
በአንድ ወቅት ሰዎቹ “በእንግሊዝ ምድር ፀሀይ አትጠልቅም” ያሉት ይቺን ወቅት አይተው ነው መሰለኝ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ይመጣል ከከሰዓቱ 10 ሰዓት ላይ ጨልሞ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እንኳ የማይነጋበት ጨለማ ወቅት፤ ይሄኔ ነው “እምዬ ኢትዮጵያ ግደይኝ” የሚያሰኘው፡፡
በእኛ ሀገር የሰዎች እኩልነት ተቸገርን እንጂ፤ ቀን እና ሌሊቱ ዝንፍ አይልም እኩል ለእኩል ነው፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎ የገና ጀንበር እንደጎረምሳ በግዜ አልገባም ብላ ታመሻለች፡፡ እርሷም ብትሆን ግን ብዙ አይደለም ከወትሮዋ ሰላሳ ደቂቃ እንኳ መቆየቷን እንጃ! ትንሽ አምሽታ “አረ ቤተሰቦቼ ይቆጡኛል” ብላ ክትት ነው የምትለው!
ታድያ የሰሞኗ የእንግሊዞች ጀንበር በግዜ አልሰበሰብ ማለት ለምን አሳሰበህ ያላችሁኝ እንደሆነ ለሙስሊም ወንድሞቼ እና እህቶቼ እላችኋለሁ፡፡
እንግዲህ የረመዳን ፆም እየተፆመ አይደል… ታድያ እኮ በረመዳን አፍጥር የሚባለው (ምግብ የሚቀመሰው) ፀሀይ ስትጠልቅ ነው፡፡ ይቺ ዘልዛላ የእንግሊዝ ፀሀይ ደግሞ ወደ ሃያ ሰዓት ሰማይ ላይ ተሰቅላ ትውላለች… አስቡትማ የፆሙ ርዝመት!
በእንግሊዝ እና መሰል ሀገር ያላችሁ ሙስሊም ወዳጆቼ፤
አቦ አላህ ያበርታችሁ!
በአቤ ቶክቻው
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar