከራቸውን በመግለጽ መግለጫ አውጥቶ ነበር። የመግለጫው ጭብጥ እንደሚያስረዳው ከሆነ፤ አምስት የፕሬስ ውጤቶች መንግስትን ሰላም የነሱ መሆናቸውና ወደፊትም በእንደዚህ መሰል የፕሬስ ውጤቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ነው ዛቻ በተቀላቀለበት ሁኔታ የተገለጸው። በአሁኑ ወቅት የሰብ አዊ መብት ገፈፋዎችን ጨምሮ ከህግ ውጭ የሚደረጉ የመንግስት አሸባሪ እርምጃዎችን፣ “ጥቁር ሽብር” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ይህ በፕሬስ ውጤቶች ላይ የተካሄደው እርምጃም የ”ጥቁር ሽብር” ሌላኛው ማሳያ በመሆኑ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው።
ጥቁር ሽብር እየተፋፋመባቸው ያሉት የፕሬስ ውጤቶች
ጥቁር ሽብር እየተፋፋመባቸው ያሉት የፕሬስ ውጤቶች
በስም የተጠቀሱት አምስት የፕሬስ ውጤቶች ክስ ሳይመሰረትባቸው፤ ለፖሊስ ቃላቸውን ሳይሰጡ፤ የፍርድ ቤት መጥሪያ ሳያገኙ ነው፤ የፍትህ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ “አሸባሪ” የሚል ስያሜ ሊሰጣቸው የሞከረው። የፍትህ ሚንስቴር መስሪያ ቤት በዚሁ መግለጫው ላይ “ፋክት፣ ጃኖ፣ ሎሚ፣ አዲስ ጉዳይ፣ እና እንቁ የሚባሉ መጽሄቶችን እንዲሁም አፍሮታይምስ የሚባለውን ጋዜጣ በሚያሳትሙ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መስርቻለሁ” ብሏል። ይህ ክስ ፕሬሶቹ በቀጣይ የህትመት ስራዎቻቸውን ለማገድ የታቀደ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ ህትመት ያቆሙ መጽሄቶች እና ጋዜጦች ስለመኖራቸው የታወቀ ነገር የለም።
ትላንት ረቡዕ ለህትመት ወጥቶ የነበረው ሰንደቅ ጋዜጣ ይህን ጥቁር ሽብር አስመልክቶ የፍትህ ሚንስቴርን መግለጫ በማስቀደም የፖለቲካ ፓርቲ ሃላፊዎችንእና ጋዜጠኞችን አነጋግሯል። ስለሁኔታው ተጨባጭ መረጃ ይኖራቹህ ዘንድ የሰንደቅ ጋዜጣን ዝግጅት በፒ.ዲ.ኤፍ አቀናብረን ከዚህ በታች አቅርበነዋል። ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ።

mandag 4. august 2014

አንድ መቶ ሰባ አምስት ኪሎ ወርቅ ከሃገር ሊወጣ ሲል ቢያዝም በሳሞራ የኑስ ትእዛዝ እንዲያልፍ ተደርጓል።

Augest 4/2014
ምንሊክ ሳልሳዊ

  • 661
    Share

የጄኔራል ሳሞራ የኑስ እንደሆነ የሚጠረጠረው አንድ መቶ ሰባ አምስት ኪሎ ወርቅ ከአገር ሊወጣ ሲል ተይዞ የነበረ ቢሆንም በጄኔራሉ ትእዛዝ ከአገር እንዲወጣ መደረጉን የአየር መንገዱ የደህንነት ምንጮች ጠቁመዋል። ይህ በሁለት ካርቶን ታሽጎ በበረራ ቁጥር 600 እና 612 ወደ ዱባይ ሊሻገር ሲል በቁጥጥር ስር የዋለው ወርቅ በጊዜው ባለንብረቱ ተፈልገው ባለመገኘታቸው እንዲቆይ ቢደረግም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ቦታው ድረስ አሽከሮቹን በመላክ እንዲለቀቅ እና እንዲያልፍ/እንዲጫን የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

ይህ የሃገር ሃብት የሆነን ወርቅ የወያኔ ባለስልጣናት ካለምንም ገደብ በማሸሽ እና በመዝረፍ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ፒያሳ አከባቢ በሚገኘው በአፍሪካ ወርቅ ቤት ሽፋን እንዳልካቸው እና ዳንኤል በሚባሉ ስሞች በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የወርቅ መጠን ከአገር በማስወጣት እና እንዲሁም የውጪ ወርቆችን ካለምንም የቀረጥ ክፍያ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት ስራ ላይ መሰማራታቸው በተጨማሪም ሃገሪቷ የምታገኛቸው የውጪ ምንዛሬዎች በጥሬው እየታሸጉ ከሃገር እንደሚወጡ ታውቋል።

የጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ የክስ መቃወሚያ ቀጠሮ ተላለፈ

Augest 4/2014

የዞን ዘጠኝ ስድስት ጦማርያንና ሶሰት ጋዜጠኞች በወንጀለኛ መቅጫ ህግና በፀረ ሽብር አዋጁ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም አቅደዋል፣ ተዘጋጅተዋል፣ አሲረዋል፣ አነሳስተዋል እንዲሁም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሁከትና በአመፅ ለመለወጥ አስበዋል ተብለው በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በህገ መንግሥትና በህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ በሚደረግ የሙከራ ወንጀል ተከሰው ባለፈው ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ከሦስት ወራት የምርመራ ጊዜ በኃላ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች በፅሑፍ የቀረበላቸውን ክስ ካደመጡ በኃላ በአቃቢ ህግና በጠበቆቻቸው መካከል በተደረገ የዋስትና ጥያቄ ክርክር ብይን ለመስጠትና የክስ መቃወሚያ ለማዳመጥ ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በዛሬው ቀጠሮ ዘጠኙም ተከሳሾች ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም በዋስትና መብት ጉዳይ በጠበቃና በአቃቢ ሕግ መካከል የተደረገው ክርክር የህግ ትርጓሜ እንደሚያስፈልገው ጠበቃዎች በጠየቁት መሰረት ከመቅረጸ ድምጹ ላይ ተገልብጦ ለህግ አስተርጓሚ እንዲላክ እንዲሁም በሌለችበት ክስ የተመሰረተባት 1ኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላት የተሰጠው ትዕዛዝ ባለመፈፀሙ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ባለፈው ቀጠሮ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ከፍርድ ቤቱ ብይን ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በዛሬው ቀጠሮ የሰጣቸው ትዕዛዞች ተፈጻሚ ባለመሆናቸው ለብይን ያስቸግረናል በሚል የክስ መቃወሚያቸውን ሳያደምጥ ቀርቷል፡፡
ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት አስተያየት በመጀመሪያው የፍርድ ቤት ውሎ ለዛሬ ቀጠሮ የክስ መቃወሚያ እንዲቀርብ ብይን የተሰጠ መሆኑን አስታውሰው ፍርድ ቤቱም ሆነ አቃቢ ህጉ የክስ መቃመወሚውን ለማየት በቂ ጊዜ የሚሰጥ በመሆኑ የክስ መቃወሚያ በጽሁፍ እንድናቀርብ ይፈቀድልን ብለው ጠይቀዋል፡፡ ችሎቱም የጠበቆችን ጥያቄ በመቀበሉ የክስ መቃወሚያው ለአቃቢ ህግና ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ ቀርቦ በቀጣዩ ቀጠሮ በንባብ እንዲሰማ አዟል።

በ1ኛ ክስ ላይ ለተዘረዘሩ የወንጀል ድርጊቶች 5 መቃወሚያ እንዲሁም በ2ኛ ክስ ለቀረቡት የወንጀል ድርጊቶች 4 መቃወሚያ ነጥቦች የተዘረዘረበት ሰነድ “የቀረበው ክስ ከተጠቀሰው የህግ አነጋገር ጋር የሚቀራረብ አለመሆኑን፣ ተከሳሾች ፈጽመዋቸዋል የተባሉት በክስ ዝርዝሩ የተመለከቱ ተግባራት በህግ የተፈቀዱና ሕገ መንግስታዊ ጥበቃም የተደረገባቸው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መሆናቸውን፣ የቀረበው ክስ ግልፅ አለመሆኑን፣ ወስደዋል የተባሉት ሥልጠናዎችና ለመገናኛ ብዙኃን ያስተላለፉት መረጃ ወንጀል አለመሆኑን የተመለከቱ መቃወሚያዎችን የያዘ ነው፡፡

በ2ኛ ክስ የቀረበው የክስ መቃወሚያ ደግሞ ጠበቃው ማሰብ የማያስከስስና የማያስቀጣ መሆኑን፣ መደራጀት፣ የሥራ ክፍፍል መፍጠር እና የተለያዩ ሥልጠናዎችን መውሰድ ወንጀል አለመሆኑን፣ በአንድ ድርጊት ሁለት ክስ መቅረቡ አግባብ አለመሆኑ፣ የቀረበው የማስረጃ ሰነድ አለመሟላትን በተመለከተ ከወንጀለኛ መቅጫ እና ከጸረሽብር አዋጁ አንቀጽ ጠቅሰው ተቃውሞዎቻቸውን በጽሑፍ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የዕለቱን ችሎት የሚመሩት ዳኛ ባስተላለፉት ውሳኔ የዋስትና መብት ጥያቄ ክርክር ከመቅረጸ ድምጽ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር ተያይዞ ለህግ አውጪ አካል እንዲልክ እንዲሁም ለ1ኛ ተከሳሽ በፕሬስ ጥሪ እንዲደረግና የክስ መቃወሚያ በንባብ እንዲደመጥ ትዕዛዝ አስተላልፈው ለነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

søndag 3. august 2014

ሠራዊቱ የህዝብ ወገንተኛነቱን የሚያስመሰክርበት ግዜ እየመጣ ነው

Augest3/2014
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የቀደመው ትውልድ ከቱርክ ኤምፓየር፤ ከግብፅ እና ከደረቡሽ፤ ከጣሊያን ወራሪ፤ ከሶማሊያ ተስፋፊ ኃይል እና ከሌሎችም የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተዋግቶ አገሪቷን ለአሁኑ ትውልድ ለማቆየት ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል። በተለይ ነፍጥ አንግቦ የተሠለፈው ኃይል የከፈለው የህይወት መሥዋዕትነት የሚረሳ አይደለም። አገራችን ኢትዮጵያ ለዛሬው ትውልድ የቆየችው ከራሱ ይልቅ ለአገርና ለወገን የሚያስብ ትውልድ በመኖሩ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይሆንም።
የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአገር ደህንነት ኃይል የቆመው አገርን ከጥቃት ለመከላከል ነው። አገር በጠላት እጅ ወድቃ በወገን ላይ ስቃይ እንዳይደርስ፤ ህዝቡም አገር አልባ እንዳይሆን መጠበቅ የአገሪቷ የሠራዊትና የደህንነት ኃይል ዋና ተግባር ነበር። ህወሃት መራሹ መንግስት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥም የቆመው ሠራዊት እና የደህንነት ኃይል ተግባሩ ሌላ ሁኗል።
በዚህ ዘመን ሠራዊቱና የደህንነት ኃይሉ የአገርን ብሄራዊ ደህንነት የሚጠብቅ ሳይሆን ህወሃት የተባለውን ዘረኛና ዘራፊውን ቡድን የሚጠብቅ ኃይል መሆንን እንዲመርጥ ሁኖ አገርን ከጠላት የመከላከል ተግባሩን ረስቷል። ይህን ኃይል የሚመሩትም ደማቸውንና አጥንታቸውን ቆጥረው ከአንድ መንደር/ጎሣ የተሰባሰቡ እና ካርታ ይዘው የቆሙበትን ሥፍራ እንኳን ለመለየት የማይችሉ መሃይማን መሆናቸው አገሪቷ ያለችበትን አደጋ ከሚያመላክቱ ምልክቶች መካከል አንዱ ነው። ህወሃቶች የደርግ ሠራዊት እያሉ ሊሳለቁበት የሚሞክሩት የቀድሞው የአገሪቷ መከላከያ ኃይል ሲመራ የነበረው አውሮፓና አሜሪካን ድረስ ተጉዘው በተማሩ፤ ማዕረጋቸውም የዓለም ዓቀፉን ደረጃ የጠበቀ፤ አገሪቷን ወክለው አደባባይ ቢወጡ የሚያኮሩ እንደነበረ የታወቀ ነው። የሹመታቸው መሠረትም ደምና አጥንት ሳይሆን እውቀታቸው፤ ችሎታቸውና ወታዳራዊ ብቃታቸው ነበረ።በህወሃት የሚመራውን ሠራዊትና የደህንነት ኃይል የሚመሩት ቡድኖች ከቀድሞዎቹ ሥርዓት የጦር መሪዎች ጋር ሲወዳደሩ የጫማቸውን ጠፍር እንኳ ለመፍታት የሚታጩ አይሆኑም።ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንደሚባለው ሆነና ጨካኞችና ነፍሰ ገዳዮች በወንበሩ ቁጭ ብለው የአገሪቷን ውድቀት እያፋጠኑት ይገኛሉ።
ዛሬ ህወሃቶች በወንበሩ ቁጭ ብለዋል። እነዚህ ከጭካኔ በቀር እንጥፍጣፊ የአገር ፍቅር የሌላቸው ቡድኖች አቋቋምን ያሉት ሠራዊትና የደህንነት ኃይልም አገሩንና ወገኑን ከመጠበቅ ይልቅ የገዛ ወገኑን የሚያሸበር ቡድን እንዲሆን ተደርጓል። ሠራዊቱ እና የደህንነት ኃይሉ ለአገርና ለትውልድ እንዲያስብ ሳይሆን የጥቂት ዘረኞችን ዕድሜ ለማራዘም ዘብ የቆመ ኃይል እንዲሆንም ሁኗል። ህወሃት እየፈጠረ ያለው ሠራዊትና የደህንነት ኃይል በጀግና ማዕረግ አገሩንና ህዝቡን ከጥቃት ተከላክሎ በህዝቡ ተከብሮና ተወዶ እንዲኖር ሳይሆን በጭካኔው ታውቆ እና የወገኑን ፍቅር አጥቶ በስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ የሚኖርን ኃይል ነው። እንዲህም ሁኖ በመቀረፁ ግደል ሲባል ገስግሶ ሂዶ የገዛ ወገኑን ይገድላል። አፍርስ ሲባል ፈጥኖ በብዙ ድካምና ወጪ የተገነባውን የወገኑን መኖሪያ ቤት ያፈርሳል። እሠር ሲባል ህፃን ከአዛውንት ሳይለይ ያገኘውን ሁሉ ወደ ወይኒ ቤት ያግዛል። በእንዲህ ሁኔታ ከወገኑ ተለይቶ፤ በወገኑ ላይ ዘምቶ፤ ወገኑን ወግቶ፤ ወገኑን አሥሮና አሰቃይቶ ራሡም እንደገና በክፉ ድርጊቱ ታሥሮ እንዲኖር ሁኗል።
ህወሃት የፈጠራችሁ እና በአገር መከላከያ እና ደህንነት ኃይል ሥም ቁማችሁ በወገኖቻችሁ ላይ እንድትዘመቱ የተደረጋችሁ የሠራዊቱና የደህንነት ኃይሎች አድምጡ። አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ዋነኛው ጠላት ህወሃት ነው። ህወሃት የዘረኞችና የዘራፊዎች ስብሰብ ነው። የዘረኝነታቸው መገለጫ ብዙ ነው። የሚያዙህ ጄኔራል ተብየዎች ደማቸውን ቆጥረው የተጫኑብህ መሆናቸውን ተመለከት። እነዚህ ጄኔራሎች አገሪቷን ከተቆጣጠሩ ዘመን ጀምሮ ያካበቱትን የሃብት ብዛት ተመልከት። ሁሉም በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ባለቤት ናቸው። ልጆቻቸው በአውሮፓና በአሜሪካን ይማራሉ። ሚስቶቻቸው አውሮፓና አሜሪካን እየሄዱ እንዲወልዱ ይደረጋል።ይሄን ለምን ያደርጋሉ ቢባል እየገዙ ያሉት አገር የራሳቸው አገር ስለመሆኗ ብርቱ ጥርጣሬ ስላላቸው ነው። ህዝቧንም እንደ ወገኖቻቸው ለማየት ሥር የሰደደ ጥላቻማላቸው። አንተ እና ወገኖችህ ግን ከሙታን ትንሽ ከፍ ብላችሁ፤ ከሚኖሩት እገር ሥር ተረግጣችሁ የህወሃቶች አኗኗሪ ሁናችሁ የመከራውን ዘመን ትቆጥራላችሁ። በድህነት የሚወቅሯችሁ እንሷቸው ይሄና አስባችሁ፤ ያንን ተናገረችሁ እያሉ በዓለም ላይ በተከለከለ የቶርቸር ዓይነት እንድትሰቃዩ ትደረጋላችሁ። ይህ የጠላት ተግባር ነው።አሁን ባለንበት ዘመንም የኢትጵያ ዋነኛው ጠላት ህወሃት መሆኑን ያለምንም ጥርጣሬ ማመን ይኖርባችኋል።
ህወሃትን ጠላት የሚያድረገው ምንድ ነው ?
ህወሃቶች ወደ ስልጣን ከመጡ ዘመን ጀምሮ ሁለት ሚሊዮን አማራ ጠፍቷል። ይሄ ሁሉ አማራ የት እንደገባ ህወሃት እስከ አሁን አልተናገረም። ይሄ ዘረኛ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ በዜጎች መካከል ሊኖር የሚገባው መተማመን ጠፍቷል። በዚህም ምክንያት ዜጎች ከኖሩበት ሥፍራ እየተነቀሉ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ሁኗል። ይሄ ዘራፊ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ግዜ ጀምሮ ከአገሪቷ ውስጥ በስምንት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተዘርፎ በውጪ አገራት ባንኮች ውስጥ ተደብቋል። ይህ ቡድን ስልጣኑን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ከአገሪቷ በሚሰደዱ ምሁራን፤ ጋዜጠኞች፤ የኃይማኖት አባቶች እና በሌሎች ዜጎች ቁጥር ኢትዮጵያን የሚያክል አልተገኘም። ህወሃት የተባለው ዘረኛ እና ዘራፊ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ በኋላ አባቶች በደምና አጥንታቸው ያቆዩት ድንበር እየፈረሰ እና ኢትዮጵያዊያን እየተፈናቀሉ ሜዳ ላይ ተጥለው መሬቱ ለባእዳን እየተሰጠ ነው። ይሄ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ድሃ ሜዳ ላይ ተጥሎ የድሃውን መሬት ህወሃቶች እየነጠቁ ባለሃብት ነን ብለዋል። ይሄ ቡድን አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ሃሳብን በነፃ መግለፅ አሸባሪነት ሁኗል። ህወሃትን መንቀፍ በሞት የሚያሰቀጣ ወንጀል እስከመሆን ደርሷል። ኢትዮጵያ ይህን በሚመስለው ጠላት እጅ ተይዛለች።
ኢትዮጵያን ከዚህ ጠላት እጅ ለማላቀቅ የሠራዊቱና የአገር ደህንነት ኃይሉ ከፍተኛ ሚና መጫወት አለበት። ከህወሃት የበለጠ ጠላት ኢትዮጵያ የላትም፤ በታሪኳም እንዲህ ዓይነት ጠላት አይታ አታውቅም። ይህን ጠላት ወደ ከርሰ መቃብሩ የሚከት የለውጥ ባቡር እየገሰገሰ ነው። ይሄን የለወጥ ባቡር ፈፅሞ ማቆም አይቻልም። ህወሃቶች የለውጡ ባቡር በፍጥነት እየገሰገሰ እንደሆነ እያዩት ነው። በዚህም አንዳንዶቹ የዘረፉትን ሃብት ይዘው እየሸሹ ነው። ሌሎቹም የሚያደርጉትን አጥተው በዜጎች ላይ በስቃይ ላይ ስቃይ እያበዙ ነው። የሠራዊቱና የደህንነቱ ኃይል የኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆንን ከመረጡ ዘረኞች ጎራ ራሱን ለይቶ የህዝብ ልጅ፤ የአገር ጥላ ከለላ መሆኑን አሁኑኑ ማሳየት መጀመር ይጠበቅበታል። የአገር መከላከያ አባል ስትሆን አገርህን ከጠላት ለመከላከል እንጂ ከጠላት ጋር አብረህ የገዛ ወገንህን ስቃይ ለማብዛት አይደለም። ከጠላት ጋር መወገንን ከመረጥክ ግን የተነሳው የለውጥ ባቡር አንተንም ጨፍልቆ እና ታሪክህን ከዘረኞችና ከዘራፊዎች ጎራ ፅፎ እንደሚያልፍ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይኑርህ።
የእኛ እምነት ግን ከህወሃቶች ጎን ቁመህ ወንድሞችህን ትወጋለህ የሚል አይደለም። ህወሃቶች ለአንት ወንድምም ጋሻም መከታም የሚሆኑ አይደሉም። በአሁን ሠዓት የህወሃቶች ጭንቀት የዘረፉትን ሃብት የሚያሸሹበትን ሥፍራ የማግኘት ነው እንጂ የአንተ ደህንነት አይደለም። ህወሃቶችን እንቅልፍ የሚነሳቸው የሠሯቸው ትላልቅ ህንፃዎች ፍፃሜ እንጂ የኢትዮጵያዊያኑ በሠላም የመኖር ጉዳይ አይደለም። ህወሃቶች የሚሞቱለትም ሆነ የሚኖሩለት አንድ እና አንድ ምክንያት ዘርፈው ያካባቱት ሃብት እንጂ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳልሆነች የታወቀ ነው። አንተ የሠራዊቱ አባል ግን የእነዚህን ዘረኞችና ዘራፊ ህወሃቶችን እድሜ ለማራዘም የምትሞተውና የምትገድለው ለምንድ ነው? የእነርሱን እድሜ ለማራዘም ብለህ ብትሞት ለህወሃቶች ወግኖ ኢትዮጵያዊያንን ሲወጋ ሞተ ተብለህ መሳለቂያ ሆነህ መቅረትህን አታውቅምን ?
እኛ ግን እንዲህ እንልሃለን ለአገርህ መሞት ክብር ነው። ለአገር መሞት ማለትም በዚያች አገር ውስጥ ለፍትህ፤ ለህግ የበላይነት፤ ለነፃነት፤ ለእኩልነት እና ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራስን አሳልፎ መስጠት ማለት ነው።በዚህ ሞትህ ማንም ማንንም ሳይጫን፤ ማንም ማንንም ሳይሸከም መኖር የሚቻልባት አገር ተፈጥራ እኩልነት ሲሰፍን የአንት ስም በአገሪቷ እስከ ዘላለሙ ሲታወስ ይኖራል። ልጆችህና ልጅ ልጆችህ በአንተ ሥራ ኮርተውና አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚሄዱ ይሆናሉ። ለዚህ ዘላቂ ክብር ብለህ ብትሞት ሞትህ የክብር ሞት ይሆናል። የሣሞራንና የጓደኞቹን የሥልጣን ጥም ለማርካት ብለህ ብትገልና ብትሞት ግን አሟሟትህ ከንቱ ይሆናል። ለነፃነት፤ ለእኩልነት እና ለህግ የበላይነት ብለው የተነሱ ነፁሃን ዜጎችን ለመግደል የታጠከውን ነፍጥ ብታነሳ ፍፃሜህ ከንቱ ሁኖ እንደሚቀር አትጠራጠር። የምትሞትለትም ሆነ የምትኖርለት ዋናው ቁም ነገር ሊሆን የሚገባው በህወሃቶች የተጣመመውን ፍትህ ለማቃናት፤ ወገኖችህና አንተ የተነጠቃችሁትን ነፃነት ለመቀዳጀት፤ እውነተኛ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት በአገርህ እንዲሠፍን፤ ጥቂት ዘረኞች ብዙሃኑን ተጭነው፤ ብዙሃኑም እነዚህ ጥቂት ዘረኞችን ተሸክመው የሚኖሩበት ሥርዓት እንዲያበቃ ሊሆን ይገባዋል። ለእነዚህ ድንቅ ሃሳቦች ብለህ ብትሰዋ መስዋዕትነትህ የጀግና መሥዋዕትነት ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ መሰዋዕትነት ለአገርና ለወገን የሚሰጥ ውድ እና ታላቅ ስጦታ ነው። ይሄን ውድ እና ታላቅ ስጦታ የሰጠ ደግሞ በታሪክ ማህደራት ውስጥ ስሙ ለዘላለም ሲታወስ ይኖራልና የለወጡን ባቡር እንድትሳፈር እንመክርሃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የፍ/ቤት ቀጠሮው ለመጪው ዓመት ተቀጠረ

በቀድሞው የ“ፍትህ” ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲሰራ ሶስት ክሶች የቀረቡበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ በተደጋጋሚ ቀጠሮው ሲተላለፍበት ቆይቶ፣ ከትላንት በስቲያ ለመጪው ዓመት ተቀጠረ፡፡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት፣ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ጋዜጠኛው የቀረቡበት ሶስት ክሶች ላይ ማስረጃዎችን መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ፣ዳኛው አዲስ ናቸው በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ ለሐምሌ 24 መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ከሰአት በኋላም በድጋሚ ዳኛው በመቀየራቸው መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ በጋዜጠኛው ላይ የቀረቡት ሶስት ክሶች በቀድሞው “ፍትህ” ጋዜጣ ላይ “መጅሊሱ፣ ሲኖዶሱና የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ማጥመቂያዎች”፣ “የፈራ ይመለስ” እና “የብሄረሰቦች መብት እስከ መጨፈር” በሚሉ ርእሶች በተለያዩ ጊዜያት በወጡት ፅሁፎች፤ መንግስትን በአመፅ ለመናድ ቀስቅሷል፣ የመንግስትን ስም አጥፍቷል፣ የህዝብን አስተሳሰብ ለማናወጥ ሰርቷል፤ የሚሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የፍ/ቤት የክርክር ሂደቱ ሁለት አመታትን መፍጀቱ ታውቋል፡፡