torsdag 30. oktober 2014

የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያው የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልና በማጽናት ተጠናቀቀ፤ የፓትርያርኩ ምሬትና ብስጭት ያሳሰባቸው ብፁዓን አባቶች ሲያረጋጓቸው አመሹ

  • ‹ከሕዝብ አጋጫችኹኝ፤ ከወንድሞቼ አንድነት ለያችኹኝ፤ ከነገራችኹኝ አንዱንም የተቀበለኝ የለም›› በሚል የተመረሩት አቡነ ማትያስ ምክራቸው ያልሠመረላቸውን ሦስት አማሳኝ አማካሪዎችን በከፍተኛ ድምፅ ‹‹ውጡልኝ›› በማለት ከፊታቸው አበረሯቸው፡፡
  • ከትላንትናው የስብሰባ ውሎ መጠናቀቅ በኋላ ፓትርያርኩ የነበሩበት የምሬትና የብስጭት ኹኔታ ተነግሯቸው ወደማረፊያቸው የተጠሩት በሹመት ቅድምና ያላቸው ብፁዓን አባቶች÷ አቡነ ማትያስ በተጠሪነት ጉዳይ የተሟገቱለት አቋም የቤተ ክርስቲያን እንዳልኾነ፣ ለአጭር ዕድሜ የኖረው የቤተ ክርስቲያን ሕግ መለወጥ እንደሌለበት ይልቁንም የአማሳኞችንና የባዕዳንን ምክር ከመስማትና ከመቀበል ተጠብቀው ትላንት ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋራ ኹነው የተከላከሉለትን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ማስከበራቸውንቢቀጥሉ በእርሳቸውና በአባቶች መካከል ያለው ውጥረት ሊረግብና ሊተራረቅ እንደሚችል አመልክተዋቸዋል፡፡
  • ፓትርያርኩ በትላትናው ምሽት አማሳኞቹን በብስጭትና በምሬትም ቢኾን ከአበረሯቸውና በብፁዓን አባቶች ምክር ከተጽናኑ በኋላ በዛሬው የምልአተ ጉባኤው ውሎ ስብሰባውን በተረጋጋና በመግባባት መንፈስ ሲመሩና ‹‹እናንተ ካላችኁት አልወጣም›› እያሉ በጋራ ሲወስኑ ውለዋል፡፡
  • የቅዱስ ሲኖዶሱን የበላይነት(ልዕልና) በማረጋገጥ በተጠናቀቀው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ አጀንዳ፣ ከፓትርያርኩ ጀምሮ እያንዳንዱ ሊቀ ጳጳስና ኤጲስ ቆጶስ(ጳጳስ) ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶሱ እንደኾነ ጸንቷል፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ኾኖ ሲሠራበት የቆየው ልምድ በማሻሻያው ተካትቶ እንዲደነገግ ተወስኗል፡፡ በልዩነት ነጥቦቹ ላይ በተላለፉት ውሳኔዎች መሠረት ረቂቁ ተስተካክሎ ሲቀርብ በምልአተ ጉባኤው አባላት ፊርማ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡
  • በደቡብ አፍሪቃ በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብና በምእመናን መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት መፍትሔ ለመስጠት በቀረበው የአጣሪ ልኡክ ሪፖርት ላይ የመከረው ምልአተ ጉባኤው÷ ብፁዕነታቸው ለጊዜው መንበረ ጵጵስናቸውን በናይሮቢ አድርገው በኬንያ፣ በጅቡቲና በሱዳን ተወስነው እንዲሠሩ፤ በደቡብ አፍሪቃ ደግሞ አገልግሎቱ በአድባራት አለቆችና በሰባክያነ ወንጌል ላይ ተመሥርቶ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡ ምልአተ ጉባኤው በሰሜን አሜሪካ በሚገኙት ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ጉዳይ መምከር ጀምሯል፡፡
  • ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ራሱን የቻለ ሊቀ ጳጳስ ስለመመደብና በሀገረ ስብከቱ የተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ በነገው ዕለት በመምከር ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ላለፉት 3 ወራት ያሰለጠናቸውን የአምስተኛ ዙር ታጋዮች አስመረቀ ።


GPF 5th round

የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ለ 90 ቀናት በተከታታይ በወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና የመረጃ እና ደህንነት ትምህርቶች ያሰለጠናቸውን ታጋዮች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት በደመቀ  ሁኔታ  አስመርቀ። 
ህዝባዊ ሃይሉ ከዚህ በፊት 4 ተከታታይ ዙሮችን ያስመረቀ ሲሆን የዛሬው ለአምስተኛ ጊዜ ነው። በምረቃ  ስነስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የህዝባዊ ሃይሉ ዋና አዛዥ ኮማንደር አሰፋ ማሩ ‘’ህዝባዊ  ሃይላችን በኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውን ዘረኛና አፋኝ የወያኔ ስርዓት ከህዝብ እና ከሃገራችን ጫንቃ ላይ አስወግዶ በምትኩ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ከተመሰረተ ጀምሮ ባለፉት ጊዚያት በርካታ ስራወችን  በመስራት አስተማማኝ ድርጅታዊ አቋም ላይ ይገኛል’’ ብለዋል። 
ኮማንደሩ አያያዘውም ‘’ይህን የአምስተኛ ዙር ምርቃት ከቀደምቶቹ የሚለየው የኢትዮጲያ ህዝብ አርበኞች ግንባር፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ እና  የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ተዋህደው ባንድ ድርጅት ጥላ ስር ትግላቸውን አስተባብረው ለመታገል የሚያደርጉትን የውህደት ሂደት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ያደረሱበት ወቅት ላይ መደረጉነው’ ብለዋል። በተጨማሪም ‘’ይህ የህዝባዊ ሃይላችን ስልጠና በግንቦት ሰባት ስም ከሚደረጉት ስልጠናወች የመጨረሻው ይሆናል ብለዋል።
በመጨረሻም ለተመራቂወች ባስተላለፉት መልዕክት ‘’ስልጠና ለአንድ ታጋይ የትግሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን በስልጠና ላይ ያገኛችሁትን ትምህርት በተግባር ለቆምንለት ዓላማ  እና ተልዕኮ በቁርጠኝነት እንደምታውሉት ሙሉ እምነቴን እገልጻለሁ‘’ ካሉ በኋላ  ለስልጠናው መሳካት የተለያዩ  ድጋፎችን ላደረጉ አካላት ምስጋና  አቅርበዋል።

mandag 27. oktober 2014

ፓትርያርኩ: የቤተ ክርስቲያን ራስ ቅዱስ ሲኖዶስ ባልመከረበትና ‹‹ለቤተ ክርስቲያን የማይመጥን ነው›› በተባለው የመክፈቻ ንግግራቸው ተገሠጹ፤ ውሳኔም ተላለፈባቸው!

  • ቅ/ሲኖዶሱኻያ ኹለት የስብሰባ አጀንዳዎችን በማጽደቅ መወያየት ጀምሯል
  • በሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያው ሥልጣናቸውን የማጠናከር ውጥን አላቸው
  • የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ አጀንዳ እንዳይኾን መቃወማቸው ውድቅ ተደርጓል
  • ሊቃነ ጳጳሳቱን ባዘለፉባቸው ሕገ ወጥ ስብሰባዎች ይቅርታ ጠይቀዋል
  • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በራሱ የሚመራው ሊቀ ጳጳስ ይመደብለታል
  • በደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ጸጥታ ጉዳይና የተሐድሶ መናፍቃን የሚፈጥሯቸው ችግሮች በአጀንዳነት ተይዘዋል
  • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤትና ከማንኛውም መዋቅር ኹሉ የበላይ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባ ያሰሙትን የመክፈቻ ንግግር ‹‹ለቤተ ክርስቲያን የማይመጥን ነው›› በሚል በጥብቅ ተቃወመው፡፡ ተቃውሞው የተገለጸው፣ ምልአተ ጉባኤው የስብሰባው ቁጥር አንድ አጀንዳ ባደረገውየፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር ላይ በተወያየበት ወቅት ነው፡፡
    በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቁጥር ፻፷፬ ድንጋጌ መሠረት ከጥቅምት ፲፪ ቀን ጀምሮ የሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲከፈት፣ ፓትርያርኩ በብዙኃን መገናኛ ፊት በንባብ ያሰሙት ንግግር፣ ከወቅታዊነቱና አግባብነቱ አኳያ ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቀድሞ ሊመክርበት ይገባ ነበር በሚል የምልአተ ጉባኤው ተሳታፊዎች በአንድ ድምፅ አቋም እንደያዙበት ተመልክቷል፡፡
    የምልአተ ጉባኤውን ስብሰባ በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ፓትርያርኩ በመክፈቻ ንግግራቸው÷ በምእመናን ፍልሰት፤ በቤተ ክርስቲያን ስም ሀብትና ንብረት ይሰበስባሉ ባሏቸው ማኅበራት፤ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በማያሰፍን እንዲኹም በቴክኖሎጂ ባልተቃኘ የሰው ኃይል፣ የገንዘብና የንብረት አስተዳደር ችግር ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ግልጽና አደገኛ ፈተናዎች እንደተጋረጡባት ገልጸዋል፡፡
    ፓትርያርኩ ከጠቀሷቸው ዐበይት ችግሮች መካከል ለማኅበራት ጉዳይ የተለየ ትኩረት የሰጠ በሚመስል ንግግራቸው÷ ማኅበራቱ፣ የሚሰጣቸውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኝነቱና ቅንነቱ የሌላቸው ኾነው እንደተገኙና በአስተዳደር ሥራ በቀጥታ ጣልቃ እንደሚገቡ በመጥቀስ ‹‹የሰላም ጠንቆች›› ብለዋቸዋል፤ ቤተ ክርስቲያን በአክራሪነት የምትፈረጀው ማኅበራቱ በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን የማይታወቅ ሀብት ስለሚሰበስቡ እንደኾነም አመልክተዋል፡፡
    በክርስትናችን ትውፊት የማኅበራት ሚና ‹‹ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ጸበል እየቀመሱ መኖር›› ብቻ እንደኾነ የተናገሩት አባ ማትያስ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማኅበራትንና የምእመናን ፍልሰትን የተመለከተ ሕጋዊና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ ‹‹ቤተ ክርስቲያንን የመታደግ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡
    የምእመናን ፍልሰትን ይኹን የሀብትና ንብረት አስተዳደርን የንግግራቸው ማጀቢያ ያደረጉት ያኽል እንደ ማኅበራቱ ጉዳይ ብዙም ያላተቱት ፓትርያርኩ፣ በነጠላ ቁጥር ወደሚጠቅሱትና ስሙን በግልጽ ወዳልጠሩት ‹አንድ ማኅበር› በመሸጋገር፣ ‹‹በሕግ ማስተካከል አለብን››ለሚለው አቋማቸው አጽንዖት ለማስገኘት ሲጥሩ ተስተውለዋል፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም ‹‹ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን ሕግ እንዲመራና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኾኖ እንዲያገልግልእ የተደረገ ነው፤›› ያሉትን ጥረታቸውን እንዲያግዛቸው ጥሪአቸውን አስተላልፈዋል፡፡
    የምእመናን ፍልሰት፣ የሰው ኃይልና የንብረት አስተዳደር ይኹን የብዙኃን መንፈሳውያን ማኅበራት ጉዳይ አሳሳቢነቱ የቱንም ያኽል ቢኾን፣ በፓትርያርኩ ንግግር ውስጥ የተጠቀሱበት መንገድ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተመከረበትና የምልአተ ጉባኤው አቋም ያረፈበት ሊኾን እንደሚገባው የገለጹ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ‹‹ቋንቋው የቤተ ክርስቲያን አይደለም፤ አይመጥናትምም›› በሚል በጽኑ እንደተቹት ተሰምቷል፡፡
    የአባ ማትያስ የመክፈቻ ንግግር ከይዘቱም አኳያ ሲፈተሽ፣ ‹‹ግልጽና አደገኛ ፈተናዎች›› በተባሉት ችግሮች ላይ ቤተ ክርስቲያን የያዘችውን አቋምና የወሰደችውን ርምጃ የማያመላክትና ወቅታዊነት የጎደለው ነው በሚል ተነቅፏል፡፡ ይኸውም በንግግራቸው ለተጠቀሱት ችግሮች መፈታት ምልአተ ጉባኤው ቀደም ሲል ጥናታዊ ውሳኔ ያሳለፈባቸው፣ የይኹንታ አቅጣጫና መመሪያ የሰጠባቸው በመኾኑና መፍትሔውም እነርሱኑ መዋቅሩን ጠብቆ ለማስፈጸም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ጉዳይ ተደርጎ በመወሰዱ ነው ተብሏል፡፡
    ለብዙኃን መገናኛ መገለጽ ያለባቸው የፓትርያርኩ ንግግሮች፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ በበቂ ከመከረ በኋላ በመጨረሻ በሚደርስባቸው ስምምነቶች ላይ ተመሥርቶ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ብቻ እንዲኾኑም በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ሙሉ የጋራ አቋም እንደተያዘበት ታውቋል፡፡ በመኾኑም ከአኹኑ የቅ/ሲኖዶስ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ በኋላ ርእሰ መንበሩ ፓትርያርክ አባ ማትያስ የሚያደርጉት የመክፈቻ ንግግር፣ በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስቀድሞ የተመከረበትና በምልአተ ጉባኤው አባላት የ‹‹እንኳን ደኅና መጣችኁ›› አቀባበል ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲኾን መወሰኑን የስብሰባው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
    በፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ጠንካራ የቃላት ልውውጥ እንደነበረና ፓትርያርኩ ‹‹ወትሮም ጠላቴ›› በሚል ሊያሸማቅቋቸው የሞከሩ ብፁዓን አባቶች እንዳሉም ተሰምቷል፡፡ ይኹንና የሢመት ቅድምና ያላቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ ኹሉም የምልአተ ጉባኤው አባላት ፓትርያርኩ በአመራራቸው፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና የቅዱስ ሲኖዱሱን ውሳኔ በመፃረር የቤተ ክርስቲያንን ክብር እያስደፈሩና ልዕልናዋን እያዋረዱ እንዳለ በመጥቀስ በተባበረ ድምፅ በመገሠጻቸው ይቅርታ ለመጠየቅ እንደተገደዱ ተዘግቧል፡፡
    ፓትርያርኩ ተግሣጹን ተቀብለው ምልአተ ጉባኤውን ይቅርታ ከጠየቁባቸው መተላለፎቻቸው ውስጥ፣ በመስከረም ወር መጨረሻ ከመዋቅር ውጭ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል በጠሯቸውና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ተደምረው በአማሳኞች የተዘለፉባቸው ስብሰባዎችና ቅዱስ ሲኖዶሱ ያልመከረበት የመክፈቻ ንግግራቸው እንደሚገኝበት ተጠቅሷል፡፡ ፓትርያርኩ ያሻቸውን እየፈጸሙ ይቅርታ መጠየቅን እንደ ስልት መያዛቸውን የሚጠቅሱ ወገኖች በበኩላቸው፣ ከይቅርታው ጋራ የፓትርያርኩ አመራርና አካሔድ ለአማሳኞች የጥፋት ምክርና ለውጭ ተጽዕኖ ከተጋለጠበት ኹኔታ ተጠብቆ የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልናና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለማስከበር የሚያስችል የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድበትና ቋሚ አሠራር (የጠንካራ እንደራሴ ጉዳይ እንደ አብነት ተጠቅሷል) እንዲበጅለት ይጠይቃሉ፡፡
    የቤተ ክርስቲያን ‹‹ግልጽና አደገኛ ፈተናዎች›› በሚል በፓትርያርኩ የመክፈቻ ንግግር ለተጠቀሱት የምእመናን ፍልሰትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሔው÷ ለመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ለውጥ የቀረቡትንና የብዙኃኑን ካህናትና ምእመናን ተቀባይነት ያረጋገጡ ጥናቶች በትግበራ ስልት ወደ ፍጻሜ ምዕራፍ በማሸጋገርና የቅዱስ ሲኖዶሱን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች በማስከበር ልዕልናውን ለማረጋገጥ የሚበቃ የመሪነት ብቃትና ቁርጠኝነት ገንዘብ አድርጎ መገኘት እንደኾነ ተገልጧል፡፡
    ስለ ማኅበራት ጉዳይ በተመለከተም ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. መመሪያው፣ የተከሠቱትና ወደፊትም ሊከሠቱ የሚችሉት ችግሮች በቀላሉ የሚታዩ እንዳልኾነ ገልጾ መንሥኤው በሕግና በሥርዐት የሚመሩበት ደንብ ስላልተሰጣቸው መኾኑንገልጧል፡፡ መፍትሔውም ማኅበራቱን ፓትርያርክ አባ ማትያስ እንዳሉት ‹‹በጸበል ቀማሽነት›› መወሰን ሳይኾን ለቤተ ክርስቲያን እየሰጡ ያሉትን ታላቅ አገልግሎትና ብዛታቸውን መቆጣጠርን የተገነዘበ፣ ‹‹ራሱን የቻለና የሚያሠራ ሕግ›› ማዘጋጀት እንደኾነም አስቀምጧል፡፡ ለዚኽም ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎች ያሉበት ደንብ አዘጋጅ ኮሚቴ ሠይሞ ነበር፡፡
    ፓትርያርኩ ‹‹ኹላችኁ የምታውቁት አንድ ማኅበር፤ ማኅበሩ›› በሚል ስሙን በግልጽ ስለማይጠቅሱት ማኅበረ ቅዱሳንም ቢኾን ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚያው መመሪያው፣ ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ ደንብ ተሰጥቶት ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ የቆየና አኹንም እየሰጠ ያለ መኾኑን አረጋግጧል፡፡ የተሰጠው መተዳደርያ ደንብና የአሠራር መዋቅሩ÷ የማኅበሩን ዕድገት የሚመጥን፣ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊና የላቀ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማበርከት የሚያስችለው ተደርጎ መሻሻል እንደሚያስፈልገው በመወሰንም የ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. መተዳደርያ ደንቡን መርምሮ የሚያሻሽል ከብፁዓን አባቶች፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከሕግ ዐዋቂዎች የተውጣጣ ኮሚቴ ሠይሟል፡፡ ደንቡ ተሻሽሎ እስከሚጸድቅም ማኅበሩ ተጠሪነቱ ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ኾኖ አመራር በመቀበል እየሠራ እንዲቆይም መመሪያ ሰጥቷል፡፡
    አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሦስት የሕግ ባለሞያዎችንና ሦስት የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮችን በአጠቃላይ ዐሥራ አንድ አባላትን የያዘው የመተዳደርያ ደንብ አጥኚ ኮሚቴም በሐምሌ ወር ፳፻፬ ዓ.ም. የጀመረውንና በተለያዩ ምክንያቶች ሲስተጓጎል የቆየውን የማሻሻያ ጥናት በ37 አንቀጾችና በ34 ገጾች አካትቶ በሚያዝያ ወር ፳፻፮ ዓ.ም. ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አቅርቧል፡፡
    ይኹንና ከማኅበሩ የታወጀ ኦርቶዶክሳዊ ዓላማ ጋራ ርእዮታዊና ሃይማኖታዊ ተፃባኢነት (ተፃራሪነት) ያላቸው የውስጥ አማሳኞችና የውጭ ኃይሎች ለፓትርያርኩ ያቀበሏቸው የሚመስለውና ፓትርያርኩ አንዳችም ሳይጨመርና ሳይቀነስ በማሻሻያው ይካተት በሚል ሕጋዊነትም ምክንያታዊነትም የጎደለው የተልእኮ አስፈጻሚነት መመሪያ ሳቢያ የማሻሻያ ረቂቁ ዘግይቶም ቢኾን ጸጽቆ በሥራ ላይ መዋል ከሚገባው ካለፈው ዓመት ግንቦት የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ አድሮ በእጅጉ ተጓትቶ ይገኛል፡፡
    ከማኅበሩ የአገልግሎት ፈቃድ ዕድሳት፣ ከአመራሮችና አስፈጻሚዎች ምርጫ፣ ከአባላት አያያዝ፣ ከሪፖርት አቀራረብ፣ ከገንዘብና ንብረት ቁጥጥር ጋራ የተገናኙ 24 ነጥቦችን የያዘው መመሪያው፣ የማኅበሩን የአገልግሎት ነፃነትና የአገልግሎት አቅሞች በሒደት የሚያዳክምና በመጨረሻም የሚያጠፋ እንደኾነ በመተዳደርያ ደንብ አጥኚ ኮሚቴው አብላጫ አባላት ስለታመነበት በማሻሻያው እንዳለ ይካተት ብሎ ለመቀበል አዳጋች እንደኾነ በወቅቱ ለፓትርያርኩ ተገልጦላቸዋል፡፡ ኮሚቴው በነጥቦቹ ላይ በወቅቱ ለፓትርያርኩ በሰጠው በሕግ ሞያ የተደገፈ ማብራሪያ፣ በመመሪያው ከተጠቀሱት ነጥቦች የተወሰኑት ቀድሞም በማሻሻያ ረቂቁ ያሉ መኾናቸውን የተቀሩት ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ደንቡ ዝግጅት ከሰጠው ውሳኔ ጋራ የሚቃረን መኾኑን በግልጽ አስረድተዋቸዋል፡፡
  • ባለፈው ዓመት ግንቦት፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ የማሻሻያ ረቂቁን በአጀንዳነት ይዞ በተወያየበት ወቅት ይህንኑ የአጥኚ ኮሚቴውን ሐሳብ የተቀበሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ የፓትርያርኩን የእልከኝነትና ግትርነት አካሔድ ተቃውመዋል፤ ‹‹24ቱን ነጥቦች ሳይጨምር ሳይቀነስ ካላስገባችኁ ውይይቱ አይቀጥልም፤ ስብሰባውንም አልመራም›› ያሉት ፓትርያርኩም ለብዙኃኑ ውሳኔ ባለመገዛታቸው የስብሰባው ሒደት እግዳት ውስጥ ገብቶ በዚያው ተቋጭቷል፡፡ ምልአተ ጉባኤው በመነጋገርያ አጀንዳዎች ላይ በተወያየበት በትላንቱ የቀትር በፊት ውሎውም ፓትርያርኩ ካለፈው ዓመት ግንቦት ለዘንድሮው ጥቅምት ያደረው የማኅበሩ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ በአጀንዳነት እንዳይያዝ በብዙ ታግለው እንደነበር ተገልጧል፡፡
    ይኹንና ፓትርያርኩ በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ቋሚ ሲኖዶሱ ለምልአተ ጉባኤው ካቀረበው የመነሻ አጀንዳ ዝርዝር ውስጥ ረቂቁ እንዳይያዝ በማድረግ ቢሳካላቸውም ምልአተ ጉባኤው የሠየመው ሰባት አባላት ያሉበትና በጉዳዩ ላይ ጽኑ አቋም የያዘው አጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ እንዳያካትተው ለመከላከል ግን ሳይቻላቸው ቀርቷል፡፡ በመኾኑም የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ከምልአተ ጉባኤው 22 ያኽል የመነጋገርያ አጀንዳዎች ውስጥ በተራ ቁጥር 14 ሊካተት ችሏል፡፡ ይህም ፓትርያርኩ በ፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ በቅስቀሳ መልክ ያነሷቸው ጥያቄዎች በአማሳኞች ጩኸትና በውጭ ኃይሎች ግፊት ሳይኾን በቅዱስ ሲኖዶሱ ታይቶ እንዲወሰን የያዘውን አቋም ትክክለኛነትና አሸናፊነት ያሳየ ኾኗል፡፡
    በመክፈቻ ንግግራቸው ማኅበሩን በሕግ ለማስተካከል የዛቱት አባ ማትያስ፣ በእጅጉ የተጓተተው የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ በአጀንዳ ተይዞ እንዳይጸድቅ መከላከላቸው፣ ፍላጎታቸው ላይ ላዩን እንደሚወተውቱት ማኅበሩን በሕግና በሥርዐት መምራት አለመኾኑንእንደሚያሳይእየተገለጸ ይገኛል፡፡ ለዚኽም ለአኹኑ ምልአተ ጉባኤ የመጨረሻ መልኩን ይዞ እንዲቀርብ በተወሰነው የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ከተሰጠው የእርምትና ማስተካከያ አቅጣጫ ውጭ ሥልጣናቸውን የሚያጠናክሩባቸው አግባቦች እንዲካተቱ መደረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
    ቅዱስ ሲኖዶሱ ተጨማሪ እርማትና ማስተካከያ እንዲያደርጉ ከሠየማቸው ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎችመካከል ልዩ ጸሐፊያቸውን ያስገቡት ፓትርያርኩ÷ በተለይም በሊቃነ ጳጳሳት ምደባና ዝውውር እንዲኹም በማኅበራት ጉዳይ ላይ የወሳኝነት ሥልጣን እንዲኖራቸው እንዲኹም ከቅዱስ ሲኖዶሱ ውጭና በላይ ራሳቸውን ተጠሪ አድርገውባቸዋል የተባሉ ሌሎች የማሻሻያ አግባቦች ምልአተ ጉባኤውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል፤ ምናልባትም የማሻሻያ ረቂቁን ከመጽደቅ ሳያዘገየው እንደማይቀርም ተሰግቷል፡፡
    የመንበረ ፓትርያርኩ መቀመጫ የኾነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የኾነበት ልማድ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ በተሾመ ሊቀ ጳጳስ ወይም ጳጳስ ወይም ኤጲስ ቆጶስ እንዲመራ ከሰፈረው ድንጋጌ አኳያ ተፈትሾ ራሱን የቻለ ሊቀ ጳጳስ ሊመድብለት እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ይህም በአኹኑ ወቅት ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ልዩ ጽ/ቤት በተዘረጋው የአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለት ካህናትና ምእመናን በተለይም የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ለውጡን የደገፉ ወገኖች፣ ‹‹ከዛሬ ነገ እንባረራለን›› በሚል ስጋት አቤት የሚሉበት አጥተው በብቀላ ዝውውር የሚንገላቱበትን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት እንደሚገታው ተገልጧል፡፡
  • ከምልአተ ጉባኤው ሌሎች አጀንዳዎች መካከል÷ ምእመናን በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን በእጅጉ ስለተፈተኑባቸው፤ የቤተ ክርስቲያን መሥሪያና የመቃብር ቦታ እስከመከልከልና እስከማጣት ስለደረሱባቸው፣ አብያተ ክርስቲያን ስለተቃጠሉባቸው በክልላዊ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ካህናትና ምእመናን ለኅልፈት ስለበቁባቸው የሐዲያና ስልጤ፣ የምዕራብ ወለጋና ቄለም ወለጋ እንዲኹም የጋምቤላ አህጉረ ስብከትይመክራል፡፡ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት አስተዳደር በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱና በማኅበሩ መካከል ስላለው አለመግባባት፤ በሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት የሕፃናት መርጃ ኾነው የተቋቋሙ ማእከላት ነባር ይዞታዎች መጠበቅ እንዲኹም በቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ከፍተኛ የግንባታ ፕሮጀክቶች ዙሪያ በመምከር ውሳኔ እንደሚያሳልፍም ይጠበቃል፡፡

mandag 6. oktober 2014

ለመላው የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያየድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ አባላት እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን በኖርዌይ በሙሉ!!

ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ /“INVEST IN ETHIOPIA”/ በሚል ርእስ በኦክቶበር 16/2014 ኦስሎ ላይ ሴሚናር ይካሀዳል፥፥ ዝግጅቱቱን ያዘጋጀው Norwegian-African Business Association /NABA/ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ የአምባገነኑ የወያኔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየስ፥ እንዲሁም የኖርዌይ አምባሳደር በኢትዮጵያ ሚ/ር አንድሪያስ ጋርደር እና አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ የተለያዩ የኖርዌጂያን የንግድ ድርጅቶች ጋር ተገናኝተው ለመወያየትና ፓሮግራም ተይዟል፥፥
ዝግጅቱ የሚደረገው በሃሙስ ኦክቶበር 16/2014 ከ 09:00-11:30 ሲሆን ከ11፥30—12፥30 የምሳ ፕሮግራም ይኖራቸዋል፥ በመሆኑም ውድ ኢትዮጵያውያን በኖርዌይ በሙሉ እንድታውቁትና በንቃትእንድትከታተሉ እናሳስባለን፥፥
አድራሻው Confederation of Norwegian Enterprise (NHO) ማለትም Næringslivets Hus
Middelthuns gate 27
Majorstuen, Oslo ሲሆን ተጨማሪ መረጃ በቅርብ ቀን
ለበለጠ መረጃ፥ http://norwegianafrican.no/news/16th-of-october-invest-in-ethiopia-seminar-in-oslo
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ነገረ ህወሓት: ህወሓትና ‹‹ወያኔ›› ምንና ምን ናቸው?

ጌታቸው ሺፈራው (ጋዜጠኛ)
‹‹ህ.ወ.ሓ.ት›› የተሰኘው የፖለቲካ ቡድን ሙሉ ስሙ ሲዘረዘር ‹‹ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ›› መሆኑ ለማንም ግራ የሚያጋባ አይደለም፡፡ በተለይ በርሃ በነበረበት ጊዜ ከረዥም ስሙ ይልቅ ‹‹ወያኔ›› መጠሪያው ሆኖ አገልግሏል፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ይህን ስም ህወሓት ከዚህ በፊት የነበረ ታሪክ ቀጣይና የትግራይ ህዝብ ታሪካዊ እንቅስቃሴ አስቀጣይ (ወራሽ) ለመምሰል ተጠቀመበት፡፡ ህወሓት ‹‹ወያኔ›› የተሰኘ ስሙን በመጀመሪያዎቹ ለጥቂት ጊዜያት በተለይ ውስጥ ለውስጥም ሆነ በቀጥታ ካስተዋወቀ በኋላ ይህን ስሙን ሌሎችም እንዲለምዱት አደረገ፡፡ ይህን ያደረገበት ምክንያቱ ደግሞ ስሙ በታሪካዊነቱም ሆነ ትርጉሙ የህወሓትን ሰብዕና የሚገነባ በመሆኑ ነው፡፡
tplf-rotten-apple-245x300
‹‹ወያኔ›› ማለት በትግርኛ አብዮት ወይንም አመጽ እንደ ማለት ነው፡፡ ህወሓት ይህን መልካም መጠሪያ የወሰደው ደግሞ በ1935 ዓ/ም አካባቢ ተነስቶ ከነበረው ‹‹ወያኔ›› ከተባለው የአርሶ አደሮች አመጽ የቀጠለ ታሪካዊና አልጋ ወራሽ ለመምሰል ነው፡፡ ሆኖም በ1930ዎቹ መጨረሻ ትግራይ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገራችን ክፍሎችም ተመሳሳይ የአርሶ አደሮች አመጽ ተቀስቅሶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የ‹‹ወያኔ›› አመጽ የፊውዳሉ ስርዓት ከነበረው ብልሹነት የመነጨና በኋላም ለተማሪዎች አብዮትም ጭምር እንደ እርሾ እንዳገለገለ ከታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ የወቅቱ አማጺያን ህዝብ ይቀሰቅሱበት ከነበረው መፈክር መካከል ቀዳሚው ‹‹ሰንደቃችን የኢትዮጵያ ነው›› የሚል ነበረበት፡፡ በአጠቃላይ እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ አንድነትን መሰረት ያደረገ እንጂ ህወሓት ‹‹ወያኔ››ን በቅጽል ስምነት አንጠልጥሎ ይከተለው ከነበረው ‹‹ተገንጣይነት›› ፖሊሲ ጋር በእጅጉ የሚቃረን ነው፡፡ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ‹‹ወያኔ›› ወይንም አመጽ ከስርዓት እንጂ ከአገር ‹‹ነጻ›› መውጣት ወይንም መገንጠልን ጋር የተገናኘ አልነበረም፡፡
ህወሓት ከአርሶ አደሮቹ አመጽ ብቻ ሳይሆን በነ መንግስቱ ንዋይ ከተሞከረው የመንግስት ለውጥ ሙከራ በተጨማሪ ‹‹መሬት ለአራሹ›› የሚል መፈክርን አንግቦ ለተነሳው የተማሪዎች አብዮት እርሾ እንደነበር ከሚነገርለት የአርሶ አደሮች እንቅስቃሴ እጅጉን ተቃራኒ ነው፡፡ ህወሓት ‹‹እየሱስ አምላካችን ነው›› የሚል መፈክር ካነገቡት አርሶ አደሮች ይልቅ የወቅቱ የማርክሲዝም አንድ መርህ ከነበረው ስለ መሬት ለአራሹ፣ ስለ ዓለም ላብ አደሮች ትብብር ከሚያወራው የተማሪው አብዮት ቅርብ ነበር፡፡ ሆኖም ከአርሶ አደሮቹ ይልቅ ለተማሪው እንቅስቃሴ አንድ አካል ነበር የሚባለው ህወሓት ከመሬት ለአራሹ ይልቅ ‹‹ስለ ትግራይ ህዝብ›› መሬት እንደሚጨነቅ አስመሰለ፡፡ ስለ ዓለም ላብ አደሮች ትብብር ሲያወራ ከነበረው የ1960ው አብዮት ወርዶ ለአንድ ብሄር ተወላጆች ትብብር፣ መገንጠል…የመሳሰሉት ተገንጣይ ጉዳዮች ቅድሚያ ሲሰጥ ነው ከተማሪዎች አብዮትም ያፈነገጠው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ወያኔ››ነት (አብዮት) ይህኔ ነው ያከተመው፡፡ ከዚህ በኋላ ህወሓት ‹‹ወያኔ›› የሚያሰኘውን ነገር ሁሉ አጥቷል፡፡ ምክንያቱም ከአርሶ አደሮችም ሆነ ከተማሪው አብዮት አፈንግጧልና ነው፡፡
ከተማሪዎች እንቅስቃሴ እንኳን ያፈነገጠው ህወሓት የቀዳማዊ ወያኔ ወራሽ ነኝ በሚል ዳግማዊ ‹‹ወያኔን›› በመጠሪያነት መጀመሪያ አካባቢ ተጠቀመበት፡፡ ህወሓት በደርግ ላይ ድል እያስመዘገበ ሲመጣ ‹‹ወያኔ›› በተለይ በወቅቱ ተቃዋሚዎች ዋነኛ መጠሪያው ሆነች፡፡ ስሙ ከመለመዱ የተነሳ እነ መንግስቱ ኃ/ማርያም ሳይቀሩ ተግባሩን ሲያወግዙ ከህወሓትና ከረዥም ዝርዝሩ ስሙ ይልቅ ‹‹በወያኔ››ነት መጥራቱን ተያያዙት፡፡ ይህ ለህወሓት መልካም ስም ነበር፡፡ እሱ ቢጀምረውም ትርጉምና ታሪካዊ ተያያዥነቱን ሳያጤኑ ያጋነኑለት የሚቃወሙትና የሚጠሉት አካላት ናቸው፡፡
የአርሶ አደሮች አመጽ በተቀሰቀሰበት ወቅት በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተመሳሳይ አመጾች የነበሩ ቢሆንም ከህወሓት ጋር የተማሪው አብዮት አካል የነበሩት ወደ ትጥቅ ትግል ሲገቡ ‹‹ዳግማዊ፣ ሳልሳዊ…›› ብለው ስማቸውን አልወሰዱም፡፡ ወያኔ የአርሶ አደሮቹ አመጽ ኢትዮጵያዊ አላማ የነበረው ቢሆንም ልክ እንደ ህወሓት አሻፈረኝ ብለው ዱር የወጡትና ከእሱም የተሻለ አገራዊ አላማ እንደነበራቸው የሚነገርላቸውና ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ያፈነገጡት እንኳን ‹‹ወያኔ›› ነን አላሉም፡፡ በእርግጥ ህወሓት የአርሶ አደሮቹን ቀደምት አመጽ ከራሱ ጋር በማዛመድ ‹‹ዳግማዊ››ነቱን ያወጀው ከመርህና አላማ አንጻር ሳይሆን ከአርሶ አደሮቹ ጋር ‹‹በብሄር›› ግንኙነት እንዳለው ለመግለጽ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም በአብዛኛው መርህና አላማ ከተማሪዎች አብዮትም ሆነ ከአርሶ አደሮቹ አብዮት የራቀና ያፈነገጠ ያደርገዋል፡፡ አሁንም አብዛኛዎቹ የህወሓት/ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ‹‹ወያኔ›› የምትለዋን ስም አሉታዊ አድርገው በስፋት ይጠቀሙባታል፡፡ እኔ በበኩሌ ይህ ስም ለህወሓት ኢህአዴግ አይገባውም ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ህወሓት ራሱን ኢትዮጵያዊ አቋም ከነበራቸው አርሶ አደሮች የቀጠለ መሆኑን ለመግለጽ ‹‹ዳግማዊ ወያኔ›› ብሎ የሚጠራበት አላማም ሆነ ታሪካዊ ትስስር ስለሌለው ነው፡፡
በነገራችን ላይ በእንግሊዘኛው ‹‹Tigray People Liberation Front›› ከተባለው ስሙ ውስጥ ‹‹ወያኔ›› ለሚባለው እኩያ ትርጉም አይገኝለትም፡፡ በቀጥታ እንተርጉመው ከተባለ ‹‹የትግራይ ህዝቦች ነጻ አውጭ ግንባር›› ነው የሚሆነው፡፡ Tigray ትግራይ ነው፡፡ People ህዝብ የሚለውን ይወክላል፡፡ Liberation አርነት (ኃርነት) ነው፡፡ Front ደግሞ ግንባር እንጂ አብዮት ሊሆን አይችልም፡፡ ስሙን እንዲሁ ለክብር ሲባል አገናኘው እንጂ ተያያዥ ትርጉም የለውም፡፡ ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹Front››ን ‹‹ወያኔ እንዳሉት እንረዳለን፡፡ ወያኔ የተሰኘው የአርሶ አደሮች እንቅስቃሴ የራሱ የሆነ እንቅስቃሴ እንጂ ‹‹ግንባር›› ወይንም ‹‹Front›› የሚባል አልነበረም፡፡ ከህወሓት ውጭ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (‹‹Tigray Liberation Front››) የሚባል ታጣቂ ቡድንም ነበር፡፡ ግን እንግሊዘኛ ስሙ ላይ ‹‹Front› የሚል ስላለው ብቻ ‹‹ወያኔ›› በሚል የሌሎችን ታሪክ ለመጋራት አልተንጠራራም፡፡
ምንም እንኳ በማርክሲሳዊ እይታ አብዮታዊ ባይሆንም ከህወሓት ይልቅ ኢዲዩ ራሱን ወያኔ ብሎ ቢጠራ ከህወሓት የተሻለ መሰረት ነበረው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የኢዲዩ አባላት ከአማጺያኖቹ አርሶ አደሮች ጋር የሚያመሳስል የርዕዮተ ዓለማዊም ሆነ ሌሎች ትስስሮች ስለነበራቸው ነው፡፡ የተገንጣይ አላማም ሆነ በአገራቸው ላይ ጥላቻ አልነበራቸውም፡፡ ይህን ስንመለከት ህወሓት በበርካታ ምክንያቶች ‹‹ወያኔ›› የሚለው ስያሜ እንደማይገባው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ‹‹ልማታዊ መንግስት››፣ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ››፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ››…..የሚባሉትን ስሞች ዝም ብሎ በሌሉበት የመለጠፍ ታሪኩ የሚጀምረው ‹‹ወያኔ››ን በመጠሪያነት ያለ አግባብ ከቀላቀለበት ጊዜ የጀመረ ይመስለኛል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ያነሳው ሁሉ በስፋት እንደሚጠላ ያውቀዋል፡፡ ይህን የማይገባውን የክብር ስምም ገና በርሃ እያለ አስተዋውቆ ዘወር በማለቱ በአብዛኛው አሉታዊ መስሏቸው ሌሎች ናቸው መጠሪያው ያደረጉት፡፡ በተለይ በተቃዋሚዎቹ ዘንድ የማይወደው መስሎ ሳይታያቸው አይቀርም፡፡ ስለሆነም አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ህወሓት/ኢህአዴግን ‹‹ወያኔ›› ብለው ሲጠሩት ግን ከሚገባው በላይ እንዳጋነኑለት፣ የማይገባውን ታሪክ እንዳወረሱት፣ አገር ወዳድና ቀናኢ አላማ እንዳለው አድርገው እየቆጠሩት መሆናቸውን መገንዘብ ይገባቸዋል፡፡ በተለይ ህወሓትን ጠበብ ብለው እየከሰሱ ቢሆን ህወሓትን ከትግራይ ህዝብ ጋር የማይነጣጠል፣ ለትግራይ ህዝብ የሚሰራ አድርገው የሚቆጥሩት ‹‹ወያኔ›› ብለው ሲጠሩ ህወሓትን ከሚከሱበት ጠባብነት አልወጡም ማለት ነው፡፡
‹‹ወያኔነት›› በገዥዎች ላይ እምብይ ባይነት ነው፡፡ የድሮዎቹ አርሶ አደሮች ይህን ስም የራሳቸው ያደረጉት በበዝባዡ ፊውዳል ስርዓት ላይ አምጸው ነው፡፡ አሁን ‹‹ወያኔ›› የሚባለው ህወሓት ዘመናዊ ፊውዳል ሆኗል፡፡ ራሳቸውን ‹‹ወያኔ›› ባይሉም የህወሓትን ዘመናዊ ብዝበዛ የሚቃወሙ እምብይ ባዮች አሉ፡፡ እነዚህ እምብይተኞች ህወሓት አሸባሪዎች ይላቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወያኔ የሚባል አካል መባል ካለበት ግን ያለ ምንም ጥርጥር ከበዝባዡና ከዘመናዊ ፊውዳሉ ከህወሓት ይልቅ ይህን አፋኝ ስርዓት በመቃወም ላይ ለሚገኙት ደፋሮች የሚመጥን ስም ይሆናል፡፡ ችግሩ ግን ተቃዋሚዎች ራሳቸው ለራሳቸው የሚገባውን ስም ለበዝባዥ አሳልፈው የሚሰጡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ለህወሓት መልካም ነገር ነው፡፡
እኔ በበኩሌ ‹‹ወያኔ›› ብዬ ጠርቼው አላውቅም፡፡ አይገባውማ! ያለ ታሪኩ!? ያለ አላማው!?

søndag 5. oktober 2014

ሰልጣኙንም አሰልጣኙንም ያንገሸገሻቸዉ ሥልጠና

አባትና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ልጁ አምርረዉ ሲጨቃጨቁ እናት ትደርስና . . . . እባክሽ ልጄ አባትሽ የሚልሽን ለምን አትሰሚም ብላ ልጇን ትቆጣታለች። ልጅት ከተቀመጠችበት ትነሳና ምነዉ እማዬ ምኑን ነዉ የምሰማዉ፤ አባዬኮ እሱ እራሱ የማያዉቀዉን ነገር ላሳይሽ እያለኝ ነዉ ብላ ንግግሯን ሳትጨርስ በቁጣዉ ብዛት ፊቱ እንደ ፊኛ ያበጠዉ አበቷ ካንቺ ማወቅ ዬኔ አለማወቅ ይሻላል፤ ይልቅ የምልሽን ስሚ ብሎ ጮኸባት። ወጣቷ ተማሪ ወላጅ አበቷ ከስምንተኛ ክፍል በላይ ዘልቀዉ እንዳልተማሩ ብታዉቅም ለግዜዉ ማድረግ የምትችለዉ ምንም ነገር አልነበረምና እሽ አባዬ ብላ አባቷን መስማት ጀመረች። ይህ የአባትና የልጅ ስሚኝ አልሰማም ጭቅጭቅ ባለፉት ሁለት ወራት መሀይሞቹ የወያኔ ካድረዎችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየስልጠና አዳራሹ ያደረጉትን ፍጥጫ አስታወሰኝ። ይህ አብዛኛዉን ዕድሜያቸዉን ትምህርት በመማር በሳለፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በወጉ ስምንተኛ ክፍልን ባላጠናቀቁ የወያኔ ካድሬዎች መካከል በክረምቱ ወራት ተጀምሮ አሁን ድረስ የዘለቀዉ የ”አሰለጥናለሁ አታሰለጥንም” ትንግርታዊ ድራማ ወያኔ አስካሁን ከሰራቸዉ ድራማዎች በአይነቱ ለየት ያለ ድራማ ነዉ።
የወያኔ ምርጫዎች ምንም አይነት ዉድድር የማይታይባቸዉ ማንም ተወዳደረ ማንም ወያኔ ብቻ የሚያሸንፍባቸዉና ምርጫዎቹ ከመካሄዳቸዉ በፊት የት ቦታ እነማን ማሸነፍ እንዳለበቸዉ ተወስኖ ያለቀላቸዉ የለበጣ ምርጫዎች ናቸዉ። ወያኔ ግን “ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” እንደሚባለዉ ምርጫዉ በቀረበ ቁጥር የሚያክለፈልፍ በሽታ ይይዘዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በ1997ና በ2002 ዓም የተደረጉትን ምርጫዎችና እርግጠኞች ነን አሁንም በ2007 ዓም የሚደረገዉን ምርጫ የሚለያያቸዉ ነገር ቢኖር በእያንዳንዱ ምርጫ መኸል የአምስት አመት ልዩነት መኖሩ ነዉ እንጂ የምርጫዉን ዝግጅት፤ ሂደትና ዉጤት በተመለከተ ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የሚችል ልዩነት የለም። ሁሉም ምርጫዎች የሚካሄዱት ወያኔ የምርጫ ተቋሞች፤ ሜድያዉንና ፍርድ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠርበት ሁኔታ ዉስጥ ነዉ። በዚህ ላይ ቅድመ ምርጫዎችን የሚቆጣጠረዉ፤ በምርጫዉ ብቸኛ ተወዳዳሪ የሆነዉና ህዝብ የሰጠዉን ድምጽ የሚቆጥረዉ ወያኔ እራሱ ነዉ። ይህም ሁሉ ሆኖ ወያኔ ከሱ ዉጭ ማንም ምርጫዉን እንደማያሸንፍ በልቡ እያወቀ አምስት አመት እየቆጠረ የሚመጣዉ ምርጫ በቀረበ ቁጥር ግርግር መፍጠር ይወዳል። በ1997 በተደረገዉ ምርጫ ማንም አያሸንፈኝም ብሎ ሜድያዉንና የፖለቲካ ምህዳሩን ትንሽም ቢሆን ለቀቅ አድርጎ የነበረዉ ወያኔ በ2002 ዓም ይጋፉኛል ብሎ የጠረጠራቸዉን ሁሉ ማሰር፤ መደብደብና እንቅስቃሴያቸዉን መግታት ጀመረ። አሁን በ2007 ዓም ደግሞ ገና በግንቦት ወር ለሚካሄደዉ ምርጫ የኢትዮጵያን ወጣት ካልተቆጣጠርኩ በሚል ትልቅ ዘመቻ ጀምሮ በከፍተኛ በሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚገኙትን የአገሪቱ ወጣቶች በሥልጠና ሰበብ ወያኔያዊ የፖለቲካ ጠበል እያጠመቃቸዉ ነዉ።
ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወያኔን ዘረኛ ነዉ፤ ጎጠኛ ነዉ፤ ነብሰ ገዳይ ነዉ ይሉታል። አዎ እነዚህ ሁሉ የወያኔን ማንነትና ምንነት በትክክል የሚያሳዩ ቃላት ናቸዉ። ወያኔ ግን ከእነዚህ ዉጭ ሌሎች ብዙ መገለጫዎች አሉት፤ ለምሳሌ ወያኔ መዋሻት የማይሰለቸዉ ዉሸታም ነዉ፤ ዕኩይ ነዉ፤ ጨካኝና የለየለት መብት ረጋጭም ነዉ። እነዚህ የወያኔ ባህሪያት ሁሉ ያናድዱናል ወይም ያስቆጡናል እንጂ አይገርሙንም ወይም እየኮረኮሩ አያስቁንም። ጉደኛዉ ወያኔ የሚገርሙና የሚያስቁ ባህሪያትም አሉት። ወያኔ የቁጥር ጨዋታ ይወዳል፤ በተለይ ከቁጥርና ከቁጥርም በዛ ካለ ቁጥር ጋር ለየት ያለ ፍቅር አለዉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የአገር ዉስጥ ምርት ከዉጭም ከዉስጥም ተገፍቶ 5% ከጨመረ ወያኔ የሚነግረን 10% አደገ ብሎ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የትምህርት ጥራት ተንኮታኩቶ ከመዉደቁ የተነሳ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀዉ ወደ ስራ አለም በሚገቡ ተማሪዎችና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ጨርሰዉ ኮሌጅ በሚገቡ ተማሪዎች መካከል ያለዉ ልዩነት ትንሽ ነዉ፤ ወያኔ ግን በኔ ዘመነ መንግስት የዩኒቨርሲቲዉ ብዛት ብቻ ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪዎች ብዛት ከ300% በላይ አደገ እያለ ይፏልላል። ካለፈዉ ሐምሌ ወር ጀምሮ ያለፍላጎታቸዉና ያለፈቃዳቸዉ በግድ ወደ ሥልጠና ማዕከላት እየገቡ የወያኔን ርካሽ ፕሮፓጋንዳ እንዲጋቱ የሚገደዱ ወጣቶችም ጉዳይ ይህንኑ ወያኔ ከቁጥርና ከብዛት ጋር የተጠናወተዉን ፍቅር የሚያሳይ ነዉ። ይህ ወያኔ በየክልሉ ሥልጠና ብሎ የጀመረዉ ቧልት የሰልጣኛቹን እዉቀት የሚያዳብር አይደለም ወይም ለአገራችን ለኢትዮጵያም በምንም መልኩ የሚጠቅም አይደለም። የሥልጠናዉ ብቸኛ አላማና ጥቅም በወጣቱ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የወያኔን አባላት ማብዛት ነዉ። ወያኔ ድርጅታዊ የፓርቲ ስራዎችን የሚሰራዉ መንግስታዊ ተቋሞችን በመጠቀም ከመንግስት ካዝና በሚወጣ ገንዘብ ነዉና እሱን የሚያስደስተዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት አሉት ተብሎ መነገሩ ነዉ እንጂ እነዚህ አባላት ታማኝ ይሁኑ አይሁኑ ወይም ድርጅታዊ ስራ ይስሩ አይስሩ ለወያኔ ጉዳዩ አይደለም።
ወያኔ በዕረፍት ላይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከያሉበት በግድ አስመጥቶ ሥልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ የወሰዳቸዉ እርምጃዎች ሁሉ በወያኔና በተማሪዎቹ መካከል ያለዉን ሰፊ የፖለቲካ ልዩነት አጉልቶ ከማዉጣቱ ባሻገር ይህ ሳይጀመር የከሸፈዉ ስልጠና ለወያኔ ምንም የፈየደዉ ፋይዳ የለም። እንዳዉም አብዛኛዉ ተማሪ የወያኔ መሪዎችን አንገት የሚያስደፋ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሥልጠና የሚያስፈልገዉ ለተማሪዎቹ ሳይሆን ለራሳቸዉ ለአሰልጣኝ ነን ባዮቹ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በብዙዎቹ የስልጠና አዳራሾች የወያኔ ካድሬዎች ተማሪዎቹ የሚጠይቁትን ጥያቄ መመለስ አለመቻላቸዉ ብቻ ሳይሆን ካድሬዎቹ በሚጠየቁት ጥያቄ እየተበሳጩ ጥርሳቸዉን ሲነክሱ ታይተዋል። በእርግጥም ጎንደር ዉስጥ የነበረዉን ጄኔሬተር ነቅላችሁ ዬት አደረሳችሁት ከሚል አፋጣጭ ጥያቄ ጀምሮ አንዳርጋቸዉ ጽጌን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በጠየቁ ተማሪዎች ላይ አሰልጣኝ ካድሬዎች “ከእናንተ ጋር በኋላ እንገናኛለን” እያሉ ሲዝቱ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም ካለ ለጋሽ አገሮች ዕርዳታ መንፈቅ መዝለቅ የማትችል ደሃ አገር ናት፤ ሆኖም የወያኔ መሪዎችና ቤተሰቦቻቸዉ የሚዘርፉትን ገንዘብና አላግባብ የሚያባክኑትን የአገር ሃብት የተመለከተ ማንም ሰዉ ድርጊታቸዉ ከደሃዋ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በፍጹም እንደማይገናኝ ለመገንዘብ ግዜ አይፈጅበትም። ወያኔ ገነባሁ ብሎ የሚያፈርሳቸዉንና በየስብሰባዉና በየጉባኤዉ ከሚያባክነዉ ግዙፍ የአገር ኃብት ዉጭ ከሰሞኑ ምንም አገራዊ ጥቅም በሌለዉና ሠልጣኞቹ አንፈልግም ብለዉ ለተዉት ሥልጠና የሚያባክነዉ የህዝብና የአገር ገንዘብ እጅግ በጣም ብዙ ነዉ። ለምሳሌ ለአሰልጣኝ ካድሬዎች ከሚወጣዉ የትርንፖርትና የዉሎ አበል ዉጭ ለእያንዳንዱ ሰልጣኝ ተማሪ በቀን የሚከፈለዉ ሃምሳ ብር ቁጥራቸዉ ከ600 ሺ በላይ በሆኑ ሰልጣኝ ተማሪዎች ልክ ሲሰላ እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ ነዉ።
ለመሆኑ ዜጎች የሚላስና የሚቀመስ አጥተዉ በሚራቡበት አገር፤ ወጣቶች ስራ ፍለጋ ያደጉበትን መንደር ጥለዉ ባሕር እየተሻገሩ በሚሰደዱበት አገርና የገንብዘብ እጥረት እየተባለ ብዙ ፕሮጀክቶች በሚታጠፉበት አገር ወያኔ ከየት እያመጣ ነዉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየከፈለ ምንም እርባና የሌለዉ የፖለቲካ ሥልጠና ሥልጠናዉ በፍጹም ለማያስፈልገዉ የህብረተሰብ ክፍል የሚሰጠዉ? ደግሞስ ከዉጭ አገር ምንጮች ምንም አይነት የገንዝብ እርዳታ እንዳያገኙ በህግ የተከለከሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የስራ ማስኬጃ ወጪያቸዉን መሸፈን አቅቷቸዉ በሚንገዳገዱበት አገር ምን ቢደረግ ነዉ ወያኔ የራሱን ፓርቲ ስራዎች በመንግስትና በህዝብ ገንዘብ የሚያሰራዉ?
የወያኔና የገንዝብ ጉዳይ ከተነሳ እነዚህ ጉደኞች ቢነገር ቢነገር የማያልቅ ከገንዘብ ጋር የተቆራኘ ብዙ የቆሸሸ ታረክ አላቸዉ። ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ዉስጥ የአገሪቱን የአየር ሞገዶች ከዳር እስከ ዳር ያጨናነቀዉ ከዚሁ ከወያኔ የረጂም ግዜ ቆሻሻ ታሪክ ጋር የተያያዘዉ የገንዘብ ጉዳይ ነዉ። ከሰሞኑ የኢትዮጵያን ባንኮች፤ ትላልቅ መደብሮችና ዘመናዊ የመገበያያ አዳራሾች በብዙ መቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠር ሀሰተኛ ገንዘብ ተጨናንቀዋል። ይህ ማን፤ መቼ፤ ከየትና እንዴት እንዳሰራጨዉ የማይታወቅ የሀሰተኛ ገንዝብ ዝርጭት ኢትዮጵያ ዉስጥ እያንዳንዱን ሰዉ እያነጋገረ ነዉ። የወያኔ ፖሊሶች ከየባንኩና ከየገበያ አዳራሹ በየቀኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሀሰተኛ የብር ኖቶች እየሰበሰቡ መሆናቸዉን ቢናገሩም ከዚህ ሀሰተና ገንዘብ ስርጭት በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለበት ግን ምንም የተነፈሱት ነገር የለም። እንደዚህ ብዛት ያለዉ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ደግሞ አቅምና እዉቀት በሌላቸዉ ተራ ወንጀለኞች የሚሞከር ወንጀል አይደለም። ለዚህም ይመስላል ብዙ ኢትዮጵያዉያን በዚህ ሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት ዉስጥ ያለምንም ጥርጥር የወያኔ ባለስልጣኖች እጅ አለበት ብለዉ በድፍረት አፋቸዉን ሞልተዉ የሚናገሩት። መቼም መሬት ቆፍሮ ቦምብ እየቀበረ በተቃዋሚዎች የሚያሳብበዉና በፈንጂ ህዝባዊ ተቋሞችን እያፈረሰ ሽብርተኛ ብሎ በፈረጃቸዉ ድርጅቶች ላይ ጣቱን የሚቀስረዉ ወያኔ የደረሰበትን ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት ለመሙላት ሀሰተኛ ገንዘብ አሰራጭቶ ሊያጠፋቸዉ በሚፈልጋቸዉ ሰዎችና ቡድኖች ላይ አያመካኝም ማለት አይቻልም። ለሁሉም የወያኔ ነገር አንቺዉ ታመጪዉ አንቺዉ ታሮጪዉ ነዉና ይህ የሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት የራሱ የወያኔ ስራ እንደሆነ ከራሱ ዉስጥ አዋቂ ምንጮች የምንሰማበት ግዜ ሩቅ አይደለም። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዉያንን የሙጥኝ ብሎ ተጣብቆ የሚያሰቃያቸዉ የዋጋ ንረት መሠረታዊ መንስኤዉ መለስ ዜናዊ በህይወት ከነበረበት ግዜ ጀምሮ ከአገሪቱ የማምረት አቅም በላይ በሆነ መልኩ በገፍ እየታተመ ወደ ኤኮኖሚዉ ዉስጥ እንዲገባ የተደረገዉ የገንዘብ አቅርቦት ነዉ። ይህ ዘንድሮ ስሙን ቀይሮ “ሀሰተኛ የገንዝብ ስርጭት” ተብሎ አገራችንን የሚያምሳት በሽታም የዚሁ የተለመደ ወያኔ እያተመ የሚያሰራጨዉ የገንዘብ አቅርቦት ችግር አካል ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለዉም። አለዚያማ ወያኔ በነጋ በጠባ ሚሊዮንና ቢሊዮን እያለ የሚያባክነዉ ገንዘብ ከዬት ይመጣል?
ስልጠና በየትኛዉም ማህበረሰብ ዉስጥ የእዉቀትና የልምድ ልዉዉጥ ለማድረግ የሚረዳ ጠቃሚ ተግባር ነዉ፤ ሆኖም ስልጠና ሲባል አላማ፤ አትኩረትና ግብ ኖሮት በተወሰነ ቡድን ወይም ቡድኖች ላይ የሚያነጣጥር የእዉቀትና ልምድ መቀባበያ መሳሪያ ነዉ እንጂ እንዳዉ በጅምላ የአንድ አገር ህዝብ እንዳለ ተመሳሳይ ስልጠና ይዉስድ እየተባለ የሚደገስ የጨረባ ተዝካር አይደለም። ደግሞም ስልጠና አሰልጣኝና ሰልጣኝ ተግባብተዉና ሁለቱም ሚናቸዉን ወድደዉና ፈቅደዉ የሚካሄድ የጋራ እንቅስቃሴ ነዉ እንጂ ሠልጣኝ አልሰልጥንም ካለና አሰልጣኝ ደግሞ ጥያቄ የጠየቀዉን ሁሉ “ቆይ ጠብቀኝ” እያለ የሚዝትበት ከሆነ ነገሩ ሥልጠና መሆኑ ቀርቶ ጦርነት ይሆናል። ለመሆኑ ወያኔ የአገሪቱን ወጣቶች ሥልጠና ብሎ ሰብስቦ ምንድነዉ የሚላቸዉ? መልሱ ቀላል ነዉ። ከብዙዎቹ ሰልጣኞች አንደበት በግልጽ እንደሰማነዉ፤ የወያኔ ካድሬዎች በየስልጠናዉ አዳራሽ የሚናገሩት በሚቀጥለዉ ምርጫ ኢህአዴግን ካልመረጣችሁ የወደፊት ዕድላችሁ ይጨልማል፤ ከሐይማኖት አክራሪዎች እራሳችሁን አጽዱ ወይም ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር እንዳትተባበሩ እያሉ ነዉ። ወያኔ በስልጣን ላይ በቆየባቸዉ አመታት ህይወቱ እንደ ሐምሌ ጨለማ የጨለመበት የኢትዮጵያ ወጣት ግን በየስልጠና አዳራሹ በተደጋጋሚ የሚጠይቀዉ እነሱ ሽብርተኛ ብለዉ ያሰሯቸዉን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ባስቸኳይ እንዲፈቱና ወያኔዎችን እራሳቸዉን በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ እያለ ነዉ።
ባለፈዉ የአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊ/መንበር ለኢትዮጵያ ወጣቶች ኑና ለነጻነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት አብረን እንታገል የሚል አገራዊ ጥሪ አድረገዋል። በየዘመኑ ለወገኖቹ መብትና ነጻነት መከበር ሽንጡን ገትሮ የታገለዉ የኢትዮጵያ ወጣት የነጻነት መሪዉ ያቀረበለትን የፍትህና የእኩልነት ትግል ጥሪ ረግጦ ከወያኔ ጋር በተላላኪነት ከሚያስተሳስረዉ ሥልጠና ጋር በፍጹም እንደማይተባበር ሁላችንም እርግጠኞች ነን። ዛሬ ዕድሜዉ ከ35 አመት በታች የሆነ ኢትዮጵያዊ ወጣት አብዛኛዉን ዕድሜዉን በወያኔ ስርዐት ዉስጥ የኖረ ወጣት ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ወጣት ወንድሙ፤ ዘመዱ ወይም የቅርብ ጓደኛዉ በወያኔ ነብሰ ገዳዮች ሲገደሉ በአይኑ እየተመለከተ ያደገ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት የወያኔ በደልና ግፍ የሚነገረዉ ወጣት ሳይሆን ይህንን በደልና ግፍ ለማቆም ቆርጦ የተነሳ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት ወያኔ ሥልጠና እያለ የሚፈጥርለትን አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀመ እራሱንና ወገኖቹን ነጻ ያወጣል እንጂ በሥልጠና ስም ከወያኔ በሚመጣለት ኮቶቶ እጅና እግሩን አስሮ የወያኔ ባሪያ ሆኖ አይኖርም። ለዚህ ቆራጥና አርቆ አስተዋይ ለሆነ ወጣት ያለን መልዕክት አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና በድል የምንገናኝበትና የአገራችን ባለቤት የምንሆንበት ቀን ቅርብ ነዉ የሚል ወገናዊ መልዕክት ነዉ።

lørdag 4. oktober 2014

ውርደት! – መለስ ፣ ስብሃት፣ የኢህአዴግ ኤምባሲ ከዚያስ? አገርና መሪ ላላቸው ኤምባሲ አገር ነው

ሰሞኑን ኢህአዴግ በፈለፈላቸው ድርጅቶች ታጅቦ የ”ባንዲራ ቀን” በሚል የመለስን ፈረጀ ብዙ ዝክር ሊደግስ ከወዲያ ወዲህ እያለ ነው። አቶ መለስ “ጨርቅ” ብለው ሲያነሱና ሲጥሉት የነበረውን ያገር መለያ ለፈጠራና ከጀርባው ተንኮል ያዘለ ዓላማቸው ሲሉ ቀኑ እንዲዘከር አድርገዋል፤ የምዕራባውያን ጉዳይ አስፈጻሚ እንደመሆናቸውም የታዘዙትን በሠንደቅ ዓላማው ላይ ጨምረዋል። በዚሁ የ”ባንዲራ ክብር” ሳይሆን በሌላ አህጉራዊ ክስተት ራሳቸው ያሰፉትን ጨርቅ ገልብጠው ባደባባይ ሰቅለውት ነበር። በወቅቱ ራሳቸው ያሰሩትን ባንዲራ አናትና ግርጌ መለየት ባለመቻላቸው ተወግዘውበታል፤ የትግራይን ቢሆን እንዲህ ያደርጉት ነበር ተብሎም ተጠይቋል።
ባድመ ስትወረር “ደርግ ኢሰፓ” ተብለው ጎዳና ላይ የተጣሉት የቀድሞው ሰራዊት አባላት ለዳግም ዘመቻ “እናት አገር ጥሪ” ሲተም በገጸ በረከትነት የተሰጠው ያደራ ቃል ኪዳን ይኸው “አታስፈልግም ጨርቅ ነህ” የተባለው መለያ ነበር። ሲፈልጉ የሚጥሉት፣ ሲጨንቃቸው የሚያነሱት መከረኛ ባንዲራ ዳግም አጀንዳ ሆኖ ሰሞኑንን ቀርቦልናል።
wedi1በአሜሪካ በሚገኘውና ኢህአዴግ “ኤምባሲ” በሚለው ቅጥር ግቢ ውስጥ ወዲ ወይኒ የሚባሉ ታጋይ የፈጸሙት ድርጊት ነው የባንዲራን ጉዳይ ዳግም አጀንዳ ያደረገው። የወዲ ወይኒ ገድለ ዜና አስገራሚ የሆነባቸው፣ ያሳዘናቸው፣ ያናደዳቸው፣ የተደፈርን ስሜት የፈጠረባቸው፣ ክስተቱን በመቃወም ኢህአዴግን በመወከል መግለጫ ያወጡ፣ እስከመቼ ኢህአዴግ “ሆደ ሰፊ ይሆናል” ብለው የጠየቁ፣ አሜሪካንን የወነጀሉ፣ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጆን ኬሪ ለፍርድ እንዲቀርቡ የጠየቁ፣ … በተለይም የሳይበር ሚዲያውን አጣበውት ከርመዋል። በሌላ በኩል ዜናውን እንደዜና ብቻ ወስደው ሚዲያ በዘነጋቸው ኢትዮጵያዊያን ላይ ለሚደርሰው ግፍ ያዘኑ ስፍር ቁጥር የላቸውም።
ዋሽንግተን በሚገኘው የኢህአዴግ ጽ/ቤት ውስጥ የመዋቅሩ “መሪ” ተብለው የተቀመጡትን ግርማ ብሩን ለማነጋገር እንደመጡ የሚናገሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ ወዲ ወይኒ ጥይት ሲተኩሱ ተሰምቷል። ታይቷል። ተረጋግጧል! በኢትዮጵያ ስም የተሰቀለው የህወሃት/ኢህአዴግ ዓርማ ወርዷል! በዚሁ በፊልም ተደግፎ በቀረበው ዜናና የማህበራዊ ገጽ ዓምዶች ላይ ዋሽንግቶን ከተማ ከዋይት ሃውስ 4 ማይል ርቀት ላይ በሚገኘው የኢህአዴግ ግቢ ውስጥ ተሰቅሎ የነበረው “ጨርቅ” ወርዶ ተጥሏል። “የጨርቁ ፍቅር ያቃጠለው” የጽህፈት ቤቱ ሰራተኛ የተጣለውን “ጨርቅ” ሰብስቦ ወደ ቢሮ ሲያስገባም ከካሜራ እይታ አላመለጠም። እንግዲህ ይህንን እውነት ነው ለመካድና “ከዓይናችሁ ጆሯችሁን እምኑ” እየተባልን ያለነው።
በሌላ በኩል የህዝብ ቀልብ ለመሳብ “ባንዲራ ያዋረዱ” በሚል “ኢህአዴግ በፈቃዱ ያሰራውን ጨርቅ” አውርደው የጣሉትን ለመክሰስና ከሃዲ አድርጎ ለመሳል ተሞክሯል፤ ሙከራውም ቀጥሏል። ሁኔታውን የሚከታተሉ እንደሚሉት “ይህ የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው” በማለት የሚጠሩትን ጨርቅ “ይህ የእኔ ባንዲራ አይደለም” በማለት ቀዳደው የሚጥሉ ዜጎች በምን ሂሳብ ተቃውሞ ይሰነዘርባቸዋል የሚል ጥያቄ እያነሱ ነው።
ህወሃት ትግራይን ነጻ ለማውጣት ትግል ጀምሮ፣ በወቅቱ ደርግ በነበረው የአመራር ጥበብ እጥረትና ሌሎች ተጽዕኖዎች ከአገዛዝ መንበር ተነስቶ ህወሃት/ኢህአዴግ አገር ገዢ ለመሆን ሲታደል የአገሪቱን ባንዲራ “ጨርቅ” ብሎ አዋርዶታል። የቀለብ መቋጠሪያው እራፊ አድርጎ ክብሩን ገፎታል። ባደባባይ አገርና ህዝብ እየተቃወመ በጠብ መንጃ ሃይል አስወግዶታል፤ አቃጥሎታል። ራሱ ባሰፋው ሌላ “ጨርቅ” ተክቶበታል። ይህ የሸፍጥ ታሪክና ተግባር የተረሳ ተደርጎ ዛሬ ህወሃት/ኢህአዴግ ደርሶ ለሠንደቅ ዓላማ ክብር ሰጪ ሆኖ ሙግት መግጠሙ ጥያቄውን የሚያነሱ ክፍሎች ተግባሩ “ያቅለሸልሻል” ባይ ናቸው።
“አገር የነሱ መፈንጫና ሃብት ማግበስበሻ የሆነችላቸው የድጋፍ ቀረርቶ ለማሰማት ቅድሚያ ቢይዙ፣ አገር የላችሁም፣ ባንዲራ አልባ ናችሁ፣ የተባልን የነሱ የሆነውን ጨርቅ አንፈልግም ብንል ምን ይገርማል?” የሚሉት ክፍሎች፣ “በሎንደን የኤርትራ ኤምባሲን ዘልቀው ለሰዓታት የተቆጣጠሩት አምባገነን በሚባሉት የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ “ዲፕሎማቶች” ጥይት አልተተኮሰባቸውም። ኢሳያስን አምባገነን በማለት የኤርትራን ህዝብ “ነጻ” አወጣለሁ የሚለው ህወሃት ግን በወዲ ወይኒ አማካይነት ህግ ባለበት አገር የህወሃትን ማንነት ባደባባይ አሳይቷል። “እዛው ህወሃት በሚነዳት አገር ውስጥ ቢሆን ኖሮ ስንቱን ይረሽን ነበር” ሲሉም የሚጠይቁ አሉ። እነዚህ ክፍሎች “አገር ቤት የተረሸኑትንና ታስረው የሚሰቃዩትን ቤት ይቁጠራቸው” ሲሉ ተደፈርን በሚል ስሜታቸውን የሚያንጸባርቁትን ወገኖች “ወዮልኝ ቀን ያጋደለ እለት” በሚል ምጸት ጥርሳቸውን ይነክሱባቸዋል።
 http://www.goolgule.com/degraded-meles-sebhat-eprdf-whats-next/?utm_content=fbshare-js-large&utm_campaign=&awesm=fbshare.me_dR51&utm