fredag 31. januar 2014

አስገራሚ ዜና – ሽመልስ ከማል ተሳደቡ፣ አስፈራሩ


አስገራሚ ዜና – ሽመልስ ከማል ተሳደቡ፣ አስፈራሩ “በአብዛኛዎቹ የህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚታየው ማስታወቂያ እንጥል እቆርጣለሁ፣ ግግ እቧጥጣለሁ የሚል የአንድ ደብተራ ማስታወቂያ ነው” አቶ ሽመልስ ከማል መንግስት የህትመት ውጤቶች አከፋፋዮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ፍንጭ ሰጠ በዘሪሁን ሙሉጌታ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በሀገሪቱ ውስጥ ፈርጀ ብዙ ኀሳቦች ለህብረተሰቡ እንዳይደርስ እያደረጉ ነው ባሉዋቸው የጋዜጣና መፅሔት አከፋፋዮች ላይ መንግስት በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቁ። ሚኒስትር ዴኤታው ይሄህን የተናገሩት “የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስትና የመገናኛ ብዙኃን ግንኙነት” በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት በኢንተርኮንቲነታል ሆቴል ሰሞኑን ባዘጋጀው የአንድ ቀን ሲምፖዚየም መዝጊያ ላይ ነው። የፕሬስ ነፃነት አፈና ሲነሳ በአከፋፋዮች አማካኝነት የሚደረግ አፈና አንዱ መሆኑን በመጥቀስ ጥቂት መፅሔቶችንና ጋዜጦችን በባለቤትነት የያዙ ግለሰቦች የማከፋፈል ስራውን በሞኖፖል ይዘው የአመለካከት ፈርጀ ብዙነት እንዳይኖር በማድረግ፣ በርካታ ህትመቶችን በለጋነታቸው ለሞት እንዲበቁ በማድረግ የአፈና ስራ ውስጥ የገቡ ወገኖች አሰራራቸው በፍጥነት መስተካከል አለበት ብለዋል። “ሚዲያን የመደጎምና የማስተካከሉ ስራ መንግስት በአግባቡ በተጠና ሁኔታ መግባት እንዳለበት ያምናል” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው በሚዲያ የኀሳብ ገበያ ውስጥ ምቹ ሁኔታዎችን በማዘጋጀት ለኢንዱስትሪው ቀና እድገት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአከፋፋዮች በኩል በርካታ ችግሮች ተለይተው እየተጠኑ መሆኑንም ጠቁመዋል። የህትመት ሚዲያው ብቻ ሳይሆን የሕዝብ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች ከችግሮች ነፃ አለመውጣታቸውንም የጠቀሱት አቶ ሽመልስ መንግስት ፈጣን መረጃ የሚሰጥ የሚዲያ ስርዓት እንዲፈጠር እንደሚፈልግ ገልጸዋል። መንግስት መረጃዎችን በገፍ የሚያቀርብ፣ ጥራት ባለውና ወቅታዊ በሆነ መንገድ የሚሰራ የሚዲያ ስርዓት እንዲገነባ ይፈልጋልም ብለዋል። ብሔራዊ የሚዲያ ፖሊሲው በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የህብረተሰቡን የፖለቲካ ብዙሃነት፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ፈርጀብዙነት ከመቀበል የሚነሳ መሆኑ አስታውሰው፤ ነገር ግን ሚዲያው በማንኛውም የባለቤትነት ውስጥ ቢሆንም ብሔራዊ መግባባትን ለማስረፅ መተኪያ የሌለው ቀዳሚ ሚና እንዲጫወት ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል። ሚዲያው በብሔራ ዊ መግባባት ላይ እንዲሰራ መንግስት ቢፈልግም ከማንኛውም ርዕዮተዓለም ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆን ይፈልጋል ብለዋል። አሁን ያለው የሚዲያ ችግር በንግድ ሚዲያ መርህ ወይም በገበያ መርህ መንቀሳቀስ አለመቻል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽመልስ አብዛኛዎቹ ሚዲያዎቻቸው ገበያቸውን ከማስታወቂያ የሚሸፍኑ አይደሉም ብለዋል። “በአብዛኛዎቹ የህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚታየው ማስታወቂያ “እንጥል እቆርጣለሁ፣ ግግ እቧጥጣለሁ” የሚል የአንድ ደብተራ ማስታወቂያ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ማስታወቂያ የላቸውም። ኮሜርሺያል አይደሉም፤ ኮሜሪሻያል ካልሆኑ ይደጎማሉ። በድጎማ የሚተዳደሩ ከሆነ ታማኝ አንባቢ ነው ያላቸው። ከተወሰኑ ርዕዮተአለማዊ አጥሮች አልፈው መጓዝ አይፈልጉም። ስለሆነም የህትመት ሚዲያ እድገት ላይ አንድ ትልቅ ጋሬጣ የሆነው ከነፃ ሚዲያ ህግጋት ውጪ ተንጋዶ የበቀለ የሚዲያ አካሄድ ነው” ያሉት አቶ ሽመልስ ይህንን ለማስተካከል መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ሊተባበሩ ይገባል ብለዋል። የሰንደቅ ዜናዎች (ጥር 21/2006)
ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ

ወያኔን ያሸበረው የግንቦት 7 መንገድ ምንድነው?

የትግራይን ሕዝብ ከብሄር ጭቆና ነጻ አወጣለሁ በሚል ጠባብ ዓላማ ተደራጅቶና ታጥቆ ለበትረ ሥልጣን የበቃው ህወሃት ወይም ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ከተቆጣጠረ 23 አመት ሊሞላው እነሆ ጥቂት ወራቶች ብቻ ቀርተውታል።
ለጋራ ቤታችን ለሆነቺው አገራችን ኢትዮጵያና በአስተዳደር በደል ለከፋ ድህነት ለተዳረገው መላው ሕዝቦቿ የሚሆን አንዳችም ራዕይ ሳይኖረው ለመንግሥትነት ሥልጣን የበቃው ይህ ቡድን ላለፉት 23 ዓመታት ከግል ኑሮአቸው አሻግረው የአገርንና የወገንን ጥቅም ማየት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉትን በዙሪያው አሰባስቦ እያካሄደ ካለው ዘርፈ ብዙ የሃብት ምዝበራ ወንጀል በተጨማሪ እየፈጸመ ያለው የመብት ጥሰትና አፈና ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ሰሞኑን እያፈተለኩ በመውጣት ላይ ከሚገኙ ምስጥራዊ የድምጽ መረጃዎች ለማረጋገጥ እንደተቻለው ደግሞ ለጥቂቶች የሃብትና የብልጽግና ምንጭ የሆነው ሥልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ በአንድ በኩል በምርጫ ስም እንዴት አድርገው ሕዝቡን ቀፍድደው የምርጫው ተሳታፊ ማድረግ እንደሚችሉ ሲዶልቱና በሌላ በኩል ደግሞ በቁጥጥራቸው ሥር የሌሉትንና ለሥልጣናቸው ያሰጉናል ያሉዋቸውን የደሃዉን ልጅ በማጋፈጥ እንዴት በጦርነት እንደሚጨፈልቁዋቸው ሲመክሩ ተሰምተዋል።
ከወያኔው ቁንጮ አንዱ የሆነው በረከት ስሞን በየደረጃው ላሉት የአገዛዙ ሹሞችና ካድሬዎች ባደረገው ገለፃ መሬትን የመንግሥት ባደረገው ኮሚኒስታዊ አዋጅ ምክንያት የመንግሥት ጭሰኛ ለመሆን የተፈረደበትን ሰፊውን አርሶ አደር “ተኛ ስንለው ይተኛል፤ ቁም ስንለው ይቆማል ፤ እንደፈለግን ብንበድለው እንኳ አያማርረንም ” እያለ ሲዘባበትበት ተደምጦአል ። በአንድ ለአምስት ኮሚንስታዊ አደረጃጀት ተጠርንፎ የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ብቻ የሚያቀርቡትን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያለውዴታው እንዲራገፍበትና ከአቅሙ በላይ ዕዳ እንዲቀፈቅፍ የተፈረደበት የኢትዮጵያ አርሶ አደር በዚህ አይነት ንቀት ደረጃ የሚዘባበትበትን መሪ ከወያኔው በረከት ስሞን በፊት ገጥሞት አያውቅም ። ለወደፊትም ሊያይ አይፈልግም ። ወያኔን ሥልጣን ላይ ለማምጣት የሰሜኑ ክፍለአገራችን አርሶ አደር የተጫወተው ሚና ተዘንግቶ በበረከት ስሞን እንዲህ መዋረዱ እጅግ ያሳዝናል። ለነገሩ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለድል ያበቃው የትግራይ ሕዝብ ቁም ስቅሉን እያየ አይደል?
ሌላው አስገራሚ ክስተት በአገር ደህንነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ባደረጉት ዝግ ስብሰባ ታማኝነታችን ለአገራችን ነው ወይስ የሥርዓቱን አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም? ብለው ላነሱት ጥያቄ የጠቅላይ ሚንስትር ተብዬው የህግ አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሰጠው መልስ ነው። ደህንነት ብቻ ሳይሆን የመከላኪያ ሠራዊትና ፖሊስ ጭማር ታማኝነታቸውና ግዴታቸው ሥርዓቱን ሥልጣን ላይ ማቆየት መሆን አለበት ሲል ጌታቸው እንቅቹን ነግሮአቸዋል ። በምላሹ “ላለፉት 23 አመታት እያደረግነው ያለው ይሄው ሆኖ ሳለ አሁን ምን ብታስቡ ነው ጥያቄ ያነሳችሁ?” የሚል ይመስላል ። ይባስ ብሎም ሥርአቱን ለመጠበቅ ያልቻለና በግንቦት 7 መንገድ የሚጓዝ ደህንነት ሠራተኛ የተስፋየ ገብረስላሴን ያህል የደህንነት እውቀት ቢኖረውም ሆነ እስራኤል አገር የዓመታት ስልጠና ያገኘ ቢሆን ዋጋ የለውም ብሏቸዋል።
ለመሆኑ ወያኔዎች እንደመርገም የቆጠሩትና ተከታዮቻቸውን የሚያስፈራሩበት የግንቦት 7 መንገድ ምንድ ነው።?
ግንቦት 7 የፍትህና፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገራችን ኢትዮጵያ የእያንዳንዱ ዜጋ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት የተከበረባት፤ የኢኮኖሚ ብልፅግናና ማኅበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ፤ የዜጎች ሕይወት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበረባት እና የሕዝቧ አንድነትና ትስስር የጠነከረባት ሃገር ሆና ማየትን ብቸኛ ራዕይ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው። ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ ደግሞ እስከ ዛሬ በጠመንጃ ኃይልና በጉልበተኖች ጡንቻ ከአንዱ ወደሌላው የሚፈራረቀው የመንግሥት ና የፖለቲካ ሥልጣን በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሂደት የሚያዝበትን ፤ የሃገሪቱ ዜጎች ምርጫ በተግባር የሚገለፅበት፤ ማኅበራዊና የፖለቲካ ችግሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈቱበት እና ዲሞክራሲያዊ ባህል የሚበለፅግበት ብሄራዊ የፖለቲካዊ ሥርዓት መገንባት አማራጭ የሌለው ነው ብሎ ያምናል።
ይህ ደግሞ ያለምክንያት አይደለም። ወያኔ የዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት ሲል ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሩን ከፈት አድርጎ በነበረበት ምርጫ 97 ወቅት ከተገኘው ልምድና ከተመዘገበው ውጤት ሕዝባችን በአምባገነኖችና በከፋፋዮች ለመገዛት አለመፈለጉን በግልጽ አስመስክሮአል።
ንቅናቄያችን ግንቦት 7 ሕዝባችን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በነቂስ ወጥቶ መሪዎቹን የመረጠበትንና ድሉን የተነጠቀመበትን ታሪካዊ የግንቦት 7 1997ን ቀን ምን ጊዜም አይረሳም። መጠሪያ ስሙንም በዚያ ታሪካዊ ቀን የሰየመው ሕዝብ የተነጠቀውን ድል በማስመለስ ፍትህ የሰፈነባት፤ የበለጸገችና የተከበረች አገር ባለቤት እንሆን ዘንድ ነው። ሁላችንም አትራፊ እንጂ ተጎጂ ለማንሆንበት ለዚህ ቅን አለማና ራዕይ ደንቃራ ሆኖ የተገኘው ወያኔና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ከወያኔ ጋር የተጣበቁ አንዳንድ ባዕዳን አገሮች ናቸው።
ወያኔ የግንቦት 7 መንገድ የሚለው ለዚህ ክቡር ዓላማ ሲባል እንቅፋት የሆነውን ሥርዓቱን በሁለ- ገብ ትግል አስገድዶ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አካል ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ በተባበረ ትግል አስወግዶ በምትኩ በሕዝብ ለሕዝብ ከሕዝብ የሚመጣ ሰላማዊ የመንግሥት ሥርዓት መመሥረትን ነው። ይህንን የተቀደስ አላማ ለማክሸፍና የተጀመረውን ትግል ለመጨፍለቅ ሲባልም ወደ ሥልጣን ለመምጣት በጦርነት ማግዶ ካስጨረሳቸው የደሃ ልጆች በእጥፍ የሚበልጡትን መልምሎ በጸረ ሽምቅ ውጊያ ከማሰልጠን ጎን ለጎን ለግንባታ ቢውል ስንት ፋይዳ ሊያስገኝ ይችል የነበረ በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ድምጽ ለማፈንና ለመሰለል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ለአገራችን ሉአላዊነት ጠቀሜታው እስከዛሬ ምንም ባልታወቀ ጦርነት ወደ መቶ ሺ የሚጠጉትን ያስጨፈጨፈ፤ የተልዕኮ ጦርነት ለማካሄድ በመንግሥት አልባዋ ጎረቤት ሱማሌ እስከዛሬ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ወገን ያስፈጀ ፤ ለሥራ ፍለጋ ውትድርና የገቡትን ወጣቶች ለይቶ በሰላም አስከባሪ ስም በድንበር ዘለል ጦርነቶች እየማገደ ገንዘብ የሚቀበል፤ ስለአገርና ስለወገን ምን ሊገደው ይችላል?
ትናንት ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት የቀደምቶቹ መንግስታት ልጆቻቸውን ለትምህረት ወደ ፈረንጅ አገር እየላኩ የደሃውን ልጅ በጦርነት ይማግዳሉ በማለት በጅምላ ሲከስ የኖረ ዛሬ በተራቸው ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ዘርማንዘሮቻቸውን ታይቶ በማይታወቅ ብዛት ወደ ፈረንጅ አገር ለትምህርት እየላኩ ለነጻነታችንና ለክብራችን የምንታገለውን እርስ በርስ ለማጨራረስ ሲዶልቱ ዝም ብሎ መመልከት ከየትኛውም ቅን ዜጋ የሚጠበቅ አይሆንም።
ስለሆነም የበላይ አዛዦቻቸው በሚሰርቁት የሕዝብ ገንዘብ ፎቅ ላይ ፎቅ እየገነቡ ሃብት በሚያካብቱት አገር ሠራዊቱን እረፍት ለመንሳት ሆን ተብለው በሚቀሰቂሱት ግጭቶች ከአንዱ ማዕዘን ወደ ሌላው ማዕዘን ያለ ዕረፍት እየተንከራተተ ያለው የመከላኪያ ሠራዊት ፤ የፖሊስና የደህንነት ኃይል ለአገዛዙ አልታዘዝም በማለት ተገዶ ሥልጣን ለሕዝብ እንዲያስረክብ የማድረግ ወገናዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ግንቦት 7 የፍትህ የነትጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪውን ያቀርባል።
የግንቦት 7 መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የተጠማውን ፍትህ እኩልነትና ነጻነት በአገራችን ለማስፈን አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የጎጠኞችና የዘራፊዎች ስብስብ በማስገደድ ወይም በማስወገድ ሰላማዊ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህንን ደግሞ የሚፈሩት በሥልጣን ቱርፋትና በሃብት ዘረፋ የሰከሩ ብቻ ናቸው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

onsdag 29. januar 2014

የታመቀው የኢትዮጵያውያን ምሬት፡ የሕይወት ማሽቆልቆልና በፍርሃት መሽማቀቅ አፋጣኝ መፍትሄ ይሻል

January 29, 2014
ኢትዮጵያ በሕወሃት ዘመነ አመራር የታወቀችባቸው ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ብዙ “እንዴ!”የሚይሰኙ ጥሩ አሳቦችም ፈልቀዋል – አፈጻጸማቸው እትይለሌ ቢሆንም። ከነዚህም መካከል መሠረተ ልማት፡ በጤናና በትምህርት መስኮች መሻሻሎች መታየታቸው ወዘተ መልካም ይነገርላቸዋል – የቢል ጌትስን የራስ ተጠቃሚነትና ኢምፓየር ግንባታ ወደጎን ትተን! በዕጦት ደረጃም በሀገራችን የስብዓዊ መብቶች አለመክበር፣ የፍትህ አለመኖርና ለአብዛኛው ሕዝባችን የምግብ ዕጦት ዋና ዋና ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው።
Prime Ministers Katainen and Hailemariam (Credit: ERTA)
Prime Ministers Katainen and Hailemariam (Credit: ERTA)
ለምሳሌም ያህል፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 30 ስላማዊ ስልፍ የማድረግንና መንግስትን መቃወምን ግልጽ ቢያደርግም፡ እሁድ ዕለት የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን ለመሰጠት ለመቃወም: ለሚመለተው አሳውቀው ስላማዊ ስልፍ ለማዘጋጀት ተፍ ተፍ ሲሉ የአዘጋጁ የስማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት ጎንደር ውስጥ ተይዘው ታስረዋል። በተመሳሳይ መንገድ ትግራይ ውስጥም የአረና አመራሮች ሕዝቡን ቀሰቀሳችሁ በሚል ውንጀላ አዲግራት ውስጥ አመራሩና አባሎቹ ክፉኛ ተደብድበዋል – ጉዳት የደረሰባቸውም ሕክምና ለመሻት ተገደዋል። ይህንኑ አስመልክቶ፡ አንዱ ተደብዳቢ መምህር አብርሃ ደስታየሚከተለውን ጽፏል፡
    “ህወሓቶች በተግባራቸው ሊያዝኑ ይገባል። ህዝብን ፖለቲካ እንዲያውቅና ራሱ ከጭቆና እንዲከላከል ለማገዝ በምንሞክርበት ግዜ መንግስት ወደ ተራ የሽፍትነት ተግባር መሰማራቱ የሚያስደምም ነው … እኛ ለህዝብ ነፃነት ነው የምንታገለው። ትግላችን ሰለማዊ ነው። ወታደርና ፖሊስም የለንም። እኛ ያለን ህይወት ነው። ያለችንን ህይወት ለህዝብ ደህንነት ስንል መስዋእት አድርገናል። በህዝብ ፊት ተደብድበናል። በፖሊስና አስተዳዳሪዎች ፊት ተደብድበናል። እኛ መክፈል ያለብን ህይወትን ነው።”
ይህ በግልጽ የሚታየው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የስብዓዊ መብቶች አንጸባራቂ ሥዕል ነው። ይህ ሁኔታ በየቀኑ በተለያየ መልኩ ሀግሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለ የመንግሥት ሕገ ወጥነት ነው!
በኤኮኖሚው መስክ ያለው ችግር ግዙፍ ነው። ድህነት ከመቀረፍ ይልቅ፡ ሥር እየስደደ መሆኑን ብዙዎች ያማርራሉ። ለጥቂቶች ግን ሀገሪቱ ምድራዊ ገነት ሆናለች። ሕዝቡ እየተደበደበም፡ በየቀኑ አልዋጥ ባይ ፕሮፓጋንዳ በግድ እየተጋተ ነው!
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ለብዙዎቹ የአዲስ አበባ መሽቀርቀር እንደአጠቃላይ የሃገሪቱ የልማትና ዕድገት መለኪያ ተደርጎ እንዲወሰድ የተቀነባበረ ጥረት የሚድረገው። የምርጫ ዘመን በመቃረቡ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቅርቡ ስንዴ ለውጭ ገብያ ሻጭ ልትሆን ነው በማለት ጥር 18፣ 2014 አርሲ ሆነው ማስማታቸው ልብ ሊባል ይገባል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በልማት ገና ሀ ሁ … ላይ ናት – በምግብ 40 በመቶ የሚሆነውን ሕዝቧን በቀን ሶስቴ ሳይሆን፡ አንዴም መመገብ ያልቻለች አገር ናት! ይህ በመሆኑ አይደል እንዴ የምዕራቡ ዓለም፡ በቋሚነት ከ10 በመቶ በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ክዓመት ዓመት በዓለም አቀፍ እህል ዕርዳታ ሕይወት በመስጠት ላይ ያለው?
ከሁሉም ጎልቶ የሚነገርለትና የሕወሃት ስዎችም ቶሎ የሚስፈነጠሩበት የአገሪቱ ከትላልቅ ጦርነቶች መላቀቋ ነው። ስለዚህም የሕወሃት ስዎችና ደጋፊዎቻቸው በመመጻደቅ ሲናገሩ መስማቱ የተለመደ ሆኖአል። በዚህም መነሻነት፡ እንዲህ ይላሉ: ባለፉት 20 ዓመታት፡ ሕወሃት ለረዥም ዘመናት አገሪቱን ያደሙትን ጦርነቶች አቁሞ ልማት ላይ እንድታተኩር አደረገ የሚባለው በብዛት ይሰማል። የሕወሃት ስዎችም ይህ በተደጋጋሚ እንዲነገርላቸው ብዙ ጥረቶች አድርገዋል፡ እያደረጉም ነው። እራሳቸውም በተደጋጋሚ እራሳቸውን በዚህ ሲያሞካሹ ይሰማል፤ ለውጭ የፕሮፓጋንዳ ድርጅቶችም ይህንን እንዲያስተጋቡላቸው፡ ከፍተኛ ክፍያዎችን በየጊዜው ፈጽመዋል።
እስከዛሬ አጥግቢ ግንዛቤ ያላገኘው ግን፡ ድሮም ሆነ ዛሬ የጦርነቶች አጋጋይ ሕወሃት መሆኑ ነው። የኤርትራንና የትግራይን መገንጠል ጉዞ በተግባር ሲተረጉም ኖረ። ቀኑ ደርሶ ጅብሃ ሲገነጠል፡ ሕወሃት ባዶ የሥልጣን ወንበር ስለታየው፡ ኢትዮጵያዊነትን መረጠ። በትግል አጋሩ ጅብሃ ዘንድ ይህ እንደክህደት እንዳይታበት – በስላም ሂዱ፡ ኢትዮጵያ ከእናነተ ስላም እንጂ ሌላው ቀርቶ የባህር በር እንኳ አያስፈልጋትም አለ። ይህንን አስመልከቶ፡ በየካቲት ወር 1994 ስብሃት ነጋ ለዓለምስገድ አባይ በስጡት ቃለ መጠይቅ የሕወሃት ቀደምት ፓሊሲ መገንጠል ሆኖ እስክ 1985 መቆየቱን ያረጋግጣሉ። ከቃለ መጠይቁ ውስጥ በጣም አሰገራሚው ነገር ግን፡ ብዙ የሕወሃት ተዋጊዎች ኢትዮጵያዊነትን ገና ድሮ አሽቀንጥርረው የጣሉ በምሆናቸው፡ ዛሬም ቢሆን በተለይ ከአማራ ጋር ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኝትን በሙል ልብ አለመቀበላቸውን ነው ያመላከቱት [See Identity Jilted: Re-imagined Identity (1998)]።
ያለፈው አልበቃ ብሎ፡ ዛሬም ሕወሃት ሀገሪቱ ውስጥ ሽብርና ፍርሃት በማንገስ የውስጥ ግጭቶችን በመተንኮስ: የተለያዩ ብሄረስቦችን አባሎች በማፈናቀልና ችግሮችን በማባባስ ተጠቃሚ ለመሆን ሲምክር ይታያል – ድ/ር ቴድሮስ ፍጹም “እኔ ያለሁበት ፓርቲ ውስጥ ይህ አይደረግም!” ብለው ዝናቸውን አጋልጠው ቢገዘቱም። ነገሩ ግን፡ ዛሬም በምሥራቅ በተለያያዩ የኦሮም ክፍሎችና ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች መካከል፡ በደቡብም እንዲሁ በተለያዩ ጎሣዎች መካከል፡ አማራንና ኦርሞችን በማጋጭት፡ ጥላቻና መቃቃርን በዜጎች መካከል ለመፍጠር ብዙ ሲሞክር ቆይቷል። አንዳንድ ቦታዎችም፡ ለምሳሌ ቦረና፡ ተሳክቶለት ስሞኑን የብዙ ዜጎች ደም ፈሷል፤ ሕይወትም ተቀጥፏል። ቤት ንብረቶችም ተደምስሰዋል። ሌላው ቀርቶ፡ የሕክምና ባለሙያ የነበሩት የአገር አስተዳደር ሚኒስትሩ – የዛሬው የሃይማኖትች ጉዳይና የጸረሽብር ኤክስፐርቱ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም – ኬንያ በሥጋቷ ምክንያት (2012ን በማስታወስ) ልተቀስቅሳቸው ብትሞክርም፡ ነገሩ አውቆ የተኛ ቢነቀንቁት አይሰማ ሆኖ እሳችውም እንደክረምት ድብ ክፉኛ አሸልበዋል።
ለማንኛውም፡ በዓለም ላይ እንደሕወሃት የተሳካለት የለም – ዕድሉን ሃገራችንን ለማሻሻል በሚገባ አልተጠቀመበትም እንጂ! ስለሆነም ክሥራ ይልቅ ፕሮፓጋንዳ፡ ዕውነትን ተናግሮ ችግሮችን በጋራ ከመፍታት ይልቅ፡ ሁሉንም ስው ማሞኘት እንችላለን በሚል ትዕቢት ብዙ የሚያሳፍሩ ተግባሮች ሲያከናወን ይታያል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፡ በበጎነታችው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደጉን የሚመኙ የውጭዎቹ የፖለቲካ፡ የዲፕሎማሲና ኅብረተስባዊ መሻሻሎችን አራማጆች ይህንን የሕውሃትን የሰላም ማስፈን የዋህ መስል ቅጽል በአመኔታ የሚጋሩት በሁለት ተክፈለው ይታያሉ፡ –
(ሀ) በእውነትም ጦርነትና የንጹሃን ዕልቂት መቆሙን፡ ኢትዮጵያ ክድህነት ተላቅቃ ማየት የሚሹ ወገኖች፤
(ለ) ጊዘው የበለጸጉት ሃገሮች ወደታዳጊ ሀገሮች ውስጥ ዘልቀው በመስፋፋትና በኢኮኖሚ ትብብር ስም የራሳቸውን ኤኮኖሚያዊ፡ የበላይነት ማቆየት የሚሹበት፡ ፖለቲካዊና ስትራተጂካዊ ጥቅሞቻቸውን የሚያበራክቱበት በመሆኑ፡ ከላይ ከተጠቀሱት ጋር ተዳብረው፡ የሕወሃትን ገድል መተረኩ፡ ለሚሹት ዓላማ አንድ ጥቅም ትስስሮሽ መፍጠር የሚያስችል መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት ወገኖችም እዚሀ ውስጥ ተስልፈዋል።
ከላይ የተመለከቱት ከተለያየ አግጣጫ ተነስተው ሁለቱም አንድ የሚገናኙበት መጋጠሚያ፡ ስለኢትዮጵያ በጎ ነገር እንዲስተጋባ ማድረጋቸው ነው። በተለይም በሁለተኝው ክፍል የሚገኙት፡ በተቻለ መጠን ስለኢትዮጵያ በጎውን በማጋነን፡ የሕወሃትን የስብዓዊ መብቶች ጽልመት፡ ጎስኝነት፡ ሙሰኝነት የሚሸፋፍን አመለካከት በምዕራባውያንም ሆነ ምሥራቃዊ ሚዲያዎች ላይ በጊዜው ያስደስኮሩላቸዋል።
በተጨማሪም፡ እነዚህ ሀገሮች ለኢትዮጵያ ግዙፍ ዕርዳታ መፍሰሱን ይደግፋሉ። ነገር ግን ይህ ዕርዳታ በብዙ መስኮች – በተለይም በግብርናው – መስክ የሀገሪቱን ችግሮች፡ በምግብ ምርት እራስን ከማስቻል ይዘት ስሌለው፡ ትኩረታችውም ሆነ ጥረታቸው – በዘለቄታ ሀገሪቱን ከምግብ ዕርዳታ ተመጽዋች ነጻ ለማድረግ አላስቻለም። በመሆኑም፡ እየተደረገ ያለው፡ ትላንት እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ኢትዮጵያ አንድ ሶስተኛ መንግሥታዊ በጀቷን በዓለም አቀፍ ዕርዳታ ተመጽዋችነት ላይ የተመሰረተ ሆኖ የውስጥና የውጭ ፖሊሲዋን በማክራየት እንድትቀጥል አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮባታል።
በአሁኑ ወቅት፡ በተለያዩ ምክንያቶች (የስብዓዊ መብቶች አለመከበር ችግር፡ የየራሳቸው የሀገሮቹ የኢኮኖሚ ችግሮች) መንስኤነት፡ ከለጋሽ ሀገሮች በቀጥታ የሚገኝው ዕርዳታ በክፍተኛ ድረጃ ቀንሷል (ክአሜሪካና እንግሊዝ በስተቀር)። በዚህም ምክንያት የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚስጠውን ብዙውን የዕርዳታና ብድር ጫና ድርሻ ተሸካሚ ሆኖአል።
ለምሳሌ፡ ሌላው ቀርቶ ስብዓዊ ዕርዳታን እንኳ በተመለከተ፡ 12 የአውሮፓ ኅብረት ሀገሮች (እንግሊዝን አይጭምርም) በ2012 ለኢትዮጵያ በባይላተራል መንገድ ለዕርዳታ ያዋጡት €24 ሚልዮን ሲሆን፡ በ2013 ይህ መዋጮ ወደ €12.4 ሚልዮን ወርዷል። ከነዚህም መካከል ትልቁን ቅናሽ ያደረገችው ጀርመን ናት – ከ€8.2 ሚልዮን ወ €4.2 ሚልዮን ዝቅ በማድረግ። በመሆኑም፡ከዚህም ከዚያም አስባስቦ የበጀት ምንጮች በማስባስብና ተጨማሪ ምክንያቶች በመፍጠር (ነፍስ ወክፈ መልሶ ማቋቋም) በ2013 እንዳደረገው፡ የአወሮፓ ኮሚሽን በ 2011-2013 12 ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ለመርዳት እንዲቻል €130 ሚልዮን ለግሷል።
አሁን ለሁሉም ለጋሾች ከባድ የሆነው “የልማት” ዕርዳታውም እንዲሁ በበዙ ጥያቄዎች ላይ መውደቁ መሆኑ ይሰማል።
በዓለም ዙሪይ ያለፉው ሩብ ምዕተ ዓመት የልማት ጊዜ በመሆኑ፡ ብዙ ታዳጊ አገሮች ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆነዋል። ኢትዮጵያ ይህ ዕድል ቢገጥማትም፡ መሣሪያ ያነገቡት የሕወሃት ሰዎችና አጫፍሪዎቻቸው ግንባር ቀድም ተጠቃሚዎች የሆኑበት ሥርዓት በመዘርጋቱ፡ የትላንቱ ጦረኞችና የዛሬዎቹ የስላም ደጋፊ-መስል የአንድ ብኄረስብ ሰዎች፡ ሆን ብለው ዕኩልነትን የሚጻረር የፖለቲካ፡ የኤኮኖሚ፡ የደህንነትና ማኅበራዊ ፓሊስዎችን በኢትዮጵያ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
ይህ ግን ዘላቂ መሠረት ስሌለው፡ ዛሬ የኤኮኖሚው የጥንድ ዕድገት ውደሳው ጋብ ብሎ፡ ሀገራችን የመንግሥት ብልግናና የሃስት ፕሮፓጋንዳ ከሚመገቡት መካክል ወድቃለች። በዚሁም ምክንያት (ሽፋኑ የውሃ ዕጥርረት፡ ድርቀት፡ የሃይማኖትና የብኄረቦች አለመቻቻልና ግጭቶች ላይ ቢመካኝም)፡ ተደጋጋሚ ዓለም አቅፍ ጥናቶችኢትዮጵያ ከሚወድቁት የአፍሪቃአገሮች (Failed States) መካከል ተደምራ፡ የወደፊት ጽዋዋ አስፈሪ እንደሚሆን ቀንደኛ ደጋፊዎቿ ድምዳሜ ላይ መሆናቸውን በግልጽ የምንሰማበት ዘመን ላይ ደርስናል።
ድሮስ ቢሆን፡ የሕዝብ ዓመኔታ ያጣ መንግሥት፡ መሣሪያውን ደግኖ በኅይል ለመግዛት ከመሞከር ውጭ ምን አማራጭ አለው? ጊዜው የጥላቻ፡ የክፋትና የቂም በቀል በመሆኑ፡ በአንድ በኩል፡ የሕወሃት ስዎች ዘረፋ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፡ በሌላ በኩል ደግሞ፡ የኢትዮጵያውያንን ስብዓዊ መብቶች በመግፈፍና መርገጣቸውን በማባባስ፡ ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ጎዳን እየገፉ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ዕድገት ይኖራል?
እንዲያውም፡ የራሱን የአገዛዝ ዘመን ለማራዘም ሲል፡ የኢትዪጵያ ሕዝብ ፍላጎትና አመለካከት ሳይጠየቅ ኤርትራን በፊርማው እንድትገነጥል ያደረገ፡ አገሪቱን የባሀር በር ለማሳጣት የደፈረ የመንግሥታዊ ባህልና ኃላፊነትና ግንዛቤ የሌለው ሕወሃት፡ ለሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ቆርጦ ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆኑ ሕዝቡን በቃ! የሚል ድምዳሜ ላይ ማድረሱ አያጠራጥርም!
በዓለም ታሪክ ውስጥም ሕወሃት “ታዋቂ” የሚሆነው፡ ራሱን ሥልጣን ላይ ለማቆየት፡ የሀገርን ልኡላዊነትና መሬት ቆርሶ ለጎረቤት ሀገርና ለከፍተኛ ብድር ስጭና ገንዘብ ለዋጭ አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ ነው።
ዛሬም ሆነ ነገ፡ ለሀገራችን ዘላቂው መፍትሄ ግን መንግሥት የሕዝብን ፍላጎት ለማክበር መቻሉና ለዚህም ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት መዘርጋቱ ነው። ይህንን ለማድረግ፡ አሁንም ትንሽ የተስፋ መስኮት አለ – የሕውውሃት ስዎች ኃላፊነት የሚስማቸው ቢሁን። ይህ ለሕወሃትና ግብረአበሮቹ ተቀባይ ሳይሆን ቢቀር፡ ቀሪው ምርጫ ሕዝቡ እየተረገጠ መቀጠል፡ ወይንም እነርሱ ከመድረኩ መወገድ ነው።
እስካሁን በዚህ ድህረ ገጽ ይህንን አሳብ አላራመድንም ነበር። የሁኔታው አስከፊነት ግን አሁን የወቅቱ አስፈላጊ እርምጃ አድርጎታል!

tirsdag 28. januar 2014

ጌዜ መስታወቱ!! ተስፋዬ ገብረአብ ማነው? (ቁጥር ሁለት)

January 28, 2014
አለማየሁ መሰለ
ውድ አንባብያን፣ ይህ ጽሁፍ ከዚህ ቀደም ከዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ ጋር ተስፋዬ ገብረአብን አስመልክቶ አወጥተን ከነበረው ሪፖርት ጽሁፍ ተከታይ ነው። በዚህ መሰረት ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር አብረን ስንኖር እጄ ላይ ከወደቁትን መረጃዎች መሃከል የመጀመሪያው ጽሁፍ ተከታይ ይሆናል ብዬ የመረጥኳቸውን ቃል በገባሁት መሰረት ከነማብራሪያቸው አቀርባለሁ።
Tesfaye Gebreab Ethiopian author and writer
ተስፋዬ ገብረአብ
ለዛሬ የማቀርበው መረጃ ተስፋዬ ገብረአብ እንደ ሸፋን ከሚጠቀምበት የደራሲነት እና የጋዜጠኘነት ስራ ባሻገር ለማመን በሚያዳግት ይሰራ የነበረውን የወንጀል ድርጊት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ከዚህ በታች አባሪ ተደርጎ የተያያዘው በእጅ የተጻፈ መረጃ፣በእጄ ላይ ካሉ መረጃዎች መሃከል ትኩረቴን የሳበው ነው።እንደምትመለከቱት በራሱ በተስፋዬ ገብረአብ እጅ የተጻፈ ነው።ከሌሎች መረጃዎች ለየት የሚያደርገው ደግሞ፣እንደሌሎች መረጃዎች በፎቶኮፒ እጄ ላይ የቀረ ሳይሆን፣ዋናው (ኦርጅናል)መሆኑ ነው። ምክንያቱም በቀጥታ ወንጀል የተጻፈበት ሆኖ ስለታየኝ ነው።ከእጅ ጽሁፉ ላይ እንደምትመለከቱት፣መኩሪያ መካሻ ከተባለ ግለሰብ ጋር ድብቅ(ህቡእ) ስራ ለመስራት ጀምረው ነበር።እንደኔ ግምት የኤርትራ መንግስትን ጥቅም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስፈጽማል ብለው ያሰቡትን ተልእኮ ለመፈጸም አሲረው ነበር፡፡እንደ መረጃው ከሆነ መኩሪያ መካሻ የተባለው ግለሰብ ከፒያሳው ቦንብ ፍንዳታ በኋላ ፈርቶ ይሁን ሌላ ባይታወቅም፣ከተስፋዬ ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጧል።የፒያሳው የቦንብ ፋንዳታ ብሎ የተገለጸው ደግሞ ሌላ ሳይሆን በ2002 እኤአ በትግራይ ሆቴል ላይ የደረሰው ፍንዳታ ነው።
የእጅ ጽሁፉን ሙሉ ይዘትና ለአንባቢ ይመች ዘንድ የተየብኩትን ይመሳከር ዘንድ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።[ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]

በእውነት ወያኔ የተረከበው የፈራረሰ አየርሃይል ነበርን? አየር ሃይልስ እንዴት ተያዘ?

January 28, 2014
ፋንታ በላይ
MiG-23 Flogger Tactical Fighter
MiG-23 Flogger Tactical Fighter Jet
የስነ ስሁፍ ሰው አይደለሁም:: ይህንን ስሁፍ እንድጽፍ ያስገደደኝ ግን በኢትዮጳያ ቴሌቪዝን አየር ሃይልን በተመለከተ የተላለፈው ዜና ነው:: በዚሁ ዜና ላይ ያሁኑ አየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ሃላፊ ኮሎኔል አስፋው ማመጫ በ 1983 ሰለነበረው አየር ሃይል ሲያስረዱ ” በ1983 የተረከብነው የደከመ የፈራረሰና የወደቀ አየር ሃይል ነበር” [i] በማለት እጅግ አስቂኝና ከውነት የራቀ መግለጫ ሰተዋል:: አዲሱ ትውልድ ስለቀደመው አየር ሃይል እውነት ጥቂትም ቢሆን ያውቅ ዘንድና አየር ሃይሉ ምን ይመስል እንደነበር እንዴትስ እጅ እንደሰጠ በጥቂቱ ልጽፍ ወደድኩ::
በመጀመርያ ወያኔ አየር ሃይሉን ሲረከብ ምን እንደሚመስል እንመልከት
1. የውጊያ የስለላና የትራንስፖርት አውሮፕላኖች
ወያኔ ግንቦት 1983 አየር ሃይሉን ሲቆጣጠር አየር ሃይሉ በበርካታ ዘመናዊ አውሮፕላኖች የታጠቀ ነበር:: በውጊያ አውሮፕላኖች ዘርፍ ሚግ 23 : ሚግ 23 ፍሎገር እና ሚግ 21 የተባሉ ሱፐር ሶኒክ የአየር ለአየርና ያየር ለምድር ተዋጊ ጀቶችን ( ሚግ 23 ማክ 3 ነው:: ይህም ማለት ከድምጽ ፍጥነት ሶስት ግዜ ይፈጥን ነበር) የታጠቀ ነበር:: ሚ 24 (ነጮቹ flying tank ይሉታል) እና ሚ 35 የተባሉ ከጠላት ጋር እየተናነቁ መዋጋት የሚችሉ ሄሌኮፕትሮችም የአየር ሃይሉ ንብረቶች ነበሩ:: ሚ 35 ከጠላት የሚተኮስበትን ጸረ አየር ሊከላከልና አቅጣጫ ሊያስቀይር የሚችል እስከ 12 ጸረ ታንክ ሚሳኤሎችን መታጠቅ ይችላል:: በግዜው ( 1970 ዎቹ መጨረሻ) ሚግ 23 ፍሎገርና ሚ 25 ሄሌኮፕተሮችን የታጠቀች የመጀመርያዋ ሰብ ሰሃራ ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች::
በትራንስፖርቱም በኩል ወያኔ አየር ሃይሉን ሲረከብ አየር ሃይሉ አንቶኖቭ(Antonov 12,22,260) : ሲ- 130 እና ቲ ዩ( TU) የተባሉ ዘመናዊ የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ነበሩት:: አንቶኖቭ ከትራንስፖርት ጠቀሜታው ሌላ በርካታ ቦንቦችን ጭኖ ውጊያ ላይ መሳተፍም የሚችል ሶቪየት ሰራሽ አውሮፕላን ሲሆን ሲ 140 ም ተመሳሳይ አገልግሎትን የሚሰጥ አሜሪካ ሰራሽ አውሮፕላን ነው:: ቲ ዩ የተሰኘው አውሮፕላን ደግሞ የአገሪቱ ርእሰ ብሔር ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ልዩ የትራንስፖርት ጀት ነው:: ወያኔ የደብረዘይቱን የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና ቤዝ ሲቆጣጠር በነዚህ ሁሉ የውጊያና የትራንስፖርት አውሮፕላኖች የተደራጀን አየር ሃይል ነበር የተረከበው::
በቁጥር መልኩ ሲተነተን አየር ሃይሉ በጠቅላላው 112 ሚግ 21 ተዋጊ ጀቶች: 37 ሚግ 23 የአየር ለአየርና የአየር ለምድር ተዋጊ ጀቶች: 15 ሚግ 17 : 20 አንቶኖቭ 12: 18 አንቶኖቭ 26 : 5 አንቶኖቭ 22: አስራ ሱኮይ ሰባት ጀቶች: አርባ ሶስት ሚ 8 እና ሰላሳ ሚ 24 ተዋጊ ሄለኮፕተሮች ነበሩት:: ከነዚህ ውስጥ ወያኔ ደብረዘይትን ሲቆጣጠር በርካቶቹን ተረክቧል::
2. አየር መቃወሚያና የስለላ ራዳሮች
ከአየር ሃይሉ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የኢትዮጵያን ያየር ክልል ለመጠበቅ የተቋቋመው ሌላው ክፍል ደግሞ አየር መከላከያ ነበር:: ወያኔ በ 1983 የደብረዘይትን ኤር ቤዝ ሲቆጣጠር አየር መከላከያ እጅግ ዘመናዊ በሆነ ራዳርና ሚሳኤሎች የተደራጀ ነበር:: በተለይ ቮልጋ ፐትቼራና ስትሬላ ( Volga, Petchera, stinger, SAM) የተባሉ በርካታ የአየር መቃወሚያ ሚሳ ኤሎችን የታጠቀ ነበር::ግንቦት 1983 ወያኔ አየር ሃይሉን ሲይዝ ሙሉና የተደራጀ አየየር መከላከያን ነበር የተረከበው:: የሚደንቀው እሰከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ የአየር መቃወሚያ ባለሙያዎች አገሪቷ ላይ ያለ የውጭ ሀገር ጀቶች እንዳይገቡ የሙያ ግዴታቸውን ሲወጡ ነበር:: ወያኔ ሲገባም ሙያቸው ያገሪቱንያየር ድንበርን ማስጠበቅ እንደሆነና ወያኔም ስለአየር መቃወሚያ ሚሳኤሎቹ ግንዛቤ እስኪያገኝ ድረስ ክፍሉን እንዳይበትናቸውና በመሃል የጠላት ሀገር ጀቶች ገበተው ኢትዮጵያን እንዳይጎዷት ለወያኔው የጦር አዛዥ ግንቢት 1983 ወያኔ አየር መከላከያን እንደያዘ ወዲያ እዛው ግቢ ውስጥ ጥያቄ አቅርበውለት ነበር::
3. የጥገገናና የድጋፍ ሰጭ ክፍሎች
ለነዚህ አውሮፕላኖችና ሚሳኤሎች ጥገናና አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ደጋፍ ሰጭ ክፍሎችም ነበሩት:: ተዋጊ ጀቶች : ሄሌኮፕተሮችና ትራንስፖርት አውሮፕላኖች የሚጠገኑበት በርካታ ሃንጋሮች ወያኔ ሲገባ አብሮ የተረከባቸው የአየር ሃይሉ አካላት ናቸው:: እነዚህ የጥገና ሃንጋሮች ወያኔ ገብቶ እስኪረከባቸው ድረስ ሙሉ ነበሩ:: አንዲትም ብሎን እንኳን አልተነካችም ነበር:: ከዚህም ባሻገር የአውሮፕላን ስፔር ፓርቶችን ሞዲፊክ የሚሰሩ አሰደናቂ ማሽን ሾፖችም እና ውድ ወርክ ሾፖችም የአየር ሀይሉ ስውር አካላት ነበሩ:: እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ በተለይ ማሽን ሾፕ በርካታ የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን በሞዲፊክ ይሰራ ነበር:: ወያኔ በ1983 ሲገባ የተረከበው እነዚህን ሙሉ ሀንጋሮች ጭምር ነበር::
4. የሰው ሃይል ማሰልጠኛ ኮሌጆች
እነዚህን ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎንና ተዋጊዎችን የሚሰለጥኑበት የሁለት ድንቅ ኮሌጆችም ባላቤት ነበር – ወያኔ የተረከበው የኢትዮጵያ አየር ሃይል:: የመጀመርያው የበራሪዎች ማሰልጠኛ ኮሌጅ ሲሆን ሁለተኛው በተለምዶ ግራውን ስኩል በመባል የሚታወቀው የግራውን ቴክኒሻን ማሰልጠኛ ኮሌጅ( ground technician college) ነው:: እነዚህ ሁለት ኮሌጆች በጊዜአቸው በአፍሪካ አሉ ከሚባሉ ማሰልጠኛዎች የሚጠቀሱ ነበሩ:: ራሺያና ሌሎች ሀገራት ሰልጥነው የሚመጡ ተማሪዎች እንኳን ስራ ከመጀመራቸው በፊት እነዚህ ኮሌጆች ውስጥ ገበተው መፈተን ነበረባቸው::አየር ሃይሉ በነዚህ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የታነጹ የባለሙያዎችና የተዋጊዎች መናሃርያ ነበር::ወያኔ ሲገባ የተረከበው እነዚህን ኮሌጆች ጭምር ነበር::
5. ማህበራዊ ተቋማትን በተመለከተ
የሰራዊቱን አካላት ለመደገፍ ይረዳ ዘንድ በርካታ ተቋማት በአየር ሃይሉ ውስጥ ነበሩ:: የሰራዊቱ አባላት ከራሳቸው ደሞዝ እየተቆረጠ ስራው የተጀመረ እጅግ ዘመናዊ ሆስፒታል ነበር:: የሰራዊቱን አባላትም ከስውር የገበያ ጥቃት ( የተመረዘ ምግብ ) ለመሰወርና ለመከላከል ኮሚሴሪ በመባል የሚታወቅ የህብረት ስራ ንግድ ማዕከል ነበር:: ይህ ድርጅት የተለያዩ የፍጆታ እቃዎችን ለአየር ሃይሉ አባላት በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ሃላፊነት ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ ራስ አገዝ ( economic cooperative) ሲሆን ሁለት የመዝናኛ ክበቦችም ( ኦፊሰርስ ክለብ እና ኤ ን ሲ ኦ ክበብ) ነበሩት:: በግዜው በከተማው ብቸኛ ፊልም ቤትም የነበረው አየር ሃይሉ ብቻ ነበር:: ያየር ሃይሉ እና አየር ወልድ አባላትም ሲያርፉ ሬሳቸው በከብር የሚያርፍበት እጅግ ያማረና በወታደራዊ ዘቦች የሚጠበቅ የመቃብር ቦታ በደብረ ዘይት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስትያን ተከልሎ ነበር:: ይም መቃብር የጦሩ የክብር መቃብር ስለነበር ከአየር ሃይልና ከአየር ወለድ ውጭ ማንም አይቀበርበትም ነበር:: ወታረዶችም ተመድበውለት ይጠበቅ ነበር:: እጅግ በጣምም ያማረና ማራኪ ቦታ ነበር::
6. የሰው ሃይል
የሰው ሃይልም ደረጃ አየር ሃይሉ ከ 6 እሰከ ሰባት ሺህ የሚደርሱ ባለሙያዎች ነበሩት:: እነዚህ ባለሙያዎች በአሜሪካ : ሩስያ: ሰሜን ኮርያ : ቼኮስላቫኪያ: እስራ ኤል ወዘተ የሰለጠኑ ብቃት ያልቸው ብሔራዊና አለማቀፋዊ ምሁራን ነበሩ:: ይህም ሰራዊት ወታደራዊ መኮንንኖችንና ሲቪል ባለሙያዎችን ያካተተ ነበር:: በርካቶቹ አባላት የአቪዬሽን መሃንዲሶች: የጥገና ባለሙያዎች : የአየር ላይ intellegence አማካሪዎች ነበሩ::
ወያኔ ሀሜን ሲቆጣጠር ( ሀሜ ሀረር ሜዳ ማለት ሲሆን ደብረዘይት የሚገኘው ያየር ሃይሉ ዋና ጣብያ ሀሜ ይባል ነበር:: ) የተረከበው እነዚህን ሁሉ ነው:: በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጊያና የትራስፖርት አውሮፕላኖች: በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳ ኤሎች: ሁለት ትልለቅ ስቴዲየሞች: የአየር ሃይል ቁጠባ ባንክ: ያያር ሃይል ሆስፒታል: ሁለት ዝነኛ ያይር ሃይል ማሰልጠኛ ኮሌጆች : ራዳሮችና ከ ስድስት እሰከ ሳባት ሺህ የሚቆጠሩ ያያር ሃይል ባላሙያዎችን ነበር::
ያሁኑ አየር ሃይል ኢንፎክትሪኔሽን ሃላፊ ኮሎኔል አስፋው ማመጫ ” የተረከብነው አየር ሃይል የተዳከመ የፈራረሰ እና የወደቀ አየር ሃይል ነበር” የሚለው መግለጫ በፍጹም ህሰትና ከውነት የራቀ ነው:: ኮሌኔሉ ወይ አየር ሃይሉን አያውቀውም ነበር ወይ ደግሞ አድር ባይነት ያጠቃው ይመስላል:: እውነትን እውነት ማለት ግን ጅግንነት ነበር:: የሚደንቀው ግን አያር ሃይሉን ያወደመውና የበታተነው ራሱ ወያኔ መሆኑ ነው:: ይሄንንም ያይን እማኝነቴን ከዚህ በታች እገልጸዋለሁ:: በመጀመርያ አየር ሃይል እንዴት ተያዘ?
ኣየር ሃይል እንዴት በሰላም እጁን ሰጠ?
እግረኛው የጦሩ ክፍል እየሸሸ በመጣባቸው ቦታዎች የወያኔን ጉዞ ለመግታት ከፍተኛ ውጊያ ሲያደርግ የነበረው አየር ሃይሉ ነበር:: ይሄን ወያኔ አሳምሮ ያውቀዋል:: በተለይ ሄሌኮፕተሮችና ተዋጊ ጀቶች እጅግ በርካታ ግዜ በመመላለስ ከእግረኛ በከፋ ሁኔታ ተዋግተዋል:: በተለይም ወያኔ ነጻ አወጣሁ በሚላቸውና የኢትዮጵያ ሰራዊት በሌለባቸው ቦታዎች ላይ ብቸኛው ተዋጊ አየር ሃይሉ ነበር::
እንደ አየር ሃይልም እንደ እግረኛም ታች ድረስ በመውረድ ፓይለቶቻችን ሰፊ መስዋትነት ከፍለዋል:: በስተመጨረሻም ወያኔ የደብረ ዘይትን አየር ሃይል ሊይዝ ውጊያ ሲያደርግ ከፍተኛ እልቂት እንደሚደርስ ተፈርቶ ነበር:: ጨፌ ዶንሳ ( ከደብረ ዘይት ወጣ ብሎ የሚገኝ ቦታ ነው) ላይ እጅግ አስከፊና ደም እንደውሃ ያፋሰሰ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ የወያኔ ጦር ወደ ኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና ቤዝ ወደ ደብረ ዘይት ሲገባ አየር ሃይሉ በሁለት ሃሳብ ተከፍሎ ነበር::
የመጀመርያው ” የአየር ሃይልን ግቢ እንዲሁ አናሲዝም እስከመጨረሻው እንዋጋለን:” የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “ደብረ ዘይት ላይና አየር ሃይል ግቢ ውስጥ ባለን መሳርያ ውጊያ ከጀመርን የሚወደመው ሀገሪቷ ለበርካታ ዘመናት የገነባችው አየር ሀይልና በውስጡ ያሉት የአቪዬሽን ባለሙያዎች : መሳርያዎች ይበልጡኑ ደግሞ የደብረ ዘይት ሕዝብ ስለሆነ አየር ሃይሉ ግቢ ውስጥ ባንዋጋ ይሻላል” የሚል ነበር:: በስተመጨረሻም ከተማው ውስጥ እንዳይገቡ ከፍተኛ ውጊያ እንዲደረግና ከተማው ውስጥ ከገቡ ግን በተለይም የአየር ሃይል ግቢ ውስጥ ውጊያ መግጠሙ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ስምምነት ላይ ተደረሰ:: በተለይ አየር ሀይሉ ግቢ ውስጥም የሚከፈተው የጅ በእጅ ውጊያ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ስምምነት ላይ ተደረሰ::
ይህም ምክንያቱ አንደኛ አየር ሀይሉ ውስጥ ተከዝነውና ተከማችተው ያሉት መሳርያዎች ይልቁንም ናፓልና ክላስተር ቦምቦች ቢመቱ ከተማዋ በሙሉ ልትጠፋ ትችላለች የሚል ሲሆን: ሁለተኛው ደግሞ አየር ሀይሉ ግቢ ውስጥ ያሉት በርካታ አገሪቱ በዲፕሎማሲና በከፍተኛ ወጭ ለሃምሳና ስልሳ አመት የገነባቸው ያቪዬሽን ቴክኖሎጂ ይወድማሉ የሚል እሳቤ ስለነበር ነበር:: ይሄንንም ተቋም ሀገሪቱ መልሶ ለመገንባት ሌላ ስልሳ አመት ይፈጅባታል:: በዚህ መሃልም የጠላት አየር ሀይል እንደፈለገው በኢትዮጵያ አየር ክልል ውስጥ ሊፈነጭ ይችላል የሚል ነበር:: ከተማዋን ከውድመት ለመታደግና አየር ሃይሉን ከጥፋት ለመታደግ አየር ሃይል ግቢ ውስጥ ወጊያ እንዳይካሄድ ስምምነት ላይ ተደረሰ:: ደብረ ዘይት ዙርያ በተለይ ጨፌ ዶንሳ : የረር ላይ ከፍተኛ ትንንቅ ተካሄደ:: በውስጥ አዋቂና ባንዳ ይመራ የነበው ወያኔ ግን ሳይታሰብ ሾልኮ ደብረዘይትን ተቆጣጣረ:: አየር ሀይልም እንደቀልድ በሰላም ተያዘ::
አስደናቂውና ወደር የለሹ በቀል _ ወያኔና አየር ሃይሉ
ወያኔ አገረቱን ከተቆጣጠረ በኋላ አየር አየር ሃይሉን ላገሪቷ ጥቅም ይጠቀምበታል የሚል እሳቤ ነበር:: ቢያንስ ፓይለቶቹንና ወታደራዊ መኮንንኖቹን ባይቀበል እንኳን ሲቪል እና የሙያ ሰዎች የሆኑትን አረጊቷ በከፍተኛ ወጭ ያሰለጠነቻቸውን የበረራ መሃንዲሶችና ሌሎች ባለሙያዎችን ይበትናል ተብሎ አልታሰበም ነበር:: ምክንያቱም እነዚህ አካላት አውሮፕላኖችንን ከመጠገን : ስፔር ፓርቶችን ከማምረትና ስለ አቪዬሽን ከማስተማር ውጭ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ውስጥ ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸው ንጹህ ሲቪል ባለሙያዎች ነበሩ::
ወያኔ አየር ሀይሉን ያለምንም ውጊያ ከያዘ በኋላ የመጀመርያ ስራው ማፍረስ እና ማፈራረስ ሆነ:: አየር ሃይሉ እንደሀገር ንብረት ሳይሆን በሚገርም ሁኔታ እንደጠላት ጠላት ንብረት ታይቶ ተበዘበዘ:: እጅግ በከባድ ወጭ ተገዝተው የተተከሉ ማሽኖች በሙሉ ከአየር ሃይሉ እየተፈቱ ተጫኑ :: በትልልቅ መኪኖችም እየተጫኑ በሌሊት ይጓዙ ጀመር:: በተለያየ ሀገር ተምረዉ ( ከምስራቁም ከምራቡም ዓለም) ከፍተኛ ያቪዬሽን እውቀት የነበራቸው የበረራ እና የአውሮፕላን ጥገና መምህራን እየታደኑ ጦላይና ብላቴ ታሰሩ:: ቀላል ቁጥር የሌላቸው ባለሙያዎች በጦላይና ብላቴ በረሃ በወባና ኮሌራ አለቁ::ይህም የተደረገው ሆን ተብሎ ነበር:: ጥቂት የማይባሉትንም ፓይለቶች ወያኔ እያደነ አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ ገደላቸው:: በተለይም ባይኔ ያየሁት የኮለኔል ጥላሁን ግድያ የማይረሳ ነበር:: በአየር ሃይሉ ውስጥ የሚገኘውንም የአየር ሃይል ቁጠባ ባንክ በዝርፊያ የተካነው ወያኔና ጀሌዎቹ ዘረፉት:: ያሁሉ ያየር ሃይል አባልና ቤተሰቡ ያለደሞዝና ጡረታ ንብረቱ ተዘርፎ ተበተነ:: ተራው የወያኔ ወታደርም የበርካታ አውሮፕላኖችን መስታውታቸውን በመሰበር እና ውስጣቸው ያሉትን የተለያዩ ሲስተሞችን በስለትና በብረት በጣጠሱት::በድንጋይ አውሮፕላን ማረክን እያሉም ዘፈኑ:: የአየር ሀይሉ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሚገኙ ልዩ ልዩ የስለላ ሚስጥሮችን : መዛግብትንና የጦሩ መረጃዎችን እንደቀልድ በተኗቸው:: ያየር ሀይሉን ማሰልጠኛ ትምርት ቤቶችና ቤተ መጻህፍት ዘበዙት:: ማንም ተራ ወታደር ቤተ መጻሕፍት ገብቶ መጽሃፍ መዝረጥ እያደረገ ማንደድና እሳት መሞቅ ይችል ነበር:: መጻሕፍቶቹ የሚያወጡት ዋጋ ; የያዙት ቁም ነገር ለነሱ ትርጉም አልነበረውም:: ምናልባትም ጀቶቹ በራሳቸው ድንገት የሚነሱ እየመሰላቸው ይመስላል : በከፍተኛ ወጭ የተገነባውን የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ በታንክ ሄዱበት :: ኮሚሴሪው : ክበባቱ: ሆስፒታሉ በሙሉ የጨፍጫፊው አየር እየተባለ ብትንትኑን አወጡት:: አየር ሃልን አፈረስነው እያሉ ደስታቸው ወሰን አጣ:: የሚደንቀው ግን አየር ሃይሉ ግቢ ውስጥ ከወያኔ ጋር አብረው ገብተው በርካታ እቃዎችን እየመረጡ ሲያስጭኑ የነበሩት ሱዳኖችና ወደ ሱዳን መሆኑ ነው::
ነገር ግን የቀድሞው ያየር ሃይል ሰራዊቱ አባላት ወያኔ የቀድሞውን ሰራዊት ባያምን እንኳን የራሱን የሚያምናቸውን ሰው እንኳን አሰልጥኖ የኢትዮጵያን ያየር ክልል ያስጠብቅ ዘንድ በርካታ ተማጽኖዎች ያደረጉለት ነበር:: ያይር ሃይሉን እንዳልሆነ ሆኖ መመዝበር የሰሙት እስር ላይ ያሉ መኮንንኖችም በየግምገማው ወቅታ( ግምገማ እያሉ በየግዜው ይሰበስቡን ነበር) ያሰሙ የነበረው ለቅሶ ለነሱ ሳይሆን ላየር ሃይሉ ነበር:: እነሱን ባያምን እንኳን የኔ የሚላቸውን ሰዎች አሰልጥኖ አገሪቱ አየር ሃይል አልባ እንዳትሆን እንዲያደርጋት ከፍተኛ ተማጽኖ ነበር::
ወያኔ ወደ ልቡ ሲመለስ “የራሴን አየር ሃይል ማሰልጠን አለብኝ ” በማለት አየር ሃይሉን ከማፍረስ እንቅስቃሴው ተገቶ ስለ ስልጠና ማሰብ ጀመረ:: የተወሰኑ የቀድሞ አየር ሃይል አባላትን በመመለስም ስራዎች እንዲጀመሩ ሆነ:: ነገር ግን ወያኔ ለፓይለትነትና ለተዋጊነት እንዲሰለጥኑለት የሚፈልጋቸው ወታደሮች ትንሽ እንኳን ዘመናዊ ትምህርት ያልቀመሱ ለአስራ አምስትና ከዛ በላይ አመት ግዜያቸውን በበረሃ ላይ ያሳለፉ ትምርት ለመቀበል እድሜያቸው የገፋ ስለሆነ ሌላ ችግር ነበር:: ከሁሉም በላይ አሰልጣኞቻቸውንና አስተማሪዎቻቸውን የማይሰሙ እብረተኞች ሰለነበሩ በርካታ አውሮፕላኖች እየተከሰከሱ አለቁ:: በዘጠናዎቹ ብቻ ከ 13 የማያንሱ አውሮፕላኖች ወድቀዋል:: ይሄ ባየር ሃይሉ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ነበር :: በተለይ ሞጆ ገበያ ላይ የተከሰከሰው አወሮፕላን አይረሳም::
የሻቢያ ወረራ
ወያኔና ሻቢያ የጫጉላ የፍቅር ግዜያቸው ሲያልቅ ጦርነት ከፈቱ:: ወያኔም ሻቢያ ወረረችኝ አለ:: በሚያሳዝን ሁኔታ ተራ ፓይለት በተራ አውሮፕላን ትግራይን ያውም የህጻናት ትምርት ቤትን ባሰቃቂ ሁኔታ ደበደበ:: ከጣልያን በኋላ ያየር ክልሏ ተደፍሮ የማታውቀው ኢትዮጵያ ያየር ክልሏ ተደፍሮ በጀት ተደበደበች:: ወያኔ ግራ ገባው:: ሰባት አመት ሙሉ ያለ ደሞዝና ጡረታ በትኖ በረሃብ ሲቆላው ለከረመው ለኢትዮጵያ አየር ሃይል አባላት ጥሪ አቀረበ:: ለባንዲራውና ላገሩ ቃል የገባው ሰራዊት ግን ቂም ይዞ ጥሪውን እምቢ አላለም:: ሁሉንም ይቅር ብሎ በሚገርም ሁኔታ አየር ሀይሉን ድጋሚ አነሳው::
ሲጠቃለል ወያኔ የተረከበው አየር ሃይል የፈረሰ : የወደቀና የደከመ አየር ሃይል አልነበረም::የተረከበው ሙሉና ብቁ የሆነ አየር ሃይልን ነበር:: አየር ሃይሉን እንደጠላት ንብረት ያፈርሰውና ያረሪቱን አቪዬሽን ወደ ኋላ የጎተተው ራሱ ወያኔ ነው:: የአየር ሃይል አባላትን እንደ ሰው ሳይሆን እንደማርያም ጠላት ተጫውቶበታል:: የአየር ሃይል አባላት ገንዘብ ያጠራቅሙበት የነበረውን የቁጠባ ባንክ ዘርፎ የአያር ሃሉን አባላት ንብረትዘርፎ ያየር ሃይሉን አባላት ቤተሰብ በሙሉ ከድህነት በታች በማድረግ ከባድ ወንጀል የፈጸመው ወያኔ ነው:: ስንቱን ምሁር የበተነው ወያኔ ነው:: አየር ሃሉን እንደጠላት ንብረት ሙጥጥ አድርጎ የዘረፈውም ወያኔ እንጂ ሰራዊቱ አንዲት ብሎን እንኳን ሳትጎል ሙሉ አየር ሃይል ነበር ያስረከበው::
እንዲህ አይነት ከባድና አሰቃቂ ውንጀል ፈጽሞም ወረራ ሲመጣና ዳግም ጥሪን ሲያቀርብ የቀድሞው ጦር አባላት እምቢ አላሉም:: ምንም አይነት ቅሬታ ሳይሰማቸው ወደ አየር ሃሉ በመመለስ ወያኔ እንክትክቱን ያወጣውን አየር ሃይል ዳግም አቆሙት:: የሚገርመው ወያኔ ግን 7 up እያለ ያላግጥባቸው ነበር:: ( ከሰባት አመት በኋላ ወደ ስራ ስለተመለሱ):: በመሃልም ያለምክንያት በፈለገው ወቅት እየተነሳ ስንቱን ፓይለቶች ይጨርስ ነበር:: እነ ሻለቃ ዳንኤል ነፍስ ይናገር::
እናም እነ ኮሎኔል አስፋው
ባጭሩ ታሪክን መበረዝና መመራዝ ለማንም አይጠቅምም:: ወያኔ የተረከበው ሙሉና ብቁ የሆነ አየር ሃልን ነው:: አየር ሃይልን እንደጠላት ንብረት የዘረፈውና ያወደመው ራሱ ወያኔ ሲሆን እንደገናም ወያኔ ያወደመውን አየር ሃይል መልሶ ያቋቋመው ያው የጥንቱ አየር ሃይል አባላት መሆናቸው አይዘንጋ:: እውነት እውነት ናት::
በዚህ አጋጣሚ የምፃፍ ችሎታው ያላችሁ ይሰራዊቱ አባላት ለሚመጣው ትውልድ ያለውን እውነት ጽፋችሁ ብታስቀምጡት መልካም ስለሆነ ጥሪዬን አቀርባለሁ

“የኢትዮጵያ ፓርቲዎች የሃቀኝነት ጥያቄ ይነሳባቸዋል”

ለ46 ዓመታት በፖለቲካ ትግል ውስጥ እንደቆዩ የሚናገሩት የ70 ዓመቱ አዛውንት የቀድሞ የኢፌዲሪ ኘሬዚዳንት ኋላም
የተቃዋሚው አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ በቅርቡ ከፓርቲ-ፖለቲካ ራሳቸውን አግልለዋል።
ዶ/ር ነጋሶ፤ ለምን ከአንድነት ፓርቲ ለቀቁ? ስለተቃዋሚዎችና ስለኢህአዴግ ምን ይላሉ? በስጋት ስለሚኖሩበት
የመንግስት ቤት ጉዳይስ?
በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ብሥራተ ገብርኤል በሚገኘው መኖሪያ
ቤታቸው አግኝቶ  በስፋት አነጋግሯቸዋል፡፡
በስጋት ነው የምኖረው መውደቂያዬን አላውቀውም
እኔ የታገልኩት ቁስ ለመሰብሰብ አይደለም
ታጋይ እንጂ ዲኘሎማት አይደለሁም
ለ46 ዓመታት በፖለቲካ ትግል ውስጥ እንደቆዩ የሚናገሩት የ70 ዓመቱ አዛውንት የቀድሞ የኢፌዲሪ ኘሬዚዳንት ኋላም የተቃዋሚው አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ በቅርቡ ከፓርቲ-ፖለቲካ ራሳቸውን አግልለዋል። ዶ/ር ነጋሶ፤ ለምን ከአንድነት ፓርቲ ለቀቁ? ስለተቃዋሚዎችና ስለኢህአዴግ ምን ይላሉ? በስጋት ስለሚኖሩበት የመንግስት ቤት ጉዳይስ? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ብሥራተ ገብርኤል በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አግኝቶ በስፋት አነጋግሯቸዋል፡፡ በስጋት ነው የምኖረው መውደቂያዬን አላውቀውም እኔ የታገልኩት ቁስ ለመሰብሰብ አይደለም ታጋይ እንጂ ዲኘሎማት አይደለሁም ለምንድነው የፓርቲ-ፖለቲካ በቃኝ ያሉት? አንደኛው፤ የእድሜ ጉዳይ ነው፡፡ ጳጉሜ 3 ቀን 2005 ዓ.ም 70 ዓመት ሞልቻለሁ፡፡ ለ46 ዓመት ያህል በቀጥታ ህይወቴን ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር አቆራኝቼ ኖሬያለሁ፡፡ አሁን ይበቃል የሚል ስሜት አደረብኝ፡፡ ከአሁን በኋላ ለወጣቶች ቦታውን መልቀቅ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በኔ በኩል የተቻለኝን ያህል በፓርቲ-ፖለቲካ ውስጥ አገልግያለሁ፡፡
አሁን ይበቃኛል፡፡ ይህን ስል ትግሉን አቆማለሁ ማለቴ አይደለም፡፡ ሁለተኛ፤ የጤንነት ጉዳይ ነው፡፡ የስኳር ህመምተኛ ነኝ፡፡ በክኒን ነው የምኖረው፡፡ የደም ግፊትም አለብኝ፡፡ እንደልቤ መንቀሣቀስ አልችልም፡፡ በሊቀመንበርነት ከመሩት “አንድነት” ፓርቲ ጋር ስላለዎት የአመለካከት ልዩነት ይንገሩን? ለእኔ ከፓርቲ-ፖለቲካ መገለል ከላይ ከጠቀስኳቸው ምክንያቶች በበለጠ ይሄኛው ዋናው ምክንያቴ ነው፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ሊደረግ በታቀደ ጊዜ፣ በአመራር ውስጥ መግባት የሚፈልጉ እንዲወዳደሩ ብለን ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ለሊቀመንበርነትም ሆነ ለብሔራዊ ምክር ቤት ለመወዳደር አልፈለግሁም። ያልፈለግሁበት ምክንያት ደግሞ እኔ ወደ አንድነት የመጣሁት በመድረክ ምክንያት ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ በፈጀ ውይይት ነው መድረክ የተመሠረተው፡፡ መጀመሪያ መድረክ ወደ ጥምረት ሲሸጋገር ድርጅቶች ናቸው ተስማምተው ጥምረቱን ያቋቋሙት፡፡ እኔ ደግሞ በወቅቱ በየትኛውም ድርጅት ያልታቀፍኩ ስለነበርኩ ሁለት ምርጫ ብቻ ነበረኝ፡፡
ወይ ከመድረክ ጋር ያለኝን ግንኙነት ማቆም አለያም በፓርቲ ጥላ ስር ሆኜ መንቀሣቀስ፡፡ ተሣትፎዬ እንዲቀጥል ስለፈለኩ፣ የግድ ወደ አንድ ፓርቲ መግባት ነበረብኝ። ኘሮግራሙን በማዘጋጀት ብዙ ረድቻለሁ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሊሠሩ የሚችሉበት ጠንካራ ኘሮግራም ነው፣ በጣምም ደስ ስለሚለኝ ተሣትፎዬን መቀጠል ፍላጐቴ ነበር፡፡ ስለዚህ በፓርቲ ለመታቀፍ ከስድስቱ የመድረክ ተጣማሪ ፓርቲዎች የትኛው ኘሮግራም የበለጠ ለኔ ይስማማኛል መምረጥ ነበረብኝ፡፡ እናም አንድነትን መረጥኩ፡፡ በዚህ መልኩ ነበር ወደ አንድነት የመጣሁት፡፡ ከመጣሁ በኋላም መድረክ ራሱን አሣድጐ ወደ ግንባር ተሸጋገርን፡፡ ይህን ስናደርግ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ብዙ ውይይቶች ነበሩ፡፡ ከየድርጅቱ ሁለት ሰዎች የተወከሉበት የሥራ አስፈጻሚ አለ፡፡ የዚያም አባል ነበርኩ፡፡ የአንድነት ፓርቲ ኘሮግራም ያስቀመጠው አቅጣጫ፤ ሁሉም ፓርቲዎች ቢዋሃዱ ለዚህች ሀገር ጠቀሜታ እንዳለው የሚገልጽ ነው፡፡ ህዝቡም ተመሣሣይ ግፊት ያደርግ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ነው መድረኩ ከጥምረት ወደ ግንባር የተሸጋገረው። የመድረኩ ሥራ አስፈጻሚ፤ የግንባሩን ኘሮግራም እና የወደፊት አቅጣጫዎች ሠርቶ ለየፓርቲዎቹ ሥራ አስፈጻሚዎች አቀረበ፡፡ የድርጅቶቹ ሥራ አስፈጻሚዎች ከተወያዩበት በኋላ በኘሮግራሙ ተስማሙ፣ አንድነትም ተስማማ፡፡ የአንድነት ሥራ አስፈጻሚ ከተስማማ በኋላ፣ የመጨረሻ ወሣኝ የሆኑት ሁለት አካላት ውሣኔ ይጠበቅ ነበር፡፡ አንደኛው፤ ብሔራዊ ምክር ቤት ሲሆን ሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡
በዚህ ተዋረድ መሠረት፣ ሥራ አስፈጻሚው የተስማማበትን የግንባሩን ኘሮግራም ወደ ብሔራዊ ምክር ቤት አወረደ፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ተቀበለው፡፡ ከዚህ በኋላ የመጨረሻ ወሣኙ ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ጠራንና፣ ጠቅላላ ጉባኤው በበጐ ተቀበለው፡፡ ይሄን አካሄድ እንግዲህ ሁሉም የመድረክ ተጣማሪ ድርጅቶች ናቸው የተገበሩት፡፡ አንድነትን ጨምሮ ሁሉም ድርጅቶች በዚህ ሂደት “ግንባሩ ይፈጠር” የሚለውን ከወሰኑ በኋላ የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠራ፡፡ ከእያንዳንዱ ድርጅት በደንቡ መሠረት 10 ሰው ተወከለ፡፡ 10 የአንድነት ወኪሎችም በመድረኩ ጉባኤ ተገኙ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ፡፡ አንደኛ፤ መድረክ የገንዘብ ችግር ነበረበት፡፡ ሁለተኛ፤ ደግሞ ሰዎች በትርፍ ጊዜያቸው ነበር የሚሠሩት፡፡ እነዚህ የስራ መጓተቶች ፈጠሩ፡፡ በዚህ የተነሳም አንዳንድ ጭቅጭቆች ተነሱ፡፡ ለምሣሌ ኘ/ር በየነ፤ በግርማ ሠይፉ ላይ ሲሠጡ የነበረው አስተያየት፣ ግርማም ሲሰጠው የነበረው ምላሽ፤ አቶ ቡልቻም በአንድነት ላይ ሲሰነዝሩት የነበረው አሉታዊ አስተያየት…፤ እነዚህ ሁኔታዎች በአንድነት አባላት ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ ፈጥረዋል፡፡ እንዴት የመድረክ አባል ሆነን አሉታዊ አስተያየት ይሰነዘርብናል የሚሉ ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ ይሄ አሉታዊ ሁኔታ እያለ ከአንድነት አባላት አንድ ሃሣብ መጣ፡፡ “የመድረክን ሂደት እንገምግም” የሚል፡፡ በብሔራዊ ምክር ቤቱም ሂደቱን ገምግመን ማጠናከር አለብን የሚል ውሣኔ ላይ ተደረሰ፡፡ አንድ ኮሚቴም ተቋቋመ፡፡ ድጋሚ የተቋቋመው ኮሚቴ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግምገማውን አጠናቆ፣ ውጤቱን ለብሔራዊ ምክር ቤቱ አቀረበ፡፡ እዚያ ላይ ነው እንግዲህ ችግሮች መፈጠር የጀመሩት፡፡
ገምጋሚ ኮሚቴ ያመጣው አንደኛው የግምገማ ውጤት፤ የመድረክ አባል ድርጅቶች ከአንድነት ኘሮግራም ጋር የማይስማሙ አቋሞችና አላማዎች አሉት፤ በዚህ ሁኔታ ግንባር ፈጥሮ አብሮ መሥራት አይቻልም የሚል ነው፡፡ሁለተኛው ደግሞ ግንባር እንዲሆን የተወሰነው በደንብ ጥናት ተደርጐበትና በቂ ውይይት ተካሂዶበት ሳይሆን አመራሩ ብቻ ያደረገው ነው የሚል ሆነ፡፡ ይሄ ነው በእኔና በአንድነት አባላት መካከል ልዩነት የተፈጠረው፡፡ በእርግጥ ቀድሞም ቢሆን መድረክ እና አንድነት የሚለያዩባቸው አንዳንድ ነጥቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለምሣሌ የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 39 ጉዳይ፣ የግለሰብና የቡድን መብት ጉዳይ፣ የመሬት ጥያቄ አፈታት፣ የፌዴራሊዝም ጥያቄ የመሣሠሉት ላይ ልዩነት ነበረው፡፡ እንዴት እነዚህ ልዩነቶች እያሉ ግንባር እናቋቁማለን የሚል ጉዳይም ተነስቷል፡፡ በወቅቱ እኔያቀረብኩት አስተያየት “እነዚህ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ዋናው በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ወደፊት ልዩነቶቹ የሚፈቱበት ሁኔታ በኘሮግራሙ መቀመጡ ነው” የሚል ነበር፡፡ በመድረክ ያሉ ፓርቲዎች ፌዴራሊዝምን የሚደግፉ ቢሆንም በኢትዮጵያ አንድነት እምነት አላቸው፡፡ በኘሮግራሙም መገንጠልን አንደግፍም የሚል አቋም ላይ ተደርሷል። “ልዩነቶች ሊያለያዩን አይገባም፤ አብረን እየሠራን ከምርጫው በፊት ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ምህዳር እንዲፈጠር በማድረግ፣ የጋራ ማኒፊስቶ አዘጋጅተን፣ ወደ ፓርላማ እንገባለን ነበር የተስማማነው፤ እኛ ብቻ ሣንሆን ኢህአዴግን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶችም ፓርላማ ይገባሉ፣ ይህን መነሻ አድርገን የጋራ መንግስት እናቋቁማለን፡፡ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት መዋቅር ከተፈጠረ በኋላ፣ የመድረኩ ግንባር ተጣማሪዎች የየራሣቸውን ኘሮግራም ይዘው ወጥተው አሊያም አንድ ሆነው የመሠላቸውን ትግል” ይቀጥላሉ በሚል ይሄን ስምምነት የፓርቲው ግምገማ አፈረሰው። በዚህ የተነሣ በሃሣብ ተለያየን፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ግምገማውን ተቀበለው እኔ ተቃወምኩኝ፡፡
ይሄ የሆነው በ2005 ሚያዚያ ወር ነው፡፡ ሁለተኛው ልዩነት የተፈጠረው ደግሞ የግምገማው ውጤት ምን ይሁን በሚለው ላይ ነው፡፡ የግምገማው ውጤት ወደ መድረክ ይሂድና ለውይይት ይቅረብ፤ በሌላ በኩል ወደ ሚዲያ ወጥቶ ህዝቡ ይወያይበት፤ ይሄ በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይደረግ በሚል ብሔራዊ ምክር ቤቱ ወሰነ። ነገር ግን ጉዳዩ በማግስቱ ከውሣኔው ውጪ ሚዲያ ላይ ቀድሞ ወጣ፡፡ አንድ ግለሰብ ጋዜጣ ላይ በስፋት አወጣው፡፡ ይሄን የመድረክ ሰዎች ሲያዩት ትልቅ ቁጣ አስነሣ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ አንድነት ራሱን ሂስ ያድርግና ማስተባበያውን በጋዜጣ ያውጣ ወይም ይሄን ባደረገው ሰው ላይ እርምጃ ውሰዱ የሚል ማስጠንቀቂያ ከመድረክ ቀረበ፡፡ የእኔ አቋም “በሚዲያ ቢወጣ ምናለበት፣ ሂስም ማድረጉ ክፋት የለውም” የሚል ነበር፡፡ ሌሎች ግን አልተስማሙም። እንግዲህ በዚህ ላይም በእኔና በሌሎች የፓርቲው አመራሮች መካከል ልዩነት ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በመድረኩ ስብሰባዎች ላይ በሙሉ ህሊናዬ ሆኜ አንድነትን ለመወከል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገባሁ፡፡ እንደ ሊቀመንበር የግድ አንድነትን መወከልና የፓርቲውን ሃሣብ ማስተጋባት አለብኝ በሌላ በኩል ደግሞ ህሊናዬ ይሞግተኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ዘንድሮ የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ከመግባት ተቆጠብኩ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ የውህደት ጉዳይ ተጀመረ፡፡ መኢአድ እና አንድነት ይዋሃዱ ተብሎ ድርድር ተጀመረ፡፡ የቅድመ ውህደት ሠነድም ተዘጋጀ፡፡ በዚያ ሰነድ ላይ እኔና ብሔራዊ ምክር ቤቱ አሁንም ተለያየን፡፡ ብዙ የልዩነት ነጥቦች ናቸው፡፡ እነሱን አሁን መዘርዘር አልፈልግም፡፡ እርስዎ ውህደቱን አይደግፉም ማለት ነው? ውህደት እደግፋለሁ፤ ነገር ግን ሲዋሃዱ በምን ላይ ነው የተመሠረቱት፤ የውህደት ስምምነቱስ ምንድን ነው? በሚለው ላይ አንዳንድ ጥልቀት ያለው ውይይት ሊካሄድባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ግን እነዚህን ውይይት የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች እንዳለ ተቀብሏል። ለምሣሌ የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 39 ጉዳይ አለ። አንቀጹ የመገንጠል መብትንም ያካትታል፡፡ ይሄን አንቀጽ የውህደቱ ተደራዳሪ ኮሚቴ አይደግፍም፤ ከህገ መንግስቱም መሰረዝ አለበት ሲል ተስማምቶበታል፡፡ በእኔ በኩል ደግሞ ይሄ የማይቻል ነው፡፡ አንቀጽ 39ን ይደግፋሉ? አዎ! እደግፋለሁ፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው የመብት ነው፡፡ መብቱ ይከበር ነው እንጂ መገንጠል ይኖራል ማለት አይደለም፡፡
ስለዚህ እኔ አንቀጽ 39 ከህገ መንግስቱ ይሠረዝ የሚለውን አልደግፍም፡፡ ይህን ተቃውሞዬን በማሠማበት ጊዜ፣ እኛ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ አንደራደርም የምትል ማሻሻያ በድርድር ሰነድ ላይ ቀረበች፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ይሄን ሙሉ ለሙሉ ተቀበለው፡፡ በእኔ በኩል አሁንም ይሄ አባባል አስቸጋሪ ነው አልኩ፡፡ መብት አክብረህም አንድ ክፍለ ህዝብ መብቴ አልተከበረም፤ እገነጠላለሁ ካለ ምንድነው የሚሆነው? ወደ ጦርነት ነው የሚኬደው ወይስ ሌላ አማራጭ አለ? እዚህ ላይ ልዩነቶች ተፈጠሩ፡፡ አሁን መጨረሻ ላይ ደግሞ በአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የምረጡኝ ቅስቀሣ ሲካሄድ ነበር። እዚያ ላይ ጠቅላላ ጉባኤው፤”ውህደቱ ያስፈልጋል በማለት በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ከመኢአድ፣ ከአረና እና ከመሣሠሉት ፓርቲዎች ጋር ውህደት እንዲፈጸም” ብሎ የወሰነውን ውሣኔ ኢ/ር ግዛቸው ወሰደና፣ “እንዲያውም ለውህደቱ የተሰጠው ጊዜ ዘግይቷል በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ አደርጋለሁ” ሲል ቅስቀሣ ማካሄድ ጀመረ፡፡ በተጨማሪም “ከአሁን ጀምሮ በጥምረት፣ በግንባር በመሣሠሉት ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፤ ውህደት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፤ በዚህ አካሄድ ነው የምሠራው” ሲል አቋሙን ገለፀ ፤ በዚህም በከፍተኛ ድምጽ ተመረጠ፡፡ ይሄ ለኔ ሌላ ትርጉም አለው፡፡ የእኔ ግልጽ አቋም ምን መሠለህ? ከተቻለ ውህደት ጥሩ ነው፤ ወደ ውህደት የምትደርሰው ግን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ነው እንጂ አድርጉ ስለተባለ መሆን የለበትም፡፡ ውህደት ላይ ሁሉም በአንድ እጅ ማጨብጨብ አለበት፤ በኘሮግራም ሙሉ ለሙሉ መስማማት አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ይሄ የመጨረሻው ውሣኔ ላይ እንድደርስ እና ከፓርቲው እንድወጣ ያደረገኝ ጉዳይ ነው፡፡
በዚህና ከላይ ባስቀመጥኳቸው ምክንያት አቅጣጫው የተለወጠ ይመስለኛል፡፡ እኔ ደግሞ ከአቅጣጫ ለውጡ ጋር ህሊናዬ ተስማምቶ ሊሠራ አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ከአንድነት ልወጣ ችያለሁ፡፡ ከፓርቲው ከወጣሁ በኋላ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ሣስብም የደረስኩበት ድምዳሜ የፓርቲ-ፖለቲካ ይበቃኛል የሚለው ሆነ፡፡ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ከፓርቲ ፖለቲካ ሲገለሉ መጽሀፍ ይጽፋሉ፣ልምዳቸውን ያካፍላሉ፡፡ እርስዎ ምን አሰቡ? ርዕሱንና ይዘቱን መግለጽ አልፈልግም እንጂ መጽሃፍ እየጻፍኩ ነው፡፡ በሌላ በኩል የፖለቲካ ምክር መስጠትና ልምድ ማካፈልም አለ፡፡ እኔ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው በአንድነትም ሆነ በመድረክ ላይ “ትክክል አይደሉም” ብዬ ጫና ለመፍጠር አልፈልግም፡፡ እንዲጐዱም አልፈልግም፡፡ ለዚህች ሀገር ፖለቲካ አስፈላጊ ኃይሎች መሆናቸውን በሚገባ አምናለሁ፡፡ ከአንድነት የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ከነበሩት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ጋርም አለመግባባቶች ተፈጥረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ መነሻው ምን ነበር? ኢ/ር ዘለቀ የድርጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበር፡፡ የፓርቲውን የድርጅት ስራ ማንቀሣቀስ ነበረበት፡፡ ግን እንደታሰበው ሣይሆን ድክመት ተፈጠረ፡፡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የተቻለውን ያህል መከርን፤ ግን አልሆነም፡፡ እኔ ነበርኩ ኃላፊነቱን የሠጠሁት፡፡ ሥራው ከተዳከመ አልንና ኃላፊነቱን እንዲለቅ አደረግን፡፡ እሱ ግን ደብዳቤ አልደረሰኝም ብሎ ጋዜጣ ላይ አወጀ፡፡ ይሄ ግን አይደለም፤ በወቅቱ ደብዳቤውን ሰጥቼዋለሁ፡፡ ይሄ ነው የግል ፀብ ያስመሰለው እንጂ የአለመግባባቱ መንስኤ የአሠራር ጉዳይ ነው፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ራሱ በአንዳንድ የዲስፒሊን ግድፈቶች የተነሳ በአባልነቱ ላይ ጥያቄ አንስቶ ነበር፡፡ በእኔና በአሥራት ላይም በየጋዜጦቹ ያወጣቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡
አሁን ደግሞ ኢ/ር ግዛቸው በሥራ አስፈጻሚነት መልምሎታል፡፡ እኔ በዚህ ምንም ቅር አይለኝም፡፡ በግል ግን እኔና እሱ ፀብ የለንም፤ እንቀራረባለን፡፡ በ46 ዓመታት የፖለቲካ ህይወትዎ ለኢትዮጵያ ህዝብ አበርክቻለሁ የሚሉት ጉልህ አስተዋጽኦ ምንድን ነው? ዴሞክራሲና ፍትህ ከሌለ፣ ጭቆናና የሰብአዊ መብት ጥሰት ከተንሰራፋ፣ ሰው ሁሉ መታገል አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔም በዚህ መርህ መሠረት፣ የራሴን ድርሻ ህሊናዬ በፈቀደው መንገድ እየተጓዝኩ አበርክቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ዴሞክራሲ እንዲኖር፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ አነቃቅቻለሁ ለማለት እችላለሁ፡፡ ለህሊና መኖር እንደሚቻል ያሣየሁም ይመስለኛል፡፡ ዋናው ነገር ሰው ሁልጊዜ መብቶቹ ካልተከበሩ መታገል አለበት፡፡ ባላደርግሁት ብለው የሚቆጩበት ፖለቲካዊ ውሣኔ ይኖርዎት ይሆን? አየህ… አሁን ለምሣሌ ሶሻሊዝምን እደግፍ ነበር። ደርግ ሶሻሊስት ነኝ ባለ ጊዜ ልደግፈው እችል ነበር፤ ነገር ግን አምባገነን ነው፡፡ ወጣቶችን የሚገድልና መብቶችን የሚደፈጥጥ ነበር፤ በዚያ ሶሻሊስት ስለሆነ ብቻ ሁሉን ሃጢያቶቹን ትቼ እሱን ለመደገፍ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም ነበር፡፡ ኦነግን ረድቻለሁ፤ ነገር ግን ኋላ ላይ ተጣላን፤ የተጣላንበት ምክንያት ተበታትኖ በየጐጡ እየተደራጁ የሚደረጉ ትግሎችን ተቃውሜ፣ ወደ አንድ መድረክ መሰባሰብ ይገባል የሚል አቋም በመያዜ ነበር፡፡ በአውሮፓ ይገኙ የነበሩ ሁለት የኦሮሞ ድርጅቶችን ለማቀራረብ ስንቀሣቀስ አንደኛው ድርጅት፤ “ይሄ ጐበና ዳጩ /የሚኒልክ ጦር አዝማች የነበሩት/ ነው “አለኝና አገለለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ኦፒኤልኤፍ ከሚባል ድርጅት ጋር እየሠራን እያለ፣ በ1983 “ዱለ ወልቂጡማ ቢሊሱማ” /ዘመቻ ለነጻነትና ለእኩልነት/ ሲታወጅና ጦሩ ከጐጃም ተነስቶ ወደ ወለጋ ሲጓዝ “ይሄ ደግሞ ቅኝ ግዛት ነው” አሉ፡፡ እኔ በወቅቱ “ይሄ ዳግም ቅኝ ግዛት ሊሆን አይችልም።
ምክንያቱም ደርግ ሌላ ቦታ ተሸንፎ መሠረት ያደረገው ኦሮሚያ ውስጥ ነው፤ ስለዚህ ይህን ኃይል ለመደምሰስ የሚደረግን ዘመቻ ዳግም ቅኝ ግዛት ነው ብሎ ያለመደገፍ ደርግ እንዲቀጥል ማድረግ ነው ብዬ አቋም በመያዝ ከእነሱ ጋር ተለያየን፡፡ እንደገና ወደ ኦህዴድ ከመጣሁ በኋላ በ1993 ዓ.ም ከኢህአዴግ የተለየሁት በአቅጣጫ ልዩነት ነው፡፡ ሶሻሊስት ነን ብዬ አብሬ ስሰራ እነሱ ነጭ ካፒታሊዝምን ነው የምንከተለው ብለው በድንገት አወጁ፤ እኔ ደግሞ በካፒታሊዝም አላምንም፡፡ ምክንያቴም ካፒታሊዝምን እንከተላለን ሲባል እንዲሁ የውሸት በመሆኑ ነው፡፡ ፓርቲዎች በነጻነት መንቀሣቀስ ባልቻሉበት እና የብሔር ጥያቄ ባልተፈታበት ሁኔታ ካፒታሊዝምን እንከተላለን ማለት ሌላ ችግር ያመጣል ብዬ ተለያየን ፡፡ ከዚህ አንጻር ህሊናዬ በሚፈቅደው መንገድ ነው ስሄድ የነበረው ማለት ነው፡፡ ህሊናህ በፈቀደው መንገድ ስትጓዝ ደግሞ የሚቆጭህ ነገር የለም፡፡ ስለዚህ እኔ አንዳችም የሚቆጨኝ ነገር የለም በውሣኔዎቼ ሁሉ ደስተኛ ነኝ፤ የራስን ሃሣብና የህሊና ጥያቄ ገፍቶ ለድርጅታዊ ውሣኔ ብቻ መገዛት በእኔ በኩል ትክክል አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ልዩነት ቢኖርህም ልዩነትህን ውጠህ እዚያው ብትቆይ ይሻልህ ነበር” የሚል ሃሣብ ያመጣሉ፤ ለኔ ግን ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ አንዳንዶች እርስዎ ዶ/ር ነጋሶ፤ “ቀጥተኛ ሁሉን ነገር በግልጽ የሚናገሩ ስለሆኑ ለፖለቲካው የሚሆኑ ሰው አይደሉም ይላሉ…. አዎ! እኔ ዲኘሎማት አይደለሁም፡፡ ቀጥተኛ ታጋይ ነኝ፡፡ ፖለቲካው ወደዞረበት እየዞረ የሚሄድ ፖለቲከኛ ዲኘሎማት አይደለሁም፡፡ ዲኘሎማት የሆኑ ሰዎች ብዙ ጊዜ በዚህም በዚያም ብለው ግባቸው ላይ ለመድረስ ነው የሚጥሩት፡፡ እኔ ያንን አልችልበትም ፡፡ ቀጥተኛ መሆንዎ ያሣጣዎት ነገር አለ? ምን ያሣጣኝ ነገር አለ? /ረጅም ሣቅ/ ምናልባት በቁሣቁስ አሣጥቶኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ማቴሪያል ደግሞ ድሮም አልነበረኝም፤ አሁንም የለኝም፡፡ ሰዎች ከኢህአዴግ ጋር ባትጣላ ኖሮ ቢያንስ እንደ መቶ አለቃ ግርማ ትኖር ነበር ይሉኛል፡፡
ያንን ካየህ በቁስ ደረጃ ያጣሁት ነገር አለ ተብሎ ሊታሠብ ይችላል፡፡ ይሄ ያለሁበት ቤትም የኔ አይደለም፤ ከዚህም ውጣ ከተባልኩ ቆይቷል፡፡ መውደቂያ ስለሌለኝ እምቢ ብዬ ነው እንጂ፡፡ አበል የለኝም፣ ከአንድነት ትሠጠኝ የነበረች 3 ሺ 800 ብር አበልም ከበቀደም ጀምሮ ቆማለች፡፡ የምኖረው እንግዲህ ከቀበሌ በማገኛት 1300 ብር ጡረታዬ ነው፡፡ ባለቤቴም መጠነኛ ገቢ የምታገኝባት ሥራ አላት፡፡ እንግዲህ አሁን ያለሁበትን የኑሮ ደረጃ ካየህ፣ አጥተሃል የሚሉኝ ሰዎች ሃሣብ ትክክል ነው ልትል ትችላለህ፤ ነገር ግን ይሄ ለኔ አይቆጨኝም፤ ስሜትም አይሰጠኝም፤ ምክንያቱም እኔ በዚህ አይደለም የታገልኩት ቁስ ለመሰብሰብ አይደለም ፡፡ እስቲ ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ አናውራ…. በአሁኑ ወቅት ለህዝብ መብትና ጥቅም በሃቀኝነት የሚታገሉ ፓርቲዎች አሉ? በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሃቀኛ ናቸው አይደሉም የሚለው ግምገማ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁሉም በመሠለው መንገድ እየታገለ ነው፡፡ ለኔ ግን ካየኋቸው ተሞክሮዎች፣ በእርግጥም ሃቀኛ ድርጅት ነው ብዬ የማምነው የህዝብን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነትን የሚቀበል ፓርቲ ነው፡፡
ለዚህ ተግባራዊነት የሚንቀሣቀስ መሆን አለበት እንጂ ለፓርቲ ኘሮግራም እና ዓላማ ብቻ የሚሠራ መሆን የለበትም፡፡ እዚህ አገር ሁሉም ፓርቲዎች ለህዝብ ነው የሚታገሉት ይባላል። ግን ከገዥው ፓርቲ ጀምሮ በሁሉም ላይ ችግር አያለሁ፡፡ ኢህአዴግ ለስሙ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ ምናምን ይላል፤ የሚሠራው ግን ሌላ ነው፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም የምንታገለው ለህዝብ የስልጣን ባለቤትነትና ለዴሞክራሲ ነው ይላሉ፤ ያ ከሆነ በጋራ መሥራትን ለምን ይፈሩታል? ከዚህ አኳያ ከተመለከትነው ሁሉም ፓርቲዎች ላይ የሃቀኝነት ጥያቄ ይነሣባቸዋል ማለት ነው፡፡ እርሶ ሲመሩት የነበረው አንድነት፤ “ገዥው ፓርቲ ሀገሪቱን በብሔር ከፋፍሎ ኢትዮጵያዊነትን ሸርሽሯል” የሚል አመለካከት አለው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ “የቁጫ ብሔረሰብ ማንነቱ ለምን አይከበርም ሲል የብሔር መብት ጥያቄ ያነሣል፡፡ እነዚህ ነገሮች እርስ በእርሣቸው አይጋጩም? በአንድነት ኘሮግራም ላይ አንድ አንቀጽ አለ። የኘሮግራሙ 3.1.5 አንቀጽ፤ “አብይ የፖለቲካ ጥያቄዎች በፖለቲካዊ መንገድ ነው የሚመለሱት፤ ይሄም በህጋዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ፤ በውይይት እና በድርድር ነው፤ በዚህ መንገድ አብይ ጥያቄዎች ካልተፈቱ ወደ ህዝብ ነው የሚሄደው” ይላል፡፡ ይሄ አንቀጽ እውነት ይታመንበታል ወይ የሚለው ለኔ ጥያቄ ነው፤ ለእኔ ከፖለቲካ ጥያቄዎች አንዱ የብሔር ጥያቄ ነው፡፡ አብይ የፖለቲካ ጥያቄ እንደሚኖር የምታምን ከሆነ፣ አንቀጽ 39ን መቃወም የለብህም ማለት ነው፡፡ የብሔር ጥያቄ የምታምንበት ከሆነ “በኢትዮጵያ አንድነት አልደራደርም” አትልም ማለት ነው፡፡ እኔ ተቃርኖውን በዚህ መንገድ ነው የማየው፡፡የቁጫን ህዝብ በተመለከተ ግን የአንድነት ኘሮግራም ላይ የግለሰብ እና የቡድን መብት መከበር እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ የቁጫ ህዝብ አንድ ቡድን ነው፤ አንድነት የማንነት ጥያቄ ሣይሆን የመብት ጥያቄውን ነው የደገፈው፡፡
ጥያቄያቸው ይሰማ ነው ያለው። እነሱ የጠየቁት ይሰማ ከሚለው አኳያ ነው እንጂ ማንነታቸው ይታወቅ የሚል አይደለም፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ጥሩ አቅጣጫ ይዟል፤ በቀጣይ ምርጫም የስልጣን ባለቤት ሊሆን ይችላል ብለው ተስፋ የጣሉበት ፓርቲ አለ? አሁን ይህን ማለት ጥሩ አይደለም፡፡ ይሄኛው ከዚህ የተሻለ ነው ብዬ መወሰንም አልችልም፡፡ ፓርቲዎች ይደራጁ፣ ይሞክሩ፤ ከተመረጡ ይመረጡ፤ አሁን አለ ወይም የለም የሉም ብዬ ከደመደምኩኝ ጥሩ አይሆንም ነገር ግን ሁሉም በተቻለ መጠን ከልባቸው ለህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ይታገሉ፡፡ በኢህአዴግ በኩልም የፖለቲካ ምህዳሩን መክፈትና ሁሉንም ፓርቲዎች በእኩል ማስተናገድ አለበት፡፡ ፓርቲዎች ከአሁን ጀምረው ተሰባስበው፣ ለዲሞክራሲ መሥራት አለባቸው፡፡ አሁን ጥሩ እየሠሩ ነው የሚሏቸው ፓርቲዎች የሉም? እየሞከሩ ነው ሶስተኛ አማራጭ አለ። አክትቪዝምን የሚከተሉ አሉ፣ አንድነትም፣ መድረክም…. ሌሎችም አሉ፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ግን ይሄኛው ይሻላል ያኛው አይሻልም ወይም ሁሉም አይረቡም በሚለው ላይ ግን አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ከፓርቲ ፖለቲካ ራስዎን ቢያገሉም በግልዎ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በግልዎ ለፓርላማ መወዳደርስ? የለም ይበቃኛል፡፡ ወደ ፓርላማው መግባትም አልፈልግም፡፡ ምናልባት በፓርቲዎች መካከል ስምምነት ለመፍጠር፣ በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል መቻቻል እንዲኖር፤ ሁሉም በብሔራዊ ጉዳይ እንዲስማማ የማድረግ እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ እሞክራለሁ፡፡ ምናልባት ኢህአዴግ፤ ለሁለተኛ ጊዜ አብረውት እንዲሰሩ ወይም በማማከር እንዲያግዙት ቢጠይቅዎ ፈቃደኛ ይሆናሉ? ምክር ከፈለገ አብሬ ብሠራ ምንም ችግር የለብኝም፡፡
ስብሰባዎች ካሉ እሣተፋለሁ፡፡ በቅርቡ አቶ ስብሃት ነጋ በሂልተን ሆቴል አንድ ሴሚናር አዘጋጅቶ ጋብዞኝ ነበር፡፡ እዚያ ላይ ተሣትፌያለሁ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጆርናሊዝምና ኮሚኒኬሽን ኢንስቲትዩት የፌዴራሊዝም ጥያቄ ላይ በተደረገ ውይይት ጋብዞኝ አስተያየቴን ሰጥቻለሁ፡፡ በቅርቡም ሌላ ውይይት ላይ እንድገኝ ጠይቀውኛል፡፡ የዚህ ዓይነት ሁኔታ ከተፈጠረ ለምን እምቢ እላለሁ፡፡ የመድረክ ሰዎች ብዙዎቹ እኮ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከቀጠረኝ የመንግስት ስለሆነ አልፈልግም አልልም፡፡ ኢህአዴግም በምክር ከፈለገኝ አማክረዋለሁ፤ “ይሄን ብታደርግ ይሻላል፤ ይሄ ጥሩ አይደለም” ለሚለው ሃሣብ በሩን ከከፈተ ጥሩ ነው፡፡ ድሮ የትግል አጋርዎ የነበሩት የቀድሞ የኦነግ አመራር አቶ ሌንጮ ለታ “ወደ ሠላማዊ ትግል ተመልሻለሁ አዲስ ፓርቲም አቋቁሜያለሁ” ማለታቸው ለኢትዮጵያ ፋይዳው ምንድን ነው? ተቀባይነትስ ያገኛሉ ብለው ያስባሉ? በአገር ውስጥ 72 ፓርቲዎች ስላሉ የእነሱ አዲስ ፓርቲ ይዞ መምጣት ብዙም ፋይዳ የለውም፡፡ ከሌሎች ጋር ቢቀናጁ ይሻላል የሚል ሃሣብ አለኝ። ምክንያቱም በኦሮሞ ስም የተደራጁ ብዙ አሉ፡፡ “በኢትዮጵያ ጥላ ስር መኖር ይቻላል” ከሚለው አኳያ ስንመለከተው የእነ ሌንጮ መምጣት የሚጨምረው እሴት ይኖራል፡፡
በሌላ በኩል በአጠቃላይ በኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሣቀሱ ፖርቲዎች ሁለት አቅጣጫ ነው የያዙት፡፡ አንዱ እንገንጠል፣ ሌላው በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነን እንኑር የሚሉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ጥላ ሥር እንኑር ለሚሉት የእነ ሌንጮ መመለስ ድጋፍ ሲሆን እንገንጠል ለሚሉት ደግሞ ድጋፉን ያጐድልባቸዋል፡፡ አገር ውስጥ በሠላማዊ መንገድ ሲታገሉ የቆዩትን የኦሮሞ ድርጅቶችና የእነ ሌንጮ ፓርቲ ውዝግብ ውስጥ እንዳይገቡ እፈራለሁ፡፡ በሌላ በኩል ኦነግ በእነ ሌንጮ ላይ ትግሉን ገድለውታል የሚል ሃሣብ የሚያነሣ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ለኦሮሚያ “ህዝብ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ እንኑር” የሚለውን አስተሣሠብ የበለጠ ያጠናክራል፡፡ በእኔ እይታም የኦሮሞ ህዝብ ይሄንን ነው የሚፈልገው፡፡ የዳያስፓራውን ፖለቲካ እንዴት ይገመገሙታል? አንዳንዶች የሃይማኖት ተቋማትን በዘር እስከ መከፋፈል ደርሰዋል በሚል ይተቻሉ… ጨለምተኛነት አለ፣ አክራሪነት አለ፣ በሀይማኖትና በጐሣ መከፋፈል የእነ ሌንጮ ፓርቲ ተቀባይነት ያገኛል ወይ የሚለው አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ 17 ዓመት ጀርመን ሀገር ስለኖርኩ አውቀዋለሁ፤ ከአንዳንድ የኦሮሞ ጓደኞቼ ጋር የምጣላው ለዚህ ነበር፡፡ ለምሣሌ እኔ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ አስመጥቼ ሳነብ ሲያዩ፡፡ “እንዴት ይሄን የአማራ ጋዜጣ ታነባለህ?” ይሉኛል ወይም መንገድ ላይ ሰውን በአማርኛ ሰላም ስል ደስ አይላቸውም ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ዛሬም አሉ፡፡ እዚያ ነጻነት አለ፤ ግን ነጻነት በዚህን ያህል ደረጃ መከፋፈላቸው፤ በአገር ቤቱ ፖለቲካ ላይ ተጽዕኖ አለው፡፡ ከኢህአዴንም ከአንድነትም የወጡት በአቅጣጫና በአመለካከት ልዩነት ነው፡፡ ከሁለቱ የበለጠ ያልተመቾት የቱ ነው? በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
የኢህአዴጉ በአንድ በኩል “የህወኃት አንጃ” ያላቸውን ሰዎች ያስተናገደበት መንገድ አስከፊ ነው፡፡ ያኔ እኔ ምርጫ ቦርድ ብሆን ኖሮ፣ ኢህአዴግን ሠርተፊኬቱን እሠርዝበት ነበር። ምክንያቱም ሰዎቹ ህገ-መንግስቱና የምርጫ ህጉ በሚፈቅደው መንገድ አይደለም የተባረሩት፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው አልተጠበቀም ያ ለኔ ብዙ ራስ ምታት ፈጥሮብኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሰኔ ላይ አቅጣጫ መቀየር መጣ፡፡ እንግዲህ እሱ እና አሁን በአንድነት ያጋጠመኝ ይመሣሠላል፡፡ እኔ ላይ ጭቅጭቅና አለመግባባት በመፍጠር ረገድ ግን የኢህአዴጉ ነው የሚበዛው፡፡ ከአንድነት ስወጣ በእድሜ መግፋት እና በጤና እንደምለቅ አስቀድሜ ስለገለፀኩ ከጭቅጭቅ ያመለጥኩ ይመስለኛል። አንድነት በዚህ በኩል ሊበራል ነው፡፡ ሃሣብን ያከብራል፤ ያለ ቅሬታ ነው የተለያየነው፡፡ የኢህአዴጉ ግን የልብ ድካም ሁሉ ያመጣብኝ ነበር፡፡ አዲሱን የኢፌዲሪ ኘሬዚዳንት በተመለከተ አስተያየት አለዎት? የኘሬዚዳንት ተቋም ኃላፊነትና ተግባር እንዲሆን የተፈለገው የእንግሊዙ ሲስተም ነው፡፡ በእንግሊዝ ንግስቲቱ ሀገርን ትወክላለች፤ ሆኖም ግን እዚያ ብዙ ጥንቃቄ አለ ንግስቲቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ትደግፋለች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፊናው እያንዳንዷን ነገር ማማከር፣ ሪፖርት ማድረግና የውሣኔ ሃሣቦችን መቀበል አለበት፡፡
እዚህ ያ የለም፤ አሁን ተፈጥሮ እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔ ባለሁበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማክሮኝ አያውቅም፡፡ እኔም ብዙ ጊዜ የኦህዴድን የድርጅት ሥራ በመሥራት ላይ ተጠምጄ ስለነበር በሌሎቹ ሥራዎች ላይ አልተንቀሣቀስኩም። ኘሬዘዳንት ግርማም በህመም ምክንያት አልተንቀሣቀሱም፡፡ የአሁኑ እንግዲህ እየተንቀሣቀሱ እንደሆነ አላውቅሁም፡፡ ሆኖም ግን በእድሜም በጤናም ደህና ናቸው፡፡ በትምህርትም ደህና ናቸው፤ በግርማ ሞገስም ገጽታቸው ለኘሬዚዳንትነት አይከፋም፡፡ ነገር ግን የኛ ህገ መንግስት ለኘሬዚዳንቱ ስልጣን አይሠጥም፡፡ በግል ቂም አለው ወይ እንዳትለኝ እንጂ የአሁኑ ኘሬዘዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እና ዳዊት ዮሐንስ ነበሩ ያኔ በእኔ ላይ የፈረዱት። ሁሉን ነገር እንዳጣ የወሰኑት እነሱ ናቸው፡፡ በ97 ዓ.ም ምርጫ ጊዜ ምርጫ ውስጥ ገብተሃል፤ ብሎ አዋጅ ጥሰሃል ስለዚህ ጥቅማ ጥቅሞችህንና መብትህን ታጣለህ” ብለው የወሰኑት እነሱ ናቸው፡፡ ዶ/ር ሙላቱ ያኔ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ነበር፡፡ አሁን የሚኖሩበት ቤት ከኘሬዚዳንትነት ሲለቁ የተሰጥዎ ነው? ከኘሬዚዳንትነት የለቀቅሁ እለት የት እንደሚያስገቡኝ ጨንቋቸው፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጠገብ ካለች አንዲት ቤት ነበር ያስገቡኝ፡፡ እዚያ 6 ወር ከኖርን በኋላ ወደ ቦሌ ወሰዱን፤ ጥሩ ቤት ነበረች፤ 3 መኝታ ቤት አላት፣ ቢሮ ግን የላትም፡፡ ግድግዳውና መስታወቱ ተሠነጣጥቆ በጋዜጣ ነበር እየሸፈንን ሁለት አመት ቆየን፡፡ ከዚያ አሁን ያለሁበት ቤት አመጡን፡፡ አሁን ከፓርቲ ፖለቲካ ሲገለሉ ጥቅማ ጥቅሜን መለሼ ላገኝ እችላለሁ የሚል ተስፋ የሎትም? የቀድሞ ኘሬዚዳንት ከወገንተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መገለል አለበት ይላል፡፡ አተረጓጐሙ እንግዲህ በኢህአዴግ እይታ አፍህን ዘግተህ ተቀመጥ ነው፡፡ የመጀመሪያው ማስጠንቀቂያ የደረሰኝ አዳማ ላይ የሮያል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በክብር እንግድነት ጋብዞኝ ባደረግሁት ንግግር ነው በወቅቱ ኢህአዴግ እንደሚለው “ልማት ያስፈልገናል፣ ልማት እንዲመጣ ዴሞክራሲ ያስፈልገናል፣ ዴሞክራሲ እንዲመጣ የመብት ጥያቄዎች መልስ ያስፈልጋቸዋል” አልኩ። አክዬም፤ “በኦሮሚያ ሠላም ስለሌለ እንደሌሎች አካባቢዎች ልማት እየተፋጠነ አይደለም፣ ይህ የሆነው ደግሞ ዲሞክራሲ ስለሌለ ነው” ብዬ ተናገርኩ፡፡ ከሁለት ሣምንት በኋላ ዳዊት ዮሐንስ ጠራኝና የኦሮሚያ ክልል ከሶሃል አለኝ፡፡ “ፖለቲካ ውስጥ እየገባህ ነው፤ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ በዚህ ሁኔታ የምትቀጥል ከሆነ ጥቅማ ጥቅምህን ታጣለህ” አለኝ፡፡ “የፈለከውን አድርግ፤ እኔ አቋሜን ከማራመድ ወደ ኋላ አልልም” አልኩትና ሄድኩ፡፡ በዚያው ውሣኔያቸውን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ እኔም ክስ መስርቼ፣ ከስሼ ሰበር ደርሶ ለእነሱ ተወሰነ፡፡
የሚሠጠኝ አበል፣ መኪና፣ ሠራተኞች፣ ቤት የመሣሠለውን አጣሁ እኔ አሁን ከፓርቲ ፖለቲካ በመውጣቴ በድጋሚ ጥቅማ ጥቅሜን አገኛለሁ የሚል ተስፋ የለኝም፡፡ ኢህአዴግ ይህን ካደረገ ተለውጧል ማለት ነው፡፡ እኔ ግን አሁንም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ መተቸቴንና መቃወሜን እቀጥላለሁ፡፡ ለኘሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በ4ዐዐሺህ ብር መኖሪያ ቤት መከራየቱን የሚተቹ ወገኖች አሉ? እርስዎ ምን ይላሉ? እኔም ከሚቃወሙት ወገን ነኝ፡፡ በዚህች ድሃ ሀገር ለምን ይሄ አስፈለገ? አንደኛ እኔ እንደሠማሁት ቤቱ 2ዐ ክፍሎች ነው ያሉት፡፡ አሁን በተሻሻለው ህግ ደግሞ ኘሬዚዳንቱ ከ3 እስከ 4 ክፍል ቤት ይሠጠዋል ነው የሚለው፡፡ በሀገራችን የድህነት ሁኔታ በ4ዐዐ ሺህ ብር ቤት መከራየት ያስፈልጋል ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ከሚያቀርቡት ወገን ነኝ፡፡ አሁን እርስዎ የሚተዳደሩት በምንድነው? እስከአሁን ድረስ ለኢኮኖሚ የሚጠቅመኝን ሥራ አልሠራሁም፡፡ ለፒኤችዲ የጻፍኳት መጽሃፍ አለች ከዚያች ትንሽ ገንዘብ አግኝቻለሁ፡፡ ከዚያ “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” ከሚለው መጽሃፌ ደግሞ ሩብ ያህሉን አግኝቻለሁ፡፡ ሌላው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሲቋቋም፣ ዘመዶች አክስዮን ግዛ ብለውኝ በ4 ሺህ ብር የገዛሁት አለኝ፡፡ ከዚያ በስተቀር ምንም የኔ የምለው ሃብት የለኝም፡፡ ደምቢዶሎ ያለው የወላጆቻችን ቦታ ተወስዷል፡፡ እዚህም የራሴ የምለው ቤትም ሆነ ቦታ የለኝም፡፡ ከዚህ ከምኖርበት ቤትም ውጣ ብለውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አቤቱታ በማቅረቤ እስከአሁን ድረስ ዝም ብለውኛል፡፡ ግን በፈለጉ ጊዜ እንደሚወስዱት አውቃለሁ፡፡ ዋስትና የለኝም፤ በስጋት ነው የምኖረው፤ ቀጣይ መውደቂያዬንም አላውቀውም፡፡ ልጆችዎ የት ናቸው? ልጃችን አሁን የፊልም ትምህርቷን ጨርሳ ሎስአንጀለስ ውስጥ ሥራ እያፈላለገች ነው፡፡ ከቀድሞዋ ባለቤቴ የወለድኳቸው ደግሞ አንደኛው ጀርመን ሀገር ይሠራል፤ ሴቷ ደግሞ ለንደን ነው ያለችው፡፡
ልጅ ወልዳለች አሁን የእነሱ ጉዳይ አያሣስበኝም፡፡ እኔ አንድ ነገር ብሆን ባለቤቴ ምን ትሆናለች የሚለው ነው የሚያስበኝ፡፡ በቅርቡ በኢቲቪ በተላለፈ ዶክመንተሪ ላይ እርስዎና ሌሎች የአንድነት አመራሮች በ“ኢሳት” ጣቢያ ላይ ቃለ ምልልስ መስጠታችሁ ተተችቷል… ዶክመንተሪውን ተከታትየዋለሁ፡፡ የመጀመሪያው ላይ አሥራት ጣሴ፣ እኔ እና ዳንኤልን ነበር የሚያሳዩት ሁለተኛው ላይ እኔና ዳንኤል ኢንተርቪው ሰጥተዋል የሚል ትችት አቀረቡ ያቀረቡት፡፡ በቃለ ምልልሱ ምን እንዳልን ግን አላቀረቡም፡፡ ይህ እንግዲህ እነ ነጋሶ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላቸው ለማለት ተፈልጐ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ይህ የአሁኑ ሌላ የኘሮፖጋንዳ ሥራ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ጨዋታ ጥሩ አይደለም፡፡ የትም አያደርሣቸውም፡፡ ቢተውት ጥሩ ነው፡፡ ለወደፊት እርሶ ምን ዓይነቷን ኢትዮጵያ ለማየት ይመኛሉ? መብትና ነጻነት የተከበረባት፣ ሁሉም የፈለገውን የሚያስብባትና ያሻውን አቋም የሚገልጽባት ኢትዮጵያን ባይ ደስ ይለኛል፡፡ ሰው በፈለገው መንገድ እየተደራጀ የፈለገውን ተቃውሞ በመንግስት ላይ የሚያቀርብባት፣ የፈለገውን ግለሰብ እና ፓርቲ የሚመርጥባት፣ዜጐች በሁሉም ጉዳዮች ላይ ወሣኝ የሚሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት ምኞቴ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሙሉ ነጻነቱ ከተከበረለት፣ አቅሙን መጠቀም ይችላል፤ ያኔም ልማት ይመጣል፡፡ ይች ሀገር በተፈጥሮ ሀብት እግዚአብሔር የባረካት ነች፣ ይህን ተጠቅመን ድህነትን የምንቀርፍባትን ኢትዮጵያ እመኛለሁ፡፡