tirsdag 29. juli 2014

41 አለማቀፍ ድርጅቶች የታሰሩት ጋዜጠኞችና ጦማርያን በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጠየቁ

July 29/2014

የጸረ ሽብርተኝነት ህጉ ይሻሻል ብለዋል
ከዚህ በፊት በሽብርተኝነት የተፈረደባቸው እንዲፈቱ ጠይቀዋል
41 የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የፕሬስ ነጻነት አቀንቃኞች፣ አለማቀፍና ክልላዊ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትና የሙያ ማህበራት መንግስት በቅርቡ የሽብርተኝነት ክስ የመሰረተባቸውን ጋዜጠኞችና የዞን 9 ጦማርያን በአፋጣኝ እንዲፈታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከትናንት በስቲያ በላኩት ደብዳቤ መጠየቃቸውን ብሉምበርግ ኒውስ ዘገበ፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ አርቲክል 19 ምስራቅ አፍሪካ፣ ሲቪል ራይትስ ዲፌንደርስ፣ ወርልድ አሊያንስ ፎር ሲቲዝን ፓርቲሲፔሽን፣ ፔን አሜሪካና የመሳሰሉት አለማቀፍ ድርጅቶች በጋራ በጻፉት ደብዳቤ፣ መንግስት ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን በሽብርተኝነት እየከሰሰ ለእስር መዳረጉን መቀጠሉ ያሳስበናል፣ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ መገታት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ሶስቱ ጋዜጠኞችና ስድስቱ ጦማርያን ሶስት ወራት ለሚሆን ጊዜ ይህ ነው የሚባል ክስ ሳይመሰረትባቸው ያለአግባብ በእስር ላይ መቆየታቸውንና አንዳንዶቹም በምርመራ ወቅት እንግልት እንደደረሰባቸው መናገራቸውን የጠቀሰው ደብዳቤው፣ ይህም አግባብ አለመሆኑን ገልጿል፡፡
ጋዜጠኞቹና ጦማርያኑ በተመሰረተባቸው የሽብርተኝነት ክስ በረጅም አመታት እስር ብሎም በሞት ሊቀጡ እንደሚችሉ ስጋታቸውን የገለጹት ድርጅቶቹ፤ ይህም አለማቀፍ ህጎችን የሚጥስና በቀጠናው የተረጋጋ ሰላምና ደህንነት ለመፍጠር የሚደረገውን አለማቀፍ ጥረት ዋጋ የሚያሳጣ እርምጃ ይሆናል ብለዋል፡፡
መንግስት አግባብነት በሌለው የጸረ ሽብርተኝነት ህግ በቁጥጥር ውስጥ አውሎ ክስ የመሰረተባቸውን ጋዜጠኞችና ጦማርያን በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቅ አስፈላጊውን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ጥያቄ ያቀረቡት እነዚህ ድርጅቶች፤ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በጸረ ሽብር ህጉ ተከሰው የተፈረደባቸው ዜጎች ጉዳይ አግባብ አለመሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳይቀር እንዳመነበትና እንዳወገዘው አስታውሰዋል፡፡
ከጋዜጠኞቹና ከጦማርያኑ በተጨማሪም፣ ከዚህ በፊት በሽብርተኝነት ተከሰውና ተፈርዶባቸው ያለአግባብ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ መንግስት በአፋጣኝ እንዲፈታና የጸረ ሽብርተኝነት ህጉንም አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መስፈርቶችን በሚያሟላ መልኩ እንደገና አሻሽሎ እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል፡፡ኢትዮጵያ የአለማቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነትና የአፍሪካን የሰብዓዊና የህዝብ መብቶች ኮንቬንሽን ፈርማ የተቀበለች ሃገር እንደመሆኗ፣  መንግስት አለማቀፍ ህጎች የጣሉበትን ግዴታ በማክበር መሰረታዊ መብቶቻቸው ተጥሰው ለእስር የተዳረጉ ዜጎችን በሙሉ ከእስር እንዲለቅ ጠይቀዋል፡፡
ደብዳቤውን የጻፉት ድርጅቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. Amnesty International
2. ARTICLE 19 Eastern Africa
3. Central Africa Human Rights Defenders Network (REDHAC), Central Africa
4. CIVICUS: World Alliance for Citizen Participation
5. Civil Rights Defenders, Sweden
6. Coalition pour le Développement et la Réhabilitation Sociale (CODR UBUNTU), Burundi
7. Committee to Protect Journalists
8. Community Empowerment for Progress Organization (CEPO), South Sudan
9. Conscience International (CI), The Gambia
10. East and Horn of Africa Human Rights Defenders Project
11. Egyptian Democratic Association, Egypt
12. Electronic Frontier Foundation
13. Ethiopian Human Rights Project (EHRP)
14. Elma7rosa Network, Egypt  15. English PEN
16. Freedom Now
17. Front Line Defenders, Dublin  18. Human Rights Watch
19. International Women’s Media Foundation (IWMF)
20. Ligue des Droits de la personne dans la region des Grands Lacs (LDGL), Great Lakes
21. Ligue Iteka, Burundi
22. Maranatha Hope, Nigeria
23. Media Legal Defence Initiative
24. National Civic Forum, Sudan
25. National Coalition of Human Rights Defenders, Kenya
26. Niger Delta Women’s movement for Peace and Development, Nigeria
27. Nigeria Network of NGOs, Nigeria
28. Paradigm Initiative Nigeria, Nigeria
29. PEN American Center  30. PEN International
31. Réseau africain des journalistes sur la sécurité humaine et la paix (Rajosep), Togo
32. Sexual Minorities Uganda (SMUG), Uganda
33. South Sudan Human Rights Defenders Network (SSHRDN), South Sudan
34. South Sudan Law Society, South Sudan
35. Tanzania Human Rights Defenders Coalition, Tanzania
36. Twerwaneho Listeners Club (TLC), Uganda
37. Union de Jeunes pour la Paix et le Développement, Burundi
38. WAN-IFRA (The World Association of Newspapers and News Publishers)
39. West African Human Rights Defenders Network (ROADDH/ WAHRDN), West Africa
40. Zambia Council for Social Development (ZCSD), Zambia
41. Zimbabwe Human Rights NGO Forum, Zimbabwe

mandag 28. juli 2014

ፖሊቲካና የግለሰብ ጠባይ (ፕ/ር መስፍንወ/ማርያም)

July 28, 2014

ለእኔ ፖሊቲካና የግለሰብ ጠባይ እንደውሃና ዘይት የማይደባለቁ ነገሮች ይመስሉኛል፤ አጼ ምኒልክ ‹‹አመልህን በጉያህ›› ያሉት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፤ ዘይትና ውሀ በባሕርያቸው የሚለዩትን ያህል ፖሊቲካና ግለሰብም የባሕርይ ልዩነት አላቸው ማለት ነው፤ የወያኔ መሪዎች ምንም ነገር የማይሰምርላቸው፣ ከመጀመሪያውኑ እነዚህን ሁለት የማይደባለቁ ባሕርዮች አደባልቀው በመንሣታቸው ነው፤ ፖሊቲካ ለማኅበረሰቡ መቆርቆር ነው፤ ለሕዝቡ መቆርቆር ነው፤ ለአገር መቆርቆር ነው፤ የፖሊቲካ መነሻም ይኸው መሆን አለበት፤ ዓላማውም የማኅበረሰቡ፣ የሕዝቡ ልማት እንጂ ጥፋት አይደለም፤ የነበረውንና ያለውን ማጥፋት የፖሊቲካ ዓላማ ሊሆን አይችልም።

የደርግ መንደር ምሥረታ የሕዝብ ዓላማ ነበረው፤ የዓላማው መሣሪያ ግን የሕዝብ ሳይሆን ወታደራዊ ጉልበት ነበር፤ በዚህም ምክንያት የሕዝብ ዓላማ ያለው ሥራ የሕዝብን ህልውና በሚፈታተን የጉልበት መንገድ መከተሉ ዓላማው እንዳይሳካ፣ ሕዝብና አገዛዙ ባላንጣዎች ሆኑ፤ ጥሩው ዓላማ በከሸፈ ጉልበተኛነት ሳይሳካ ቀረ፤ በመንደር ምሥረታው ዓላማ ደርግ ክፋት ወይም ቂም ቋጥሮ አልተነሣም፤ ስሕተቱ ከውትድርና ባሕርይ የመጣ ይመስለኛል::

 ማጥፋት ዓላማ ሲሆንና ጉልበት የማጥፋት መሣሪያ ሲሆን ፍጹም የተለየ ነው፤ማጥፋት የሚመጣው ከግል ጠብና ከግል ቂም ነው፤ የራሱን ወይም የአባቱን፣ ወይም የእናቱን ቂም በልቡ ቋጥሮ ፖሊቲካ ውስጥ የሚገባ ሰው ለጥፋት የተዘጋጀ ነው፤ ለጥፋት የተዘጋጀ ሰው ፖሊቲካ ውስጥ ሲገባ እሳት አደጋ መኪና ላይ ቆሞ ቤት እንደሚያቃጥል ሰው ነው፤ አታላይ ነው፤ ዓላማውንም የዓላማውንም መሣሪያ አያውቅም፤ የሚንቀሳቀሰው በጥላቻና በቂም ነው፤ ወይ የሕጻን ልጅ ወይም የተስፋ-ቢስ ደደብ ጠባይ ነው፤ እንዲህ ያለ ሰው ፖሊቲካ ውስጥ የሚገባውም በዚሁ በደደብነቱ ምክንያት ነው፤ የደደቡ ፖሊቲከኛ ሥራ የማያስወቅሰው ፖሊቲከኛውን ብቻ አይደለም፤ በዚያ ፖሊቲከኛ የሚመራው ሰው ሁሉ አብሮ የሚወቀስ ነው፤ እንዲያውም በፖሊቲከኛው እውቀትና ችሎታ ማጣት የተነሣ የሚደርሰው ስቃዩና መከራው፣ ችግሩና አበሳው በዚህ ዓይነቱ ፖሊቲከኛ ላይ አይደርስም፤ ሰቃዩንና መከራውን፣ ችጋሩንና አበሳውን የሚጋፈጠው በዚህ ዓይነቱ ፖሊቲከኛ የሚመራው ሕዝብ ነው፤ ሕዝብ መሪውን በትክክል መምረጥ ያለበትም ለዚህ ነው፤ ተንጋሎ የተፋ ለራሱ ከፋ የሚባለው ይደርሳል።

 ዛሬ እያጎረሰ ምረጠኝ የሚለው ነገ ቆዳህን ልግፈፍ ይላል፤ እንደምንሰማው ወደቦሌ አካባቢ ‹መቀሌ› የሚባል የሰማይ-ጠቀስ ፎቆች መንደር አለ ይባላል፤ የዚህ መንደር ባለቤቶች የወያኔ ባለሥልጣኖች ለመጦሪያቸው የሠሩአቸው ናቸው ይባላል! በአንጻሩ እኔ የማውቀው አንድ ወያኔ አለ፤ በውጊያ ላይ በደረሰበት ጉዳት ይመስለኛል አንድ ዓይኑን ክፉኛ የታመመ ነው፤ ስለሚሸፍነው የጉዳቱን መጠን ባላውቅም ጉዳቱ ይሰማኛል፤ ሚስትና ሁለት ልጆች አሉት፤ ሚስቱ ጠዋት በጀርባዋ ከባድ ነገር አዝላ ልጆቿን ወደተማሪ ቤት ታደርሳለች፤ እንደምገምተው አንድ ቦታ ገበያ ዘርግታ የምትሸጠውን ትሸጣለች፤ ወደማታም እንደጠዋቱ ተጭና ወደቤትዋ ከልጆችዋ ጋር ትመለሳለች፤ የዚህ አንድ ጉዳተኛ ወያኔ ቤተሰብና የባለሰማይ-ጠቀስ ሕንጻ ባለቤቶች የሆኑት ወያኔዎች ኑሮ የሰማይና የመሬት ያህል የተራራቀ ነው፤ ለአንድ ዓላማ አብረው የተነሡ ሰዎች በሃያ ዓመታት ውስጥ ይህንን ያህል መራራቃቸው በጣም ያሳዝናል ብሎ ማለፉ አይበቃም፤ ደሀው ወያኔ ሕመሙንና ስቃዩን የምገነዘብበት መንገድ ባይኖረኝም አንድ ዓይኑን ማጣቱ ብቻ ጉዳቱን ያሳየኛል፤ እንግዲህ ባለሰማይ-ጠቀስ ወያኔዎችና ይህ ደሀ ወያኔ በጦርነት ላይ ያደረጉት አስተዋጽኦ በጉዳታቸው ቢመዘን የዚህ ደሀ ወያኔ እንደሚበልጥ አልጠራጠርም፤ ቢያንስ እንደአንዳንድ መሪዎቹ አልሸሸም፤ ታዲያ በምን ተበላልጠው እነሱ እዚያ ላይ እሱ እዚያ ታች ሆኑ? ይህንን አሳዛኝና አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ሁነት የሚያመጣው እሳት አደጋ መኪና ላይ ቆሞ ቤት እንደሚያቃጥለው ሰው ያሉ ፖሊቲከኞች-ነን-ባዮች የተዛባ ሚዛን ነው፤ በዚህ የተዛባ ሚዛን በየጦር ሜዳው አሞራ የበላቸው የታደሉ ናቸው፤ ተስፋቸው ትርጉም አጥቶ ሳያዩ፣ ውርደት ሳይሰማቸው፣ ችግርንና ግፍን ሳይቀምሱ ቀርተዋል፤ ለነገሩ ነው አንጂ እንኳን ወያኔ በሥልጣን ምኞት ከወገኑ ጋር የተዋጋውና ከኢጣልያ ወራሪ ጦር ጋርም የተዋጉት አርበኞችም ተመሳሳይ ዕድል ገጥሟቸው ነበር፤ ዛሬ ኢትዮጵያን ለክፉ ነገር የዳረጋት የእነዚህ ሰዎች ጡር ይመስለኛል።

የፖሊቲካ ተግባሮቻቸውን ከግል ጠባዮቻቸው እየለዩ የሚኖሩ ፖሊቲከኞች በአንዳንድ አገር አሉ ለማለት ይቻላል፤ ከአውሮፓ ስዊድንና ኖርዌይ፣ ስዊትዘርላንድ፣ ከእስያ ዛሬን እንጃ እንጂ በነኔህሩ ዘመን ህንድ የሚጠቀስ ነበር፤ በአብዛኞቹ አገሮች ግን ፖሊቲከኞቹ እንደየደረጃቸው ለሀምሳ፣ ለሠላሳ፣ ለሀያ፣ ለአሥር ሰዎች የሚበቃ የተሟላ ቤት ውስጥ አምስት መቶ ሰዎችን የሚያስተዳድር ደመወዝ እያገኙ የሚኖሩ ሲሆኑ ምግባቸው ግን አብዛኛውን ጊዜ የአንድ ሰው ይመስለኛል፤ የዚህ ትርጉሙ ምንድን ነው? ለፖሊቲከኞቹ መቀማጠል በላባቸው የሚከፍሉት ደሀዎች ናቸው፤ ከተፎካካሪዎቻቸው ተንኮል የሚጠብቋቸው ደሀዎች ወታደሮች ናቸው፤ ምርጫ ሲደርስ በነቂስ ወጥተው ፖሊቲከኞቹን የሚመርጧቸው ጦማቸውን የሚያድሩት ደሀዎች ናቸው፤ እነዚህም ጊዜያዊና ትንሽ የግል ጥቅምን ከዘላቂው የአገርና የሕዝብ ጥቅም መለየት ያልቻሉ የሕዝብ ክፍሎች ከተበላሹት ግለኛ ፖሊቲከኞች የማይለዩ ናቸው።

ወደፍሬ ነገሩ ልምጣና፤- በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖሊቲከኞች የሚወጡትና የሚወርዱት ለየትኛው ዓላማ ነው?

1. የበትረ መንግሥቱን ሥልጣን ከወያኔ ፈልቅቆ ለማውጣትና ለመያዝ?
2. በምክር ቤት ገብቶ የወያኔ አጫፋሪ በመሆን ደህና ደመወዝና ነጻ ቤት ለማግኘት?
3. ከውስጥ ሆኖ ወያኔን ለማጋለጥ?

የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖሊቲካ ቡድኖችን ሲደግፍ የፖሊቲካ ቡድኖቹን ዓላማዎች አጣርቶ በማወቅ መሆን አለበት፤ አለዚያ በሎሌነት እየኖሩ ጌታ መለወጥ ነው።

fredag 25. juli 2014

መኢአድ የሕዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች መንግሥት በአስቸኳይ እና በተገቢው ሁኔታ መልስ እንዲሰጣቸው ጠየቀ

July 25/2014
ከመላው ኢዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ
(ፎቶ ከፋይል)
(ፎቶ ከፋይል)

ለረዥም ጊዜ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ በነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ህውሓት/ኢህአዴግ የወሰደውን የኃይል እርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን ፡፡ እንደ መኢአድ እምነት ለጥያቄዎቻቸው ተገቢውን መልስ መስጠት ሲገባ በግልባጩ መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሳዘነና ያስቆጣ የኃይል እርምጃ መወሰዱ የህውሓት/ኢህአዴግን ማንነት በተግባር ያሳየ ድርጊት ነው፡፡
ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም የእስልምና እምነት ተከታዮች በአንዋር መስጊድ በፀሎት ሥነ-ሥርዓታቸው ላይ ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው ጥያቄዎቻቸውን ወደጐን በመተው የኃይል እርምጃ በመወሰዱ ችግሩ ይፈታል ብለን አናምንም፡፡ ሆኖም በእለቱ በእምነቱ ተከታዮች ላይ እና በአካባቢው በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የፀጥታ ሃይሎች የወሰድትን የሀይል እርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን፡፡ አሁንም ቢሆን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥያቄዎቻቸው በሰላማዊና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት መፈታት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ የህውሓት/ኢህአዴግ አባገነን ሥርዓት በእምነት ተቋማት ላይ እጁን አስረዝሞ የሚያደርገውን የአፈና ተግባር ማቆም አለበት፡፡
መኢአድ ለእስልምና እምነት ተከታዩችም የሚያስተላለፈው መልዕክት ከአሁን ቀደም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቻችሁን እንዳቀረባችሁት ሁሉ መፍትሔ እስክታገኙ ድረስ በሰላማዊ መንገድ መቀጠል እንዳለባችሁ ያሳስባል፡፡ በመጨረሻም መኢአድ የሚያምነው ችግሩ ስር ነቀል መፍትሔ የሚያገኘው የህውሓት/ኢህአዴግ አባገነን ሥርዓት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲተካ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የሙስሊሙ ማህበረሰብ መኢአድ የሚያደርገውን ሰላማዊ ትግል በመቀላቀልና በመደገፍ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፉለን፣፣
አንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም

torsdag 24. juli 2014

የትግል ጓዶቼን ባሰብኩ ጊዜ! (ኣቶ ኣስራት ኣብርሃ – ኣንድነት ፓርቲ)

ሀብታሙ አያሌውና ዳንኤል ሺበሺ የማውቃቸው አንድነትን ከመቀላቀሌ ቀደም ብሎ ነው። የመድረክ ስራ አስፈፃሚ ሆኘ በምስራበት ወቅት የባለራዕይ ወጣቶች ሀያ ሁለት አከባቢ በሚገኝ አንድ ሆቴል አድርጎት በነበረው ስብሰባ ለመገኘት በሄድኩ ጊዜ ነበር ሀብታሙን ለመጀምሪያ ጊዜ በአካል ያየሁት። የባለራዕይ ወጣቶች እንዲያ ተሰባስበው ስለሀገገር ጉዳይ ሲመክሩ ስመለከት ተስፋ ነበር የታየኝና ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም ነበር። አዲሱ ትውልድ በራሱ ጉዳይ ራሱን ችሎ ሲመክር በህይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ ያየሁበት ቀን በመሆኑ ነው ደስታዬ እጥፍ ድርብ ያደረገው። ከስልሳው ትውልድ ተፅዕኖ የተላቀቀ ፍፅም አዲስ የሆነ አስተተሳስብ ያለው፤ በአከባቢያዊነት ወይም በቋንቋ ሳይሆን በሀሳብ በኢትዮጵያዊነት የተሰባሰበ፤ አንድነታችን ከልዩነታችን በላይ ነው የየሚል አዲስ ትውልድና አደረጃጀት መሪ ሆኖ ሳገኘው ለሀብታሙና ለአባላቱ አድናቆቴን የምገልፅበት ቋንቋም ሆነ አቅም አልነበረኝም። ንግግር እንንዳደርግ ስጋበዝ “ይሄ ተቋም የወደፊት የሀገራችን መሪዎች የሚፈጠሩበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ነበር ያልኩት፤ በኋላ የተወሰኑ በአንድነት ሳገኛቸው ደስ ብሎኛል።
Habtamu Ayalew
ሀብታሙ በተለያዩ ጊዜያት ንግግር ሲያደርግ ተመልክቸዋለሁ አንደበተ ርቱዕ የሆነ የፖለቲካ ሰው ነው፤ በተለይ በፀረ ሽብር አዋጁ ላይ በቴሌብዥን ቀርቦ ያደረገው ክርክር ብዙ ሰው የሚያስታውሰው ይመስለኛል። የፖለቲካ እስረኞችን ለመጠይቅ ወደ ዝዋይ በሄድን ጊዜ አንድ ወጣት በቴሌብዥን አይቼሀለሁ ሲለው ስምቻለሁ።
ሀብታሙ ባለትዳርና የልጅ አባትም ነው። ልጁ ማታ ማታ “ሀብታሙ ይመጣል ተይ በሩን አትዝጊው!” እያለች እናቷን እንደምታስቸግር ሰማሁ፣ የልጅ ነገር ልጅ ያለው ነውና የሚያውቀው እንደልጅ አባት ሆነህ ስታይው ያማል!
ዳንኤል ሽበሺ እጅግ የሚገርም ሰው ነው። ዓረና ወደ አንድነት እንዲመጣ ብጣም ይፈልግ ነበርና በዚህ ጉዳይ ላይ ከእኔ ጋር በተደጋጋሚ ተነጋግረናል፤ከእኔ የአቶ ገብሩ አስራት ስልክ ውስዶ ተቀጣጥረው አነጋግሮታል፤ አንድነትን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ፓርቲ የማድረጉ ሂደት ጥንክረው ሲሰሩ ከነበሩ የአንድነት ሰዎች ዳንኤል አንዱ ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ አንድነትን በሁለት እግሩ እንዲቆም ብዙ ፅህፈት ቤቶችና አባላት እንዲኖሩት ጊዜው፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን ሳይሰስት የሰዋ ምርጥ የአንድነት ልጅ ነው ዳንኤል ሸሺበሺ! በዚህ ላይ የቁጫ ህዝብ እንደህዝብ እንዲታወቅቅ ያደረገ፤ የቁጫ ህዝብ ታጋይና የሰብኣዊ መብት ተማጓች ነው።
Daniel Shibeshi
ዳንኤል ሺበሺ ለእኔ የትግል አጋሬ ብቻ አይደለም፤ አንድ ሰፈር ስለነበር ጓደኛዬም ነው። አንዳንድ ጊዜ አየር ጤና በሚገኘው ሳሚ ካፌ እየተናኘን ሻይ ቡና እንል ነበር። ከታሰረ በኋላ ሳሚ ካፌ ጭር ብሎብኛል፤ እናም ወደዚያ አልሄድም፤ ጥሩ ስሜትም አይሰማኝም።
የዳንኤል ቤተሰቦች እሱን ለመጠየቅ ወደ ማዕከላዊ በሄዱ ጊዜ “እንዴት ነው መገናኘት አይቻልም ወይ?” ብለው ጠባቂዎቹ ቢጠይቋቸው፤ ፌስቡክ እንዲጠቀሙ ስለተፈቀደላቸው በፌስቡክ ተከታተሉ እንዳሏቸው ሰማሁ፤ እውነት ፌስቡክ በማዕከላዊ መጠቀም የሚቻል ቢሆን ኖሮ እኔ ራሴ እሰሩኝ ብዬ እሄድ ነበር። ምክንያቱም ውጭ ገንዘብ እየከፈልኩ ነው ኢንተርኔት የምጠቀመው። እስሩ እንደሆነ አሁንስ መቼ ነፃ ሆንኩ! በሰፊው ስርቤት አይደለ ያለሁት!
እንግዲህ እስሩ እየቀጠለ ነው፤ አንንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮነን፣ ርዕዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋ፤ በቀለ ገርባ፣ ውብሸት ታዬ፤ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፤ ዞን ዘጠኝ፤ አብርሀ ደስታ፣ ሀብታሙ አያሌው፤ የሽዋስ ሌሎችም በርካታ ዜጎች በሽብርተኝነት ስም በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ፤ እንግዲህ ሽብርተኛ ማለት እኔ እንደሚገባኝ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም ቦንብ ያፈነዳ እንደሆነ ነው! ኢህአዴግ ሽብርተኛ የሚለው ግን የእርሱን ስርዓት በሰላማዊም ሆነ በማነኛውም መንገድ የሚቃወሙት ነው! በዚህ ጉዳይ ላይ እርሱ እንደ መንግስት እኛ እንደ ዜጋ እኮ መግባባት አልቻልንም። በመሆኑም እስርን ራሱ እንደ አንድ የሰላማዊ ትግል ስልት እንወስደው ዘንድ ነው የምንገደደው!
አብርሃ ደስታን ባሰብኩ ጊዜ!
Abraha Desta
በ2003 ዓ.ም. አጋማሽ በአንዱ ዕለት መቀሌ በሚገኘው የዓረና ዋና ፅህፈት ፀሀፊዬ በአጋጣሚ ስላልነበረች ብቻዬ ቁጭ ብያለሁ። ከሰዓት ነበር፤ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጣ፤ ስሙንና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሰራ ነገረኝ። በማስከተልም አባል ለመሆን እንደመጣ አስረዳኝ፤ እኔም የፓርቲውን ህገ ደንብና ፕሮግራም በመሰጠት በመጀመርያ እነዚህን አንብብና ከዚያ የአባልነት ፎርም ትሞላለህ አልኩት። ቀድሞ አግኝቷቸው ኖሮ አይቸዋለሁ አለኝ። እንግዲያውም በጣም ጥሩ ብዬ የአባልነት ፎርም ሰጥቼው ሞላ። ያ ሰው አብርሃ ደስታ ነበር። ከዚያ በኋላ በተመደበበት መሰረታዊ ድርጅት ውስጥ በንቃት ከመሳተፉም በላይ ለአባላት ስልጠና በመስጠት በእኩል ጥሩ አስተዋፅኦ ማድረግ ጀምሮ ነበር። ከዚያ በኋላ እኔ ወደ አዲስ አበባ በመምጣቴ በየጊዜው መገናኘታችን ቢቀርም አዲስ አበባ ሲመጣ አንድ ሁለት ጊዜ አግኝቼዋለሁ፤ ሁልጊዜ ስንገናኝ ባደረግናቸው ውይይቶች ጥሩ ተግባቢና ሀሳብ ለመቀበል የማያዳግትው ሰው ሆኖ ነው ያገኘሁት። በነገራችን ላይ ብዙ ሰው የአረና አባል መሆኑ ያወቀው በአረና ሶስተኛ ጉባኤ አመራር ሆኖ በተመረጠ ጊዜ ነበር።
በነበረው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የትግራይ ህዝብ፤ በተለይ ደግሞ ምንም የሚዲያ እድል የሌላቸው የክልሉ ገበሬዎች ድምፅ ሆኖ አገልግለዋል፤ በስርዓቱ እስኪታሰር ድረስ። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን በትናንትናው ዕለት ሕድሮም የሚባል የአረና አባል ከወቅሮ አፅቢ ደውሎ እየደረሰባቸው ስላለው ሰቆቃ ነገረኝ፤ ሌሊት የአረና አባላት ሲደበደቡና ሲጨሁ በድምፅ የተቀዳውን አሰማኝና “አብርሃ ነበር ድምፃችን፤ እሱ ታሰረብን” ሲለኝ እንባ ነው የተናነቀኝ። አሁን ጥያቄው ስርዓቱ አብርሃን በማሰር የህዝቡን የፍትህና የነጻነት ጥያቄ ዝም ማሰኘት ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ነው። በማህበራዊው ሚዲያ ብዙ አዳዲስ ወጣቶች እያየሁ ነው፤ ስለዚህ ትግሉ ተጠናክሯል ማለት ነው ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል!

mandag 21. juli 2014

በሰሜን ሸዋ የመርሃቤቴ ወረዳ ህዝብ ከወያኔ የፀጥታ ሃይሎችና ፌደራል ጋር ከባድ ውጊያ እያካሄደ ነው፣

July22/2014

ውጥረት በሰሜን ሸዋ መርሃቤቴ በርትቷል

ደብረብርሃን አከባቢ መግቢያና መውጪያ መንገዶች ተዘግተዋል።
ለወረዳው አለም ከተማና አካባቢዋ አገልግሎት ይውላል ተብሎ ከብዙ ጊዜ በሁአላ የገባውን መብራት የወያኔ መንግስት ህዝቡ የሚገለገልበትን መብራት አቁሞ ትራንስፎርሜሽኖቹን ነቅሎ ለአስቸኩአይ ጉዳይ ይፈለጋል ብሎ ወደ ትግራይ ለመውሰድ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የወረዳው 27ቱም ቀበሌ ተጠራርቶ ትራንፈርመሩን በቁጥጥር ስር በማድረግ ከላይ ከተጠቀሱት የወያኔ የፀጥታ ሃይሎች ጋር ኣሁን ድረስ ውጊኣ እያደረገ ሲሆን እስካሁን 7 የወያኔ ወታደሮች የሞቱ ሲሆን ከህዝብ ታጣቂ በኩል 1 ሞቷል። ባሁኑ ሰዓት ወረዳውን መሉ በሙሉ የህዝቡ ታጣቂ ተቆጣጥሮት ይገኛል። ወያኔ ከአዲስ አበባና ከተለያዩ አካባቢወች ተጨማሪ ሃይል ወደ አካባቢው እያንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቁኣል።ሁኔታው የሚመለከታችሁ ወገኖች ሁሉ እየሆነ ያለውን ሁሉ በመከታተልና አስፈላጊውን ድጋፍ እንድታደርጉ ያስፈልጋል።
ቁስለኞች ሆስፒታሉን አጣብውታል ። ቁስለኞቹ የሚታከሙት በፖሊስ ታጅበው ሲሆን ህክምናውን እንደጨረሱ ውእደ እስርቤት ይወሰዳሉ ።ከቦታው የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እስከመቼ ተታለን እንኖራለን የሚሉ የሰሜን ሸዋ ነዋሪዎች ዱር ቤቴ ብለው ሸፍተዋል። ከዚህ በታች የምትመለከቱት ከአከባቤው ከሚገኘው ሆስፒታል የተላከልንን ምስል ነው።

ዶክተሮቹን በስልክ ለማነጋገር እንደሞከርኩት የወመኔው ወታደሮች ቁስለኞች ከቁጥር በላይ ናቸው።
23
10502071054430

lørdag 19. juli 2014

የሰማያዊ ፓርቲዋ ወጣት ወይንሸት ሞላ ተፈንክታ፣ እጆቿ በፋሻ ጠቅልሎ፣ ሰውነቷ ዝሎ ፍርድ ቤት ቀረበች

July 19/2014

(ፎቶው የተገኘው ከሰማያዊ ፓርቲ ነው)
(ፎቶው የተገኘው ከሰማያዊ ፓርቲ ነው)
በትናንትናው እለት የአንዋር መስጊድ አካባቢ የሕወሓት አስተዳደር በንጹሃን የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ አሰቃቂ እርምጃ እየወሰደ በሚገኝበት ወቅት መርካቶ አካባቢ ለሥራ ጉዳይ ሄዳ የነበረችው የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤትና የሴቶች ጉዳይ አባል ወጣት ወይንሸት ሞላ በደህነንቶች ታፍና ከተወሰደች በኋላ ከፍተኛ ድብደባ ሲፈጸምባት ቆይቶ በዝግ ችሎት ቀርባ 14 ቀን የምርመራ ቀጠሮ ተጠየቀባት።
የነፃ አሳቢ ዜጎች መሰቃያ በሆነውና ከማዕከላዊ አጠገብ በሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስር ቤት ውስጥ የምትገኘው ወጣት ወይንሸት ማንም ሰው እንዳይጠይቃት በፖሊሶቹ መከለከሉ ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ዛሬ ረፋዱ ላይ ሜክሲኮ አካባቢ ያለ ፍርድ ቤት የቀረብቸው ወጣት ወይንሸት ምንም እንኳ ችሎቱ በዝግ ቢደረግም ጭንቅላቷ ተፈንክቶ፣ ቀኝ እጇ በፋሻ ተጠቅልሎና አንገቷ ታስሮ የተመለከቷት ሲሆን የህግ አማካሪ እንዳታገኝም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መከልከሉን የዘ-ሐበሻ ምንጮች አረጋግጠዋል።
ዘ-ሐበሻ

አቶ አንዳርጋቸው ታፍኖ የተወሰደበት ቦታ እስከአሁን አልታወቀም ነገር ግን በደህንነት ሰዎች በደረሰበት ድብደባ ራሱን በመሳቱ ለህክምና ከአዲስ አበባ ውጪ ይዘውት ወጠዋል የሚሉ አስተያየቶች እየተበራከቱ ነው።

July 19, 2014
አባይ ሚዲያ 
አቶ አንዳርጋቸው ታፍኖ የተወሰደበት ቦታ እስከአሁን አልታወቀም ነገር ግን በደህንነት ሰዎች በደረሰበት ድብደባ ራሱን በመሳቱ ለህክምና ከአዲስ አበባ ውጪ ይዘውት ወጠዋል የሚሉ አስተያየቶች እየተበራከቱ ነው።
ዛሬ የአዲስ አበባ ምንጫችን ብዙ ቦታዎችን ለማካለል ሞክሬ ነበር ነገር ግን የአንዳርጋቸው ይኖርበታል ተብሎ የሚገመቱ ቦታዎችን ማግኘት እንዳልቻለ ይሁን እንጂ ከደህነነት ሰዎች አንዱ በሆነ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሊኖርም እንደሚችል የግል አስተያየቱን ልኮልናል።
ዘጋቢያችን አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በማናገር አቶ አንዳርጋቸው በአሁኑ ሰአት ከሰውነት ክፍሉ ውስጥ አንዱን ሰብረዉት ወይም ቆርጠውት እንደሚሆን  ስቃዩን በማብዛት ነገር ግን  እንዳይሞትባቸው ከአዲስ አበባ ውጪ ለህክምና ይዘውት ወጥተው ይሆናል የሚል በርካታ አስተያየቶች  መሰብሰቡን ዘግቦል።
አዲስ አበባ ላይ ሊያክሙት አይችሉም እንዴ ብለን ላነሳንለት ጥያቄ ሲመልስ፡ ይህን በአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ሊያደርጉት አይችሉም 1ኛ መረጃው ይወጣባቸዋል የራሳቸውን ሆስፒታል እንኮን አዲስ አበባ ላይ አያምኑትም። በወያኔ ውስጥ ውጥረት አለ! ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰውየውን ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ግራ የገባቸው ይመስላል። ስለዚህ እውነትም በአካሉ ላይ ጉዳት ደርሶበት ከሆነ ወደ ማይታወቅበት ስፍራ ወስደው ሊያሳክሙት ይችላሉ የሚለው ገዢ ሃሳብ ያመዝናል።
ይሁን እንጂ አቶ አንዳርጋቸው በሚያደርሱበት ጭካኒያዊ ድብደባ ሂወቱ በድንገት ሊያልፍ የሚችልበት አጋጣሚም ከፍተኛ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢቲቪ ድብደባውን በመደበቅ በደረሰበት አደጋ  ሂዎቱ በእስር ቤት አለፈ የሚል ዜና ሊያሰማን ይችላል የሚል ስጋት አለኝ ሲል አያይዞ ስጋቱን ገልጾልናል።
በዚህ አጋጣሚ አቶ አንዳርጋቸውን የታፈነበትን አካባቢ እና ቦታ ለድህረ ገጻችን ከሀገር ውስጥ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን መረጃ ለምትሰጡን አባይ ሚዲያ ማበረታቻ እንደሚሰጥ ማሳወቅ እንፈልጋለን፡፡

fredag 18. juli 2014

ፌደራል ፖሊስ ሕዝቡን ሲቀጠቅጥ፣ ሲያሸብር፣ አንዋር መስጊድን ሲከብና ሙስሊሙን ሲያስር የሚያሳዩ ፎቶዎች

ከድምጻችን ይሰማ
ሰላማዊው ሙስሊም እረፍት የነሳቸው የመንግስት ሃይሎች ዛሬም የጎዳና ላይ ነውጥ ፈጥረው እየደበደቡ እና ያለምንም ልዩነት መንገድ ላይ ያገኙትን ሁሉ እያሰሩ ነው፡፡ ፖሊሶች ከተክለሃይማኖት ጀምሮ አንዋር መስጂድ ድረስ መንገድ ዘግተው ቆይተዋል፡፡ አደባባይ ላይም ያገኙትን እያሰሩ ነው፡፡ አንድ ፖሊስ በተፈጠረው ግርግር በራሳቸው በፖሊስ መኪና ተገጭቶ ከፍተኛ አደጋ ደርሶበታል። መንግስታዊ ሽብር ዜጎች ሰላም እንዳይሆኑ የሚያደርግ ፀረ ህዝብ አቋም ነው! ህዝበ ሙስሊሙ ዛሬም በቀደሙት መንግስታት ይደርስበት እንደነበረው በእምነቱ እየተጨቆነ በአምልኮ ቤቱ እርምጃ እየተወሰደበት ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ዲኑን እስከዛሬ ያቆየው በመስዋእትነት ነው! ለዚህ ድንቅ ትውልድ ምስጋና ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም!
demtschin yesema 1
demtschin yesema 2
demtschin yesema 3
demtschin yesema 4
demtschin yesema 5
demtschin yesema 6
demtschin yesema 7

የዘንድሮ እስር ‹‹ጸበል ቅመሱ›› ሁነብኝ ጃል! (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)

July18/2014

(የህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 30 ሳይሻር ተሽሮ ከሆነ መሻሩን ተቃዋሚዎች ይወቁት!)
========
የምንወዳት ኢትዮጵያ ሀገራችን በተለያዩ ሥርዓታት ውስጥ የተለያዩ የሰዎችን እስር አስተናግዳለች፤ ዛሬም እያስተናገደች ትገኛለች፡፡
በ97 ዓ.ም ምርጫውን ተከትሎ የቅንጅት አመራሮች፣ የግል ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማኅበራት አመራሮች …ታስረው ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት በኋላ በይቅርታ፣ በነጻ …መፈታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጊዜም በኋላ፣ በተለይ አፋኝ በሆነው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ብዙዎች ታስረዋል፣ እየታሰሩም ይገኛሉ፡፡
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና
በዘንድሮ ዓመት ግን የምናየው እስር የተለየ ሆነብኝ፡፡ የሕገ- መንግሥቱን አንቀ ጽ 30 መሰረት በማድረግ ሰላማዊ ሰልፍ የሚጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና አባላቶቻቸው ለሰልፉ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት እየተያዙ ለቀናቶች ታስረው መፈታት የተለመደ ሆነ፡፡ (ወይ ይህ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 30 ሳይሻር ተሽሮ ከሆነ መሻሩን ተቃዋሚዎች ይወቁት!)
አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ይሄንን እርምጃ ዘንድሮ በደንብ አይተውታል ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያኖች፣ ፖለቲከኞችና በርካታ ዜጎች በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል፣ ክስም ተመስርቶባቸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንቡን በመፈረም የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆነው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የፊታችን ቅዳሜ ሜክሲኮ በሚገው የመብራት ሐይል አዳራሽ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ አቅዶ ስድስት አባላቱ ዛሬ ቂርቆስ አካባቢ በመኪና ህዝቡን በመቀስቀስ ላይ እያሉ መታሰራቸውን ሰማን፡፡
ፖሊስም ‹‹የስብሰባ እንጂ የቅስቀሳ ፈቃድ አልያዛችሁም›› በማለት ጥዋት አካባቢ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንዳሰራቸው እና የፓርቲው አመራሮች በፖሊስ ጣቢያ ድረስ በመገኘት ከኃላፊዎቹ ጋር ቢነጋገሩም ልጆቹ ቃላቸውን መስጠታቸውንና ፖሊስ ልቀቃቸው የሚል ትዕዛዝ ሲደርሰው እለቃቸዋለሁ ማለቱን ወዳቻችን ዳዊት ሰለሞን በፌስ ቡክ ገጹ ዛሬ አስነብቦን ነበር፡፡
እኔም እንደጋዜጠኛ ጉዳዩን ለማጣራት የቀድሞ የኢዴፓ ሊቀመንበር ወደሆኑት አቶ ሙሴ ሰሙ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ደውዬ እውነት መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ እንዲያውም፣ አቶ ሙሼ የተደረገው ነገር አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ በነገው ዕለት በግል መኪናቸው ቅስቀሳ ለማድረግ ማቀዳቸውን አጽንኦት ሰጥተው ነግረውኛል፡፡
እንዲሁም፣ በዛሬው ዕለት በእነሀብታሙ አያሌው የክስ መዝገብ አንድነት ፓርቲ ላቀረበው አቤቱታ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በአራዳ ፍርድ ቤት ለማድመጥ በችሎት ተገኝተው የነበሩ ስድስት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባላት (ዳንኤል ፈይሳ፣ አብነት ረጋሳ፣ ጥላዬ ታረቀኝ፣ ፋሲካ አዱኛ፣ ብርሀኑ ይግለጡና መሰለ አድማሴ) በደህነት ሃይሎች ተይዘው በቶዮታ ደብል ጋቢና ኮድ 3-50559 መኪና ወደ ማዕከላዊ መወሰዳቸውን የፍኖተ ነፃነት የማዕከላዊ ምንጮች ገልጸው ነበር፡፡ ከሰዓታት በኋላም የታሰሩት የፓርቲው አባላት ተፈትዋል፡፡
እስያዊቷ ሀገር ማሌዥያ፣ የመንገደኛ አውሮፕሏኖቿ አንዴ ሲሰወሩ፣ አንዴ ሲከሰከሱና በሮኬት ሚሳይል ሲመቱ ዛሬም ድረስ ደርሰዋል፡፡ በዛሬው ዕለት እንኳን ከሆላንድ አመስተርዳም ወደ ማሌዥያ ኩዋላላምፑር ሲጓዝ የነበረ ቦይንግ 777 የመንገደኞች አውሮፕላን በሮኬት ሚሳይል ተመትቶ (በራሽያ መሆኑ እየተነገረ ነው) በዩክሬን ግዛት በመከስከስ 295 ሰዎች አልቀዋል፡፡ 
በሀገራችን ደግሞ ሁሉን ዓቀፍ የእስር እርምጃ በመንግሥታችን እየተወሰደ መመልከቱ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ነው፣ በርዕሴ ‹‹የዘንድሮ እስር ‹‹ጸበል ቅመሱ›› ሁነብኝ ጃል!›› በማለት የገለጽኩት፡፡
ወዳጄ ዳዊት ሰለሞንም “Ethiopia the land of prisoners” (ኢትዮጵያ የእስረኞች ምድር) የሚል መልዕክት ከአምስት ሰዓታቶች በፊት በፌስ ቡክ ገጹ አስፍሮ ተመልክቻለሁ፡፡ ማሌዥያ በአውሮፕላን አሳዛኝ አደጋ ጣጣ በዓለም ስትታወቅ እኛ ደግሞ ዜጎችን በገፍ መማሰር እንታወቅ?!
እኔ ደጋግሜ ብያለሁ፣ እስር መፍትሄ አይደለም፡፡ ዜጎችን ማሰር ብዙ የማይገርምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ መንግስታችን ሆይ! ዜጎችን የማሰር ጉዞውን በአንክሮ አስብበት! አሊያ… ከባድ ነው! መዘዝ አለው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! —

mandag 14. juli 2014

ሰበር ዜና - የእንግሊዝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከእንግሊዝ ለኢትዮጵያ ዕርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶች በሙሉ (የእንግሊዝ መንግሥትንም ጨምሮ) ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ቅድምያ መስጠታቸውን እና አለመስጠታቸውን በሚያጣራ መልኩ ሕጋዊ ምርመራ እንዲደረግ አዘዘ

July14/2014
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት (ሁማን ራይት) ዛሬ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ባሰራጨው ዜና  የእንግሊዝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከእንግሊዝ ለኢትዮጵያ  ዕርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶች በሙሉ (የእንግሊዝ መንግሥትንም ጨምሮ) ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ  መብት ይዞታ ቅድምያ መስጠታቸውን እና አለመስጠታቸውን በሚያጣራ መልኩ ሕጋዊ ምርመራ እንዲደረግ ያሳለፈውን ውሳኔ  ''ጠቃሚ እርምጃ'' በማለት አሞካሽቶታል።
ውሳኔው በተለይ በቅርቡ ከአርበኛ አንዳርጋቸው ፅጌ መታገት በኃላ የእንግሊዝ መንግስት  ''የባህር ማዶ የልማት ትብብር ድርጅት'' (UK Department for International DEVELOPMENT (DFID) ) ለኢትዮጵያ መንግስት የገንዘብ ድጎማ ሊያደርግ የነበረ ከመሆኑ አንፃር የዛሬው ውሳኔ ከፍተኛ መልዕክት ማስተላለፉ አይቀርም።በሌላ በኩል የዛሬው የፍርድቤቱ ውሳኔ ይሄው የልማት ድርጅት (DFID) በበቂ ሁኔታ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ ይዞታ ጉዳይ አለመመርመሩን ጠቁሞ በእዚሁ አዲሱ የፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ሕጋዊ ምርመራ እንዲደረግበት ማዘዙን ያብራራል።
የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የእርምጃውን ፋይዳ ሲያስረዳ  የድርጅቱ የአፍሪካ ክፍል ተጠሪ የተናገሩትን በመጥቀስ ነው።እንዲህ ይነበባል -

''የእንግሊዝ ከፍተኛው ፍርድቤት ውሳኔ ለሌሎች መንግሥታት እና እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የማንቅያ ጥሪ ነው።ምክንያቱም ሀገራትም ሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚሰጡትን የልማት ፕሮግራም ሁሉ ቅድምያ ከሰብዓዊ ይዞታ አንፃር እንዲመለከቱ ያደርጋል''ይላል።

mandag 7. juli 2014

ሰበር ዜና: እንግሊዝ ከፍተኛ የሚኒስቴሮች ቡድን ከማስጠንቀቂያ ጋርወደ አዲስ አበባ ትልካለች ።


የካምብሪጅ ጠበቆች ቡድን ከእንግሊዝ ውጪ ጉዳይ ባለስልጣናት ጋር ነገ በአንዳርጋቸው ዙሪያ ይሰበሰባል። እንግሊዝ ከፍተኛ የሚኒስቴሮች ቡድን ከማስጠንቀቂያ ጋርወደ አዲስ አበባ ትልካለች ።

July 6, 2014
አንድአርጋቸው ቴዲ አፍሮ ወይንም ብርቱካን ሚደቅሳ አይደለም !!!

573C78C ወያኔዎች አንዳርጋቸውን አስረው የፖለቲክ ትርፍ የሚያገኙ መስሏቸዋል። አንዳርጋቸው ሳይታሰር ከሚፈጥረው ተጽእኖ ይልቅ ታስሮ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም ፡ በውጪ ከሚታገለው ኤጥፍ በላይ በወህኒ በሚከፍለው መስዋትነት በወያኔ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ይፈጥራል። አንዳርጋቸውን በማሰራቸው የሚጸጸቱበት ቀን ሩቅ አይደለም ። ወያኔ ዝም ያለው የህዝብ ቁጣ በመፍርት ስኢሆን በሚስጥር የተብተኑ ደህንነቶች የሕዝቡን ትኩሳት እየለኩ መሆኑን ታውቅውል፤ ሃይለማርያም ደሳለንም ሆነ ሌሎች የወያኔ ባለስልጣናት የ አንዳርጋቸውን መታፈን የሰሙት ከግንቦት ስባት መግለጫ መሆኑ ተረጋግጧል። የወያኔ ድህረ ገጾች ላለፍት2 ሳምንታት ዝምታን መርጠዋል፡ ይህ የሚያመለክተው ወይኒ በራስ መተምመኑን ምን ያህል እንዳጣ ነው፡ ይህ ማለት ፕሮፌሰር አስራትን የያዙበት ግዜ አይነት አይደለም ዘመኑ አሁን የበሰለ ነው ሲሉ መረጃውን ያመጡት ተናግረዋል።
ነገ የሚሰበሰበው የካምብሪጅ የጠበቆች ቡድን ለ እንግሊዝ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ከባድ እና ህጋዊ ማስጠንቀቂያ በመስጠቱ ይህንን እንደሚያደርግ የሚጠብቀው ቢሮው የጠበቆቹን ቡድን አስከትሎ ክፍተኛ ሚኒስትርን ወደ አዲስ አበባ ይልካል ፤ በ እንግሊዝ የሚገኘው ታዋቂ የካምብሪጅ የጠበቆች ቡድን ከባድ ማስጠንቀቂያ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰጥቷል።
በመላው አለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እስከድል ጫፎች ድረስ ጫናችንን መቅጠል አለብን ።

torsdag 3. juli 2014

በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ… ኤርትራ እና የመን ተፋጠዋል


መልእክተ ዜና – በዳዊት ከበደ ወየሳ
ኤርትራ የየመንን አየር መንገድ እንደምትዘጋ አሳወቀች (ምክንያቱ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታሰር ነው)
Andargachew-Tsige
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ
(ኢ.ኤም.ኤፍ) አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰና፣ የመን ውስጥ በየመን የጸጥታ ሃይሎች ታፍኖ መታሰሩ ብሎም አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አለመታወቁ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመን ላይ ትራንዚት እያደረገ በነበረበት ወቅት ነበር በየመን ታጣቂዎች ታፍኖ የተወሰደው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በየቦታው ድምጻቸውን ለማሰማት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ከ’ነዚያ ሁሉ ድምጾች ግን ጎልቶ የወጣው በኤርትራ በኩል የተላለፈው መግለጫ ነው። ይህን የኤርትራን መግለጫ መሰረት በማድረግ፤ ሌሎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የራሳችንን ሃሳብ እንሰጣለን።
ኤርትራ ለየመን በላከችው መልዕክት መሰረት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ካልተፈታ፤ በኤርትራ አየር ላይ የሚሄዱትንም ሆነ፤ ምድር ላይ የሚያርፉት የየመን አውሮፕላኖች የሚታገዱ መሆኑን ገልጿል። ይህ ደግሞ እያደገ ለመጣው የየመን አየር መንገድ ትልቅ ኪሳራን የሚያስከትል ነው። ኤርትራ የጀርመኑን ሉፍታንዛ ካገደች ወዲህ፤ የየመን አየር መንገድ ሉፍታንዛን ተክቶ፤ አስመራ ውስጥ በመስራት ላይ ይገኛል። በዚህም መሰረት ወደ አውሮፓ የሚሄዱም ሆኑ የሚመጡ አውሮፕላኖች በየመን በኩል አድርገው ማለፍ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። አሁን ኤርትራ የየመን አየር መንገድን እንደሉፍታንዛ የምታገድ ከሆነ፤ የየመን መንግስት የሚያገኘው ከፍተኛ ገቢ ሊቀንስበት ይችላል።
ከዚህ በፊት ባቀረብነው ዘገባ ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእንግሊዝ አገር ዜግነት ያለው እና የእንግሊዝን ፓስፖርት ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ስለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስናወራ፤ የ እንግሊዝንም መንግስት የጉዳዩ ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል። እንግሊዝ ዜጋዋ በየመን ታስሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይላክ በአውሮፓ ዲፕሎማሲያዊ ስራ መስራት ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ እና የመን እስረኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ቢኖራቸውም፤ የመን የ እንግሊዝ ዜግነት ያለውን ሰው አሳልፋ እንዳትሰጥ በዛቻ ሳይሆን፤ በህጋዊ መንገድ የመንን መሞገት ያስፈልጋል።
ከ እንግሊዝ በተጨማሪ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችም በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ ማድረግ ሌላው ብልሃት ነው። አሜሪካ ከየመን ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት በመጠቀም አቶ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈታ በየመን የአሜሪካ ኢምባሲ ጥረት እንዲያደርግ ጫና መፍጠር ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ግንቦት ሰባት የሚያወጣቸው የማስፈራሪያ መግለጫዎች ድምጸታቸውን በማስተካከል እንደአንድ በሳል የፖለቲካ ድርጅት የሚታይ ዲፕሎማሲያዊ ስራ በመስራት ለውጤት መብቃት አለባቸው። በመሆኑም ከማስፈራሪያ መግለጫዎች ይልቅ፤ ከዲፕሎማሲያዊው ዘመቻ ጎን ለጎን… ህጋዊ ጠበቃ በየመን አዘጋጅቶ፤ ጉዳዩ በኢሚግሬሽን እና በዋናው ፍርድ ቤት እንዲታይ በማድረግ፤ ቢያንስ አቶ አንዳርጋቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይላክ ጊዜ መግዛት ይቻላል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእንግሊዝ ዜግነት ያለው እንደመሆኑ መጠን ዲፕሎማሲያዊው ዘመቻ በእንግሊዛውያን ጭምር እንዲሰራ፤ ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ሚዲያዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ተገቢ ነው። የምናወጣቸውም መግለጫዎች በአማርኛ ሳይሆን ሁሉም አገራት በሚረዱት እንግሊዘኛ ቋንቋ ሊሆን ይገባዋል። ከዚያ ውጪ ግን “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ባስቸኳይ ካልተፈታ በኢትዮጵያ እና በየመን ባለስልጣናት ላይ እርምጃ እንወስዳለን” አይነት መግለጫዎች፤ ወያኔ ኢህአዴግ “ግንቦት ሰባት የአሸባሪዎች ድርጅት ነው” የሚለውን አባባል ከማጠናከር ውጪ ብዙም ፋይዳ ላይሰጥ ይችላል።
ይህ ብቻም አይደለም። በማህበራዊ ድረ ገጾች እና ሌሎች ሚዲያዎች ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከዚህ በፊት ያደረጓቸው ንግግሮች እየተለጠፉ መሆኑን ታዝበናል። እንዲህ አይነቶቹ… ቀደም ሲል የተደረጉ ንግግሮችን አሁን ለእይታ ማቅረቡ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እስሩ እንዲጸናባቸው እንጂ፤ እንዲፈቱ ስለማይረዳቸው፤ በዚህ ረገድ ሌላ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በድጋሚ ለማሳሰብ ያህል… ግንቦት ሰባትም የማስፈራሪያ መግለጫዎችን ከማውጣት ይልቅ፤ በሌሎች ዜጎች እየተደረጉ ያለውን ጥረት ማስተባበር እና ዲፕሎማሲያዊ ይዘት እንዲኖራቸው ማድረግ አለበት። ኤርትራ ያደረገችውን ውሳኔ በማድነቅ፤ ሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ማበረታታት ከግንቦት ሰባት አመራሮች የሚጠበቅ ነው።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው መሆኑን፣ ንብረታቸው በወያኔ ኢህአዴግ መወረሱን፣ ወላጅ አባታቸው እና ቤተሰባቸው በእስር መንገላታቱን አጉልቶ በማውጣት የወያኔ ኢህአዴግን አስከፊ ገጽታ ማሳየት ይቻላል። አሁንም የየመን መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ወደ ኢትዮጵያ ብትመልስ በወያኔ ኢህአዴግ ሊደርስባቸው የሚችለውን የግድያ ወንጀል ማሳወቅ እንጂ፤ “አቶ አንዳርጋቸው ካልተፈታ ወዮላቹህ!” የሚለው አይነት ማስፈራሪያ ህሊና ለሌላቸው የሁለቱም አገራት አምባገነን መሪዎች ላይሰራ ይችላል። ህዝብ እና አገር የሚመሩት በእውቀት እና በጥበብ ጭምር በመሆኑ፤ ህጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመከተል… ነገር ግን በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ አቶ አንዳርጋቸውን የማስፈታቱን ሂደት እንቀጥል – የዛሬው ዜና መልእክታችን ነው።

tirsdag 1. juli 2014

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን ባለሥልጣናት እገታ ላይ መሆኑን በማስመልከት የወጣ መግለጫ


አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን ባለሥልጣናት እገታ ላይ መሆኑን በማስመልከት የወጣ መግለጫ
ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም
የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓም ለሥራ ጉዳይ በየመኒያ አየር መንገድ አይሮፕላን ተጉዞ በትራንዚት ሰንዓ ከተማ እያለ በየመን መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ ታግቷል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመን የጉዞው መዳረሻ አልነበረም፤ ከየመን ጋርም የሚያገናኘው ምንም ጉዳይ አልነበረውም። የየመን መንግሥት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አግቶ ለአንድ ሰዓት እንኳን ለማቆየት ምንም ምክንያት የለውም። በዚህም ምክንያት ያለአግባብ የታገተብን የንቅናቄያችንን አመራር በአስቸኳይ እንዲፈታ በተለያዩ መንገዶች ላለፈው አንድ ሣምንት ያደረግነው ጥረት እስካሁን አልተሳካም። እንዲያውም የየመን ባለስልጣናት አምባገኑን ወያኔ ለመርዳት ባለው ፍላጎት ሳቢያ መሪያችንን አሳልፎ ሊሰጠው ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ጊዜውን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ፤ ዝግጁነቱንም በተግባር ያሳየ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው። የየመን መንግሥት ከዘረኛውና ፋሽስታዊው ወያኔ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ታጋይ መሪያችን ላይ እየፀመ ያለውን ደባ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅ የንቅናቄዓችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወስኗል።
ትግላችን መስዋትነት እንደሚያስከፍል እናውቃለን። ከዚህ በፊትም ብዙ ጓዶቻችን መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ወደፊትም ብዙ መስዋዕትነት መከፈሉ የማይቀር ጉዳይ ነው። አሁን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የደረሰውና ወደፊትም ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ምሬታችን በማብዛት፣ ቁጣችንና ዝግጁነታችን ከማጠንከር በስተቀር ቅንጣት ታክል እንኳን ወደ ኋላ እንድናፈገፍግ እንደማያደርገን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለአባሎቻችንና ለደጋፊዎቻችን ሁሉ መግለጽ እንወዳለን።
መንግሥታት ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። ኢትዮጵያና የመን ግን ጎረቤታሞች ሆነው መቆየታቸው የማይቀር ነው። የየመን መንግሥት የወያኔ እድሜ አጭር መሆኑ የተገነዘበ አይመስልም። በዚህም ምክንያት የየመን መንግሥት የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች የቆየ ወዳጅነት የሚያደፈርስ እርምጃ ወስዷል። የየመን መንግሥት የየመንን የወደፊት የረዥም ጊዜ ጥቅም እንዲያሰላና ያገተብንን መሪ በአስቸኳይ እንዲፈታ እንመክራለን። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በመሪያችን ላይ ጉዳት ቢደርስ ወይም ለወያኔ አሳልፎ ቢሰጥ የመን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የማይሽር ቂም ውስጥ የምትገባ መሆኑን የየመን መንግሥት አውቆ በጥብቅ እንዲያስብበት እናስጠነቅቃለን።
በየመን መንግሥት አልሰማ ባይነት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለፋሽስቱ የወያኔ አገዛዝ ተላልፎ ቢሰጥ በአካሉና በሕይወቱ ለሚደርሰው ሁሉ የወያኔ ፋሽስቶችን ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ከአሁኑ እናስጠነቅቃለን። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስና ሕይወት ላይ የሚደርሰው ማንኛውም ጥቃት ለነፃነታቸው ለመሰዋት ዝግጁ የሚሆኑ እልፍ አዕላፍ ታጋዮችን እንደሚፈጥር ጥርጥር የለንም። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስ እና ሕይወት ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ሁሉ በማንኛውም መንገድ በማንኛውም ቦታ የምንበቀል መሆኑንና ብዙ የወያኔ ሹማምንት ዋጋ የሚከፍሉበት እንደሚሆን እንዲያውቁት እናስጠነቅቃለን ።
በመስዋዕትነት ድልን እንቀዳጃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!