(ዘ-ሐበሻ) የአማራ ክልል መሬቶች ለሱዳን እንዲሰጡ ከገዢው ሕወሓት ጋር በመተባበር ወንጀል፣ እንዲሁም ከጉራፈርዳ ተባረው ወደ አማራ ክልል የመጡ ዜጎች የሚቀበላቸው የክልል መስተዳድር ጠፍቶ ለርሃብና ለሞት በመዳረጋቸው በዚህም ወንጀል እንደሚጠየቁ የሚነገርላቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አያሌው ጎበዜ ስልጣናቸውን አስረከቡ።
አቶ አያሌው ጎበዜ
የአማራ ክልል አስቸኳይ ስብሰባውን ከትናንት ምሽት ጀምሮ በባህር ዳር ያካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት ክልሉን ላለፉት 8 ዓመት ተኩል የመሩትን የአቶ አያሌው ጎበዜን ጥያቄ ወዲያውኑ በመቀበል ከስልጣን ያወረዳቸው ሲሆን በምትካቸውም በሕወሓት ተላላኪነታቸው ከአቶ ደመቀ መኮንን አይተናነሱም የሚባሉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተተክተው ተሾመዋል። አቶ ገዱ የአማራ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንትና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን አቶ አያሌው አልፈጽምም ሲሉ የነበሩ ሥራዎችን ለሕወሓት በማደር ይሰሩ እንደነበር እርሳቸውን የሚያውቁ ወገኖች ለዘ-ሐበሻ ጠቁመዋል። በተለይም አምባገነንና እኔ ያልኩት ይድመጥ የሚል ባህሪይ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ ገዱ የአማራ ክልል ስር ያሉ የኢትዮጵያ መሬቶችን ለሱዳን በመስጠት ከሕወሓት ጋር አብረው እንደሚሰሩ ይጠበቃል።
ሌላው የዘሐበሻ የፌስቡክ ተከታይም እንዲሁ “የአማራን ክልል መሬት ለሌላ አሳልፌ አልሰጥም በማለታቸው ስልጣናቸውን እንደለቀቁ ነው” የማምነው ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተውናል።
አንድ ቀን በኢትዮጵያ ነፃነት ሲመጣ ምንም እንኳ እርሳቸው አልፈረሙም፤ የፈረሙት አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው የሚባል ወሬ ቢኖርም አቶ አያሌው ጎበዜ ለሱዳን በተሰጠው መሬት፣ በአማራ ክልል ለደረሱ ጭፍጨፋዎች፣ በዜጎች መፈናቀል ዙሪያ ላሳዩት ቸልተኝነት ለፍርድ ይቀርባሉ የሚሉ ወገኖች ብዙ ናቸው።
Posted By.Eden Mamo
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/11034
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar