torsdag 19. mars 2015

በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ግሰለቦች የዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ ! ‹‹ለእኔ ብቸኛው አሸባሪ ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ የህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ነኝ›› አብርሃ ደስታ


በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ግሰለቦች የዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ
‹‹እኔ አሸባሪ አይደለሁም፡፡ ኢህአዴግ አሸባሪ ነው፡፡ ለሽብር ሀሳቡም ፍላጎቱም የለኝም›› ዳንኤል ሺበሺ
‹‹የተባለውን ለነገር አለማድረጌን ከእኔ በላይ የከሰሰኝ መንግሥት ጠንቅቆ ያውቃል›› ሀብታሙ አያሌው
‹‹ለእኔ ብቸኛው አሸባሪ ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ የህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ነኝ›› አብርሃ ደስታ
‹‹ይሄ 19ኛ ችሎት የጦር ፍርድ ቤት ችሎት እየመሰለ ነው›› የሺዋስ አሰፋ
‹‹ሃይማኖቱንና ማኅበረሰቡን ከሚፈራ ህዝብ ወጥቼ እንዲህ አይነት ተግባር አልፈጽምም›› ባህሩ ታዬ
————————
ዛሬ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት እና በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ያሉ 10 ሰዎች ቀርበው ነበር፡፡ መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመቀበል እና ከ1-5ኛ ተራ ቁጥር ያሉ ተከሳሾች በእስር ቤቱ ደረሰብን ብለው ባቀረቡት አቤቱታ ላይ አስተያየት ካላቸው ለመቀበል መሆኑን የችሎቱ የግራ ዳኛ ገልጸዋል፡፡
የተከሰሾቹን የጽሑፍ አስተያየት በጠበቃ ተማም አባቡልጉ በኩል ቀርቦ ከመዝገብ ጋር ከተያያዘ በኋላ ተከሳሾቹ በየተራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ የግራ ዳኛው በመናገር 1ኛ ተከሳሽን ‹‹በክሱ ላይ እንደቀረበው ወንጀሉን ፈጽመሃል ወይስ አልፈጸምክም?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡
ዘላለምም ‹‹አቃቤ ሕግ ባላደረኩት ነገር ህጉን መደገፍ ስለሚሆንብኝ ምንም መልስ አልሰጥም›› ሲል ዳኛው ‹‹በሥነ ሥርዓት ሕጉ ክሱን ክደው ተከራክራል› በሚል መዝግበነዋል›› በማለት መዝገብ ላይ አሰፈሩ፡፡
2ኛ ተከሳሽ አቶ ሃብታሙ አያሌው በበኩሉ ‹‹የተባለውን ለነገር (ሽብር) አለማድረጌን ከእኔ በላይ የከሰሰኝ መንግሥት ጠንቅቆ ያውቃል፤ እረዳለሁም፡፡ አቃቤ ሕግ ለምን እንደከሰሰኝም አውቃለሁ፡፡ የቆምኩለትን ሕጋዊ ፓርቲንም አፍርሶታል፡፡›› ብሏል፡፡
3ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺም ‹‹ሽብር የሚባለውን ነገር የሰማሁት ከሟቹ ኦሳማ ቢንላዳንና ከዘቶ መለስ ዜናዊ ነው፡፡ አደረክ ለተባልኩት ነገር ሃይማኖቴ፣ ዓላማዬ …አይፈቅድም፡፡ በዚህ ምክንያት ቤቴ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ እኔ አሸባሪ አይደለሁም፡፡ ኢህአዴግ አሸባሪ ነው፡፡ ለሽብር ሀሳቡም ፍላጎቱም የለኝም፡፡ መንግሥት ፓርቲዬን ለማፍረስ የፈነቀለው …›› ብሎ ሳይጨርስ ፍርድ ቤቱ ንግግሩን እንዲያቋርጥ አስገድዶታል፡፡
4ኛ ተከሰሽ አብርሃ ደስታ መናገር ከመጀመሩ በፊት ‹‹ድርጊቱን መፈጸም አለመፈጸምህን ብቻ ተናገር›› ተብሎ ከችሎቱ ተነግሮት ነበር፡፡ አብርሃም በተረጋጋ መንፈስ ‹‹መልሱ እሱ አይደለም፤ የፈለኩትን እናገራለሁ፡፡ ሀሳቤን ልግለጽ›› ሲል ተናገረ፡፡ ዳኞች ሳይዋጥላቸው እንዲናገር ፈቀዱ፡፡ ‹‹ክሴ ከአሸባሪ ጋር በመገናኘት …የሚል ነው፡፡ አሸባሪ ለሚፈልገው ዓላማ ሰላማዊ ያልሆነ /ሰውን የሚጎዳ ድርጊት የሚያስፈጽም ነው፡፡ ለእኔ ብቸኛው አሸባሪ ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ ህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ነኝ …›› የግራ ዳኛው የአብርሃን ንግግር አቋረጡትና ‹‹ክሱ ላይ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚል የለም፡፡ ክሱን መቃወም አለመቃወምህን ብቻ ተናገር›› አሉት፡፡ አብርሃም ‹‹ሕወሃት /ኢህአዴግ፣ ደህንነቱ ማፊያ ነው … ›› ዳኞቹ በድጋሚ አቋረጡት፡፡ አብርሃ ‹‹አልጨረስኩም›› ቢልም ዳኞቹ ከዚህ በላይ ሊሰሙት አልፈቀዱም፡፡
5ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋም ‹‹ዛሬ ለመጨረሻ ጊዜ ነው የምናገረው፣ ስሙኝ›› ሲል ለችሎት ገለጸ፡፡ ዳኞቹ ክሱን መቃወም አለመቃወሙን ብቻ እንዲናገር ገለጹለት፡፡፡ የሺዋስ ‹‹ትንሽ ሁለት ደቂቃ የምትሞላ ንግግር ነች፡፡›› አላቸውና ቀጠለ፡፡ ‹‹ሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 75/4 ላይ ልዩ ፍርድ ቤት ስለማቋቋም ይደነግጋል፡፡ ይሄ 19ኛ ችሎት የጦር ፍርድ ቤት ችሎት እየመሰለ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ዳኞች ነጻ ስለመሆናቸው ይደነግጋል፡፡ የእኔ ችግር ችሎቱ ላይ ነው፡፡…›› ዳኞች የየሺዋስን ንግግር አቋረጡት፡፡ የሺዋስም ‹‹ዛሬ ብቻ ነው የምናገረው›› በማለት እንዲህ አለ፡- ‹‹በሕገ-መንግሥቱ ላይ ዳኞች ነጻ መሆን እንዳለባቸው ቢቀመጥም የመርማሪ እና ዐቃቤ ሕጎችን ሀሳብ ብቻ የሚሰማው፤ እኛን አይሰማ አሻንጉሊት ፍርድ ቤት ነው፡፡…›› የሺዋስም መናገር የቻለው ይሄን ብቻ ነው፤ ዳኞች ድጋሚ አስቁመውታል፡፡
6ኛ ተከሳሽ፣ ዮናታን ደግሞ ‹‹ያለፈቃድ እንድተውን እየተገደድኩ ነው›› ብሏል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ (ስሙን የዘነጋሁት) ‹‹የተቀነባበረ ክስ ስለሆነ ምንም ማለት አልችልም፡፡›› ሲል 8ኛ ተከሻሽ ባህሩ ታዬም ‹‹ሃይማኖቱንና ማኅበረሰቡን ከሚፈራ ህዝብ ውስጥ ወጥቼ እንዲህ አይነት ተግባር አልፈጽምም፣ አለፈጸምኩምም፡፡ …ጊዜ እውነቱን ይፈርዳል›› ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡ 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾችም ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም›› ብለዋል፡፡
ችሎቱም ‹‹ለአንድ ወር የለንም›› ካሉ በኋላ 15 የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለግንቦት 13፣ 14 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

tirsdag 10. mars 2015

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተላለፈባቸው


Habitamu
  • በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
  • ᎐ተጨማሪ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል
• ‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው›› አብርሃ ደስታ
• ‹‹ችሎቱ ላይ ያጨበጨብነው በማፌዝ ሳይሆን በምሬት ነው›› የሺዋስ አሰፋ
• ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› ዳንኤል ሺበሽ
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከስምንት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እንዲሁም የዓረና ትግራይ ፓርቲዎች አመራሮች ‹ችሎት በመድፈር ወንጀል› ጥፋተኛ በመባላቸው ዛሬ መጋቢት 1/2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በሦስቱ አመራሮች ላይ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
የካቲት 26/2007 ዓ.ም ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና ንብረትም እንደተወሰደባቸው በመግለጽ አቅርበውት ለነበረው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨቡና 3ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ሳይፈቀድላቸው ‹‹ጥሩ ፍርድ፣ ጥሩ ብይን›› በማለት አቶ የሺዋስን በመደገፍ ችሎት ደፍረዋል ተብለው ጥፋተኛ መሰኘታቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተሰይሞ በአብርሃ ደስታ፣ በየሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ላይ የሰባት ወራት እስራት በእያንዳንዳቸው ላይ ወስኗል፡፡ ሦስቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ድጋሜ ችሎት ውስጥ አጨብጭበዋል፡፡ በዚህም ድጋሜ ጥፋተኛ ተብለዋል፤ ከሁለት ቀናት በኋላም የቅጣት ውሳኔ ይወሰንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሦስቱ ተከሳሾች ‹‹እድል ስጡን እንናገር፣ አቤቱታም አለን ተቀበሉን›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ሊሰማቸው አልፈለገም፡፡ በተለይ ዳንኤል ሺበሺ ‹‹ሌላ አቤቱታ አለኝ፣ ፍርድ ቤቱ ያዳምጠኝ›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ አሁንም ችሎቱ ላይ እያፌዛችሁ ነው በሚል ጥፋተኛ ሲላቸው ሦስቱም አመራሮች ፍርድ ቤቱን ማስፈቀድ ሳያስፈልጋቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው፡፡ ‹Already› የተደፈረ ችሎት ነው›› ሲል አብርሃ ደስታ ተናግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳኞቹ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል›› ሲሉ አብርሃ በበኩሉ ‹‹አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?›› ሲል መልሷል፡፡
አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ ‹‹ከስምንት ወር በላይ ታፍነናል፡፡ በህግ አይደለም የተያዝነው፡፡ ደግሞ ማጨብጨባችን በችሎቱ ከማፌዝ ሳይሆን ከምሬት በመነጨ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ መብታችን ተጥሷል፡፡ እኔ ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኔ ነው የታሰርኩት፡፡›› ብሏል፡፡
አቶ ዳንኤል ሺበሽ ድግሞ ‹‹አሁንም ችሎት ደፍራችኋል ካላችሁ ቅጣቱን ጨምሩብንና ሸኙን፡፡ በእርግጥ ዳኞች ላይ ያለውን ጫና እንረዳለን፡፡›› ሲል ችሎት ውስጥ ተናግሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ በተከሳሾችና በችሎቱ መካከል ያለው አለመግባባት ሲጨምር ዳኞቹ መጋቢት 3/2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ በመጥቀስ ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ከችሎት እየወጡ እያሉም አቶ ዳንኤል ሺበሽ ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፤ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› እያለ ችሎቱን ለቅቆ ወጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት መውጣታቸውን ተከትሎ፣ ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ ላይ በቀረበው አቤቱታ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ላይ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ አቤቱታው እንዲመዘገብለት የጠየቀው አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ‹‹በበኩሌ ያሉኝን መረጃዎች እያቀረብኩ ስነ-ስርዓቱን አክብሬ ክርክሩን አቀጥላለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡