lørdag 30. november 2013

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ከተቃዋሚዎች ጋር ተወያዩ


በአወዛጋቢው የ1997 ዓ.ም ምርጫ የታዛቢ ቡድን መሪ የነበሩት አና ጐሜዝን ጨምሮ “ለአፍሪካ ፣ ካሪቢያን፣ ፓስፊክና የአውሮፓ ህብረት” የጋራ ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ሰሞኑን ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር  ተወያዩ፡፡ፓርቲያቸውን ወክለው በውይይቱ እንደተካፈሉ የተናገሩት የኢዴፓ ማዕከላሚ ኮሚቴ አባል አቶ ልደቱ አያሌው፤ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት የኢትዮጵያ  የዲሞክራሲና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ምን አዲስ ነገር አለ? የወደፊቱ አቅጣጫ ምን ይሆናል? በማለት ጥያቄ እንደሰነዘሩ ገልፀዋል፡፡ የፓለቲካ ምህዳሩ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊጠናከሩ የሚችሉበት እድል ከጊዜ ወደ ጊዜ መጥበቡን ተናግሬያለሁ የሚሉት አቶ ልደቱ፣ የሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሂደት እንደሚያሳስበንና የአውሮፓ ህብረት እርዳታ የፓለቲካ መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለባቸው አስረድቻለሁ ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ለአገራችን እርዳታ መስጠቱን እንደማንቃወም፣ የእኛን ችግር እነሱ እንዲፈቱ እንደማንጠብቅ ገልፀንላቸዋል ያሉት አቶ ልደቱ፤  ከዲሞክራሲያዊና ከሰብዓዊ መብት አያያዝ አኳያ ማድረግ የሚገባችሁን ወደኋላ ትታችኋል፤ እርዳታ ሰጪ እንደመሆናችሁ ማድረግ ያለባችሁን ነገር ዘንግታችኋል የሚል አስተያየትሰጥቻለሁ ብለዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሃፊ አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው፣ የፓለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን፣ የሠላማዊ ትግል ተስፋ መዳፈኑንና ህገ መንግስቱ እየተከበረ አለመሆኑን እንዳስረዱ ጠቅሰው፤ በነፃው ፕሬስ ህግ፣ ተሻሽሎ በወጣው የፓርቲ  ህግ፣ በፀረ ሽብርተኛ አዋጁ ዙሪያ እንደተወያዩበት ተናግረዋል። በ2002 ዓ.ም. ምርጫ በዝርፊያና በንጥቂያ ኢህአዴግ 99.6 በመቶ ድምፅ አግኝቶ ማለፉን በመጥቀስ፤ 2007ዓ.ም. የሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ አጣብቂኝ እንደሆነብን ለአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት አስረድቻለሁ ብለዋል - አቶ አስራት፡ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝቡን ሰብስበን ማነጋገር፣ ሠላማዊ ሰልፍ  ማድርግ እንዳልቻልንም፣ የመንግስትን ጫና በማሳየት ገለፃ አድርጌያለሁ በማለት አቶ አስራት ተናግረዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት አባላት ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትም ጋር ቀደም ብለው ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት አና ጎሜዝ፣ አገሪቱ በኢኮኖሚ ማደጓለ እንደሚገልፅና ልማቱ ግን  ህዝቡን ከድህነት ያላወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ለሚደረገው አገራዊ ምርጫም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አና ጐሜዝ ገልፀው፤ ታዛቢዎችን ከመላክ በተጨማሪ በየሁኔታው እና በየወቅቱ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ መድረክ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በውይይቱ ላይ ተካፋይ እንደነበሩ ታውቋል፡፡

Source: Addis Ademas

fredag 29. november 2013

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የመኪና አደጋ ደረሰ


ዛሬ ማለዳ ከጠዋቱ 11 ሰዓት ላይ ከሰሜት ሆቴል ወደ ጊዮርጊስ ቁልቁል ሲሄድ የነበረ አንድ ከባድ የጭነት ማመላለሻ(SINO TRUCK)  መኪና ባጋጠመው የፍሬን ችግር ምክንያት ሹፌሩ መኪናውን መቆጣጠር አቅቶት ቀጥታ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅጽርን ደርምሶ በመግባት ከፍተኛ አደጋ አድርሷል ፡፡  በወቅቱ በቦታው ላይ በእቅልፍ ላይ የነበሩ ሁለት ጎዳና ተዳዳሪዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች ላይ ከባድ የሆነ አደጋ ደርሶባቸዋል ፤ ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸው ሶስቱ ሰዎች ወዲያውኑ በእሳት አደጋ ሰራተኞች እና አካባቢው ላይ ባሉ ሰዎች ጥረት ራስ ደስታ ሆስፒታል ተልከው ጊዜያዊ እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወስደዋል ፡፡ በአደጋው የቤተክርስቲያኑ መግቢያ በር እና ግንብ ከፍተኛ አደጋ የደረሰበት ሲሆን በተጨማሪ ሰው በፍርስራሽ ውስጥ ይኖራል ተብሎ በመገመቱ በአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ፍርስራሹን የማንሳት ስራ ሲያከናውኑ ተስተውሏል፡፡ የደረሰው አደጋ አሰቃቂ መሆኑን በቦታው የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡
ከአደጋው በኋላ የመኪናው ሹፌር በሰጠው ቃል መሰረት የመኪናው ንፋስ እምቢ በማለቱ አደጋው የደረሰ መሆኑን ተናግሯል፤ በአሁኑ ሰዓት  ፖሊስ የመኪናው ሹፌር ላይ ተጨማሪ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
source.አንድ አድርገን

በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አጠገብ የተገኘው ጥቅል ቦምብ መሆኑ ተረጋገጠ


በሩሲያ ሞስኮ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አቅራቢያ በፖሊስና አነፍናፊ ውሻ አማካይነት የተገኘው ጥቅል፣ ቤት ሠራሽ ቦምብ መሆኑን የአገሪቱ የደኅንነት አገልግሎት ማረጋገጡን ዘገባዎች አመለከቱ፡፡
ዘ ቮይስ ኦፍ ራሺያ (የሩሲያ ድምፅ) የተሰኘው የአገሪቱ ሬዲዮ በድረ ገጹ እንዳለው፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ በፖሊስና በአጋዥ አነፍናፊ ውሻ አማካይነት በኢትዮጵያ ኤምባሲ አቅራቢያ ተቀምጦ የተገኘው ጥቅል ዕቃ ወደ ላብራቶሪ ተወስዷል፡፡
በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አካባቢ ከሚገኝ የቆሻሻ መጣያ አቅራቢያ ወድቆ ከተገኘውና በኋላም በቤት ውስጥ እንደተሠራ ከተረጋገጠው ቦምብ ጋር አብሮ የሞባይል ስልክ ተያይዞ መገኘቱን የአገሪቱ የደኅንነት አገልግሎትን የጠቀሰው ዘገባ ያመለክታል፡፡
በሩሲያ የአገር ውስጥ ደኅንነት አገልግሎት ላብራቶሪ የተመረመረው ጥቅል ዕቃ፣ በሦስት የፕላስቲክ ብልቃጦች ውስጥ በግምት 400 ግራም የሚሆን ፓይሮ ፓውደርና ሮው ቦልትስ የተሰኘ ተቀጣጣይና የፈንጂ ዱቄት ተሞልቶ ታሽጐ ነበር፡፡ የታመቀ ተቀጣጣይ ዱቄት ከተሞሉ ብልቃጦች ጋር ተያይዞ የተቀመጠው የሞባይል ስልክም ከርቀት ፍንዳታውን ለመቆጣጠር ያለመ መሆኑን ምርመራው አረጋግጧል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለማግኘት ያረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
ethiopian reporter

የህዝባችን መከራ የወያኔ የፖለቲካ መጠቀሚያ አይሆንም! (ግንቦት 7)

November 28, 2013
Ginbot 7 weekly editorialበሳውዲ አረቢያ ውስጥ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሁንም መከራና ስቃይ ላይ ናቸው። የደረጃ ጉዳይ ነው እንጂ ችግሩ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የተንሰራፋ ነው። በመላው አለም ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ካለማቋረጥ ያደረገው ወገንና ሀገር አኩሪ ጩኸትና አቤቱታ ችግሩ በአለም ዙሪያ ትኩረት እንዲያገኝ ባያደረግ ኖሮ የወገኖቻችን መከራ ከዚህም በከፋ መልክ ይቀጥል እንደነበር ጥርጥር የለውም። አንድ ቀን እንኳን ለሚገዛው ህዝብ ሀላፊነትና ተጠያቂነት ተሰምቶት የማያውቀው የወያኔ ጉጅሌ መንግስት እግሩን እየጎተተ ቢሆንም ወደ ችግሩ አቅጣጫ እንዲመለከት የተገደደው በዚሁ የወገን ጩኸት መሆኑ ግልጽ ነው።
ወያኔ ስላልቻለ ነው እንጂ ይህንን ከአለም አጽናፍ እስከ አለም አጽናፍ ያስተጋባ የወገን ደራሽ ድምጻችንን አዲስ አበባ ላይ እንደ አደረገው በሃይል ለማፈን ወደኋላ አይልም ነበር።
ሀፍረት የለሾቹ የወያኔ መንግስት ባለስልጣኖች ይህን የተጋለጠ ሀገርና ህዝብ አዋራጅ ተግባራቸውን እና በውሸት የተበከለ ገመናቸውን ለመሸፈን ከዚያም አልፈው የዋሆችን በማታለል የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ የተለመደ ቲያትር መስራቱን ተያይዘውታል። ቴዎድሮስ አድሃኖም ችግሩ ባለበት በሳውዲ መሬት ላይ ሳይሆን የሳውዲ አረቢያ መንግስት በራሱ ወጪ አሳፍሮ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ባፈሰሳቸው ኢትዮጵያውያን መሃል እየተጎማለለ ያዛኝ ቅቤ አንጓች ቲያትሩን ሲሰራ ትንሽ እንኳን ሀፍረት አይታይበትም።
እነዚሁኑ ወደ ሀገር የተመለሱ አእምሯቸው በችግር የተመሰቃቀለ ዜጎች ወደ ካሜራ እየገፉ ስለ ሳውዲ ኤምባሲያቸውና ስለመንግስታቸው ‘ድንቅ” አገልግሎት እንዲናገሩ ያስጠኗቸውን ተመሳሳይ አረፍተ ነገር መስማት የሚያሳዝን ባይሆን ኖሮ ተወዳዳሪ የሌለው ኮሜዲ ይወጣው ነበር።Dr. Tedros Adhanom Ghebreyesus, the Minister of Foreign Affairs of Ethiopia.
እውነቱ ዛሬ በሀገራችን የሰፈነው ስደትና አብሮት የሚመጣው መከራ ሁሉ ዋናው አምራች ፋብሪካ ወያኔ መሆኑ ነው። ወያኔ የገነባው ጥቂት ጀሌዎቹንና ሎሌዎችን ተጠቃሚ ያደረገና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተለይ ወጣቱ በሀገሩ ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረገው ስርአት ነው። የስደታችንና የመከራችን ምንጭ ስደት የሚመጣው በሀገር ተስፋ መቁረጥ ነው። እንጀራ ፍለጋና ጭቆናና አፈና ሽሽት አምልጠን በየባዕድ ሀገሩ እንድንከራተት የሚያደርገን የወያኔ ስርአት ነው። በታሪካችን ውስጥ ተሰደን በባዕድ የተዋረድነው በወያኔ ምክንያት ነው።
በሀገር ውስጥ በአፈና ስር ሆናችሁ፣ በውጪው አለምም በየኢምባሲው የምታሰሙት ጩኸትና የምታፈሱት እምባ እብሪትና ትእቢት ያደነደነውን፣ ዝርፊያ ያደነዘዘውን የወያኔን ልብ እንደማያሸብረው ማወቅ አለብን።
የወያኔ ሹማምንቶች ይግረማችሁ ብለው ከአላንዳች ሀፍረት ያውም በሳውዲ አረቢያ ወጪ ተጓጉዘው ሀገር የገቡትን ግራ የተጋቡ ስደተኞች ለፖለቲካቸው ማሳመሪያ በቴሌቪዥን ስእልና ፎቶግራፍ መነሻ ሲያደርጉትና ለፖለቲካ ስራ መሳሪያ ሲያውሉት እያየን ነው። በነሱ ቤት ብልጥ ፖለቲከኞች መሆናቸው ይሆናል። በኛ ቁስል ላይ እንጨት እየሰደዱ መሆናቸውን ግን ፈጽሞ አይሰማቸውም።
ወያኔ በመካከለኛው ምስራቅ ተሰደው ለፍተው የሚኖሩት ወገኖቻችን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ያውቃል። ቢያንስ በየኢምባሲው ያስቀመጣቸው ነጋዴዎች ይነግሩታል። ችግሩን እንዳላየና እንዳልሰማ የሚያየው ከዜጎች ይልቅ እነሱ አፈር ግጠው ለፍተው ለሚያመጧት የውጪ ምንዛሬ የበለጠ ፍቅር ስላለው ነው። በዚህ ተግባሩ ወያኔ ወገኑን የሸጠ ባሪያ ፈንጋይ ነጋዴ እንጂ የመንግስት መሪ መሆኑ ያጠራጥራል።
ግንቦት 7 የፍትህና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ዘወትር እንደሚለው ሁሉ ይህ የዜግነትና የሀገር ውርደት፣ ይህ ሁሉ የወገን መከራ የሚቆመው የዚህ ሁሉ መሰረት የሆነው ወያኔና ስርአቱ ከመሰረቱ ሲነቀልና ሲወገድ መሆኑን ላፍታም አይዘነጋውም።
እንባችን የሚደርቀው ደማችን በየቦታው መፍሰሱ የሚቆመው መብታችን እንደዜጋ ተከብሮ ቀና ብለን የምንሄድበት ሀገር በትግላችን የተቀዳጀን ጊዜ ብቻ ነው።
ግንቦት 7ን ተቀላቀሉ በያላችሁበት ግንቦት 7 ሁኑ!! እኛ ከዚህ ውርደት ሞቶ የሚገኘው ነጻነት ይሻላል ብለን የተነሳን ልጆቻችሁ ነን። እርሰዎስ?
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

tirsdag 26. november 2013

ተዋርደን አንቀርም!! ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

November 26, 2013
ሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እያደረሰች ያለውን ግፍና በደል በሰላማዊ ሰልፍ ለመቃወም ፓርቲያችን በወሰነው መሰረት ለሚመለከተው ክፍል አሳውቀን ነበር፡፡መቸም ህዝባችን በጭቆና ውስጥ ስለኖረ በመብቱና በግዴታው መሀል ያለውን ድንበር በውል ካለመረዳቱ የተነሳ ሰልፉ እንዲደረግ ስለመፈቀዱ በተደጋጋሚ ስንጠየቅ ነበር፡፡ህጉ የሚለው ግን ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡በተቃራኒው መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ሳቢያ በእለቱ ለሰላማዊ ሰልፉ የደህንነት ከለላ መስጠት የማይችልበት ሁኔታ ከገጠመው ሰልፉን ለጠራው አካል ችግሩን ገልጾ ቀኑ እንዲተላለፍለት ይጠይቃል፡፡በመሆኑም ይህን መሰል ጥያቄ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ለፓርቲያችን ባለመቅረቡ በሙሉ ልብ ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉን ተያያዝን፡፡Interview Eng. Yilkal Getnet
ሁሌም ቢሆን መንግስት ሰበብ ፈልጎ ሊወነጅለንና ከመስመር ሊያስወጣን እንደሚፈልግ በሚገባ እናውቃለንና በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ለሚመለከተው መስሪያ ቤት ባሳወቅን በአስራ ሁለት ሰአታት ውስጥ ምላሽ ስላልመጣ ሙሉ በሙሉ ህጋዊነታችንን አረጋግጠናል ማለት ነው፣እነሱ ደግሞ ጠብ-መንጃ በእጃቸው አለና የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡
አቶ ሽመልስ ከማል ለሚዲያወች የሰጡትን ፍጹም ከእውነት የራቀ ውንጀላና ሰበብ አዳምጨዋለው፡፡ “ሰላማዊ ሰልፉን ያገድንበት ምክንያት ጸረ-አረብ መፈክሮች ስለነበሩ ነው“ብለዋል፡፡መጀመሪያ ደረጃ ሰልፉ ገና ከግቢው ፈቅ ሳይል ነው ያፈኑት፣ሆኖም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንድ በአንድ እየሆንን ወደ ሰላማዊ ሰልፉ መዳረሻ ለመሄድ ስንሞክር የተወሰኑ አመራሮችን አራት ኪሎ አካባቢ ያዙን፣እነሱ ቀድሞውኑ ሰልፉ እንዳይካሄድ ስለወሰኑ ነው እንጅ ትንሽ እንኳ ተንቀሳቅሶ የሰልፉን ባህሪ ለመገምገም ምንም እድል አልሰጡንም፡፡
ለምሳሌ ሰልፉን እንደምናደርግ ይፋ ባደረግን ማግስት ከራዲዮ ፋና ተደውሎ አንዳንድ ጥያቄዎች ተጠይቄ ነበር፡፡በቃለ-መጠይቁ ሰላማው ሰልፉ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም እንደምናደርግ ተናግረናል፡፡ጋዜጠኛው ለሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መልዕክት ካለ ብሎ በጠየቀኝ ወቅት የሳውዲ አረቢያ ሰንደቅ አላማ ላይ ያለው ምልክትና ጽሁፍ ሀይማኖትን የሚመለከት በመሆኑ ዜጎች በስሜታዊነት ባንዲራ እንዳያቃጥሉ፣እነሱ ቢያዋርዱንም እኛ ግን ክብር ያለን ዜጎች ስለሆንን ተቃውሟችንን ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ማካሄድ እንዳለብን ተናግሬ ነበር፡፡ከሰላማዊ ሰልፉ በፊት በዚህና በተለያየ መንገድ በማያሻማ ሁኔታ መልዕክት ባስተላልፍም እነሱ ግን ይህን በመቁረጥ አላስተላለፉትም፡፡እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ሲደመሩ የአቶ ሽመልስ ከማል ንግግር ነጭ ውሸት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡
ሁለተኛ የአንድ ሀገር መንግስት ዜጎቹ እየተደፈሩ፣በማጎሪያ ካምፕ በረሀብና በውሃ ጥም፣ሌላው ቢቀር መጸዳጃ ቤት እንኳ ተከልክለው ፍጹም ከሰውነት ክብራቸው ወርደው እየተበደሉ፣እየተገደሉ ባለበት ወቅት ገና ለገና ተቃዋሚ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ በሚንጸባረቅ ጥላቻና ተቃውሞ የዲፕሎማሲ ግንኙነቴ ይበላሽብኛል ብለን መናገር እንችላለን?ሌላው ይቅር አንድ ክፉና ደጉን የለየ ሰው የሚያስበው ጤነኛ ሃሳብ ነው ማለትስ ይቻላል?
ከእገዳው ባሻገር የሚደንቀው ነገር ደግሞ በፓርቲያችን አመራሮችና አባላት ላይ የተደረገው ድብደባ ነው፣የሆነ ማስተላለፍ የፈለጉት ነገር ያለ ይመስላል፡፡የጭካኔያቸውን መጠን እንድናውቅ የሚደበድቡት አቅመ-ደካሞችን፣ሽማግሌወችንና ሴቶችን እየመረጡ በፍጹም አረመኔነት ነበር፡፡ይህን ተግባራቸውን ስመለከት የደረሱበትን የዝቅጠት ደረጃ መታዘብ ችያለው፡፡ከፖለቲካ ልዩነትም፣ከአምባገነንነትም በላይ ሰወቹ እንደታመሙ ነው ለመረዳት የቻልኩት፣ስር የሰደደ የቁስ ሰቀቀንና የስልጣን ጥም የተጣባቸው፣ለዚያ ሲሉም የትኛውንም አይነት ውርደት ለመቀበል የቆረጡና የሞራል ልዕልናቸውን ሙሉ በሙሉ ያጡ ሰዎች ናቸው፡፡ስነ-ልቦናቸው ክፉኛ ተቃውሷል እንጂ ሀገር እመራለው የሚል ቡድን እንዲህ ያለ ተግባር ይፈጽማል ለማለት እቸገራለው፡፡በአባላቶቻችን ላይ ክፍኛ ድብደባ ተፈጽሟል፣እስከዛሬም እግሮቻቸው መራመድ የማያስችላቸው፣የሚያነክሱ ሰዎች አሉ፡፡እውነት ለመናገር ይሄ እብደት ነው፡፡አንዲት እራሷን መከላከል የማትችል ሴትን ለሶስት መደብደብን ከዚህ በተሸለ ልገልጸው አልችልም፡፡
አንድ ማስገንዘብ የምፈልገው ነገር ለኛ ዋነው ጉዳይ የዜጎቹ ህጋዊነት ወይም ህጋዊ ያለመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡በምንም አይነት መንገድ ሴቶች እየተደፈሩ፣ወንዶች በየስርቻው እንደ ውሻ ተቀጥቅጠው እየተገደሉ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ታጉረው ይህን ሁሉ መከራ መቀበላቸውን ልንታገሰው፣ወይም ከህጋዊነት አንጻር እየተራቀቅን ልንመለከተው አንችልም፣ስለ ህግም ከተወራ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ጭፍጨፋው ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ባላቸው ላይ ጭምር ሲፈጸም እንደነበር አምኗል፡፡
ባለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የአንዱ ሀገር ዜጋ ካለ ሀገሩ መገኘት አገር ይያዝ የሚያስብል አይደለም፡፡መውጣት ካለባቸው ጊዜ በመስጠት፣ከመንግስታቸው ጋር በመነጋገር በዘዴ ነገሩን መከዎን እየተቻለ አንድ ሀገርና መንግስት በሰዎች ላይ እንዲህ የጭካኔ ጥግ የሆነን አቋም ይዘው መንቀሳቀሳቸው ፍጹም ኢ-ሰብአዊነት ነው፡፡
ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለ አስከፊ ጊዜ የለም፣እውነቱን ለመናገር ለአገዛዙ ሰዎች የነበረኝ ጭላንጭል ተስፋም አፈር ተደፍቶባታል፣እንዲህ ግልጽ የሆነ ጭፍጨፋ እየደረሰብን እንኳ በድፍረት ለመናገር አልፈለጉም፡፡ስለ ኢትዮጵያውያን መገደል ለማውራት ሲፈልጉ ሌላ ሀገር ይጠቅሱና እነሱም እኮ እየተገደሉ ነው ይላሉ፣ወገን ከምንለው የማህበረሰባችን አካል ይሄን መስማቱ ከጥቃቱ ይበልጥ ያማል፡፡
ለምሳሌ ኢቲቪ ስጉዳዩ ሲያወራ ህገ ውጥ ሊባል የሚችል ድርጊት ተፈጽሟል በማለት ነው፡፡ተመልከቱ! እንዴት ያለ ባዕድነት ነው?ኢትዮጵያውያን በድህነትም ውስጥ እንኳ ለክብራችን የመሞት ባህሪ አለን፣ይሄ ከቀደሙት አንጡራ ኢትዮጵያውያን የወረስነውና ዛሬም ያለን ሀብታችን ነው፡፡
ትናንት ፍየል ጠባቂ የነበረ በረኸኛ ይህን ክብራችንን ገፍፎ እንደውሻ ቀጥቅጦ ስርቻ ሲጥለን ያልተቆጣ መንግስት ኢትዮጵያዊ ነው?ከዜጎቹ የወጣና ለህዝቡ የቆመ እውነተኛ መንግስት ከዚህ የበለጠ የሚቆጣበት ጉዳይ ከወዴት ይመጣል? እውነተኛ መንግስት ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሳውዲ ካምፓኒዎችን በሰአታት ውስጥ ማባረር፣ኢምባሲውን ዘግቶ አምባሳደሩን ማሰናበትን የመሳሰሉ ውሳኔዎችን ያሳልፉ ነበር፡፡የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፣የድፕሎማሲ ግንኙነቴ ሊበላሽ ይችላል ብሎ እኛ ድምጻችን እንዳናሰማ ደበደበን፣አፈነን፡፡በግልጽ እንደሚታየው የጥቅም ትስስሩ ነው አፋቸውን ያዘጋቸው፣ይህች ጥቅማቸው እንዳትቋረጥ በዜጎች ህይዎት መደራደርን መርጠዋል፡፡
ስነ ልቦናቸው የተቃወሰ በመሆኑና ተራ ስስታሞች በመሆናቸው እንጂ ኢንቨስትመንትም ሆነ ዲፕሎማሲ ግብአትነታቸው ለሰው ልጅ ነው፣እንደ አህያ ሲያፈጋ ከርሞ ሬሳቸውን ለላከ መንግስት እንዴት ተመጣጣኝ ምላሽ ለመመለስ ይገዳል?እንዴት እንደ ኢትዮጵያ ያለች ታሪካዊትና ለአፍሪካ የነጻነትና የኩራት ተምሳሌት የሆነች ሀገርን እየመሩ እንዴት ትናንት የነዳጅ ዘይት ባቆማቸው እረኞች ስትዋረድ ዝም ይላሉ?!::
እንዴት!በዜጎች ህይወት የተደራደረው አገዛዝ ማለፉ አይቀርም፣ለዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ታሪክ ለመጥቀስ ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልግኝም፡፡የቅርብ የሰሜን አፍሪካ አምባገነኖች የከፋ ፍጻሜ አለና፡፡ኢትዮጵያውያን ፍቅርም ጸብም እናውቃለን፣ሳውዲወችም የፈጸሙትን ግፍ ማወራረዳቸው አይቀርም፡፡በዚህ ክፉ ጊዜ ስለስብአዊ መብት ቆመናል የሚሉ አለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው እውነተኝነታቸውን ለመመርመር ጥሩ እድል ይሰጠናል፡፡
መንግስት ቢኖረን ኖሮ ይሄ ሁሉ ውርደት ይፈጸምብን ነበር ብየ አላስብም፡፡በዚህ ሰአት ርዕሰ-መንግስት ብሆን ኖሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ድርጅት እንደመሆኑ፣ወደየትኛውም ሀገር የሚደረገውን ጉዞ አቋርጨ ዜጎቸን ማስወጣትን አስቀድም ነበር፡፡ያሄ ጥቂት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሊያመጣብን ቢችልም ከከፋው የዜጎች ስቃይ ጋር ግን በአንድ ሚዛን ላይ አይቀመጥም፡፡የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚባል ድርጅት አለ፡፡በዜጎቻችን ላይ ጎርፍና ድርቅ ሲመጣ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው? ይሄም ሰው ሰራሽ አደጋ ነው ሙሉ ሀይሉን ወደዚህ አዙሮ ሊንቀሳቀስ ይገባው ነበር፡፡
እርግጥ ነው ባቀድነው መሰረት ሰላማዊ ሰልፉ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡ጩኸቱ ግን ይቀጥላል……ባለን አቅም ሁሉ አፈናውንም፣ወከባውንም ተቋቁመን ለዜጎቻችንና ለኢትዮጵያዊነት እንታገላለን፡፡
አገዛዙ ይሄን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያፍን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንድ መልእክት አስተላልፏል፣ይህን መልእክት እንዲያስትላልፍ ማስገደዳችንም ለኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡የሳውዲ መንግስት ያሻውን ያደርግ ዘንድ የፈቀድኩት እኔ ነኝ፣በመሆኑም እሱን በመቃወም ግንኙነቴን አታበላሹ ብሎ እርምጃ በመውሰዱ ህዝቡ የነገሩ ቁልፍ የት እንዳለ፣የአጥቂወቹ በራስ መተማመን ምን ላይ እንደቆመ በጠራ ሁኔታ ለመመልከት እንዲችል ሆኗል፡፡
ይሄ ሁሉ ነገር እየተፈጸመ የተስተዋለ አንድ ነገር አለ፡፡የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታ እውነተኛ ማንነታቸው፣እውነተኛ በአገዛዙ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ያሳየን ክስተት ነው፡፡እንደሚታወቀው እሳቸው በኢህአዲግ እንጂ በኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጡ አይደሉም፡፡ኢህአዲግ የሚናገረው ከሌለ እርሳቸው የሚሉት አይኖርም፡፡እንደ አንድ ሀገርና ህዝብ መሪ ግን የመኮነንም ሆነ የማጽናናት ቃል ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
ባሉበት ቦታ ያስቀመጣቸው ህወሀት ነው፤ድርጅቱ ደግሞ ይሄን አቋም አልወሰደም፡፡ስለዚህ እንደሚቆጣቸው ስለሚያውቁ ዝምታን መረጡ፣ቸልታንም አስበለጡ፡፡በሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከዚህ በላይ ሽንፈት ያለ አይመስለኝም፡፡
(ይህ ጽሁፍ በፋክት መጽሄት ተስተናግዷል፣ነገር ግን መጽሄቱ ላልደረሳቸው ሰዎች ይደርስ ዘንድ እዚህ ለማስተናገድ ወደድኩ፡፡)

ጠጉረ ልውጦች ከአራት ኪሎ እንጅ ከሶማሊያ ወይንም ከኢራቅ ይመጡ ይሆን?

ጠጉረ ልውጡ ‹‹መንግስት››
………
ሰሞኑን በኢቲቪና በሬዲዮ፣ እንዲሁም ህዝቡን እየሰበሰቡ ‹‹ጠጉረ ልውጥ ሰው ካያችሁ ጠቁሙን!›› ሲሉ ሰንብተዋል፡፡
ጠጉረ ልውጥ ማለት አገሪቱን አሊያም ህዝቡን የማያውቅ ማለት አይደለም፡፡ እሱማ ፈልጎም ሆነ አፈላልጎ ወደዛው ደርሷል፡፡ ጠጉረ ልውጥ የሚገኝባት አገርም ሆነ ህዝብ በውል የማያውቁት በዕድ ማለት ነው፡፡
አሁን ወደ ጥቆማው እንግባ፡፡ በእርግጠኝነት ጠቁሙ የተባልነው የውጭ አገር ዜጎችን አይደለም፡፡ እንደዛ ከሆነማ ቻይናዎቹንም አናውቃቸውም፡፡ የሶማሊያ ስደተኞችንስ ስናሳስር ልንውል ነው እንዴ? እኔ እንደሚመስለኝ እነሱ ጠጉረ ልውጥ ብለው ያተኮሩት ከ90 ሚሊዮኑ ህዝብ መካከል ነው፡፡ ስለሆነም ማተኮር የፈለኩት እዚሁ አገር ውስጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ለተለያዩ ጉዳዮች በአገሪቱ ይዘዋወራሉ፡፡ በተለይ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን መነሃሪያ ነች፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች አዲስ አበባ ትንሽ መንደር አይደሉም፡፡ ሰውን እንዲሁ ‹‹ጠጉረ ልውጥ›› መሆን አለመሆን ማወቅ አይቻልም፡፡ ‹‹መንግስት›› የፈለገው ይህኛውን አይደለም፡፡ በተቃራኒው ከእሱና ከደጋፊዎቹ አንጻር ‹‹ፖለቲካ ልውጥ››፣ ‹‹ ብሄር ልውጥ››፣ ‹‹እምነት ልውጥ›› ያላቸውን ነው ጠቁሙን የሚለው፡፡ ሽብር እንዲህ በወሬ ሳይጦዝ ከ30ና 40 አመት በላይ የኖሩትን አርሶ አደሮች ‹‹ጠጉረ ልውጥ›› አድርገው አባርረዋቸዋል፡፡ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ከጥቂቶቹ በስተቀር ኢትዮጵያውያን እስር ቤት ውስጥ ሊታጎሩ ነው፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም አካባቢ ይምጣ፣ የትኛውንም ቋንቋ ይናገር፣ የትኛውንም ብሄር ይምረጥ፣ ……ጠጉሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ የከሳ፣ የጠቆረ፣ የተጎሳቆለ ከሆነ እሱ በድህነት የሚማቅቅ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የተናደደ፣ አንገቱን የደፋ፣ ፊቱ ላይ በደል የምታይበት አንዳንዴም ጨርቁን ጥሎ ያበደ ከሆነ እሱ የተገፋ፣ አገሩን የተቀማ የአገርህ ሰው ነው፡፡ እነዚህን ኢትዮጵያውያን የበደል፣ የስቃይ፣ የጭቆና ጠጉር አንድ ያደርጋቸዋል፡፡
‹‹ስለ እውነት›› እያወራ የሚያፍረው፣ ስለ ‹‹ማንነቱ›› እየተናገረ የሚደነግጠው፣ ስለ ነጻነት እየተሰበከና እየሰበከ የሚገዛው፣ ስለ አንድነት እያወራ የሚከፋፈለው እሱ ዘመኑ የፈጠረው፣ ስርዓት ያበላሸው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ይህኛው በአንድ በኩል በጭቆናው ከጭቁኑ ያልተላቀቀ በሌላ በኩል ከገዥው ጋር በኪሱ የተገናኘ የዘመኑ ሆድ አደር ካድሬ ነው፡፡ አገሩም፣ ህዝቡም፣ ስርዓቱም፣ እራሱም ላይ እምነት እንደሌለው ግንባሩም፣ አይኑም፣ ድምጹም ላይ ትለይበታለህ፡፡ ይህ አንድ ደረጃ ከፍ ሲል ግን ጠጉሩን ይለውጣል፡፡
እንገቷን በደፋችው አገር በማን አለብኝነት ደረቱን የሚነፋው፣ ስታለቅስ የሚደሰተው፣ ስታነባ የማይጨንቀው፣ ስትራብ የሚያበሰናው፣ ኩርምት ባለችበት የሚቦርቀው፣ እንቅልፍ ባጣችበት ለሽ ብሎ የሚተኛው ይህ ኢትዮጵያ የማትለየው፣ ዜጎቿ ጋር ተገናኝቶ የማያውቅ ጠጉረ ልውጥ ነው፡፡ በቆረቆዘችበት የለማ፣ በጨለመችበት የበራው፣ በተጠማችበት የረካውና የሰከረው በምስኪኗ ኢትዮጵያና ዜጎቿ ዘንድ የማይታወቅ ባዕዳና ጠጉረ ልውጥ ነው፡፡
እነዚህ ጠጉረ ልውጦች ከአራት ኪሎ እንጅ ከሶማሊያ ወይንም ከኢራቅ አይመጡም፡፡ እንደ ሶማሊያውያኑ አሊያም ሌሎች መንገድ ላይም አናገኛቸውም፡፡ ከማያውቃቸው ህዝብ ለመራቅ መንገድ ዘግተው፣ ሰራዊት አሰልፈው የሚውሉት እነሱ ‹‹ጠጉረ ልውጦች›› ናቸው፡፡
አዎ! ሁሌም ባይሆን በአብዛኛው ጠጉረ ልውጥ ይሰርቃል፣ ያሸብራል፣ ይገድላል፡፡ የእኛዎቹ ጠጉረ ልውጦችም ግን ተግባራቸው ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በእርግጥ ስለ እነሱ መጠቆም መጠቋቆም አያስፈልግም ‹‹ቤተ መንግስት›› የሚሉት አገር ውስጥ መሽገዋል፡፡ ‹‹መንግስት›› የሚሉት ቡድን አቋቁመው ኢትዮጵያውያን የማያውቁት ጸጉር አከናንበውታል፡፡ ምን አልባትም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ጠጉረ ልውጥ በግል ሳይሆን በቡድን ያደማት፣ ያሸበራት፣ የዘረፋት አገር መሆኗ ነው፡፡ Getachew Shiferaw

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ሰራዊት በጋራ ወታደራዊ ጥቃት ፈፀሙ

November 26, 2013

የጋራ ትግል አስፈላጊ መሆኑን በፅኑ የሚያምኑት የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር /ኢሕአግ/

Ethiopian freedom fighters
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ /ጋሕነን/ በሕዳር 13/2006 ዓ.ም በሁመራ ሉግዲ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1፡00 ለሶስት ሰዓት ያህል በወሰደው ውጊያ የወያኔው 24ኛ ክፍለ ጦር ድባቅ ተመቷል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት በ24ኛው ክፈለ/ ጦር ላይ በተመሳሳይ ሥፍራ  ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱ ይታወሳል።
በሕዳር 13/2006 ዓ.ም የኢሕአግና የጋህነን ሰራዊት በወሰዱት ድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃት 66 /ስልሳ ስድስት/ ገድለው 113 /አንድ መቶ አስራ ሶስት/ በማቁሰል እንዲሁም ቁጥራቸው የበዛ የጦር መሳሪያዎችን ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ማርከዋል።
ሁለቱ ድርጅቶች በጋራ በተለያየ የትግል መስክ ሲተጋገዙና ሲተባበሩ ቆይተዋል የግንኙነታቸውን እድገትና ለውጥ የሚያሳይ ወታደራዊ ጥቃትም ፈፅመዋል።
ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመኘውና የሚፈልገው የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ስምምነትና አንድነት መገለጫ ሊሆን የሚችል አኩሪ ጥቃት መሆኑ ይታመንበታል ። በጥቃቱ የተካፈሉ የሁለቱ ድርጅቶች ታጋዮች እንዳብራሩት ዛሬ በጋራ የጀመርነው ወታደራዊ ጥቃት በዚሁ የሚያበቃ ሳይሆን የጋራ ዓላማና ራዕይ እስካለን ድረስ ወደኋላ የማይቀለበስ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህም አክለው የዚህ ወታደራዊ ዘመቻ ዓላማ አገር እንደሌለው ሁሉ በሰው አገር ፍዳውን እያየና እየተሰቃየ እንዲሁም ለሞት እየተዳረገ የሚገኙውን በሳውዲ አርቢያ ለተፈፀመው በደል ለመበቀልና ሕዝባዊ ወገንተኝነታችንን ለማሳየት ታስቦ የተወሰደ ወገናዊ እርምጃ ነው በማለት አብራርተዋል።
በውጊያው ከሞት ተርፎ ለከባድ ቁስልና የአካል ጉዳት የተዳረገው የወያኔው ቅጥረኛ የ24ኛ ክፈለ ጦር አባላትን ከሁመራ አንስቶ እስከ ትግራይ የሕክምና ማዕከሎች ማጋጋዝ ዋነኛ ተግባሩ ሆኗል።
ይህንን የጀግና ጥቃትና ድል የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ሰራዊቱን እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ በመቀበልና ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ አጋርነቱን ያስመሰከረ ሲሆን የተጀመረው ወታደራዊ ጥቃት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንዲደገም ያላቸውን ልባዊ ምኞት ገልፀው በንፁሃን ላይ ያለ አግባብ ሲወሰድ የነበረው የቅጥረኞች እርምጃ አንጀቱ ላረረው ሕዝብ እምባ ያበሰ እንደሆነም ተናግረዋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር/ ኢሕአግ/ እና የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ /ጋህነን/ ወያኔ ለ22 ዓመት ያህል አገሪቷን ሲበዘብዝና ሕዝቡ የዲሞክራሲያዊ መብቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን በሃይል የመግዛቱ ሂደት እንዲያከትም የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውን አስታውቀዋል።

onsdag 13. november 2013

Photos of TPLF’s failed Assassin ( ያልተሳካለት የወያኔ የግድያ ቅጥረኛ)

የወያኔ የግድያ ቅጥረኛ ሙሉቀን መስፍን እና ታናሽ ወንድሙ ገብሬ የግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ አቶ አናዳርጋቸው ጽጌን፣ የዴምህት ሊቀ መንበር አቶ ሞላ አስገዶምን፣ እንዲሁም በግንቦት 7 ህዝባዊ ኃይል የሰራዊት ምርቃት ሰነስርአት ላይ የሚገኙ የኤርትራ ባለስልጣናትን ለመግደል ወያኔ በወንድሙ በኩል የላከለትን ሸጉጥና ፈንጅ ሲቀበል በግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይሉ እጅ ከፍንጅ ከተያዙ በኋላ የተነሱት ፎቶዎች።
ሙሉቀን መስፍን ከወያኔ የትላከለትን ሽጉጥ እያየ።
Image
ሙሉቀን መስፍን አና ወያኔ የላከውን መሳሪያ ይዞ የመጣው ታናሽ ወንድሙ ገብሬ።
Image
ሙሉቀን መስፍን ከወያኔ የተላከለትን ፈንጅ እያየ።
ትግሉ መሯል፤ እኛም ዝግጁዎች ነን :: #Ethiopia #EPRDF #GINBOT7
በንቅናቄዓችን ፀሐፊ እና በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አመራር አባላት ላይ የተቃጣው ረዥም ጊዜ የወሰደ የግድያ ሴራ መክሸፉ አስደስቶናል። ይህ ሴራ የወያኔ የስለላና የግድያ ኃላፊዎች በሆኑት ጌታቸው አሰፋ እና ጸጋየ በርሄ የቅርብ ክትትል የተመራ፤ የአሻንጉሊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ እውቅናና ይሁንታ የተሰጠው፤ ወያኔ ከፍ ያለ ተስፋ የጣለበት ሴራ ነበር።
“ወያኔ-ኦ-ሚሊኒየም” የተሰኘው ይህ በወያኔ የመጨረሻ ከፍተኛው አመራር የተመራው ሴራ ስለወያኔ ውስጣዊ አደረጃጀት ጠቃሚ መረጃዎችን ሰጥቶናል። ከዚህም በተጨማሪ የወያኔ ሹማምንት ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ንቀት፤ ከአመት በኋላ ስለሚደረገው ምርጫ ውጤት፤ ለሰላዮቻቸው ስለሚሰጡት ጉርሻ መጠን፤ እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ተስፋ ከጣሉበት ቅጥረኛ ነብሰ ገዳያቸው ጋር ካደረጉት የስልክ ንግግሮች ማድመጥ ይቻላል። ይህ ለበርካታ ጥናቶች በግብዓትነት ሊውል የሚችለውን በድምሩ ከስምንት ሰዓታት በላይ የሚፈጀው የስልክ ንግግር ቅጂ በሕዝባዊ ኃይሉ የመረጃ ክፍል አማካይነት ለሕዝብ በኢንተርኔት በነፃ ተለቋል። በአጋጣሚውም የወያኔ ገበና ተጋልጧል።
በአንፃሩ ደግሞ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል የተደራጀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢሆንም ምን ያህል ወያኔን እንቅልፍ እንደነሳ ተጨባጭ ማስረጃ ሆኗል። ይህ ለነፃነት ታጋዮች ከፍተኛ የስነልቦና ብርታት የሚሰጥ ነገር ሆኖ ተገኝቷል።
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል የተቃጣበትን ጥቃት ከማክሸፍ በተጨማሪ የወያኔን ገበና ማጋለጥ በመቻሉ የመጀመሪያው ሁነኛ ድል ተቀዳጅቷል።
ግንቦት 7 : የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ወያኔ ኦ ሚሊኒየም” አፕሬሽንን ላከሸፉ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አመራርና አባላት ያለውን አድናቆት ይገልፃል። ለወደፊቱም ተመሳሳይ ጥቃቶች ሊደርሱ የሚችሉ መሆኑን በመገንዘብ የመከላከል ብሎም የማጥቃት ኃይሉን እንዲያጠናክር ይመክራል።
የንቅናቀዓችን እና የሕዝባዊ ኃይሉ አመራርና አባላት ለመስዋዕትነት የተዘጋጁ ናቸው። “ወያኔ ኦ ሚሊኒየም” ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ትግላችን ይገታ ነበር ማለት አይደለም። ትግላችን መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን እናውቃለን። ጓዶች ሲወድቁ ሌሎች ሺዎች አርማቸውን አንስተው ትግሉን ይቀጥላሉ።
ትግሉ የሚጠይቀንን መስዋትነት ከፍለን ወያኔን ከሥልጣን አስወግደን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሆነባት ኢትዮጵያ እንደምትኖረን እርግጠኞች ነኝ።
ትግሉ መሯል፤ እኛም ዝግጁዎች ነን።
ድል ለግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

mandag 11. november 2013

በሳዑዲ አረብያ የመከራ ማጥ ውስጥ ላሉት ወገኖቻችን ሲባል ፈጥነን እንነሳ!

November 11, 2013
ዳኛቸው ቢያድግልኝ
እንደ ሰው አንድ የሚያደርገን ባሕርይ፣ እንደ ኢትዮጵያዊነትም ሁላችንንም የሚመለከተንና የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ልዩነት የማይነጣጥለው በደል በሳዑዲ አረብያ ግዛት እየተፈጸመ ነው። የጥቃት ዒላማዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የጥቃቱ ልክ የለሽነትና አሰቃቂነት ደግሞ ይበልጥ የጎላው በሴት እህቶቻችን ላይ ነው። ይህ ዛሬ በሳዑዲ አረብያ የሚደረገው ጥቃትን ማስቆምና ቁጣችን መቆምያ እንደማይኖረው ማሳየት ለነርሱ ብቻ ሳይሆን ለራሳችን ደህንነትም ጭምር የምናደርገው ነው። ምክንያቱም ነገ ተመሳሳይ ጥቃትና በደል በመላው አለም ይስፋፋል። በአፍሪካ ሀገሮች የተበተኑ ኢትዮጵያን ከሶማሌና ኤርትራ ከሚሰደዱት በተለየ ይዘረፋሉ፣ ይደፈራሉ ይዋረዳሉ። እንደ አገር ልጅ አብረው እንዳይቆሙ በዘር በሀይማኖትና በፖለቲካ አቋም ምክንየት የተበተኑ ናቸው። ለሰላሳና አርባ አመት አምባገነኖች ያደረጉት ጭፈጨፋና በደል ፍርሃትን ሰማይ ጥግ አውጥቶታል። እናም ኢትዮጵያዊ በየተበተነበት ሁሉ ተኛ ሲሉት የሚተኛ አውልቅ ሲሉት እርቃኑን የሚቆም ፈሪ እንዲሆን ተደርጓል። ሲቸግረው የሚጮኸውን ያህል ሲመቸው ለወገን የሚደርሰው ጥቂቱ ነው። ይህ ሊቀጥል አይገባም!Protest at Saudi Arabia Mission to United Nations!
ቀደም ባለው ጊዜ አንድ ኢትዮጵያዊ ጥቃት ቢደርስበት ባገኘው መሳርያ ዘነጣጥሎም ቢሆን ይገድል ስለነበር ማንም አይደፍረውም ነበር። በዘመነ ኮሎኒያሊዝም ኢትዮጵያውያን በሄዱበት ሁሉ አንገት የማይደፉና ክብራቸውን የማያስነኩ ነበሩ። ዛሬ ጠቁመው የሚያስይዙ፣ ወገናቸውን የሚያሻሽጡና የሚሰልሉት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የዚህ ጽሁፍ መነሻም ሆነ መድረሻው የድሮውን አሁን እየሆነ ካለው ጋር ማወዳደር አይደለም። ለዚህ የሚሆን የቅንጦት ጊዜም የለንም። ዓላማው አሁን እየደረሰብን ያለውን በደል በቁርጠኛነት አንታገለው ነው። ይህ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ከዳር እስከዳር ማስነሳት ካልቻለና ቁጣቸውንም ለመላው አለም ማሳየት ካልቻለ እውነትም አገራችን እያበቃላት ነው ማለት ይቻላል።
የዱር አውሬ እንኳን ከዚህ የተሻለ ክብር አለው። እነዚህ አጅግ ሁዋላ ቀር የሆኑ አረመኔዎች ከእንስሳ እንኳን አንሰው አንዲት በፍርሃት ነብሷን የሳተችን ሴት አስር ሆነው የሚደፍሩትን እያየን የተደፈሩት ህጋዊ ናቸው ህገወጥ የሚል የሕግ አንቀጽ መረጣ ውስጥ ልንገባስ እንዴት ይቻለናል? በመላው አለም ያለ የሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ ሊደረግና የሳዑዲ ወሮበሎች በወጣት ሴቶች ላይ እያደረሱ ያለው ግፍ በመረጃም ተደገፎ በበራሪ ወረቀትም ተዘጋጅቶ ለአለም ሕዝብ ሊበተን ይገባዋል። ተፈጥሮ ዘይትን ስትቸራቸው አእምሮ ግን እንደነፈገቻቸው ከዚህ በላይ መረጃስ ከየት ይመጣል?
እንደ ትውስታ ከወሰድነው በኬንያ ያሉ ስደተኞች ላይ በደል ይደርስ በነበረበት ወቅት ያ በጨካኝነቱ የሚታወቀው መንግሥሰቱ ሀይለማርያም አንኳን “ኢትዮጵያውያኑ የተሰደዱት የምናራምደውን ፖለቲካ እንጂ ሀገራቸውን ጠልተው አይደለም…” በሚል ኬንያን ማስጠንቀቁን መስማቴ ትዝ ይለኛል። በየወሩ 40 ሺህ ሴቶችን እንልካለን እያለ እንደ እንቁላል በየአረብ ቤቱ ሲያከፋፍል የነበረው መንግስት ዛሬ ዜጎቹ እንዳይሆን መጫወቻ ሲሆኑ ዝም ብሎ መመልከቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው። ኢትዮጵያውያኑ ምናልባትም ኤምባሲውን ራሱን መቆጣጠር የሚገባቸው እስኪመስል ያስቆጣል።
በኢትዮጵያዊነት ላይ የተነጣጠረን ክፋት እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ ካላስቆምነው በሳዑዲ የተጀመረው መረን የጥላቻ ሰደድ ሊቀጣጥል የሚችልና የየሀገሩ የፖለቲካ ኪሳራ ማስተንፈሻ የሚሆነው አገር አጥቶ የተሰደደው ኢትዮጵያዊው ላይ ሁሉ ይሆናል። ይህንን በአስቸኳይ ለመቃወም ያሉ የትግል መንገዶች ሁሉ ክፍት ሊሆኑ ይገባል። እኔ አዘጋጀሁ እኔ ጠራሁ የሚል ደካማ የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ መንቀሳቀስ ሳይሆን ለሰብዓዊ ክብርና የመከራ ማጥ ውስጥ ሆነው የወገን ያለህ ለሚሉት እህት ወንድሞቻችን የድረሱልን ጥሪ ምላሽ እንስጥ። በጣም የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ለስራ የሚሄዱት ወጣቶች የትምህርት ደረጃቸው አነስተኛ የሆነና በድህነት ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የሆነው ይሁን ብለው ከቤታቸው የወጡ ናቸው። አንዳንዶቹም ግሩም እድል አንደሚገጥማቸው በደላላዎች እየተነገራቸው ከቤት ወጥተው የቀሩ ናቸው። ለኒህ አጋር መሆን ለሀገር እንኳን ደንታ ባይኖረን ለነብስ የሚበጅ ስራ ነው። የኢትዮጵያ ኮሙኒቲዎች፣ በኢትዮጵያ ስም የተቋቋሙ የሀይማኖት ማዕከላት፣ ሲቪክ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ለዚህ ዓላማ ቢቻል አደራጆች ካልተቻለም ዋንኛ ተሳታፊዎች ሊሆኑ ይገባል። ይህ በደል እጅ ለእጅ ሊያስተሳስረንና አንድ ላይ እንድንቆም ሊያደርገን የሚችል የጋራ ጉዳይ ነው። ዛሬ ነገ ሳንል በተደራጀና አለም አቀፍ ትኩረት ሊኖረው በሚያስችል አቅሙ እንነሳ ለወገንም አንድረስ።የመከራ ቀናችንን ለማሳጠር እንደ ሕዝብም ከአንገታችን ቀና እንድንል በያለንበት እንትጋ!

lørdag 9. november 2013

የግንቦት 7 መሪዎችን ለመግደል የተጠነሰሰው ሴራ ከሸፈ

andargachew tsige (dc)
(ኢሳት) በኢትዮጵያ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ሃለፊ በአቶ ጌታቸው አሰፋ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ በአቶ ጸጋየ በርሄ ቁጥጥር የተመራና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌና በግንቦት7 ህዝባዊ ሀይል መሪዎች ላይ የተቀነባበረው የግድያ ሙከራ ከሸፈ። ከግንቦት7 ህዝባዊ ሀይል  ከኤርትራ ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንዳመለከተው ለግድያ የተላከው ሙሉቀን መስፍን የተባለው ግለሰብ፣ በትናንትናው እለት በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ በየደረጃው ከሚገኙ የደህንነት ሀላፊዎች ጋር በስልክ ሲያደርግ የነበረው የመልእክት ልውውጥም  በህዝባዊ ሀይሉ የመረጃ ክፍል ሲቀዳ ቆይቷል። “ ወያኔ-ኦ-ሚሊኒየም” በሚል የተመራው የግድያ ዘመቻ -በነገው እለት ጥቅምት 30/2006 ዓም ሊካሄድ ታቅዶ እንደነበር የድምጽ መረጃው ያመለክታል። የግንቦት 7 ህዝባዊ ሀይል ሰራዊት የምረቃ በአል በነገው እለት የሚካሄድ መሆኑን መነሻ በማድረግ በእለቱ በግንቦት7 ህዝባዊ ሀይል መሪዎችንና የኤርትራ ባለስልጣናትን ለመግደል የታቀደው ዘመቻ ከመነሻው ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ፣ ፍጻሜው ዋዜማ ላይ ሲደርስ ሙሉቀን መስፍን የተባለውን ለግድያ የተላከውን ግለሰብ ህዝባዊ ሀይሉ በቁጥጥር ስር በማድረግ ወያኔ-ኦ-ሚሊኒየም የተባለው ኦፕሬሽን መክሸፉን ይፋ አድርጓል።

Leave a comment

Your email address will not be published.

torsdag 7. november 2013

ኢትዮጵያ፣ የቦምብ ፍንዳታ እና ማስጠንቀቂያው

ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ጥቃቶች ሊደርሱ ይችላሉ በሚል የጸጥታ ኃይሎች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ በታዘዙበት በኣሁኑ ወቅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኣንድ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በፈነዳ ቦምብ አራት ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ።
 Die Gambia Street und Churchill Avenue führen schnurgerade auf das Rathaus der äthiopischen Hauptstadt Addis Abeba. Aufnahme vom Januar 2007. Foto: Peter Smolka +++(c) dpa - Report+++
ከሶስት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አዲስ ኣበባ ላይ ከናይጄሪያው ቡድን ጋር በሚጫወትበት ዕለት ጥቃት ለማድረስ ሲዘጋጁ ነበር የተባሉ ሁለት የሶማሊያ ኣጥፍቶ ጠፊዎች በራሳቸው ቦምብ መሞታቸው ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡም ጥንቃቄ እንዲያደርግ መንግስት እያሳሰበ ሲሆን የጥንቃቄ ማስጠንቀቂያውን ተከትሎም በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ቁጥጥሩ መጠናከሩም ተሰምቷል።
የዛሬ ሶስት ሳምንታት ገደማ መሆኑ ነው የኢትዮጵያ የእግር ኩዋስ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አዲስ ኣበባ ላይ ከናይጄሪያው ብ/ቡድን ጋር በሚጫወትበት ዕለት ጥቃት ለማድረስ ሲሞክሩ ነበር የተባሉ ሁለት የሶማሊያ ኣጥፍቶ ጠፊዎች የራሳቸው ቦምብ ፈንድቶባቸው ከቤታቸው ሳይወጡ መሞታቸውን የኢትዮጵያ ፖሊስ ኣስታውቆ ነበር። ይኽንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ የደህንነትና ጸጥታ ባለስልጣናት ኣልሸባብ በአዲስ ኣበባ እና በተለያዩ የኣገሪቱ አካባቢዎች ጥቃት ለማድረስ እየተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ የፖሊስ እና ጸጥታ ኃይሎች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ማዘዛቸውን ገልጿል።
 Nigeria's attacker Victor Anichebe (C) struggles for possession of ball with Ethiopian skipper Samson Gebreegziabher (R) and Abebaw Bune during the African Cup of Nations qualifying match between the two countries in Abuja Sunday, March 27, 2011. Nigeria defeated Ethiopia 4 - 0. AFP PHOTO/PIUS UTOMI EKPEI (Photo credit should read PIUS UTOMI EKPEI/AFP/Getty Images)
ባለፈው ማክሰኞ ደግሞ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰኞ ገበያ በተባለ ስፍራ በህዝብ ማማላለሻ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ላይ የፈነዳ ቦምብ አራት ሰዎችን መግደሉ ተዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግስት ከኣልሸባብ በተጨማሪም በኤርትራ መንግስት ይደገፋሉ የሚላቸውን ሌሎች በኣገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎችን ከሽብር ጥቃት ጋር ኣያይዞ ሲወነጅል መቆየቱም ኣይዘነጋም።
የፊታችን ህዳር 29 ቀን በጅጅጋ ከተማ ይከበራል ተብሎ ከሚጠበቀው ዓመታዊ የብ/ብ/ ቀን ጋር በተያያዘ ዓማጺው የኦጋዴን ነጻ ኣውጪ ግንባር ጥቃት ሊያደርስ ይችላል በሚል በጅጅጋ ከተማ እና በአካባቢው የጸጥታ ቁጥጥሩ እጅግ መጠናከሩ ሲታወቅ በጅጅጋ ጎዳናዎች ላይ በየ 50 ሜትሩ ሰዎች በፍተሻ እንደሚዋከቡና ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ ደግሞ በጅጅጋ ከተማ የቤት ለቤት ፍተሻም እየተካሄደ መሆኑ ተሰምቷል።
በተቀሩት የኣገሪቱ ኣካባቢዎችም ህዝቡ የጸጉረ ልውጥ ሰዎች እንቅስቃሴን እየተከታተለ ለመንግስት እንዲጠቁም እና በተለይ የሆቴሎች አልጋ ኣከራዮችና በየመንደሩ ያሉ ቤት ኣከራዮችም ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ የተለየ ነገር ሲያጋጥም ወዲያውኑ ለመንግስት እንዲያሳውቁ መንግስት ኣሳስቧል።
ስለዚሁ ጉዳይ እንዲያብራሩልን የኢትዮጵያው የኮሞኒኬሺን ጉዳዮች ሚኒስትር ዲዔታ አቶ ሽመልስ ከማል ዘንድ ስልክ ደውለን ነበር። ፈቃደኛ ግን ኣልነበሩም። የኮሚኒኬሺን ጉዳዮች ሞኒስትሩ አቶ ሪድዋን ሁሴን ግን ለመንግስታዊው የኢትዮጵያ ቴሌቪዢን እንደገለጹት መንግስታቸው የሽብር ጥቃት መታቀዱን መረጃ ማግኘቱን ኣውስተው ህዝቡ ጥንቃቄ በማድረግ እና ለመንግስት ጥቆማ በማቅረብ እንዲተባበራቸው ጥሪ ኣድርጘል።ሆኖም ግን ከጥንቃቄ ያለፈ ህብረተሰቡ ተሸብሮ የዕለት ተለት እንቅስቃሴውን እንዲያቆም የሚያስገድድ ነገር ኣለመኖሩንም አቶ ርድዋን ኣስረድቷል።
በኣልሸባብ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ፍጥጫ መኖሩ ኣይካድም የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ጀዋር መሃመድ የኣሁኑ የኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያና መግለጫ አዲስ ነገር የለውም ይላሉ። እንደ አቶ ጀዋር ይህ የኢትዮጵያ መንግስት ተቀናቃኞቹን ለማሰር እና የፖለቲካ ትርፍ ለመሸመት የሚጠቀምበት የተለመደ የፕሮፓጋንዳ ስልት ነው።
A young Alshabab soldier prepares to join fighting between Alshabab and Ethiopian forces near the presidential palace in Mogadishu, Somalia on 12, January 2009. Islamic fighters launched heavy attacks on two Ethiopian bases on the eve of Ethiopian expected withdrawal from Somalia. EPA/BADRI MEDIA +++(c) dpa - Report+++
በዩኤስ አሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ጥናት በማድረግ ላይ የሚገኙት አቲ ጀዋር መሐመድ ከወዲሁ ማስተካከያ ካልተበጀለት የዚህ ኣይነቱ ኣካሄድ አደጋም ኣለው ባይ ናቸው። ምክኒያቱም አቶ ጀዋር እንደሚሉት ተጨባጭ ነገር ሳይኖር ጥቃት ሊፈጸም ነው እየተባለ ህዝቡ የተለመደ የመንግስት ፕሮፓጋንዳ ነው እያለ በተዘናጋበት ኣጋጣሚ እውነተኛው የሽብር ጥቃት በተቃጣ ጊዜ መንግስት ከጎኑ የሚቆምለት ህዝብ ያጣል። አደጋውም የከፋ ይሆናል።
ባሳለፍነው ወር የአልሸባብ ታጣቂዎች በኬኒያ ናይሮቢ በሚገኘው የዌስት ጌት የበያ ማዕከል ላይ በጣሉት ጥቃት 67 ንጹኃን ዜጎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን እ ኣ ዘ ኣ በ 2010 በጎረቤት ኡጋንዳ የዓለም ዋንጫ ጫወታን ለመከታተል በታደሙ ዜጎች ላይ በደረሰ የቢምብ ፍንዳታም እንዲሁ 74 ያህል ሰዎች መሞታቸው ኣይዘነጋም።

የመፀሃፍ ግምገማ: “ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” – ደራሲ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ


- ግምገማ በጥላሁን አፈሣ
(PDFብርሃኑን ከ ፳፭ አመታት ላላነሰ ግዜ በቅርብ የማውቀው ጓደኛየ ነው። ለሥራ ትጋቱ፣ ለቆመለት አላማ ፅናቱ፣ የማይረግበው የይቻላል መንፈሱ፣ ካወቅኩት ግዜ ጀምሮ ያልተለዩት መላያ ባህርዮቹ ናቸው። በእነዚህ አምታት ውስጥ፣ የአገሩን ጉዳይ በሚመለከት የተሳተፈባቸውንና ያከናወናቸውን መጠነ ሰፊ ተግባሮች መዘርዘር ይህ ቦታው ባይሆንም፣ በዚህ አጋጣሚ፤ እንደው በጥቅሉ ብርታቱን የሰጠው ግለሰብ መሆኑን በጨረፍታ ገልጬ ማለፍ እወዳለሁ። ሌላው ቢቀር ፣ የራሱን የግል ነፃነት ተነፍጎ፣ የነፃነት ጭላንጭል በማይታይበት በቃሊቲ ወህኑ ቤት ነዋሪ በነበረባቸው በነዛ ሁለት ፈታኝ ዓመታት ውስጥ፣ “የነፃነት ጎህ ሲቀድ” በሚል ርዕስ በቁርጥራጭ ወረቀቶች ላይ ከትቦ ገና ከቃሊቲ ሳይሰናበት ለህትመት አብቅቶ ያቋደሰንን ከ ፮፻ ገፆች በላይ ያካተተውን መጸሃፉን በማንበብ ብቻ፣ በእርግጥም ብርታቱን የሰጠው ሰው መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። በተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ላይ ሆኖ በፃፋት በዛች ድንቅና ተስፋ ጫሪ መጽሃፉ መግቢያ ላይ፣ “ከአሜሪካ ኑሮዬ የተገነዘብኩት የነፃነት እና የኢኮኖሚ ብልፅግናን ጠንካራ ግንኙነት ነበር”፤ አገር ቤት ከተመለሰኩ በሗላ በጻፍኳቸው የተለያዩ ጽሑፎቼም “የዴሞክራሲ እና የኢኮኖሚ እድገት ትስስርን በሚመለከት በአጠቃላይና በተለይ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ብልፅግና የዜጎች ነፃነትና ዴሚክራሲያዊ ስርዐት አስፈላጊነትን መክሪአለሁ” በማልት በጽኑ የሚያምንበትን መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ አስምሮበት አልፎ ነበር።
“ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” ብሎ በሰየማት በዚች ሁለተኛው መጸሃፉ ውስጥም እንዲሁ፣ “የአሜሪካን የፖለቲካ ስርዓት በገቢር በማየት የስርዓቱ የማዕዘን ድንጋዮች የህዝቡ የተለየ ጥሩነት፣ የፖለቲከኞቻቸው ልዩ ችሎታና ብስለት ሳይሆን ስርዓቱን ተሸክመው በያዙት ተቋማት ላይ መሆኑን አምኛለሁ። የተቋማት ጥንካሬ፣ የተቋማት ነፃነት፣ ከግለሰቦች ይልቅ ለተቋማት የሚሰጠው ክብርና ታማኝነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ለማድረግ እጅግ አስፈላጊው መሳሪያ መሆኑን በፊት ከማምነውም የበለጠ ያለምንም ጥርጣሪ እንድረዳው አድርጎኛል” በማለት ገልጾልናል። ይህን መሰረታዊ እምነቱንም ነው በዚች መጸሃፉ ውስጥ በሰፊው በምክንያታዊ ትንተና የተደገፈ ሃተታ የሰጠበት።
ብርሃኑ ይህችን መጸሃፍ ለህትመት ከመብቃቷ በፊት፣ የመጀመሪያውን ንድፍ ልኮልኝ አስተያየቴን እንድሰጠው ጋበዞኝ ስለነበር፣ በኔ አስተያተት፣ መጸሃፏ ወቅታዊና መሰረታዊ በሆኑ የአገራችን ችግሮች ላይ ያነጣጣረችና የተለመችውን ኢላማ በብቃት የመታች መሆኑን ጠቁሜው በአስቸኳይ ለህትመት እንዲያበቃት ጎትጉቸው ነብር። ለህትመት ስትበቃም፣ በሽፋኗ ጀርባ ላይ ባጭሩ ከሰፈረው ስለመጸሃፏ ያለኝ አጠቃላይ አስተያየት ውስጥ፣ “የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ማንም ሰው ይህን መጽሃፍ በክፍት አዕምሮ ማንበብ ብቻ ሳይሆን አንብቦም ከሌሎች ዜጎች ጋር የምር ውይይት ማድረግ ይጠበቅበታል” የሚል ይገኝበታል። በዚች መጻጽፍም ፣ መጽሃፏ ካዘለቻቸው በዛ ያሉ ቁምነገሮች ውስጥ መሰረታዊ ናቸው ብየ ባመንኩባቸው ሁለት ነጥቦች ላይ አተኩሬ አስተያየቴን በማቅረብ አንባቢን ለውይይት እጋብዛለሁ። ወደ እነዚህ ሁለት ነጥቦች ይዤያችሁ ከመጓዜ በፊት ግን፣ የመጸሃፏን አጠቃላይ ይዘት አንባቢው እንዲረዳ፣ በአምስቱም የመጸሃፏ ምዕራፎች ሥር ደጋግመው ተንጸባርዋል የምላቸውን መሰረታዊ ሃሳቦች ባጭሩ እቃኛለሁ።
ብርሃኑ፣ የዚች መጽሃፍ አላማ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ዴሚክራሲያዊ ካልሆኑ ስርዓቶች በሁሉም መስፈርት የተሻለ እንደሆነ ማስረዳት መሆኑን በዚች መጸሃፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ገልጾልናል። ይህንንም አወንታ፤ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታዎች ለናሙና እያቀረበና ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከአካባቢ ጥበቃ ችግሮች ጋር እያዛመደ፣ ለአንባቢ በማይሰለች ብዕር፣ በሰፊው፣ በብቃትና በጥራት በመተንተን እንድንረዳ አድርጎናል። በዚህም ጉዞው፣ በመጀመሪያ የአምባገነን ሥርዓቶች መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው፣ ለአገር ልማትና ግንባታ የዴሞክራሲ መኖር ወሳኝ አለመሆኑን ለማሳየት የሚጠቀሙበትን መከራከሪያ ሃሳቦች በማቅረብ፣ የነዚህን ሃሳቦች ብኩንነት በወጉ እያገላበጠና እያደቀቀ በአምስቱም የመጸሃፉ ምዕራፎች ሥር በረድፍ በረድፉ አካቶ አመርቂ ትንታኔ አቅርቦበታል።
ብርሃኑ በዚች መጽሃፍ ላይ ያተኮረው፣ ለኢትዮጵያችን የሚያስፈልገው የትኛው አይነት የኢኮኖሚ ስርዓት ነው የሚለው ላይ ሳይሆን፣ የሚሻለውን ለመምረጥ የሚኬድበት ሂደት ላይ ነው። እንደብርሃኑ እምነት፣ ይህ “ደግሞ ባብዛኛው የሚመለከተው የፖለቲካ ሥርዓቱን” ስለሆነ፣ “በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ላይ የሚደረግ ትርጉም ያለው ውይይት በመጀመሪያ መመለስ ያለበት ይህንን ጥያቄ ነው።” ስለዚህም ይመስለኛል፣ የመጀመሪዎቹን ከመቶ ገጾች በላይ ያካተቱ ሁለት ምዕራፎች በፖለቲካው ጥያቁዎችና ችግሮች ላይ እንዲያጠነጥኑ ያደረገው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሥር፣ አንድን የፖለቲካ ስርዓት ጥሩ የሚያሰኙትን ንጥረ ነገሮችና ከነዚህ ውስጥ የአገራችን የፖለቲካ ስርዓት አላሟላቸውም የሚላቸውን መስፈርቶች በሰፊው አትቶባቸዋል። እነዚህን የጥሩ ፓለቲካ ስርዓት አመልካች የሚላቸውን አምስት መሰረታዊ መስፈርቶች ለእያንዳንዳቸው ንዑስ ክፍል በመስጠት ሰፋ ያለ ትንታኔ አቅርቦማቸዋል። ይህን ምዕራፍ ሲያጠቃልልም፣ “ማህበረሰቡ ከጥቂት ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ባሻገር ለሃገሩና ለፖለቲካ ስርዓቱ ታማኝ የሆኑና የባለቤትነት ስሜት የሚሰማቸው ዜጎችን በቀጣይነት ማፍራት የሚችለው” ሥርዓቱ እነዚህን ጥሩ የሚያሰኙትን መሰረታዊ መሥፈርቶች ሲያሟላ ብቻ መሆኑን አስምሮበት ነው። እነዚህን ዋቢ መስፈርቶች መጸሃፉን በማንበብ በሰፊው ልትተዋወቋቸው ስለምትችሉ፣ እዚህ መዘርዘር አስፈላጊ አይመሰለኝም።
የሁለተኛው ምዕራፍ ትኩረት፣ እነዚህን መሰረታዊ መሥፈርቶች ለማሟላት ሲፈለግ የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን መቃኘት ነው። በዚህ ምዕራፍ ሥር ፣ “የማንነት ፖለቲካ”በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዐት ምሥረታ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ የችግሮቹ ሁሉ ቁንጮ ለመሆኑ ያለውን ግንዛቤ በሰፊው አትቶበታል። ይህን ትንተናውን ያካተተው ደግሞ “የታሪክ ጠባሳ” በሚሉ ሁለት ቀልብ ሳቢ ቃላት በሚጀምር ንዑስ ርዕስ ስር ነው። ታሪክ ትቶልን ያለፈውን “ጠባሳ” ከመግለጹ በፊት ግን፣ የመጀመሪያዎቹን አምስት ገጾች በመንደርደሪያነት በመጠቀም ታሪክ ምንድን ነው? የሚለውን መስቀለኛ ጥያቄ ይቃኝል። ይህን ቅኝት ተመርኩዞም፣ በታሪክ ላይ ተመስርቶ የዛሬውን የጋራ ህይወት ለመቅረጽ የሚደረግ ሙከራ ሁሌም ችግር ውስጥ የሚገባ ስለሆነ፣ የታሪክ ዘገባውን ለታሪክ ሰዎች ትተን፣ ለችግሩ የፖለቲካ መፍትሄ እንድንፈልግለት ይማፀነናል። ብዙም ሳይቆይ ግን፣ ይህንኑ የማንነት ፖለቲካ አሰመልክቶ በሁለት አቢይ ተዋንያን የህብረተብ ወገኖች የሚተረኩ ታሪኮች የሚላቸውን ይዞልን ይቀርባል። በዚህ ጊዜ ግን፣ እኛ እንድንሸሸው የተማጠነንን በታሪክ ላይ የተመሰረተ ዘገባ፤ እራሱ ማምለጥ የቻለ አልመሰለኝም። አስተያየቴን አቀርብባቸዋለሁ ካልኩት ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች ውስጥ የመጀመሪያው በዚሁ የብርሃኑ የታሪክ ዘገባ ላይ ያጠነጠረ ስለሆነ፣ እመለስበታለሁና እዛው እስክደርስ አብራችሁኝ እንድትጓዙ በትህትና እጠይቃለሁ።
ብርሃኑ፣ በመጽሃፉ ሶስተኛ ምዕራፍ ሥር ፣ ጥሩ የሚባል የኢኮኖሚ ስርዓት ማካተት አለበት የሚላቸውን ንጥረ ነገሮችን በብቃትና በሰፊው ትንተና ያቀርብበታል። ይህን ሲያደርግም፣ ጥሩና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ስርዓት የትኛው ነው የሚለውን አከራካሪና ፍልስፍናዊ መልስ የሚሻ ጥያቄ ወደጎን ትቶ፣ በኢኮኖሚ ፍልስፍና ላይ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሁሉ በጋራ ይሰማሙባቸዋል ብሎ የሚያምንባቸውን ንጥረ ነገሮች ብቻ በመቃኘት ነው። ብርሃኑ ይህን ስሌት የመረጠበትን ምክንያት ሲያስረዳ፣ መጽሃፏ በዋናነት እንድታነጣጥር የተለመበትን አቅጣጫ እንዳትስት ለማረግ መሆኑን ይገልጻል። በራሱ አባባል፣ “የተለያየ የግል ጥቅም ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ” እና “በተለያየ መስፈርት ሲለኩ ብዙ አማራጭ መፍትሄዎች በሚኖሩበት ሁኔታ ጥሩውን እንዴት ነው የምንመርጠው? በሚለው የሂደት ጥያቄ ላይ እንድናተኩር ነው።” ይህን ምዕራፍ ሲቆጭም፣ የኢኮኖሚው ስርዓት እነዚህን መሰረታዊ ንጥረ ነገሮች ማካተቱ የሚለካው፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲው አወጣጥም ላይ ሆነ አተገባበር ላይ፣ የማህበረሰቡን አጠቃላይ ጥቅም የሚያስቀድም፤ ለማንም የተለየ ቡድን አድልዎ የማያደርግ መንግሥት መኖር ሲችል ብቻ ነው በማለት አሁንም የሂደት ጥያቄ በመጀመሪያ መመለስ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ መሆኑን በጎላ ድምጽ በማሰማት ነው።
ምእራፍ ፬ ጥሩ የኢኮኖሚ ስርዓት በአገራችን ለመገንባት ያሉብንን መሰረታዊ መዋቅራዊ ችግሮች በአራቱም የጥሩ ኢኮኖሚ መለኪያ መስፈርቶች አኳያ በመመዘን ይፈትሽና በነዚህ መሥፈርቶች ስትለካ ሀገራችን ፍጹም ሗላ የቀረች መሆኗ ብዙ የሚያከራክር ጉዳይ አለመሆኑን ያስረዳል። እነዚህ ዘርፈ ሰፊ የአገራችን ችግሮች፣ መንግሥት ስለተቀየረና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ስለተመሰረተ በቶሎ የሚጠፉ ስላልሁኑ፣ ለማንኛውም አይነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓት ፈታኝ እንደሚሆኑና አመርቂ መልስ የሚሹ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል ሲል ያሳስበናል። አሁንም ለብርሃኑ ዋነኛው ቁምነገር፣ ከብዙ የፖሊሲ አማራጮች ውስጥ፣ የፖለቲካ ስርዓቱ የትኛውን መፍትሄ እንዴት ይመርጣል የሚለው የዚያን የፖለቲካ
ኢኮኖሚ ምንነት የሚያሳይ አይነተኛ ገላጭ መሆኑን መገንዘብ መቻላችን ነው። በአመራረጥ ሂደቱ ላይ ያልተስተካከለ የመወዳደሪያ ሜዳ፣ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ውጤት ሲተነትንም ውጤቱ በሙስና ግዙፍ ጫና የተቀፈደደ ጭንጋፍ ኢኮኖሚ እንደሚሆን ለአንባቢ መረዳት ዳገት ባልሆነ ትንተና አስረድቶናል። በዚሁ ምዕርፍ ሥርም፣ ስለ እድገት/ልማትና የልማታዊ መንግሥት ከአርሶ አደሩና ከአርቢው መደብ መሬት መፈናቀል በሰፊው ዘክሮበታል። ይህን ምዕራፍ ሲያጠቃልልም፣ የኢኮኖሚ ችግሮቻችን ብዙ ቢሆኑምና እነዚህን መጠነ ሰፊ ችግሮቻችንን መፍታት ቀላል ባይሆንም ቅሉ፣ ሂደቱን በጥንቃቄ ካዘጋጀነው መፍትሄው ከችሎታችን ውጪ አንዳይደልና ተስፋችንን ጨለምተኛ እንዳናደርገው ምሁራዊ ምክሩን በመለገስ ነው።
ብርሃኑ በምዕራፍ ፭ ስር የአካባቢ ጥበቃ ችግሮቻችንን አስመልክቶ፣ የህዝብ ብዛት፣ የአየር ፀባይ መቀየር፣ የደን መመናመን፣ የመሬት መሸርሸር/መከላት የሚያመጡትን ችግሮች አገሪቷ ካለችበት ሁኔታ ጋር አዛምዶ አሁንም ሰፋ ያለ ትንተና አቅርቦበታል። በብርሃኑ እምነት፣ እነዚህ መጠነ ሰፊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ተቀባይነት ያለው እቅድ መንደፍ የሚቻለው፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እራሳቸው በመረጧቸው ወኪሎቻቸው አመካኝነት በሰጥቶ መቀበል ሂደት ተወያይተውበትና ተከራክረውበት ለብዙሃኑ የሚበጀውን ውሳኔ መስጠት ሲችሉ ብቻ ነው። ይህንን ምዕራፍ የሚደመድመውም፣ መፍትሄው ላይ ከመድረሳችን በፊት፣ ዋናው ጥያቄ ወደመፍትሄው የምንጓዝበት ሄደት መሆኑን ለአንድ አፍታም መዘንጋት እንደሌለብን በመጠቆም ነው።
ይህችን አጭር ግምገማ በወጉ ያነበበ ሁሉ ሊረዳው እንደሚችለው፣ ብርሃኑ፣ ሳይሰለች በአምስቱም ብዕራፎች ሥር ደጋግሞ የነገረን መሰረታዊ እምነቱ፣ ለጥያቄዎቻችን በዛ ያሉ ተወዳዳሪ መልሶች፣ ለችጎሮቻችን ብዙ አማራጭ መፍትሄዎች በሚኖሩበት ሁኔታ፣ መፍትሄውን ለመፈለግ የምንጓዝበት ሄደት ዴሞክራሲያዊ መሆን ወሳኝነት እንዳለው ነው። መፀሃፉን አጠቃሎ በማሳረግ የተሰናበተንም፤ “ከእወነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውጪ ማህበራዊ ልከኛ የሆነ መፍትሄ ሊሰጠን የሚችል ሌላ የፖለቲካ ስርዓት የለም። ይህን ስርዓት በኢትዮጵያ መመስረት ለሁሉም አይነት ማህበረሰባችን ችግሮች የመፍትሄው መጀመሪያ ብቻ ሳይሆን፤ የመፍትሄው ዋና ቁልፍ ነው” በማለት ነው። የሁለተኛው ትዝብታዊና ጥያቄ አዘል አስተያየቴም፤ ብርሃኑ መሰረታዊ እምነቱ መሆኑን ሳያሰልስ ባስታወቀንና እኔም እሰየው ብየ በምቀበለው የዴሞክራሲያዊ ሂደትን ወሳኝነት ከሚያረጋግጠው ንጥረ ሃሳብ ጋር የተያያዘ ይሆናል። አሁን በቀጥታ ወደ አስተያየቶቼ ይዣችሁ ላዝግም።
“በማንነት” ጥያቄ ላይ
ብርሃኑ፣ የ “ማንነት”ን ጥያቄ አሰመልክቶ ያቀረበውን ትንተና ያካተተው “የታሪክ ጠባሳ” በሚሉ ሁለት ቀልብ ሳቢ ቃላት በሚጀምር ንዑስ ርዕስ ስር መሆኑን ቀደም ብየ ጠቁሜያለሁ። በኔ አስተያየት፣ የብርሃኑ የታሪክ አተረጓጎም ችግር የሚጀምረው ከዚህ ነው።
ጠባሳ የደረቀን ቁስልን አመልካች ነው። ይህ አባባል፣ ብርሃኑ በዚህ ምዕራፍ ሥር ያተኮረበት የወቅቱን የኦሮሞ ብሄረሰብ ጥያቄ በተመለከተ ፣ የሚሰጠው ፍቺ የታሪክ ቁስላችሁ ደርቋል የሚለውን ነው። የኦሮሞ ብሄረተኞች ፣ ቁስላችን አልደረቀም ብቻ ሳይሆን፣ እያመረቀዘ ያለ ሰለሆነ፣ በወቅቱ መድሃኒት ካልተተኘለት ከጊዜ በሗላ መላ ፖለቲካዊ ሰውነታችንን ወሮና አጠቃላይ አገራዊ ህልውናችንን ሸርሽሮ ሊገነጣጥለን የሚችል ሞገደኛ በሽታ ነው የሚሉት። ኦሮሞ ያልሆንነውንና “ዴሞክራሲያዊ“ ሃገራዊ ብሄረተኞች ነን የምንለውን የሚጠይቁት፣ ቁስላችው እንዲሰማን አይመስለኝም። እኔ እስከተረዳሁት ድረስ፣ እየነገሩን ያለው፣ ቁስላችን አሁንም ድረስ ይሰማናል ስንላችሁ ስሙን እንጂ። መሠማማት የሚቻለውና መሥማማት ላይ የሚደረሰው፣ በመጀመሪያ መሥማት ሲቻል ነውና አስቀድማችሁ ጆሯችሁን ለግሱን ነው የሚሉን የሚመስለኝ ። በኔ ግምት፣ ብርሃኑ ቃሉን በገላጭነት የተጠቀመበት ትርጉምን ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን፣ በዚህ ጥያቄ ላይ እራሱ ለሚተርከው ታሪክ ጠባሳ ከቁስል የተሻለ ቅርበት ያለው መግለጫ ሆኖ ስላገኘው ይመስለኛል። ይህን ያልኩበትን ምክንያት ላስረዳ። ለዚህ እንዲረዳኝ፣ በመጀመሪያ ብርሃኑ የተዋንያኖቹን ማንነት የገለጸበትን ስሌት ልመዝግብ።

ስየ አብርሃ የኢትዮዽያ ሰራዊት አሰባስቦ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ለመገልበጥ እያሴረ ነው በሚል ህወሓቶች ተሸብረዋል


ህወሓቶች ባስቸኳይ ስብሰባዎች ተወጥረዋል። ሰሞኑ በመቐለ ከተማ የደህንነቶች፣ የታማኝ ካድሬዎችና የምክርቤት ስብሰባዎች ነበሩ/አሉ። የተጨናነቁበት አንድ ጉዳይ አለ።
ህወሓቶች ካድሬዎችን ሰብሰበው የሆነ ግለሰብ ወይ አካል ዒላማ አድርገው ስሙ በማጥፋት ከህዝብ ለመነጠል ጥረት ያደርጋሉ። ቀደም ሲል “አብርሃ ደስታ የሚፅፋቸው ነገሮች ዉሸት ናቸው እያልን ህዝብ እንዳይሰማው እናድርግ” በሚል አብርሃ ደስታ በመላው ትግራይ በራሳቸው አንደበት አስተዋውቀውታል።
አሁን ደግሞ በመላው ትግራይ ስለ ስየ አብርሃ መጥፎ በመናገር ስሙ ለማጥፋት ታቅዷል። በህወሓት መንደር ዋነኛ ስጋት የፈጠረው (ባሁኑ ሰዓት) አብርሃ ደስታ ወይ ዓረና ፓርቲ አይደለም፤ ስየ አብርሃ እንጂ። ስየ እንዴት ለህወሓቶች ስጋት ፈጠረ? ‘ስየ ከፖለቲካ ራሱ አግሏል’ እየተባለ አልነበረም?
ከህወሓቶች የደረሰኝ መረጃ እንደሚያሳየው ስየ አብርሃ የኢትዮዽያ ሰራዊት (ከኢትዮዽያ ዉጭ በሰላም ማስከበር ተልእኮና በሌላ ምክንያት የሚገኝ) አሰባስቦ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ለመገልበጥ እያሴረ ነው በሚል ስጋት ህወሓቶች የሚያደርጉትን ጠፍቷቸዋል።
የአልሸባብና የኤርትራ አሸባሪ መጣ ፣፣ ምናምን እያሉ የተሸበሩም ከስየ ስጋት የተቆራኘ ነው። ስለ እውነታዊነቱ እርግጠኛ አይደለሁም። ህወሓቶች በስየ አብርሃ መሸበራቸው ግን እርግጠኛ ነው። ካሁን በኋላ ስየ በትግራይ ህዝብ ድጋፍ እንዳይኖረው ለማድረግ ህወሓቶች ስም የማጥፋት ዘመቻ ይከፍታሉ።

ሀገራዊ ውርደት እንዲያበቃ ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ!!!

November 7/2013

የወያኔ ገዢ ጉጅሌ በባህርዩ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አጋጥሟት የማያውቅ ፍጹም ኢሰብዓዊና ነውረኛ ስብስብ እንደሆነ ለመረዳት ኢትዮጵያዊያንን ለማዋረድ የሚጠቀሟቸውን ተግባራትና ቃላትን ማጤን ይበቃል።
በሶማሌ ክልል የኦብነግን ታጣቂዎች ቅስም ለመስበር ልጃገረዶችንና እናቶችን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም ጭምር በቤተሰብ ፊት በደቦ የሚደፍሩ፤ ለዚህ ተግባር የሠለጠኑ የልዩ ጦር አባላት መኖራቸው በስፋት የሚታወቅና በተደጋጋሚም የተዘገበ ጉዳይ ነው። ወያኔ፣ የኦጋዴን ወገኖቻችን በዚህ ጥቃት ተሸማቀው ያነገቡትን መሣሪያ ጥለው ፀጥ-ለጥ ብለው ይገዛሉ ብሎ ተስፋ ያደረገ ቢሆንም እየሆነ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ዛሬ የሶማሌ ክልል ወንዱም ሴቱም፤ ወጣቱም አዛውንቱም በፀረ-ወያኔ አቋም የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል። በኦጋዴን የወያኔ አስነዋሪ ጥቃት የፈጠረው ምሬት በውጭ አገራትም በሚደረጉ የፀረ ወያኔ ትግሎች የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ተሳትፎ እንዲጎለብት አድርጎታል። በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
በአፋር ክልልም ተመሳሳይ ጥቃት የዘወትር ትዕይንት እየሆነ መጥቷል። የአፋር የወል የግጦሽ መሬቶች ለሸኮራ አገዳ ልማት በሚል ሰበብ ሲነጠቁ የተቃወሙ የአገር ሽማግሌዎች ተደብድበዋል፤ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ተደፍረዋል። በአፋርም ውስጥ ለጾታዊ ጥቃት የሰለጠነ የወያኔ ልዩ ጦር ተሰማርቶ በሴቶች ብቻ ሳይሆን በወንዶችም ላይ አስነዋሪ ጥቃት አድርሷል። በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
በጋምቤላ ውስጥ ወያኔ ወገኖቻችን ከፈጀ በኋላ በሕይወት የተረፉትም ቅስማቸውን ለመስበር ጾታዊ ጥቃት በመሣሪያነት ተጠቅሟል፤ አሁንም እየተጠቀመ ነው። በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
የወያኔ ዝቅጠት ዘግናኝ ነው። ወያኔ ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ጾታዊ ጥቃት ያላደረሰበት የአገራችን ክፍል የለም። ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉል … በሁሉም ቦታዎች ያልተነገሩ ጥቃቶች በዜጎታችን ላይ ደርሷል፤ እየደረሰም ነው።
በአንድ ወቅት በመሀል አገር፤ በሰሜን ሸዋ አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት በእብሪተኛ ወያኔ የተገደለውን ባለቤትዋን ብልት ይዛ አስክሬኑን እንድትጎትት መደረጉን ከዓይን እማኞች አንደበት ሰምተናል። በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሰበብ መስዋዕትነት እየተቀበሉ ያሉ ወገኖቻችን “ሽንታም አማራ” እየተባሉ ብልቶቻቸው ይቀጠቀጥ እንደነበር የሰማነው እና የምናውቀው ጉዳይ ነው። በወያኔ መዳፍ ውስጥ ውስጥ ገብተው በእስር ቤቶች በሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ዘግናኝ ተግባራት እንደሚፈፀሙ መረጃዎች አሉ። በአዲስ አበባ በየቦታው ባሉት ስውር የማሰቃያ ቤቶችም ተመሳሳይ ተግባራት ዘወትር እንደሚፈፀሙ ይታወቃል።
ወያኔ ለጾታዊ ጥቃት ያሰለጠናቸው ሰዎችን በከተሞችም ውስጥ አሰማርቷል። በእነዚህ ጥቃቶች ግለሰቦች ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ቢሆንም የተደፈርነው፣ የተዋረድነው ሁላችንም መሆናችን አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል። የተደፈርነው እኛ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነን። የተዋረደችው የምንወዳት አገራችን ኢትዮጵያ ነች።
ኢትዮጵያ አገራችን እፍረት ባልፈጠረባቸው ነውረኛ የወያኔ ዋልጌዎች እንድትገዛ እንድትረገጥ በመፍቀዳችን ጥፋቱ የኛም ጭምር ነው። ይህን ነውረኛ ቡድን በሥልጣን ላይ እንዲቆይ በፈቀድንለት መጠን በኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያችን ላይ የሚደርሰው በደል እየባሰ እንደሚመጣ በዓይኖቻችን እያየን በጆሮዎቻችን እየሰማን ነው።
ሰሞኑን በአንድነት ፓርቲ የምክር ቤት አባል ላይ የደረሰው ጥቃት የዚሁ አካል ነው። እኚህ ወገናችን የደረሰባቸውን ዘርዝሮ ለመናገር የሚከብድ መሆኑ ገልፀዋል። ማፈር የነበረባቸው ጥቃት አድራሾቹ መሆን ይገባቸው ነበር፤ ሆኖም ግን ይሉኝታ አልፈጠረባቸው። ምንም ይሁን ምን በወገናችን ላይ የደረሰው ጥቃት በእሳቸው ላይ ብቻ የደረሰ ሳይሆን በሁላችንም ላይ የደረሰ መስሎ የሚሰማን መሆኑን ልንነግራቸው እንወዳለን። የተዋረደችው ኢትዮጵያ አገራችን ነች።
ይህ ውርደት እንዲያበቃ ወያኔ ከሥልጣን መወገድ ይኖርበታል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ” ቀዳሚ ሥራችን ነው የሚለው ኢትዮጵያን ለማዳን ከዚህ የሚበልጥ አንገብጋቢና አጣዳፊ ሥራ ስለሌለ ነው። ወያኔን ለማስወገድ እንተባበር።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

የኢትዮጵያዉያን ስቃይና መከራ በሳዉዲ አረቢያ

የመጣኸዉ ባዶህን ነው! ባዶ ሆነህም ትመለሳለህ!…ኢንተ-ጃኢ-ፋዲ ወተርጃእ-ፋዲ…የሳዉዲዎች አመለካከት!
የፈለጋቹበት ዉሰዱን ግን አትደብድቡን…ይላል ኢትዮጵያዊዉ…ለካስ አትደብድቡን ማለቱ የሚያስደበድብ ነበር…
አይደለም የሰዉ ልጅ እንስሳ እንኳ እንደዚህ አይደረግም። የምታዩአቸዉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በሳዉዲ ዜጎች ተይዘዉ ወደ ጀዋዛት (የስደተኛ መምሪያ) ሲወሰዱ ነዉ። እነዚህን ደሃና ከርታታ ኢትዮጵያዉያን በቁጥጥር ስር ያዋለዉ ያገሪቱ ፖሊስ ሳይሆን ያገሪቱ ዜጎች ናቸዉ።”እክስር የዱ!…እጁን ስበረዉ!…” ይላል አንዱ። ከታች ሆኖ የጣር ድምጽን የሚያሰማዉ ኢትዮጵያዊ “ሐላሊ…ሐላሊ… ላቤን ያፈሰኩበት የልፋቴ ዋጋስ? በማለት ሲጠይቅ ዱላዉ ይጠነክርበታል።
ሰዉ የመሆን ማእረግን የተነፈገዉ ሌላኛዉ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ዱላዉን እርግጫዉን እየዋጠ ስቃዩን ለመቀነስ “ኻላስ-አነ-ገልጣን…በቃ! በቃ! እኔ-ነኝ-ጥፋተኛ” ይላል። ከሳዉዲ ዜጎች አንደኛዉ ኢትዮጵያዉያኑ በመያዛቸዉ ባይከፋም ዱላዉን እንዲህ እያለ ይቃወማል “ተራ ኤይብ-መጅሙዓ-ተድርቡነ?… ይህ ነዉር ነዉ በህብረት ትደባደባላችሁ?” ግን ማን ሊሰማዉ። የኢትዮጵያዉያኑን የሰራ-አካል ማሰቃየት ብቻ ሳይሆን የሚያራግፉባቸዉም የቃላት ናዳ ስነልቦናን ይሰብራል።The Misery of Ethiopians in Saudi Arabia
አገር ዉስጥ ካለዉ ስቃይ ለመዳንና የተሻለን ህይወት ለራስም ለቤተስብም ለማምጣት የሚሰደዱት ኢትዮጵያዉን የሚደርስባችዉ መከራና እንግልት ተቆጥሮ አያበቃም። የሳዉዲ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ (ኢቃማ) የሌላቸዉ ወይም ከአሰሪያችዉ ጋር የማይሰሩ (ከፊል) በመጡበት የስራ ዓይነት (ሚህና) የማይሰሩት ከአገር እንዲወጡ ወይም የመኖሪያ ፈቃዳቸዉን እንዲያስተካክሉ የሰጠዉ ግዜ ስላበቃ ሰዎችን በዜግነት በሐማኖት ሳይለዩ ማፈሱን ተያዘዉታል። ባንጻሩ እነዚህ ሰደትኞችን ወደ ሳዉዲ በማስገባት ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙን የሳዉዲ ዜጎች መንግስቱ ወጥ የሆነ እርምጃ ሲወስድባቸዉ አይስተዋልም። ስለዚህ የሳዉዲ ዜጎችም ይሁኑ መንግስቱ ተጠያቂ ከመሆን አይድኑም።
ሰዎች ወደ ሳዉዲ እንዴት ይገባሉ የሚለዉን ስንቃኝ…
1) በሐሃጅና በኡምራ(ጸሎት)
ሰዎች ከተለያዩ አገራት ጸሎት እናደርጋለን በማለት ወደ ሳዉዲ ከደረሱ በሗላ እዚያዉ ይቀራሉ። እነዚህን ሰዎች ቀጥሮ በማሰራትም ይሁን ከቦታ ቦታ በድብቅ በማመላለስ ህገወጥ ተግባር ላይ የሚሰማሩት የሳዉዲ ዜጎች ናቸዉ። በነዚህ የሳዉዲ ዜጎች ላይ መንግስቱ በቂ የሆነ እርምጃ አይወስድም፤ የርምጃዉ ሰለባ የሚሆኑት ስደተኞቹ ብቻ በመሆናቸዉ መንግስቱ ተጠያቂ ነዉ።
2) የኮንትራት ስራ (ጠለብ)
በኮንትራት የሚመጡት ሰራተኞች ከዘመናዊ ባርነት ባልተናነሰ መልኩ ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸዋል። ረጅም ሰዓታትን መስራት ብቻ  ሳይሆን ከኮንትራቱ ዉል ዉጪ ለዘመድና ለጎረቤት በተጨማሪ እንዲሰሩ የሚገደዱ አሉ። የጠለብ (የኮንትራት) ሰራተኞች ድብደባ፣ግርፋት፣አስገድዶ መድፈር (rape)ወዘተ ይደርስባቸዋል፤ በዚህም ሳቢያ ከአሰሪያቸዉ በመጥፋት በግል ተቀጥረዉ መስራት ይጀምራሉ።የሳዉዲ መንግስት ዜጎቹ የሰራተኛን መብት እንዲያከብሩ በቂ ግንዛቤን ባለመፍጠሩና  ይሕንን መስል ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፍጽሙትን ዜጎች ሕግ ፊት በተገቢዉ መልኩ ባለማቅረቡ ተባባሪ ያስመስለዋልና ተጠያቂ ነዉ።
2) በባህርና ድንበር አቋርጦ መግባት
የሳዉዲ ጎረቤት ከሆነችዉ የመን በኩል ብዙ ስደተኞች ወደ ሳዉዲ ይገባሉ። በተለይም ጀዛን የሚባለዉ የሳውዲ ግዛት ቀድም ሲል የየመን የነበረ ሲሆን ድንበሩን አንድ አይነት ጎሳዎች ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦችም ይጋሩታል፤ በሁለቱም አገራት ያሉ የህግ አስከባሪ አካለት የሚዛመዱበት አጋጣሚ ብዙ ነዉ። በተቀነባበረ የኮንትሮባንድ ስራ ፖሊሶችና ድንበር ጠባቂ ሐይላት ሰዎችን በህገወጥ መንገድ በማስገባት ይተባበራሉ። የሳዉዲ መንግስት በድንበሩ ላይ ባሉ የህግ አስከባሪ ሐይላት ላይ በቂ ቁጥጥር ባለማድረጉ ተጠያቂ ነዉ።
ስደተኞች ወደ ሳዉዲ ሲገቡ የአገሪቱን ግዛቶች አቋርጠዉ ከቦታ ቦታ እንዲዘዋወሩ የኮንትሮባንድን ስራ የሚሰሩት የሳዉዲ ዜጎች ናቸዉ። ለምሳሌ አንድ ስደተኛ ከየመን ድንበር-ጀዛን ወደ ሪያድ ወይም ወደ ጂዳ መግባት ቢፈልግ በጭነት መኪና ከእቃ ጋር ተደብቆ እንዲገባ ይደረጋል፤ካልያም ወንዱ እንደሴት ቀሚስ-ሻሽ-የፊት መሸፈኛ እንዲለብስ ይደረግና የሳዉዲ ዜጎች እንደ ሚስት ወይም ልጆች ጭኖ በኮንትሮባንድ ሰዎችን ከቦታ ቦታ ያመላልሳሉ። በዚህ የኮንትሮባንድ ተግባር ፖሊስ (ሹርጣ) ተባባሪ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነዉ። ለዚህ ህገ ወጥ ተግባር ከሳዉዲ መንግስት ሌላ ማንም ተጠያቂ ሊሆን አይችልም።
ወደ ሳዉዲ ለምግባት ኢቃማ (የመኖሪያ ፈቃድ) በዉድ ገዝተዉ የሚገቡ ስደተኞች አንዳንዴ የውሸት አሰሪያቸዉ (ከፊል) ጠፍቶባቸዉ የመኖሪያ ፍቃድ ለማዉጣት የሚቸገሩበት አጋጣሚ አለ። አንዳንዴም የመኖሪያ ፍቃዱን ቢያገኙም ፈቃዳቸዉ ሲቃጠል ለማደስ (ተጅዲድ) አሰሪያቸዉ ጠፍቶ ወይም ፍቃደኛ ሳይሆን ይቀርና ሳይወዱ በግድ ህገወጥ ይሆናሉ። ለዚህ ህገወጥና የተዝረከረከ አሰራር ከሳዉዲ መንግስት ሌላ ማን ተጠያቂ ሊሆን ይችላል?
በሳዉዲ ከተሞች ዉስጥ በስፋት ያሉት ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮዎች (መክተበል ሙአቂብ) የመኖሪያ ፍቃድን በተመለከተ የተለያዩ የማጭበርበር ስራዎች (ተዝዊር) በመስራት ይታወቃሉ። እነዚህን ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮ ከፍቶ ለመስራት የሳዉዲ ዜጋ መሆኑ ግዴታ ነዉ። በነዚህ ቢሮዎች የዉሸት የመኖሪያ ፍቃድን ከማዘጋጀት ጀምሮ፤ስደተኞች ያለ አሰሪያቸዉ (የዉሸት አሰሪም ቢሆን) ፍቃድ ከአገር ወጥተዉ እንዲመለሱ (ኹርጀል አዉዳ) እስክማድረግ ይሰራል። በነዚህ ቢሮዎች ዉስጥ ሌላዉ ቀርቶ ከስራ ሰዓት ዉጪ ከኢምግሬሽን (ጀዋዛት) በመመላለስ ባዶ ኢቃማ የመኖሪያ ፈቃድ በማምጣት የዉሸት የምኖሪያ ፍቃድ የሚሰጡ የመንግስት ሰራተኞች በርካታ (ነበሩ)ናቸዉ። በዉሸት ከአንድ አሰሪ ወደ ሌላ አሰሪ (ተናዙል-ነቅለል-ከፋላ) በማድረግም የሳዉዲ ህግ አስከባሪ አካላት በመተባበር ህገወጥነትን ያስፋፋሉ። ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ተጠያቂዉ ዛሬ በየመንገዱ እንደ እንስሳ እየታደኑ ኢሰብዓዊ ተግባር የሚፈጽምባቸዉ ስደተኞች ሳይሆኑ የሳዉዲ መንግስት ነዉ። ከሳዉዲ መንግስትም ባሻገር አገሪቷን የተቆጣጠሩት የንጉስ አብድልአዚዝ ቤተሰቦች ያንበሳዉን ደርሻ ይይዛሉ።
በሳዉዲ ዉስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆኑ በትክክለኛዉ መንገድ ሰርትዉ የከበሩ፤ላገር፣ለቤተሰብ፣ለወገን የተረፉ በርካታ ናቸዉ። ባንጻሩም እንደ ወጡ የቀሩ፤ ጤነኛ ሆነዉ ታመዉ የተመለሱም ይኖራሉ። በህገወጥ መንገድ አረቄና አስካሪ መጠጥን በመጥመቅ ብሎም በዝሙት የሚተዳደሩም ይኖራሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ እዚያዉ-ሳዉዲ የተወለዱ ኢትዮጵያዉያን ህጻናት ሲኖሩ በአገሪቱ ደንብ መሰረት ሁለተኛ ደረጃን ከጨረሱ በሗላ የኮሌጅ ትምርት የማግኘት እድላቸዉ የመነመነ ነዉ (አይቻልም ማለት ይቻላል)። አቅም ያለዉ ልጆቹን ወደ አዉሮፓ እና አሜሪካ ለከፍተኛ ትምርት ሲልክ ዉስን አቅም ያለዉ ልጆቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ በተለያዩ ኮሌጆች ያስተምራል። ሁለቱንም ማረግ ያልችለ ልጆቹ ያለትምርት የሚባክኑበት አጋጣሚ ሰፊ ነዉ።የባህረ ሰላጤዉን ስደት አስመልክቶ ብዙ ግዜ የሚነገረዉ ለአቅመ አዳምና ሔዋን ለደረሱት ኢትዮጵያዉያን ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የወደፊት እጣ ፈንታቸዉን የማያዉቁ ሕጻናት ስለተዘነጉ ለነርሱም ማሰቡ ታላቅ ሰብዓዊ ግዴታ ነዉ።
በዚህ መከራና ስቃያ ዉስጥ ላሉ ኢትዮጵያዉን ለመታደግ ለዜጎቹ የሚቆረቆር ሁነኛ መንግስት ቢያሻም ሪያድ ያለዉ የሳዉዲ ኤምባሲና ጅዳ ያለዉ የቆንስላ ጽ/ቤት በመጣመር ዜጎችን የሚበድሉ ቢሆኑ እንጂ ለዜጎች ደራሽ ሲሆኑ አይታይም። ከተወሳሰበዉ የሳዉዲ ህግ ለመዳንና የመኖሪያ ፍቃድን ለማደስ ለፓስፖርት እድሳት ኤምባሲ የሚሔዱ ኢትዮጵያዉን ከፍላጎታቸዉ ዉጪ ለአባይ ቦንድ ግዙ ተብለዉ እንደሚቸገሩ ቀደም ሲል የተዘገበ እዉነታ ነዉ።ኤምባሲዉ ኢትዮጵያዉያንን በዘር በብሔር እየመተረ በልማት ስም አፍን ብልጓም ሲዘጋ ኢትዮጵያዉያን በየመንገዱ ላይ ከእንስሳ ባነሰ መልኩ እየተደበደቡ እየተገረፉ ክብራቸዉ ተገፎ ወደ ማጎሪያ ቤት (ተርኺል) እየተወረወሩ ነዉ።
ይህ ኢሰብዓዊ ተግባር አለም አቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝ ለተለያዩ የስብዓዊ መብት ድርጅቶች ማሳወቁ ተገቢ ሲሆን ጉዳዩ ከፍትኛ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ኢትዮጵያዉያን በያሉበት መንቀሳቀስ አለባቸዉ።የፖለቲካ ድርጅቶችም ኢትዮጵያዉያኑ የሚደርስባቸዉን በደል በማዉገዝ ለጉዳዩ ልዩ አትኩሮትን በመቸር አቅማቸዉ በቻለዉ መጠን ሊንቀሳቀሱ ይገባል። የተለያዩ የሐይማኖትና የሲቪክ ማህበራትም ይሁኑ አክቲቪስቶች በመጣመር የሳዉዲ ኤምባሲዎች በሚገኙበት አገራት ሰላማዊ ሰልፍን ቢያረጉ መግለጫዎችን ቢያወጡ የወገኖቻንን ስቃይና መከራን ማስቆም ባይችሉ እንኳ ሊቀንሱት ይችላሉና-ወገን ለወገን መድረሱ ግድ ይላል።
የመጣኸዉ ባዶህን ነው… ባዶ ሆነህም ትመለሳለህ…(ኢንተ፡ጃኢ፡ፋዲ ወተርጃእ፡ፋዲ) ለሚባሉት ኢትዮጵያዉይን ከኛ  ሌላ ደራሽ የላቸዉምንና እንድረስላቸዉ። ልብ ያለዉ ልብ ይበል!

mandag 4. november 2013

ኢህአዴግ የቀድሞው የአፈና ገመዱ መንተቡን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየታቸውና አለመተማመን መንገሱ ተጠቆመ።


በህወሃት ውስጥ የዕርቅ ሃሳብ መነሳቱ ተሰማ

“የኢህአዴግ የአፈና ገመድ ነትቧል፣ ድርጅቱ ተናግቷል”
ኢትዮጵያ ግራ በሚያጋባና ሊተነበይ በማይችል የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መገኘቷን ያመኑ የህወሃት ሰዎች መካካል የእርቅ ሃሳብ ላይ ለማተኮር እቅድ እንዲያዝ ሃሳብ ማንሳታቸው ተሰማ። ኢህአዴግ የቀድሞው የአፈና ገመዱ መንተቡን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየታቸውና አለመተማመን መንገሱ ተጠቆመ።
ጎልጉል መረጃ በመስጠት የሚታወቁ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራርና ዲፕሎማት እንዳሉት ህወሃት ውስጥ “እርቅ አስፈላጊ ነው” በሚል እቅድ እንዲያዝና እንዲሰራበት ሃሳብ ቀርቧል። በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ አለመተማመን ሳቢያ ስጋት የገባቸው የህወሃት ሰዎች የእርቅ ሃሳብ እንዲሰራበት ያቀረቡት ሃሳብ ግን በመደበኛ ስብሰባ አይደለም።
በህወሃትና ህወሃት በሚያዛቸው አቻ ፓርቲዎች መካከል ያለው የመከባበርና የመገዛት ስሜት ከመለስ ሞት በኋላ መበላሸቱ፣ በኢህአዴግም ሆነ በህወሃት ደረጃ የተፈጠረው ልዩነትና በሙስና ስም የተጀመረውን ዘመቻ ተከትሎ የተነሳው አለመግባባት አደጋ እንዳያስከትል ተፈርቷል። የመረጃው ምንጭ እንደሚሉት በጣም ጥቂት ካልሆኑ በስተቀር ከሙስና የጸዱ አለመኖራቸው “ማን ንጹህ ሆኖ ማንን ይጠይቃል?” የሚል ቅሬታ አስነስቷል።
ህወሃት ባሰበው በሁሉም መንገድ የበላይ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይችል ከየድርጅቶቹ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በስፋት እየተነገረ መሆኑንን ያነሱት እኚሁ ሰው፣ ይፋ ባልሆነ መንገድ የቀረበው እርቅን የመቀበል ጥያቄ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የተነሱት አስደንጋጭ ችግሮች ተከትሎ መሆኑን አልሸሸጉም።
ሊታመን በማይችልና ባልተለመደ መልኩ የሃይማኖት አባቶች ኢህአዴግን አንደበታቸውን ከፍተው በግልጽ ማውገዛቸውን፣ “አገሪቷን ገደላችኋት” በማለት መኮነናቸውን ተከትሎ በኢህአዴግ ዘንድ መደናገጥ እንደተፈጠረ ለማወቅ ተችሏል። የእምነት ጉዳይ ጥንቃቄ የሚያሻው በመሆኑ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት የተቆጠቡት ዲፕሎማት “ኢህአዴግ በቀድሞው ፓትሪያርክ ፈቃድና ውዴታ ያደርግ እንደነበረው አሁንም በደኅንነት ሃይሎች ቤተክርስቲያኒቱን መቆጣጠርና አመራሮቹን አንደበታቸውን ማፈን የማይችልበት ደረጃ መድረሱን አምኖ ተቀብሏል። በዚህ ላይ ደግሞ እስካሁን ምላሽ ያላገኘ የድምጻችን ይሰማ ጉዳይ አለ” ኢህአዴግ እንደተምታታበት አመላክተዋል።
ሲኖዶሱ በጉባኤው ያነሳቸው ነጥቦች ኢህአዴግ ነገሮች ቀስ በቀስ ከእጁ እንደወጡበት የሚያሳይ እንደሆነ ያመለከቱት የኢህአዴግ ሰው “ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የኢህአዴግ አባላት በልብ ከድርጅቱ ጋር እንደሌሉ ሪፖርት ቀርቧል። አብዛኛው አባልና ደጋፊ ባለሃብቶች የሚባሉትን ጨምሮ ሰላማዊ ለውጥ እንዲካሄድ ኢህአዴግ ወደ እርቅ መንገድ እንዲሄድ ይፋ (ኦፊሴላዊ) ባልሆነ መልኩ ያነሳሉ” በማለት ድርጅቱ የገባውን ስጋትና መሸርሸር ያስረዳሉ።
እርቅ ከተፈለገ ለምን በግልጽ አይቀርብም በሚል ለቀረበላቸው ሃሳብ ዲፕሎማቱ ምላሽ ለመስጠት አልፈለጉም። ይሁን እንጂ “ከማን ጋር ነው የምንታረቀው? እነማንን ነው ለእርቅ የምንጋብዘው? እርቅ ጠያቂ መሆን ያለበትስ ማን ነው?” የሚሉት በግልጽ ባይቀርቡም ተመሳሳይ የስጋት ጥያቄዎች እንዳሉ ሳይገልጹ አላለፉም።
በቅንጅት ጊዜም በተመሳሳይ የዕርቅ ፍላጎትና “ሥልጣን እናስረክብ” የሚል አቋም ተነስቶ እንደነበር ያስታወሱት ምንጫችን፤ በወቅቱ ሃሳቡ ተግባራዊ ያልሆነው “ወያኔዎችን ወደመጡበት ጠራርገን እንመልሳቸዋለን” በማለት አንድ የቅንጅት አመራር ለሕዝብ መፈክር ሲያወርዱ ከተሰማ በኋላ ነበር፡፡
በመከላከያ አዛዦችና በደህንነት የተለያዩ መምሪያዎች የሃላፊዎች ለውጥ እያካሄደ ያለው ኢህአዴግ ከአቻ ፓርቲዎች ጋር ውህደት በማድረግ ብሔራዊ ፓርቲ ለማቋቋም በሁለት ጉባኤዎች ሃሳብ ቢቀርብም ተግባራዊ አላደረገውም። ፓርቲው ህብረ ብሔር ከሆነ ህወሃት የገነባቸው የንግድ ድርጅቶችና በሞኖፖል የያዘውን ቁልፍ ስልጣን እንዲያጣ ስለሚያደርገው ጊዜ ሲያጓትት መቆየቱን ያመለከቱት የመረጃው አቀባይ “ይህ ፍርሃቻ አሁንም ሆነ ወደፊት ለሚፈለገው በሃሳብ ደረጃ ያለ እርቅ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል የውስጥ ለውስጥ ሃሜት አለ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ሆኖም እጅግ የተወሳሰበ የፖለቲካ ትወና ውስጥ ያሉት ካልሆኑ በስተቀር በማናቸውም መልኩ እርቅን ለመቀበል የማያቅማሙ እንደሚበዙ ግን አልሸሸጉም፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ አለመተማመን መንገሱን የሚናገሩ ወገኖች “ለራሳቸው መተማመን ያቃታቸው ክፍሎች እንዴት ሌላውን አስማምተው ይመራሉ” በማለት መጠየቅ ከጀመሩ ቆይተዋል። በተለይም አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ወደ መንበሩ ከመጡ በኋላ አገሪቱ በደቦ መመራቷ የኢህአዴግን መሽመድመድ የሚያሳይ እንደሆነም እየተቹ ነው።
sebhat negaሁሉም ሰላም ነው፤ ልማት ነው፤ ዕድገት ነው፤ ህዳሴ ነው … በማለት አንድም ችግር የሌለበት ለመምሰል የሚሞክረው ህወሃት ደግሞ በውስጡ የመከፈል አደጋ አጋጥሞት እንደማያውቅ ምንነታቸውና የስራ ደርዛቸው በውል በማይታወቀው አቶ ስብሃትአማካይነት እያስታወቀ ነው። እሳቸው እንደሚሉት ችግር የህወሃት “ሰማያዊ ስጦታውና በረከቱ ነው” አቶ ሃይለማርያምም በበኩላቸው “ኢህአዴግ መካከል መከፋፈል አለ የሚሉ የዋሆች ናቸው” ሲሉ አንድነት የሰፈነበት አመራር እንዳለ ለማስተጋባት ሞክረዋል።
የእርቅ ሃሳብ ተሰንዝሯል በማለት መረጃውን የሰጡን ዲፕሎማት ግን ይህንን አይቀበሉም። “በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚታይ ነው። አንዱ እኔ ነኝ። ሌሎችም አሉ። ብዙዎች ሰላማዊ ህይወት ናፍቆናል። የተወሳሰበውን አገራችንን ፖለቲካ አካሄድ ለመተንበይ ተቸግረናል። መፍትሔው የእርቅ ሃሳብ ብቻ ነው” በሚል ተከራክረዋል።
በድርጅታቸው ውስጥ የበላይና የበታች መጥፋቱን፣ የበታቹ የበላዩን እንደሚያዘው፣ አንዳንዴ የበላይ መስለው ምንም ዓይነት የውሳኔ ሰጪነት ሚና የሌላቸው ክፍሎች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር እንደሆነ የሚናገሩት እኚሁ ሰው፣ “እርቅና ዋስትና የሚሰጥ አግባብ ቢያገኝ የመጀመሪያው ስምምነት ፈራሚና ደጋፊ ስብሃት ነው። ቀሪውን የጡረታ ዘመኑንን በትዝታ ያለውን እየበላ መኖር ይፈልጋል። እሱ ብቻ ሳይሆን ብዙዎች ተመሳሳይ ፍላጎት አለን። አስከማውቀው ድረስ ችግሩ ከራስ ምግባርና ከድርጅት ተልዕኮ በመነጨ የተሰሩት ጥፋቶችና ሃጢያቶች መብዛታቸው ከለውጥ በኋላ የሚያመጣቸው የተጠያቂነት ጣጣዎች ናቸው” ብለዋል፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ ንጹህ ሰዎች አሉ ለማለት የማይቻልበት ደረጃ መደረሱን የሚያመለክቱት ዲፕሎማት፣ ህወሃትም ሆነ ኢህአዴግ አሁን የጋራ ነጠብ የሌላቸው፣ የርስ በርስ ትስስራቸው የላላና የተለያየ፣ አንዱ ሌላውን ለመንካትና ለመገምገም የሞራል ብቃት ያጣበት፣ እርስ በርሱ በወንጀል የሚጠቋቆምበት የውድቀት ጫፍ ላይ መድረሱን የውጪ አገር ወዳጆቹም ተረድተውለታል፤ አሁን ለእነርሱም ችግር የሆነባቸው ቁጭ ብለው ሥልጣን ላይ የሰቀሉትን ህወሃት አሁን ቆመው እንዴት ማውረድ እንደሚቻል መቸገራቸው ነው ብለዋል። የእርቅ ሃሳቡ ከውጪ አገር ወዳጆቻቸው ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ግን ፍንጭ አልሰጡም።
በህወሃትም ሆነ በኢህአዴግ ደረጃ የውስጥ ስጋት ቢኖርም “ሕዝብ እስኪ ዛሬን ልደር” በሚል የሞራል ውድቅት ውስጥ በከተተው ድህነት የተመታ በመሆኑ ለጊዜው ያምጻል የሚል ግምገማ አለመኖሩን ዲፕሎማቱ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ህዝብ በኢህአዴግ ደስተኛ አለመሆኑ፣ የጥበቃና የቁጥጥር መረቡ እንደወትሮው ትጋት ማጣቱ፣ የአካባቢ ስሜትና “ወገኔን ለምንና እስከመቼ አሳልፌ እሰጣለሁ?” የሚል አስተሳሰብ መበራከቱ፣ አጋጣሚ ተቃውሞ ቢነሳ መቋቋም እንደማይቻል፣ ረብሻ ከተነሳ የስርዓቱ ባለሟሎች ህልውና ጉዳይ አስጨናቂ እንደሚሆን ግንዛቤ ስለመኖሩ አላስተባበሉም። በማያያዝም እሳቸው በዚህ ደረጃ ስርዓቱን ከገመገሙና ችግሩን ከተረዱ በይፋ የማይከዱበትን ምክንያት ተጠይቀው “ለጊዜው በምስጢር ጠባቂነት የዝግጅት ክፍሉ ቃሉን ይጠብቅ። የቀረውን ወደፊት እናየዋለን” የሚል ድፍን መልስ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሰጥተዋል።

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡