tirsdag 24. februar 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ ቢኖር – ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

የጎረቤት ኬንያ ዳኛ ለኬንያ መንግሥት አስፈጻሚው ክፍል ልኩን ነገረው፤ ሕገ መንግሥቱን በመርፌ አስተኝተህ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ሕግ ለማውጣት አትችልም፤ ስለዚህም የሰነዘርኸውን የጉልበት ሕግ አንሣ፤ አለው፤ ዳኛ አይጥፋ! ሌላ ቢቀር ከጎረቤት ዳኝነትን እንስማ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ ቢኖር ስንት ጋዜጠኛ፣ ስንት የሃይማኖትና ስንት የፖሊቲካ መሪዎች ከየወህኒ ቤቱ ይወጡ ነበር! ሁላችንም እንደልባችን ሳንፈራ፣ ሳንፈራራ በሙሉ ነጻነት ችግሮቻችንን የወያኔን ጭቆና ጨምሮ ለመወያየትና መፍትሔዎችን ለመለዋወጥ የምንችልበት መድረክ፣ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ራድዮና ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖረን ነበር፤ ስንት ሰው ሥራ ያገኝ ነበር፡፡
ከሁሉም በላይ በየመንገዱ ጠመንጃ የያዘ ሊያስፈራራን የሚሞክር ሆድአደር እያየን፣ እንደዚሁም በየጫካው ያሉትን እያሰብን ሰላማችንን ከምናጣ አበባውን ትተን፣ ሩዙን ትተን፣ የተወደደልንን ጤፋችንን እያመረትን አዲስ ኑሮ ብንጀምር የተሻለ ነበር፡፡
ግን አንድ እንቅፋት አለብን፤ እነዚህ ከየኪዮስኩ እውቀት ገዝተን አዋቂዎች ሆነናል የሚሉት እንትኖች እንመጀመሪያ ችግሩ እንዲገባቸው፣ ሁለተኛ መፍትሔው እንዲገባቸው፣ ሦስተኛ ጉልበትና እውቀት አንድ አለመሆናቸውን ብቻ ሳይሆን በጉልበት እውቀት የማይገኝ መሆኑን ማሳመን በረዶ እየወረደ የስሜን ተራራን መውጣት ነው፤ በረዶ ሳይኖር ወጥቼዋለሁ!
እነዚህን የጉልበት አዋቂዎች — ስለሽማጌሌዎችና አሮጊቶች ሳያስቡ፣ ስለመብራት ኃይል ሳያስቡ፣ ስለውሀ ሳያስቡ ሁሉም በጉልበት ፎቅ ይውጣ የሚሉ! ይባስ ብለው ለእስረኛውም ፎቅ እየሠሩለት ውጣ! ሊሉት ነው!
እነዚህ የጉልበት አዋቂዎች የአበሻ ኑሮ፣ ቡናው፣ ሙቀጫው፣ ምጣዱ፣ በርበሬው፣ ቁሌቱ፣ ቄጤማው፣ ዶሮና በግ ማረዱ፣ ኧረ ስንቱ! ሳይገባቸው ቻይና በነገራቸው የሚያውቁትን የሚረሱ ማን ያስተምራቸው! እናውቃለን ስለሚሉ እንዴትስ ይማራለ? በእውነት ለመማር ቢፈልጉስ ስንት ዓመት ሊያስፈልጋቸው ነው! እግዚአብሔር እንሱንም እኛንም በምሕረቱ ይጎብኘን! የሚያስተምር ጎረቤት አያሳጣን!

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በጨለማ ቤት መታሰራቸውን አስታወቁ

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ የሚገኙት የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀጠና/ዞን አመራሮች ለ16 ተከታታይ ቀናት በጨለማ ክፍል መታሰራቸውን ለፍርድ ቤት አስታወቁ፡፡
ዛሬ የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡት የሰማያዊ (የፓርቲው የጎንደር አደራጅ አቶ አግባው ሰጠኝ)፣ የአንድነት እና መኢአድ የዞን አመራሮች ‹‹መረጃ አውጡ፣ የደበቃችሁትን ሁሉ ተናገሩ›› እያሉ እንደሚደበድቧቸውና በጨለማ ክፍል እንዳሰሯቸው ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ አሁንም መረጃየን ሰብስቤ አልጨረስኩም በሚል ተጨማሪ 8 ቀናት ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡
ተጠርጣዎቹ በማዕከላዊ እየደረሰባቸው የሚገኘውን ሰቆቃ አስመልክተው ለፍርድ ቤት አቤት ማለታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የቀረበበትን አቤቱታ እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የዛሬ አራት ወር ገደማ በፖሊስ ታስረው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ የተደረጉ ሲሆን፣ ጠበቃቸው በተደረገባቸው ክልከላ ምክንያት ተጠርጣሪዎቹን ካገኟቸው 2 ወር እንደሞላቸው ተናግረዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ አግባው ሰጠኝ እየተፈጸመበት ያለውን የመብት ጥሰት በመቃወም የርሃብ አድማ ላይ መሆኑ የታወቀ ሲሆን አድማውን ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት አመራሮቹ የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

fredag 20. februar 2015

አረና ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ምርጫ ያስመዘገባቸው እጩዎቹ ራሳቸውን ከምርጫው ለማግለል እየተገደዱ መሆኑን አስታወቀ።

አረና ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ከ100 በላይ እጩዎቹ ቢመዘገቡም በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰባቸው ጫና ምክንያት በርካቶች ከውድድር መውጣታቸውን ፓርቲው አመልክቷል። የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት ሳይቀሩ ካርድ የለም ተብለው እንዲመለሱ መደረጉን የፓርቲው የሕዝብ ግኑኙነት ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
አረና ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ምርጫ ያስመዘገባቸው እጩዎቹ ራሳቸውን ከምርጫው ለማግለል እየተገደዱ መሆኑን አስታወቀ። አረና ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ከ100 በላይ እጩዎቹ ቢመዘገቡም በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰባቸው ጫና ምክንያት በርካቶች ከውድድር መውጣታቸውን ፓርቲው አመልክቷል። የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት ሳይቀሩ ካርድ የለም ተብለው እንዲመለሱ መደረጉን የፓርቲው የሕዝብ ግኑኙነት ለዶቼቬለ ተናግረዋል። የክልሉ የምርጫ ቦርድ ሃላፊ ግን የአረናን አቤቱታ መሠረተ ቢስ ሲሉ አጣጥለዋል። ዝርዝሩን ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሄር አዘጋጅቶታል ።

søndag 1. februar 2015

ሬድዋን ሁሴንና የወደቀው ክሱ !


በኢትዮጵያችን ህግ ትርጉሟን አጥታ፤ፍትህም ተዋርዳ ከተጣለች የህወሃትን እድሜ ብታስቆጥርም እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ስለ ህግ የበላይነት ማውራታቸውን አላቆሙም። እነዚህ ቡድኖች የህግ የበላይነት ሲሉ እነርሱ ከፍ ብለው ከህግ በላይ፤ ከእነርሱ መንደር ያለሆነው ደግሞ ዝቅ ብሎ ከሥር ከጫማቸው ሥር ሁኖ እነርሱን ተሸክሞ የሚኖርበትን ሥርዓት ማስጠበቅ የሚችለውን ህግ ነው። እናንተን መሸከም ከበደኝ፤ ቀንበራችሁ ሰበረኝ የሚል ሰው ከተገኘ የሚጠብቀው ፍርድ “አሸባሪነት” ነው። ይህ የክፉዎችና የልበ ደንዳኖች ፍርድ ፍትህ ተብሎ በህወህቶች መንደር ይወደሳል። መፅሃፍ እንዲህ ይላል “ክፍዎች ሰዎች ፍርድን አያስተውሉም”። ህወሃቶች ባወጧቸው ህጎች የስንት ንፁሃን ዜጎች ቤት እንደፈረሰ፤ ስንት ህፃናት አሳዳጊ አልባ እንደሆኑ፤ ስንቶች አገራችውን ትተው ተሰደው እንደጠፉ ቆጥረን አንዘልቀውም። በህወሃት መንደር ህግ ዜጎችን ማጥቂያ እና ማስጨነቂያ መሣሪያ እንጂ የፍትህ ማስከበሪያ መሳሪያ አይደለም። በህወሃት ህግ ብዙ ዜጎች ጠፍተዋል፤ ብዙዎች ደግሞ በብዙ ጭንቀት እና መከራ ውስጥ ይገኛሉ።

በህወሃት መንደር የተሰባሰቡ ግለሰቦች እንደምን ያለ ብርቱ ጭለማ እና ድንቁርና ውስጥ እንደሚገኙ በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት እንችላለን። ለአሁን ግን ማሰብ ካቆሙ ቅጥረኞች መካከል ሬድዋን ሁሴን የተባለው ግለሰብ የሆነውን እንመልከት። ሬድዋን ሁሴን፤ ጌቶቹ እና ሌሎች መሰሎቹ ያሉበትን ዘመን ረስተው ወይም መረዳት ተስኗቸው፤ ከስልጣኔ መንገድም ወጥተው እንዲሁ በጭለማ ዓለም እየተደናበሩ ይገኛሉ። ሬድዋን ሁሴን ያለበትን ዘመንና የያዘው የህዝብ ስልጣን የሚያስከትልበትን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት መገንዘብ ስለተሳነው ቀና ብሎ ተናገረኝ ባላው ወጣት ላይ በአሜሪካን አገር ክስ መመሥረቱን ስንሰማ በብርቱ ተደንቀናል። አገራችንም በእንደነዚህ ዓይነት ማስተዋል በጎደላቸው ግለሰቦች የምትመራ መሆኑም በእጅጉ ያሳዝነናል።

ሬድዋን ሁሴንን በቨርጂኒያ አገረ ግዛት ያገኘው ወጣት ህወሃቶች በወገኖቹ ላይ የጫኑባቸው ሸክም ያሳመመው፤ በዚህም ህመም የተቆጣ ቁጣውንም በሰላም የመግለፅ መብቱ ያለ ገደብ የተከበረባት አገር ውስጥ ኗሪ ነው። ሬዲዋን ሁሴንን የመሰለ ራሱን ለምናምንቴ ነገር አሳልፎ የሸጠ ትንሽ ግለሰብ ይቅርና የሃያሏ አገር አሜሪካን ፕሬዝዳንትም ብዙ ወቀሳና ስድብ ይደርስበታል።ፕሬዝዳንቱም የህዝብ ተቀጣሪ መሆኑን ስለሚያውቅ ተወቀስኩ ወይም አንድ ዜጋ ተናገረኝ ብሎ የበቀል ሰይፉን አይመዝም። ፕሬዝዳንቱ ተሰደብኩ ብሎ ክፉ ቢናገር የሚከተለው መዘዝ ከስድቡ የበለጠ ጉዳት ስለሚያደርስበት ስድቡን መቻል እና መሸከም የሥራው አንዱ አካል ይሆናል።ህግ ባለበት አገር የአገሩ መሪ ህዝቡን ፈርቶ ይኖራል እንጂ፤ ህዝብ መሪውን ፈርቶ አይኖርም። ሬዲዋንና መሰሎቹ ግን እንዲህ አይደሉም። ህዝብን ረግጠውና አስፈራርተው መኖር የጎበዝ ተግባር ነው ብለው አምነው ተቀብለዋል።

ህወሃት ትንሹንም ትልቁንም ፈርቶ፤ ፍርሃቱ በወለደው ጭካኔ ዜጎችን ሁሉ አስሮ መኖር ልማዱ ሁኗል። በኢትዮጵያ ዜጎች ህወሃቶችን ፈርተው፤ ህወሃቶችም ዜጎችን አስፈራርተው የሚኖሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይሄ ሁኔታ ለማንም ወይም ለምንም እንደማይበጅ ለህወሃቶች ብንነግራቸውም ልቦናቸው በትዕቢት ታውሯልና አይሰሙንም። ሬድዋን ሁሴንም የዚህ መራራ ትዕቢት ትሩፋት ነው። እንደምን ሁኖ ቀና ብለው ያዩኛል፤ እንደምንስ ሁኖ ይናገሩኛል፤ እንደምንስ ሁኖ ስሜ በገበያ መሃል ይነሳል የሚል ትዕቢት ስለተፀናወተው ክስ መሠረተ፤ ክሱ ግን በህግ ፊት ሚዛን የማይደፋ በመሆኑ በአቃቤ ህጉ ውድቅ ተደረገ። ሬዲዋንም የፍትህን መራራ ፅዋ ተጎንጭቶ ሊውጣት ግድ ሆነበት። የህወሃት ቅጥረኞችና ህወሃቶች ውድቅ ከሆነው ከሬድዋን ህሴን ክስ ልትማሩ የሚገባችሁ የህግ የበላይነት በሰፈነበት አገር እናንተ ከተራው ዜጎች እኩል እንጂ የበላይ ልትሆኑ እንደማትችሉ፤ ከመጋረጃው ጀርባ ሁናችሁ ፍትህን የምትጠመዝዙበት እጃችሁ እንደሚታሰር እና ገና ወደፊት ደግሞ የእጃችሁን እንደምታገኙ ነው። እናንተን ከተራው ዜጋ እኩል የሚያደርግ ህግ ሲፈጠር የታጠቃችሁት ጠብመንጂያ የሸንበቆ ምርኩዝ፤ የመኖሪያ ድንኳን የሆናችሁ ማን አለብኝነታችሁ ደግሞ ፀሃይ እንዳየው ጤዛ እንደሚተን ልብ ልትሉ ይገባል። ሬዲዋንን የተናገረው ወጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁኖ ቢሆን ኑሮ ዛሬ እነሬዳዋን ፈተው በሚለቋቸው ውሾች ሊደርስበት የሚችለውን ስቃይ ስናስበው ይዘገንነናል። ከባህር ማዶ መሆኑ ከሥጋዊ ስቃይ አድኖታል።

እንግዲህ ህወሃቶች የምትፈፅሟቸው ግፎች በየደረሳችሁበት እየተከታተሉ እረፍት ማሳጣታቸውን የሚያቆሙ አይሆንም። የምትሠሯቸው ግፎች የሚያሳድዱት እናንተን ብቻ አይደለም። ከእናንተ አብራክ የሚፈጠሩ ልጆቻችሁንም ጭምር የክፉ ሥራዎቻችሁ ሰለባዎች ከመሆን አያመልጡም። ልጆቻችሁ ተሳቀው ከህዝብ ዓይንና ጆሮ ተደብቀው መኖር ዕድል ፈንታቸው ይሆናል። እናንተ የምትፈፅሙት ወንጀል ለልጆቻችሁ ኩራት ሳይሆን እፍረት፤ ክብር ሳይሆን ውረደት ሁኖ ይቆያቸዋል። ቢያንስ ለልጆቻችሁ ሠላም ስትሉ ከእኩይ ድርጊታችሁ መታቀብ ይሻላችሁ ነበር። እናንተ ግን ለትውልዱ ሠላም የሚሻለውን ትታችሁ የጥፋቱንና የደም መፋሰሱን መንገድ መርጣችኋልና ወዮታ አለባችሁ።

እናንተን መታገል ከስጋና ከደም ጋር የሚደረግ ትግል ብቻ አይደለም። የምትፈፅሟቸው ግፎች ከሰው ልጅ አዕምሮ የሚፈልቁ ብቻ አይመስልም።ከእናንተ ጋር የሚሰራ ሌላ የማይታይ የክፋት አባት ያለ እስከሚመስለን ድረስ ግፋችሁ አንገፍግፎናል። ይህን ግፍ ዝም ብለን የምናይ አይመሰላችሁ። ሊከፈል የሚገባውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል። ወጣቶችም ሳያቅማሙ አያቶቻቸው በተመላለሱባቸው ኮረብቶች ላይ ተሰማርተዋል። ክፉውን ለመቃወም፤ ደም አፍሳሹን ለማስቆም፤ ሌባውን ተው ለማለት፤ ትዕቢተኛውን አደብ ለማስያዝ፤ የነፃነት ቀበኛውን ለማስተማር ሰይፋቸው ከአፎቱ ተስማምቶ ተዘጋጅቷል።

የተከበራችሁ ያገራችን ዜጎች ሆይ !

ህወሃቶች በዜጎችቻን ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ ለእናንተ መንገር ለቀባሪው እንደ ማርዳት ይሆንብናል።የእነዚህ ቡድኖች ግፍ ፅዋውን ሞልቶ እየፈሰሰ ነው።የአገሪቷን ታሪክ አንድ በአንድ ለማጥፋት እየሠሩ ይገኛሉ-በየቦታው በእሳት የሚቃጠሉት ታሪካዊ አምባዎቻችን የአገሪቷን ታሪክ የማጥፋት ዘመቻ አካል ነው።ዜጎች አገር አልባ እንዲሆኑ ተደርገዋል፤ አብሮ በኖረው ህዝብ መካከል የሚዘራው የጥላቻ ዘር ለአገራችን አደጋ ሁኖ ተደንቅሯል። አገራችን ታሪኳ በሚመሰክርላት ሥፍራ ላይ እንዳትሆን፤ ለአፍሪካ ቀንድም ሆነ በአጠቃላይ ለዓለም ሠላም መጫወት የሚግባትን ሚና እንዳታከናውን ተደርጋለች። በተቃራኒው የግጭት አምባ፤ የችጋር ምሳሌ፤ የስደት ምልክት ሁና ከውዳቂ መንግስታት ተርታ ገብታለች። ይሄ ሁሉ እርግማን በህወሃት ምክንያት የመጣ ነው።

እኛ በአገራችን ላይ የተተከለውን ህወሃት የተባለውን እርግማን ነቅለን ለመጣል የምንችለውን ሁሉ እያደርገን ነው። ህወሃቶች የነፃነትን ዋጋ ተረድተው፤ ለፍትህ ክብር ሰጥተው፤ ዜጎችን አክብረው፤እኛም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር እኩል ነን። ከማንም አንበልጥም፤ ሌላውም ከእኛ አያንስም ብለው በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየት ፍርሃታቸው እና ድንቁርናቸው ቢፈቅድላቸው ለሁላችንም መልካም ነበር። ይህ መልካም ነገር ግን የእኛ ምኞት ብቻ ሁኖ ቀርቷል።ህወሃቶች የተፀናወታችው ትዕቢት የሰይጣን ትዕቢት ስለሆነ እንዲሁ በቀላሉ በጄ የሚሉ አይሆኑም። እኛ የቀረን አንድ መንገድ በማንኛውም መንገድ አገራችንን ከጥፋት ማዳን ብቻ ነው። ይህም ታሪካዊ ግዴታችን ሁኗል።

ይህን አገርን የማዳን ታሪካዊ ግዴታ የዚህ ቡድን ወይም ደግሞ የዚያ አካል ብቻ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ተግባር አይደለም። እያንዳንዱ ማሰብ የሚችል እና ለራሱ ትንሽ ክብር ያለው ዜጋ ሁሉ ኢትዮጵያን ለመታደግ የሚችለውን ጠጠር መወረወር ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያ ሬድዋን ሁሴንን በመሳሰሉ ምናምንቴዎች ስትዋረድ እጅን አጣምሮ ቁሞ መታዘብ ትክክለኛ ተግባር አይሆንም። የአገሪቷ ድሃ ዜጎች ስቃያቸው በዝቶ እና ጭንቀታቸው ልክ አጥቶ እያየን ዝም ብንል እርግማን ይሁንብን ካሉ ዜጎች ጋር መተባበሪያ ግዜው አሁን ነው።

እኛ አርበኞች-ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለፍትህ ንቅናቄ አገራችን ከገባችበት የውርደት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት የጀመርነውን ትግል እለት እለት እያደስነው፤ እለት እለት እያሰፋነው፤ እለት እለት እያሳደግነው ቀጥለናል። እኛ ዓይናችን እያየ ህዝባችን አይዋረድም፤ አገራችንም ከሥፍራዋ በታች ስትሆን ዝም አንልም።የሚከፈለውን ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፍለ አናቅማም። በአያት ቅደመ አያቶቻችን ደም ተከብራ የኖረች አገር ዳግም በእኛ ደም ተከብራ ትኖራለች። ቀጣዩ ትውልድም የተከበረች አገር ተርክቦ፤ እርሱም ተከብሮ ይኖር ዘንድ እኛ እንሰራለን እግዚአብሄርም ያከናውንልናል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!