onsdag 24. desember 2014

በነ ሀብታሙ አያሌው የክስ ጉዳይ የተሰየመው ችሎት ‹አስገራሚ› ውሎ

∙ተከሳሾቹ ‹‹ዘረፋ›› ተፈጽሞብናል ብለዋል
∙‹‹ለማን አቤት ይባላል?›› ሀብታሙ አያሌው
በላይ ማናዬ
ዛሬ ታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ጨምሮ 10ሩም ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት ቀርበው ነበር፡፡ የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች ተሟልተው ፍርድ ቤት ተገኝተዋል፡፡
ችሎቱ የተሰየመው ታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ወቅት ተከሳሾች በቀረበባቸው የሽብር ክስ ላይ የሰጡትን መልስ በተመለከተ 7ኛ ተከሳሽ መልስ በዕለቱ ባለማቅረባቸው አሟልተው እንዲቀርቡ ነበር፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾች በእስር ላይ ባሉበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊጎበኟቸው የሚሄዱ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ወደ እስር ቤቱ ሲገቡ በተለየ መዝገብ እንዲመዘገቡ እየተደረጉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ስለነበር ይህን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ በታዘዘው መሰረት ማብራሪያውን ለመስማት ነበር፡፡
የተከሳሾች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች በጥየቃ ወቅት በተለየ መዝገብ ይመዘገባሉ የተባለውን አቤቱታ በተመለከተ፣ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በደብዳቤ መልስ መስጠቱ የተገለጸ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ‹‹ማረሚያ ቤቱ በሰጠው መልስ እስረኞች ከሌሎች በተለየ የደረሰባቸው ችግር የለም›› ማለቱን ገልጾ ይህንኑ መልስ ሙሉ ለሙሉ መቀበሉን አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በዛሬው የችሎቱ ውሎ ላይ ተከሳሾች ለየት ያለ አቤቱታ በጠበቆቻቸው በኩል አቅርበዋል፡፡ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ለችሎቱ እንዳስረዱት ደንበኞቻቸው ከሌሎች በተለየ መልኩ ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ አቶ ተማም አባቡልጉ በታህሳስ 12 ለ13 ቀን 2007 ዓ.ም አጥቢያ ሌሊት ስምንት ሰዓት ጀምሮ ደንበኞቻቸው ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ የግል ማስታወሻዎቻቸው፣ ገንዘብ እና በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ እያዘጋጁት የነበረው መቃወሚያና መከራከሪያ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡
‹‹ደንበኞቼ ላይ እየተደረገ ያለው ጉዳይ ለህይወታቸውም የሚያሰጋቸው ነው፡፡ በማረሚያ ቤቱ በሌሊት ፍተሻ ያደረጉባቸው ሰዎች ቀደም ሲል በምርመራ ወቅት ‹ህገ-ወጥ› ተግባራት ሲፈጽሙባቸው የነበሩ የፌደራል ፖሊስና የደህንነት አባላት ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ደንበኞቼ ያውቋቸዋል፡፡ ስለሆነም ፍተሻው የተከናወነው በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አልነበረም ማለት ነው፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው የተለየ የስም ዝርዝር ተይዞ ከሌሎች በተለየ መልኩ ነው፡፡ ለአብነት ደንበኞቼ አቶ አብርሃ ደስታና በሌላ የክስ መዝገብ የተከሰሰው አብዱራዛቅ አክመድ ላይ የሆነው ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ነው፡፡ ፍተሻው ስለት ነገር አልያም ሌላ ህገ-ወጥ ቁሳቁስ ለመያዝ የተደረገ አለመሆኑን ከተወሰዱት ንብረቶች ማየት ይቻላል›› ሲሉ አቶ ተማም ለፍርድ ቤቱ በደንበኞቻቸው ላይ የተፈጸመውን ድርጊት አስረድተዋል፡፡
ይህን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ‹‹ማረሚያ ቤቱ መንግስት ዜጎች ታንጸው እንዲወጡ ያሰራው ነው፡፡ ይህን አሰራር ለመጠበቅም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የተለያዩ ስራዎችን ሊሰራ ይችላል፡፡ እየቀረበ ያለው አቤቱታም ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ነው›› ብለዋል፡፡
ጠበቃ ተማም የደንበኞቻቸውን አቤቱታ ከህግ አንጻር ያስረዱ ሲሆን፣ ‹‹በመሰረቱ ፍተሻ ሊካሄድ መቻሉ ላይ አይደለም አቤቱታው፡፡ የተካሄደው ፍተሻ ግን ህገ-ወጥ ነው፤ ምክንያቱም ፍተሻው የተከናወነበት ሰዓት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ሳይሆን ሌሊት 8 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ይህ ህገ-ወጥ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ፍተሻው በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አይደለም የተከናወነው፡፡ በደህንነቶችና የፌደራል ፖሊሶች ነው ፍተሻው የተደረገው፡፡ ይህም ማረሚያ ቤቱ ደንበኞቼን ለመጠበቅ ፍላጎቱም ሆነ ብቃቱ እንደሌለው ያሳያል፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ይህን መሰል ድርጊት የፈጸሙት አካላትና በማን ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን›› ብለዋል፡፡
ጠበቃ ተማም በተጨማሪ ከደንበኞቻቸው ላይ በፍተሻው ወቅት የተወሰዱባቸው ንብረቶችና ማስታወሻዎች እንዲመለሱላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ‹‹የተለየ ከፍተኛ በደል ደርሶብኛል›› በሚል ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዱ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበሩት 3ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺ የጠየቁት የመናገር እድል ሳይፈቀድላቸው ቀርቷል፡፡
በጠበቆቹ አማካኝነት የቀረበው አቤቱታን በተመለከተ ችሎቱ አስተያየት የሰጠ ሲሆን በተለይ ጠበቃ ተማም አቤቱታውን ባቀረቡበት ወቅት ‹‹ማረሚያ ቤቱ ደንበኞቼን ለመጠበቅ ፍላጎትም ብቃትም የለውም›› ያሉት አገላለጽ ተገቢ ስላልሆነ እንዲታረሙ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በቃል የገለጹት የመሐል ዳኛው፣ ‹‹እንዲህ አይነት አገላለጽ ማረሚያ ቤቱ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ የሚገፋፋ እንዳይሆን…›› በማለት ሌላ አስገራሚ መነጋገሪያ ከፍተዋል፡፡
ይህን የዳኛውን ንግግር ተከትሎ 2ኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ አያሌው የመናገር እድል ከተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላ ለአጭር ጊዜ ተፈቅዶለታል፡፡ እናም፣ ‹‹እርስዎ እያሉት ያለው ነገር ተገቢ አይደለም፡፡ በህይወቴ ላይ የደህንነት ስጋት አለብኝ ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ይህንን ስጋቴን ለችሎት እያስረዳሁ ነው፡፡ ግን እርስዎ ‹የበቀል እርምጃ› እንዲወሰድብን ማሳሰቢያ እየሰጡ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ በእርግጥ አሁንም የበቀል እርምጃ እንደማይወሰድብን ማረጋገጫ የለንም፡፡ እሺ ለማን አቤት ይባላል? የደረሰብንን በደል ለፍርድ ቤት ከማስረዳት ውጭ ለማን አቤት እንላለን….አሁን እኮ ፍርድ ቤቱ ከማረሚያ ቤቱ ጋር መወገኑን ነው እያየን ያለነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የእኛን አቤቱታ እየሰማ አይደለም፡፡ ከፍርድ ቤት ውጭ ለማን አቤት እንበል?›› ሲል አቤቱታውን በስሜት ውስጥ ሆኖ አስረድቷል፡፡
የሀብታሙን ንግግር አዳምጠው አንደኛ ዳኛ ‹‹እኛ ሳንሆን ህጉ ነው ይህን እንድንል የሚያደርገን›› በማለት አጭር መልስ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ መልኩ ቀጥሎ የዋለው ችሎት በተከሳሾች በኩል የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ፍርድ ቤቱ ይህን ጉዳይ የማየት ስልጣን አለው ወይስ የለውም በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት፣ እና መደበኛ ክሱን ለማየት ለታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተጥቷል፡፡

mandag 22. desember 2014

የወደፊቱ የተሻለ የህይወት ተስፋ ያለው ወያኔ መቃብር ላይ ነው!!

ግንቦት 7
ወያኔ በሀገራችን የዘረጋው ማህበራዊ ፖለቲካዊና የኢኮኖሚ ስርአት ለጠቅላላ ህዝባችን፣ በተለይ ለወደፊቱ ሀገር ተረካቢ ወጣት ሲኦል መሆኑ ቅጥሏል። በሀገሬ ውስጥ፣ ሰርቸ የተሻለ ህይወት እኖራለሁ ብሎ ማለም ቅዠት ሆኗል። ከዚህ ይልቅ ያብዛኛውን ወጣት ተስፋ ሀገር ጥሎ በገፍ መሰደድ ከሆነ ውሎ አድሯል።
በእጅጉ በሚዘገንን ሁኔታ በግፍ ተሰቃይተው ከሳውዲ አረቢያ ወደሀገራቸው ከተመለሱት ከ160 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ግማሽ ያህሉ ተመልሰው መሰደዳቸውን በቅርቡ የወጣ ጥናት አረጋግጦል። በዚህ ሁኔታ ከተሰደዱ ወገኖቻችን ውስጥ ቁጥራቸው ከ70 በላይ የሚሆኑት ቀይ ባህር ላይ የነበሩበት ጀልባ ሰምጦ አልቀዋል። እነዚህ ወገኖቻችን ጉዞቸው በሞትና ህይወት መሃል መሆኑን አስቀድመው ያውቃሉ። ይህንን ያስመረጣቸው ግን የወያኔ ስርአት ነው። የወያኔ ስርአት የተመቻቸው ለስርአቱ ሹመኞችና ለዘመድ አዝማድ ከዚያ ከተረፈ ለጎሳ ተወላጆቻቸው ብቻ ነው። ሀገሪቱ ውስጥ ተገኘ የሚባል የኢኮኖሚ እድገት ካለም ከዚሁ ከጠባብ ቡድን ጥቅም አልፎ መከረኛውን ህዝብ የሚጠግን አልሆነም።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ከተስፋ ቆራጪነትና ሞትና ህይወትን ከሚያስመርጥ አስከፊ ህይወት ያለፈ ምርጫ አለ። ዋናው ምርጫቸውም ይህ ሊሆን ይገባል፤ ምርጫው ለዚህ መከራና ሀዘን ውርደት የዳረገንን ጨካኝ የወያኔ ስርአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ነው።
ወያኔ የህዝቡ ጉስቁልናና ስቃይ ጉዳዩ አለመሆኑን ባለፉት ሳምንታት ከ70 በላይ ወገኖቻችን ቀይ ባህር ውስጥ ሰምጠው: አለም በሀዘን በሚመለከተንና መንግስት አለ ብሎ የሀዘን መግለጫ በሚልክበት ሰአት የብሄረሰብ ቀን በሚባል የቦልት በአል የወያኔ ሹሞች ብዙ ሚሊዮን ብር አውጥተው በውስኪ እየተራጩ ይጨፍሩ ነበር።
ይህ አልበቃ ብሎ አሻንጉሊቱ ሃይለማርያም ደሳለኝ በስደተኛው ላይ ለሰሚ የሚቀፍ የወረደ አሉባልታና ስድብ ሲያወርድ ሰምተናል፣ ራሱን ያወረደ ተረት ተረትም ተናገረ። በሥልጣን የመባለግ ዝንባሌያቸው ሳይውል ሳያድር በሚጠቀሙት የባለገ አዋራጅ ቃላት የመጠቀም ርሃባቸው አሳየን።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፦ በምድረ ኢትዮጵያ የተስፋ መቁረጥና ለወያኔ ሎሌዎቹ መሳለቂያ እንድንሆን ያበቃን ይህ የነቀዘ ዘራፊ የወያኔ ስርአት ብቻ ነው። ይህ ሁሉ ስቃይና ውርደት የሚቆመው ወያኔ ሲወገድ ብቻ መሆኑን ሁላችንም ጠንቅቀን ልንረዳ ይገባል። በቅርቡ ዱላውንና ግፉን ሁሉ ለመቀበል ቆርጠው ወያኔን ከተጋፈጡት የሰማያዊ ፓርቲ አባልና ደጋፊ ወጣቶች ብዙ ልንማር ይገባል። እንደእባብ በጭካኔ መቀጥቀጣቸው አጠነከራቸው እንጂ አላዳከማቸውም።
ወያኔ ዛሬ ከመቸውም በበለጠ ነቅዞል። የጭካኔውና የፍርሀቱ ምንጪ ጣር ሞቱ እንጂ ሌላ አይደለም።
ሞትና ህይወትን ከሚያማርጥ ስደት የደረሰው ወጣቱ አርበኝነትን መምረጥ አለበት። ከቀን ጅቦች ራስን በማዳን ውርደትን፣ ስደትን ማስወገድ ይቻላል። ይህ የነገ ሳይሆን የዛሬ ውሳኔ መሆን ይኖርበታል።
በመሆኑም ግንቦት 7 ወጣቱ በያለህበት በራስህ አነሳሽነት እንድትደራጅ ያበረታታል። አመች ሁኔታ ያለህ ወጣት ደግሞ ተቀላቀለን። ሰራዊቱ ውስጥ ያለህ ወጣትና ሎሌነት የሰለቸህ ሁሉ የነጻነት ሀይሎችን ትቀላቀል ዘንድ ጥሪያችን ይድረስህ።
የሀገራችን የህዝባችንና የያንዳንዳችን የተሻለ ህይወትና ዘመን ተስፋ የተቀመጠው ወያኔ መቃብር ላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ድል ኢትዮጵያ ህዝብ!!!
source www.ginbot7.org

በምርጫ ቦርድ ደባ አንድነት አይደናገጥም! ሲል አንድነት ፓርቲ መግለጫ ሰጠ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የ2ዐዐ7 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍና ለዚህም መተማመኛው ሕዝቡ መሆኑን ገልፀ «ተደራጅ 2007 ለለውጥ» በሚል መፈክር አንግቦ አገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትና ኢህአዴግን በቃህ ለማለት ሌት፣ ከቀን በንቃትና በትጋት እየሠራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ነፃ ሚዲያ በታፈነበትና በተዘጋበት አንድነት የራሱን የማተሚያ ማሽን ገዝቶ በየጊዜው ሆን ተብሎ በሚመስል መልኩ በሚጠፋው የኤሌክትሪክ ችግርን ለማሸነፍ የራሱን ከፍተኛ ኃይል ያለው ጀነሬተር በመግዛት በሣምንት የራሱን ጋዜጦችን እያተመ እያንዲያሰራጭ ተገዷል። ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ጋዜጠኞችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለወሳኑ የ2007 ምርጫ ትግል እየተቀላቀሉት ይገኛሉ። አንድነት በአሁኑ ሰዓት ከመቼውም ጊዜ በላይ ትግሉን በአግባቡ ለመምራትና ለውጥ ለማምጣት በተሻለ ቆመና ላይ ነው ያለው።
በምርጫ ቦርድ በአንድት ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ሆነ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ የሌለውን የጠቅላላ ጉባኤ አባላትና የምላተ-ጉባኤ ቁጥር በተሻሻለው ደንባችን ውስጥ እንድናካትት የተወሰነብንን ፈርድ ገምድል ድርጊት ሕገ-ወጥ መሆኑን ብናውቀውም ጠቅላላ ጉባኤ መጠራትን እንደ ጉዳት ሳይሆን አንደ ልዩ እድል በመቁጠር፣ 320 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በመጥራት የምርጫ ቦርድ ተወካይ በተገኘበት የተሳካና አንፀባራቂ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደናል። የጠቅላላ ጉባኤውንም ሰነድ ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም ለምርጫ ቦርድ ገቢ ተደርጓል።
ሁሉ እንደሚገነዘበው በአሁኑ ሰዓት ሕዝቡ በኑሮ ውድነትና በሥራ እጦት ከመሰቃየቱም በላይ ሙስና ሰፍኗል፤ መልካም አስተዳደር የሕግ የበላይነት ከቶውንም ጠፍቷል። የሕዝብ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ገዝፎና አፍጥጦ እየመጣ ነው። በመሆኑም ኢህአዴግ በፍርሃትና በጭንቀት እየራደ ነው። ምረጡኝ ብሎ ሕዝብ ፊት ለመቅረብ የሚያስችለው የፖለቲካና የሞራል ኃይል ስለሌለው ውሸት፣ ማስፈራራት ማሰር መግደል ማሸነፊያ መሣሪያዎች እንዳልሆኑትም በግልጽና በትክክል ተደራጅቷል። አሁን የቀረው ማሸነፊያው መንገድ አንድነት ፓርቲን በመዝጋት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ጥንቱንም የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች የሆነውን ወኪሉን በመጠቀም በአንድነት ላይ ዘመቻ ከፍቷል።
ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም በምርጫ ቦርድ ከፍተኛ አመራር የተሰጠው በቅጥፈትና በውሸት የተሞላው መግለጫም የሚያሳየውና የሚመሰክረው ይህንኑ ነው። ነገር ግን እውነቱን በአጭሩ እንደሚከተለው እናስቀምጣለን፡፡ አንድነት ፓርቲ ታህሣሥ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም ያካሄደውን የጠቅላላ ጉባኤ ሰነድ ለምርጫ ቦርድ ካስገባ በኋላ ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 20 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ በዘጠኝ ነጥቦች ላይ ማብራሪያ እንድንሰጥ ጠይቄን መልስ ሰጠን፤ በመቀጠልም ጥቅምት 2ዐ ቀን 2ዐዐ7 ዓም በተፃፈ ደብዳቤ ጥያቄ ከዘጠኝ ወደ ሦስት አውርዶ ላከልን ለዚህም አንድነት መልስ ሰጠ፡፡ ቀጥሎም ቦርዱ ህዳር 10 ቀን 2007 በተፃፈ ደብዳቤ ጥያቄውን ወደ አንድ አወረደው እንዲያውም በመጨረሻ ህዳር 19 ቀን 2007 ዓም በተፃፈ ደብዳቤ። «ፓርቲው በሰጠው ምላሽ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ብዛት 320 እንደሆነ አሳውቋል። ይሁን እንዷ በተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ አካቶ ያላቀረበ በመሆኑ ይህንኑ አሟልታችሁ እንድታቀርቡ በአክብሮት እናሳውቃለን» የሚል ነው። እኛም ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተን ይህንኑ ጥያቄ እንዲሟላ ከማድረጋችንም ባሻገር በሕገ-ደንባችን መሠረት በብሔራዊ ም/ቤት ተመርጠው የነበሩት የፓርቲውን ፕሬዚደንት ሹመት በጠቅላላው ጉባኤ አፀድቀናል። እንጂ አይነቱን በሕገ-ደንቡና በሥነ-ሥርዓት ለተከናወኑ ጉዳዮች ያልተገባና የተሳሳተ መግለጫ መስጠት በጣም አሳኝ ነው። በተለይም የሕዝብ ታዛቢዎች ታህሣሥ 12 ቀን 2007 ዓ.ም እንደሚመረጡ እየታወቀ ይህን ዓይነት መግለጫ መስጠት ሕዝቡ በጥንቃቄና በተደራጀ ምልኩ ትክክለኛነትና ሀቀኞች የሆኑ ታዛቢዎችን እንዳይመርጥ ለማሰናከል የታቀደ ይመስላል። በመሆኑም ዛሬም ሆነ ነገ አንድነት ፓርቲ ከሕዝብ ጋር ሆኖ ትግሉን አጠንክሮ ይቀጥላል አባላትም ሆነ ሕዝቡ ከፓርቲያችን ጎን ተሰልፎ ትግሉን እንዲያጧጡፈው ከአክብሮት ጋር እንጠይቃለን።
ድል የህዝብ ነው!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

torsdag 18. desember 2014

ንግድ ባንክ የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራርን ከስራ አገደ

የሰማያዊ ፓርቲ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ እያስፔድ ተስፋዬ ከሚሰራበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአዳር ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ በደረሰበት እስር ምክንያት ከስራው ታገደ፡፡ እያስፔድ ተስፋዬ በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ጨለማና ቀዝቃዛ ክፍል ታስረው ከነበሩት አመራሮች መካከል አንዱ ሲሆን ከእስር ከተፈታ በኋላ ታስሮ ስለመቆየቱ ማስረጃ ቢወስድም ለ15 ቀን ከስራ ታግዶ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

‹‹ታስሬ መቆየቴን የሚያሳይ ማስረጃ ወደምሰራበት ቅርንጫፍ ስወስድ ከእኛ አቅም በላይ ስለሆነ ወደ ዲስትሪክት ውሰድ ተባልኩ፡፡ ዲስትሪክት ስወስድ የንግድ ባንክ ዳይሬክተር የሰው ኃይል አስተዳደር ማመልከቻና ታስረህ የቆየህበትን ማስረጃ አስገባና እነሱ ወደ ስራ ገበታህ ተመለስ ካሉህ ነው የምትመለሰው፤ እነሱ ተመለስ እስኪሉህ ድረስ ግን ወደ ስራ ገበታ መመለስ አትችልም አሉኝ፡፡ ባሉኝ መሰረትም ለሰው ኃይል አስተዳደር ደብዳቤና ከፖሊስ ጣቢያ የተሰጠኝን ማስረጃ ወሰድኩ፡፡ ዳይሬክተሩ እስኪያየው ድረስ ተብሎ አንድ ቀን ቀጠሮ ተሰጠኝ›› የሚለው እያስፔድ በቀጠሮው መሰረት ሲሄድ ጉዳዩ ለቅሬታ ሰሚ ኮሜቴ እንደተላከ፣ ነገር ግን የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባሎች ስልጠና ላይ በመሆናቸው ለ15 ቀን ስራ መግባት እንደማይችልና ለታገደበት ቀናትም ደመወዝም እንደማይከፈለው እንደተገለጸለት ለነገረ ኢትዮጵያ አስረድቷል፡፡

ቀደም ሲል የሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ አቶ ወሮታው ዋሴ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተባረሩ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

ምንጭ ነገረ ኢትዮጵያ

በአዳር ሰልፍ ወቅት ተይዘው ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ምክትል ፀኃፊ ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው

በአዳር ሰልፍ ወቅት ተይዘው ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ምክትል ፀኃፊ መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ ራሳቸውን ስተው ሆስፒታል እንደገቡና ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ እንደሆነ የፓርቲው ፕሬዝደንት አቶ ሽዋንግዛው ገ/ስላሴ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በአዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ተይዘው ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን ለአምስት ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ የስኳር በሽታ መድሃኒታቸውን በመቀማታቸውና ህክምናም ባለማግኘታቸው ታመው እንደነበር ለማወቅ መገለጹ ይታወሳል፡፡

መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በድብደባውና በስኳር በሽታ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ዘውዲቱ ሆስፒታል የሚገኙ ሲሆን ሆስፒታል ከገቡበት ቅዳሜ ታህሳስ 4/2007 ዓ.ም ጀምሮ ሰው ማናገር አለመቻላቸውን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አክለው ገልጸዋል፡፡


ምንጭ ነገረ ኢትዮጵያ

torsdag 11. desember 2014

በሃገራችን ላለው ችግር የሴቶች ተደራጅቶ መታገል አስፈላጊ እና ወቅታዊ ምላሽ ነው፦

ዛሬ ዛሬ ከረጅም አመታት ጀምሮ በሃገራችን የተነሳው የሴቶች መብት ይከበር የሚለውን ይህዝብ ጥያቄ
ለመቃረን እስኪመስል ድረስ ከባለፉትም ጊዜያቶች በባሰ ሁኔታ የሴቶች መብት እየተጣሰ ይገኛል።
ከዛም አልፎ ተቆርቋሪ አካል የሌላቸው የሃገራችን ሴቶች ህይወታቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ለዚህም በየጊዜው ወደ ተለያዩ አፍሪካና አረብ ሃገራት በተለይም በሱዳን በየመን የሚፈልሰው
የኢትዮጵያውያን ሴቶ ች ቁጥር መጨመር ማረጋገጫ ነው። በተለያዩ በሱዳን በየመንና በተለያዩ አረብ
ሃገራት ያሉ ሴቶች እህቶቻችን ተጠሪ እንደሌላቸው በመገመት የየሃገራቱ ዜጎች እና መንግስታት
እንደፈለጉ ሲያሰቃዩዋቸው እያየን ያለነው እውነታ ነው። ተጠሪ እንደሌላቸውም በቅርቡ በወያኔ ኤምባሲ
ፊለፊት ተደፍራ የተጣለችው እህታችን እና ወደዛው አካባቢ እየደረሰ ያለው ስቃይ እና የስርአቱ ምላሽ
ማረጋገጫ ናቸው። ሌላው መቼ ከእኛ ከ ኢትዮጵያውያን አዕምሮ የማይወጣው በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ
በእህቶቻችን የደረሰው ግፍ እና ብሄራዊ ውርደትን ተያይዞ መንግስታችሁ ነኝ ባዩ የሰጠው ምላሽ
የምትፈልገውን ለም መሬት ከኢትዮጵያ በመውሰድ በስርአቱ ተጠቃሚ የሆነችው ጎረቤት አገር ሱዳን
በኢትዮጵያውያን ሴቶች እየተፈጸመ ያለው በደል መቼም ቢሆን ከእኛ ሴቶች ብቻ ሳንሆን ኢትዮጵያዊ
ለሆነ ሁሉ የእግር እሳት እንደሆነ ነው። የእነዚህ ሃገራትህዝብ እና መንግስታት እንደፈለጉ መሆናቸው
የወያኔን ለቡድን እንጂ ለህዝብ ዴንታ ቢስነት መገንዘባቸው ይመስላል። ለነገሩ በውጭ ሃገራት አልን
እንጂ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በ።ሃገራቸው የሚደርስባቸ መከራ እና እንግልት ከቀን ወደቀን እየተባባሰ
ነው።እንደውም የዚህ ስርአት ዋና ተጠቂ ሴቶች መሆናቸውን በመዲናችን አዲስ አበባ በገሃድ የሚታይ
ነው።አዲስ አበባ ዓለም ዓቀፍ ከተማ እንደመሆኗ እንግዶችን ሊስብ የሚችሉ በርካታ ሰራዎችን መስራት
እየተቻለ ለወገን ለሃገር እና ስለነገው የማያስበው ይህ ስርዓት ለዚሁተግባር ደላሎችን በማሰማራት እና
የተለያዩ ነገሮችንበመጠቀም ቆነጃጅት እህቶቻችንን ለተርካሻ ስራ እያሰማራ ይገኛል።ከዚህም ሌላ በዚሁ
ሃገር አጥፊ ስርአት ባመጣው ቅጥያጣ ሙስና መስፋፋት የአስተዳደር ብልሹነት እና ብቃት ማነስ የተነሳ
በተፈጠረው የኑሮ ውድነት ታዳጊ ሴቶች ሳይቀሩ ኑሮን ለማሸነፍ ስጋቸውን ሸጠው ለመኖር መገዳደቸው
በመዲናችን ጎዳና እየታየ ያለ ሃቅ ነው።ይህ ትውልድን ጎጂ ተግባርም በአሁኑ ወቅት ወደ ተለያዩ ሃይ
ስኩል እና ኤለመንተሪ ትምህርት ቤቶች አቅራቢያ እየተስፋፋ ይገኛል። በበርካታ የአዲስ አበባ ት/ቤቶች
አካባቢ የሺሻ የጫት እና የመጠጥ ቤቶች ንግድ ተጧጡፏል።የነዚህ ነገሮች በትምህርትቤቶች አካባቢ
መስፋፋት ደግሞ ታዳጊዎችን ወደ አላስፈላጊ መንገዶች መምራቱ የታወቀ ነው። ይህም ተጽእኖ በሴቶች
እህቶቻችን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ ነው። ለዚህም ጉዳይ ስርአቱ መደሰቱን ለወላጆች ጩከት
ዝም በማለት እና ስለጉዳዩ ሲነሳ ጆሮ ዳባልበስ በማለት አረጋግጦልናል። በቅርቡ በታዳጊዋ ሃና ኦላንጎ
ላይ የደረሰው ግፍ የተሞላበት ድርጊት የዚህ ማረጋገጫ ነው። እንደዚሁም ስርዓቱ ለሴቶች ምንም ትኩረት
እንዳልሰጠ በርእዩተ አለሙ፤ በማህሌት ፋንታሁንና ኤዶም ካሳዬ እንዲሁም በሌሎቹም ስርዓቱን
በመቃወማቸውና በብዕራቸው የስራአቱን እኩይ ሴራ ስላጋለጡ በእስር ቤት የሚደርስባቸው መከራ እና
እንግልት ማረጋገጫ ነው።
የሆነው ሆኖ ሃያሶስት ዓመት ያስቆጠረው የጥፋት ስርዓት አንድም ቀን ለሴቶች መብት ሲቆም አላየንም
አንድም ደረጃ የሴቶችን መብትሲያሻሽል አላየንም ያሻሽላል ብለንም አንጠብቅም።የነሰምሃር እና
መሳዮዎቹዋ እና የስርዓቱ ተጠቃሚዎች ቅምጥል ኑሮ እና እንክብካቤ የአብዛኛው የስርዓቱ ሰለባ እና
የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነውን ሴቶች ኑሮና የመብት ደረጃ ሊወክል አይችልም። እንደውም ማስተዋል
ለቻለ ይህ ስርአት በቆየ ቁጥር አሁን ላይ በሃገራችን ሴቶች ላይ ያለው ጥቃት ምን ደረጃ ሊደርስ
እንደሚችል መገመት ይችላል።
ታዲያ የዚህ ስርአት ለጥፋት መነሳትን የተረዳን እና የጥፋቱ ሰለባ የሆንን ሴት ኢትዮጵያውያን ከያለንበት
ተሰባስበን ስለመፍትሄው ልንወያይበት የሚገባበት፤ እንዲሁም ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት የምንደራጅበት
ጊዜ አሁኑኑ መሆን አለበት። ለዚህም በመጀመሪያ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ስርአት ፍጹም የህዝብ እና
የሃገር ጠላት መሆኑን ማወቅ እና ማረጋገጥ፤ መፍትሄውም ይህን አጥፊ ቡድን ከህዝባችን ጫንቃ ማውረድ
በሚለው ቁርጥ አቋም ላይ መስማማት ይኖርብናል። ጠላትችን ከሆነው አምባገነናዊ ስርአት ጋር
ለምናደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል በድል እንወጣ ዘንድ የሴት የጀግኖቻችንን ትግል ታሪክ መመርመርና
ማወቅ ወሳኝ በመሆኑ ገድላቸውን በማውሳት ልንማማር ይገባልም እላለሁ። እንደነ እቴጌ ጣይቱ እና
ሌሎችንም ተጋድሎ በማስታወስ እኛም የነሱ አብራኮች መሆናችንን ባለመዘንጋት እንደነሱ ታሪክ መስራት
እንደምንችል በማመን ትግላችንን መጀመር ይኖርብናል። ስርአቱን ከማስወገድ ባሻገር በአገራችን
የተከሰቱት ያለፉት ታሪካዊ ስህተቶቻችንን እንዳይደገሙ ቆም ብለን እያሰብን ለወጠነው ዲሞክራሲያዊ
ስርአት እኛ ሴቶች ተደራጅቶ ለመታገል መነሳት አለብን። የኛ የትግል ተሳትፎ በአገራችን እየተቀጣጠለ
ባለው ህዝባዊ ትግል ላይ ሲደረብ የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም። ስለዚህ ስርዓቱ ከሃገራችን ተወግዶ
የህዝብ መብት ይከበር ዘንድ ህዝባዊ እና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትመሰረት ዘንድ እኛ ሴቶች
ተደራጅተን በመነሳት የበኩላችንን የትግል አሻራ እናበረክት ዘንድ ወገናዊ ጥሪየን አቀርባለሁ።
ህዝብ ያሸንፋል!!!

onsdag 10. desember 2014

የህወሃት የጦር አበጋዞች – የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ፂዬን ዘማርያም)

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (Metals and Engineering Corporation (METEC)
በመከላከያ ሚኒስትር ስር የሚገኘው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ/ሜቴክ)፣ሲጀምር አስራሁለት የሚደርሱ የተለያዩ ከደርግ/ወታደራዊው መንግስት በተወረሱ ፋብሪካዎችን ሥራ የጀመረ ድርጅት ነው፡፡ ሜቴክ በ2010 እኤአ በአስር ቢሊዩን (10,000,000,000)ብር መነሻ ካፒታል የተመሠረተ ድርጅት ነው ይሉናል፡፡ በአሁኑ ግዜ በህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ዘመን ከስባ አምስት ፋብሪካዎች በላይ ያሰባሰበ ድርጅት ለመሆን ችሎል፡፡ ሜቴክ ኮርፖሬሽን ከ13,000 ሠራተኞች ሲኖሩት ከነዚህ ውስጥ 1,000 ዎቹ ማሃንዲሶች ናቸው፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ትስስር መሪ ዶክተር ደብረፂዋን ገብረሚካኤል ሜቴክ በሃገር ውስጥና ከባህር ማዶ ሃገራት የቢዝነስ አጋሮቹ ጋር በመሆን ወደሃገር ውስጥ የሚገቡ ምርትና ሸቀጦችን በመተካት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን ሜቴክ ይንቀሳቀሳል ቢሉም ሜቴክ የሰራው ምርትና ያዳነው የውጭ ምንዛሪ ደፍረው አልገለፁም፡፡ ሜቴክ መንግስታዊ ሞኖፖሊ እንደሆነ የግሉን ዘርፍ ስራ እየነጠቀ እንደሆነ ዶክተሩ የሚመሩት ቴሌኮም ከዓለማችን ካሉ ሃገራት የመጨረሻ ተርታ ውስጥ መሆኑን መረዳት የተሳናቸው ኢንተርኔት አጠቃቀም ባለመቻላቸው ነው ተብለው ይታማሉ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ውሳኔዎችን አስተላለፈ

• ‹‹አገዛዙ የወሰደውና ወደፊት የሚወስደው ከእስካሁኑ የባሰ አረመኔነት እርምጃ ይበልጡን ያጠናክረናል››
የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ትናንት ህዳር 30/2007 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ትግሉን ያጠናክራሉ ያላቸውን ውሳኔዎችን አስተላለፈ፡፡ ብሄራዊ ምክር ቤቱ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ‹‹ህወሓት/ኢህአዴግ በፈፀመው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ እና እስር ምክንያት ክፍተት ሳይፈጠር የፓርቲው እንቅስቃሴ እንዲቀጥልና ትግሉም እንዲጠናከር የሚያስችሉ ናቸው›› ሲሉ የብሄራዊ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰይድ ኢብራሊም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ብሄራዊ ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ህወሓት/ኢህአዴግ በአመራሩ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ ላይ የፈጸመው ጭካኔ ለሰላማዊ ታጋዮች ባለው ጥልቅ ጥላቻና ጭካኔ በተሞላበት እርምጃው ከትግሉ ያፈገፍጋሉ ከሚል ስሌት እንደሆነ በመግለጽ ‹‹አገዛዙ የወሰደውና ወደፊትም ሊወስደው የሚችለው ከእስካሁኑ የባሰም አረመኔነት የተሞላበት እርምጃ ይበልጡን ያጠናክረናል እንጅ ከትግላችን ቅንጣት ያህል ወደኋላ እንደማናፈገፍግ›› ብሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በአንድ በኩል ‹‹ምንም ችግር ሳይፈጥሩ በቁጥጥር አዋልናቸው›› ያላቸውን ሰላማዊ ታጋዮች በሌላ በኩል ፍርድ ቤት አቅርቦ ‹‹መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውደመዋል›› ሲል መክሰሱም በገዥው ፓርቲ የሚዘወሩ ተቋማት በጉዳዪ ላይ አንድ አይነት አቋም እንደሌላቸውና ይህም የተጀመረው ሰላማዊ ትግል ስርዓቱን መያዣ መጨበጫ እንዳሳጣው ያሳያል ብሏል፡፡
ከህወሓት/ኢህአዴግ ከዚህ የባሰ ጭካኔን እንጠብቃለን ያለው ምክር ቤቱ ‹‹በምናደርገው ትግል ሁሉ የሚጠበቅብንን መስዋእትነት ለመክፈልና ሀገራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችን እየገለጽን መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀንለትና የምናከብረው ህዝብ ከጎናችን እንዲቆም›› ሲል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ምክር ቤቱ እሁድ ታህሳስ 5/2007 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባ የጠራ ሲሆን የተላለፉት ውሳኔዎች በምን መልኩ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተወያይቶ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
source Negere Ethiopia

tirsdag 25. november 2014

ወጣቱ ፖለቲከኛ ሀብታሙ አያሌው የተናገረው

በግልፅ ከተቀመጠው አላማዬ ውጪ ሌላ የተደበቀ አላማ እስከሌለኝ የትም ቦታ ንፁህ አዕምሮ አለኝ ፡፡ንፁህ አዕምር ይዤ እኖራለሁ የመጨረሻው አማራጭ ወደ እስር ቤት መወርወር ሊሆን ይችላል እድል ፈንታችን ይሔ ሊሆን ይችላል ፡፡ይሔ ለኛ የተለየ አዲስ ነገር አይደለም በሰው ሁሉ ላይ ከደረሰው በእናንተ ላይ የደረሰ ምንም ነገር የለም ይላልና መፅሀፍ እኔም የተለየ ነገር ሊደርስብኝ አይችልም ፡፡ከቀድሞም ጀምሮ ኢትዮጵያ እንደዚህ ልጆቿን ስትበላ የኖረች ሀገር ናት፡፡አባቶቻችንም በተረት ይሉታል‹‹ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ››እንስራ ለዚች ሀገር ባልን እንደዚህ አይነት ፈተናና መከራዎች መጋረጣቸው ያሳዝናል፡፡ቢያንስ ትውልዱ እንደዚህ አይነት ፈተና እንዳይገጥመው፤ልጄ እንዲህ አይነት ፈተና እንዳይገጥማት እኔ ይህንን ፈተና ተጋፍጬ ማለፍ አለብኝ፡፡ግን ሁሌም ዲሞክራሲያዊ መሆን አለብኝ ብዬ አምናለሁ ፡፡ፀረ ዲሞክራሲያዊ የሆነ አስተሳሰብን በፀረ ዲሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት አይቻልም፡፡ፀረ ዲሞክራሲያዊ የሆነን አስተሳሰብ መፍታት የሚቻለው በዲሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡በዲሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ደግሞ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡

mandag 24. november 2014

“ምስጢር ካወጣህ ቤተሰቦችህን እንፈጃቸዋለን” “ብዙ አይነት የድብደባና የስቃይ መአት ደርሶብኛል”




“የደረሰብኝን ስቃይ ለማንም ብናገር ቤተሰቦቼን በሙሉ እንደሚፈጁ አስጠንቅቀውኛል”
ወጣት ተስፋዬ ተካልኝ በዝዋይ እስር ቤት ለወራት ስቃይ የተፈፀመበት

ወጣት ተስፋዬ ተካልኝ መኮንን ይባላል፤ አርሲ አርባ ጉጉ ተወልዶ አዳማ/ናዝሬት አድጎ፣ በ1998 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሲዮሎጂ ተመርቋል፡፡ በ2000 ዓ.ም በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር በሲኒየር ካልቸራል ኤክስፐርትነት የስራ መደብ እስከ ሚያዝያ 2003 ሰርቷል፡፡ ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በግልፅ ባልተረዳው ምክንያት የመንግስት ደህንነት ሀይሎች ተያዞ ለ23 ወር በዝዋይ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ እየተፈፀመበት መቆየቱን ይናገራል፡፡ መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም ከእስራት ሲለቀቅም አንድ ጊዜም እንኳን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ ለፍኖተ ነፃነት አስረድቷል፡፡ ከወጣት ተስፋዬ ተካልኝ መኮንን ጋር ያደረግነውን ቆይታ ተከታተሉን፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ማን ነበር ያሰረህ?

ወጣት ተስፋዬ:- ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በማለዳ ቤቴ ተንኳኳ፤ ተነስቼ ከፈትኩኝ፡፡ የማላውቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ “ና ውጣ፤ ልብስህን ለብሰህ ውጣ” አሉኝ፡፡ እኔ እናቴ ሞታ ሊያረዱኝ የመጡ መስሎኝ “ምነው ቤተሰብ ደህና አደለም? የተፈጠረ ችግር አለ?” አልኳቸው “ዝም ብለህ ናውጣ” አሉኝ፡፡ ልብሴን ለበስኩኝና ወጣሁ፤ አንቀው መኪና ውስጥ ከተው ወደ ማዕከላዊ ወሰዱኝና 3 ወር አሰሩኝ ከዛም አንድ አመት ከ8 ወር ዝዋይ ማረሚያ ቤት፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- መታሰርህን ለቤተሰብ ተናግረሀል?

ወጣት ተስፋዬ:- ለማንም ሰው እንድናገር አልፈቀዱልኝም፤ መስሪያ ቤቴ አልጠየቀኝም፣ ደሃዋ እናቴ ያለችው ናዝሬት ነው እሷም የምታውቀው ነገር አልነበረም፡፡ አባቴ አቶ ተካልኝ አስተማሪ ነበር አርባ ጉጉ ላይ ነው በ1985 ዓ.ም በነበረው ግጭት ነው የተገደለው፡፡ ማንም ሳይጠይቀኝ፣ፍ/ቤት ሳልቀርብ 23 ወር ታሰርኩ ልብስ ምግብም የሚያመጣልኝ ሰው አልነበረም፡፡ እናቴም መታሰሬን እንኳ አታውቅም መስሪያ ቤቴም ስኮላርሽፕ አግኝቷል፤ ወደ ውጪ ሃገር ሊማር ሊሄድ ነው የሚባል ነገር ስለነበረ አልጠየቁኝም፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- የት ነበር ስኮላርሺፕ ያገኘኸው?

ወጣት ተስፋዬ:- የዛሬ 2 ዓመት አካባቢ የራስመስ ሙንደስን ስኮላርሽፕ አግኝቼ ነበር፡፡ ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያና ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ቶክዮ ባሉ ምሁራን ሪኮመንድ ተደርጌ በጣሊያኑ ፌራሪ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ እንደተፈታሁ ሄጄ ስጠይቃቸው ብዙዎቹ ጓደኞቼ በጣም ደነገጡ፡፡ በማላውቀው ነገር 23 ወር ሙሉ ቅማል ተወርሬ … ባካችሁ ተውኝ … ምንም የሌለ ነገር የለም በጣም ተጎድቻለሁ፡፡ ከማረሚያ ቤት እንደወጣሁ እናቴ ጋ ስሄድ በጣም ደነገጠች፣ በሕይወት ያለሁ አልመሰላትም 23 ወር ሙሉ ከቤተሰብ ስለተለየሁ ግራተጋባች፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በእስር ወቅት የደረሰብህ ድብደባና ማሰቃየት ነበር?

ወጣት ተስፋዬ:- ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ በኤሌክትሪክ ጀርባዬ ላይ አቃጥለውኛል፣ በብልቴ ላይና በኩላሊቴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሱብኝ ሽንት ችዬ አልሸናም፣ ሽንቴን መቆጣጠርም አልችልም፡፡ ኩላሊቴንም በጣም ያመኛል፡፡ ውሃ ውስጥ እየነከሩ በጣም ደብድበውኛል፡፡ አሁን ስናገር ያመኛል ብዙ አይነት የድብደባና የስቃይ መአት ደርሶብኛል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- እንደው ስታስበው ለእስር ያበቃህ ወይም ከመንግስት ጋር ያጋጨህ አጋጣሚ ነበር?

ወጣት ተስፋዬ:- መስሪያ ቤቴ ውስጥ የኢህአዴግ አባላት ነበሩ፤ በጣም ይከታተሉኛል፡፡ በቢ.ፒ.አር ላይ ስብሰባ በተደጋጋሚ ይጠራ ነበር፡፡ እኔም ሠራተኛ ላይ ተፅእኖ የሚያደርሱ ነገሮች ሲመጡ እኔ አልቀበልም በግልፅ እናገር ነበር፤ ሠራተኛውም እኔን ይደግፋል፡፡ ከመታሰሬ ጥቂት ጊዜ በፊት ገነት ሆቴል ስብሰባ ነበረን፡፡ በዛ ስብሰባ ላይ በጣም ተከራከርኩ፤ ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አቶ ፀጋዬ ማሞ የሚባሉ አሰልጣኝ፣ ከውጭ ጉዳይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲና ከንግድና ኢንዱስትሪም የመጡ ነበሩ ስማቸውን የማላስታውሳቸው ባለስልጣን ነበሩ፤ እዛ ላይ ሀሳብ አንስቼ ተከራክሬ ነበር፡፡ “የሠራተኛን ሀሳብ ዳይቨርት ያደርጋል” ይሉኝ ነበር፡፡ መቼም ግን ሀሳቤን በመናገሬ ይህን የመሰለ ስቃይ ይደርስብኛል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ “አሸባሪ፣ ግንቦት ሰባት” እያሉ እኔ በማላውቀው ነገር 23 ወር ሙሉ ፍርድ ቤት ሳልቀርብ ያለምንም ፍርድ በርሜል ውስጥ ውሃ ጨምረው እያስተኙ አሰቃዩኝ፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- እንደዚህ ያሰቃዩህ ምን አይነት ምንም አይነት መረጃ ሳያገኙ ነው?

ወጣት ተስፋዬ:- እኔን ጥፋተኛ የሚያስደርግ ምንም መረጃ አላገኙም፣ እኔን አስረው ወደ መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ ይደውሉ እንደነበር ይነግሩኝ ነበር፡፡ የኢሜይል አድሬሴንም ተቀብለው በርብረዋል ግን ምንም አላገኙም፡፡ እኔ ከማንም ጋር ሊንክ የለኝም ኢሜሌ ላይ የስኮላርሺፕ መልዕክት ካልሆነ በስተቀር ምንም የለውም፡፡ በመስሪያ ቤቴ ሪሰርቸር ነበርኩ፣ በሶሲዮሎጂ ነው የተመረኩት፡፡ ሉሲ የተገኘችበት ሣይት ላይ አፋር፣ ጋምቤላ ብዙ ሳይቶች ሰርቻለሁ፡፡ ከአለቆቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት ሰላማዊ ነው እነሱ ናቸው ስኮላርሽፕ ሪኮመንድ ያደረጉኝ፡፡ አንደኛው ፕሮፌሰር 25 ዓመት ሙሉ እዚህ አገር ሰርቷል፣ አርዲን ያገኘው እሱ ነው፡፡ ሄነሪ ጊልበርት ይባላል፤ እሱም ሪኮመንድ አድርጎኛል፡፡ እኔ በጣም የሚቆጨኝ ደሃዋ እናቴ አረቄና ጠላ ሸጣ ነው ያስተማረችኝ ምን ብዬ ልንገራት እንደዚህ አትጠብቀኝም ከበደኝ፣ አሁን እሷ የምትሰጠኝ ምግብ ራሱ ደምደም አለኝ… (ረጅም ለቅሶ)፡፡ ልጄ በደህናው አይደለም የጠፋው ሞቷል ወይም መኪና ገጭቶታል ብላ ነበር የምታስበው፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- የከመታሰርህ በፊት ፖለቲካ ተሳትፎ ነበረህ?

ወጣት ተስፋዬ:- 1997 ዓ.ም የቅንጅት ደጋፊ ነበርኩ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበርኩ በ97 የነበረው ሁኔታ ስንት ሰው አለቀ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነበር ታውቃላችሁ ምንም የምናደርገው ነገር አልነበረም ፡፡ በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን መያዝ እንደማይቻል ተረዳሁኝ፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አልሆንኩም፡፡ ከዚህ በኋላ ከምንም ነገር የተገለልኩ ሆኛለሁ፡፡ አንድ ብርጭቆ ሳትሰብር አሸባሪ ስትባል አስብ እንግዲህ አንድ ብርጭቆ እንኳን ሰብሬ አላውቅም ባለኝ እውቀት እንደውም ለእውቀት ነው የምጓጓው እውቀቴን አሳድጌ አገሬን ለመለወጥ ነው የማስበው እኔን ምንም የሚመለከተኝ ነገር የለም አሸባሪም ግንቦት ሰባትም አይደለሁም፡፡ስትደበደብ፣ ስትሰቃይ ያላደረከውን አድርጌያለሁ ትላለህ፤ በርሜል ውሃ ሞልተው ይከቱሃል ያሰቃዩሃል፡፡ አያሳዝንም ይሄ? እንዴት አድርጎ እዚህ አገር ይኖራል? 23 ወር ሙሉ አስረው ማሰቃየታቸው ሳያንስ የደረሰብኝን ስቃይ ለማንም ብናገር ቤተሰቦቼን በሙሉ እንደሚፈጁ አስጠንቅቀውኛል፡፡ እኔ ግን ከዚህ በላይ ሞት የለም ብዬ ነው የነገርኳችሁ፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- አሁን የት ነው የምትኖረው?

ወጣት ተስፋዬ:- መኖሪያ የለኝም … (ረጅም ለቅሶ)

ወጣት ተስፋዬ ተካልኝን ለመርዳት የምትፈልጉ አንባብያን ከፍኖተ ነፃነት መረጃ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ (ምንጭ ፍኖተ ነጻነት)

በፒያሳው ቦንብ ፍንዳታ ዋና አቀናባሪው ተስፋዬ ገ/አብ መሆኑን ያውቃሉ? (ሊያነቡት የሚገባ) (በአለማየሁ መሰለ )

Image
ለዛሬ የማቀርበው መረጃ ተስፋዬ ገብረአብ እንደ ሸፋን ከሚጠቀምበት የደራሲነት እናየጋዜጠኘነት ስራ ባሻገር ለማመን በሚያዳግት ይሰራ የነበረውን የወንጀል ድርጊት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።ከዚህ በታች አባሪ ተደርጎ የተያያዘው በእጅ የተጻፈ መረጃ፣በእጄ ላይ ካሉ መረጃዎች መሃከልትኩረቴን የሳበው ነው።እንደምትመለከቱት በራሱ በተስፋዬ ገብረአብእጅየተጻፈነው።ከሌሎችመረጃዎች ለየት የሚያደርገው ደግሞ፣እንደሌሎች መረጃዎች በፎቶኮፒ እጄ ላይ የቀረሳይሆን፣ዋናው(ኦርጅናል)መሆኑ ነው። ምክንያቱም በቀጥታ ወንጀል የተጻፈበት ሆኖ ስለታየኝ ነው።ከእጅጽሁፉ ላይ እንደምትመለከቱት፣መኩሪያ መካሻ ከተባለ ግለሰብ ጋር ድብቅ(ህቡእ) ስራ ለመስራትጀምረው ነበር።እንደኔ ግምት የኤርትራ መንግስትን ጥቅም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስፈጽማልብለው ያሰቡትን ተልእኮ ለመፈጸም አሲረው ነበር፡፡እንደ መረጃው ከሆነ መኩሪያ መካሻ የተባለውግለሰብ ከፒያሳው ቦንብ ፍንዳታ በኋላ ፈርቶ ይሁን ሌላ ባይታወቅም፣ከተስፋዬ ጋር ያለውን
ግንኙነት አቋርጧል።የፒያሳው የቦንብ ፋንዳታ ብሎ የተገለጸው ደግሞ ሌላ ሳይሆን በ2002 እኤአበትግራይ ሆቴል ላይ የደረሰው ፍንዳታ ነው።የእጅ ጽሁፉን ሙሉ ይዘትና ለአንባቢ ይመች ዘንድ የተየብኩትን ይመሳከር ዘንድ እንደሚከተለው
አቅርቤዋለሁ።አሰሪ መሆንና በቀጥታ ከእሳቱ ጋር መጋፈጥ ልዩነት አላቸው መኩሪያ መካሻ የተባለው ሰው ጥሩ ጀምሮነበረ።ፒያሳ ላይ ቦምብ ሲፈነዳ ከእኔ ጋራ ያለንን ግንኙነት አቁዋረጠ።በጣም ጉዋደኛየ ነበር ለስራውስል ሰዋሁት። ጉዋደኛንመሰዋቴ ትልቅ ነገር አይደለም።ህይወታቸውን የሰዉ፣ክቡር ዜጎች ያሉበት ሃገርሰው ነኘና። እዚህ ላይ በትክክል ማሰብ እችላለሁ።አስቃቂውን ስሜቴን ግን ለመግለጽ ያህል ነው።ያሸማቅቁሃል ሲሳካልኝ በደስታ መጠጣት፣ሲከሽፍብኝ በንዴት መጠጣት፣ልምድ አደረግኩት።ደረጀደስታ እራሱ ከገፋፋኝ በሁዋላ መልሶ በኢትኦጵያ የማምን ኢትዬጵያዊ ነኝ ሲለኝ ምን እንደሚሰማገምቱት።
ሚኒስትር የነበረው ደስታ ወልደማርያም ጋር ለዘላለሙ ተለያይቻለሁ።እነዚህ ሰዎች ለወያኔ ነግረው ምንያስፈጽሙብኝ ይሆን የሚል ስጋት አለብኝ።ያድዋን ወረዳ ያበላሸው ………… የደረሰበትን ታሪክእያሰብኩ መሰቃየቴን አልተውኩም።ከብብቱፈልቅቄ ካስቀረዋቸው መረጃዎች ከዚህ በታች እንደምታዩት በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ላይየኢትዬኤርትራ ጦርነት በሁዋላ እሱም እንዳለቆቹ እንዳቄመ ነው የምናየው።እስከጦርነቱ መጀመሪያ ድረስግን፣የህወሃት አባልነቱን ግዴታ ለመወጣት በአለቆቹ ታዞ ይሁን በራሱ ተነሳሽነት የአማራንና የኦሮሞንህዝብ ለማጋጨት ነበር ስራዬ ብሎ የተያያዘው።አሁን ደግሞ በኤርትራ የመረጃና ደህንነት መስሪያቤትፕሮጀክት ተቀርጾለት የትግራይ ህዝብንም የትኩረታቸው መነሻና መድረሻ አካተው በተቀረው የኢትዬጵያህዝብ ለማስጠላትና ለማሸማቀቅ፣የተስፋዬ ገብረአብን ብእር እንደዋነኛ መሳሪያ እየተጠሙበት እንደሆነበግልጽ ማየት ይቻላል።ከላይ እንደገለጽኩት መስሪያ ቤቱ በሃገራችን ህዝቦች መሃል ያለውን መተማመን እና አንድነት ለማትፋትፕሮጀክት ተቀርጽለት ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት በዚህ ግለሰብ ኣማካኝነት እየተፈፀመ የከረመው እና
ሊፈፀም እየቴሰረ ያለው ሤራ እንደሚከተለው ይሆናል፥፥አጠቃላይ የግቡ አላማ የኢትዮጵያን አንድነት ማዳከም ነው፥፥ ስልታዊ አካሄዳቸው ድግሞ አንዱንብሄረሰብ ከሌላኛው ጋር እርስ በእርስ እንዳይማመኑ በማድረግ በመሃላችን አንድ ሃገራዊ አጀንዳና እሴትእንዳይኖረን ማድረግ ነው፥፥
ለዚህ ማጠናከሪያ የሚሆነው፣የአማራ፣የኦሮሞ እና የትግራይ ብሄረሰቦችን ለምሳሌ ያህል ብንወስድአንድ የኦሮሞ የዘር ሃረግ ያለው ግለሰብ፣አማራ ከሆነ ግለሰብ ጋር አብረው በጓደኝነት፣በጋብቻሊኖሩ የሚችሉበት የግኑኝነታችው መሰረት አንድና አንድ ብቻ እንዲሆን ነው የሚፈለገው፡፡ ያምየትግሬ ጥላቻ ነው።በተቀረው ሁለቱ ግለሰቦች የጋራ የሆነ ሃገራዊ አጀንዳ እና እሴት ቀርጸውስለዲሞክራሲ፣ፍትህ፣ልማትና የሰብአዊ መብት መከበር እንዲሁም ሌሎች ሃገራዊ አጀንዳዎች
እንዲያግባቧቸው ፈጽሞ አይፈለግም።የወዳጅነታቸው መሰረት አንድ ብቻ እንዲሆን ነውየሚፈለገው፣እርሱም የትግሬ ጥላቻ ብቻ ነው። በሌላኛውም መአዘን የትግራይና ኦሮሞ ብሄርተወላጆች የወዳጅነታቸውና ያብሮነታቸው መሰረት መሆን ያለበት፣የአማራ ጥላቻ ብቻ እንዲሆንነው እቅድ ወጥቶለት ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦለት በተግባር ላይ እንዲውል እየተደረገ ያለው።ይህንን ለምሳሌ አነሳን እንጂ ሁሉም የሃገራችን ብሄሮች በተገኘው አጋጣሚና እድል በዚህ መልክበጎሪጥ እንዲተያዩ በማድረግ እንደሰው ወይንም እንደ ኢትዬጵያዊ ማሰብ አቁመን ሳንፈልግበመረጥነው የብሄር ማንነታችን ላይ አትኩረን ስንኩላን እንድንሆን የተሸረበ ሴራ አካል ነው።እዚህጋ በኤርትራ የደህንነትና መረጃ መስሪያቤት ሙሉ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በመታገዝ
የተስፋዬ ስነ-ጽሁፍ የበኩሉን የማናከስ ሚና በመጫወት ሃገራችንን ወደማያባራ ጦርነትና እልቂትለመክተት የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።ሁለት አመት ለሚቆጠር ጊዜ ቤቴ አስጠግቸው ሲኖር ከሚያደርጋቸው የስልክ ልውውጦች
እንደተረዳሁት ከሆነ በተስፋየ ገብረአብ ስም ይወጡ የነበሩ ጽሁፎች በአብዛኛው ማለት ይቻላልከኤርትራ የመረጃና ደህንነት መስሪያቤት የፕሮፓጋንዳ መልእክቶች እንደነበሩ ህያው ምስክር ነኝ።ይህ ማለት ተስፋየ በጋዜጠኝነት ወይንም በደራሲነት ሽፋን የመረጃ መስሪያቤቱ የፕሮፓጋንዳማስተላለፊያ መሳሪያ በመሆን ለኤርትራን ብሄራዊ ጥቅም የሚውል ስራ ይሰራ የነበረ መሆኑን
አስረጂ ነው።ለምሳሌ ከደህንነት መስሪያቤት የላኩለትን ምንም ለውጥ እንዲደረግበት ሃሳብሲያቀርብ፣እነሱም ሃሳቡን ሳይቀበሉት ሲቀሩ በር ዘግቶ በስልክ ሲጨቃጨቅና ሃሳቡ ሲሸነፍበተደጋጋሚ መስማቴን አስታውሳለሁ።እንደ እኔ እምነት ከሆነ ራሱ የኢትዬጵያ መንግስት እያራመደ ያለው የተንሸዋረረና የከረረ የዘርማንነትን ብቻ ማእከል ያደረግ የፖለቲካ ስርአት፣ከውጪ ሊመጣ ለሚችል እንዲህ አይነትየማጋጫት ወይንም ሃገር የማፍረስ ጣልቃገብነት በር እንደሚከፍት ለመተንበይ አዳጋች አይሆንም።ወደ ነጥቤ ልመለስና ከላይ በጠቀስኩት መሰረት፣አማራን ከተለያዩ የሃገሪቱ ብሄሮች ጋር እንዴትሲያላትምእንደነበረ፣ ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ ጋር በክፍል አንድ ሪፖርታችን ላይ በሰፊውሄደንበታልና አሁን አልመለስበትም። ከዚህ በታች ደግሞ የትግራይ ብሄር አባል በሆኑ ግለሰቦች ላይማህበራዊ ፤ የስነልቦና የአካል ጥቃት መፈጸሙ፤ የሱ መጽሃፍ ስኬት ውጤት እንደሆነ ለኤርትራየመረጃና ደህንነት መስሪያቤት የቅርብ ተጠሪው ለሆኑት አቶ ዓለም እንዲህ በማለት በጽሁፍየፋክስ መልእክት ረቂቅ (ድራፍት ) ያስተላልፍ እንደነበረ መረዳት እንችላለን፡

torsdag 20. november 2014

መምጫውን የማያውቅ መድረሻውን ያጣል

ታሪክ ለሰው ልጅ ስሩና መሠረቱ ነው።ታሪኩንና መምጫውን የማያውቅ ህዝብ መድርሻውን የማያውቅና ራሱንም ለባርነት አሳልፎ የሰጠ ይሆናል፡፡ ለክብሩ ለእርሱነቱ ለህብረቱና ለነፃነቱ ፀንቶ መቆየት እና የጥንካሬውና ተሳስሮ የመዝለቂያው ሰንሰለት ታሪኩ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የአሜሪካ ባርያ ፈንጋዮች ትናንት በገፍ ከአፍሪካ በባርነት ያመጡዋቸው አፍሪካውያን አንድ ቀን በአንድ ቆመውና በህብረታቸው ጠንክረው ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት እንዳይነሱ ሀ ብለው የነጠቋቸው ማንነታቸውን፤ ታሪካቸውንና መገኛቸውን ነበር፡፡ እንደ እቅዳቸውም እነሆ ዛሬ አብዛኛው ጥቁር አሜሪካዊ እኔ ማን ነኝ? መምጫዬስ ከወደየት ነው? በሚሉና በመሳሰሉ ጥያቄዎች ተተብትቦ ለምላሹ ሲውተረተር መገኘቱ፤ እንዲሁም ዛሬም ከተገዢነት መንፈስ ራሱን አላቆ በሁለት እግሩ ለመቆም ሲታትር ይገኛል፡፡
ሌላው የኢጣልያ ወራሪን ሀይል ቅስም የሰበረውና በአለም አቀፍ ደረጃ ቅሌት ያከናነበው የአድዋ ጦርነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ቅሌት በደም አጥቦ ሀያልነቱን ለአለም ለማሳየት በሞከረበት ሁለተኛው ወረራ ወቅት ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ የአድዋ ጦርነት የመሩት የአፄ ሚንሊክ ሀውልትን ከጥልቅ ጉድጓድ መቅበር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ባጠቃላይ አንድ ህዝብ እንደ ህዝብና ሀገር ጠንክሮና በነፃነት ኮርቶ ለመኖር ብሎም ከትውልድ ትውልድ መሸጋገር መቻል ከማረጋገጫው አንዱ የትናንት ማንነቱና የመገኛ ታሪኩ መሆኑን ከላይ በምሳሌነት ያነሳናቸው ነጥቦች ያረጋግጣሉ፡፡
ታሪክ ለአንድ ህዝብ የማንነቱ መገኛ፤ የመገኛው ምንጩና መምጫውን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን የነገ መዳረሻውን የመመልከቻ መነፅርና ጠንክሮ የመንቀሳቀሻው ጉልበቱ ሆኖ የሚያገለግል ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አንድ ህዝብ ታሪኩ ከጠፋ ሊገጥመው የሚችለው ችግርና ፈተና እንዲህ በቀላሉ የሚገመት ያለመሆኑንና እንደ ህዝብ እንደ ሀገር ቀጣይነቱን በቀላሉ መፍትሄ ከማይገኝለት ፈተና ውስጥ ይከተዋል ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያችን ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ህልውናዋ አደጋ ላይ የወደቀበት መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ባለፉት 23 አመታት በዘረኞቹ የወያኔ ጉጅሌዎች እጅ ከወደቀችበት እለት ጀምሮ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆኑ የታሪካችንና የባህልችን ዋና ዋና እሴቶች ዋነኛ ኢላማ ሆነዋል፡፡ ይህንንም በተደጋጋሚና በግልፅ ከወያኔው መሪ እስከ ተራ ደጋፊው የሚወረወረው በትር ያረጋግጣል፡፡ ጉጅሌዎቹ የነፃነት ምልክት የሆነውንና በዕልፍ አዕላፋት ደም መሥዋዕትነት ፀንቶ የቆየውን ሰንደቅ ዓላማ በሶ መጠቅለያ ጨርቅ ከማድረግ ጀምረው ዛሬ በምሁራን ጥረትና በእያንዳንዱ ዜጋ ድጋፍ የተሰባሰቡት የታሪኮቻችን መዛግብት በጥንቃቄ ከተቀመጡበት (ቤተ-መዛግብት) እያወጡ ከማውደምና ለስኳር መጠቅለያነት እስከ መሸጥ ደርሰዋል፡፡
ታሪካዊ ገዳማት ፈርሰዋል፤ ታሪካዊ ቅርሶች ለባእዳን አልፈው ተሽጠዋል፤ የነፃነት ታሪካችን እየተደለዘ በወያኔያዊ ዘረኛ የፈጠራ ታሪክ መተካቱ ቀጥሏል፤ ታሪካዊ ጀግኖቻችንን ማዋረድና ማውገዝ የእለት ተእለት ስራቸው ሁኗል። ወ ያኔዎች ኢትዮጵያዊነት ቅዝት ሆኖባቸዋል፤ ስለዚህም ቀንደኛ ጠላታቸው አድርገው ፈርጀውታል፡፡ ይህ የዘረኝነትና የዘረፋ ስርዓታቸው ውሎ ማደር የሚረጋገጠው ኢትዮጵያዊነት መመታት ሲችል ብቻ ነው ብለውም በፅኑ ያምናሉ፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነታችንን ሊያዳክም ብሎም ሊያጠፋ ይችላል ብለው የገመቱትን ሁሉ ከመፈፀም የማይመለሱት፡፡ ለዚህም ነው በስንት ጥረትና በብዙዎች ድካም ተሰባስቦና ተደራጅቶ የቆየውን የታሪክ መዛግብትና መፅሀፍት ከቤተ-መዘክር አውጥቶ በኪሎ ለመቸብቸብ የበቁት፡፡
ታዲያ ኢትዮጵዊ ነን የምንል ሁሉ ዘሬም እንደትናንቱ ይህን በማንነታችን ላይ የሚደረግ የጥፋት ዘመቻ ለማስቆም መነሳት ግድ ይለናል። እየተፈፀመ ያለው የታሪክ ማጥፋት ዘመቻ ለነፃነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ከምናደርገው ትግል እኩል ጎን ለጎን ለታሪካዊ ቅርሶቻችንና መዛግብቶቻችን ከጥፋት የመከላከልና የማዳን ስራ የመስራት የትውልድ ኃላፊነት አለብን፡፡ አለበለዚያ መምጫውን የማያውቅ መድረሻውን አያውቅምና የምናደርገው የነፃነት ትግል የተሟላ ውጤት ማስገኘቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡ ተገንዝበንም ወያኔን በቃህ ልንለው ይገባል፡፡
በመጨረሻም ጂኦርጅ ኦርዌል ‘The most effective way to destroy people is to deny and obliterate their understanding of their own history” ብሎ ጽፎ ነበር። ህወሃቶች የዚህ ፍልስፍና ተከታዮች መሆንን በመምረጥ ለራሳቸው ውረደትን ፤ለአገራቸውም ውደቀትን ተመኝተዋል። ኢትዮጵያችን መንግስት በጠላትነት ተሰልፎ ከአገራችን ከህዝብና ለአገሪቷ እሴቶች ጋር የሚዋጋበት አገር ሁናለች። ህወሃት በብዙ መልኩ ሲታይ የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት መሆንን የመረጠ ቡድን ነው። የህወሃት በኢትዮጵያ ላይ በጠላትነት መቆሙ ያስቆጣቸው ወጣቶች እምቢ ለአገሬ፤ እምቢ ለክብሬ ብለው ተነስተው ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ተሠማርተዋል።ግዜው ከእነዚህ ወጣቶች ጎን የምንቆምበትም ጭምር ነውና ተነሱና ለነፃነታችንና ለአገራችን ዝና ለህዝባችን ክብር አብረን ታግለን ጠላትን የመረጠውን ህወሃትን እናስወግድ እና ንፁህ አገር እንፍጠር።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

የማንዴላን ጽዋ የተጎነጨው ሃብታሙ አያሌው (በዳዊት ሰለሞን

በ1972 የበጋ ወራት ኔልሰን ማንዴላ ከ27 ዓመት የእስር ፍርዱ 18ቱን ዓመት ወደሚያሳልፍበት ሮቢን ደሴት መጣ፡፡ጠባብ በሆነች ክፍሉ ወለሉ መኝታው፣ መጸዳጃው ደግሞ ቅርጫት ነበረች፡፡ ከባድ ስራ እንዲሰራም ይገደድ ነበር፡፡በዓመት ውስጥ ለ30 ደቂቃ እንዲጎበኘው የሚፈቀድለት ለአንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ በየስድስት ወራቱ አንድ ደብዳቤ እንዲቀበልና እንዲጽፍ ይፈቀድለት ነበር፡፡››

ሐብታሙ አያሌው ደቡብ አፍሪካ ያስተናገደችውን የዓለም ዋንጫ ለመመልከት ወደ አገሪቱ ባቀናበት አጋጣሚ ከልቡ የሚያደንቃቸው ኔልሰን ማንዴላ ለ18 ዓመታት የታሰሩባትን ታሪካዊዋን ክፍል በመጎብኘት የመታሰቢያ ፎቶ ግራፍ ተነስቶ ነበር፡፡

 የጸረ አፓርታይድ ትግል እንዲቀጣጠልና ጥቆሮች በገዛ አገራቸው ባይተዋር የሚሆኑበት የነጮች አገዛዝ እንዲያከትም ኢትዮጵያ ድረስ መጥቶ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደው ማንዴላ በሮቢን አይስላንድ ከዓለም ተነጥሎ እንዲቀር ብዙ መከራ ተቀብሏል፡፡

 ወጣቱ ሐብታሙ በአእምሮው ይህንን እያሰላሰለ የነጻነት መንገድ ውጣ ውረድ እየታየው ገጽታውን ለካሜራ ባለሞያ የሰጠ ይመስለኛል፡፡ሐብታሙ በዚያን ወቅት የበሰለ እንጀራ ሌሎች ጋግረው እርሱ እንዲበላ ብቻ የሚጠበቅ ሰው ነበር፡፡

 ልክ ሙሴ በፈርኦን ቤት አድጎ የፈርኦን ልጅ መባልን በመጠየፍ የተራ ሰው ህይወት መምራት እንደጀመረ ሐብታሙም ሮቢንን የጎበኘው ‹‹ኢህአዴግ የጋገረውን እንጀራ ከመብላት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ የዘመናችን ሮቢን (ማዕከላዊ) መታሰርን እየመረጠ ነበር፡፡

 ሐብታሙ ከደቡብ አፍሪካ መልስ ‹‹አንድነታችን ከልዮነታችን በላይ ነው›› በሚል መሪ ቃል ‹‹አንድነት›› የሚል ቃልና ስም አምርሮ ከሚጠየፈው ኢህአዴግ ጋር ትግል ጀመረ፡፡

 ሮቢንን የጎበኘው ሐብታሙ የማንዴላ መንፈስ ተጠናውቶት የኢትዮጵያ ፖለቲካ መፍትሄ ፍቅር፣መቻቻልና ብሄራዊ እርቅ ማድረግ መሆኑን መስበክ ቀጠለ፡፡

 ይህ ለኢህአዴግ ተንበርካኪነት፣የኒኦ ሊበራሊዝም አቀንቃኝነትና የነፍጠኞች አካሄድ ነው፡፡ ሐብታሙም ጥርስ ውስጥ ገባ፡፡ ‹‹ኢህአዴግ ከታሪክ ይማር›› የሚለው ውትወታው ጆሮ አለማግኘቱ ይታወቅ ዘንድም በአንድ ማለዳ ብሶት የወለዳቸው ነፍጥ አንጋቾች ሐብታሙን መሬት ላይ አስተኝተው እየጎተቱት ማዕከላዊ (ሮቢን) አስገቡት፡፡

 ሐብታሙ በኢትዮጵያው ሮቢን ቅዝቃዜው አጥንት ሰብሮ በሚገባ ክፍል ውስጥ ታስሯል፣ መኝታው ወለሉ ናት፤ ለወራት ቤተሰቦቹን እንዳያገኝ ጠበቃውም እንዳይጎበኙት ተደርጓል፣ ድብደባ ተፈጽሞበታል፣ ህክምና እንዳያገኝ ተደርጓል፣ ያልፈጸመውን ነገር እንደፈጸመ በማድረግ ቃሉን እንዲሰጥ ተገድዷል፣ክፍሉ በጨለማ የተዋጠች ከመሆኗም በላይ ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይገናኝ ተወስኖበታል፡፡
ሐብታሙ ሮቢንን ሲጎበኝ
ሐብታሙ ሮቢንን ሲጎበኝ

የማንዴላ መንገድ በኢትዮጵያ ተመሳሳዩን ጽዋ እንደሚያስጎነጨው ተገንዝቧል፡፡ እናም ጽዋዋን ለመጠጣት የማንዴላ መንፈስ እንዲረዳው ጸሎት አድርጓል፡፡
But Robben Island became the crucible which transformed him. Through his intelligence, charm and dignified defiance, Mandela eventually bent even the most brutal prison officials to his will, assumed leadership over his jailed comrades and became the master of his own prison. He emerged from it the mature leader who would fight and win the great political battles that would create a new democratic South Africa.
በሮቢን ደሴት የብረት ግግር የተቆለፈበት ማንዴላ በዚያ የሚገኙ አረመኔ የእስር ቤት ሃላፊዎችን ልብ በማሸነፍ በሳል መሪ ሆኖ እንደወጣ ሁሉ ሮቢንን የጎበኘውና በኢትዮጵያው ሮቢን (ማዕከላዊ) የሚገኘው ሐብታሙም በዚሁ መንፈስና ጥንካሬ እንደሚወጣ እምነታችን ጽኑ ነው፡፡

tirsdag 18. november 2014

ዩጋንዳና የቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዕጩ ጉዳይ

የዩጋንዳ «ናሽናል ሬዚዝተንስ ሙቭመንት» ፓርቲ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒን እአአ ለ2016 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በዕጩነት ለማቅረብ የያዘው ዕቅድ ብርቱ ክርክር አስነስቷል።
ዮዌሪ ሙሴቬኒ እአአ ከ1986 ዓም ወዲህ በዩጋንዳ የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን እንደያዙ ይገኛሉ። ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት በተደጋጋሚ ባማሻሻል ካለፉት 28 ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱን መምራታቸውን ቀጥለዋል።
በአንድ ወቅት የአንድ አፍሪቃዊ ሀገር ርዕሰ ብሔር ከአስር ዓመት በላይ በሥልጣን መቆየት የለበትም ሲሉ የተናገሩት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ከሥልጣናቸው ለመውረድ ሀሳብ እንደሌላቸው የፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል። በዩጋንዳ የሚታዩት ሁኔታዎች እንደጠቆሙት፣ በምሕፃሩ «ኤን አርኤም» በመባል የሚታወቀው ገዢው የዩጋንዳ «ናሽናል ሬዚዝተንስ ሙቭመንት» ፓርቲ እአአ በ2016 ዓም በሀገሪቱ ለሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ብቸኛው ዕጩ አድርጎ ለማቅረብ እየጣረ ነው። ሙሴቬኒ ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን በዕጩነት እንዲወዳደሩ የተያዘውን ጥረት የተቃወሙ ሶስት የመብት ተሟጋቾች ይህንኑ ተቃውሟቸውን ለምሥራቅ አፍሪቃ የፍትሕ ፍርድ ቤት አቅርበዋል።
rechts<br />
“>
የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደታዘቡት በገዢው ፓርቲ ውስጥ የሥልጣን ፉክክሩ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። ይሁንና፣ እንደ ፖለቲካ ተንታኙ አንጀሎ ኢዛማ ግምት፣ ይኸው ፉክክር ለቀጣዩ ምርጫ ያን ያህል ስጋት የሚፈጥርባቸው አይሆንም።
« ፕሬዚደንቱ ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ እየተከተሉት ያለውን አሰራር ስንመለከት፣ ፉክክሩ ቀላል አለመሆኑን ለመረዳት እንችላለን። በተለያየ ደረጃ፣ ማለትም ከቀድሞ ታጋይ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲን ማጠናከር ከሚፈልገው የወጣቱ ትውልድም ፉክክር ገጥሟቸዋል። በቀጣዩ ምርጫ ግን ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ ከገዛ ራሳቸው የ«ኤን አርኤም» ፓርቲም ሆነ በጠቅላላ ከዩጋንዳ የፖለቲካ መድረክ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆንባቸው የሚችል አንድም ተቀናቃኝ የላቸውም። »
አርያም ተክሌ

fredag 7. november 2014

የሰላም ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ ታሰረ

ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማስተባበርና በማቀራረብ እርቅ ለማስፈን እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት የመግባባት፣ አንድነትና ሰላም (ሰላም) ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ መታሰሩን ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ አቶ ፋንታሁን የታሰረው ‹‹የሰላም ጥሪ›› በሚል ነጭ ሰንደቅ አላማ በማውረብለብና የማህበሩን አላማ የሚገልጹ፣ እንዲሁም ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ለአገሪቱ ችግር የሚላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር የያዘ በራሪ ወረቀት ለህዝብ በመበተን ማህበሩን በማስተዋወቅ ላይ በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በራሪ ወረቀቱ የህሊና እስረኞች መፈታት እንዳለባቸው፣ መንግስት በሀይማኖቶች ላይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዜጎችን ማፈናቀሉ እንዲቆምና መንግስት በተቋማት ላይ ከሚያደርገው ጣልቃ ገብነት እንዲቆጠብ የሚመክሩ ሀሳቦች እንዳሉበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ነጭ ሰንደቅ አላማ ሲያውረበልብ፣ የማህበሩን አላማና በህዝብ ላይ አሉ ያላቸውን ችግሮች ለህዝብ ሲያስተዋወቅ የተያዘው አቶ ፋንታሁን ህዝብን ለማነሳሳትና አመጽ ለመቀስቀስ ሙከራ በማድረግ በሚል እንደተከሰሰም ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

አቶ ፋንታሁን እሁድ ጥቅምት 23 ሽሮ ሜዳ አካባቢ በራሪ ወረቀት ሲበትን ተይዞ ላዛሪስት በሚባለው ፖሊስ ጣቢያ ታስ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

fantahun berhanu

torsdag 6. november 2014

የደህንነት ሃይሎች ዜጎችን እያፈኑ መውሰዱን ቀጥለውበታል

ጥቅምት  (ሃያ ስድስትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን ተጠናክሮ የቀጠለው የገዢው ፓርቲ አፈና መንግስት ራሱ ያስታጠቃቸውን ታጣቂዎች ትጥቅ እስከማስፈታት መድረሱን ምንጮች ገለጹ

በትግራይና በአማራ ክልሎች ባለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው አፈና ቀጥሎ ጥቅምት 26 ቀን 2007 ኣም የሰላም ታጋይ እየጠባለ የሚታወቅ ወጣት ሽሻይ አዘናው በመቀሌ ከተማ በትግራይ ክልል የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ገ/ህይወት ካህሳይ እና በደህንነት ሃይሎች ከሚሰራበት የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት የትግራይ
ክልል ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ታስሮ እና ቤቱ ተበርብሮ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዷል። ሽሻይ አዘናዉ የዓረና ትግራይ መስራችና ማእከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረ በቅርቡ ደግሞ ከዓረና  ወደ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ የተቀላቀለ ወጣት ነው።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ቋራ በደላ ቀበሌ አካባቢ መሳሪያ የታጠቁ አርሶአደሮች መሳሪያቸውን እየተነጠቁ ነው። ትክል ድንጋይ አካባቢም እንዲሁ በርካታ ታጣቂዎች መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ መደረጋቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ቀናት በትግራይ ክልል በምዕራባዊያን ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ ዳንሻ ከተማ የአረና ፓርቲ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዘነበ ሲሳይ ጥቅምት 25፣ 2007 ዓም ከቤታቸው ተወስደው ሲታሰሩ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ቀን በሁመራ አረና የቁጥጥር ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አማረ ተወልደ  ታስረዋል። ከወራት
በፊት የታሰሩትን አብራሃ ደስታንና አያሌው በየነን  ጨምሮ 7 የፓርቲው አመራሮች በእስር ላይ ናቸው። በተመሳሳይ ቀን በአማራ ክልል ምዕ/ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ  የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አበበ እና ሶስት የድርጅቱ አባላት ተይዘው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል።    ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ ከ10
ያላነሱ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል። የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት አንዱአለም አራጌ፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ ናትናኤል መኮንንና ሃብታሙ አያሌው አሁንም በእስር ላይ ናቸው።
የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል እና የሰሜን ጎንደር የዞን ሰብሰቢ አቶ አግባው ሰጠኝም እንዲሁ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል። ሶስት የሰማያዊ ፓርቲ  የአርባምንጭ አመራሮች አሁንም ድረስ በእስር ላይ ናቸው።
በምእራብ ጎጃም  በፍኖተሰላም ከተማ የመኢአድ የወረዳው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ( መኢአድ) ሰብሳቢ የሆነው  ዘሪሁን ብሬ ረቡዕ ጥቅምት 26፣ 2007 ዓም ተይዞ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስዷል።

tirsdag 4. november 2014

← የአሜሪካ መንግስት የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ጠየቀ!!

ለአቶ ዛይድ መነሳት ምክንያት የሆነው ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ላይ ባይተነተንም፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባቀረበው ጥያቄ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔውን እንዳሳለፈ ደብዳቤው አትቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ሪፖርት ያቀርባል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየው የመንገድ ባለሥልጣን ቦርድም ሰብሳቢ ናቸው፡፡
ሰሞኑን አቶ ዛይድና አቶ ወርቅነህን የማያግቧቧቸው ነገሮች እየተካረሩ መምጣታቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ አቶ ወርቅነህ የደረሱበት ድምዳሜ ለረዥም ጊዜ የሠሩትን አቶ ዛይድ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በላይ በጥልቀት በመሄድ ሁለቱን ባለሥልጣናት ያላግባባው፣ በቅርቡ ለቻይና ኩባንያዎች የተሰጡ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንደሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ኩባንያዎቹ ከዚህ ቀደም የወሰዱትን የመንገድ ፕሮጀክት ሳያጠናቅቁ ተጨማሪ ሥራ ሊሰጣቸው አይገባም በሚሉ ሐሳቦች ላይ አቶ ወርቅነህና አቶ ዛይድ መግባባት አለመቻላቸው ተጠቅሷል፡፡
አቶ ዛይድ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ ከአቶ ዛይድ በትምህርታቸው ትራንስፖርት ኢኮኖሚስት ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ መንገድ ልማት ዘርፍ ብዙ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይነገርላቸዋል፡፡ አቶ ዛይድ ባለሥልጣኑን በተለያዩ ደረጃዎች በኃላፊነት ማገልገላቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡
ከባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ትልቁ የበጀት ተጠቃሚ የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የመንገድ፣ የድልድይ ግንባታዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ አቶ ዛይድ ከተነሱ በኋላ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ቦታቸው ላይ ሰው አልተሾመም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ዛይድ አስተያየት እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2007 በጀት ዓመት ግንባታቸውን ለማስጀመር በዕቅድ ከያዛቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሰባቱን ከሳምንታት በፊት ለአገር ውስጥና ለውጭ ኮንትራክተሮች መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አምስቱ ለውጭ ተቋራጮች ሲሰጡ፣ አራቱን የቻይና ኩባንያዎች መውሰዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ምንጭ:- ሪፖርተር

“ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ” የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ፕሮግራሙን ይፋ አደረገ የ24 ሰዓት (የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል

9 parties
ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም 9 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሰረቱት ትብብር “ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚል ለአንድ ወር የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር የህዝባዊ ትግል ፕሮግራሙን ዛሬ ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ይፋ አደረገ፡፡
“ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ የማይታሰብ በመሆኑ የተዘጋውን በር ለመክፈት የ‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ› በሚል የፕሮግራም መርሃ ግብር ለመክፈት ወስኖ የመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ” እንዳዘጋጀ ያሳወቀው ትብብሩ የትግሉ ዓላማ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጾአል፡፡
“ምርጫ ቦርድ ለገዥው ፓርቲ ያለውን ወገናዊነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት ፍንትው አድርጎ አሳይቷል” ያለው መግለጫው በመጀመሪያ ዙር የአንድ ወር ፕሮግራሙ 6 ዋና ዋና ተግባራትን ለመፈጸም ዝርዝር እቅዶችን አውጥቶ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ በህዳር ወር የሚያከናውናቸው ተግባራትም፡-
1. በቤተ እምነት ጸሎት እንዲደረግና ጥሪ ማቅረብና አማኞች እንደየ እምነታቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረግ
2. የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግ
3. የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት (ሰላማዊ ሰልፍ)
4. ለመንግስት ተቋማት ደብዳቤ ማስገባት
5. በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶችን ማድረግና
6. የህዝብን ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሆኑ በመግለጫው አሳውቋል፡፡
ከእቅዶቹ መካከልም በሶስት ተከታታይ እሁዶች በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች 3 የአደባባይ ስብሰባዎች እንደሚኖሩ፣ በመጨረሻው መርሃ ግብርም ህዳር 27ና 28 በፕሮግራሙ ማጠቃለያነት የ24 ሰዓት (የውሎና የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡
በገዥው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ጥምረት ይፈጸማል ያለውን ህገ ወጥ ተግባር በመታገል ለሰላማዊ ትግሉ አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት እስከመጨረሻው በፅናት ለመቆም መዘጋጀቱን የገለጸው ትብብሩ በአገር ቤትና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ በትብብሩ ሂደት ቆይተው እስካሁን ያልፈረሙና ሌሎች ፓርቲዎች እና የዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡ (በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር)